አጤ አስቻለው ፈጠነ (Ardi) ተከድኖ የቆዬውን ትንፋሽዋ ጎንደር ቃና የሙዚቃ ቅኝት ገለጠ። ለእኔ ሙዚቃ ብቻ አይደለም ፍልስፍናም ጭምር።
አጤ አስቻለው ፈጠነ (Ardi) ተከድኖ የቆዬውን ትንፋሽዋ ጎንደር ቃና የሙዚቃ ቅኝት ገለጠ።
ለእኔ ሙዚቃ ብቻ አይደለም ፍልስፍናም ጭምር።
ዬእኔ ድንግል ትጠብቅልኝ። አሜን።
እናትዋ ጎንደር | Aschalew Fetene (Ardi) | New Ethiopian Music 2023 (Official Video) | SewMehon Films
#በር።
በሙዚቃ ጥበብ ዘርፍ ቅባአው የለኝም። ለፀጋዬ ራዲዮ ራሱ የተፈጥሮ ሙዚቃወችን ነበር እምጠቀመው። ጓደኞቼ ኢትዮጵያ ሲሄዱ ይዘውልኝ ይመጣሉ። ዬመሳሪያ ቅኝቱ ይሻለኛል። በሥሜ ሙዚቃ ሲወጣም ሥራዬ ብለው ጓደኞቼ አዳምጠው ዘንድ ይጋብዙኛል። የቅኔው ዕንቡጥ ዶር ቴወድሮስ ካሳሁን ሰብልዬን ሲያመሳጥር አልሰማሁም ነበር። ጓደኞቼ ጋብዘው አስደመጡኝ። ደካማ ነኝ። አቅጄ ሙዚቃ ከፍቼ አዳምጬ አላውቅም። ያለ ፀጋው አይሆንም። እኔ የወንዝ ዬወራጅ የፏፏቴ የዝናብ የእንሰሳት የእጽዋት ሹክሹክታ እና ዝማሬ ይመስጠኛል። ገንዘብ አውጥቼም እገዛለሁኝ። የዝናብ እራሱ እወዳለሁ። የሳተ ጎመራ ላርባ ጎርፍን ማዬትም ያስደስተኛል። ብቻ ፈንገጥ ያሉ ፍላጎቶች አሉኝ።
ባባቴም በአበይ፤ በእናቴም በእብዬ ወገን ቤተ ክህነታዊ ቢሆኑም አበይ የመፀሐፍ ንባብ ላይ፤ በፍልስፍና ኩነት፤ በዝምታ ተፈጥሮ ዬሰከነ ነበር። እናቴ ደግሞ በፍልቅልቅ ሳቂታ በሞድ እና በሙዚቃ ጥበብ የተመሰጠች ነበረች። ከሁለቱም ለተፈጥሮዬ የተፈቀደልኝን ወስጃለሁኝ።
#ፏ።
በኢትዮጵያ ዬቤተክርስትያን ዬዝማሬ ቅኝት አራራት፤ ግእዝ እና ዕዝል ፀጋወቻችን በቅዱስ ያሬድ ተፈጠሩ። መንዙማም በእስልምና። ለነፍስ፤ ለመንፈሥ ትፍስህት። ለስጋ ለጋህዱ ዓለም መኖር ደግሞ አንች ሆዬ፤ ትዝታ፤ ባቲ፤ አንባሰል ተፈጠሩ። ዬውጩ ዓለም እንደ ኢትዮጵያ ገህዱ እና ዓለም እና መንፈሳዊው ዓለም በተጠና ደንበር ስለመቀመራቸው ለዘርፋ ታላላቅ ባለሙያወች ልተወወ።
ኢትዮጵያ ዬሚስጢር ቅኝቷ ሰው ሰራሽ ብቻ ነው ብዬ አላምንም። አንዱን ዘለላ አመክንዮ ብናነሳ የእድሜልክ ዩንበርስቲ ነው። ያለልኩ ዬተሰፋው ጥብቆ ኦነግ መራሽ አስተሳሰብ ባልኖረበት ዬተኖረበትን ዬአቅም ፍንቀላ እና ዘረፋ፤ እንዲሁም ብረዛ ሳስብ የእርግማን መሆኑን እረዳለሁኝ። ታሪክ በቀደመ ህዝብ ይሰራል። የመኖር ጥበብም በቀደመ ህዝብ ይቀመራል። ትናትን ዬፈጠረ ትናታዊ አቅም ዛሬን ስለሰጠ ሊመሰገን ሲገባ ትናት ዛሬን ሰጥት ተዛሬ ላይ ተሁኖ ትናንትን ለማጥፋት የአቶ ቀጀላ ዬኢትዮጵያ ዬባህል ሚር መሆን ትልቁ ዬምርምር ኦብጀክት ሊሆን ይገባል። አቅም ቢኖር በሆነ። አቅም በብላሽ ተንጠልጥሎ ነው እያፈረሰ ዬሚገኜው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ፏ ያለ ገፆዋ ምንጩ ሃዲዱ የእኔ የምትለው ቀለም፤ ለዛ እና ወዘና ያላት አገር መሆኗ ነው። ከማርክሲስትም፤ ከሊበራል ዲሞክራሲም፤ ከፌድራሊዝም ሆነ ከኮንፈደሬሽን ሥልጣኔ ቀድማ ሠልጥና ዬተፈጠረች አገር ናት። ምንም ዬትውስት ርዕዮት አያስፈልጋትም ነበር። ለዚህም ነው ከተፈጥሯዋ ውጪ ዬተፈጠሩት ዬፖለቲካ ድርጅቶች ዬትውልድ ሳይሆኑ መክነው ዬሚቀሩት። እኔ በደረስኩበት መደምደሚያ ኢትዮጵያ ዬፖለቲካ ድርጅት አያስፈልጋትም። ኢትዮጵያም ውራጅ ርዕዮታዓለም አያስፈልጋትም።
ፏ ፍንትው ያለ ርዕዮት አላት። ኢትዮጵንያዝም። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ሃሳብ ዬላችሁም እያሉ ነጋ ጠባ ዬፖለቲካ ሊሂቃንን ይወርፋሉ። ሃሳብ አለን። ያልተበረዘ፤ ያልተተመነ። ኢትዮጵያኒዝም።
#ቅኝት ታከለ ፀድቆ።
በመጀመሪያ ሳዬው እንዲሁ አለፍኩት። ያመጣልኝ ቴሌቪዥኔ ነበር። ከዛ በከፈትኩት ቁጥር ቤት ለእንግዳ እያለ ፊታውራሪ ቴሌቪዥኔ ሲታክት ይሁንልህ ብዬ ከፈትኩት። ሳዳምጠው ያ ያ ያ ያ የገበሬ መንደር መስክ፤ ጋራ ሸንተረሩ፤ የወፎች ዝማሬ፤ የህዝቡ ዬማይጠገብ ተፈጥሮ እንዴት አለሽልኝ እሙሃዬ ሆዴ ሲል በናፍቆት ለስላላ ቅባዕው ዳሰሰኝ፤ ውስጤ ገብቶ አቀፈኝ። አንገት ለአንገት ተናንቀን ተሞጫመጭን፤ ሆድ ለሆድ ተገናኝተን ዕንባ ተራጨን።
ይወርዳል
ይነጉዳል
እዬፈላ ጉንጬን አልፎ ደረቴን አካለለ። ፈቀድኩለት። ዝም አልኩት ፀጥ ብዬ እንደ ማህሌት በተደሞ ውስጥ አብረን ከተመን። እዝልዋ ጎንደር እናትዋ ጎንደር ናፍቆትዋ ጎንደር አካልዋ ጎንደር ትንፋሽዋ ጎንደር ኧረ ረ ጎንደር ቀልቤን ገዝቶ ተመስጦዬን አናረው። ብቻዬን ቁጭ ብዬ አሰብኩት። ጎንደር ከተማ ተውልጄ አድጌ ገጠር ስሰራ የወረድኩት እና ዬወጣሁበት አቅበትና ቁልቁለት፤ ዳጡና ወንዝ ሙላቱ፤ የሠርግ ውሎ፤ ፋከራ እና ቀረርቶው፤ የእብድ ሃሙስ ትዝታ ዬድሪ ድኮቱ፤ ዬአልቦው የአንባሩ፤ ዬአንኮላው የሌማቱ የጥሩው፤ ዬኮረፌው፤ ዬፍርንዱሱ፤ ዬዝግኑ የስቅስቆው፦ የተልባ ንፍሩው፤ የእርጎው የአይቡ፤ የቁርጡ የዶሮ ወጡ፤ ዬቸረቸራው የጋኑ፤ ዬቶፋው የጎታው፤ ዬሰፌዱ የጥራሩ ሁሉም ለሁሉም አደግድጎ መስተንግዶው፤ የጀንዴው የላመነቱ የአጎዛው የምንጣፋ ሁሉም ጓዛቸውን ጠቅልለው ተነሺ ብረሪ ሂጂ መጪ በይ አለኝ።
በጠባቧ ክፍሌ ዕንባዬ እዬወረደ እንዳሻው እዬዘነበ ተንጎረደድኩኝ። ሳይበረዝ ሳይከለስ የመግቢያው ቃናገዛኝ ከምል በሃሳብ ናፍቆት ሠረገላ እንደ አሻው አሰገረኝ። ይህ ቅኝት አምስተኛ ሆኖ ይመዘገብ ዘንድ ለባለሙያወች አሳስባለሁኝ። እኔ አውቀዋለሁ የገበሬውን ህይወት ሁሉም ዕድል ይቅርብኝ ብዬ አጣጥሜዋለሁና። ብዙ እድሎች ተሰጥተውኝ ነበር። በህይወቴ እንደ ገበሬ ዬምወደው ማህበረሰብ ዬለም።
ባይገርማችሁ …… አወን ይግረማችሁ
አጤ አስቻለው ፈጠነ ገበሬ የዛው ቀበሌ መንደር ነዋሪ መስሎኝ ነበር። ትወናዕውን ሲሆን ይህን ያህል መሆንን ያነግሣል። ሁለመናው ዕፁብ ድንቅ ነበር። ስጽፈው እያለቀስኩ ነበር ይላል ደራሲው አጤ አስቻለው ፈጠን። ልዕልት ጎንደር እንዲህ ትጣራለች። ጥሪኝ አላት። የቻግኒው ዘውዴን በምን አቅሜ ስለ እሱ ልጣፍ ብዬ ሙግት ላይ ሳለሁ ቅድስት ተዋህዶ ፈተና ገጠማት። እና ሃሳቤ ተበተነ። ዛሬ እንሆ ያን ጊዜ ባሰብኩት ልክም ባይሆን የፀነስኩትን ዕውነት ልገላገል።
ይህን የመሰለ ዬፀደቀ ፀጋ ነው እያወኩት የሚገኙት። ቁም ተቀመጥ እያሉ እዬበጠበጡት የሚገኙት።እጅግ በጥልቅ ሃዘን አራት ዓመት ሙሉ አሳልፈናል። ግን ዬአጤ አስቻወውን ዕውነት ጥሶ ወጥቶ ሙሉ ተጽእኖ አሳደረብኝ። በብዙም ተጽናናሁኝ። አይዞሽም ብሎኛል። እና እናት ሆዱ ዬእኔ ድንግል ትጠብቅልኝ። አሜን።
ጧፍን ተመስጬበት ነበር። በራሱ አቅም ድንቅ ነበር። እናትዋ ጎንደር ደግሞ ውስጤን ሃራም ያልኩበትን ጉዳዮች ሁሉ ከልቶ በሥልጣኔ አቅሙ አዋደደኝ ከምል አዋህደኝ። አናባቢም ተነባቢም ተፈጥሯዊም ሰዋውም ዬሆነ መኖርን በገጠር ያነበበ፤ ያመሳጠረ ዬተረጎመ ዕፁብ ድንቅ የጥበብ ሥራ አዲስም ጎዳና ነው።
የእኔ ጌታ ተሰልፌ ፊርማህን ባገኝ፤ ልሳንህን ባደምጥ ምንኛ በታደልኩ ነበር። ብዙ በጣም ብዙ ረቂቅ የጽናት እና የመጽናናት ፀጋወችህን በገፍ ችረህኛል። የበሞቴ ልዕልቴን ካጣሁ ወዲህ ዓለም ለምኔ፤ ናፍቆት ለምኔ ነበርኩኝ። ይህን ይግባኝ የማይጠይቅበት ውሳኔዬን ቢና ጢናውን አውጥተህ በጥምቀት የነበሩ ሙሉዑ ሥርዓቶችን፤ የቁንጅና ውድድሩን፤ የንጉሥ የራት ማዕዱን ሁሉንም በአትኩሮት እከታተል ዘንድ በአጤነትህ መርተህኛል። ተባረክልኝ። ኑርልኝ።
በዬዘመኑ እንዲህ ልዕልት ጎንደር በመከፋት አውሎ ስትናጥ ከች ትሉናጎባጣን አቃንታችሁ፤ ስንክሳሩን ገርታችሁ፤ አባጣ ጎባጣውን ለግታችሁ ባእታችሁን አጉልታችሁ እጬጌነትን ትሾሟታላችሁ፤ ቅባዓችሁን ትሸልሟታላችሁ። በዛ ጭንቅ ዘመን ዶር ቴወድሮስን አስነሳ፤ በዚህ ቅጡ በማይታወቅ ግራጫማ ዘመንም አንተን ፈጣሪ ሰጠን። ተመስገን። ኑርልን የእኔ ጌታ፤ የመንፈሴ ልዑል።
" ……… እናና ዬባልቴት ውበት ደሞ ወይዘሪት
አይነጥፍ ጅረት ሞት ለነፃነት
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ሲከልላት
ምሰሶዋን ሥም ጎንደር አላት
(እኔና መቼን) እንደ አለች አለች ታተይ ሙሽሪት
እንደታዘበች
አዬ አዬ አዬ
ኧረ ዳማዬ ዳማዬ{ ×4 }
እስኪ እህ ልበል
ጥቂት ባንቺ ቦታ
አንጀትሽ ላይ ሆኜ
እልብሽ ባንድ አፍታ
እንዴት ነው አዘዞ
ጮማ በልቶ ጠጅ አንቺ የሚደርሰው
መግደርደርሺ እንጂ
አባቴ ማረጉ ወጉን ወጉን በአዳበላ
አሳድጋኝ አለች እሽሩሩ ብላ
ከምድር መዳኛው ታጠነ አርባራቱ
ለስታዋ ቅርቡ
ስለት ለታቦቱ
እናትዋ ጎንደር
ትንፋሽዋ ጎንደር
እህልዋ ጎንደር
አካልዋ ጎንደር
ኧረ በፈጣረህ
ኧረ እንዲያው በሞቴ
እስኪ ተው እናትህ አትጽናናኝ እቴ
ይልቅስ ውሰደኝ ከአለበት እትብቴ
መጽናኛዬ እሷ ናት ልሂድ ወደ እናቴ
እናትዋ ጎንደር
እሽሩሩ ጎንደር
ኧረ ረ ጎንደር
ትንፋሽዋ ጎንደር
???
ውኃም ካልፈቀደ
ወሰን ከለላት
በካሳ ጀግንነት
በፋሲል በላት
እጎንደሮች መዳፍ
ስንቆርስ እዛም እዛው
ተመልሼ መጣሁ እጄም ሳላደርግ
ክፋ አስለምደሽኝ ጮማ እና ወርረች
እናና ተጎዳሁ እኔ ስርቅ ካንቺ
እናትዋ ጎንደር
ትንፋሽዋ ጎንደር
ስስትዋ ጎንደር
እህልዋ ጎንደር
አካልዋ ጎንደር
ተይ ደሜ ተይ ደሜ
ተይ ደማም፤ ተይ ደማም
የበሽታን ነገር ሀኪም ይሰጡታል
የአጋንንትን ነገር ፀበል ይገቡታል
የጎንደርን ናፍቆት እንዴት ያረጉታል
እነቴጌ ሙሽራ
ኧረ እንደምን ናችሁ?
እነዋዋ ሙርሻ ኧረ እንደምን ናችሁ?
ጉብጉብ አርገሽው አፈር ልብላችሁ
ዬመሳፍንቱ እናት እነ እቴ ማንአብሮት
ጉድጉድ በይልኝ ድንገት መጣሁብሽ
ተይ ደሜ ተይ ደሜ
ተይ ደማም ተይ ደማም
እንደ ህማማቱ
አንቺም ፆመኛ ነሽ
…………
አርግፎ እዬሄደ በሰማይ አሞራ
ደንበር ጠባቂ ነው ለጠላት አይሞትም
መሳሪያው ደምመላሽ እንደ ታናሽ ወንድም
ተይ ደሜ ተይ ደሜ
ተይ ደማም ተይ ደማም
ኧረ ጀግኔ ጀግኔ፤ ኧአ ጀግኔ
ኧረ ጎንደር
እንስፍስፏ ጎንደር
አካልዋ ጎንደር
ተይ ደማም ተይ ደማም
#ከማህል ስንኞች የዘለልኳቸው አሉ። ባህል፤ ታሪክ፤ ትውፊት፤ ትሩፋት፤ ፀጋ፤ መኖርማንነት በምልሰት በዛሬ በነገ የተቀነባበረ ተውኔት ነው። ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ዬሥልጣኔ ደረጃም መሠረቱን ያልሳተ ዬኖረ ግን ሃብትነቱ ዕውቅና ሳያገኝ ሊስትም ውስጥ ሳይገባ ዬተዘለለ ተከድኖ የኖረ ሲሳይ ፍንትው ፏ ብሎ የተገለጠበት በኽረ ማስተር ፒስ ሊሆን የሚችል ባለ ጉልበታም ማእረግ ነው። ግጥሞቹ አወራረዳቸው ጎንደር ላለደገ የቀበልኛ ምቱ እና የሥንኛቱ ሆሄያት ሊከብዱ ይችላሉ።
ከወር በላይ ሆነ ካላዬኋቸው ዬቤታችን ሰው አጋይሥት ዓለሙ ሥላሴ ስል ዕ ቀርቷል ብለው ሲሞግቱኝ ነበር። እኔ እምጽፈውም እምናገረውም በጎንደር ከተማ ዘዬ ነው። ደብረታቦር ወይንም ወልቃይት ወይንም ደባርቅ ደግሞ አማርኛው አማርኛ ነው ዘዬው ይለያል። ደባርቆች እሌ፤ ሽ ያዘወትራሉ፤ ደብረታቦር ደግም እንዴ ይላሉ እንደ አዲስ አበባ፤ በጭልጋ ዝምታ ጫታ ይባላል፤ እንዴት ሰነበታችሁም ጫ ብላችሁ ሰነበታችሁን ይባላል።
አንዳንድ ፊደላት ተረግጠው፤ አንዳንድ ፊደላት ላልተው ግን ሲነበቡ ወይንም ሲነገሩ ሳይጮሁ ወይንም ላይ ሳይወጡ ይሆናል። ቃል አጋኖ እና ስላቅ ሲኖርም የድምጽ ምት ቅኝቱ ሆነ ፍሰቱ እስከ ጅረቱ ይለያል። እኔ አጤ አስቻለው እዛው የተወለደው ወደ ማህል አገር ሲሄድ አዘመንኩም ብለው ይሁን በሌላ "አላቅልህም" ሲሉ አዳምጣለሁኝ። ጎንደር አላውቅልህም ነው የሚባለው። ዬሚገርመው ይህ ዬማንነት ቀውስንም ያመጣል። እራስን ሆኖ መኖር የተሳነው መንፈስ መቼውንም አይድንም። ማን ይሁን ማን። ታላቅ እህቴ ሙሉ ዘመኗን አዲስ አበባ ኑራለች። በተፈጠረችበት በዓት ቃና እና ዘዬ ዬፀደቀች ናት። በራስ ውስጥ መሆን መታደል ነው።
ቃናውም ይለያል። "አላውቅልህም።።!" በተፈጥሮው ቁጡ ቃል ነው። ብስጩ ቃል ነው። ለስልሶ ትህትናዊ ግን አይአዊ ሆኖ ይቀርባል ጎንደር ላይ። ብዙ አይን አፋር ቃሎችን ከ20 ዓመት በላይ ለፕሬስ አብቅቼዋለሁኝ። በዓለም ዓቀፍ ራዲዮ መስናዶ ብቻ ሳይሆን ለህትምትም በቅተዋል።
፨ክወና፨
በእያንዳንዱ የጎንደር የአገላለጽ ዘይቤ የቃና፤ የቃላት ክብካቤ እና የውስጥ ርህርህና ቁልምጫን አክሎ ይከወናል። ይህን ነው ወደ አዲስ አበባ መኖር ያሰቡ የሚዘሏቸው። አጤ አስቻለው ግን ለአደባባይ አብቅቶ አስከበራቸው። ዘውድ ደፋላቸው እንደ አባት አደሩ። እራሱ እሱ ትውፊትም ነው። ወዘኛ፥ ለዘኛ፥ ጌጥማ ሙሽራ ልሳኖችን እጅግ አስውቦ አቅርቧቸዋል።እጅግ ባለውለታ ቅን፤ ንፁህ ልብ እና ዬህሊናዊነት ሰብዕና እንዳለው አስተውያለሁኝ። ከእነተፈጥሮው ተፈጥሮን ተጠበበት ማለት እችላለሁ። ሰሃ ዬማይወጣለት አንቱ ልቅና ነው። ነባሩ የቃላት፤ የዜማ፤ የቅኝት አወራረድ ወደ ላይም ሲወጣ ወደ ታችም ሲመጣ መሃልም ሲያሰኜው ዕፁብ ድንቅ በሆነ ክህሎት የትውልዱን ድርሻ ተወጥቶበታል። ድምጽ አብሮት ተጠንስሶ አብሮት ተወልዶ አብሮት የአደገ ሆኖ እኛዊነትን፤ አኃታዊነትን በገጠር በከተማ የነበረውን ወሰን ደረማምሶ እንደ ኤዶም ገነት በአንድ ወጥ አቅም መርቶታል። ታላቅ ሰው!!!!
ኑርልን አባቱ አጤው ንጉሥ አስቻለው ፈጠነ።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
አክባሪህ ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
04/04/2023
ጥበብ ይገራል፤ ይፈውሳል የትውልድም ይሆናል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ