የኢትዮጵያ ሴቶችን የደህንነት ዋስትና የሚያስጠብቅ ክብራቸውን የሚያስጠብቅ #አዲስ #ህግ #በእናት #ሥም ለኖረችው ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል።

 

የኢትዮጵያ ሴቶችን የደህንነት ዋስትና የሚያስጠብቅ ክብራቸውን የሚያስጠብቅ #አዲስ #ህግ #በእናት #ሥም ለኖረችው ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል።
 
የመጀመሪያዋ #ትምህርት ቤት እናት ናት።
የመጀመሪያዋ የፊደል ገበታም እናት ናት። 
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን። 
 
 May be an image of child
 
ምዕራፍ ፲፯
 
እንዴት ሰነበታችሁ የቅንነት ክብረቶች? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ። የኢትዮጵያ ሴቶች የኢትዮጵያዊነት ጽንሰ ሃሳብ ከተጸነሰ ጀምሮ የጎላውን ድርብ ድርሻ የተወጡ ጀግና የማህበረሰብ አካሎች ናቸው። በዲፕሎማሲው ዘርፍም ቀደምት ናቸው። በአገር መሪነትም መቅድም ናቸው።
 
የሆነ ሆኖ የሴቶች እናትነት ጸጋ ለማናቸውም ችግር የመፍቻ ቁልፍ ነው። ይህ ደግሞ ሰው - ሰራሽ፤ ጊዜ - ሠራሽ፤ ሥልጣን - ሠራሽ፤ ስልጣኔ - ሠራሽ፤ ዘመን - ሠራሽ ጉዳይ አይደለም። በፈጣሪ አምላካቸው/ በአላሃቸው ተባርኮ እና ተቀድሶ የተሰጣቸው ሰማያዊ ምርቃታቸው ነው።
 
የእናቶች ምርቃታቸው እንከን የለሽ ነው። ምርቃታቸው ጊዜ የማይሽረው ዘመን የማያወይበው ነው። ሴቶች አገቡም // አላገቡም፤ ወለዱም // አልወለደሙ ሴቶች የተፈጠሩበት ታላቅ ሚስጢር #እናትነት ነው። እናታዊነት ከእነ ሙሉ ጸጋው በእያንዳንዷ አንስት ውስጥ ተለብጦ ሳይሆን ተዋህዶ ማንነቷን አብርቶ እና አፍክቶ እንዲገኝ የሚያደርግ ንጥረ ነገር ነው። የሴቶች የማንነት ገላጭ ምስክራቸው እናታዊ ጸጋቸው ነው። 
 
* እናታዊነት ርህርህና ነው።
** እናታዊነት አዛኝነት ነው።
*** እናታዊነት አጽናኝነት ነው።
**** እናታዊነት አይዟችሁባይነት ነው።
***** እናታዊነት ቅንነት ነው።
****** እናታዊነት ኃላፊነት እና ተጠያቂነትን በህብራዊነት አስማምቶ የሚተረጉም የመኖር ዊዝደም ነው።
*******እናታዊነት የመኖር ማሰልጠኛ ረቂቄ ተቋም ነው።
******** እናታዊነት የማህበራዊነት ፍልስፍና ማክዳ ነው። የማህበራዊነት መሥራቾችም መሪወችም ሴቶች ናቸው።
 
#በእናታዊነት ውስጥ ……
 
እህታዊነት፤
ሚስታዊነት፤
አክስታዊነት፤
ጓደኛዊነት፤
አማካሪያዊነት፤
መሪነት፤
አስታራቂያዊነት፤
አስማሚያዊነት፤
አዋህጂነት፤
አቀራራቢነት፤
አደራጅነት፤
መጋቢነት፤
ናፍቆታዊነት፤
ተፈጥሯዊነት፤
ተስፋዊነት።
ሰዋዊነት፤
ወላዊነት፤
መቀራረቢያዊነት፤
ውባዊነት፤
መልካማዊነት፤
አብነታዊነት፤
ለችግር ደራሽነት ወዘተ በአንድም በሌላም በገኃድም ይሁን ተመስጥረው ጊዜ ሲሰጣቸው ወይንም አጋጣሚውን ሲያገኙ ተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉ የእናትነት ዕንቁ የመዋለ መንፈስ #ዕምቅ ሃብታት ናቸው።
 
በእስልምና እምነትም ይሁን በክርስትና እምነት ከሴትነት ብቻ የሚገኘው እናታዊነት የምሥራች ነጋሪነትም ነው። ብሥራት የተበሰረው በግራ ቀኙ ሃይማኖት በአንስት ቅዱሳን ነው። እናትነት መልካም #ዜናዊነት ነውና። ለዚህ ፀጋ እና በረከት የተገባው ክብር በልኩ መስጠት የማህበረሰቡ ግዴታ ቢሆንም ሥልጣን ላይ የሚገኝ መንግሥት ግን ከሁሉም የላቀ ተጠያቂነት እና ኃላፊነት አለው።
 
እኔ በደረስኩበት ዘመን ሴቶችን በሚመለከት፤ ከሴትነት የሚገኘውን እናታዊነት በሚመለከት ብልጭ ድርግም የሚል ተስፋ ቢታይም አጥጋቢ እና ዘላቂ የመሆን አቅሙ ግን ሽብሽብ ነው። ዕድለኛ ነኝ እና እኔ በሴት አደራጅነትም ሠርቻለሁኝ። የሴት አደራጅነቴን ዕውቀት ለማሻሻል ሴቶች ምን ይላሉ የሚል ጥናትም አሰርቼ ነበር። 
 
ሴቶች #መምህርም ናቸው። እናትነት የሚገኜው ሁልጊዜ በምግባር እና በግብረገብነት ውስጥ ነው። እኔ እንኳንስ ሰውን በአካል አግኝቼ ቀርቶ፤ ፎቶ ለእኔ ብዙ የውስጥነት ጉዳዮችን የምመራመርበት ተቋሜ ነው። እንኳንስ የሰው የጉም ፔንቲንግ። የጭስ ፔንቲንግ። የነበልባል ፔንቲንግ በተደሞ የምመሰጣባቸው ቁምነገሮቼ ናቸው።
 
ሴቶችን፤ እናቶችን በአገኜሁ፤ በአየሁ ቁጥር ብዙ በጣም ብዙ ጥልቅ ቁምነገሮችን ከሴቶች ተምሬያለሁኝ። ይህ የዕውቀት ዘርፍ መንደራዊ አይደለም፤ በሥራ አርሲ ክፍለ አገር ጢቾ አውራጃን አሰላን ጨምሮ፤ በጉብኝት ጎጃም ክፍለ አገርን፤ ሽዋ ክፍለአገርን፤ ኢሊባቡር በግል፤ ለሥልጠና በተላኩበት አዲስ አበባም ለእናታዊነት ውስጤ ያለው ቃና ልዩ ነውና የእናቶች የተፈጥሮን ጠረን ከውስጤ ለማድመጥ ዕድሉን አግኝቻለሁኝ። 
 
ሴቶች ከድምፃቸው ጀምሮ ያላቸው ጸጋ በራሱ ለእኔ እንደ አንድ #የዕውቀት ዘርፍ የምወስደው ፒላራዊ ጉዳዬ ነው። እናታዊነት በራሱ የላቀ የዕውቀት ዘርፍ ነው ለእኔ። ሊማሩት የሚገባ የምርምር ማዕከልም መሆን የሚችል ተፈጥሯዊ ተቋም ነው።
 
ለዚህም ነው ዛሬ ይህን ጹሁፍ እንድጽፍ የተነሳሳሁበት ምክንያት። ድምጼን ከፍ አድርጌ ለድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ ሴቶች መጮሄ፤ መታገሌ ያስገኜው ነገር ቢኖር በዘመነ አብይዝም በርከት ያሉ የሴት ሊቃናት የፖለቲካ ውክልና ማግኜታቸው ነው። 
 
ይህም በሃይማኖት፤ በዕውቀት፤ ይሁን በዞግ ስብጥሩ ሲታይ ስለመመጣጠኑ ዳታ ስላልሠራሁበት ይሄ ነው ያ ነው ለማለት አልደፍርም። በርከትከት ብለው የማያቸው ጉዳዮች ግን አሉ። አንዱ በአንዱ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ጥንቃቄ ቢደረግበት መልካም ነው።
 
ቀደም ባለው ጊዜ ለዚህ ዕድል የተበቃበት አመክንዮ የኢትዮጵያ ሴቶች ዕንባ መበራከት መንስኤው የወይዘሮ ታደሉ ልጅቸው ተገድሎ፤ በሬሳው ላይ እናቱ ተቀምጠው መደብደባቸው፤ በአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ በጎጃም እና በጎንደር የነበረው አሰቃቂ ኢሰብዓዊ ድርጊት፤ በሬቻ በዓል አከባበር የደረሰው ዘግናኝ ጭፍጨፋ የኢትዮጵያ ሴቶች የፖለቲካ ሊቃናት የፖለቲካ ውክልናቸው #ስስነት እንደሆነ በብዙ፤ በጣም በብዙ አምንበት ስለነበር ሞግቼበታለሁኝ። 
 
ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው እግዚአብሄር ይመስገን እንዳልል የፈለግሁት የኢትዮጵያ ሴቶች ክብር በልኩ አላገኜሁም። ይልቁንም የተረዳሁት ቁምነገር ሴቶች ወደ ፖለቲካ ውክልና መምጣታቸው ሥር የሰደደውን የኢትዮጵያ ሴቶች ችግር ሊያስወግድ ቀርቶ የጭካኔ #ማዕበል ነው እኔ እያዬሁ እና እያደመጥኩ የምገኜው። በመፈናቀል ውስጥ፤ በጦርነት ውስጥ፤ በፖለቲካ ፋክክር ውስጥ በርደኑን የተሸከሙት ከህፃናት ሴቶች ጀምሮ ያሉ የፆታ አጋሮቼ ናቸው። 
 
በዚህ በከፋው ዘመኔ በሂደቱ ሁሉ የማደምጠው እና የማየው በህፃናት - ሴቶች፤ በታዳጊ - ሴቶች፤ በወጣት - ሴቶች ላይ የሚደርሰው መከራ እጅግ የሚያንገፈግፍ ነው። በአብይዝም ካቢኔ ውስጥ በቂ የሴት ሚኒስተራት አሉ። 
 
በምክትል ሚኒስተር ደረጃም እንዲሁ፤ በአንባሳደርነትም፤ በፓርላማው፤ በፌድሬሽን ምክርቤት፤ በፍትህ አካሉ፤ በየመምሪያው ሳይቀር ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡ ብዙ ሴቶችን አያለሁኝ። 
 
……… ግን አንዳቸውም በሴቶች ላይ ያለው የዘመን ልበለው የምን በእናትነት ላይ ያለው የጭካኔ ሁኔታ መፍትሄ ያገኝ ዘንድ ሲታገሉ እና ሲያታግሉ ፈጽሞ አይቼ አላውቅም። ቦታውን እንዲያገኙ የታገልኩት እኔ ለእነሱ የሞድ ትዕይንት አልነበረም። 
 
ቢያንስ ይህ በሴቶች ላይ የሚደርሰው #ደመከልብነት እንደምን አይቆጭም? በማንም ይፈጸም በማን፤ በየትኛውም አካል ይፈጸም ጭካኔውን ሃራም ብሎ ማውገዝ ፊት ለፊት የተቀመጡት የሴት ባለሥልጣናት ተግባር ሊሆን ይገባ ነበር። 
 
የኢትዮጵያ ሴቶች የዛሬ ህፃናት የነገ - እናቶች፤ የዛሬ ታዳጊ ወጣቶች የነገ - እናቶች፤ የዛሬ ወጣቶች የነገ - እናቶች ናቸው። እናታዊነት ከማደጉ በፊት ከተቀጨ ነገን ማግኜት ጋዳ ነው። ሰርክ የሚደመጠው የሴቶች - መታገት፤ የሴቶች - መሰወር፤ የሴቶች - ግድያ፤ የሴቶች #መቀጣጫነት፤ የሴቶች በስጋት ተሸብበው መማር የሚችሉት ከትምህርት ይልቅ ጎዳናን፤ ወይንም በፆታ መተዳደርን መምረጥ ውስጣችን ሊያንገረግበን ይገባል። የማየው ግን ፍዝ ነገር ነው። ከጫፋም አልተደረሰም በእናታዊ ጸጋችን ስለ ዛሬም ይሁን ስለ ነገ የእናትነት ጉዞ ዕጣ ፈንታ። 
 
ሁሉም ፍቅረኛውን አቅፎ ሐሤቱን እየከሰከሰ፤ ሁሉም ሚስቱን አቅፎ እየተፍነሸነሸ ግንየነገ የትውልድ ሚስትም - እናትም፤ እህትም - አክስትም፤ አማካሪም - መሪም ሊሆኑ የሚችሉት እንደ ጥንቸል የመርዝ መፈተኛ የጭካኔ መሞከሪያ ጣቢያ ሲሆኑ ማድመጥ መለመዱ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ገብያ ማደማመቂያ #ኖራ መሆኑ ሊያንገበግበን ይገባ ነበር እንደ እዮራዊ ጸጋችን። 
 
#በመፃህፍቶቼ ላይ አበክሬ እንደገለጽኩት እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ ጥሪ ይዞ ይወለዳል።
#እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል።
#እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መልዕክት ይዞ ይወለዳል። ፓስተኛ ነው የሰው ልጅ በተፈጥሮው።
ይህ ፀጋ አደጋ ላይ ነው። 
 
አንድ ጆሮ ጉትቻ፤ ግማሽ ጸጉር ሹርባ ግንጥል ጌጥ ነው። ደህንነት የሌላት የጽንስ ኢንቢሬው ተሳክቶለት ቢፈጠር እንኳንጎድሎበት ነው። ስለ እናታዊነት መልካም ዜነ የለም። ነፍሰጡሯ እናት ጭንቅ እያደመጠች፤ ፍርሃትን ውጣ፤ ስጋትን ተጎንጭታ ነው ዘጠኝ ወሩ የሚጠናቀቀው። የሲቃው ቀን ደግሞ ጽንሱ ሴት ከሆነች ነው።
 
እናትነት፤ ሴትነት መቀጣጫ ሁኗል እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ። መረጃው ድፍርስ ነው። ዜናው በአውሎ የተናጠ ነው። የተጠቁ ሴቶች ጉዳይ ደመከልብ ነው። በዚህ ውስጥ ሁላችሁም እናታችሁን እሰቡ። ከሴት ያልተፈጠረ የለም እና። የሰው ልጅ ፍጹም አሰቃቂ ዜና ሲሰማ የአገሩ ልጅ ባይሆን /// ባትሆንም ዜናውን ሲሰማ ሰውነቱ ሊርድ ይገባ ነበር። ካለ ፈቃዱ ዕንባው ሊፈስ ይገባ ነበር። ግን እኛ #ተፍቀናል። ግን እኛ #ተፈቅፍቀናል። ያለን ይመስለናል እንጂ የለንም።
 
ለመራር ሃዘኑ የሚደረግለት የጭካኔ ማስያዥ በራሱ እኛ ማን ነን? ስለምንስ ተፈጠርን ብለን ሱባኤ ልንገባ በተገባ ነበር። ስፍስፍ ብሎ ማዘን ሊቀድም ይገባ ነበር። ማመሳከሪያ እያቀራረቡ ከተፈጥሮ ጋር ግብግብ ከመግጠም ይልቅ። እልሁ ቁጭቱ ሃፍረቱ ሰውኛ ባልሆን ፖለቲካችን ውስጥ ዙን የሙጥኝ ማለታችን ሸሽጉን ሊያስብል በተገባ ነበር።
 
አጋድሜ የምጽፈው በአንድም በሌላም ጭካኔን ስንደፍር ሁላችንም ጨካኝ መሆናችን አገናዝበነው ስለማናውቅ። ውግዘቱ ከእራስ ቢጀመር መልካም ነው እንደማለት። እራስን መመርመር፤ የቆሙበትን የሰብዕና ደረጃ መፈተሽ ከእያንዳንዳችን በግል፤ ከሁላችን በጋራ የሚጠበቅ ግዴታችን ይመስለኛል። ነቃፊው በሚነቅፈው ውስጥ እንኳን ሰው ዶሮ የሞተ አይመስለውም። እናሳዝናለን። በጣም። 
 
በዘመኑ ሥልጣን ላይ ያለው ብልጽግና ብቻ ሳይሆን የብልጽግና ፓርቲ ተጠማኙም፤ የብልጽግና ፓርቲ የነገ ውህደኛ፤ የብልጽግና ፓርቲ ለስላሳ ተፎካካሪ፤ የብልጽግና ፓርቲ ጽኑ ተቃዋሚ፤ ብልጽግናን በመሳሪያ የሚፋለሙትም ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እያንዳንዳችን በግል በአረማዊነት ድርጊት #ልናፍርበት ይገባል። 
 
ለዚህም ነው ቀደም ባለው ጊዜ ሁላችንም እንፈር ብየ አንድ አውዲዮ የሠራሁት። ማፈርን ከልብ መቀበል። ለማፈር ዕውቅና መስጠት። ከማፈር ጋር የማያገናኙ ሞራላዊ ንጹህተግባር ለመፈጸም መትጋት ይገባ ነበር። አልሆነም። 
 
#የኢትዮጵያ ሴቶች ለእኔ #ኢመርጀሲ ሩም ላይ እንዳሉ ይሰማኛል። 
 
ደቡብ፤ ሱማሌ ክልል የተሻለ ዕድል ቢኖርም ቤንሻንጉል ጉምዝ፤ አማራ፤ አፋር፤ ትግራይ ክልል፤ በስሱ መዲናዋን በተለያዬ ሁኔታ የማያቸውን ህፃናት ሴት ልጆች፤ ታዳጊ ሴት ልጆች፤ ወጣት ሴት ልጆች የነገ እርግጠኝነት ስለሌቸው ብቻየን ቤት ዘግቼ አለቅሳለሁኝ። አቅመቢስነት ይሰማኛል። ላድናቸው - አልችልም። ይህ ጉዳይ ብሄራዊ አጀንዳ ሆኖ ውይይት ሊካሄድበት ይገባ ነበር። ፌክ ያልሆነ ውይይት ችግሩን ፍርጥር አድርጎ ፊት ለፊት መነጋገር ይገባ ነበር።
 
ሥልጣን ላይ ባለው አቤቱ ብልጽግናም በሴቶች ጥቃት ላይ ቆፍጠን ያለ፤ የለበጣ ያልሆነም እርምጃ ሊወሰድ ይገባ ነበር። ሰሞኑን በአገረ እንግሊዝ በተፈጠረ የፆታ ትንኮሳ አንድ ኢትዮጵያዊ ታስሮ በመፈታቱ የለንደን ፖለቲካ እየታመሰ ነው። 
 
ይህን አስባችሁ የእኛን ኢትዮጵያን ስታስቡ መቼ የዚህ ሥልጣኔ ቤተኝነት ለመሆን እንደምንችል ይርቅባችኋል። እኔ ራቀኝ። ሰው የተፈጠረው ለሰውነት እንጂ ለአውሬነት ፈጽሞ አይደለም። እንደዛማ ባይሆን አፈጣጠራችን በፈጣሪ አምሳል ባልሆነ ነበር። 
 
«በዩኬ በወሲባዊ ጥቃት የተከሰሰው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ የ12 ወራት እስራት ተፈረደበት»
«የዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲከኞችን እያወዛገበ ያለው የኢትዮጵያዊው ስደተኛ ጉዳይ»
«በዩኬ በጾታዊ ትንኮሳ የተፈረደበት ኢትዮጵያዊ ስደተኛ 'በዚህ ሳምንት' ከአገር እንደሚባረር ተገለጸ»
 
///
 
የሆነ ሆኖ ሴቶች ፍጥረታቸው ጥበብ ነው። ለሴቶች ጥበባዊነትን የተሰጣቸው ነው ብየ አምናለሁኝ። ጥበቡ በብልህነት የተቀመረ ስለሆነ የመፍትሄ አንበሎች ናቸው ሴቶች። ጥበበኛ ሴቶች ግን - ጊዜ፤ ዘመን፤ የቆረጠ ሰዋዊ ሥርዓት እና ተቋም ሲያገኙ ብቻ ነው እራስ እግሩ በመፍትሄ ይበራ የነበረው።
 
ሴቶች ፈርተው ካደጉ ከተፈጥሯቸው ቁጥብነት + ከሃይማኖት ዶግማና ቀኖና + ከባህላዊ ሁነቶች ጋር ተጨማምሮ በራስ የመተማመን አቅማቸው ሊሰደድ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ጸጋቸውን በልኩ ለመፈጸም ይሳናቸዋል። ይህ በራሱ የትውልድን በረከት ተቀናቃኝ እና ፈታኝ ገጠመኝ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። አሁን በማየው ልክ የ10/15/ 20 ዓመታት ኢትዮጵያ ከጥበበኛ ሴት ልጆቿ ልታገኝ የምትችለው አቅም ተቀናቃኝ ሁነት እንደተጋረጠበት ይሰማኛል። ሚዛኑን የጠበቀ አገራዊ ሥርዓት አመጣጥኖ ለማስኬድ ግጥ የሆነ ዕጣ ፈንታ ሊገጥም ይችላል። 
 
በራስ መተማመን ዝቅ ባለ ቁጥር የማንነት ቀውስ ይመጣል። በየትኛውም የቀውስ ዓይነት ውስጥ የሚገኝ፤ የሚበረክት ክህሎት ደግሞ ሊኖር አይችልም። የትኛው ዓይነት ተፈጥሮ ማንነት አለው። ቀውስ ከገጠመው አዋኪ ይሆናል። በእናት አገር ኢትዮጵያ ጎልተው ከወጡት ችግሮች ዓይነታው እናት አልቦሽ ትውልድን የማሰብ ክሱ ዕይታ ነው።
 
 የጭካኔወችን ሂደት ልብ ብሎ ላስተዋለው መዳረሻው እናትነት በለጋው ካቀጨጨ ነገን ማግኜት አይቻልም። ፈጽሞ። ፈሪ ትውልድ እንኳንስ አደራን ሊያስቀጥል እራሱንም ለመምራት የተሳነው ይሆናል። 
 
ስለሆነም የሴቶችን መብት - ደህንነት - የዜግነት አቅም - የመኖር ነፃነት - የመተንፈስ አስቀጣይነት - የመኖር አስፈላጊነት በተለዬ ህግ እና ድንጋጌ እራሱን በቻለ ልዩ ህግ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል። እንደ አርጀንቲናውያን ማህበረሰባዊ ዕውቅና እና ተቀባይነት የሴቶች አቅም ባንታደል፤ እንደ አርመን ቢያንስ ለሴቶች የአፈጣጠራቸው ሁነትን ልዩ ጥበቃ ስለሚያስፈልግው ልዩ አትኩሮት ሊሰጠው ይገባል። የህግ ድጋፍ፤ የህግ ድልዳል ሊበጅለት ይገባል ባይ ነኝ። 
 
የኢትዮጵያ ሴቶች የየትኛውም የጭካኔ ዓይነት መሞከሪያ ጣቢያ ሊሆኑ አይገባም። እናትነት በዚህን ያህል ጭካኔ ሊቀጣ አይገባም። እናትነትን በጭካኔ በመቀጥቀጥ የምትቀጥል ኢትዮጵያን ማሰብ ዕብንነት ነው። ፍላጎትን ለማሳካት ይሁን፤ ምኞትን ለማግኜት በቀንበጦች የነፍስ ገብያ ሊሆን አይገባም። አገር ለማስቀጥል ከስንጥቋ አክርማ እስከ ገዘው ሞሰብ ማዕደኛውን ሁሉ አትኩሮት በጊዜው መስጠት ይገባል። የሴቶች ጉዳይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወጣ ገባ ነው አትኩሮቱ። 
 
የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተፈጥሮው ከስታሊኒዝም የተቀዳ ወይንም የተኮረጀ ስለሆነ ሩህሩህ አይደለም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰብዓዊ አይደለም። ከሰብአዊነት ጋር ግብግብ እንደገጠመም ነው። እርካታ የነሳውም ለዚህ ነው። ፖለቲካ ለሰው የተሠራ ሥርዓት ሆኖ የሰውን ተፈጥሮ የሚፈታተን ሆኖ ነው የሚታዬው። 
 
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሰው ልጅ ማገዶነት ዕውቅና የማይሰጥ ጊዜ የማያስተምረው ነው። ይህ ባህሉ ሄዶ ……… ሄዶ ዛሬ ከደረሰበት ተደርሷል። ሁልጊዜም እንደምለው ጭካኔን ጭካኔ አያድነውም፤ አንዱ ጭካኔ ሌላውን አይፈውሰውም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሴቶች ላደረግነው ሥፍር ቁጥር ለሌለው ተጋድሎ እና ተሳትፎ ሥጦታችን ይህ ሊሆን አይገባም ነበር። በሌላም በኩል ተመስጋኝም፤ ተከባሪም እኛ እንጂ ሌላ ሊሆን አይገባም ነበር። ማንም በችሮታ ምንም አድርጎልን አያውቅም ----- ና።
 
እንዲያውም አንገታችን ቀና አድርገን መኖራችን ረስተን ስንገበር ስንሳደድ ነው የኖርነው። ይህም ሆኖ በዘመኑ የሚደመጠው ግፍ ደግሞ እጅግ የሚመር የሚጎመዝዝም ነው። ለኢትዮጵውያን መላ ዜጎች በከሳሽ እና ተከሳሽ ሳይሆን የሚፈውሰን፤ ይልቁንም ልዩ ስጦታውን #እናትነት የተሰጠን ሚስጢር በልኩ አክብረን ለመያዝ ስንታደል ብቻ ነው ነገን ማግኘት የሚቻለው። በስተቀር ሥሩ እያረረ ላዩ የሚለመልም ተክል አይኖርም። አይደለም ቡቃያ ለማየት የጠወለገ፤ የጠነዘለ፤ የወየበ ቡቃያን ለማግኜት እንኳን በዚህ አያያዝ የሚቻል አይመስለኝም። 
 
ትልቁ መፍትሄ ግራ ቀኙን በአገር ውስጥ በመካሄድ ያሉ ጦርነቶችን ማስቆም፤ ለሌላ ጦርነትም ባጉም ባጉምን መግታት ያስፈልጋል። ህዝብ መኖሩ በመከራ ስለምን ይታጨቃል። ወገኖቻችን ድህነታቸውን በሰላም ታቅፈው እንዲኖሩ ለማድረግ እንኳን ለምን አይቻልም???
 
እኔ እንደማስበው ቅንነት - በድፍረት፤ ቀናነት - በኃላፊነት ስሜት ድርጊት ላይ መዋል ያስፈልጋል። እኩል ሊራመድ የሚገባው ጉዳይ የኢትዮጵያ ሴቶች፤ እናታዊነት ቀጣይ ተስፋን አስመልክቱ ተፈጥሯዊ ተከታታይ ውይይት በእጅጉ ያስፈልጋል። ከዚህ በላይ የህግ ልዩ ጥበቃ ለሴቶች ማድረግ እንዲቻል የተለየ የህግ ድንጋጌ ጥናታዊ ሂደቶችን መጀመር ያስፈልጋል። 
 
በዚህ ዙሪ በጣም ተዘግይቷል። የሚያሳዝነኝ አሁን ያለው የሴቶች ችግር ብሄራዊ ዕውቅና የለውም። ስለሆነም ለአጀንዳ አልበቃም። በፖለቲካ ድርጅቶች ስብሰባ ይህ አሳፋሪ፤ አሸማቃቂ ጭካኔ ውይይት አይካሄድበትም። እናት ተትታ ጉዞ ወደ የት???? 
 
#እርገት ይሁን። 
 
የሴቶች ጉዳዩ የሰሞናት የፖለቲካ ገብያ ማድመቂያ ይሆናል፤ ከዛ ይረሳል። ሌላ የሴቶች ግፍ ሲመጣ እንደ አዲስ አጀንዳ ይሆናል። ይህም ይረሳል። ዘላቂ መፍትሄ ለችግሩ ያስፈልጋል። ቋሚ የሆነ የህግ ድጋፍ ለችግሩ መፍቻ ያስፈልጋል። በየትኛው የፍትህ አደባባይ ህጉ ዕውን ሊሆን ይችላል የሚል ሙግት ሊኖር ይችላል። እንቁላል ሳይኖር ዶሮ አይታሰብም ይሆናል መልሴ። የኢትዮጵያ ሴቶች በሚደርስባቸው ጥቃት ዙሪያ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የእኔ ጉዳይ ነው እንዲለው የማድረግ ተግባር እስኪ ተደፍሮ ይጀመር።
 
የመንግሥት ይሁን የከፋኝ ታጣቂወች በሰብአዊነት ላይ ልል ያልሆነ ጥብቅ ሰብዕዊ ስልጠና ያስፈልጋቸዋል። የሰው ልጅ ህሊናው በተፈጠረው ልክ ለሰባዕዊነት ሊሆን ይገባል። ይህን ማስተማር ያስፈልጋል። በተከታታይ። ከቁንጮ ጀምሮ። ይበለው፤ ይቅመሰው፤ ያገኛታል፤ ጠብሰቅ አድርጋችሁ ቅጡልኝ ወዘተ የጭካኔ #ፋፋ ናቸው። 
 
ለተቃዋሚውም ሆነ ለገዢው የፖለቲካ ድርጅት ጭካኔ ዶግማ ሊሆን አይገባም። ይህ ከተደፈር ሰው ሳንሆን ወደ እንሰሳዊ ዓለም ተለውጠናል ማለት ነው። መደንገጥ ሊቀድም ሲገባ ትንታኔው ስለ ፖለቲካ ሴራ መሆኑን ሳይ ከሰውነት ጋር ተፈጥረን ምን ያህል ተራርቀን እንደኖርን እያስተዋልኩት ነው። የሚገርመው ደግሞ የንግግሩ ዘይቤ ጭካኔውን በፖለቲካ ሴራ እግረ ሙቅ አድርጎ የድምጸቱ ቃና ንዴቱ፤ ብስጭቱ ነው። እያንዳንዱ የሰው ልጅ እኔ ብሆን፤ የእኔ ልጅ ብትሆን፤ የእኔ እህት ብትሆን ብሎ ማሰብ እንዴት ያቅታል? የሰውነት ሚዛን ዘንበል ሳይሆን ረግረግ ላይ እንደሚገኝ ያመላክታል ህሊና ላለው የሰው ልጅ። 
 
ፎቶውን እያዬሁኝ ከውስጤ አዘንኩኝ። የመኖር ዋስትናቸውን አድራሻ ለመተንበይ አቅም ስለአነሰኝ። የእነኝህ ልጆች ነገ አድራሻ ቢስ ነው። ይህ ሊያሳስበን ይገባል። ይህ አጀንዳችን ሊሆን ይገባል። ይህ እራሳችን ልመዝንበት ይገባል። እኩል አናዝንም እንፈር አብረን።
በሰው ደረጃ እያለን መስሎን ከሆነ፤ የለንም። እናትነትን፤ እናታዊነትን፤ ሚስትነትን፤ አክስታዊነትን፤ እህታዊነትን በጭካኔ ማዕበል፤ በአረመኔነት ዓውሎ እየተናጠ እናት አለኝ እወዳታለሁኝ፤ ሚስት አለኝ እወዳታለሁኝ ማለት እራስን መካድ ነው። 
 
ሰሞኑን ብዙ በጣም ስብሰባወች አህጉራዊም ብሄራዊም አየሁኝ። በዚህ ሁሉ አቅም በፈሰሰበት ሜጋ ሂደቶችግን ቅንጣት አትኩሮት ስለ አስፈሪው የሴቶች ተስፋ ጭንቅ ላይ ስለመሆኑ ያዳመጥኩት የለም። ወጪው፤ ድካሙ፤ ደስታው፤ ፍሰሃው፤ ትርሲቱ፤ ፌስታው ሁሉ ተንሳኤው እናት አልቦሽ????? 
 
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀናእንሁን። አሜን።
 
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
 
ኑሩልኝ። አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
27/10/2025
 
ክብር ለኢትዮጵያ ሴቶች!
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።