#አብረን #እንፈር። የኢትዮጵያ ሴት የፖለቲካ ሊቃናት የአቤቱ ብልጽግና የካቢኔ #አባላት የት ናችሁ????
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
የእኔ ክብሮች የአገሬ ልጆች እንዴት አደራችሁልኝ? እንዴት አረፈዳችሁ? ይህን መሰል #የዕንባ ውስጥን #የሚያውክ ዘገባ ባላቀርብ በወደድኩኝ። ግን እፍረቱ የጋራ ነው እና ስቃዩን ልንጋራ ይገባል ብዬ። አውጥቼ አውርጄ ከቢቢሲ ያገኜሁትን ዘገባ ለጥፌዋለሁኝ። እኔ በዘመነ ደርግ ተማሪ ነበርኩኝ። ደርግን የሚፋለሙ ህወሃት እና ኢዲዩ የሚባሉ በጎንደር አካባቢ ሽምቅ ተዋጊወች ነበሩ። በከተማም ነጭ ሽብር እና ቀይ ሽብር የሚባሉ የበቀል ገደላ ገደሎች ነበሩ። በአዋሳኝም ህወሃት ነበር። በኡምናህጀር በሰቲት አካባቢ የሻብያ ሁነት እንደነበረ አላስታውስም።
ግን የመንግሥት ሠራዊት፤ የተፋላሚወች የኢዲዮው እና የኢህአፓ ሠራዊት በዛን ጊዜ ከብልጽግና እና ከህወሃት ጦርነት ወዲህ የምሰማው ዓይነት #ሴቶችን #የጭካኔ አዲስ ማንነት እንዲኖራቸው የሚያስገድድ ዜና ሰምቼ አላውቅም። በዘመነ ደርግ የወጣቶች እስር ነበር። ትምህርት ቤት ላይም ድብደባ ነበር። እስር ቤት #ቶርች ነ ግድያም ነበር። የአደባባይ እርሸናም ነበር።
ከትምህርት ቤት በጅምላ ተወስደን ፋሲል ግንብ በጉልበት የእንብርክክ የመሄድ ቅጣትም ነበር። ካለምግብ እና መጠጥ እዛው ባዶ ክፍል ላይ ማደር፤ ውሃ በመኪና ሲመጣም #የጎርፍ ውሃ መሰጠት ነበር። ተሻምተን የጎርፍ ውሃ ጠጥተናል። የደረቀ ዳቦውንም ኮርሽመናል። እኔም ይህን ቀምሸዋለሁኝ። ከዚህ ውጪ #መደፈር እንዲህ በጀምላ አልሰማሁም። በህወሃት ጊዜም ታስሬ ነበር። በዘመነ ደርግ የወጣት ስደት በስፋት ነበር አቅጣጫው ወደ ሱዳን። በዘመነ ህወሃት ደግሞ ስደቱ ሁለተኛ አገር አግኝቶ ወደ ኤርትራ አቀና። በዚህ ሁሉ ስቃይ የሰቆቃው ዳፋ የወላጆች ነው።
#መደፈር ቀራኒወ + ጎለጎታ። አፍ ባለው መቃብር መኖር።
አሁን አሁን እምሰማው ደግሞ ሴት ልጅ ሆኖ መፈጠርን የሚርድ ሆኗል። የአማራ ሴት ህፃናት፤ ሴት ታዳጊ ወጣቶች፤ ሴት ወጣቶች፤ ሴት የዩንቨርስቲ ተማሪወች #የቁም #ሙትነት ተፈርዶባቸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ዕንባ አባሽ የሚባል የሚ/ር መቤት አለ። ወግ አይቀርም። ደሞዙን ተቀብለው እህል ውሃው ከጉሮሯቸው እንዴት ሊወርድ እንደሚችል እራሳቸውን ይጠይቁ።
የሴቶች የልጆች እና የወጣቶች፤ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በዘመነ ህወሃትም፤ የሚባሉ ተቋማት በዘመነ ህወሃት ነበሩ፤ በዘመነ ብልጽግናም ቀጥለዋል። ለየትኛው ድርጊታቸው #በጀት እንደተመደበላችው አላውቅም። ህሊና ላይ ሊሠሩ የሚገባቸው ጠንካራ ጉዳዮች አሉ።
አያስተምሩ፤ ሰሚናር አያዘጋጁ፤ ከመንግሥት አካላት ጋር አይሟገቱ፤ ከጸጥታ፤ ከደህንነት አካላት ጋር ፓናል ዲስከሽን በጋራ አያካሂዱ ይህን ችግር እንዳይቀጥል፤ ይህ የወል ሃፍረትን የመቋቋም አቅም ሊያመነጩ ይገባ ነበር። ተቋማቱ ሥራቸው፤ ውሎ አዳራቸው ምን እንደሆነ በፍጹም አይገባኝም? እንደ እኔ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ምልከታ የእነሱ #በጀት ታጥፎ ለሌላ ጠቃሚ ተግባር ቢውል ህልሜ ነው። #ጣዖቶች ናቸውና።
በሌላ በኩል ፍትህ ሚ/ር ለዛውም በሴት ሊቅ የሚመራ፤ የህብረተሰብ ጤና፤ ጤና ሚር ለዛውም በሴት ሊቅ የሚመራ፤ ቀይ መስቀል፤ የደህንነት ተቋማት፤ የጸጥታ ኃይሎች መከላከያው በሴት ሊቅ የሚመራ፤ ትምህርት ሚር፤ የሰብአዊ ድርጅት ተቋማት፤ ራሳቸውን ማዳን ቢሳናቸውም የሃይማኖት ተቋማትም አሉና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ማዕከል ያደረገ #ጠንካራ ውይይት በዚህ ጉዳይ ለምን አይደረግም?
መቸም በዘመነ ብልጽግና የሴት የፖለቲካ ሊቃናት ውክልናቸው ተመጣጣኝ አይደለም ብዬ ልሞግት አልችልም። አሉ። ቁልፍ ኃላፊነት ተስጥቷቸዋል፤ ባህል ሚር፤ ቱሪዝም፤ የጠቅላይ ሚር ጽህፈት ቤት ኃላፊነት፤ የኮምኒኬሽን ኃላፊነትም አንስት። የዓለም 4ኛዋ የዲፕሎማት #ከንቲባም ሴት፤ ብዙ ዘርፎችም በሴት ሊቃናት ተይዘዋል።
ቦታውን መያዝ ብቻውን ግን ግብ አይደለም። ሁሉም ሴትነትን በተለየ አስተሳሰብ እና አትኩሮት ማገዝ አልቻሉም። እናትነት ጸጋቸውን ማስከበር #ተስኗቸዋል። ማንም ይፈጽመው ማንም የሴቶች ጥቃት የእኔ ነው ብሎ የፋመውን፤ የጋመውን ፈተና ፊት ለፊት መጋፈጥ ያስፈልጋል። በማን #ኡኡ ይባል??? የኢትዮጵያ ሴት ሊቃናት አይደለም በብልጽግና በአህጉር፤ በዓለም ዓቀፍ ተቋማትም ዕውቅና እያዬሁ ነው። በአገር ውስጥ በቂ ውክልና አላችሁ የኢትዮጵያ ሴት የፖለቲካ ሊቃናት ከሙሉ ሎጅስቲክ እና #ፍርስስ ካለ ህይወት ጋር።
የእህቶቻችሁ፤ የእናቶቻችሁ የሴቶች ጥቃት #ላርባ ሆኖ እንዲያንገበግባችሁ ስለምን እንደማትፈቅዱ በውነቱ አይገባኝም።
የመከላከያ ሚኒስተሯ እኮ ክብርት ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ባልተለመደ ሁኔታ #ሴት ናቸው? የአሁኗ የአውሮፓ ህብረት ቁንጮ ዶር ኡርዙላም የጀርመን የመከላከያ ሚር ነበሩ። የዛ ኮፒ ይመስለኛል። የሆኖ ሆኖ ክብርት ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ድርጊቱ እኔን አስገድዶ መድፈር ነው ብለው የሚመሩትን አካል መጠየቅ ይገባቸው ነበር።
በሌላ በኩል የጤና ሚኒስተሯ ክብርት ዶር መቅደስ ዳባ ናቸው። ተገደው ተደፍረው መኖራቸው ለተዘቀዘቀ ሴት እህቶቻቸው ልዩ ትኩረት፤ ልዩ እንክብካቤ ሊፈጽሙ በተገባ። የክህሎት ሚኒስትሯ ከወጣቶች ጋር ይያዛል ክብርት ሙፍርያት ናቸው …ሴት የነጠፈባት ኢትዮጵያ ሊያሳስባቸው ይገባ ነበር። የባህል ጥሰትም ስለሆነ ሴቷ የባህል ሚኒስተሯም ችግሩን የእኔ ብለው ሃዘኑን መጋራት ይጠበቅባቸው ነበር።
የኢትዮጵያ በየደረጃው ያሉ ሴት የፖለቲካ ሊቃናት ከቀዳማዊት እመቤቷ ጀምሮ ያሉት ሁሉም … ከላያቸው ላይ ያለው የሹመት ተክሊል ለእኛ ለሴቶች ጥቃት፤ መደፈር፤ ዕንባ እና #ንቀት ካልሆን ለማን ሊሆን ነው።
ባለፈው ሰሞን የእኔ የተግባር ልዕልት የቀድሞዋ የጀርመን ካንስለር ወሮ አንጊላ ሜርክል #ፌሚኒስት ነኝ ብለው ደፍረው ሲመልሱ ሰምቻለሁኝ። ይህ አገላለፃቸው በመሆን የጸደቀ ስለመሆኑ እኔ በ፲ እጣቴ እፈርምላቸዋለሁኝ። እናትነታቸው ለዓለም ህዝብ፤ በተለይ ለዓለም ሴቶች ነው። የእኛወቹ ቦታውን ይዛችኋል ግን ምንም የአጽናኝነት፤ ፈቅዶ ቀድሞ ለእህቶቻችሁ የመድረስ {}። አብረን እንፈር የምለው ዛሬ አይደለም። ድካማችን ሳያፈራ ከዕንባ ጋር ትቅቅፋችን መዝለቁ የሥራችን ጥራት ጉድለት ነው።
ውስጣችን የጎሼ ነውና ልፋታችን ሊያሰብል አልቻለም። እንዲያውም በዘመን ወለድ የበቀል እርምጃ ብዙ አጋጣሚወች በሴቶች መኖር ላይ ዳመና እና ጢስ እያስፋፋ ነው። በዚህ ሃሳብ ላይ የኢትዮጵያ ሴት ሊቃናት የጭምቱ ማህበረሰብን የዝምታ ዓውድ ብታከብሩት፤ ብትጠቀሙበትም በትህትና አሳስባችኋለሁኝ። ህመሙ ካልተሰማችሁ ዕንባው ምርቃት እንዲነሳ ያስገድዳል። የምር ነው የምጽፈው። የውስጤንም።
ባላፋት ወራት ከትምህርት የተስተጓጎሉት የአማራ ወጣቶች ካለ ዕድሜያቸው የመንገድ ኑሮን፤ ፆታቸውን ለመተዳዳሪያነት በታዳጊ ወጣትነት ዘመናቸው መፍቀዳቸው ሪፖርተር ላይ እየሰቀጠጠኝ አንብቤያለሁኝ። "በፌድራሉ" (ፌድራልን በቅንፍ የማስቀምጠው ፌድራሊዝም ያለው አማራ ክልል ላይ ነው። ለማዕከላዊ መንግሥት የፖለቲካ አቅም ፌድራሊዝም አይመጣጠኑም )።
የሆነ ሆኖ በህወሃት ጦርነት የአማር ክልል እጅግ ተጎጂ ነበር። የተረፋ ጥቂት ከተሞች ነበሩ። ጎንደር ከተማ እና ሙሉ ጎጃም ብቻ። የደቡብ አፍሪካ ስምምነት ሲፈረም ዘገባውን በፍጥነት በእልልታ ያቀረብኩትም የአስከፊ ጦርነት ዶፍ ጥቂት ከተሞች ስለተረፋ ነበር።
የሆነ ሆኖ መገፋትን፤ መገለልን፤ አትኩሮት በበቂ አለማግኜትን ተንተርሶ ከአደባባይ ሰላማዊ ትግል ወደ ትጥቅ ትግል በተሸጋገረው የጦርነት ድባብ በብልጽግና እና በፋኖ ጦርነትም የተጎዳው #የአማራ ክልል ነው። ይህን ጉዳት አስቁሞ፤ የተጎዳውን ሁነት እንዲያገግም ለማድረግ ጥረቱ የለም። እስከ መቼ ይህ የመከራ ሊቀጥል እንደሚችል አላውቅም። ችግሩን ሊያስቆም የሚችለው የመጀመሪያው እርምጃ የአፈሙዝ #ፈንጠዝያ #ጸጥ እረጭ ሊል ይገባል። በስምምነት።
ስምምነቱ እልህን በረድ አድርጎ፤ ቁጭትን አስታግሶ፤ ብስጭትን ሃግ ብሎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ውይይት ማዘንበሉ ይጠቅማል። የረጅም ጦርነት ቢያተርፍ ኢህአፓንም፤ ኢዲዩንም፤ ህወሃትንም ድሉ እራሱ ህዝበጠቀም አላደረገም። ለአማራ ህዝብ "ላም አለኝ በሰማይ" ሳይሆን ቢያንስ ድህነቱ ሰላም ሊያገኝ ይገባል። መካሪ ያስፈልጋል። ፍላጎት ያላቸው የፖለቲካ ሥልጣን ምኞተኞች ይሁኑ የጦርነት ዘጋቢ ባለሚዲያወች በየክልላቸው ጫካ አለና በየጫካቸው ሰማዕትነትን ሼር ያድርጉት። ሁልጊዜ በአማራ ትክሻ ግን ፍጹም #ጨካኝነት ነው።
ሁልጊዜ ነው የምጽፈው ከተከበሩ የዩክሬን መሪ ከፕሬዚዳንት ዘለንስኪ የሥልጣን ዘመን መማር በእጅጉ እንደሚያስፈልግ ነው። ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ማለት ለአገር መሪነት ብቃት ማለት አይደለም። ይህንን አንጥሮ በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል። የፕሬዚዳንት ዘለንስኪ የህይወት ጉዞ ካሪክለምም ነው። ይህን በአውዲዮ ሁሉ ሠርቻለሁኝ። ድልን፤ አውራነትን፤ ጎልቶ መታየትን ከሌላ በሚገኝ ሃብት የራስን ህዝብ በመማገድ የሚገኝ ልዕልና ቤርሙዳ ትርያንግል ነው።
1) ዩክሬን ምን አተረፈች?
2) ፕሬዚዳንቱስ ምን አሳኩ?
3) ተጉጂውስ ማነው?
4) ማገዶውስ የቱ ነው? የዩክሬን ህዝብ ያሳዝነኛል። የተሳካ ህይወቱ ነው የታወከው። ለሰው ልጅ ልዩ ስጦታ አለ ከተባለ ዕንባ ሳይሆን ሰላሙን በሁሉም አቅጣጫ ማረጋገጥ ነው። ብርዱ እራሱ ከጦርነቱ በላይ ህዝቡን አጎሳቁሎታል።
እርግጥ ነው የአገር መሪ ሲኮን ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ይቻላል። የሚዲያ አውራ ሆነዋል ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ። የአንድ አገር መሪ ሲኮን አቅም ኖረ አልኖረ በልኩ ክብር ይኖራል። ክብር የህዝብ የጸና ሰላም እና ቋሚ መረጋጋት ካልሰጠ የአንድ አገር መሪ ክብር፤ ተጽዕኖ ፈጣሪነት የጉም ሽንት ነው።
ይህ ሁነት ለተጠቁት ብቻ ሳይሆን፤ ጥቃቱ ላልደረሰባቸውም የሥነ ልቦና ጉዳት ያመጣል። መፍትሄው ጦርነቱን ግራ ቀኛችሁ እባካችሁ አቁሙ። እባካችሁ ተለመኑኝ። ሥልጣን ላይ ያላችሁ ከሊቅ እሰከ ደቂቅ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናትም መንሹ በእጃችሁ ነውና መከራውን አቅርባችሁ ተወያዩበት። ዕንባው ውስጣችሁን ይጎበኜው ዘንድ እባካችሁ ፍቀዱለት።
በተለይ ክብርት አይንሻ መሀመድ የዩዲት ታሪክ ተጋሪ እንዳይሆኑ ከውስጥ ቢያስቡበት በትህትና አሳስበወታለሁኝ። ይህ ዜና ለህወሃት ሆነ ለግብጽ እና ለመሰል ኢትዮጵያን በግልጽም፤ በስውርም ለሚቀናቀኑ፤ ለሚቀኑባትም ብርንዷቸው ነው። ቢያንስ የእኛ ችግር ብላችሁ አቅም ፈጥራችሁ በህብረት ብትነቃነቁ ጥሩ ነው።
የእኔ ውዶች ቸር ዜና ንፍቅ አለኝ። ሰው መሆን መቻል እና የማስቻል አቅም የሚኖረንስ መቼ ይሆን? የሴቶችን ዘላቂ ሰላም በልዩ ሁኔታ የሚያስጠብቅ አዲስ ህግ ያስፈልጋል። እናፍቃለሁም።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
19/11/2025
የሴቶች ጥቃት በኢትዮጵያ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይቁም!
የሴቶችን ሰላም በልዩ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ህግ ያስፈልጋል።
ትዕግሥት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል።
ዕውነት ለፈሪነት አልተፈጠረም።
================================================================
BBC
• "ቢገድሉኝ ይሻል ነበር"፡ የሴቶችን ሕይወት እያበላሸ ያለው የተዘነጋው የአማራ ክልል ጦርነት» BBC.
«ማሳሰቢያ፡ ይህ ዘገባ የመድፈር እና ወሲባዊ ጥቃቶችን ክስተት በዝርዝር የሚገልፅ በመሆኑ የሚረብሽ ነው።የጥቃት ሰለባዎቹ ስም የተቀየረ ሲሆን፣ ማንነታቸውን የሚያመለክቱ ዝርዝሮች ለደኅንነታቸው ሲባል እንዲቀሩ ተደርገዋል።»
«እናት እሁድ ጠዋት ወታደሮች ወደ ቤቷ ሲመጡ ከስምንት ዓመት የእህቷ ልጅ ጋር እንደነበረች ትናገራለች። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም. በአማራ ክልል እየበረታ የመጣውን የፋኖ ታጣቂዎች አመፅ ለመከላከል ከሚወስደው እርምጃ ጋር በተያያዘ የቤት ለቤት ፍተሻ እያደረገ ነበር።»
«እናት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የደንብ ልብስ የለበሱ ሦስት ወታደሮች ደቡብ ጎንደር ወደ ሚገኘው ቤታቸው እንደመጡ እና ስለማንነቷ እንዲሁም የፋኖ ታጣቂዎች ከምትሠራበት ጠላ ቤት እንደሚመጡ መጠየቅ መጀመራቸውን ትናገራለች።»
«የ21 ዓመቷ እናት የፋኖ ታጣቂዎች እንደሚመጡ ማረጋገጧን ትገልፃለች።»
"እንዴት ብለን እንዋሻለን? እንዴት ብለን እንክዳለን?"
«ነገሮች ወዲያው ብዙም ሳይቆዩ ተካረሩ። ስለቤተሰቦቿ ማንነት ከጠየቋት በኋላ እናት ወታደሮቹ በአፀያፊ ቃላት እንደሰደቧት ትናገራለች። ከዚያም ሕፃኗ ማልቀስ ስትጀምር በመሣሪያቸው እንዳስፈራሯት ታስታውሳለች። እናት ከዚያም አንደኛው ወታደር በሌሎች ወታደሮች እርዳታ በእህቷ ልጅ ፊት እንደደፈራት ተናግራለች።»
"እንዳይጎዱኝ ተማፀንኳቸው። ታቦታትን እየጠራሁ ለመንኳቸው። ግን ልባቸው አልራራልኝም። አበላሹኝ።"
• "በሺህዎች የሚቆጠር መድፈር እና ጥቃቶች"
"እናት ብቻዋን አይደለችም፤ እናት የአማራ ክልል የትጥቅ እንቅስቃሴ ከተቀሰቀሰ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል ተብሎ ከሚታመኑ በሺህዎች ከሚቆጠሩ ሴቶች ውስጥ አንዷ ናት።"
"ምንም እንኳ እውነተኛው ግጭት ነክ የወሲባዊ ጥቃት መጠን ሪፖርት ባለመደጉ እና ባለመርመሩ በትክክል ባይታወቅም፤ ቢቢሲ ያሰባሰበው መረጃ ከሐምሌ 2015 እስከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ድረስ ከስምንት ዓመት እስከ 65 ዓመት ዕድሜ ያላቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው ያመለክታል።"
"ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን በክልሉ ያለውን ግጭት ለመዘገብ በተጣለባቸው ክልከላ እና ገደብ ምክንያት ወደ ክልሉ መግባት ባይችሉም የቢቢሲ የናይሮቢ ጋዜጠኞች ቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ተጎጂዎችን እና የጤና ባለሙያዎችን በማነጋገር ቀውሱ በሰብዓዊነት ላይ እያሳረፈ ያለውን ጠባሳ የሚመለከት መረጃ አግኝቷል።"
"የአማራ ክልል የትጥቅ ግጭት መንግሥት ለሁለት ዓመታት በነበረው ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት የተሳተፉትን ኃይሎች ጨምሮ የክልል ልዩ ኃይሎችን ለመበተን ሲሞክር ነበር የፈነዳው።
የፋኖ ኃይሎች በእርምጃው ክህደት የተሰማቸው ሲሆን እንደ መብት ተሟጋቾች መረጃ በተለይም የአማራ ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መባባሳቸውን ተከትሎ፤ ከትግራይ እና ከሌሎች ክልሎች የደኅንነት ስጋት እንዳሳደረባቸው ያምናሉ።"
"ከወራት አለመረጋጋት በኋላ የፋኖ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ዋና ከተሞችን በመቆጣጠር አመፃቸውን ጀምረዋል። የፋኖ ኃይሎች ራስን በራስ የማስተዳደር ትግል እና ማኅበረሰቡ በመንግሥት ደርሶበታል ብለው ከሚያምኑት የዓመታት መገለል እየተከላከሉ እንደሆነ ይናገራሉ። የፋኖ ኃይሎችን "ፅንፈኛ ብሔርተኛ" የሚላቸው መንግሥት ለአመፁ ምላሽ የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ ከባድ እርምጃ እየወሰደ ነው።"
"ግጭቱ ሲጀመር አንስቶ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ያለ ፍርድ ግድያ፣ ከሕግ ውጪ እስራት፣ አስገድዶ ስወራ፣ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ እንዲሁም ሰፊ ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማድረስ ይከሰሳሉ።"
"አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግሥት ተመጣጣኝ ያልሆነ ጥቃት መፈፀሙን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳለ አሳውቀዋል። ድርጅቶቹ ከዚህ በተጨማሪ የአማራ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በፀጥታ ኃይሎች እና በሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ሆን ተብሎ በሚፈፀሙ ጥቃቶች ኢላማ እንደሆኑ ይናገራሉ።"
"እናት የጥቃቱ ሰለባ ከመሆኗ በፊት በቤተሰቧ ውስጥ እንዳሉ ሌሎች ሴቶች ሁሉ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት አስተምህሮ መሠረት በተክሊል የማግባት ዕቅድ ነበራት። "ከዚያች ቀን በፊት ወንድ [የወሲብ ግንኙነት] አላውቅም ነበር" ትላለች። "አበላሽተውኝ ሄዱ። ቢገድሉኝ ይሻል ነበር።"
• 'ቤተሰቦቼ መንገድ ዳር ወድቄ አገኙኝ'
"የ18 ዓመቷ ትዕግሥት የምዕራብ ጎጃም ነዋሪ ስትሆን የመድፈር ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት በቤተሰቦቿ ሻይ ቤት ትሠራ ነበር። ጥር 2016 ዓ.ም. 'ሻይ ቡና' ለማለት የሚመጣ ወታደር ተደጋጋሚ ጉንተላ ሲያደርስባት፤ "ሥነ ሥርዓት ያዝ" በሚል የሰጠችው ምላሽ ለደረሰባት ጥቃት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ታምናለች።"
"'ቆይ አሳይሻለሁ' ብሎ ዝቶብኝ ወጣ። "ምሽት አካባቢ ከሥራ ወደ ቤት ስትመለስ ትዕግሥት ቀን ላይ የጎንተላትን ጨምሮ ሦስት ወታደሮች መንገድ ላይ አድፍጠው እንደጠበቋት እና መንገድ ዳር በደቦ እንደደፈሯት ተናግራለች። "ቤተሰቦቼ ስቆይባቸው እኔን ፍለጋ ሲወጡ መንገድ ዳር ወድቄ አገኙኝ" ስትል ታስታውሳለች ትዕግሥት።"
"አፋፍሰው ወደ ጤና ጣቢያ ወሰዱኝ። እዚያም አምስት ቀን ቆየሁ።" ጥቃቱ ከተፈጸመባት ጊዜ አንስቶ ትዕግሥት በሰዎች እና በውጭው ዓለም ፍትሃት ተሸብባ ከቤቷ መውጣት እንደማትችል ትናገራለች። "ፍርሃት ስላደረብኝ ሥራውንም ተውኩት። . . . ወታደሮችን ሳይ በጣም እፈራለሁ። ወንዶችንም ሳይ ፍርሃት ያድርብኛል፤ እሸሻለሁ" ትላለች ጥቃቱ ከደረሰባት ከዓመት በኋላ።»
«ትዕግሥት የምታውቀው ሕይወት እንዴት እንደተመሰቃቀለ ስትገልፅ ከእጮኛዋ ጋር መለያየቷን እና ምን እንደተፈጠረ ምክንያቷን እንዳልነገረችው ትገልፃለች።» «በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጠችው ትዕግሥት ራሷን ለማጥፋት ብትሞክርም ቤተሰቦቿ በጊዜ ደርሰው አትርፈዋታል። ከዚህ ጊዜ በኋላ ትዕግሥት በተደጋጋሚ ራሷን ለማጥፋት አስባ እንደነበር ሳትደብቅ፤ ነገር ግን ለቤተሰቦቿ ራሷን ለማጥፋት በድጋሚ እንደማትሞክር ቃል መግባቷን ተናግራለች።»
• 'ሴት ሆኖ መፈጠር ያስጠላል'
«ቢቢቢ በአማራ ክልል ስለተፈጠረው ቀውስ መረጃ ለማግኘት 4 በመቶ ከሆኑት የክልሉ 43 ጤና ጣቢያዎች እና የሕክምና ምንጮች መረጃዎች ሰብስቧል።»
«በእነዚህ ተቋማት ከሐምሌ 18/2015 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ድረስ 2,697 ሰዎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው ሪፖርት አድርገዋል። ከእነዚህም ውስጥ 45 በመቶ የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ናቸው።»
«ከተጎጂዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በደረሰባቸው ጥቃት በአባላዘር በሽታ ሲያዙ፤ በርካቶች ደግሞ ለእርግዝና እና ለከባድ የሥነ ልቦና ቀውስ ተዳርገዋል።»
«ይሁን እንጂ በርካታ የወሲባዊ ጥቃት ተጎጂዎች መገለልን በመፍራት፣ የአባላዘር በሽታ መያዛቸውን ወይም መፀነሳቸውን ላለማወቅ የተፈፀመባቸውን የመደፈር ጥቃት ሪፖርት ማድረግም ሆነ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አይፈልጉም።»
«ለዚህም ነው በደኅንነት ስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ከፍተኛ የጤና ባለሙያ በአማራ ክልል ግጭት ወደ ጤና ተቋማት የመጡ ተጎጂዎች "ከባሕሩ በጭልፋ ናቸው" የሚሉት።»
«ለምለም እንደ ኤችአይቪ ዓይነት በሽታ ተላልፎብኝ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት የተፈፀመባትን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ሪፖርት ካላደረጉት እና የሕክምና እርዳታ ካላገኙ ተጎጂዎች መካከል ናት።»
«የ23 ዓመቷ የደቡብ ጎንደር ነዋሪ ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም. የመንግሥት ወታደሮች በተለመደ እንቅስቃሴያቸው "መሣሪያ ያለውን ሠው ጠቁሚን ብለው" መረጃ ፍለጋ ወደ ቤታቸው መምጣታቸውን ትናገራለች።»
«የሚፈልጉትን መረጃ ባለመስጠቷ አንደኛው ወታደር ከዛተባት በኋላ እንደደፈራት ተናግራለች።» "'ጩኸት ብታሰሚ አንድ ጥይት ነው የሚበቃሽ' ብሎ አስፈራራኝ" ትላለች ለምለም። አንድ ወር ሙሉ አለቀስኩ። ምግብ አይርበኝም። ሥራዬ ማልቀስ ብቻ ሆነ። ቆሜ ለመሄድም ተቸገርኩ። ሕመምተኛ ሆንኩ።"
«ማኅበረሰባዊ ሐሜትን በመፍራት ጭንቀት ውስጥ መግባቷን የምትናገረው ለምለም፤ ከቤተ ክርስቲያን መራቋንም ተናግራለች።» "ሴት ሆኖ መፈጠር ያስጠላል። ወንድ ብሆን ደብድበው ጥለውኝ ይሄዳሉ እንጂ እንደዚህ ሕይወቴን አያበላሹትም ነበር"
"ስትል ለምለም የደረሰባት ጥቃት ቁስል በሴትነቷን ላይ ያሳደረባትን ከባድ ስሜት ታብራራለች። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ወሲባዊ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨመራቸውን ተናግረዋል።»
"እያለቀሱ፤ በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ፤ ለማውራት እየከበዳቸው ነው የሚመጡት" ሲሉ አንድ የጤና ባለሙያ የተጎጂዎችን ስሜት ይገልፃሉ። ሆኖም ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ተጎጂዎች የአጥቂዎቻቸውን ማንነት ለመናገር እንደሚያመነቱ እና ፍትሕን ፈልገው እንደማይመጡ ባለሙያዎች አመልክተዋል። ይህም በከፊል በግጭቱ ምክንያት ሕግ እና ሥርዓት በመስተጓጎሉ ነው።»
«ለዚህ ዘገባ ሠላም እያልን የምንጠራት 18 ዓመት ወጣት ይህ ክፍተት ለሁለተኛ ጊዜ የጥቃት ሰለባ ያደረጋት ተጎጂ ናት ሠላም እንደ ሌሎች ወጣቶች ራሷን እና ቤተሰቦቿን ለማስተዳደር እንጀራ ፍለጋ ነበር ወደ ከተማ የሄደችው። "
"የኮሌጅ ትምህርት ብትማርም በሰሜን ወሎ በሚገኝ አንድ ከተማ የቀን ሥራ ፍለጋ በወጣችበት ሰኔ 2017 ዓ.ም. ሥራ እንቅጠርሽ ብለው በወሰዷት ሁለት ሲቪል ወንዶች በቡድን ተደፍራለች።»
"ከቤት እንኳ አትወጣም" የሚሉት ሐኪሟ፤ "መረጋጋት የላትም፤ የሚረዳት ሰውም የለም" ሲሉ የደረሰባትን ጉዳት ይናገራሉ። ይህም ሠላም ምን ያህም የአእምሮ ቁስለት እንደደረሰባት እና ብቸኝነት ውስጥ እንዳለች አጉልቶ ያሳያል።»
«ምንም እንኳ ሠላም ጥቃቱን ለፖሊስ ሪፖርት ብታደርግም ከወራት በኋላም ቢሆን ተጠርጣሪዎች አልተያዙም፤ ፋይሉም ምን ደረጃ ላይ እንዳለ አይታወቅም።»
"ከዚህ በፊት ከተማ ላይ የሚታየው ኬዝ ውስን ነበር። ለሕግ በአስቸኳይ ነበር የሚቀርበው። ... [አሁን ተጎጂዎች] ድጋፍም አያገኙም። ያለው ሁኔታ ነው አሁን ክፍተቱን እየፈጠረ ያለው" ሲሉ የጤና ባለሙያው የግጭቱን ዙሪያ መለስ ዳፋ ይገልፃሉ። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች ለሕክምና ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ተጎጂዎች በእርግዝና ፍርሃት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።»
«ሌሎች ደግሞ ጥቃቱ ከደረሰባቸው በኋላ ዘግይተው ወደ ጤና ተቋማት የመምጣት አዝማሚያ ያላቸው ሲሆን፤ ኤችአይቪን ጨምሮ የአባላዘር በበሽታዎች መከላከያ በማይሠሩበት ወቅት ይደርሳሉ። በተለይም በጎጃም አካባቢዎች ዘግይቶ ወደ ሕክምና ተቋም የመምጣት አዝማሚያ ከፍተኛ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ተጎጂዎች አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያ (ፖስት ፒል) እንዲሁም የኤችአይቪ ቅደመ መከላከል አይወስዱም ብለዋል።»
«ኤችአይቪ 'ፖስት ኤክስፖዠር ፕሮፊሊክሲያ' በሚባል ሕክምና አስቀድሞ መከላከል የሚቻል ሲሆን፤ ነገር ግን ሕክምናው ጥቃቱ [ወሲባዊ ግንኙነት] ከተፈፀመ በአጭር ጊዜ መሰጠት አለበት። ሌላ የጤና ባለሙያ ግጭቱ ባሳደረው የትራንስፖርት መስተጓጎል እና መንገድ መዘጋት ምክንያት በርካታ ተጎጂዎች የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን እንደሚገልፁ ተናግረዋል።»
«አንድ ከፍተኛ የጤና ባለሙያ በዚህም የተነሳ የሕብረሰተሰብ ጤና እና የማኅበራዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። ከጤና ተቋማት በተሰበሰበ መረጃ መሠረት ባለሙያው "የኤችአይቪ [ሥርጭት] እንደሚጨምር የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። የሥነ አእምሮ እና ሥነ ልቦና ጤና ችግሮች እጅግ የከፋ ደረጃ ሊያደርስ ይችላል" በማለት ስጋታቸውን ሲገልፁ፤ ራሳቸውን ያጠፉ ተጎጂዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።»
«በ2015 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር አሃዛዊ መረጃ የአማራ ክልል የኤችአይቪ የሥርጭት ምጣኔ ከ100 ሰዎች 1.1 [ከ1,000 ሰዎች 111 ሰዎች] መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፤ ይህም ከብሔራዊው አማካኝ ምጣኔ ከፍ ያለ ነው። የመድፈር ጥቃቶች በግጭቱ እየተሳተፉ ባሉት በሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች እየተፈፀሙ ቢሆንም የጤና ባለሙያዎች ከፋኖ ታጣቂዎች በበለጠ የመንግሥት ወታደሮችን ማየታቸውን ተናግረዋል።»
«ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ እና ለመረጃ ቅርብ የሆኑ አንድ የመንግሥት ሠራተኛም ከፋኖ ጋር የተያያዙ ጥቃቶች "ውስን" መሆናቸውን የጤና ባለሙያዎችን ሀሳብ በማጠናከር ገልፀዋል። አብዛኞቹ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች መከላከያ ሠራዊት ካምፕ በመሠረተባቸው እና በሚቆጣጠራቸው ከተሞች አካባቢ የተፈፀሙ ቢሆንም፤ ባለሙያዎች የከተማ ነዋሪዎች የተሻለ ግንዛቤ እና የጤና አገልግሎት ስለሚያገኙ ጥቃቶችን ሪፖርት የማድረግ አዝማሚያቸው ከፍ ያለ ነው ይላሉ።»
«ቢቢሲ በፋኖ ኃይሎች የጥቃት ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎችን ተዋጊዎቹ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ባለው ገደብ ምክንያት ማግኘት አልቻለም። የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቢሮ ሰኔ 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው የግጭት ዓውድ ሕፃናት ላይ ጨምሮ ወሲባዊ ጥቃቶች የተፈፀሙት በመከላከያ ሠራዊት ነው ብሏል።»
«ቢቢሲ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለቀረቡበት ክሶች እና ወቀሳዎች ምላሽ እንዲሰጥ የጠየቀ ሲሆን፤ ከወራት መጠበቅ በኋላ ምላሽ አላገኘም። ቢቢሲ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።»
«የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል ሰብሳቢ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ አስረስ ማረ ለቢቢሲ ተዋጊዎቻቸው የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ስለመፈፀማቸው እውቅና እንደሌላቸው እና የቀረበባቸው ክስም እንደሌለ ተናግረዋል። ምክትል ሰብሳቢው አክለውም ወሲባዊ ጥቃት የፈፀመ ተዋጊ "ያለርኅራሄ" እስከ ሞት የሚያደርስ ቅጣት የሚጥል ሕግ እንዳላቸው ገልፀዋል።»
«ቢቢሲ በመንግሥት የተፈቀደ እና በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የሚመራ ቡድን ከግጭቱ ጋር ተያይዞ በሴቶች ላይ የደረሰውን ወሲባዊ ጥቃት እያጠና እንደሆነ እና የግኝቱ ውጤትም በሚቀጥሉት ወራት ይፋ እንደሚሆን ማወቅ ችሏል። በ2013 ዓ.ም. በትግራይ ጦርነት ወቅት ፋኖን ጨምሮ በመከላከያ ሠራዊት እና በአጋሮቹ ላይ ተመሳሳይ ክስ ሲቀርብ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት አስገድዶ መድፈርን በማውገዝ ክሱን "አድሏአዊ እና ጉድለት ያለበት" በሚል ውድቅ አድርጎታል።»
«እስካሁን ድረስ አጥቂዎች ላይ የተወሰደ ይፋዊ እርምጃ ስለመኖሩ ለሕዝብ አልተገለፀም። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀጣይነት ያለው ከባድ የተጠያቂነት ቸግር እንዳለ ስጋቱን በተደጋጋሚ አስታውቋል። የተቋሙ ተመራማሪ ሃይማኖት አሸናፊ "አጥቂዎችን ወደ ፍትሕ ለማምጣት ትርጉም ያለው ጥረት የለም" ይላሉ። "እስካሁን ድረስ እየተዋጉ ነው፤ ለፈፀሙት ጥቃት ካለምንም ቅጣት እስካሁን እየተንቀሳቀሱ ነው። . . .ሕይወት የሚቀይር ጥቃት የተፈፀመባቸው ተጎጂዎች ፍትሕ ያስፈልጋቸዋል" ብለዋል።
«ለእናት ጥቃቱ ያስከተለባት ፈተና ብዙ ነው። ጥቃቱ ከተፈፀመባት ከአንድ ወር በኋላ የደረሰባትን የአእምሮ ቁስለት ለማምለጥ መንደሯን ለቅቃ ተሰድዳለች። ከዚያም ግን ከጥቃቱ መፀነሷን ተረድታለች። "ያስመልሰኝ ጀመር" ስትል ታስታውሳለች።»
«እናት ፅንሱን ለማቋረጥ አስባ ነበር። በኢትዮጵያ የመድፈር ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እስከ 12 ሳምንት እርግዝና ድረስ ፅንስ ማቋረጥ በሕግ የተፈቀደ ነው። "እግዚአብሔርን ፈራሁ። እናቴም አሳዘነችኝ። ብሞትባት ምን ትሆናለች?" ትላለች እናት የሕይወቷን አጣብቂኝ ምርጫ ስታብራራ።»
«በመጨረሻም እናት ባለፈው ዓመት ነሐሴ መጨረሻ ላይ ከሦስት ቀናት ምጥ በኋላ ሴት ልጅ ተገላግላለች። ምንም እንኳ እናት ልጇ የደረሰባት የመድፈር ጥቃት ውጤት ብትሆንም፤ "የእግዚአብሔር ስጦታ" አድርጋ ትመለከታታለች። ይሁን እንጂ አሁን ላይ እናት ከዘመድ ተጠግታ የምትኖር ሲሆን፤ ልጇን መንከባከብ ስላለባት ሥራ መሥራት አትችልም። እናት ልጇን ለማሳደግ እና ራሷን ለማስተዳደር የወደፊቱ ጊዜ ያስጨንቃታል።»
"ይህ መኖር ከተባለ አዎ እየኖርኩ ነው" ስትል ታክላለች።

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ