ለመላከ ሞት ሚስጢርን በገፍ መመገብ ዕቀባ ሊደረግበት ይገባል። ሚስጢር ላልተገባው እርኩሰት መግለጥ የመላእከ ሞት መንገድ። በሁዳዴ በስጋ መረቅ ላበደ መንፈስ ቤተመቅደስንቧ አድርጎ መክፈትስምየለሹ የገመና ረግረግ።
ለመላከ ሞት ሚስጢርን በገፍ መመገብ ዕቀባ ሊደረግበት ይገባል።
ሚስጢር ላልተገባው እርኩሰት መግለጥ የመላእከ ሞት መንገድ።
በሁዳዴ በስጋ መረቅ ላበደ መንፈስ ቤተመቅደስንቧ አድርጎ መክፈትስምየለሹ የገመና ረግረግ።
እዛው ላይ ደርቀው ይቀራሉ ብዬ አስቤ ነበር። ድፍረታቸውን ከውስጤ መረመርኩት እና መሃከነ አልኩኝ። መጀመሪያ ሳዬው ግን ደነገጥኩኝ። በሌላ በኩል ድቁና ለአሳትያን ሲሰጥ እና እንዲህ ሲወራኝበት በቤተ መቅደስ ዝምታ ምራኝ ሲባል ምንኛ አላዛሯ ኢትዮጵያ ቀራንዮ ዕለቷ፦ ጎለጎታ ማዕልቷ እንደሆነ አስተዋልኩት።
በቅድሚያ ከ7 ጊዜ በላይ ጎንደር የተገኙት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ የሱማሌን መሪ፤ የኤርትራን መሪ ይዘው ጎንደር ሄደው ነበሩ። ያን ጊዜ አገር አቋርጠው ቱሪስቶች ዬሚዩት ዬዓለም ቅርስ እና ውርስ ሳይሆን ጉዳያቸው ሰው ሰራሽ ግድብ ነበር። ለዛውም በደርግ ጊዜ የተወጠነ ፕሮጀክትን አሳይተው ተመለሱ።
እሳቸውም ከባለቤታቸው ጋር ሆነ በተናጠል በሚያደርጉት የወረራ ጉብኝት አንድም ቀን ትዝ ብሏቸው ስለማያውቅ አበክሬ እወቅሳቸው ነበር። የሚገርመው ዬጎንደር ከንቲባ መልካም ነገር አደረጉ ተብሎ ዜና ካዳመጡ ሳምንት ሳይሞላ ከሃላፊነታቸው ይነሳሉ። ጎንደር #ኩሽናቸው። አንዱ ከንቲባ ለመጀመሪያ ሰው ተገኜ ሲባል ጎንደሬን ለማፍዘዝ ስሜን አሜሪካ ተልከው እዛው እያሉ ነበር ከሥልጣናቸው ተነስተው ከአዲስ አበባ ሰው ተልኮ ካለ ደሞዝ ከንቲባ እንዲሆኑ አንድ ነፍስ ዬተመደቡት። ሃይማኖቱን ተከድኖ ይንተክተክ። ሁለገብ ምንጠራ ሁለገብ ነቀላ በቱሪዝም፤ በባህል ዘርፍ በከተሞች ፖለቲካ።
ልክ አዲስ አበባ ከተማ እንደሚጫወቱት ገበጣ ጎንደር ላይም ይከወናል በአቻ። እሳቸው ስልጣን ከያዙ ጀምሮ እስካሁን ከስድስት ያላነሰ ከንቲባ ተመድቧል። ጎንደር ከተማ ላይ፤ ብቅ እንዲል፦ ቀና እንዲል አይፈቀድም። የሚፈቅዱት ጎብጦ እና አነክሶ ታቱ እንዲል እንጂ። በ2015 ድንቅ ክንውን ያደረጉት ከንቲባ በሚዲያቸው በEMS ካዩ በኋላ እረፍት አጡ። ተቁነጠነጡ። ተክለፈለፋ። እናም በዓሉ ባለፈ በማግሥቱ የሞጋሳ ተጠማቂ የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊያቸውን የጎንደር ተጠሪያቸውን ከንቲባ አደረጉ። አሁንም ይቀዬራሉ።
የሰከነ አመራር፤ ዬአመራር ተከታታይነት እንዳይኖር ማወክ አንዱ ስትራቴያጀው ነው። የንጉሥ ግብረ ሰላም ሲከወን እሳቸው ዓይናቸው ደም ለብሶ፤ ሲቁነጠነጡ ቆይተው አሁን ጎንደር ተገኝተው ቤተ መንግሥቱን መንፈሱን ለማወክ ተገኝተዋል። ያ ዬወደቀ በቅርሚያ የተሰበሰበ ዬሃሳብ አዟሪት ይሸጥ ዘንድ ሳቢያው ቤተ መንግሥቱ ሆነ። ለመሆኑ የቅዱስ ላሊበላ ፕሮጀክት ዬት ደረሰ? ሰላማዊ ሰልፍ ሲታቀድ ያላለቀ የርብ ፕሮጀግት ምረቃ ታለመ፤ ዛሬም እንደ ትቅማጥ የመርገምቱን የመጋቢት 24 ኑ እንርገም ጥሪ በባህርዳርም በጎንደር ለማስተጓጎል ተገኙ። በባእታቸው የድጋፍ ሰልፍ በሚዲያ ሽፋን በአማራ ክልል አፈና በዝርፊያ በድፍረት በብርበራ። ባላባቷ ባለቤታቸው ክብርት ዝናሽ ታያቸውም ሲመላለሱ ቲማቸውን ይዘው በአዲሱ ማንነታቸው ፋሲልን ጠይቀው አያውቁም ነበር። ይህን እንታዘባለን። እንዘግባለን። አሁን ምን እግር ጣላቸው????
የጎርጎራ ፕሮጀክት የሳቸው አይደለም። ይህን ፕሮጀክት ያቀደው የተከበረው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ነበር። ይህን ጊዜ ጦፈው በግብታዊነት ነጥቀው የራሳቸው መጠሪያ አደረጉት። የጎርጎራ ፕሮጀክት የደርግ ስለነበር አገሬው ሠርጉን፤ መዝናኛውን አቅዶ ሄዶ የሚከውንበት ሲሆን የታሪክ አውራ በሆነ ጎንደር ጣና እና ዝልቅ ሚስጢራቱም የታደሙበት ባእት ስለሆነ ያን እምቅ ሃብት ለመቧጠጥ፤ ለመዝረፍ፤ ለመጎርጎር ከባህርዳር ቤዛዊት ጣናን ደክቶ ፋሲልን አቀዱ። ዬገዳ ወረራ ግርሻ።
ዘራፊ ቤተ - መንግሥት ካለ ማን ጌታ አለበ? ቋሚ ዬቤታችን ታዳሚወች እንደምታስታውሱት የንጉሦች ንጉሥ አጤ ቴወድሮስን ያዘከረ የፀጉራቸው ከስደት መልስ በጽኑ ተቃውሜ ነበር። ኢትዮጵያ አገራችን ሁነኛ መሪ እስክታገኝ ድረስ ቅርሶቻችን ባሉበት ይቆዩ እንደ ስኬት አትዩት፦ ዘመኑ ዬገዳ ወረራ፤ ዬገዳ መስፋፋት፤ ዬገዳ አስምሌሽን ዬገዳ ዲስክርምኔሽን ነውና ጥንቃቄ ይደረግ ብዬ አሳስቤ ነበር። የጎርጎራ ፕሮጀክት ከአትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ሲዘረፍም እንዲሁ።
ሚስጢር ሚስጥርን ለመቀበል ለበቃ ብቻ ነው ዬሚገለጠው። ለኢትዮጵያ ሚስጢር ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ልኩ አይደሉም። አቶ ኃይለማርያም ደሴም ሥልጣን ላይ እያሉ ቤተ - መንግሥቱን አያውቁትም ልካቸውን ያውቁ ስለነበር አልተዳፈሩም።
ኦነጋዊው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ግን ትልልፍ የታወቀ ስለሆነ ጥሰው ሚስጢራትን እያነኮሩት ነው። ለቀጣይ ምርጫ አዲሱ ዬድፍረት እንኩቶ ጉዞ ይህ ነው። ለዚህ የሳጥናኤል ዬአድማ ምክረ ሃሳብ አለበት። የጎንደር የባህርዳር በአጠቃላይ የአማራ ውርስና ቅርስ ዬመላ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ክብረ አሻራ ታሪክ ነው። ግን በደም፤ በቅናት፤ በቂም በቀል፤ በበቀል ለታወከ መንፈስ ልኩ ከቶ ሊሆን አይገባም ነበር። ግን ባለቤት አልባ አገር ያሻውን ባሻው ሰዓት እንዲህ ይፈነጭበታል።
በቅዱሱ ዬሁዳዴ ፆም ለገደፈ ሰብዕና ገድለ ትውፊትን ማስነካት ያሳዝናል። ስብራትም ነው። አንድ ቀን ያቃጥሉታል፤ ወይ ያዘርፋታል፤ ወይንም ይበርዙታል። ዴሞግራፊ ይሠሩበታል። "ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቁመው ማውረድ" ይቸግራል። ዬሚስጢራት ባለቤት ፈጣሪው ቢሆንም የተገለጣቸው እንደ ቄጤማ ከመነስነስ ቆጥበው ቢይዙት በትህትና እገልጣለሁኝ። ውሸት ፖሊሲ፤ ንደት ራዕይ ለሆነ ዕብን መንፈስ ውስጥን ገልጦ ማስረከብ እኔ ከመሳሳት በላይ ነው የማዬው። ፈጣሪም ፍርዱን ይስጥ። ዶር አብይ የነኩት ዬተነፈሱበት ሁሉ የጨለማው ስለሆነ ሬሳ ይነባበርበታል። ከሬሳ ትርፍ የለም። መቃብር እንጂ።
#ክው ብዬ ደረቅሁኝ። ቅዱሱ ደጋ እስጢፋኖስ በአረማዊ እጅ ሲወድቅ።
እነኛ ቅዱሳን ተጎንብሰው ለቬርሙዳ ትርያንግል ሲያደገድጉ። ደነገጥኩ ከምል ደረቅኩኝ። መቅሰፍት ይወርዳል ብዬ አስቤ ነበር። ቤተ መቅደስ በጭካኔ፤ በደም ንክር የተዘፈቀን መንፈስ አክብራ ጎንበስ ቀና ስትል ከፈጣሪ ዬተላከ መላእከ ሞት ሆኖ ተሰምቶኛል። ከድፍረቱ #ክንውኑ። ከግራኝም፤ ከሳኦልም፤ ከፈርኦንም፤ ከሄሮድስም፤ ከጋዳፊም ከዬትኛውም ብሄራዊ ሆነ ግሎባል ጨካኝ ጋር አቻ አላገኝለትም ለዚህ ዘመን መሪ ለአሳቻው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ። ይህንን በተለያዬ ጊዜ በተለያዬ አጋጣሚ እና ሁነት ገልጨዋለሁኝ።
ዶር አብይ ሃይማኖት አላቸው ብዬ አላምንም። ዓለም ዓቀፍ ከሆኑ ከኢትዮጵያ ተፈጥሮ ጋር የማይመጣጠኑ የተከደኑ ሚስጢራት ማህበራት ውስጥ ሁሉ ይኖራሉ ብዬ አስባለሁኝ። "ዬገንዘቡ ምንጭ ዬት መጣ ብላችሁ" አትጠይቁኝ ዬሚሉትም ለዚህ ነው። በያንዳንዱ ዬታሪክ #ስንድድ ውስጥ ሞት አለ። ህልፈት አለ። ፍድሰት አለ። መፈግፈግ አለ። ዬረገጡት፤ ዬነኩት ሁሉ ብክል ነው። እርኩሰት ይዋኝበታል። እሳቸውን ለማስረዳት ዝቅ ያሉት ሁሉ ሞት ይታቀድላቸዋል። ነገን አያዩትም። ጠብቁት።
ትዳራቸው ለዚህ ሁሉ ታቅዶ ዬተከወነ ነው። ጎንደርን አፍርሶ መሥራት በህረ ዬጥፋት ፕሮጀክታቸው ነው። ዶር አንባቸው የተገደሉት፤ ዬስሜን ፓርክ ዬተቃጠለው፤ 80 ሺህ ጎንደሬ በባእቱ የተፈናቀለው የግራኝ መሐመድ እጥፍ ድርብ ብቀላ ነው። የግራኝ መሐመድ ታሪክ የተደመደመው ጎንደር ላይ ነው ግራኝ በርም ያለው። የአቶ ጃዋር አነሳስም ከዚህ ነው ምንጩ።
በዚህም በዚያም የሚራወጡ መንፈስ አያለሁኝ። ሁሉ ነገር አባይን በጭልፋ ነው። ጎንደሮችን አታውቁንም። ምን እንዳለን፤ ምን እንደሚገባን፤ ምን እንደሚፈቀድልን፤ ምን ደግሞ እንደማይፈቀድልን በዝልኙ ሳይሆን ተገርተን ተገስፀን አድገንበታል። መታበይ ሳይሆን በልካችን ልካችን አውቀን ስሜታችን ገርተን ዘመንን እናስተዳድር ዘንድ መርሆው ሁል አቀፍ ነው። ጎንደር ያለው ቅዱስ መንፈስም ከሰው አቅም በላይ ከእግዚአብሄር ከአላህ ሥህነ - ሥልጣን በታች ክቡር ሞገስን ያነበበ ግርማን የተጎናፀፈ ነው። የሚስጥር አፈጣጠር ትርጓሜ እና እድምታው ጉልት ገብያ አይደለም። ቅባዓ ይጠይቃል። ጎንደር ማንነቱ የተቀባ ነው። የተመረቀም። በትንቢት የተፈጠረም፤ በምርቃት የሰከነ። ሙያ በልብ በልኩ ተመጥኖ የተቀመረበት ባዕት ነው ጎንደር።
ቅርጥምጣሚ፤ ብጥቅጣቂ ውሮ ሃሳብ ጎንደርን አይመራም። የገዘፈው ኢትዮጵያዊነት እንጅ። ደርባባ፤ ደልዳላ፤ ያልጓጎለ ማንነት ያለው ጎንደር መልካምነትን በአብሮነት፤ አብሮነትን በገሃዱ ዓለም እና መንፈሳዊው ኩነት አጨመቶ የማደራጀት፤ የማቀናጀት፤ መምራት አቅሙ አንቱ ነው። በደርበቡ ወይንም በርግብግቡ አይደለም። በተፈጠረበት ዲካ ላይ ሰክኖ በመሆን መግቦት ህይወቱን አስክኖበት የሚከወን ነው። ጎንደር ላይ ከጥንስሱ እስከ ፍፃሜው ዬታሰበበት እና የተሰናዳ ሁለመና በሁሉዬ ክክሎት ይከወናል። አስደስቶ፤ አሻራ ሆኖ፤ ቋሚ ተቋም ከፍቶ።
መታረም ያለበት ስለ "ጎንደር አፈርኩ"
ይህን የሚሉ አይቻለሁ። ማፈር ካለባቸው ከተፈጥሯችን ላፈነገጠው ለራሳቸው ሰብእና ይሸልሙ። እኔ በጎንደሬነቴ ተንጠራርቼም ታቤዬ አንገቴን ደፍቸም ተጎንብሸ ሄጀ አላውቅም። ወይንም እንደ አንዳንዶች ባገኙት ዝና ጎንደር ሲደርሱ ጓሮ ለጓሮ የሚሉት ከፀረ ጎንደሮች ጋር ማእደኛ እንደሆኑት አይደለሁም። እራሴን ተወርጀው ወይንም ተበድሬው ኑሬ አላውቅም። ወደፊትም። ጎንደርን ነፍሴን የምሳሳለትን ያህል እሳሳለታለሁኝ። እያንዳንዱ እኔ እምገኝበት አውድ ሁሉ ህግ ተላልፌ በዓቴ በእኔ ግድፈት እንዳይነሳ እጥራለሁኝ። አሳዳጊዬ ዬጎንደር ቅዱስ መንፈስ ነውና። እንኳንስ ላፍር እዛ በመፈጠሬ ዬተፈጥሮ ዩንቨርስቲዬ ስለሆነ በርከክ ብዬ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁኝ። ብልህነት ከእርጋታ ጋር በገፍ መግቦኛል። ቅንነትን በደግነት አጉርሶኛል። ኧረ ስንቱ።
ሌላው የቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸውን #ዩዲት #ጉዲት የሚሉ ጭንጋፍ ዕይታወችን አስተውያለሁ። ቆባ እሳቤ ነው። ፖለቲካ ለክብርቷ ፀጋቸው አይደለም። አልኖሩበትም። በፖለቲካ ዘው ብለው "ዳቦ ብሉ ተብላችኋል" ሲሉ በልኩ አክብሬ ሞገትኳቸው። ከዛ ሚዛን ተፈሪ በነበራቸው ቆይታ ፖለቲካ ላይ ትውር አላሉም። ለዚህ የከበረ ምስጋናዬ ይድረሳቸው። እሳቸው የመሩት ደርማሽ ባታሊዮን ሳይኖር ዩዲት ጉዲት ያልተገባ ትልልፍ ነው። ይገባኛል ብዙው ከጎንደር ጥላቻ የተቀዳ ነው። ቀዳማይ እመቤትነት ከሆነ ለእኛ ብርቃችን አይደለም። እቴጌነት አብሮን የተፈጠረ ነው። እቴጌ ተዋቡ፤ እቴጌ ምንትዋብ፤ እቴጌ ጣይቱ፤ ወሮ አዜብ መስፍን ሄሮዳዳይ፤ አልፈውበታል።
ወደ ወሮ ዝናሽ ስመጣ ቀስ ያሉ፤ ሰብእናቸው ቁጥብ እና ዝግ ያለ ነው። ለቦታውም ብቁ ናቸው። ቤተሰባቸውም ዬታወቁ ባላባት መሳፍንቱ ወገን ናቸው። ሌላው በትዳራቸው ስኬት ከሆነ ሌላ ቀመር ነው። የትዳር ህግም አለ። ጉዲት እና ዩዲት ሊባሉ አይገባም። ጭካኔን ለምን አላስቆሙም ከሆነ የፖለቲካ አቋም እና ችሎታ ሙያን ይጠይቃል። ሚስት ናቸው እንጂ እንደ እቴጌ ጣይቱ አማካሪ፤ መሪ አይደሉም። የንግሥናው የዘር ሐርግ ቢኖራቸውም። የትዳራቸው ስኬት የተወለዱበት ዕለት እና የደም ዓይነትም የራሱ ተጽእኖ አለው። ዘለግ አድርጎ ማዬት ይገባል። ሌላው ግን ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን በሳቸው ዬህሊና ልክ ማወቅ ፀጋቸው ነው ብዬ አላምንም። እዬረሸኑ እኮ ነው ኖቬል ዬተሸለሙት። አይደል? ከዚህ ሁሉ ምድራዊ ገሃነም መሃልም ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጋር ቁጭ ብለው ኳስ ሲመለከቱ አስተውዣ።ያለሁኝ። ዓለም ዬማያውቃቸው ፈታኝ ሰው ናቸው።
ዬሆነ ሆኖ "ስለ ጎንደር አፈርኩ" ድፍረቱ ጨረቃን ከሰማይ አውርዶ ይፈጠፍጣል። ጎንደር የሚስጢር ማህለቅ በጥልቀት እና በተደሞ የተሟላበት ማንነት ያለው ባእት ነው። ይህን ብላችሁ የምትጽፋ ለራሳችሁ እፈሩ። ዝልቦ ሰብእና እንደ ፌንጣ በዘለለና ቋጥኝ በቆጠረ ቁጥር ካለ ልካችሁ ጎንደርን ለመዝለፍ እና ለማንኳሰስ ባትውተረተሩ መልካም ነው። ትረገማላችሁ እና።
ጎንደርን ህወቶችም አልቻሉትም። ፋክክሩ ሁሌ ከጎንደር ጋር ነው። በዘመነ አጤውም ሆነ በደረግ በባሰው ክፋ ዘመን በሄሮድስ መለስ ዘመንም ፈተናን ድል አድርጋ መንበሯን ሳታስደፍር በልኳ እንደ ልኳ ተመጥና በተፈጠረችበት ጣዝማ ንጥር ኖራለች ጎንደርዬ ትቀጥላለችም። መንገድ የሚዘጋው እኮ የአገር ውስጥ ቱሪስቱን ማቀብ እንዲቻልም ነው። ነገ የአውሮፕላን በረራውንም ሊያግቱት ይችላሉ። እስከተኛን ድረስ።
ቀድሞ ነገር የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መናህሪያ ልትሆን የሚገባት እቴጌ ጎንደር ነበረች። የአፍሪካ ሊቃናት ሁሉ አዳራሽ የመጀመሪያው ቅዱስ ፓላስቸው ይሆን ዘንድ ፕሮጀክቱን ተረክበው ቢሰሩበትእንመክራለን። እኛም ታሪክ አለን፤ እኛም ትውፊት አለን እኛም ትሩፋት አለን ብለው እራሳቸውን ያደምጡ ዘንድ ፓን አፍሪካኒስቶችን እንመክራለን። ወጣት ፓን አፍሪካኒስት ኢትዮጵውያን ይናፍቁኛል። ይህን በጥበብ፦ በልቅና በልህቀት የሚጠቡበት። ከእለት አቲካራ ፦ የብሽሽቅ #የትምክህት አንባጓሮ ወጥተው። ኳታርን ይዩ። እንደምን በአጭር ዘመን ሙሉ አቅላችን ገዝታ በተፈጥሮዋ ልክ አስደምማ አስደግድጋ እንደመራች።
ቢሆን …… ቲም እንቶፎንቶ ……
ነገረ ጎንደርን አትዳፈሩ፤ አትፎካከሩ፤ እላፊም አትሂዱ። ብዙ እጅግ ብዙ መጠነ ሰፊ የመንፈስ ወዘና፦ ለዛማ ጥሪኝ በቅኔ ያለባት ባዕት ናት። ትምክህት ባይገባም የተሰጠኝ ያገኜሁት ያለኝ ጥቅም ላይ ያልዋለ የታገት አቅሜን እኔ አውቀዋለሁ። ምንጩ ባእቴ ፃድቋ ጎንደርዬ የእኔ ልእልት፦ ቅድስቴ፦ ብሩኬ የበሞቴ ልዕልቴ የአይዟችሁ አጽናኝ እመቤቴ የአብሮነት ንግሥቴ ናት።
ዓለምን የፍቅራዊነት ተፈጥሮ ካሪክለም ይንደፍ፤ የፍቅራዊነት ፈላስፋ፤ ኤክስፐርት፤ ዩንቨርስቲ፤ ሙዚዬም፤ መጋዚን፤ ቴሌቪዥን፤ ራድዮ የመንገድ ላይ ትርኢት ኮሌጅ ይክፈት ብላ የሞገተችው የጎንደሯ መንፈስ ናት። መረጃው አለ። ጅማሮውም ዩቱብ ቻናል አለው። ከ8 ዓመት በላይ ማንም ሳይኖር የፍቅር ተፈጥሮ ህግጋት ተተግቷል። በኢትዮጵያ እንባም ተመድን፤ የጀርመን መንግሥትን መንፈስ ማርካ ሙሉ አቅም የመገበች የጎንደር ባተሌ መንፈስ ናት።
ጎንደር ለኢትዮጵያ #ቫወል ናት። ዛር ያለበት ይሰጥስጠው እንዲህም፤ እንዲያም። በቅናት የሚባዝነውም ይናጠው።
ለማንኛውም በዝግታ በማስተዋል እንሁን። የሰሞናቱ የገዳ ወረራ እና ጉርጎራ ላይ አንቴናችን ሳናዝል እንከታተለው።
"የቤትህ ቅናት በላኝ።"
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
04/04/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ