የኢትዮጵያ #ኦርጋኒክ ተፈጥሮ #ያልከበዳቸው ሊቀ - ሊቃውንት #የኔታ ኢኒጂነር ጌዲዮን አስፋው።

 

የኢትዮጵያ #ኦርጋኒክ ተፈጥሮ #ያልከበዳቸው ሊቀ - ሊቃውንት #የኔታ ኢኒጂነር ጌዲዮን አስፋው።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
 
 
የህዳሴ ግድቡን ዶሴ የያዙት ኢንጅነር
ግብፆች አንድ ሳተላይት መድበው ይከታተላሉ ኢ/ር ጌዲዮን አስፋው ‪@ethiopian_reporter‬
 
• ይህን ደርባባ የትውልድ የሆነ ሊቀ - ክህሎት ብጽፍበት ነው የሚሻለኝ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
አንድ የወግ ገበታ መፃፍ ያንሰዋል። ይህ ለዘመኑ የምርምር መዕከል የሚያስከፍት #ተቋማዊነት ነው። ይህ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ #ካሪክለም ተነድፎለት ልጆች ሊማሩት የሚገባ ስኩን የክህሎት ሂደት ነው። ይህ ኢትዮጵያ የተረጋጋ መንፈስ መጠነ ሰፊ ህሊና እና የመቻል አቅም ያላቸው ልጆች እንዳሏት የሚያስነብብ፤ የሚተረጉም፤ የሚያመሳጥር የቅኔ #ቀንዲል ነው።
 
እንዲህ ዓይነት ስኩን ተግባር ይከውኑ የነበሩ እኔን በቅርበት ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው የቀረጹኝ በዘመነ ኢሠፓ የጓድ ገብረመድህን በርጋ፤ የቺኮዝሎባካያ እና የሃንጋሪ አንባሳደር የነበረው የአንባሳደር ወንድወሰን በዘመኑ የነበሩ የሌሎችም የፖለቲካ ሊቀ- ሊቃውንታት የሙያ ርጉ አባቶቼ የተግባር አምሳያ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱን ክፍል ሦስት /// ሦስት ጊዜ አዳምጨዋለሁኝ።
 
ኢትዮጵያ ህግ ናት። ኢትዮጵያ ፍልስፍና ናት። ኢትዮጵያ ሳይንስ ናት። ኢትዮጵያ ዩንቨርስ ናት። ኢትዮጵያ #ይሉኝታም ናት እያልኩ በድፍረት መፃፍ ከጀመርኩ ወደ ፲፭ ዓመታት ተጠግቶኛል። ይህንን ምልከታዬን ያረጋገጠ ክህሎት - ማስተዋል - ብቃት - ልቅና - ቅንነትም ያገኜሁበት የዘመናችን ታላቅ ቃለ - ምልልስ ሆኖ አግኝቸዋለሁኝ። በአጤ አባይ፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በኢትዮጵያ ቴሌኮም፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ነክ ጉዳዮች፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዙሪያ ጠንቃቃ እና ሲበዛ ቁጥብ ነኝ። ጠቅሞኛልም። 
 
#የአጤ አባይ ግድብ መነሻ ሂደቱ ብቁ ነበር ማለት እችላለሁኝ።
 
እኔ ከቃለ ምልልሱ በአገኜሁት መረጃ መሠረት፤ የሂደቱ ክንውን በብስጭት የተነከረ ሆኖ አላገኜሁትም። ይህ ሂደት በእልህ የተቀመረ አይደለም። ይህ የስኬት ውጥን በማንአህሎኝነት የተጀመረ አይደለም። ይልቁንም ይህ ክንውን በተገባቸው ባለሙያወች ዊዝደምን ሰንቆ፤ ትዕግሥትን ማኒፌስቶ አድርጎ፤ ቅንነትን ምራኝ ብሎ፤ ግሎባላይዜሽንን በአብሮነት ቤተኛ አድርጎ፤ ዓለም ዓቀፍ ህግጋትን ግዛኝ ብሎ ፈቅዶ፤ የጉርብትናን ትውፊት ቅደመኝ ብሎ ወዶ፤ ትናንትን - ዛሬን - ነገን በሚያገናኝ ወርቃም ድልድይ ያገናኜ ሐዋርያዊ ተግባር ነው። 
 
ከዚህ ጋር የተዘለለው የውሃ ቴክኖሎጂ ምስረታ በኢትዮጵያ፤ የሸለቆወች ጉዳይ አጀንዳ የማድረግ ጥበብ በደርግ ዘመን መሆኑ ምስክርነቱን አዳምጫለሁኝ። ጠቃሚው ነገር በዚህ ዙሪያ መስኩ ከፖለቲከኞች የበቀል ፋስ ማምለጡ ነው፥ የግድቡን የምሥራች እርጋን ያጎናጸፈው ብዬ አሰብኩኝ። የአመራር ተከታታይነት፤ የኢትዮጵያዊነት ውስጥነት ቅኝቱ በቅኔ ተውቧል። 
 
ሂደቱ ደልዳላ ነበር። ሂደቱ ርጉ ነበር። ሂደቱ እሩቅ አሳቢ ቅንነት ተተርጉሞበታል። 
 
#ሂደቱ ተቋምነቱ።
1) ይገርማል።
2) ይደንቃል።
3) ያስተምራል።
4) ይመረምራል።
5) ይፈታትሻልም። 
 
የአባይ ግድብ መነሻ መሠረቱ በተጠረገ ንጹህ - ልቦና፤ በፃዕዳ - መንፈስ፤ ኢትዮጵያ ቀደም ብላ ባቋቋመቻቸው ተቋማት ጥሪት፤ አባይን በሚመለከት ብቻ ሳይሆን የተማረ ትውልድ ለመፍጠር በተጋችባቸው የኢንተግሬሽን መስኮች ሁሉ ከአጤ ኃይለሥላሴ ተነስቶ፤ ደርግን አክሎ፤ ኢህአዴግን ጨምር፤ አሁን ሥልጣን ላይ ያለውን ብልጽግናን እንደ ተሳትፏቸው በሰመረ ቅብብሎሽ ትውልድን በሙያ ከማብቀል ጀምሮ፤ በሥልጠና አግዞ፤ በኢትዮጵያዊነት መንፈስን አንፆ ትውልድ ለትውልድ ይወራረስ ዘንድ ቁሞ ያስተማረ የድርጊት #ዓውራ ነው ለእኔ የሂደቱ ጉዞ። ለቀጣዩ ጉዞም በብቃት መቀጠል መሠረቱ ያማረ - የሰመረም ስለሆነ ስኬቱ ይቀጥላል ባይ ነኝ። 
 
ከንፍሮ ጥሬ ያወጣቸው ልቦናቸው ቧ ያሉ ሰፊ ሰብዕናወች ሁሉን ወጀብ፤ ሁሉን ወጨፎ፤ ሁሉን የጊዜ በቀል ፈተናወች እና ገጠመኞች ታግሰው በአገር ውስጥ ሆነው፤ እናት አገር ኢትዮጵያ ከእኔ ምን ትጠብቃለች የሚለውን ማሳካት ለእኔ የቁም #ፃድቅነት ነው። ኢትዮጵያ ቅንነቷ፤ ለህግ ተገዥነቷ፤ ለቲም ወርክ ያላት ተነሳሽነት፤ የሌላ አገርን ፍላጎትን ሳትረገጥ ወይንም ሳትጠቀጥቅ፤ በማይመች ሁኔታም ይሁንታን ፈቅዳ እግዚአብሄር ከፈጠረው ትዕግሥት በላይ ታግሳ፤ እግዚአብሄር ከፈጠረው ግልጽነት በላይ ግልጽነቷን ለዓለም አሳይታ የፈጸመችው ትንግርታዊ ሂደት በውነቱ መመካት ባያስፈልግም #አኩሪ ነው። ይህን ዝክረ ምዕት ማነወር፤ ማቃላል ማንም አቅሙ ይኖረዋል ብየ አላስብም። 
 
ይህንን የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ገዢም ይሁን ተፎካካሪ፤ ተፎካካሪም ይሁን #ተጠማኝ ሊያቃለው ሊያጣጥለው አይችልም። ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ማኒፌስቶ በላይ በራሷ በኢትዮጵያ ኦርጋኒክ ተፈጥሮ በበዛ ጨዋነት፤ በበቃ ሙያዊ ክህሎት፤ ደረጃውን በጠበቀ ማስተዋል የተከናወነው ተግባር ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው የምለውን ብሂል በተግባር ያደመጥኩበት ቃለ ምልልስ ነው። ሪፖርተር ይህን የመሰለ መንፈስን ሙሉ ለሙሉ የሚያሳርፍ፥ ትዕግሥትን - የጠገበ፤ ብቃትን - ለልዕልና የሚያስረክብ ቃለ - ምልልስ ስለአደረገ እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁኝ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ጠያቂውም ልኩ ነበር ለዚህ ብቁ ሂደት። 
 
ትውልዱ ይህን ቃለ - ምልልስ ይቅረጸው - #ያጥናውም። ይህ የሂደቱ ስኩን ጉዞ ለትውልዱ ክብሩ - ማዕረጉ፤ ዩንቨርስቲው ነውና። ወደ ተከበሩ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ሰብዕና ስመለስ ትውልዱ በአንድም በሌላም ሮልሞዴል አጣ ለሚለው ሞጋች ዕሳቤም መልስ የሚሰጥ ይመስለኛል። በእጅጉ እርጋታቸው #ይመስጣል ሰብዕናቸው። ሳጠቃልለው የኢትዮጵያ ኦርጋኒክ ተፈጥሮ #ያልከበደቻቸው፤ ኢትዮጵያን በቅንነት ውስጣቸው ያደረጉ፤ በሙያችው ብቻ ኃላፊነት እና ተጠያቂነታቸውን ያከበሩ እና ያስከበሩ ዓራት ዓይናማ፤ #አይነታ ሊቅ ሆነው አግኝቻቸዋለሁኝ። እግዜአብሄር ይስጥልኝ #የኔታ
 
በጣም ብዙ ጥቅል ጉዳዮች ተፍታተው በግልጽነት በቃለ - ምልልሱ ቀርበዋል። እኔ እንዲያውም በእንግሊዘኛም ቢሆን፤ ሽቶትጋርድ ጀርመንም የመማር ዕድሉ ስለገጠማቸው በጀርመንኛም ቅናዊ ሂደቱን የዓለም ህዝብ ቢያውቀው ፋታ አጥተው በታወከ ስሜት ለሚጓዙት የግብጽ የፖለቲካ ኢሊት የሚያቀርቡትን የክስ ሁነት ረብ ሊያደርገው ይችላል ብየ አስባለሁኝ። በሌላ በኩል የጀርመን፤ የፈረንሳይ፤ የእንግሊዝ እና የደቡብ አፍሪካ የቲሙ አባላትም በዚህ ዙሪያ ዕውነቱን ቢገልጹ ጥሩ ነው ባይ ነኝ።
 
የኢትዮጵያ የመንግሥት ሚዲያወች የውጭ አገር ባለሙያ ሆኑ፤ ታዛቢ የነበሩ ዜጎችን በዕቅድ በተከታታይ ቃለ ምልልስ ሊያደርግላቸው ይገባል ባይ ነኝ። ጊዜውን መሻማት ይገባል። ይህን ስኬት ከፕሮፖጋንዳ ጋር ማነካካትም ፈጽሞ አይገባም። እራሱን የሚገልጽበት ብቃቱ ለፕሮፖጋንዲስታዊ ተግባር ልኩ ስላልሆነ። 
 
በቃለ - ምልልሱ ቀረ የምለው የተሳታፊወች ሥም ቢኖር መልካም ነበር። መሠረታዊ ነውና። ወይንም ቃለ - ምልልሱን ሪፖርተር ጋዜጣ በሰነድ መልክ ቢያዘጋጀው፤ የቴክኒክ ግሎባል ባለሙያወችን ዘርዝሮ ቢያቀርበው ታሪክ - በታሪክነቱ ለህዝብ ተደራሽ መሆን ይችላል። የሂደቱ ክንውን ሁሉም መሰነዱን አዳምጫለሁኝ። ወደ ፱፻ ገፆች እንዳሉትም አድምጫለሁኝ። ለግሎባሉ ዓለም ይህን መሰል ቃለ - ምልልስ ተተርጉሞ ቢቀርብ የግብጽ የፖለቲካ ኢሊትን መወራጨት ያስታግሳል ባይም ነኝ። አይደለም የውጩ ዜጋ በፖለቲካ የሚሳተፈው ወገን ሂደቱን በዚህ ዓይነት ጥልቀት ያውቀዋል ብዬ አላስብም። ሂደቱ እኮ በራሱ የጥበብ ቅኔያዊ ጥልፍ ሆኖ ነው ያገኜሁት። ጥንቃቄው አልተዘከረም። ቅድመ መሰናዶው በቅጡ አልተብራራም። 
 
#እርገት ይሁን።
 
አቤቶ ግብጽ፤ አቤቶ ሱዳን ግድባቸውን ሲሰሩ ኢትዮጵያን አላማከሩም። የዊዝደም ባለቤቷ ኢትዮጵያ ግን በግልጽነት፤ በመርህ፤ በቅንነት፤ በአክብሮት እና በርህርህና የፈጸመችው ተግባር ኢትዮጵያን #ነፍሷን እንዳይ አግዞኛል። እግዚአብሄር ይስጥልኝ ለሁሉም የአጤ አባይ ቅኖች። አሜን።
 
ሂደቱን ለመተቸት መንጠራራቱ አያስፈልግም። ደራጃው ልክ ስለማይሆን። ጠባብ ልብስም፤ ልቅ ልብስብም ካለልኩ ከሆነ ይወጥራል ወይን ይንቦረቀቃል። ጎንደሮች ባለቅኔወች ናቸው። "ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" ይላሉ። #ልካችን እንወቅ። በተረፈ ውጭ የሚኖሩ የሙያው ባለቤቶች፤ አገር ቤት የሚኖሩ የሙያው ባለቤቶች፤ ለፈጸሙት የነፃ የፈቃደኝነት ስኩን ተግባር ምስጋናዬ ከህሊናያ፤ አክብሮቴም ከንጹህ መንፈሴ ነው። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን። 
 
እንዲህ የማያሳፍር፤ እንዲህ አንገት የማያስደፋ፤ እንዲህ የማያሸማቅቅ ጥርት፤ ጥንቅቅ፤ ልቅም ያለ #ንጥር ሰብዕና እና የተግባር ሂደት በእራሱ #አገር ነው። በራሱ አናባቢም - ተነባቢም ነው። ተመስገን።
 
"አድርገህልኛል እና አመሰግንኃለሁኝ።"
 
ቸር አስበን ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
16/09/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?