#ወይ #ጢቾ? #የጢቾን የቀደመ ጥልቅ #ተፈጥሯዊነት #አቤቱ #የኦህዴድ #ሊቃናት #መልሱልን።
#ጠብታ። 

ከየት እንደምጀምር አልውቅም። እኔ ለምለሙን ጢቾ እማውቀዋለሁኝ። ጢቾሻን እኔ የማውቀው ግን በዚህ አሰቃቂ ግፍ እና ሰው ጠል በሆነ፤ መስቀልን ገፊ #የማፈናቀል ታሪክ አልነበረምና ከበጎው ከናፍቆቴ ልነሳ። በአሜሪካኖች ሃሙስ በእኛ አርብ ነበር አደባባይ ሚዲያ ካርታውን ሲያቀርብ ጢቾም እንዳለበት የተገነዘብኩት። ቀደም ብሎም ምስራቅ አርሲ የሚል ጉግል ላይ ፈልጌ በጉልህ ላገኜው አልቻልኩም።
በእኛ አርብ ዕለት ግን አደባባይ ሚዲያ በጉልህ ሲያወጣው ማህጸኔ እንደ ዱባ ነው የተቀረደደው። አደባባይ ሚዲያ ገረጭራጫ ሚዲያ አይደለም፤ በስሜት ግንፍል ግንፍል የሚልም ሁነትም በርክቶ አላይበትም። በቃላት አጠቃቀም፤ በቅደም ተከተል አመክንዮወች፤ ሃሳብን በልዩነት አቻችሎ በማስተናገድም #ስክነት ስለማይበት በመደበኛ እከታተለዋለሁኝ። የቲሙ የሃሳብ ፍልሚያም ለትውልድ የመቻቻል ቀጣይነት አቅጣጫ ጠቃሚ ይመስለኛል።
"የጊዜ ባለቤት" ብሎ አምላካችን አመስግኖ የሚጀምረው የመምህር አቤል ጋሹ በር ከፋች ቃለ ህይወትም ይናፍቀኛል። #ይጠራኛልም። ያው ልጅ ተክሌ እና እኔ ስንሟገት ነው የኖርነው፤ በቀረበበት ሚዲያ ሁሉ ናፍቄ አዳምጠዋለሁኝ። ቅንም ነው። አይሰስትም ትጉኃንን አጉልቶ ለማውጣት። ለኮሚኒቲውም ነፃ አገልጋይ ነው።
ባለቤት አልባ እስረኞችን ኢትዮጵያ ሲሄድ በአካል ያያል። ቀጠሮ ካላቸው በአካል ይገኛል። ሁነኛ #ተስፋዬ ነው። እኔ ኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኛ እንዲኖራት ፈጽሞ አልሻም እና ለእኔ በኽረ ጉዳዬ ነው። ቤተሰብ መስርቶ ለማየትም እናፍቃለሁኝ። በአደባባይ እሞግተዋለሁኝ፤ ግን ከውስጤ እንደ ታናሽ ወንድሜ ነው እማየው።
አደባባይ ሚዲያ በሳምንት አንድ ቀን ብቅ ይላል። ይህም ተመስገን ነው። በፊት የመስቀል ወፍ ነበር። አሁን ደግሞ ጥቃት መካች በፋክት ሆኗል ከሰኞ እስከ አርብ ይሰራል። ተመስገን።
#እናም።
አደባባይ ሚዲያ በቅኒት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጥቃት ዙሪያ የሠራውን ትጋቱን አሰባስቤ ሊንኩን ለጥፌያለሁኝ። ከመሆን መቻል ሃጂ፤ ሙፍቲ የክብር ሽኝት ጋር ጉዳዩን እኔ ስለማየው እሱንም አብሬ ፖስት አድርጌዋለሁኝ። የኢትዮጵያዊነት ሚስጢር ሲያብብ #የአሜባ በሽታ ለሚያንገላታቸው ወገኖቻችን ያ በመራራ ስንብቱ የታየው ልዩ አብሮነት መከፋትን ፈጥሯል ብየም አስባለሁኝ። ኢትዮጵያዊነት ግን ከመፈጠሩ በፊት አሸናፊ ነውና። አናባቢ ነውና። ይህን የመከራ ቀን ተሻግረን የምናይበት #ፏ ያለ ቀን ይመጣል።
#ነበር።
የሆነ ከአርሲ ወደ ጎንደር ለሥራ ይሁን ለትምህርት የአርሲ ልጆች ሲመጡ ክፍለ አገሩ #የእኛ ልጅ እዛ አለች ሰብለ ትባላለች ብለው ሙሉ አድራሻየን ሰጥተው ይልኳቸው ነበር። እንደመጡ ወገኖቼ ያገኙኛል። የተለመደው ቤተሰባዊ ግንኙነት ይቀጥላል።
ከኢትዮጵያ የቅኔው ጎጃም የማንኩሳ ኮክ እና ሙዙ፤ የገበሬ መንደሮች ውብ ጸዳል እና ጠረን፤ እና የአባይ ጉዞ ድልድዩ፤ ባህርዳር ጣና -- ቡሬ -- የገብሬ ጉራቻ ቅቅሉ፤ ከአሁኑ የጉራጌ ዞን ደግሜ ያልበላሁት ያ ገና ጥርስ ሳይነካው ሞከኬው ክትፎው እና ከጭልጋው የአዳኝ አገር የሴቶች የባህል ዕቃ አቀማመጥ ከጉራጌ የገበሬ መንደር ጋር መሰሉን ያገኜሁበት ሁነት፤ አሰላ ጭላሎ ተራራ፤ መላ ጢቾ ሮቤ፤ ጋሞ አርባ ምንጭ የአቶ በቀለ ሞላ አሳ ጥብስ፤ አዲስ አበባ እንጦጦ ኪዳነምህረት እና ምሽት ላይ ቸርቸል ጎዳና ዕትብቴ እንደተቀበረባት እንደ ጎንደሪና ይናፍቁኛል።
#እንዴት ሆነ?
በጣም በአጭር ጊዜ ዕድል ቀናኝ እና በብሄራዊም፤ በዓለም ዓቀፍም ደረጃ መድረክ አገኜሁኝ። ብዙ በጣም ብዙ ጠቃሚ ጉዳዮች ጋር ፈጣሪዬ አገናኜኝ እና መረጃወቼ ለሙ ወይንም አሰበሉ። የአገር ውስጥ ቆይታዬ እስር ቤቱ፤ ጫካው፤ የስደት ህይወቴ ግማዱ ሁሉ ለእኔ ዩንቨርስቲወቼ ናቸው። ጢቾን እማውቀው ለሥራ ከዛ ተመድቤ ነው። አርሲ ክፍለ አገር ከተማው አሰላ ነበር። ክፍለ አገሩ ሦስት አውራጃዋች ነበሩት። ጭላሉ፤ አርባጉጉ እና ጢቾ።
የጢቾ ቆይታዬ አጭር ነበር። ለ5 ወር ብቻ። ግን ጢቾ ዩንቨርስቲዬ ነበር። የብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ድህረ ገጽ እና ሙሉ ፲፯ ዓመቱን አጠናቆ መስከረም 18/2025 ወደ ፲፰ኛ ዓመቱ የተሸጋገረው የጸጋዬ ራዲዮ ምስረታ ገፊ ምክንያቱ የጢቾ ቤተሰባዊ ንጹህ ግንኙነት የፈጠረልኝ የአስተውሎት ልክ ነበር። 7ኛ መጸሐፌ የውጭ ሽፋኑ አርሲን ያጠይቃል። መልካምነት #እርሾ አለውና።
#ጢቾ ባለጸጋ ነው።
በአዕዝርት ይሁን በእንሰሳት ተዋፆ በረከት የተሰጠው፤ ሁሉን የተቸረውም። ኢትዮጵያ ውስጥ በርኒ አትክልት በዛ ዘመን የለም። የቀመስኩት ጢቾ ጠና ወረዳ ላይ ነበር። ጢቾ ሦስት ወረዳወች ነበሩት። አምኛ፤ ሴሩ እና ጠና። የቀረ ካለ እከሉበት። ዲክሲስ ትልቁ የመንግሥት እርሻ የነበረበት ነው። የአምኛን የእርሻ ዲካ መገመት አትችሉም።
ሴሩ ሞቃት ቢሆንም ማሩን አስታውሳለሁኝ። ጠና ላይ የማይረሱኝ ሁለት ነገሮች የእንጨቱ ድርጁነት ነው። እርጎውን በተመሳሳይ ጣዕሙ ያገኜሁት ጎንደር እስቴ አንድአቤት ላይ ነበር። ይወራረሳል በረከቱ። ስጦታው የአንድዬ ነውና። የአሪሲው የአምኛ የስንዴ ማሳ እና የጋይንቱ የስማዳ ማኛ ጤፍ አዕዝርትም አቻ ነው። የገብስ እሸቱም ከወገራ ጋር መሳ ለመሳ ነው። ወገራ በአብሽ ምርትም አንቱ ነው። ጎንደር ገብስ ብቻ ወደ አራት የሚጠጋ ዓይነት አለው። አለፋ ጣቁሳ ደግሞ የቅመማ ቅመም ንጉስ ነው። አሳም አይረሳም። ፍቅር ተደፋ እንጂ እኛ የምርቃት ጸጋ ነበረን። ሸምጋይም አጣን። ሁልጊዜ የነገር ፍላት። ረብ የማይል።
የሆነ ሆኖ ስንዴው የጢቾ እንደ አዲስ አበባም እንደ ጎንደርም አይደለም። ይለያል። አስፈጭቼ ዳቦ ስጋግረው ጣዕሙም ውበቱም ተለየብኝ። ለእሽታ ልዕልቴ ለእናቴ ለእብየ ሆዴ 20 ኪሎ ስንዴ ላኩላት። ሳላስፈጭ ዛላውን ጭምር እንድታየው፤ ዛላውን ጭምር ነበር የላኩላት። ከጢቾ ወደ ጎንደር ከተማ። ስታስፈጩት #አይልምም። ሽርክት ነው።
ገንፎውም ዳቦውም ልዩ ነው።ስለ ገንፎ ከአነሳሁኝ የጢቾ ገንፎ ከለመድነው ይለያል። ዳቦ ቆሎ ተገንፍቶ እሰቡት። በባለሙያ የተሰራ የካብ ትዕይንት ነው። እንዴት እንደሚያዘጋጁት አላውቅም።
ገብያ ላይ የ2.00 ብር አይብ ብትገዙ የ6.00ብር አይብ ይዛችሁ ቤታችሁ ትመለሳላችሁ። ልግስናው ደንበር የለውም። ጭኮ ጢቾ ላይ ቀረ። እኔ የበሶም የጢቾም ፍቅር የለኝም። ግን ጢቾ ላይ ጭኮ ሜሮን ነው። በልተን ደግሞ ከእነ ዕቃው ወደቤት እንወስደው ዘንድ ያስገድዱናል። ልምላሜው የእዝርት ብቻ ሳይሆን የሰብዕናም ነበር።
#ተዚች ላይ።
ሳልረሳው የጢቾ ገበሬ ምንም ላይገዛ፤ ምንም ላያቀና ለመረጃ ብቻ ፈረሱን ጭኖ ቅዳሜ ገብያ ይገኛል። ዓለም እንዴት ሰነበች የጢቾ #ራዲዮ ቅዳሜ ገብያ ነበር። ከገብያተኛው ፈረሱ ስለሚበዛ ምንድን ነው ብየ ስጠይቅ ነው የነገረኙ። ዜና ፍለጋ ነው የሚመጡት አሉኝ።
#ህወሃት ነፍስህን አይማረው እንደ ጋጥ ከልለህ ምድራችን ቀራንዮ አደረግካት።
ህወሃት ነፍስህን አይማረው ፈጣሪዬ። የዚህ ሁሉ ጠንቅ ጠንሳሽም፥ ፈፃሚም አስፈፃሚም አንተ ነህና ብንም፤ ትንም ያድርግህ ፈጣሪ አምላክ። የአሁኑ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕልቂትም የአንተ የእጅ ሥራ ነውና ፈጣሪ አምላክ አለኝ የምትለውን በረከትህን ሁሉ ፍርድ ይሰጥበት ዘንድ ጌታዬን፤ ንጉሤን እየሱስ ክርስቶስን እለምነዋለሁኝ። ምርቃትህ ሁሉ ሙጥጥ ብሎ ይነሳ ዘንድ ፈጣሪ ያድርገው። ዕድሜየን ሙሉ አንተን መታገሌም የተገባ ነው። በምንም ታዕምር መንበሬ ተመልሼ አራጥጬ እገዛለሁ፤ አዳዲስ መርዝም አበቅላለሁ ብለህ አትሰበው። አንተ የቀራንዮ ቅዱስ ትሩፋት መንጣሪ ነህና።
#እንዴት ልመን?
ያ ደግ የጢቾ ህዝብ (ምስራቅ አርሲ ተለጥፎበት)፤ ያ ትሁት ህዝብ፤ ያ በልቼ የጠገብኩ የማይመስለው - ህዝብ፤ ያ የተኛሁበት፤ የተቀመጥኩበት ተመቻት አልተመቻት ብሎ እራሱ ሞክሮ የሚያስቀምጠኝ ሆነ የሚያስተኛኝ ህዝብ ለሚወደው፤ ለሚያከብረው የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለሚተጋለት አዕዝርት እንዲህ ሲጨክን???? ካርታውን ሳይ ደነገጥኩኝ። ሰውነቴ ተንዘፈዘፈ። ተቀየረች ሲባል የሞትኩ ያህል ነበር የተለቀሰልኝ። ስትሳፈር አናይም ነበር ያሉት። ዜናው እንደ ተሰማ ሥራ የገባ አልነበረም። ገጠሩም ያውቀኛል። ሽልማቱ ጉድ ነበር። የባህ ዕቃወች ሁሉ እናቴ በህይወት እያለች ቤት ውስጥ በክብር ነበር።
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የአርሲ፤ የአሰላ የጭላሎ፤ የአርባጉጉ፤ የጢቾ ልጆች የፖለቲካ ሊቃናት፤ ዘመን የሰጣችሁ ባለሃብቶችም ብትሆኑ #ሰውነትን የተቀበላችሁ ከሆነ፤ አምላክ // አላህ ፈጣሪ አለን ብላችሁ እምታምኑ ከሆነ ወደ ቀያችሁ ተመልሳችሁ አስተምሩ ሰውነትን፤ ተፈጥሯዊነትን ስበኩ፤ በዓለም አደባባይ በጭካኔ ከመጠራት በላይ ሸምቆቆ የለምና። ተሰባሰቡ፤ ለተጎዱት ድረሱ። አይዟችሁን ቀልቡ። ጭካኔውን አስቁሙ። ትዕዛዝ ግን አይደለም። መንገድ እንጂ።
ረፍዷል፤ እየመሼ ነው፤ ተሎ ድረሱ፤ ጊዜ የለም። አዝነናል፤ ተጸጽተናል፤ አይዟችሁ ማነን ገደለ???? ህወሃት ናፈቃችሁን? እየሠራችሁ ያላችሁት የህወሃትን ምኞት ነውና ከጨቀጨቁ ውጡ። ማፈር - ፈቅዶ። መሸማቀቅ - ፈቅዶ። መጸጸትን - ፈቅዶ። ድንቅ ነገር ነው። የሚደመጠው ሁሉ የነገን ትውልድ አያበረክትም። የሰው ቀርቶ #የአዕዝርት አምላክ ይፈርዳል።
#እርገት ይሁን። መላከ ኤዶም እርፍ አደረጉን።
ስለ ቅኒት ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መከፋት በጥንቃቄ ኃላፊነት ወስዶ ከውስጥ የሚሠራ ሚዲያ ማግኘት ምርቃት ነው። የአደባባይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ መላዕከ ኤዶም እና ቲሙ አሳረፋን። ውስጤ እርፍ አለ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ማህበረ ቅንነት እንዴት አረፈዳችሁ። ዝልቅ መረጃ በሚዛናዊነት እና በማስተዋል የተቀመረበት ተግባር ነውና የሚመቻችሁን ብታደምጡ ጥሩ ነው። ላይክ፤ ሼር፤ ሳብስክራይብም አይከፈልበትም ስለማተባችሁ መንቆጣቆጥን አሸንፋት። እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
«ሙፍቲ "ያከሸፉት መርዝ" || ቅ/ሲኖዶስ እና የመረረው የክርስቲያኖች ቅሬታ || የጦር ወንጀል እንደ ጦር ስልት»
«በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የጋራ ድምፅ ለምን የለንም? ብዙ ሆነንስ ለምን ኃይል አጣን?»
«ጭፍጨፋውን ለማስቆም፤ ሕዝቡን በአካል ለመጎብኘት፣ ወንጀሉን ለዓለም ለመንገር»
«የአርሲ ጭፍጨፋ ዜና ከዋይት ሐውስ፣ ከኔዘርላንድ ፓርላማ ደርሷል፤ ይቀጥላል || ከጭፍጨፋው ጀርባ ያሉ ባለሥልጣናት ስምና ፎቶ ይዘናል»
«ይድረስ ከሌ/ጄ/ል ድሪባ መኮንን፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር»
«በመሪዎቻቸው የተካዱት የምሥ/አርሲ ኦርቶዶክሳውያን»
"በአርሲ ሙሉ በሙሉ ከክርስቲያን የጸዱ አካባቢዎች ተፈጥረዋል" || ክርስቲያኖቹ የት ገቡ? መንግሥት ለምን ፍጅቱን ይደብቃል?»
An Urgent Appeal for the Orthodox Christians of the East Arsi Zone, Oromia, Ethiopia
«ኢብራሂም ከድር፦ ከሻሸመኔ ጭፍጨፋ እስከ አርሲ እልቂት፤ ከም/ከንቲባነት እስከ ዞን አስተዳዳሪነት»
«የክርስቲያኖች ግድያ || የመንግሥት ተቋማት ተባባሪነት እና በቁጣ ላይ ያለው ምዕመን»
ሥርጉተ@ሥላሴ
Sergute©Selassie
15/11/2025
አማኑኤል አባቴ መቼ ይሆን ቅድስት ተዋህዶ አለሁልሽ፤ ወህ በይ የምትላት? እጠብቅኃለሁኝ።


አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ