#አስታዋሽ ያጣ ብሄራዊ ዕንቁ። የተዘለለ የጥበብ አገራዊ #ልቅና።
አንዳንድጊዜ ኢትዮጵያ የጥበብ ባለሙያወች ብቻ #ሰገነት ትመስለኛለች። ክብሩ፤ መወደሱ፤ ድጋፋ አትኩረቱ፤ ሹመቱ ሽልማቱ፤ ዕድል እና እንክህ እንክህ መባሉ በአስተውሎት እከታተለዋለሁኝ። ለካስ ይህ ለሁሉም የጥበብ ሰወች አይደለም። በጥበብ ተሳትፎ ውስጥ የክት እና የዘወትር፤ የእዳሪ እና የቤት ልጅ፤ ዓይነታና እንጥፍጣፊ የሚል እጅግ የሰፋ የሚያስከፋ አድሏዊነት አለ?
የክብር አንባሳደርነቱ፤ የማስታወቂያ ዕድሉ ሁሉ …………--------#ለተወሰኑት ብቻ??? ፍትኃዊነት ቢያንስ በእጅ ባለ ነገር መተርጎም ምን ያቅታል? አሻግሮ ከመጠየቅ??? በመዳፍ ያለ አቅም ስለምን ያቅታል??? ብዙ በጣም ብዙ የጥበብ ጥሪወችን በእኩልነት ላስተናገደች #ዕንቋችን አትኩሮቱ ስለምን ተሰደደ? ተቋማት ሰው መሆን የመቻል አቅማቸው መለኪያው ለእኔ #ፍትኃዊነት ነው። ጉማ አዋርድ፤ ለዛ አዋርድ ወዘተ የሚባሉ ሥርዓት ሲከውኑ አያለሁኝ። የጥበብ ቤተኞችም ተሞሽረው ይገኛሉ። #ባሊህ #ባይ ያጡ ደግሞ እንዲህም የጥበቡ #ቀንዲሎች አሉ። ቢያንስ ለባዕሉ የታዳሚነት ጥሪ ምኑ አነሰ #የአርቲስት አልማዝ አበበ??
ክብርት አርቲስት አልማዝ አበበ በዩቱብ የተለቀቁ ተውኔት ላይ ተሳትፎዋን አያለሁኝ። ከእሷ የማየው ለየገጸባህሪው #ተፈጥሯዊነት ብቃት በጥቂቶች ብቻ የሚገኝ ጸጋ ይመስለኛል። ብዙ ጊዜ እናት ሆና ነው የምትሰረው። ይህ ደግሞ #ሰፊነትን ያመሳጥራል። እናትነት የአደብነት ተጠሪነትም ነው። እናትነት የአቅል ተቋምነትም ነው።
ለአንድ ሰብዕና መልክ ብቻውን፤ ድምጽ ብቻውን፤ ዲግሪ ብቻውን ለጸጋወች ሁሉ ልክ አይሆንም። አገር ቤት እያለሁኝ እንደ እህት የማያት ልዩ ጓደኛዬ በአማርኛ ቋንቋ ተመርቃለች። ግን #አትጽፍም። #አታነብም። #አትሄስም። በአማርኛ ቋንቋ የተመረቀ ሰብ ወይ አንባቢ፤ ወይ ጸሐፊ፤ ወይ ሃያሲ ሊሆን ይገባል። ትምህርቱ ካለ ጥሪ ሊሆን ካልቻለ።
አገር ቤት እያለሁኝ አንድ የኖርወይ ድርጅት በልጆች ላይ የራዲዮ ፕሮግራም ነበረው። ግፊቱ ከዛ የመጣ ይመስለኛል #መንትዮሽ የሚል የልጆች አጫጭር ልቦለድ ፃፍኩኝ እና እንደ እህት ለማያት የአማርኛ ቋንቋ ባለባችለር ለእርምት ሰጠኋት። አንድ ዓመት ጠበቅኩኝ። #ንክች አላደረገችውም። ለህትምት እንዲበቃም አማከርኳት አክሰሱ ስለነበራት፤ በእኔ ሥም ይሁን ብላ ደፍራ ጠየቀችኝ። ታላቅ እህቴ መምህር ናት እና አማከርኳት፤ ደንግጣ "የህሊና ውጤት እንዴት ለሌላ ይሰጣል። እሰቢበት አለችኝ።" በቃ ቀረ። ያ ስክርቢት በዛ ዘመን ዕውቀቴ ልክ ከእኔ ጋር ስደቱን ይቀጫል። የተፃፈው ደግሞ በእጅ ነው።
ምን ለማለት ነው፤ ከክብርት አልማዝ አበበ #መሰጠት ጋር ቋንቋውን የተማሩ፤ በፊልም ጥበብ ይሁን በቲያትር ጥበብ የተመረቁትም ቢሆኑ ካልተሰጣቸው ከእሷ ጋር ሊለካኩ አይችሉም። የጥበብ ጥሪ #ሸቀጥም አይደለም። ገብያ ተሂዶ በቦንዳ እና በችርቻሮ የሚገዛ አይደለም ። ጸጋው የባለቢቱ የአንድዬ ነው። ይህን የአንድዬ ሥጦታ ካለ አድሎ አክብሮ መገኜት ከእያንዳንዳችን በግል ከሁላችንም በጋራ ይጠበቃል። በተለይ ተቋማት መሠረቱ ያማረ የእኩልነት መርህ ቢከተሉ አብነት የመሆን አቅም ሊኖራቸው ይችላል።
ይህቺ የጥበብ ዕንቁ በየትኛውም የሽልማት ተቋም ተጋብዛ አታውቅም። #ጥምንምን ያደርጋል። ለሽልማት ቀርባም አታውቅም፤ ለውድድር እንኳን። ጉዳዩ አጥንትን እንደ ራሺያ ብርድ ዱድማ ያደርጋል። ከውስጤ ነው የከፋኝ። በእንግድነት እንኳን ተጋብዛ አታውቅም። ሰይፋሻ ሸውም ስለመቅረቧ አላውቅም። የመንግሥት ሚዲያወች ላይም አጋጥሞ አይቼ አላውቅም። አሻም ቲቢ ላይ ሳያት ተሻምቼ ነው ያዬኋት። መደመጥ ስላለባት በጽሞና አዳመጥኳት።
#የጥበብ አፍቃሪ ድንቅ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሆዬ! እባካችሁ መላ በሉ።
ትችላላችሁም! እባካችሁ ልዩ የክብር ቀን አሰናዱ። የገረመኝ #ቅን ልቦችም ይህን ለምን #እንዳላሰሰ ገርሞኛል። "ፎቶ እና ወግ" መሰናዶ የፍጼ አዲስ ሸው አለው። እንዲህ ያለውን አገራዊ ክፍተት ቢያሟላበት ምኞቴ ነው። አሜሪካን አገር፤ ካናዳ ለሊቀ ትጉኃን የሽልማት ዕድሉ አለ። እባካችሁን አትኩሮታችሁን ለግሱት ለዚህ መሰል ክፍተት። ህሊናን ጉርብጥብጥ ያደርጋል። የሆነ ብልህ ነገር ያጎድላል እንዲህ ዓይነት ዝበት። ታውቆም ይሁን ሳይታወቅ ጥሩ አይደለም።
"ጥበብ ቤቷን ሠራች፤
ሰባት ምሰሶም አቆመች።"
አሻም ቲቢን አመሰግናለሁኝ። እሷን ስላየሁም ነው ያዳመጥኩት።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
በጥበብ ብልህነት እና ቤተኝነት ይከበር።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ