ዴሞክራሲን ስትታገልለት እና ስትታገለው አስተውለው። ቃሉ ብቻውን ግብ አይሸልምም እና።
ይድረስ ለአጤ ቅንነት ቡናችን ፋት እያልን እኛ እኛኑ ይፈታትሸው።
ዬውስጥ ቤተመቅደሶቼ እንዴት አላችሁልኝ??
ዬርህርህናችሁ መጠን ቁሞ አስተማረኝ። ውስጣችሁን አሳዬኝ። ቤተ ሰለሞን የጨመተ ለእንባ፤ ለእውነት፤ ለፍቅር፤ ለሞራል፤ ለእሴት የሚሞግት በጨዋነት ዬአብርኃሙ ቤት ነው። የጥበብ ሰወች፤ ሞጋቾች፤ የሲዊዝ ፖለቲከኞ በቀለም የማይገናኙን የሁሉም እምነት፤፦ዬሁሉም ፖለቲካ አቋም አራማጆች ጠንካራ ሚዲያወች ሁሉም ከሊቅ እስከ ደቂቅ በቤታችን ይገኛሉ። እርግጥ ነው ሰብሰብ ብለን በተን ዬሚያደርጉን ተለዋዋጭ የፖለቲካ ቁመናወች እና የኃይል አሰላለፎች ቢኖሩም ዙረን የምንገናኝበት እሸቱ፤ ጎልማሳው አዛውንቱ፤ ሩህሩሁ ኢትዮጵያዊነት ነው። ሰብላቢያችን እሱ ነው።
መሪያችን ቅንነት። ከሰሞኑ የአንዲት እናት ፎቶ ሼር አድርጌ ሼር የተደረገው ወደ ሁለት ሺህ ሊጠጋ ነው። በእኔ ልፋት ሪከርድ ሰባሪ ነው። በፁሁፌ ውስጥ ቃለ ህይወትን እጠቀማለሁ ፕሮፋይሌ የፃድቁ አባቴ ብፁዑ ሐዋርያ የቅዱስ መርቀርዮስ ነው። የሁሉም ዕምነት ተከታዮች፤ የማያምኑትም ሳይቀሩ ደስ ብሏቸው የህሊናዬ ምርት ታዳሚወች ናቸው ከዚህ በላይ ዘመንን ቁሞ ያሰተማረ አብሮነት ዬለም። አብረን እንደ ተፈጠር አብረን መሆናችን አሻራው ይህ ነው።
ክፍት ሲለኝ በዝምታ የቤታችን ወገኖቼ ጋር አክብሬ መራራ ስንብት ሳደርግ እንኳን ሥም ቀይረው መጥተው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። ቤታችን የፈቀዱ፤ ዬወደዱ አዲሶች ውዶቻችን ደግሞ ስለሚሞላባቸው ዬቤታችን አባላት ፈቅደው እስኪለቁ መጠበቅ ግድ ስለሚሆንባቸው በጓዳ መጥተው ይጠይቁኛል። ታግሰው ቤተኛ ይሆናል። ጥሪዬ ዬትውልድ ነው። ትውልድ መገንባት ያለበት ፈርሶ በሚሠራ ተለዋዋጭ የግለሰቦች ሰብእና ሳይሆን ፈጣሪ፤ አላህ በፈጠረው ተፈጥሯዊነት፤ ፈጣሪ በፈጠረው ሰዋዊነት መርቆ በተሰጠን ዕውነት፤ ቅንነት እና ርህርህና ሊሆን ይገባል።
ዕውነት አንፃራዊ ነው። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ዬእኔ እውነት የሆነው የሌላው እውነት ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ሙሉ አምስት ዓመት ጭካኔን ዬደገፋ ቲም መሳይ እኛ እውነት ባልነው ውስጥ አልነበሩም። የዛን ጊዜው ዬእነሱ እውነት ለእኛ እውነት አልነበረም። ዛሬም አይደለም። ለአርቲስት አስቱዬ በዳኔ ግን ዬቀደመው የቲም መሳይ እውነት ዛሬም ነው። በአሁኑ ንግግሯ እነ ቲም መሳይን ሸንቁጣቸዋለች። ለእሷ የዶር አብይ መንገድ ዕፁብ ድንቅ ነው። እውነት ነው ብላ ታምናለች። መብቷ ነው። በእኛ አቅም ግን ወጣ ገባ እያለች እኛነታችን ልታራግፍ አይፈቀድላትም። ይህ ሥርዓት ለዝንታለም እንዲኖር ትፈልገዋለች። እኛ ተመንጥረን ንጡህ እልፍኝ ላይ ለመዋኜት ምኞት ያላቸው ገልጠው ተገልጠው ሊታዩ ይገባል።
ሂደቱም ለእኛ ባእድ ነው። ስለዚህ እሷን ወደ እኛ እውነት ለማምጣት የእኛ ኃላፊነት አይደለም። የእውነት ተጋድሎ፤ ዬዘመን መለከት እንጂ። በሌላ በኩል ከእኛ ጋር የነበሩም ወደ አስቱ እውነቴ እውነት ነው ብለው የተጠቃለሉም አሉ። ስለዚህም ቤታችን ለቀው ሊወጡ ይችላሉ። በዚህ ውስጥ ከአራት ኪሎው ቤተኝነትም አክ ብለው እኛ እውነት ወደ አልነውም ዬሚመጡ ይኖራሉ። እውነት አንድ ነው። የክት የዘወትር የለውም። ግን እውነት አንፃራው መሆኑ ግን እርግጥ ነው።
በትውልድ ውስጥ የሚሠሩ ጋዜጠኞች ይሁኑ የፖለቲካ ሰወች ሰው ሰው መሆኑን ቢቀበሉ። ፖለቲካ ሰው መሆኑን ቢያምኑ መልካም ይመስለኛል። ትናንት አማራ መደራጀት የለም ብሎ ሞግቶ አቅሙን ሲይ ግን ስትራቴጅስት ለአማራ የህልውና እና የማንነት ተጋድሎ ነበርኩ የሚል ሰብእና በተጣራ መስመር ትውልድ እንዲጓዝ ስንሞግት ዬተሰወረበት አብሮ መጪ ሲል ከገዢው በላይ ሲያሳድደን፤ ሲያለነቁጠው ትግሉን ኖረ።
ዛሬ ደግሞ አማራ መደራጀቱ ለፌስቲባል እንጂ ለፖለቲካ ስልጣን ሊሆን አይገባም፦ ብሎ ሠራዊቱን ሞክ ሲያደርገው ራድ ሆኗል። መጥኖ መደገፍ። አጥንቶ መራመድ አለመቻሉ ትውልዱን አባከነው። የቅኔው ጎጃም ዬተስፋ ፋናወች 12993 ዬ12ኛ ክፍል ተማሪወች ዕድል መሰበር፤ ዬንገረው አዲስ ሰማዕትነት፤ ዬ14 ሺህ ከዛም የሚዘል የፋኖ እስር፦ የስልጠና መቆም የዚህ ሁሉ ባልተገባ ጉዞ ያልተገብ ዕውቅና አሰጣጥ ጦስ ነው። ቀድሜ ተናግሬ ዛሬ የምጨምተው ለዚህ ነው። ላም እረኛ ምን አለን እንደ ድልህ ስለደቆሱት።
ዬታዘብኩት ቅንጣት መታመን ያልቻለው ዕውነት ዛሬ ላይ ሁሉን ገልጦ ሁሉም የወለሌ ገበታ ላይ ነው። ከመሠረቱ ዬአንተን ዕውነት የሚጠዬፍ ዬሌባ ግርግር ካልሆነ በስተቀር አካልህ ሊሆን አይችልም። #መናጆነት ለግል ህይወት ይሁን። ያን የገዘፈ ዬአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ፤ ዬኢትዮጵያንዚም ልዩ ቃና ተበርዞ፤ ተከልሶ ጥገኛ ፓራሳይት ፍለጋ መኳተን ትርፋ #የሃሳብ #ሬሳ መሰብሰብ ነው። ያዬሁት ይህን ነው። የሚገርመኝ የፖለቲካ ሳይንስ የተማረው የአካውንታንቱ በብልጠት መርቶት ሁለመናውን እንኩቶ ሲያደርገው መማር እና አለመማር የማን ደም ፈሰሰ ሲባባሉ #እውነት #ፋክት #ትውልድ አላስፈላጊ ሰማእትነት ይቀበላሉ። የሚያንገበግበኝ ይህ ነው።
እኔ ለእኔ ውድ ልጆች ለወጣቶቼ እምመክራቸው በጥሞና እንዲራመዱ። የእኔ ልጆች የማህበረሰቡ ልጆች ናቸው። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ እንደሚፈጠር አምነው "#እኔም የትውልዱ ነኝና መኖሬ ለትውልዴ ያስፈልጋል፤ ዬራሴን አሻራ እኔው አበጀዋለሁ፤ ለራሴ አሻራ የማይነጥፈውን እውነት ይዤ ማግሥትን አለሁልህ እላለሁ ማለት ይኖርባቸዋል። ማገዶነቴ ሳይሆን አትራፊነቴ በመኖሬ ውስጥ የማበረክተው ቁም ነገር ጨምቼ ስራመድ ነው ብለው ጥሞና ወስደው ከራሳቸው ጋር መክረው አቋም ይይዙ" ዘንድ በትህትና አሳስባለሁኝ።
ለዚህ #የቬርሙዳ ትርያንግል የአብይዝም የመቃብር ሥፍራ ዘመን ዘመን፤ ለቀደመው የሲኦል የህወሃት ዘመን ዘሃ ግራው የነበሩ፤ ያሉም ጥሪያቸው ነው። ለጥሪያቸው መትጋት መብታቸው ነው። ዜግነት የማንም ፈቃዳዊ ስጦታ አይደለም። ውግዘትም አያስፈልግም። ግን ማጭበርበሩም መጭበርበሩም የተገባ አይደለም። የእኛ አይተኬ ተጽዕኖ ፈጣሪወች በለቅ ያስመቱት ተስፋችን በዚህ ውሽልሽል ዝልቦ ላንቁሶ ጉዞ ነው። ዬአማራ ትውልድ ተማገደ። ብዙ ተስፋ በስል ተገበቶ እንዲያር ሆነ።
ይልቅ እነሱ እነሱ ሳይሆኑ የእኔ ናችሁ ብሎ በገፍ ክብር አቅም ዬለገሰው ለራሱ መራገፍ አብሮ በባንድ ያዜመው ተጠቂ ተግ ብሎ እራሱን በፀፀት ሊቀጣ፦ ንሰሃ ሊገባ ይገባል። አሁንም በዚህ ድብልቅልቅም ሌላም የሚያገረሽ ይኖራል። የሚያሰክነው ስክነት ብቻ ነው። ብስጭት --- ጥላቻ --- ቂም --- በቀል --- ትውልድ አይገነባም።
በዚህ ውስጥ የዶር አብይ መንፈስ በበቀል የታነፀ ታቅቦ በጉድጓድ ውስጥ እራሱን ቀብሮ የኖረ እፋኝት ስለሆነ ጦሮውን ፊት ለፊት በተናጠል እዬተማገዱ ሳይሆን በስክነት፤ በስልት፤ በጥበብ በትህትናን ወጀቡን ዝቅ ብሎ ለማሳለፍ ነገ ለምትስቀው ጠሐይ ቤተኛ ለመሆን ወጣትነትን ተላልፎ እንደ ሙሉ እድሜ ማሰብ መራመድ ይገባል። በጥዋቱ ነው እኔ መማገድ የጀመርኩት።
ወጀብ ሲበዛ ግን ዝቅ ብዬ አሳልፋለሁኝ። ጥፍት እላለሁኝ። አሁን ከዚህ በድምጽም በአካልም ማንም አያገኜኝም። መታመን ስለተሰደደ። እራሴን በዬዘመኑ እማተርፈው እኔ ብቻ ነኝ። አልፈላም። ወይንም አልበርድም። በተስተካከለ ሙቀት ገድሜ እኖራለሁኝ። ኢትዮጵያም አልቀረባትም። ከእንባዋ ለደቂቃ ዞር ብዬ አላውቅም። ስለኖርኩኝ። ኑሩ እያልኩ ነው። መኖርን እሰቡት እያልኩ ነው። ሞት እኮ ተመልሶ የሚመጣበት የሽርሽር ጉዞ አይደለም።
ሌላው ቁልፋ ነገር አለመተላለፍ ይገባል። ፍላጎትን ማወቅ ይገባል። ሁሉም ያሻውን መስመር የመከተል መብት አለው ብሎ መቀበል ይገባል። ዲሞክራሲ ስትታገልለት እና ስትታገለው አስተውለው። ቃሉ ብቻውን ግብ አይሸልምም እና። እራሱን ችሎ መቆም የማይችል ፍዝ አላማ እና ግብ ጥገኛ ነው። ጥገኝነቱ ያልተጠና ስለሚሆን ብዙ አመክንዮ አብሮ ይደቃል።
ዬሰኔ 15/2011/፤ የደንቢደሎ የአዲስ አበባ ተማሪወች የእገታ ብቀላ፤ የተካሄዱ የአማራ ህዝብ ተጋድሎ ለስኬት አለመብቃት፤ የልዩ ኃይል ብቁ አመራር ሂደት መጨናገፍ፤ የአማራ ልጆች አፈሳ እና ወከባ፤ የአዲስ አበባ ሽኝት፤ የቶሌ ጭፍጨፋ፤ የጠነከሩ መፈናቀሎች ስጋት እና ገደላቸው፤ ከወለጋ ተፈናቅለው ዶሮ ኩስ ጋር እንዲኖሩ የተበዬነባቸው ወገኖች፤ የአዲስ አበባ የሚኒሊካውያን ጥድፊያ እና ከበባ፤ የአማራ ህዝብ ቀይ የደም ሴል ፋኖ ጥርስ ውስጥ የገባበት ሁነት በልዝ፤ በፍዝ የፖለቲካ ሂደት መስመር #ዲፕሎማት #አንባሳደር አመራር እና መሪ ከማጣት የመነጨ ነው።
የተዋህዶን መከራም የጫነው ካለ ልኩ የተንቦራቀቀው ሂደት ነው። የኖረች ተቋም የዜጎቿ መብት እና ግዴታ የሚመራ ብሂል እያለ ከእሷ እኔ እበልጣለሁ ዬማለት ዝንፈት። የወይብላው መከራ የቁጫን መወጣጫ የሆነው፤ ለመስቀሉ እሮጣለሁ የታገተው ብልሃት በሌለው ጣልቃ ገብነት ስለተደወረ። በአሁኑ የተዋህዶ ንቅናቄም ብዙ ፈተናወች ብቅ ጥልቅ ቢሉም አበው ታግሰው በሄዱበት ጉዞ ሺወች ነፍስ ተርፏል። በተለይ አዲስ አበባ።
ይህ ባልተገባው ሁሉ ጣልቃ እዬተገባ ሲተራመስ ሁለመናውን አከበደው። ነገስ? "እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል ሰው ግን አያስተውለውም። " #አናርኪዝምን ለትውልድ መጋበዝ እዳ ከሜዳ ነው። አንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ እኔ ነኝ ማኒፌስቶ፤ እኔ ነኝ ደንብ ካለ፤ የሥራ ወሰን ከጣሰ። አናርኪዝም ነው። ሰው ሰው እንጂ ሃሳብም አንቀጽም ማኒፌስቶም ሊሆን አይችልም። ፓርቲወች ማኒፌስቶ አላቸው። አያውቁትም። በአንድም የፖለቲካ ድርጅት #ፋኖ የሚል ተጽፎ አይገኝም። ለመዋጥ ዬነበረው ፋክክር ግን አስገበረ። ተስፋንም አዛለ። ዜሮ ላይ ቁጭ አደረገ። ቃ!
ቤታችን ሰክኖ ሲያስተምር ቆይቷል። አቅም አላስባከነም። ምክንያት --- ከመነሻው ፖለቲካዊ አቋም ስለተነሳ። ያ ደግሞ #ከዘመኑ #የፖለቲካ #ባህሬ። የዘመኑ የፖለቲካ ባህሪ አሉታዊ ዴሞግራፊ ፋሽዝም ነው። ይህ ደግሞ በገዳ ወረራ፤ በገዳ መስፋፋት፤ በገዳ አስምሌሽን፤ በገዳ ዲስክርምኔሽን፤ በገዳ ተሃድሶ ስለመሆኑ፦ አዲስ አበባ በኦሮምያ ህገ መንግሥት ከመስከረም 5/2011 ጀምሮ እንደምትመራ በተገባው ልክ ነጥብ በነጠብ በአደረጃጀት መርህ፤ በፍልስፍናው አመክንዮ ልክ፤ በተመክሮ ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከከተማ እስከ ስደት በተገኙ የልምድ ክህሎቶች በፀጋዬ በራዲዮ፤ በከበቡሽ ሚዲያ በሥርጉተ ሥላሴ ሚዲያ ዩቱብ፤ በፌስ ቡክ እና በከበቡሽ ብሎግ በፁሁፍ በአማርኛ እና በጀርመንኛ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ለዚህ ነው ዛሬ እማልባክነው። ድርጅታዊ ሥራ መቀመጥን አብዝቶ ይጠይቃል። እንደ ፌንጣ መዛለልን ሳይሆን።
ሌላው ቀርቶ ትናንት የወልቀይት ጠገዴን ጉዳይ #ምእራባውያን፤ #አውሮፓ ጭብጡን ተቀብሎ ህውሃት #በቃውን ያፀደቀበት አመክንዮ አድሮ ጥጃ እንዲሆን ያስደረጉት አላዋቂ ሳሚ ፖለቲከኞች ዬይፋውን አራት ኪሎ እንታገላለን፤ ህወሃት እንዳያገግም እናደርጋለን ብለው ስውሩን የህወሃት እና የኦነግን #ግርብብ #እርግብግብ በቅጡ ያልተከደነ፤ በቅጡ ዬማይናገር ባይብሬሽን ሰብእናን ደራጎን መሪ፤ አማካሪ ስትራቴጅስቲ ነዳፊ አድርገው፤ የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎን መንፈስ ጽንሰቱን #ጎንደርን ሲያስቀጠቅጡ፤ ሲያስደበድቡ ባጅተው እንደ ገና አወን እንደ ገና ወደ 2008 ሐምሌ 5 ቀን መለሱን። እግዚአብሄር ይይላቸው። አሜን።
በዚህ ሂደት ቅኑ ዘኔ አስረሱም ሰለባ ሆነዋል። ማስሬም አርቆ ትልሙ ዝሏል። ራዕዩ ተጨናግፏል፤ የአማራ ህዝብ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ በርዶታል። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተጋድሎ ዬተደረገባቸው መሰረት የያዙ አመክንዮወች ፈተና ገጥሟቸዋል። ቅኑ የአማራ ህዝብ ብቻውን ቁሟል።
አሁን እንኳን አቅምን በአቅም ለማገዝ ሲጠዬቅ ትኩረትም፤ ቁጭትም የማይታይበት ቸለልተኝነት ለናሙና ብዬ ከምሰጣቸው ቀንጣ የቤት ሥራወች ስንፍናቸውን አስተውላለሁኝ። ሌላ በምሰራበት ጊዜ ብዙ ድካሜን ያባዙታል። ሥንቱን ይኮን? ቪዲዮ ማሰባሰብ፤ ሊንኮችን ማሰባሰብ፤ የፎቶ ጋለሪ መስራት፤ መተርጎም፤ በእጅጉ የገዘፋ የቤት ሥራወች አሉብን። ግን ለተደራጀ እና ለተቀናጀ ቀልጣፋ እሺታ ቅድሚያ አይሰጥም። ጎልቶ ግርማ ሞገስ ያገኜው የእዬዬ፤ ዬስሞታ ፓለቲካ ብቻ። ይህ ደግሞ ቋት አይገፋም።
ይህም ሆኖ ድካሜ ደግሞ ለአሽኮኮወች፤ ለእሽኮኮችም እንዲሁም ለእፋኝት እንዳይሆን ሰፊ ስጋት አለብኝ። ዝም እንዳልል አጤ እንባ ያሳዝነኛል አንጀቴን ያላውሰዋል።
"ዬቤትህ ቅናት በላኝ።"
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ኑሩልኝ። አሜን።
ፎቶ ላይ የምታዩት አበባነት ዛሬ የለም። ከድኜ የምሠራቸው እራሴን እማባክንበት ስኬቱን የሚያስተዳድር አጥቶ ባክኖ ተኖ ሲቀር ቁስለቱ ብዙ ነገሬን አዛብቶታል። በዚህ ውስጥ ለግለግ ብለው የሚወጡ የአማራ ልጆች ምን ይሆኑብኝ ይሆን ብዬ ልቤ እንደ ቅል ተንጠልጥላ ውላ ታድራለች።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
03/04/2023
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ