ኢትዮጵያ ሥመ - ጥር፤ ጀግና ጨዋ የሠራዊት መሪ ነበራት።

 

ኢትዮጵያ ሥመ - ጥር፤ ጀግና ጨዋ የሠራዊት መሪ ነበራት። 
 
"አቤቱ ንጹህ ልብን ፍጠርልኝ።" አሜን። 
 May be an image of 1 person
በዘመኔ ያየኋቸው ቆፍጣና፤ ንቁ፤ ትጉህ፤ ዲስፕሊንድ የኢትዮጵያ የሠራዊት መሪወች፤ የሠራዊቱ አባሎች አቋቋማቸው፤ አረማመዳቸው፤ የአነጋገር ዘይቤያቸው #ቁጥብነት፤ ሥርዓታቸው፤ የአለባበሳቸው ጥራት ፈጽሞ አይረሳኝም። 
 
በእኔ የልጅነት - ዘመን፤ በእኔ የወጣትነት - ዘመን፤ በእኔ የሥራ - ዘመን፤ በእኔ የኃላፊነት እና የተጠያቂነት - ዘመን ያዬኋቸው #ቆፍጣና#ጥንቁቅ፤ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ብቻ #መለዮቸው ያደረጉ ድንቆች አይረሱኝም። ኢትዮጵያ ብቃት ያለው ሠራዊት ነበራት። ያው የኢትዮጵያ የችግር ምንጭ የፖለቲካ ኢሊቱ የአመራር ጥበብ ማነስ ይሁን ሌላ ብቻ በጣም ብዙ መስዋዕትነትን የከፈሉ ዕንቁ የጦር መኮንኖች፤ የሠራዊቱ አባላቱም ህወሃት ሥልጣን ሲይዝ በተናቸው። ያ በተመክሮ፤ በዕውቀት፤ በብቃት የሠለጠነ ተቋም በአመዛኙ በህወሃት አማተር ሠራዊት ተተካ። በጫካ ዲስፕሊን ነገሩ ሁሉ ተቀመመ። 
 
የኢትዮጵያ ሊቃናት ስለምን #አድካሚውን መንገድ እንደሚመርጡ ባይገባኝም፤ የትውልዱ ድካም እና ልፋት ባክኖ መቅረቱ ግን በእጅጉ ያንገበግበኛል። በየቤታችን ወንድሞቻችን ገብረናል በናቅፋ በአፋቤት በርሃ።
 
የሆነ ሆኖ ትልቅ ሰው #አይሞትም ህያው ነው። ክቡርነታቸው ልጆችም ስላላቸውም ተመስገን ነው። እኒህን ታላቅ ሰው ኢትዮጵያ ስታጣ ኢትዮጵያን እግዚአብሄር #ያጽናሽ ማለት ይገባል።
 
በተጨማሪም ለቤተሰብ፤ ለወዳጅ ዘመድንም መጽናናቱን እመኛለሁኝ። ከእኛ የቀደመው ትውልድ መራራ ስንብት እያደረገ ነው። አይዋ አይለዬ #ሞት ወደ እኛም እየገሰገሰ ነው። ቀጣዮቹ እኛው ነን። እርምጃችን #በጥንቃቄ እና #በዲስፕሊን ቢሆን ምርጫየ ነው። አክሰሱ ላላቸው ልጆቻችን #በሚያስተምር መልኩ ቢሆን #ትጋታችን ምርጫየ ነው።
 
በተረፈ ጊዜያቸውን ሳያባክኑ ከልጅነት እስከ ዕውቀት እናታቸውን በቅንነት ላገለገሉት ለተከበሩ ብ/ ጄኒራል ውበቱ ጸጋዬ ለከፈሉት መስዋዕትነት ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁኝ። እግዚአብሄር ይስጥልን። አሜን።
 
ይህን መረጃ ከኖር በእግዜር ነው ያገኜሁት። የክቡርነታቸው በአገልግሎት ጊዜን ይመለከታል።
ሥርጉትሻ 2025/09/16
 
"የናቅፋው ጀግና የሁለተኛው አብዮታዊው ሠራዊት ዋና አዛዥ የነበሩት ብ/ጀነራል ውበቱ ፀጋዬ አርፈዋል። ብ/ጀነራል ውበቱ ፀጋዬ የቀኃሥ ገነት ጦር ትምህርት ቤት 18ኛ ኮርስ ምሩቅ ናቸው። በኮንጎ ጠቅል ብርጌድ የሰላም ማስከበር አለማቀፍ ተሳትፎም ዘምተዋል። አጠቃላይ የውትድርና ህይወታቸውን ያሳለፉት በፈታኙ የኤርትራ አውደ ውጊያዎች ውስጥ በማለፍ ነው።"
 
"ከ1971 -- 1979 ዓ.ም የ 508ኛ ግብረኃይል ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ቀጥሎ የግብረ ኃይሉ አዛዥ ፤ ቀጥሎ የናደው ዕዝ አዛዥ ፤ ቀጥሎ የግዙፉ ሁለተኛ አብዮታዊው ሠራዊት (ሁአሠ) አዛዥ ፤ በመጨረሻም የብሔራዊ ውትድርና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሆነው ሀገራቸውን ግንባራቸውን ሳያስደፍሩ ትልቅ አመራር የሰጡት ጀግና የጦር መሪ ነበሩ።"
 
"በቀይ ኮከብ ዘመቻ ጊዜ በጦራቸው ፊት በናቅፋ ግንባር ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እጅ የጀነራልነት ማእረግ ያገኙ መኮንን ናቸው።" 
 
"ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር" የተሠኘ ዳጎስ ያለ መጽሐፍም ፅፈው ለተደራሲያን አቅርበዋል። ብ/ጀ ውበቱ አሜሪካን ሀገር ህክምና በመከታተል ላይ እንዳሉ ነው ያረፉት።
 
አብዮታዊው ሠራዊት ገፅ በጀግናው ብ/ጀ ውበቱ ፀጋዬ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል። ለልጃቸው አርክቴክት እስክንድር ውበቱ ፣ ለቤተሰቦቻቸው ፣ ለወዳጆቻቸው እና ለቀድሞ ሠራዊት አባላት በሙሉ መፅናናትን እንመኛለን።"
 
ኢትዮጵያን ስላገለገሏት ከልብ እናመሠግናለን ጀነራል ውበቱ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?