ኢትዮጵያ የገነፈለ ሁሉ #ፍላት ማጠራቀሚያ በርሚል አይደለችም። ሁልጊዜም "ማህረቤን ያያችሁ" ሰለቸን። ገለማን!
ኢትዮጵያ የገነፈለ ሁሉ #ፍላት ማጠራቀሚያ በርሚል አይደለችም። ሁልጊዜም "ማህረቤን ያያችሁ" ሰለቸን። ገለማን!
#ምዕራፍ ፲፯
#ጠብታ።
የኢትዮጵያን ልኳን በልኳ ልክ መጠኖ መነሳት ይገባል። ለኢትዮጵያ የክት እና የዘወትር፤ የእዳሪ እና የቤት፤ ምርጥ ዘር እና አልባሌ፤ ዓይነታ እና አሰርውሃ የሚባል ጉዳይ የለም። የዜግነት እርቦ እና ሲሶ የለውምና። ሺ ሚሊዮን ጊዜ ይመስጠር፤ ይከደን የሃቅ አቅም ይንደዋል። ሁልጊዜ ልበጣ በስልቃ #ቃ ያለ ጉዞ ነውና።
#ኢትዮጵያ ለከበደችው ስኬቱ አይደለም ተሸፍኖ፤ ገሃድ ሆኖም ጋዳ ነው፤ ገድጋዳ - ገዳዳም።
ሰሞኑን የልጅ ሞገስ ሚዲያ እንደ ነገረን፥ ሰነዱንም አንብቦልናል፤ አሜሪካ ላይ የተቋቋመው ልክ ግንቦት 7 "አገር ማዳን" በሚል ለዛውም ግለሰቦችን ሳይሆን ግንቦቲዝም ተቋማትን ነበር ያሰባሰበው። ያው በአሰልቺው ድግግሞሽ "ኢትዮጵያን ማዳን" በሚል እራሱን #የፈራ፤ እራሱን የሸሸ ቡድን "አገርን ስለማዳን" ቅርንጫፋን አውሮፓ አምስተርዳም ላይ እንደ ፈጠረ ዜናውን ነግሮናል።
ልጅ ሞገስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ በትጋት እየተሳተፈ፤ አውሮፓ ተቀምጦ ስለምን እንዳላከሉት አላውቅም። የሆነ ሆኖ በግልጽ ቀርቦ ቀጥተኛ ፍላጎትን፤ ዓላማ እና ግብን ማሳወቅ የቲሙ መብት ሳይሆን ግዴታው ነው።
እነኝህ ክንብንብ ያሰኛቸው እነማን ናቸው??? ኢትዮጵያ እኮ ሉዓላዊ የተከበረች አገር ናት። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ዕውቅና ላላት አገር፤ በገሃድ ላለች፤ ዓለም በብዙ ሁነቶች ለሚያውቃት ቀደምት አገር በስውር ቲም ትንሳኤሽን እናመጣለን #ጠብቂኝ የገበጣ ጨዋታ ነው። የተኮረኮደ - ገጠመኝ። እንደ ታደሉት ባንሆን፤ ድምጽ የመስጠት መብቱ ባይኖር እንኳን ቢያንስ ማነህ? ማን ትሰኛለህ ለሚለው ምላሽ የምንሻ ዜጎች አለን። ንቀት የትም አያደርስም። የናቀ ፖለቲከኛ መጨረሻው ታይቷል።
ሚሊዮኖች ተስፋ ያደረጉት፤ በብዙ ሁነት አቅም የነበረው ግንቦት 7 እንኳን ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ሞክሮ እግዚአብሄር የወደደው ነው የተፈጸመው። በቃ! ከጥዋት ከማታ ያልታሰበ "የሱሴ" ማዕበል ነው ቀን ያወጣው። እንኳንስ ተቋም የለሽ፤ ግንፍል ግንፍል የቁጣ ይሁን - የምቀኝነት፤ የምቀኝነት ይሁን - የቅናት መንፈስ በሚዘውራቸው ሰብዕናወች ተመርቶ ለድል ሊበቃ ቀርቶ።
ትክንክን ፡- እርር የሚሉ ወገኖቼን ሳይ ለጤናቸው አስባለሁኝ። የውነቴን። የሆነ ሆኖ ልጅ ሞገስ ዘውዱ ሥማቸውን አውቆ ከገለፃቸው ውስጥ አንድ ሰከን ያለ ሰብዕና ሥም ሰምቻለሁኝ። እሳቸው እራሱ በዛው ሰሞን አንከር ሚዲያ ላይ ቀርበው በነበራቸው ቆይታ እንደ አብነት እማዬውን ሰብዕናቸውን ፈልጌ ማግኜት አልቻልኩም።
ከልቤ ነው የምነግራችሁ፤ ለክፋ ቀን ይሆናሉ ብየ በጽኑ የማስባቸው ትልቅ ሰው ጠቅላይ ሚኒስተሩን እንደ ሌላው አንጠልጥለው በተደጋጋሚ ሲጠሩ ነው የሰማኋቸው። #ደንግጫለሁኝ። ሰው ቢነግረኝ ፈጽሞ አላምንም ነበር። በጣም በብዙ የመሰከርንላቸው ጠንካራ ሰብዕና በምን ሁነት እንደምን እንደዚህ ቅይር እንዳሉ አላውቅም። ሰው አይበርክትላችሁ ተብለን ተረግመናል። የሆነ ሆኖ ከሳቸው ውጪ የሚኖረው የተለመደው በተለመደው መንገድ ነው፤ ሁልጊዜ እንደ ሽንብራ ቂጣ መገላባበጥ። መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ ብለናል ………
እርግጥ ነው ከምንም የማይሻል ነገር ስለለ መሞከሩ ባይከፋም፤ በወደቀ ተመሳሳይ መንገድ ተሂዶ የሚታፈስ ድል የለም። ኑሮም አያውቅም። #አያ #እንቶኔ፤ #አያ #እከሌ፤ #እንትን እና #እንትን ተጣምሮም ወይንም ተባዝቶም በዚህ የዲችታል ዘመን የኢትዮጵያን ትንሳኤን ያሳካል የሚል ዕሳቤ ከጥንስሱ ቀጭጮ ነው የሚቀረው፤ ወይንም ጨንግፎ።
ለምን? አኩራፊው ብዙ ነው፤ መሰናክሉም ያን ያህል። በማይታወቅ ዓላማ እና ግብ የተጠቀለለ፤ ለዛውም በፍፁም #አግላይ ሁነት ስኬት እጅግ በጣም #ሩቅ ነው። ሰነዱ በልጅ ሞገስ ተነቧል። መታመን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ቤት ነው። እነማን እንደሆኑ ልጅ ሞገስ ባይነግረንም ጎርፍ አምጥቶ ደለል ላልሰራብን ሰብዕናወች እንተዋወቃለን። አውሮፓ ብርድ ስለሆነ ዴክሉ ይሙቃቸው ብርድ እያመጣ ነውና። መጠቅለሉ ከጠቀመ "ይታያል ጉዱ የቤተዘመዱ" ነው።
በአመዛኙ አፍቅሮተ ህወሃት ልባቸውን ጥፍት ያደረገው ናቸው። ለእነሱ ደግሞ ይለፍ የማይሰጡ የጨመቱ ልጆች ኢትዮጵያ አላት። ለምንም ዓይነት ድርድር አይቀርብም የነገረ - ህወሃት ዳግሚያ ትንሳኤ በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥርዓት መንበረኛ የመሆን ህልም። ሙሉ ዕድሜ እና ሙሉ የወጣትነት ዘመን የተገበረበት አመክንዮን ቤንዚን አርከፍክፎ የሚያቃጥል #ዕብን የለምና። በዚህ የዘበጠ መንገድ እና ዳጥ የሚገኝ ተረፈ ዕሴት ቢኖር ሰባራ ገልነት ነው። ሰባራ ገል ደግሞ ለእሳት መጫሪያ ብቻ ነው የሚሆነው።
#ሌላው ……
ሌላው አንከር ሚዲያ ከዶር ዮናስ ብሩ ጋር ጠንከር ያለ ውይይት አካሂዶ ነበር። "አብይዝም ይሸኝ እንጂ ትርፋ ገብስ ነው" የአንከር ሚዲያ አዘጋጅ የልጅ መሳይ አቋም ነው። ያው ዶር. ዮናስ ብሩ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ቀጥተኛ፤ ግልጽ እና ጠንካራ ዕይታቸውን አቅርበዋል። የአንከር ሚዲያ ይሁን የአዘጋጁ የግል ዕይታ "ብቻ አብይዝም ይወገድ" ይህም ተሞክሮ የወደቀ አመክንዮ ነው።
"ህወሃት ይውረድ እንጂ" ተብሎ የታፈሰው ምን እንደሆን ታይቷል። ተመዝኗል። ተገምግሟል። ያን ጊዜ በዘመነ ግንቦት 7 እርምት ይሰጡ የነበሩት ድምጾች ተደምጠው ቢሆን ኖሮ …?? ብሎ በጥልቀት ማሰብ ይገባል። በዘመነ ቅንጅት ፓርላማ ተገብቶ ቢሆን ኖሮ? አዲስ አበባን ቅንጅት ተረክቦ ቢሆን ኖሮ????
ቢያንስ የፊደል ገበታ ቢሆን ምን አለበት። ሁልጊዜ ጸጸትን መሰነቅ ብቻውን ለዘላቂ መፍትሄ አይረዳም። ከቅንጅት ጀምሮ ያለው ጊዜ ክህሎትን አመንጭቶ ለስኬት አላበቃም። ውጥን። ጭንግፍ። በቃ ያዬነው፤ የሰማነው ይህ ነው።
ሁልጊዜም ግንፍል ግንፍል በሚል ስሜት ይወጠናል፤ መንገድ ላይ ይጨነግፋል። ለዛውም የወይራ፤ የአባሎ፤ የክትክታ፤ የዋንዛ እንጨት አይደለም፤ የሰው ልጅ ነው የሚማገደው። ኢትዮጵያዊ ትውልድ ነው የሚታጨደው። የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ልጅ በፋመ ትግል ገብቶ ሰማዕትነትን ሲቀበል አልታየም። ዱር ቤቴ ያሉት የቅርባቸው ሊኖር ይችላል።
የሆነ ሆኖ ያው የድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ እናቶች ማህጸን ነው ለዘወትር #ቄራነት የሚታሰበው። አሁን ከመሼ እንኳን በተቋቋሙ ሰላማዊ ድርጅቶች ስንት ባለተስፋ ወጣቶች አሳር አዩ???? ለትውልድ ይታዘን። የማይችሉ አርፈው ቢቀመጡ ቢያንስ ሰብአዊነት ነው። ሁልጊዜም ተማገዱልን ይሉኝታ ቢስነትም ነው። ለዛውም በተሰወረ ፍላጎት። "#ማህረሜን ያያችሁ" በሉልን።
የሆነ ሆኖ ባልጠራ መርኽ፤ ቅጥ መጠኑ ባልታወቅ ግብ፤ በድፍርስርስ ግንኙነት፤ እራሳቸውን ባልገለጹ ሰብዕናወች ሌላ - ሞት፤ ሌላ ግብግብ፤ ሌላ - እልቂት ማጨት የተገባ አይመስለኝም። ለማይታወቅ፤ ላልተፈተሸ ለተጠቀለለ ስውር ኃይል ይሁን፤ እሺ ቢባል ካለው የባሰ እንጂ የተሻለ ዕድል አይኖርም። ለዛውም ዕድሉን ካገኜ ነው። ጭምቱ ማህበረሰብ #ይለፋን ከመረቀ።
ጭምቱ ማህበረሰብ አቅሙን አያባክንም። በዝምታ ይቆያል። #ጐሏን ግን ያስገባል። የልቡን የሚያደርስ ወይንም ያደርሳል የሚል ዕሳቤ ከገጠመው። ከሰሞኑ እንኳን የክቡር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ (ዶር) በሥጋ መለየት የነበረው የሃዘን ድባብ ልኩን መመዘን ይገባል። የማይፈልጉት ሚዲያወች ሁሉ የድባቡ ጫና ልዩ ፕሮግራም እንዲያዘጋጁ አድርጓቸዋል።
ኢትዮጵያ መንግሥት ያስፈልጋታል። በዚህ ግልጽ አቋም መያዝ ያስፈልጋል። ከችግሩ ለመውጣት የመፍትሄ መንገዱ ያለውን የብልጽግና ሥርዓት ዕውቅና ሰጥቶ የመፍትሄው አካል አድርጎ መነሳትን ይጠይቃል። አናንቆ፤ አጃጅሎ ወይንም አጣጥሎ የሚሆን አይደለም። ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን ህዝብ በላይ አላት ይባላል። ለእኔ ይህ ህዝብ ከ80 በላይ ብሄረሰብ የሚለውን የሚሽር ይመስለኛል። ሁሉም የራሱ ጌታ ነው። ሁሉም የሹም ዶሮ ነው። ስለሆነም ብርቱ ጥንቃቄ፤ የበሰለ የፖለቲካ ጥበብ ይጠይቃል። ማን ተሸኝቶ --- ማን ጉብ ሊል???? በማን ማገዶነት ማን ሊፍነሸነሽ?????
ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ ብትሆን ስንት ነገር #ሊናድ እንደሚችል ማሰብ ይገባል። ማዕከላዊ አመራር የሌለው ማንኛውም ሥብስብ የሚፈጥረው #ሥርዓተ #አልበኝነትን ነው።
ይህን ፋኖን እመራለሁ ብሎ ሲነሳ አቤቱ ባልደራስ ከመነሻው ብሄራዊ ያልሆነ ስለነበር ፤ ባልደራስ የአዲስ አበባ ብቻ ስለሆነ፤ አፋርም አማራ ክልል ሲሄድ አመራሩ ማኒፌስታችሁን የቡና መጠቅለያ መጋዚን አታድርጉት፤ አንብቡት። የሥልጣን እርከናችሁ ከአዲስ አበባ ውጭ አይደለም። በተጨማሪም ፋኖን ለመምራትም ሁነቱ አይፈቅድም ተው።
ሰብዕና - ለውትድርና፤ ሰብዕና - ለፖለቲካ መሪነት፤ ሰብዕና - ለህክምና ሙያተኝነት፤ ሰብዕና - ለክህነት፤ ሰብዕና - ለመምህርነት ……… ይጠይቃል። መቀባትም። ጭራሽ ሰብዕናቸው ለሚሊተር ያልሆኑ እንደምን እና እንዴትም ረጅሙን ፈታኝ የትጥቅ ትግልን አደራጅቶ ለመምራት መታሰቡ በራሱ ጋዳ ስለነበር አስቀድሜ ነው የተናገርኩት። ስንት የተደከመበት የአማራ የማንነት እና የህልውና ተጋድሎ እንዲህ እና እንዲያ። ያቆስላል። ስንት ብልህ አቅም ሰብሰብ ብሎ ተቀምጧል።
ስለሆነም የከተማ ድርጅቶች ለተደራጁበት የሥራ ቦታ ሊሆኑ ይገባ ነበር። ይህ ከተዘለለ አናርኪዝም ነው ተው ብዬ ዘለግ አድርጌ ጽፌም ነበር። የፋኖን ተፈጥሮም ከበዓቱ - ከነተፈጥሮው ስለማውቀው ለዘላቂ ትግል እና ስኬት በማዕከላዊ አመራር ለማምጣትም ጋዳ ሊሆን እንደሚችል አበክሬ አስገንዝቤ ነበር። አውዲዮም ሠርቻለሁኝ፤ በብዙ ተቆጥቤ ከቆየሁ በኋላ። የፋኖ አደረጃጀት ቀያዊ ነውና። ቤተ- ዘመዳዊም ሊሆን ይችላል። ማን ቢወልድ ማን አለበት። ትልቅ ሠራዊት ካለ ማዕከላዊ አመራር ይከብዳል። የሚፈታተነው ብዙ ክስተት ስለሚኖር። እኔ ገበሬ አደራጅም ነበርኩኝ። ጫካዋ ጋርም እንተዋወቃለን። ላም እረኛ ምን አለ? አልተደመጠም።
ግብረ መልሱ ስንት ህዝብ አልቆ፤ ስንት ቅርስ ወድሞ፤ የአማራ ክልሉ ድቅቅ ብሎ፤ የሚያሳሱ፤ የሚያስጎመጁ ቀንበጦች ረግፈው፤ መሪወችም እነሱም ከሰውነት ተራ ወጥተው፤ ቤተሰብም በጭንቀት ተንገላቶ፤ ስንት ተማሪ ከትምህርት ገበታው ታቅቦ፤ ዛሬ እምናዳምጣቸው እጅግ አሰቃቂ ገጠመኞች ምንጩ ከመነሻው የአደረጃጀት፤ የአመራር ዝበት ነበረበት።
ማድመጥ እንደምን ያቅታል? "እግዚአብሄር በአንድም በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።" የሆነ ሆኖ ነፍስን ይዞ መውጣት ከተቻለም እሰየው ነው። ያልተቻለን ነገር ማስቻል ባይቻል እራስን ማትረፍን መቻል አንድ ነገር ነው። መሸነፍ አይደለም ህይወትን ለማትረፍ በብልህነት መወሰን። ቢያንስ ለቤተሰብ መኖር ተስፋ ነው።
ለወደፊትም ሥርዓተ አልበኝነት በተመለከተ በአደብ ውይይት ሊደረግበት ይገባል። በአጀንዳ ደረጃ። የሥርዓተ ዕሳቤ ቁጭ ብሎ መወያዬት ይጠይቃል። ሁሉም ፖለቲከኞች ሥልጣን ላይ ያለው አይዋ ብልጽግናም፤ ለስላሳ ተፎካካሪወች ይሁኑ ጽኑ ተቃዋሚወችም በየትኛውም ሁነት ሥርዓተ አልበኝነት እንዳይከሰት ጥንቅቅ ያለ ውይይት ሊያደርጉበት ይገባል።
ሥርዓት አልበኝነት የሚያጠቃው ህፃናትን፤ ሴቶችን፤ አዛውንታትን፤ የአካል እክል የገጠማቸውን፤ አልጋ ላይ የዋሉ ህሙማንን፤ በጥቂት ሁነት በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ወገኖችን ነው፥ ቋሚ ገቢ የሌላቸውን፤ ቀጥተኛ ተጠቂ የሚያደርገው። በተለይ የህፃናት መደፈር እና ማለፋቸው እጅግ የሚሰቀጥጥ ብቻ ሳይሆን በአገር ጉዳይ ለምንተጋ ወገኖች ሃፍረትም ነው። በእኛ ዘመን እንዲህ ዓይነት የላሸቀ ጨቀጨቅ ገጠመኝን ማረቅ ሳይቻል መቅረት እጅግ አሳዛኙ ገጠመኝ ነው። "የዝብሪት ቤት ሳይዘጋ ያድራል" እንደተባለው ነው የሆነው። ጠያቂም ተጠያቂም የለም። ሰቀቀኑ - ይደመጣል፤ ማን የት ሙሉ መረጃ የለም። ህዝባችን ተሰቃዬ። ስለሆነም ለወደፊቱም በዚህ ዙሪያ ጥንቅቅ ያለ፤ ጠፈፍ ያለ የህሊና መሰናዶ እና የተግባር እርምጃ መውሰድ ይጠይቃል።
በተነቃነቀው ልክ የሚደፍን ህገ - ሥርዓትን ይምራን ማለት ያስፈልጋል። ህዝብ ጠባቂ ያስፈልገዋል። በግልብልብ ሁነት የሚከወን ማናቸውም ክስተት "ድሮ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ወጪት ጥዶ ማልቀስ።" ያመጣል። ዕውን ለሰው ልጅ እንደ ሰውነት የሚታሰብ፤ የሚታዘን ከሆነ ብርቱ ጥንቃቄ ለማድረግ መሰናዳት ያስፈልጋል። እልህ፤ ቁጭት፤ ብስጭት ከሚያመጡ የአነጋገር ዘይቤወች ሁሉ መታቀብ ያስፈልጋል አገር ለመምራት እራሱን በግል ይሁን በህብረት ላጨ።
#ለቀጣዩ ተስፋ እነማን ይሆኑ የታጩት?
ጸረ ሰው እነ አቶ እከሌ? ወይንስ ፀረ ክርስትናው እነ አያ እንቶኔ ይሆን የኢትዮጵያን ትንሳኤ // ትንሳኤውን የሚያቃርቡት? የኢትዮጵያ ህዝብ በማስተዋል ሁሉንም ዓይነት አማራጭ በጥራት እና በጥልቀት ሊገመግም ይገባል። ከችኮላ ስክነትን ቅደመኝ ማለት ይገባል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ክስተትን አክብሮ መነሳት ይጠይቃል። ማድጋ እንኳን ጆሮ አለው፦ እንኳንስ የሰው ልጅ። ስለአከበርክ ብትከበር እንጂ አትዋረድም።
ትውፊታችንም፤ ይተብኃላችንም መለያችንም የእኛ የኢትዮጵውያን አክብሮት ነው። አቶ እከሌ፤ ወሮ/ ት እከሌ፤ በሠፈር እንኳን ጋሼ እከሌ፤ በቤተዘመድ እያያ፤ ጋሻዬ፤ ክንዴ፤ እትዬ፤ እታለም ወዘተ ነው፤ እንኳንስ የአገር መሪ። ኢትዮጵያን ለመምራት ተጠሪዋ ተከብሮ ሊሆን ይገባል። የኢትዮጵያ ……… ባለ ዕዳው ያቀለለውን አሞሌ መሆን አይገባም። ኢትዮጵያ እኛ እናውቃታለን ከምንለው በላይ የከበረች ድንቅ አገር ናት። እሷን ሳያከብሩ፤ ወይንም በእሷ ተፈጥሮ ልብ ሸፍቶ መነሻው ይሁን መዳረሻው አይበረክትም። አምላክ አላት እና።
#ሌላው አቅላይነት ነው።
"ቢገፋት ይወድቃል" ከተባለ ብልጽግና ስንት ወራት አለፈው? ኧረ በሞቴ አይከብድህና አብይዝምን ገልብጠህ አሳየን ብየም ለአቶ ጃዋር ከፃፍኩኝ ስንት ወራት ተከታትለው ነጎዱ። "መንግሥት መገልበጥ ሰልችቶናል" ስለተባል። ለዛውም ባልነበረበት ቁምነገር። በህወሃት ፈቅዶ ስልጣን መልቀቅ የስንጥር ታህል አይደለም ጀዋሪዝም ያ ጠንካራው ግንቦቲዝምም እንኳን እጁ አልነበረበትም። ሻብያም አለነበረበትም። የእግዚአብሄር ጥበብ በራሱ ጊዜ የከወነው የዘመን ክስተት ነበር።
የሆነ ሆኖ በሁለቱም በኩል #አቅላይነት አስተውላለሁኝ። ይህም ቋት አይገፋም። " ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል" ይላሉ ባለቅኔወቹ ጎንደሮች። ለነገሩ ጎንደር ሲነሳ ጸጉራቸው የሚቆም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊቃናት እንዳሉ ባውቅም ዕውነት ቦታዋን ለቆ አያውቅም። ዕውነት ወረፋም ጠባቂ አይደለም። ቦታውን የለቀቀው ሽፍንፍና ነው ዘብጦም፤ ተለብጦም ይሁን ተለሙጦም የሚገኘው።
#ፈላስፊት ኢትዮጵያ ለሁላችንም ነው የከበደችን።
የኢትዮጵያ ተፈጥሮዋ ኦርጋኒክ ነው። በዛ ልክ መሆን ቁመቱም፤ ስፋቱም፤ እርዝማኔውም፤ ወርዱም የለም። እሷን ለመምራት ሁሉም እራሱን ያጫል። ለዚህ ነው በየዘመኑ በሰው ግብር ላይ የሚታቀዱ፤ ግን በማይበረክቱ ስብስቦች "አሞራው በረረ፤ ቅሉ ተሰበረን" ተስፋ ሲጋት የኖረው ህልሙ ሁሉ።
ባለ ቅኔወቹ ጎንደሮች እንደሚሉት " ረጅም ጦር ባይወጉበት ያስፈራሩበት" ከሆነ ሸጋ ነው። መሰባሰቡ ይሁን መመካከሩ። ወደ መስዋዕትነት የሚያዘነብል ከሆነ ግን፤ ለዚህ ተብሎ የሚፈሰው አቅም በተለይም ለእስር፤ ለሞት ማገዶነት የተዘጋጄ ገራገር ከኖረ ግን ቁጭ ብሎ ይሰበው።
በተለይ አገር ቤት በሰላማዊ ትግል ላይ ላሉት ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ውጭ ያለው ዴክል ካሰኜው ለእነሱማ ደንዳና ብረት ለበስ ካሊም ያስፈልጋል። ለማገዶነት በየዘመኑ የሚታጨው ትውልድም ይመዝነው። ያስላው። ያንሰላስለው። በዚህም ተባለ በዚያ ለየትኛውም የትግል ዓይነት ማገዶው ትውልዱ ነው። የኢትዮጵያ እናቶች ማህጸን ቄራነትም ሊቆም ይገባል። አሁንም እንደ ተለመደው አገር ቤትም ቅርንጫፍ አለን ተብሎ በገፍ ያ መከረኛ ህዝብ በሌለ ኑርው ላይ ለካቴና እንዳይዳረግ ስጋቴ የገዘፈ ነው። መጠንቀቅ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። ለሽፍንፍን ሽብልል መገበር ይታሰብበት እንደማለት።
#ክወና።
ግን ግን ማህበረ ኦነጎች ምን ቀረብን? ምን አጣን ብለው ይሆን ይህን ያህል በጫካም በዲያስፖራም ……… ሰልፍ ያበዙት? የአምስተርዳሙ ሰብሳቢ ናቸው አሉ ልጅ ሞገስ እንደ ነገረን። በሌላ በኩል የተስማሙበትን ሰነድም አንብቦ አስደምጠጦናል። አዬ ልጅ ሞገስ የትኛው ሰብዕና በፃፈው ///በሚጽፈው ውስጥ ተገኝቶ ያውቅና??? ይህ ጥሩ ነው ሲል ስለሰማሁት። ይበሉ ዝም ብለው።
የሆነ ሆኖ ማህበረ ኦነጎች ምን አጥተው እንዲህ እንደሚሆኑ የማይገባኝ ይህ ብቻ ነው። ኦነግ በአብይዝም ያገኜው ሲሳይ ተመን የለውም። ኦነግ ካሰበው፤ ከአቀደው ከፖለቲካ አቅሙ በላይ የናጠጠ ፍላጎቱን ሁሉ እያዋዙ፤ ብዙም ሳያስጠጡ እኮ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ብዙ በጣም ብዙ የኦነግ ህልሞችን አሳክተዋል ከመገንጠል ባሻገር። አዲስ አበባ እንደሆን ከመስከረም 5/2011 ዓም ጀምሮ መሪዋ ኦሮምያ ክልል ነው። ለዚህ እኮ ነው ሰላማዊ ሰልፍ የሚከለከለው። ይህን በተደጋጋሚ ጽፌዋለሁኝ።
ለመሆኑ የትኛው የማህበረ ኦነግ የፖለቲካ ሊቅ ይሆን አቅምስ ያለው እሳቸውን ለመተካት???? ኦነግ በዘመኑ ምን አሳካ? ይህ ዕድል እኮ "ኢትዮጵያ ሱሴ ናት" የኢትዮጵያኒዝም አቀንቃኞች ሙሉ ክህሎት አዘናግቶ ያስገኘለት በረከት እኮ ነው። በገራገሮች እና በኢትዮጵያኒዝም አናብስት የተከወነ ዊዝደም ነበር ቲም ገዱ ዕድሉን እንደ አልባሌ አሰር ደፍቶ፤ የአማራ ትንታግ ሊቃናቱ የአፈር ራት እነ ዶር አንባቸው ሆነው ያ ሁሉ የተደራጄ አቅም ቆፍጣና መሪ አጥቶ ብክንክን ብሎ ነው የቀረው። የተገበረው ተገብሮ። ገዱኢዝም ዛሬም ተገበሩልኝ አለበት። ይገርም እስከወዲኛው ነው።
ዛሬ የተለያዩ ፕሮጀክቶች አገር ቤት ሲመረቁ ትናንት በወላፈኑ ያልነበሩ፤ ለዛውም የህወሃት አራጊ ፈጣሪ የነበሩ ሌሎችም በለስ የቀናቸው ጨረፍታም ያልነካቸው ያልነበሩ፤ ከሁሉም የሌሉ አመስጋኝ እና ተመስጋኝ ሆነው ሲለባበሱ - ፍንሽንሽ፤ ፍልቅልቅ ሲሉ ሳይ ግርም ይለኛል። ሰሞኑን ዳግሚያ ተንሳኤው የኢህዴግ ነበር ማለት ይቻላል።
የኢህአዴግ የዳግም ተሃድሶ ሳቅ ሰሞናት ነበር ማለት ይቻላል። በጣም ነው የሚገርመኝ። በሌላ በኩል ደግሞ እንደገና - ሞት። እንደገና - ስደት። እንደገና - ጭንቀት። ደግሞ እንደገና - መገበር ደግሞ ይጠየቃል። ለዛው ማን ይሁን ማን ለማይታወቅ ስውር ስብስብ። ስክነት። ጥሞና። በጥልቀት ማሰብ በእጅጉ ያስፈልጋል። ግልቢያ - ለፈረሰኛ!
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች ሸበላ ጊዜ እመኝላችኋለሁኝ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀናእንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
24/10/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ቦታውን ለቆ አያውቅም።
ዕውነት ወረፋም ጠባቂ አይደለም።

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ