A+ #ብራቦ አማራ ክልል። በዘመንህ እንዲህ የልብ አድርስ ተግባር ብየ እምመሰክርልህ አልነበረኽም።

 

A+ #ብራቦ አማራ ክልል። በዘመንህ እንዲህ የልብ አድርስ ተግባር ብየ እምመሰክርልህ አልነበረኽም።
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
ምዕራፍ ፲፯
 
 
#የማንነት #ቀውስ እና ሙሁርነት #ግብግብ ገጠሙ። "ግዕዝ የሞተ ቋንቋ ነው ዶር በድሉ ዋቅጅራ።" መሃከነ!
 
አይዋ እከሌ፤ ቢማሩ --- ቢመራመሩ ግዕዝ በአበጃት አገር ላይ ነው። ፈላስፋ ቢሆኑ ሳይንቲስት፤ ኤክስፐርት ቢሆኑ የዩንቨርስቲ መምህር፤ ከመጨረሻው የዕውቀት፤ የሥልጣን መንበር ላይም ቢደረሰም፤ የዘመን ጋሻነትም ቢኖር፤ በመልክ፤ በቁመና የሚያስጎመጁ ዓይነት ሸበላም ቢሆኑም #የማንነት #ቀውስ ካለ የሃሳብህ ክሳትን ቀጫጫነትን እርስወን መዝኖ መዝኖ አደባባይ ላይ #ያሰጣል። 
 
#ሙጃ ሃሳብ ለትውልድ #የአረም ክርም ነው። የግዕዝ ቋንቋ ቋንቋ ብቻ አይደለም #የሚስጢር#የፈውስ#የስኬት #ማህጸን እንጂ። ለእርስወ ይቀራል እንጂ እጬጌው ግዕዝ በግሎባል ደረጃ ከፍ ብሎ ከተቀመጠበት መንበር ንቅንቅ ሊያደርጉት ከቶውንም አይቻልም። #ቁጭላ ሃሳብ ቋት አይገፋምና። በትንታ አጋዢነት በኖ ይቀራል። 
 
ልባሞቹ አገራት፤ ትንግርቶቹ - አህጉራት፤ ሥልጣኔያቸው የተቀመመው በግዕዝ የሚስጥራት ጥልቅ #ልቀት ነው። ለዚህም ነው ቋንቋውን ልጆቻቸው ይማሩት ዘንድ በከፍተኛ ተቋሞቻቸው የተገባውን ደረጃ ሰጥተው እንዲማሩ የሚያደርጉት። የአጤ ጀርመን የመዳህኒት ቅመማ ከኢትዮጵያዊው የፈውስ መጸሐፍ ልቅናም ይቀዳል። የራሳቸውን የሚያከብሩት ጀርመኖች፤ የዕውቀት ዘርፍን በድንበር ወይንም በዞግ ሳይከልሉ ነፃነቱን ዓውጀውለታል። ይባረኩ። አሜን።
 
ማህበረ አያ እከሌወቼ የተፈጠሩበትን ዝሃ - ግራ፤ የተገኙበትን የእትብት ልቅና እንዲህ አጣጥሎ፥ አሽቀንጥሮ መጣል የጤና አይደለም። በዚህ አያያዝ ጤናው የታወከ በርካታ ሰብዕና እንዳለ አመላካች ነው። ነጣዩን የጥላቻ silent Discrimination የሚከበክብም እራሱን ቢመረምር መልካም ነው። በአማርኛ ቋንቋ ላይ ያለው መጨነቅ መጠበብ አልበቃ ብሎ በእጬጌው ግዕዝ ላይ ይህን ያህል ዱላ ልዝነት ነው። ለነገሩ ልዝ እንጨት ወይ አይነድ፤ ወይ አያነድ ጭስ ብቻ።
 
ድፍረትም #ልክ አለው። #መቀናጣትም መጠን አለው። #መንጠራራትም ደረጃ አለው፤ የሚሊዮኖች ግሎባል ቀደምት ዕንቁን ልሳነወርቅ ቋንቋ ሲዳፈሩት የትኛው ፕላኔት ላይ ሆነው እንደሆን እራስን መመዘን የሚገባወት ይመስለኛል አይዋ - እንቶኔ። መማር ማለት ማወቅ ነው። ማወቅም ዝቅ ሲል ጥበብ ከፍ ሲል ዊዝደም ነው። መማር እራሱን ***መማርን #ተቃውም ሲታይ ግን የመማር ትርጉሙ #ቁርጭምጭሚት ያሰኘዋል። በተለይ በብዙ ጉዳዮች ከምናውቃቸው ሙሁራን ዘንድ ይህን የመሰለ ውስጥን የሚያዋርድ ውርዴ ሃሳብ ማድመጥ ይቆጠቁጣል። ያስተዛዝባልም። ጊዜ ደጉ ወንፊቱን፤ ማንዘርዘሪያውን ወበራውን ይዞ እንዲህ ከቸች።
 
ቀድሞ ነገር የትኛውንም ቋንቋን በመማር ዘርፍ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ አያስፈልገውም። #ዳፍንት ህሊና ቤት ለእንግዳ ካላለ በስተቀር። ለዚህም ነው እኔ ኢትዮጵያ የከበደችን ለሁላችንም ነው የምለው። በውነት ከብዳናለች። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ትናንት በልዩ እዮራዊ ዩንቨርስ አቅሙ አጤ ግዕዝ #ያጣፈጣት#የቀመማት#የተቃኛት የዜማ ጉልላት ናት። ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንከር ስትባል እኮ በመደዴ ወይንም በዝርግ ዕሳቤ አይደለም። መሆኗን ባመሳጠረ ዓራት ዓይናማ ተግባሯ እንጂ። ለዚህ ደግሞ እጬጌው ግዕዝ ኃላፊነቱን እና ተጠያቂነቱን የተወጣ ጀግና ልሁቅ ቋንቋ ነው።
 
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር በመሆኑ በስውር ለሚወጉት ሁሉ ፍርድ እና ዳኝነቱን እንዲህ በግላጭ ይገልጠዋል። ይህ ተመስገን ነው። ከጅምላ ጉዞ #ተግ ብለን እናስብ ዘንድ ባትሪያችን ይሆናል።
 
"የዝም አንልም" በዘመነ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የእስልምና ተከታዮች ጨዋ ንቅናቄ ላይ በሙሉ አቅሜ እተጋ ነበር። እናም ከእስር ሲፈቱ ለሊቃናቱ ግዕዝ እንዲያጠኑ ዕይታየን አጋርቼ ነበር። ምክንያቱም ግዕዝ ዩንቨርሳል ዕውቀትን በልኩ የሚመሳጠርበት #እጬጌ ቋንቋ ስለሆነ። ቢማሩት የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ቢጠቀሙ እንጂ አይጎዱበትም። የዩንቨርስን የላቀ ሚስጢር ለማመሳጠር አጤ ግዕዝ ብሩኽ እና ቀና እንዲሁም ቅንም ጎዳና ነው።
 
ግዕዝን ቀድመው የተማሩ የኢትዮጵያ ሊቃናት፤ የግሎባሉም ሊቃናት ከሌላው የቀለም ተማሪ ጋር በዓይነትም በይዘትም ይለያሉ። ግዕዝ የተፈጥሮ ሳይንስን፤ የማህበራዊ ሳይንስን፤ የየአገሩን የሃይማኖት ፍልስፍናወችን ሁሉ በጥልቀት እና በስፋት የሚጠበብ የዕውቀቶች ሁሉ #በኽረ መንበር ነው። የአማራ ክልል ልጆች ይህንን ዕድል እንዳታሳልፋት። ተጠቀሙበት። እንኳንም ደስ አላችሁ።
 
የሚገጥሙ የቴክኒክ፤ የሎጅስቲክ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። መጀመሩ ግን ታላቅ #የምስራች ዜና ነው። በርታልኝ አማራ ክልልሻ! ወሳኝ እና ወቅታዊ እጅግም ጠቃሚ ውሳኔ ነው። አንቱ የሆነ የህሊና ብቃትን የሚያመሳክር - ውሳኔ። ተመስገን። እንኳን ለዚህ አበቃህ አማራ ክልልሻ። 
 
#አቤቱ የአማራ ክልል በነካ እጅህ ………
 
ትምህርት ሰላማዊ መረጋጋትን ስለሚጠይቅ #ከፋን ካሉ ልጆችህም ጋር በእልህ ሳይሆን፥ በጥበብ፤ በብልጠት ሳይሆን በብልህነት ተቀራርበህ ለችግሩ መፍትሄ አብጅለት። ዘላቂ መፍትሄ በችሮታ ሳይሆን ልዩ ጥረትን ይጠይቃል። ፌካዊ ሳይሆን ተጨባጭ ዕውናዊ ጥረትን። በክልልህ ታስረው የሚገኙ የፖለቲካ እስረኛ ልጆችህንም ፍትህ መግባቸው። ትውልድ በካቴና፤ ከካቴና የሚመገበው ዕውቀት የለም እና። ዕውቀት ያለ ሙሉ ነፃነት እና ሰላም ለስኬት አይበቃም።
 
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ዛሬ ዘለግ ያሉ ዕይታወቼን አጋራሁኝ። የዛሬ 5/4/3/2 ዓመታትንም አጤ ፌስቡክ አስታውሶኝ ጠቃሚወችን ብቻ ለይቼ አጋርቻለሁኝ። በሌላ በኩል ለሥርጉትሻ ቅን ቤተኞች ይበጃሉ ያልኳቸውንም ሃሳቦችን በዕለቱ ባሊህ ብያለሁኝ። ነገ እንገናኛለን። ምዕራፍ ፲፯ ይቀጥላል።
 
የቢቢሲ የአማርኛ ክፍል ልቅም፤ ጥንቅቅ አድርጎ ለሰጠን መረጃ የከበረ፤ ዘንካታ አክብሮቴን አክዬ አመሰግናለሁኝ። ሙሉውን ታገናዝቡት ዘንድ ለጥፌዋለሁኝ።
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
16/09/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ለሚስጢራችን ዘብ እንቆማለን።
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
"ግእዝን ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ማስተማር ወደፊት ለመሻገር ወይስ ወደ ኋላ ለመመለስ?
 
በአማራ ክልል ከዘጠኝ ሺህ በላይ አንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ተገልጿል።" 15 መስከረም 2025.
"የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ በሁሉም የአንደኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የግእዝ ትምህርት እንደሚሰጥ አስታውቋል።
 
ትምህርቱን ለመስጠት የታሰበው አገር በቀል እውቀት ለትውልድ መተላለፍ አለባቸው በሚል እሳቤ ከሕብረተሰቡ በቀረበ ጥያቄ መሠረት እንዲሁም የትምህርት ባለሙያዎች ባደረጉት ጥናት የቋንቋው ፍላጎት መኖሩን በመረጋገጡ እንደሆነ ተገልጿል።"
 
"ሆኖም የግእዝ ቋንቋን ከታች ክፍል ጀምሮ የማስተማር አስፈላጊነትን በተመለከተ በርካቶች የተለያየ አቋም ይዘው እየተነጋገሩበት ይገኛሉ። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ላቀው የተባሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ትምህርቱ መሰጠቱን በበጎ ተመልከተውታል።"
"አብዛኞቹ የሃይማኖትም ሆኑ የታሪክ ጥንታዊ መጻሕፍት እንዲሁም ከሕክምና ጋር የተያያዙ መረጃዎች የተጻፉት በግእዝ በመሆኑ" ልጆች ቋንቋውን መማራቸው የአገራቸውን ታሪክ ለማወቅ ዕድል ይሰጣቸዋል ብለዋል።"
 
"የቋንቋ ጉዳይ ፖለቲካዊ እየተደረገ ነው እንጂ" ሁሉም ተስማምቶበት በአገር ደረጃ ቢሰጥ መልካም ነው የሚል ሃሳብም አላቸው።"
"መሐመድ የተባሉ የወልዲያ ከተማ ነዋሪ ግን ትምህርቱ መሰጠቱ ላይ ተቃውሞ ባይኖራቸውም" "ጊዜው አሁን አይደለም" ይላሉ።
"ትምህርቱ እንዲሰጥ እንዴት እንደተጠና እንደማያውቁ የሚገልጹት መሐመድ፣ ትምህርቱ እንዲሰጥ የተወሰነበትን ወቅት የተመለከቱ ሁለት ነጥቦችን አንስተዋል። አንደኛው በክልሉ የቀጠለው ግጭት ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ዓለም አንድ እየሆነ የመጣበት እና ቴክኖሎጂ የተራቀቀበት ዘመን መሆኑ ነው።"
 
"መሐመድ ምንም እንኳን ለልጆች ተጨማሪ ቋንቋዎችን መስጠት ምንም ጉዳት እንደሌለው ቢያምኑም፣ በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት መደበኛውን ትምህርት መስጠት ባልተቻለበት ሁኔታ ተጨማሪ ትምህርት የመስጠቱ ውሳኔ ውሃ አያነሳም ይላሉ።"
"ከዚህም ባሻገር ዓለም አንድ እየሆነች በመጣችበት በዚህ ዘመን ለሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ትኩረት መስጠቱ የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚል ሃሳብ አላቸው።"
 
"ይሁን ቢባል እንኳን በቂ መምህራን እና መጽሐፍትስ አለ ወይ?" ሲሉም ውሳኔው ብዙ ጉዳዮችን ከግምት ያስገባ እንዳልሆነ ያምናሉ።"
"የቋንቋ ምሁራንም ውሳኔውን በተመለከተ የተለያየ ሃሳብ ነው ያንጸባረቁት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ሙሉሰው አስራቴ፣ የተግባራዊነቱ እና የአፈጻጸም ሒደቱ ላይ ጥያቄ ቢኖራቸውም፣ ቋንቋው እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት መሰጠቱን በበጎ ነው የሚያዩት።"
 
"ግእዝ ለኢትዮጵያ ነባር የቅርስ ቋንቋ ነው። አውሮፓውያኑ ላቲን፣ ግሪክም የግሪክ ቋንቋ፣ እስራኤሎች እብራይስጥ፣ ሕንድም ሳንስክሪት እንዳላቸው ሁሉ ኢትዮጵያም ሥልጣኔዋ፣ ቅርሷ፣ ታሪኳ እና እውቀቷ በሙሉ የተከማቸበት ቋንቋ በመሆኑ መሰጠት አለበት" ይላሉ።
"በዚያው ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ መምህር እና ደራሲ የሆኑት በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) ግን ከመምህር ሙሉሰው የተለየ አቋም ነው ያላቸው።"
 
"ግእዝ የሞተ ቋንቋ ነው" የሚሉት መምህር በድሉ፣ ይህንን ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ መስጠቱ እርባና የለውም ብለዋል።"
 
"አንድ ቋንቋ ከ25 ሺህ በታች ተናጋሪ ካለው አደጋ ውስጥ እንደሆነ፣የአፍ መፍቻ ተናጋሪ ከሌለው ደግሞ ሞቷል እንደሚባል የሚናገሩት መምህሩ፣ ይህንን "የሞተ ቋንቋ" ከታች ከፍል ጀምሮ መስጠት የተማሪዎችን ጊዜ ማጥፋት እንደሆነ ገልጸዋል።"
 
"መምህሩ "ግእዝ የሞተ ቋንቋ ነው" ቢሉም አንድ ቋንቋ የአፍ መፍቻ የሚያደርገው እና የሚነጋገርበት ሰው መጥፋቱ ቋንቋውን እንደማይገድለው የሚናገሩ ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎችም አሉ። ለዚህም አንድ ተናጋሪ ያለው ቋንቋም ቢሆን ተጨማሪ ተናጋሪዎችን የማፍራት ዕድል ይኖረዋል የሚል ምክንያት ይሰጣሉ።"
 
"አንድ ቋንቋ ሞተ ለማለት የሚያስችለው ስለዚያ ቋንቋ ምንም ዓይነት ጥንታዊ ታሪክ መናገር የሚችል ሰው ማግኘት ሳይቻል ሲቀር ብቻ ነው ሲሉም ይሞግታሉ።"
 
"ቋንቋን የመማር ወሳኝ ዓላማ ለተግባቦት እና ሕይወትን ለመምራት እንደሆነ የሚናገሩት መምህር በድሉ ግን፣ ግእዝ ለተግባቦትም ሆነ ሕይወትን ለመምራት አሁን ላይ ጥቅም የለውም ብለዋል።"
 
"ሆኖም የግእዝ ቋንቋ ጭራሽኑ በትምህርት መልክ መሰጠት የለበትም የሚል አቋም የላቸውም።
 
የግእዝ ቋንቋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በጀርመን እና በፈረንሳይ ውስጥ ይሰጣል የሚሉት መምህር በድሉ፣ ቋንቋው የሚሰጠው በግእዝ ቋንቋ ምርምር ማድረግ ለሚፈልጉ ብቻ መሆኑን ይጠቅሳሉ።"
 
"በመሆኑም ትምህርቱ ይሰጥ ከተባለም መሰጠት ያለበት ከ9 ክፍል ጀምሮ ወይም ለአንትሮፖሎጂ፣ ለታሪክ እና ለቋንቋ ጥናት ፍላጎት ላላቸው የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች እንዲሆን መምህሩ ይመክራሉ።"
 
"ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ለአንድ ዓመት የግእዝ ቋንቋ መማራቸውን የሚናገሩት መምህር በድሉ፣ ግእዝ አይጠቅምም የሚል አቋም ባይኖራቸውም፤ የተግባቦት እና የሕይወት ጥቅሙ ውስን የሆነን ቋንቋ ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ መስጠት "ለተማሪዎች የጊዜ ብክነት ነው የሚሆነው" ሲሉ ውሳኔውን ተችተዋል።"
 
"ተማሪዎቹስ ዘጠኝ ዓመት ሙሉ ምንድን ነው የሚማሩት?" ሲሉም በሚኖረው ዝግጅት ላይም ጥያቄ አንስተዋል። የግእዝ ቋንቋ ትምህርት በሙሉ ትግበራ ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ መሰጠት የተጀመረው ባለፈው ዓመት ቢሆንም በመምህራን እጥረት ምክንያት በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ማዳረስ ሳይቻል መቅረቱን ክልሉ ለቢቢሲ መግለጹ አይዘነጋም።"
 
• ግእዝ ወደፊት ያሻግረናል ወይስ ወደ ኋላ ይመልሳል?
 
"መምህር ሙሉሰው "የኋላውን የተወና ራሱን የማያውቅ ሕዝብ ሥር ሳይኖረው እንደሚበቅል ተክል ነው" ይላሉ።
"የኋላውን ትቶ ወደፊት መሻገር የለም፤ ሥር የሌለው ተክል የሆነ እክል ከገጠመው ወዲያው ነው የሚደርቀው" ሲሉም ጥንታዊ እውቀትን መመርመር እና ማወቅ ለአንድ ትውልድ ወሳኝ መሠረት እንደሆነ አስረድተዋል።
 
"በግእዝ ጽሑፍ ውስጥ ሃይማኖት፣ ፍልስፍና፣ የባህላዊ መድኃኒት እውቀት፣ የሥነ ፍጥረት እውቀት፣ ታሪክ እና ባህል አለ" የሚሉት መምህሩ፣ እነዚህን ሁሉ ቆፍሮ ለማውጣት እና ወደፊት ለመራመድ የግእዝ መሠረታዊ ዕውቀት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
"ግእዝን የምንማረው በየዕለቱ ዳቦ ወይም ቡና ለመግዛት አሊያም መግባቢያ ቋንቋ ስለሌለን አይደለም" ብለዋል።
 
ከዚህም ባሻገር ዘመናዊ የሆኑ ጽንሰ ሃሳቦችን ለመሰየም የረዳ ቋንቋ በመሆኑ ለአማርኛም ሆነ ለትግርኛ እንዲሁም ለሌሎች የሴም ቋንቋዎች ማደግም እንደ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ይጠቅሳሉ።
 
ግእዝ ሃይማኖታዊ ቋንቋ ነው የሚልና ሌሎች የተሳሳቱ አመለካከቶች እንዳሉ የሚጠቅሱት መምህሩ፣ አዎንታዊ ነገሩ ላይ ትኩረት በማድረግ ሌሎች ክልሎችም ይህንን ቋንቋ ከግንዛቤ ቢያስገቡ መልካም እንደሆነ ይመክራሉ።
 
አቶ ላቀውም የመምህር ሙሉሰውን ሃሳብ ነው የሚጋሩት። "ግእዝን መማር ወደ ፊት ያሻግራል እንጂ ወደ ኋላ አያስቀርም" ብለዋል።
"የኋለኛውን ብዙም ስለማናውቀው የወደፊቱም ከኋለኛው የተሻለ ነው ብሎ ማሰብ አይቻልም" ሲሉም ይሞግታሉ ነዋሪው። ለመምህር በድሉ ግን ይህ አይዋጥላቸውም።
 
"የትምህርት ዓላማው ተማሪዎች ለወደፊት ሕይወት እንዲዘጋጁ ማድረግ ነው" የሚሉት በድሉ (ዶ/ር)፣ ተማሪዎች በዚህ ዘመን ግእዝን ከሚማሩ 'ፈረንሳይኛ' ቢማሩ እንደሚጠቀሙ ያምናሉ።
 
ግእዝ መሰጠት ያለበት በዚያ ዙሪያ ፍላጎት ላላቸው እና እንደ ታሪክ እና አንትሮፖሎጂ ባሉ የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፎች ላይ ለሚሰማሩ ተማሪዎች እንደሆነም ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
 
"ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ የሚሰጠው የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ይዘልቃል ብዬ አላስብም፤ ቢዘልቅም ተግባራዊ የሚሆን አይደለም።"
 
• ብዙ ቋንቋዎችን መማር ምን ዓይነት ጫና ይፈጥራል ?
 
አቶ ላቀው ልጆች አዳዲስ ቋንቋዎችን ለመማር አእምሯቸው ክፍት መሆኑን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን እየተማሩ መሆናቸውን በመጥቀስ ተጨማሪ ቋንቋ መስጠቱ በልጆቹ ላይ የተለየ ጫና ይፈጥራል ብለው አያስቡም።
 
መምህር ሙሉሰው ግን ተማሪዎችን በቋንቋዎች የማጨናነቅ ጉዳይ የትምህርት ሥርዓታችን ተግዳሮት ሆኗል ይላሉ።
ተማሪዎች በትምህርት ሥርዓት ውስጥ በሚያልፉበት ጊዜ ሦስት፣ አራት ወይም ከዚያ በላይ ቋንቋዎችን እንዲማሩ ይደረጋል የሚሉት መምህሩ፣ ይህም በተማሪዎች ላይ ጫና መፍጠሩ ጥያቄ እንደሌለው ይናገራሉ።
 
መምህር በድሉም በዚህ ላይ ያላቸው ሃሳብ ተመሳሳይ ሃሳብ ነው።
 
"ቋንቋ ካለው ፋይዳ አንጻር ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾላቸው የሚሰጡ ቋንቋዎች ተማሪው ሥራ የሚሠራበት፣ የትምህርት ዕድል የሚያገኝበት ወይም ሕይወቱን ማሻሻል የሚችልበት ሊሆን ይገባል" ብለዋል።
 
በኢህአዴግ አስተዳደር ዘመን በትምህርት ዓይነት መሰጠት ስላለባቸው ቋንቋዎች ጥናት አድርገው እንደነበር ያስታወሱት መምህር በድሉ፣ በጥናታቸው ወቅት "የቋንቋ ብዛት ችግር" እንደነበር አስታውሰዋል።
 
"አንድ ተማሪ በትምህርት ሕይወቱ ብሔራዊ ቋንቋ፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ የክልሉ የሥራ ቋንቋ እና ሌሎች የውጭ ቋንቋዎችን ይማራል። ይህም በአንድ ቀን ውስጥ ካለው የትምህርት ክፍለ ጊዜ አብዛኛውን የሚወስድ ነው" ብለዋል።
 
በመሆኑም "ለተወሰነ አገልግሎት ወይም ለቤተ ክህነት ብቻ የሚያገለግልን ቋንቋ" ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ መስጠቱ የተማሪዎችን ጊዜ ከማባከን ያለፈ ጠቀሜታ እንደሌለው ያስረዳሉ።
 
መምህር ሙሉሰው በበኩላቸው በቂ ዝግጅት ከተደረገበት ግእዝ መሰጠት የለበትም የሚል አቋም ባይኖራቸውም፣ አሁን ላይ ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑን ተናግረዋል።
 
"ትምህርት ከመብላት እና ከመጠጣት ቀጥሎ መምጣት ያለበት ወሳኝ ጉዳይ ነው። በቅድሚያ ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማመቻቸት ይገባል።" 
 
የወልዲያ ከተማ ነዋሪው መሐመድም ይህንኑ ነው የሚሉት።
 
"ተማሪዎች አድራለሁ፣ እውላለሁ የሚለው ጭንቀት ቀርቶ ተምሬ ጥሩ ደረጃ እደርሳለሁ ብሎ የተዘጋጀበት ጊዜ አይደለም" የሚሉት መሐመድ፣ ግእዝን እንደ ተጨማሪ ትምህርት መስጠት በትምህርት ዓይነት ብዛት መሰላቸትን ከመፍጠሩ ባሻገር ለተማሪዎች ይከብዳቸው ይሆን ወይ የሚል ስጋት አላቸው።
 
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት፣ በተለያዩ ክልሎች በሚካሄዱ ግጭቶች እና በሌሎችም ምክንያቶች ከ5500 በላይ ትምህርት ቤቶች ሥራቸውን እንማያከናውኑ እና ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በአማራ ክልል እንደሚገኙ ገልጿል።
 
በዚህም ምክንያት በክልሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ኮሚሽኑ መግለጹ ይታወሳል።
ዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ግንቦት ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት በክልሉ 4.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው ብሏል።
 
ድርጅቱ በሪፖርቱ በክልሉ ያለው ግጭት በርካታ ቤተሰቦችን ከማፈናቀሉ ባሻገር የትምህርት ዘርፉን በእጅጉ እንደጎዳው ገልጿል።
ክልሉ አሁን በግጭት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ግጭት በተባባሰባቸው አካባቢዎች ተማሪዎች ትምህርታቸውን ካቋረጡ ሦስተኛ ዓመታቸውን እየያዙ ነው።
 
• ተጨማሪ ቋንቋዎች እንዲሰጡ መወሰን ያለበት ማን ነው?
 
በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ውስጥ ተማሪዎች ሊማሯቸው የሚገቡ ቋንቋዎች የሚወሰኑት ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ ነው ሲሉ አካሄዱን ይተቻሉ።
 
"በምክር ቤት ድምጽ ነው ቋንቋ የሚጫነው" ይላሉ።
 
ሆኖም ልጆች በራሳቸው መወሰን የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ካሉ ምርጫው የእነርሱ መሆን እንዳለበት ያምናሉ።
ብዙ ቋንቋዎች ባሉባት ኢትዮጵያ በተማሪዎች ምርጫ እንዲወሰን ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቅሱት መምህር በድሉ፣ ገደቦችን አበጅቶ በማጠጋጋት የአብዛኛውን ወስዶ መስጠት የሚቻልበትን መንገድ መከተል እንደሚገባ ይመክራሉ።
 
"በዋናነት የተማሪ እና የወላጅ ምርጫ ተይዞ፣ የሥነ ትምህርት ሰዎች ሃሳብ አካቶ ነው ቋንቋ በትምህርት መልክ መሰጠት ያለበት" ብለዋል።
መምህር ሙሉሰው በበኩላቸው ቋንቋን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት የመስጠት ውሳኔ ለመንግሥት አካል ብቻ መሰጠት እንደሌለበት እና ተማሪዎች እና ወላጆች ይጠቅማል የሚሉትን ቋንቋ መርጠው መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሌላውን ዓለም ተሞክሮ በማሳያነት በመጥቀስም በኢትዮጵያ ግን ተማሪዎች የሚማሩትን ቋንቋ ለመምረጥ የሚጠየቁበት መንገድ እንደሌለ ይገልጻሉ።
 
"በፍላጎት አራት ቋንቋ መርጦ የተማረ እና እንዲማር የተጫነበት ተማሪ እኩል ውጤታማ አይሆንም። እንዲመርጡ የሚያስችል ሁኔታ ግን በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ የለም" ብለዋል።
 
በመሆኑም ተማሪዎች እንዲሁም ወላጆቻቸው በዚህ ላይ የመወሰን መብት ሊኖራቸው እንደሚገባ ባለሙያዎቹ ያስረግጣሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከቋንቋ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውዝግብ ተነስቶ እንደነበር አይዘነጋም።
 
• ተጨማሪ የአገር ውስጥ ቋንቋዎችን መማር ለምን?
 
በበርካታ አገራት በአብዛኛው የአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ ብሔራዊ ቋንቋ እና አንድ የውጭ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ይሰጣሉ።
ሆኖም እንደየ ትምህርት ቤቱ ዓይነት ሌሎች የውጭ ቋንቋዎችም የሚሰጡበት ሁኔታ ይኖራል። በኢትዮጵያ በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የውጭ ቋንቋዎችን ጨምሮ ከአራት በላይ ቋንቋዎች ይሰጣሉ።
 
በትምህርት ቤቶች የሚሰጡ ቋንቋዎችም እንደየክልሎቹ የተለያየ ነው። የአፍ መፍቻቸው አማርኛ ያልሆነ ክልሎች የአፍ መፍቻ ቋንቋን፣ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ [አማርኛ] እና እንግሊዝኛ ቋንቋን በመደበኛነት ይማራሉ። የአፍ መፍቻቸው አማርኛ የሆኑ ክልሎች ደግሞ የአፍ መፍቻቸውን እና አንድ የውጭ ቋንቋን [እንግሊዝኛ] ብቻ ነው የሚማሩት።
 
ከዚህም ባሻገር ክልሎች ወጥ እና ተመሳሳይ የሆነ የሥራ ቋንቋ የላቸውም። ይህም ዜጎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ በመሄድ እንዳይሠሩ እና ሕይወታቸውን እንዳይመሩ እንቅፋት ሆኗል።
 
ይህ አገሪቷ ካላት ሕገ መንግሥት እና ከምትከተለው ፖለቲካ ጋር የሚገናኝ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ የሚያዝ ሲሆን፣ ክልሎችም የየራሳቸው የሥራ ቋንቋ እንዲኖራቸው ይፈቅዳል።
 
ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው ወሳኝ እንደሆነ የሚገልጹት መምህር በድሉ፣ ሆኖም የየክልሎች የሥራ ቋንቋ መለያየቱ ክልሎች ከሦስት በላይ ቋንቋዎችን እንዲያስተምሩ አስገድዷል ብለዋል።
 
ከዚህም ባሻገር አንድ የጋራ ብሔራዊ የሥራ ቋንቋ ባለመኖሩ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ተንቀሳቅሰው ሥራ እንዳይሰሩ እንዳደረገ ገልጸዋል።
 
በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረትም ተጎጂ የሚሆኑት የአማርኛ ቋንቋ የአፍ መፍቻቸው እና የሥራ ቋንቋ የሆነባቸው ክልሎች መሆናቸውን አመልክተዋል።
 
በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ካልተሻሻለ በስተቀር አሁን ባለው ሕገ መንግሥት የአማራ ክልል ከግእዝ ይልቅ ብዙ ተናጋሪ ያላቸውን የአገር ውስጥ ቋንቋዎችን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ማካተት ነው የሚበጀው ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
 
በመሆኑም "ተማሪዎች ከቤተሰባቸው ጋር ተማክረው ለወደፊት ሕይወታቸው የሚጠቅማቸውን ቋንቋ መርጠው መማር አለባቸው" ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።
 
ግእዝ ቋንቋ ከዓለማችን ጥንታዊ ቋንቋዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለሚነገሩ በርካታ ቋንቋዎች መሠረት ነው።
በግእዝ ቋንቋ ከጥንታዊው ዘመን አንስቶ በተለያዩ የዕውቀት ዘርፎች የተዘጋጁ ጽሑፎች እና ዕውቀቶች ያሉ ሲሆን፣ በበርካታ የዓለማችን ዩኒቨስቲዎች እና የምርምር ተቋማት ውስጥ ይገኛሉ።
 
ከጊዜ ወደ ጊዜ የቋንቋው ተናጋሪዎች ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱ ቋንቋው በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ የተገደበ ሆኗል።"

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?