ዘመንን ያናገረ ድንቅ ሰብዕና #ሐዋርያ ነው፤ #ቅኔበቃናየቀና። የሰዋዊነት ካፒቴንም ነው ልክ እንደ ክቡር (ዶር)ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ።

 

ዘመንን ያናገረ ድንቅ ሰብዕና #ሐዋርያ ነው፤ #ቅኔበቃናየቀና። የሰዋዊነት ካፒቴንም ነው ልክ እንደ ክቡር (ዶር)ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ።
 
አቤቱ ኢትዮጵያዊው #NBC ይቅርታ ጠይቅ። መራራ ስንብት የሙዚቃ ድግስን ስለሚጸየፍ። 
 
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
 
 
 
 
ጤና ይስጥልኝ ቤተ ቅንነት? እንደምን ሰነበታችሁ? እኔ አምላኬ ክብሩ ይስፋ ደህና ነኝ።
 
ሰሞኑን #ተግ ብዬ ነበር። ምክንያቴ ኢትዮጵያ የውስጧን #ቅኔበቃናየቀናውን ልጇን ሞት ስለወሰደባት ነበር። የሆነ ሆኖ በኢትዮጵያ ህዝብ የእኛ ሃዘን ብሎ የተቀበለበት ዕውነት የእናቱን የልዕልት ኢትዮጵያ ኦርጋኒክ ተፈጥሮን ያነበበ፤ የተረጎመ፤ ያመሳጠረ ክስተት ነበር።
 
የዘመኑ የኢትዮጵያ ልጆች በብሄራዊ ሰንደቅ፤ በታሪክ፤ በብሄራዊ መዝሙር፤ በዞግ፤ በወሰን፤ በሃይማኖት፤ ከዚህም ባለፈ በቀጨር መጨሬው የነበረው ጉጉስ #በአደቧ#በአቅሏ#በዋርካዋ ዋርካ የሚለውን ትምህርተ ጥቅስ ያላስገባሁት በጽኑ መታመማቸውን ስሰማ እራሴው የፃፍኩት ኃይለ ቃል ስለሆነ ነው። የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያ አደብ፤ የኢትዮጵያ አቅልን በሥጋ መለየት በሚመለከት ሃዘኑ እኩል ስለሆነ መጽናናቱን ለሁላችን ይስጠን ፈጣሪያችን // አላሃችን። አሜን። የኢትዮጵያም የምር ሃዘኗ ነው እና እናት ዓለም ሆዴ እግዚአብሄር ያጽናሽ። አሜን።
 
አንድ መንግሥታዊ ሥርዓት በሚወስዳቸው ማናቸውም እርምጃወች ቀድሞ የጨመተውን ማህረሰብ ዕይታ ማጥናት ይገባዋል። ሪሰርች ሊሠራ ይገባዋል። ውድቀትን ስለሚያመጣ። የክቡር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ (ዶር) ከሃላፊነታቸው መገለል ወይንም የተገለሉበት ሂደት በምን ያህል ልክ ኢትዮጵያውያንን ከህሊና አሳዝኖ እንደ ነበር በሰሞናቱ ክስተት መገምገም ይቻላል። 
 
ምድር አፍ አውጥታ፤ ዕንባዋን #ዘልላ ምስክርነቷን የሰጠችበት አጋጣሚ ነበር። ይህ ታላቅ ክስተት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ሁሉም ግምትም፤ ዕውቅናም የማይሰጡት የጨመተው ማህረሰብ ያለውን የተጽዕኖ ፈጣሪነት አቅም ያዬንበት ገጠመኝ ነው። ስሜትን፤ ፍላጎትን፤ ዕይታ በአንድ አቅጣጫ አስተባብሮ እና አዋህዶ የመራ የተፈጥሯዊነት የውሃ ልክ ነበር። ከውስጥ ለውስጥ የተሰጠው ክብር ፌክ አልነበረም። የጸዳ እና ስኩን ደርባባ ነበር። ጉልላትም። 
 
ይህ ክስተት እራሱን ችሎ የማስተማሪያ ክስተት ነው። በዚህ አጋጣሚ ሁላችን ያስማማ ዕጹብ ሰብዕና ነውና ትምህርት ሚኒስተር የኢትዮጵያው በመማሪያ መፃህፍት ውስጥም ሊካተተው ይገባል። አርያነቱ ብቁ ነውና። ክስተቱ የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን የተደራጀበት ሁነትን ቁሞ አስተምሯል። የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጣችን ይህ ነው ብሎ እራሱን ገልጦ አሳይቷል። ሁሉም ነው የደነገጠው። ሁሉም ነው በእኩልነት ከውስጡ ያዘነው። ስደት ላይ ያለሁት እኔ ዕንባዬ ሲፈስ ፈቃዴን አልጠየቀም።
 
መሪነት ለህዝብ ቅርብነት ስለመሆኑ ያረጋገጠ የዘመናችን #ዕውነት ይህ ነው። የኢትዮጵያ የምክክርኮሚሽኑ ድካም እና የተቋቋመበት ዓላማ፤ የሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ፤ ያለው እሰጣ ገባ ሁሉ ስመዝነው መንገዱን ያላገኜ ሁነት ነው የታየኝ። ኢትዮጵያውያንን የልብ ማዕከል ለማግኜት ይህ ክስተት በቂ ነውና። 
 
የኢትዮጵያ ህዝብ በእናት አገሩ ተፈጥሮ ልክ የሆነ ሰብዕና ሲያገኝ ለፍቅሩ፤ ለክብሩ ወደርም፤ ደንበርም የለውም። ስጦታው የላይኛው የአማኑኤል የአላህ ነውና። ስጦታውን ያወቀ እና ያከበረ ህዝብ የተሰጠውን ለመስጠት #ንፋግ አይደለም። የተሰጠው ምን ይሆን? ካሉ ምርቃት፤ በረከት ነው። 
 
የኢትዮጵያ ህዝብ ለጭዋ ወገኖቹ፤ የምድሩንም የሰማዩንም ህግ አክብረው በተሰጣቸው ልክ የአደብ፤ የአቅል ኢኒስቲቲዩት ለከፈቱ ነብያቶቹ ለልቅናቸው #ይሁንታውን፤ ለድርጊታዊ ክህሎታቸው #እሺ ባይነቱ በራሱ ዓራት ዓይናማ ነው እንዲህ ያሳያል። የዘመን መስታውት ነውና። " እስላም አይገዛነም፤ አማራ ወይንም ኦሮሞ፤ ወይንም ተጋሩ፤ ወይንም ሶማሌ ወይንም አፋር ወይንም ወላይታ፤ ጋሞ፤ ጉምዝ አያስተዳድረነም" የሚሉ ተለጣፊ የሆነ የሰነፎች ዕይታ የኢትዮጵያ ህዝብ መሻት አይደለም። አደቡ፤ አቅሉ፤ አቅሙ፤ ብቃቱ፤ እርጋታው፤ በተፈጠረበት ልክ ሆኖ፤ ህግ አክባሪነቱ ከአሰባሳቢነቱ ጋር ያለው ሰብዕናን ጨዋው የኢትዮጵያ ህዝብ ካገኜ በራሱ አሸናፊ ሆኖ እንዲህ ይወጣል። 
 
አባት ሙፍቲ ቅንነታቸው፤ የሰላም አባትነታቸው ሥልጣን ላይ እያሉም፤ ተገለውም፤ ጥሞና ላይ ሳሉም፤ አሁን በሥጋ ሲለዩንም በዓይናችን ዓየን። ቅንነት ካለ ድልም፤ ተቀባይነት በላቀ አክብሮትም ሁሉም ይኖራል። የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳንስ በልስልስ አንደበታቸው ብቻም ሳይሆን በምግባረ - ድርጊታቸው፤ በሞራላዊ ልዕልናቸው የሚያውቃቸውን ሃጂን ቀርቶ፤ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ፕሮፖጋንዲስት፤ ካድሬ አላስፈለገውም ነበር። ዶር አብይ አህመድ አሊ ሳይታወቁ በገፍ ተደገፋ። ይህን በዘመናችን አይተናል እኮ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለፍቅር ተፈጥሮ እራሱ ነብይም፤ ሐዋርያም ነውና። 
 
ሁሉም የሚዲያ ዓይነት ሁሉ በአንድነት ነበር ሃዘኑን የተጋራው። ብዙ ታዋቂ፤ ተጽዕኖ ፈጣሪወች፤ ቴሌኮምን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ጨምሮ ሃዘናቸውን በዕውነት ስለ ዕውነት በንጽህና ገልጸዋል። #ከNBC ኢትዮጵያ በስተቀር። #NBC ኢትዮጵያ #ላይፍ ላይ የሙዚቃ ውድድር ነበረው። እርዕሱን ነው ያዬሁት። #ሰቀጠጠኝ። 
 
NBC ሚዲያው ዓለም ዓቀፍ ሁነቶችን ስለሚዳስስ የምከታተለው ሚዲያ ነው። የሆነ ሆኖ ሰሞኑን የፈጸመው ግድፈት ግን ነውር ነበር። #ይቅርታ የኢትዮጵያን ህዝብ ቢጠይቅ ጥሩ ነው። ካለ ልዩነት በስምምነት ካለምንም አስገዳጅ ኃይል፤ የመንፈሳችን አህታዊ ሰዋዊ እና ተፈጥሯዊ መሪ ህልፈት በሙዚቃ ውድድር ምሽት መታጀብ ስለለበት። ባህላችንም አይደለም። እኒህ አባት የመልካምነት አብነት ናቸው። #አገርም ናቸው። በ100 ዓመት ውስጥ የማይገኙም ናቸው። NBC የአንድ ቀን ፕሮግራሙ ቢስተጓጎል ምን ይኮናል። እኔ ውስጤ ቁስል ነው ያለው። እግዚአብሄርም ክፍት ይለዋል። ቅብዓ ከእሱ ዘንድ ነውና።
 
የግድ እኮ #መሪነት #በፕሮቶኮል መጠበቅ አይኖርበትም። የክቡር ተቀዳሚ ሙፍቲ ዝምታቸው እራሱ መምህር ነበር። በየትኛውም ሁኔታ የተገለሉ ወይንም የተገፋ ሰብዕናወች መከፋታቸውን በብስጭት፤ በቁጣ ሊገልጹ ይችላሉ። ይህን በክቡርነታቸው ሰብዕና ውስጥ አላየነም። ኩርፊያ፤ አድማ፤ ግሳፄ ሆነ እርግማንም አላዳመጥነም።
 
ክቡር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ (ዶር) ሁሉን ነገር በአርምሞ፤ #በጥሞና ነው የያዙት። ኃላፊነት ላይ እያሉም ሆነ ከሃላፊነት ሲገለሉ ጭምትነታቸው በፍጹም ልቤ የተቀበልኩበት አመክንዮ ነው። መከበርን አስከብሮ ማስቀጠል የዊዝደም #ዓይነታ ነው። ደልዳላው አባት፤ ታጋሹ አባት ብዙ በጣም ብዙ ፍሬ ነገር አስተምረዋል። ኢትዮጵያን ቁምነገር የማድረግ ዓላማ ማለትም በትክክል ይህ ነው። 
 
እንደዚህ ስክን ያሉ፤ እንደዚህ ውስጣቸው ሰላም የሰፈነበት ሰብዕና ያላቸው ወገኖች ለኢትዮጵያ ሆነ ለትውልድ ሽልማት ልዩም ስጦታ ናቸውና። ለዚህም ነው እኔ የሃዘኑን ዜና ስሰማ የኢትዮጵያ #አደብ፤ የኢትዮጵያ #አቅል ብየ የፃፍኩት። ሰሞናቱን ቀጥ አድርጎ፤ ትርምስምሱን፤ ወጣ ገባውን ቀጥቶ፤ ጎርበጥባጣውን የኢትዮጵያ ፖለቲካውን ገርቶ፤ #ጥላቻን አስታግሶ፤ ልዩነትን #አሳፍሮ ዕውነትን አፍልቆ፤ #እኛነትን አስፈንድቆ፤ ህብራዊነትን አስጊጦ እንደ ትናንቱ ዛሬን ኢትዮጵያንእና ኢትዮጵያዊነትን በአንቱታ ያቀለመ ክስተት ነው ሃዘኑ እራሱ የፈጠረው።
 
ሐዋርያነት ብቻ ሳይሆን እኔ ያስተዋልኩት የአብነት #አርበኝነትንም ጭምር ነው። ለዚህም ነው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም የሃዘኑ ታዳሚ የሆነው ለዛውም በንጹህ ልቦና ሆኖ የታየው። የታደሉ አባት ናቸው። ኢትዮጵያን ሚስጢሯን ያገኙ። ኢትዮጵያ ያልከበደቻቸው። ኢትዮጵያን የማንበብ ሙሉ አቅም የነበራቸው። ኢትዮጵያን የመተርጎም ብቃት የተሰጣቸው። ኢትዮጵያን የማመሳጠር ልዩ ምርቃት የታደላቸው። የአንድነት አርበኛ። 
 
ሰላማችን ናቸው እናአምላካችን እና ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ነፍሳቸውን በሰላም ያሳርፍልን።ሃዘኑ ወላዊ ነውና ስለመልካምነት ለሚጨንቃቸው ቅናውያን ሁሉ መጽናናትን እመኛለሁኝ። አሜን።
 
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ለሥልጣን የምትፎካከሩ ከሂደቱ ብትማሩበት መልካም ነው። የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽንም እንዲሁ ከድካሙ ታግሶ ፍሬነገሮችን ቢመረምር የውስጥነት አድራሻ ማግኜት የሚችል ይመስለኛል። ለዕውነታዊ ግልጽነት ማገዶ አያስፈልግም።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን። 
 
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን፤ አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ አሜን።
የመጽናናት ጊዜ ይሁንልን።አሜን።
 
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
22/10/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ጋራጅ ሆነ ወጌሻ አያስፈልገውም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

የእኔ እማ ልዕልቴ እንዴት ነሽ?

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።