#የጨመተው ደቡብ እና ስኬቱ። • እቴጌ ጎንደር ሆይ! ከዚህ የብልህነት #ልዕልና ምን ተማርሽ?
#ምዕራፍ ፲፯
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።




በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ክስተታዊ ውሳኔ የወሰነ የፖለቲካ ኢሊት የሚገኝበት የደቡብ ክልል ነው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚር አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ብዙወቹ ቁምጥ የሚሉለትን የ፬ ኪሎ የክብር፤ የማዕረግ ሥልጣን፤ የጠቅላይ ሚኒስተርነትን ቦታ በፈቃዳቸው የለቀቁ ታላቅ ሰው ናቸው።
የተከበሩ አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ ለትውልዱ የፖለቲካ ሥልጣን ማለት ከህዝብ ፍላጎት በላይ እንዳልሆነ ተቋም፤ ሐዋርያ ሆነው በተግባር አሳይተዋል። አብነትም ናቸው። በዘመናቸው ለአጎደለቱ፤ ለጠቀሙት ጉዳይ ዘመን የሚፈታው አመክንዮ ነው። እኔ እራሴ ብርቱ ሞጋቻቸው ነበርኩኝ። አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መልቀቃቸ ግን የሚያሸልም የልዩ የታሪክ ክስተት መሥራች ናቸው።
#የደቡብ ህዝብ።
የደቡብ ህዝብ ለስላሳ ህዝብ ይመስለኛል። የደቡብ ህዝብ የማይቸኩል ዝግ ያለም ይመስለኛል። የደቡብ ህዝብ ያስተዋለም ይመስለኛል። የደቡብ ህዝብ #ዕድሉን #የማያፈስ ይመስለኛል። ይመስለኛል እምለው ኑሬ ስላላየሁት፤ በጥናትም መረጃውን በዳታ ሰለአላቀነባበርኩት ነው። በኮርስ፤ በሥራ ዓለም ግን ደቡቦችን በተወሰነ ደረጃ አውቃቸዋለሁኝ። ለዚህም ነው #የጨመተ የሚለውን ኃይለ ቃል የተጠቀምኩት።
የደቡብ ህዝብ ኢሊቶች ህዝባቸውን #በመገበር አይታወቁም። የደቡብ ህዝብ የፖለቲካ ኢሊቶች የህዝባቸው የውስጥ ሰላም እንዲታወክ አይፈቅዱም። ይልቁንም መሻታቸውን፤ የትግል ፍላጎታቸውን ይዘው ምቹ ድልዳል ወደ አለው ጠጋ ብለው ሲያቀናጁ፤ ሲያስተባብሩ አስተውያለሁኝ። በዛም በሌላው ወገን በተለይ አባ ቅንዬ በአማራ ሰፊ የህዝብ ተቀባይነት ያገኙ ሊቃናት ደቡብ አላቸው።
ይህ ብልህነት የደቡብ ህዝብ ከአለው ሥርዓት ተግባብቶ፤ ተስማምቶ መኖሩን እንዲያሰለጥን አግዞታል - እረድቶታል። ሌላው ግን የግንባር ሥጋ ሆኖ ተማግዷል። ዕድሉ፤ ዕድሜው፤ የወጣትነት ዘመኑ ለካቴና፤ ለስደት ከዚህም በከፋ የመጨረሻውን መራራ ሞት ተቀብሏል።
የደቡብ ህዝብ ሊቃናት ሁልጊዜ ወደ አትራፊው ጎዳና ያቀናሉ። ለዚህ ነው ጉዟቸው በትርፍ ላይ ትርፍን የሚያሰብለው። ሌላው ቀርቶ በዘመነ ህወት የክልል ዕሳቤ የደቡብ ህዝብ የሥራ ቋንቋ #አማርኛ እንዲሆን መወሰኑ ለየትኛውም ዘመን የልጆቹ ሊቅነት ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ እንቅፋት አልሆነበትም። ዛሬ ቤተመንግሥቱን በሙሉ በማዕከልነት በቁልፍ ኃላፊነት እንዲመሩ ዕድሉን ሲያገኙ አልተቸገሩም። እራሱ የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ የአውሮፕላን ትኬት የመቁረጥ ያህል ነበር። የነገረ ወልቃይትን ጥያቄ የመፍትሄ የውሳኔ ሂደት ከዚህ አንፃር ስናስበው ሰማይ ደጅ ምስጋን ይንሳው።
#ዕድል አብዝታ የመረቀችው ደቡብሻ።
ዕድሉ ሲገኝ የተማሩ፤ የበቁ፤ በሰዓቱ አግብተው የወለዱ፤ የከበዱ ሊቃናት ልጆቹ በተገባው ቦታ የተገባውን ክብር እና ሞገስ እንዲህ ያገኛሉ። በዘመነ ህወሃትም እስከ ጠቅላይ ሚር ደረጃ መድረስ ፍፁም ልዩ ዕድል ነበር። ሌላው ቀርቶ ከተፎካካሪወች ሊቃናት ሰብዕና ስናስተውል ነፍሳቸውን ይማረው እና ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በተደጋጋሚ አግኝቼ ሳነጋግራቸው ገረጭራጫ መንፈስ አላይባቸውም ነበር። ለህወሃትም ጠንከር ያለ ቁጣ ያለበት ንቅናቄ ሲያደርጉ አላየሁም። በአካል ሳገኛቸው ብዙ ጊዜ ሴት የፖለቲካ #ኢሊቶችን ወደፊት በማምጣት እረገድ ነበር እኔ እምሞግታቸው።
በሌላ በኩል ዛሬ ካሉት ተፎካካሪወችም ውስጥ ዶር ራሄል ባፌ ፈልጌ የማደምጣቸው ብቁ ሊቂ ናቸው። ደቡቦች የልጆቻቸውን #የትምህርት ጊዜያቸው በምንም ሁኔታ አይስተጓጎልም። ደቡቦች #የትዳር ጊዜያቸው አይሰናከልም። በሰዓቱ ያገባሉ። በሰዓቱ ዘር ይተካሉ። ደቡቦች በኢትዮጵያ የሚገኙ በረከቶች ሁሉ አያልፋቸውም። ሰላማዊ እና የጨመቱ ናቸው። በማስተዋል ነው የሚራመዱት። ዕድገቱ፤ ሽልማቱ፤ የውጭ የትምህርት ዕድሉ ሁሉ ለደቡብ ይተማል። ለምን???? በበዛ እና #በበቃ ሁኔታ ስክነት አላቸው ሊቃናቶቻቸው።
ሊቃናቶቻቸው በሚሳተፋባቸው መድረኮች ሁሉ ህዝባቸውን #ለባሩድ አይማግዱም። በዕታቸውን የዱር ቤቴ የከፋኝ መናህሪያ አያደርጉም። ባድማቸው ላይ የማን ደም ፈሰሰ ግብግብ እንዲኖር ፈጽሞ አይፈቅዱም። በዘመናቸው የሚመጡ የፖለቲካ መሻቶችን ለማስገኘት የመታገያ ማሳቸው #አዲስ አበባ ወይ ስሜን ኢትዮጵያ ነው። ይህ የላቀ ብልህነት እንሆ በየዘመኑ የደቡቦች በዓት መኖር ሰልጥኖ፤ ስጋት የነጠፈበት፤ ፍርሃት የመነነበት፤ ጭንቀት በሌለበት ሁኔታ ልጆቻቸው #ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። ይህ ጤንነትን ለሥነ ልቦና የመለገሥ ጥበብ ነው። ደቡቦች በልጅነት የሚኖሩ የጨዋታ ጊዜያቸውን፤ የወጣትነት ወቅቶቻቸውን ሳያሳልፋ ይጠቀሙበታል። በደቡቦች ዘንድ ከዕድሜ ጋር ትልልፍ የለም። ለየሥርዓቱ የታማኝነት ሁነትን ያሳያሉ።
እኔ የማስታውሰው #የልጅነት ጊዜ የለም። እኔ የማስታውሰው #ሰላማዊ የወጣትነት ጊዜ የለም። ታላቅ እህቴም እንዲሁ። ታናናሾቼም እንዲሁም። የእኛ ዘመን ላይበቃ ለማይታወቅ ሰብዕና፤ አንድ ቀን ህወሃት መንበሩን ከመልቀቁ በፊት ያን አሳርኛ በአት ልይህ ያላለ፤ ዛሬም የጎንደር ወጣት፤ የጎንደር መኖር፤ የጎንደር ሥልጣኔ እንደ ጉም ሽንት ወደ ኋላ እንዲጎተት ተደርጓል።
የህወሃትን ፈቅዶ መንበረ ሥልጣኑን መልቀቅ ለስኬቱ #በጥገኝነት ሳይሆን #በአማጭነት በጨመተ የተግባር ጥበብ ጎንደር የጎላ የጎለበተ ተግባር ከውናለች። ሚስጢሩን የተረጎመው የላይኛው ነው። ማንም ተመራምሮ ሊደርስበት አይችልም የእግዚአብሄርን የአላህን ውሳኔ። ግን ያን ዕድል ግን የማስቀጠል ጥበብ ጠፍቶ ዛሬም የእቴጌ ጎንደር ልጆቿ ለስደት፤ ለስጋት፤ ለመታፈን፤ ለመታገት፤ ለመሳደድ፤ ለመገለል ተዳርገዋል።
ወደፊትም ከፋኝ ያለው ሁሉ አቅም ቢያጣ የሚተመው ወደ #ጎንደር ይሆናል። ጠብቁት። ሁልጊዜ ጎንደር በሞኝ ክንድ ዘንዶ ይለካበትን በድርጊት የፖለቲካ ኢሊቶቿ ይተረጉሙበታል። ከህወሃት እና ከፋድራሉ ጦርነት ውድመት ዳነች ሲባል በራስ ክብሪት ማቅ ለበሰች። ጸጥታዋ ደፈረሰ። በባዕቷ ከ80 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ነበር። የስሜን ቃጠሎም አይረሳም። ያ ላይበቃ የሽምቅ እና የኮንቤንሽናል ውጊያ በዛች የሁሉ ቤተ ማዕድ ተከናወነ። ማህጸንን እንደ ዱባ ይቀረድዳል። የፖለቲካ ኢሊት ልጆቿ ሁልጊዜ ቁልቁል።
እቴጌ ጎንደር በእናትነቷ በድካሟ ልክ ቀርቶባት መብጠልከሏ ተግ ቢል በማን ዕድል???? " ስኳድ " ትርጉሙን ባላውቀውም የሚል ቅጥል እሰማለሁኝ። ሁለት ያጣ ጎመን። የጎንደር የፖለቲካ ሊቃናት ካላችሁ ነገንስ እንደምን ህዝባችሁን #ከመገበር፤ #ከአንጋችነት አድናችሁ ወደ ቀደመው ሰላሟ እና የጸጥታ የሱባኤ ጊዜዋ ልትመልሷት እንደምትችሉ እሰቡበት። እሰቡበት። ህወሃትን መናፈቃችሁ እራሱ እየገረመኝ ነው። በጣም።
ከጨመተው፤ ከሰከነው ከደቡብ ህዝብ የፖለቲካ ሊቃናት አያያዝ እና አመራር መማር ብልህነት ነው። ምን አልባት የወደፊቱ ጠቅላይ ሚር ደቡብ ይሆናል ብዬ አስባለሁኝ። ሰላሞች ናቸውና። ደቡብ ለፖለቲካ መሻት የሚያዋጣው እና የሚያገኜው ስኬት መመዘን አይቻልም። ፈጽሞም አይመጣጠንም። #አትራፊ ናቸው። ሁሉም ይቅር ልጆቻቸው በሰላም ወደ ትምህርት ቤት ሄደው መመለስ፤ የጠበንጃ #ሩምታ አለመስማት ገነትነት ነው። መታደልም። መመረቅም ነው።
የፓርላማ አፈ ጉባኤ፤ ቁልፍ ደህንነት፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር፤ የጠቅላይ ሚር ቢሮ የጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ የባንክ ገዢ፤ የመንግሥት ተጠሪ፤ የትምህርት ሚር፤ የሥራ ክህሎት ሚር ይህ ሁሉ ቁልፍ ቦታ የጨመተው የደቡብ ሊቃናት ነው። ሌላም ይኖራል። በታማኝነት ስለሚያገለግሉ የሚነፈጋቸው አይኖርም። ለሥልጣን ግፊያ እና ግብግብ ብዙም ፍቅር ያላቸው አይመስለኝም አብዛኞቹ የደቡብ ሊቃናት። በብልጽግናው መዋቅርም ከመንግሥቱ መዋቅር በበለጠ ደቡቦች እንደሚኖሩ አስባለሁኝ።
ከትምህርት ሚኒስተር በስተቀረ ባሳለፍናቸው መራራ የመገበር የትግል ዘመን መስዋዕትነቱን እና ስኬቱን ስትመዝኑት ለማነፃፀር አይቻልም። ዛሬም መገበር አለ በአማራ፤ በኦሮሞ፤ በትግራዋይ። ከብልህነት ጋር ትልልፍ ስለተሆነ። ነገም ቆራጥ፤ ብልህ የአባቶቻችን ዊዝደም ያልራቃቸው ሊቃናት ስስነት ጎንደር ለአዲሱ ተስፈኛ የከፋኝ #አንጋችነት ትታጫለች። ጎደለ ለምንለው ነገር ሁሉ በጸጥታ፤ ሰላማዊ በሆነ መልኩ በሃሳብ፤ በአመክንዮ በመከባበር መሞገት ይቻላል ብልጽግናን። ትውልድ ግን ሊገበር ለአፈሙዝ አይገባም።
ፈጽሞ።
ለዛውም ነገ ለማን ምን ላሳካው? ምን ክህሎት ላለው? ምን ሊያስተርፍ????? የሚለው ግልጽ መልስ ሳይኖር ልጅን፤ ዕውቀትን፤ ጊዜን፤ ጸጥታን መገበር???? የብልህነት ጎዳና አይመስለኝም።
ግን ግን ------------------------------------ሁልጊዜ #ማገዶነት አይሰለቻችሁንም ጎንደሮች? አንዲት የሳቅ ቀን ጥምቀት ተቀንቶበት ድፍንፍን ነው ያለው እኮ። ይህ አያርመጠምጥምን?? ስኩን ያስተዋለ ተተኪ ማፍራት በዚህ አያያዝ አይቻልም። ፈጽሞ። የትምህርት ውጤት በረጅም ጊዜ ነው የሚታየው። በአንድም በሌላም ሙሉ ፯ ዓመታት ትምህርት ሰላሙን አላገኜም። #ልሙጥነትን መናፈቅ ምን የሚሉት ማንስ ይሰኝ? ሥም የለሽ ዕዳ።
ደቡብ ትናንትም የጨመተ። ዛሬም የጨመተ። ፍላጎቱን ከጠየቀው በላይ 150% ያሟላ። በመስዋዕትነት ህዝቡን እና መንፈሱን የማያውክ፤ የተረጋጋ ሊቃናት መኖር ወላጆች የልጆቻቸውን ሰብል በጸጥታ እንዲህ --- ይኮመኩማሉ። የታደሉ። አንድ ሰው ብቻ ነው የሚበልጣቸው። በሁሉም ቁልፍ ፖዝሽን ደቡቦች ተመስጥረውበታል። ዊዝደም የመራው መሻት እንዲህ ይሳካል። በእነሱ ሥር ባሉ መዋቅሮች ሁሉ ቀረቤታቸውን ያረጋግጣሉ። ይህ ደግሞ ሌላው የትርፍ መሰላል ነው። እነሱን እያዩ የሚማሩት ልጆች ነገን የሚሰናዱበት ድልድይም እንዲህ በሰመረ ሁኔታ ተዘርግቷል።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
16/09/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ