"#ሁለገብ ትግል" እና ትውልዱ።
"#ሁለገብ ትግል" እና ትውልዱ።
የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች እንዴት አደራችሁ?
#ምዕራፍ ፲፯
"የሁለገብ ትግል" መሠረተ ሃሳብ ጠንሳሹ ግንቦት 7 ነበር። በዛ ዘመን "ሁለገብ" የሚለው የመነሻ ሃሳብ እርሾ ነበረው። እኔ እንደማስበው ከቅንጅት መራራ ስንብት በኋላ የተፈጠሩት፤ አገር ውስጥ ይታገል የነበረው አንድነት የግንቦት 7 አዲስ የሁለገብ ፍልስፍና መንፈስ የመጋራት አቅምን አጠይቆ ይመስለኛል ግንቦቲዝም ሁለገብ ትግል ዶግማው የነበረው፤ ይመስለኛል። ይመስለኛል እምለው እራሱን ችሎ ጥናት ስላልተደረገበት ነው የአቀረብኩት አመክንዮ።
አገር ውስጥ ግንቦቲዝምን በበዛ ጉጉት ይጠብቁ የነበሩ ተናጠላዊ መንፈሶችም ሊኖሩ እንደሚችሉ አስባለሁኝ። ግንቦቲዝም የቅንጅትን መራራ የስንብት መንፈስ ትንሳኤውን ያወጄ ንቅናቄ ስለነበር። ዲያስፖራ ላይ አንጃ አልተፈጠረም፤ ወጣ ገብም ሁነት አልነበረም። ግንቦት 7 ዲያስፖራውን በአካል የመምራት አቅም ስለነበረው ለሌላ ኃይል ድውለት አልሆነም።
#ግን ሁለገብ ትግል የትኛውን የትግል መሥመር ሊከተል ይችላል?
በዘመነ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የሁለገብ ትግል አራማጅ ተብለው፤ "በአሸባሪነት" ተፈርጀው ብዙ በጣም ብዙ #ንጹኃን የጥቃት ሰለባ ሆነዋል። በተለይ በበዛ ሁነት የአማራ ልጆች። ሙየህወሃትን መንበር ከሥሩ የነቀለው ግን ከሁለቱም የትግል ስልቶች ውጪ የነበረ ዝቅ ሲል ጥቃት አሻም ያለ #ቅን መንፈስ፤ ከፍ ሲል #የዊዝደም ሙሉ አቅም በእግዚአብሄር ፈቃድ ብዬ ነው እማምነው።
የትግል ስልቱም #በሦስተኛነት መያዝ የሚቻል ይመስለኛል። ይህን ነው የዝምታ ዕድምታ ያልኩት። ያ የጸጥታ ስኬታማ አቅም ለየትኛውም ንቅናቄ፤ ለየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት፤ ለየትኛውም የተጽዕኖ ፈጣሪ የማይገዛ ስለሆነ፤ ከቁጥጥር ውጪ ነው። የፖለቲካ ሊቃናቱም እንደ አለ አይቆጥሩትም። የዝምታ ዕድምታ አይክለፈለፍም። አይበረግግም።
ውሃ በቀጠነ አይካሰስም። ከኮፒራይት ሽሚያ ውስጥ ድርሽ አይልም። አታሞ አያሰኜውም። ተቋማዊም ስላልሆነም አድራሻው ሆነ የአቅጣጫው ሁነትን ለማወቅም፤ ለመምራትም የሚቻል አይመስለኝ። በዛ ውስጥ የጥቂቶች የጊዜ ወይንም የመዋለ ንዋይ መስዋዕትነት ውጪ የሰው ልጅን ለማገዶ አያቀርብም። አያሸብርም፤ አይፈላም። አይቀዘቅዝም። በስክነት ያደምጣል። ኮሽ አይልም ነው። በፈቀደለት ጊዜ ትርፋማ ጎዳናም ይመስለኛል።
#የዘመናችን የሁለገብ ትግል ምኞተኞች።
ወጥ ይሁኑ? ተቋማዊ ይሁኑ? አባላቱ ይሁኑ አካላቱ እነማን ይሁኑ ሥም የለሽ ይመስለኛል። በዚህ በሁለገብ ትግል የግንቦቲዝም ትጉኃን በምኞቱ ውስጥ ተመክሯቸውን ሊያጋሩ ይችላሉ። ብዙ ጊዜ የሁለገብ ትግል ፍላጎተኞች ሥር - ነቀል ለውጥን እንጂ ጥገናዊ ወይንም በእኔ አገላለጽ #ተኃድሷዊ ለውጥን አይሹም።
ሥልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲንም ከመፍትሄ አካልነት ገለል አድርገው የሚዩትም ይመስለኛል። በሁለገብ ትግል መሥመር በቋሚነት፤ የዘለቀ ትውልዳዊ የኢትዮጵያኒዝም ተቋም ደግሞ እስካሁን የለም። ሁልጊዜ የሌላ አገር ንቅናቄ ሲነሳ ያን መጠለያም ያደርጋል። "ሁለገብ ትግል" ፍልስፍናው የግንቦት 7 ነበር። እሱ ደግሞ እራሱን አፍርሶ ኢዜማን ፈጥሯል፤ ኢዜማ ከጦርነት አስተሳሰብ ጋር የተፋታ ይመስለኛል አገር ቤት ያሉ መሪወቹ ከሚሰጡት ቃለ- ምልልስ ስረዳ።
#አደጋ።
ሁለገብ ትግል አቀንቃኞች ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርጉ የሚገባ ይመስለኛል። ማህበራዊ መሠረታቸው ………
1) ከፋኝ ያሉትን የትጥቅ ታጋዮችን፤ ይሁንታ ከሰጧቸው ሊሆን ይችላል?
2) ባለቤት አልባውን የዲያስፖራ ለውጥ ፈላጊ ማህበራዊ መሠረታቸው ቢያደርጉ ሊያዋጣቸው ይችላል። አገር ቤት ሰላማዊ ነዋሪውን እንመራዋለን፤ ከዛ የእኛ ሴል አለ ካሉ ግን ትውልዱን በአዲስ ማጭድ ቀራንዮ ማዋል ይሆናል። ከሁሉ በላይ ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በሙያቸው ሰላይም ናቸው። ቆዳቸው ገራገር ሆነው ሊታያቸው ይችላል ለተቃዋሚወቻቸው። ግን ጥንቃቄ የሚሹ፤ ጥበብን ምራኝ የሚል ብልህነት ይጠይቃል። ሁሉም ዓይነት ውጥን።
በሌላ በኩል ደግሞ በሰላማዊ ትግል ውስጥ የሚገኙ ጽኑ ተፎካካሪወችን እናት ፓርቲን እና ኢህአፓን እንደ ሦስተኛ ማህበራዊ መሠረታቸው የሁለገብ ትግል አራማጆች ካሰቡ ግን ለትውልዱ #አዲስ #ማጭድ #መሳል ይሆናል።
እናት ፓርቲ ይሁን ኢህፓ የተነሳበትን የሰላማዊ ትግል በውዞ የሁለገብ ትግልን አራምዳለሁ ቢሉ፤ ሦስት አፍ ያለው ስለት ከገዢው የብልጽግና ፓርቲ ይጠብቀዋል። ትውልዱም አሳሩን ያይበታል። አሁን እስር ቤት ያሉትን ማስፈታት ቀርቶ ስለ እነሱ መፃፍ፤ መሞገት፤ የተፃፈውን ሼር ማድረግ የማይቻል ሆኖ እያለ፤ አዳዲስ ወገኖቻችን ለካቴና፤ ለባሩድ፤ ለመሰወር፤ ለመደብደብ መዳረግ ጭካኔ ነው። ባልደራስ ይኑር አይኑር አላውቅም፤ አብንም እንዲሁ። ግን በአብን እና በባልደራስ የአዲስ አበባ ህዝብ ስንቱን አሳር ተቀበለ? የአማራ ክልል ነዋሪ ስንቱን ፍዳ አስተናገደ???
1) ብልጽግና።
2) ከፋኝ ብለው መሳሪያ ያነሱ የትጥቅ ታጋዮች።
2) ብልጽግናን በሁለገብ ትግል እንጥላለን ብለው እየተሰባሰቡ ያሉ የውጭ አገር ነዋሪወች የለውጥ ፈላጊወች ጭምርም ናቸው።
ስለዚህ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉትም ይሁን፤ በሁለገብ ትግል የሚታገሉት እራሳቸውን በዲስፕሊን ገርተው፤ ፍላጎታቸውን ከርክመው በተለይ እናት ፓርቲ እና ኢህአፓ ባላቸው ጠባብ መድረክ የበኩላቸውን ያደርጉ ዘንድ ሙሉ ነፃነታቸው ሊያውጁላቸው ይገባል ባይ ነኝ። "አንድ ሰው ሁለት እግር አለኝ ብሎ በአንድ ጊዜ ሁለት ዛፍ መውጣት አይችልም" የሚባለውም፤ ከዚህ አንፃር ነው።
በተለይ ሚዲያወች፤ ትግሉን የሚመሩ ግለሰቦች ሁሉ #በአነጋገራቸው፤ በገለፃወቻችው ሁሉ ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። የህዝብ ማህበራዊ ንቃተ ህሊና እኮ ከፖለቲካ ሊቃናት ቀድሞ በጣም ቀድሞ ተከታታይ ተጋድሎ በሰላማዊ ሁኔታ አገር ውስጥ በተለይ በአማራ ክል የተባ ተሳትፎ አድርጓል። የብልጽግና "ከጎዳና ወደ ፓርላማ" ስሎጋኑ እኮ መነሻ መሠረቱ ያ ብቁ አቅም ነበር። በተለይ አማራ ክልል።
ያን የነቃ እና የበቃ ተጋድሎ መምራት ያቃተው የተቃዋሚ ድርጅት የፖለቲካ ኢሊት ነው።
የበረደውን ሰላማዊ ንቅናቄ በምን ብልህነት በነበረው መልኩ ማስቀጠል ይቻላል፤ ለሚለውም ጉዳዩን አገር ውስጥ ላሉ ሰላማዊ ታጋዮች መተው ይገባል። ይህን መወሰን እና ሆኖ በመገኜትም የህዝባችን መስዋዕትነቱንም በብዙ ያቀለዋል። በኮፒ ራይት ትርምስምሱ ከቀጠለ ግን ስኬቱ #ጢስ ነው የሚሆነው። በተለይ ድምጽ አልባወቹ የኢትዮጵያ እናቶች የመከራው ሁሉ ቀጥተኛ ተጠቂ ይሆናሉ። በተለይ የታጣቂው ኃይል መሪወች እና የውጭ አገር ነዋሪወችን አታግላለሁ የሚለው መንፈስ እራሱን ችሎ በአቅሙ ልክ መቆም እና መመኜት ይገባዋል። በራስ አቅም መቆም። በራስ አቅም ማቀድ። በራስ ክህሎት መጠጋት።
አንድ ጊዜ "ለመስቀሉ እሮጣለሁ" የሚል ትዕይንት ታሰበ፤ ፖለቲከኞች ቲሸርት አሰርተው መሪ እንሁን አሉበት። ተከለከለ። ባለፈው ጊዜ የመርካቶ ነጋዴወች ንቅናቄ፤ ከዛም ቀጥሎ ጠንከር ያለ የህክምና ባለሙያወች ንቅናቄ ስኬቱ የጨነገፈው እኛም አለንበት በሚሉ ፖለቲከኞች ነው።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢሊቶች እራስን ሰርቶ መገኜት እንጂ በሌላው ጥያቄ ላይ #የፖለቲካ #ጥገኝነት መጠየቅ ትክክለኛው ጥያቄ እና ፋክት ተዳፍኖ የሚቀረው ከአያያዝ ሽሚያ ነው። እራስን ከመግራትም ችግር ይመስለኛል። ኮሽ ባለ ቁጥር አለንበት ከሆነ ከስኬት ጋር መገናኘት አይቻልም፤ ጥረቱም ሳያፈራ ጠንዝሎ ይቀራል። የህዝብ መንፈስም ማገዶ ይሆናል። ስጋትም፤ ፍርሃትም ይነግሳል። የትኛውንም የራስ #እንደራሴ ጥያቄ ህዝብ ሲያነሳ ለባለቤቱ መተው እንደ አንድ በኽረ ዲስፕሊን ሊወሰድ ይገባል። ሚዲያወችም ፍላጎታቸውን የማስከን፤ መሻታቸውን የማጨመት መንገድን ሊከተሉ ይገባል።
ለነፃነት የሚታገል ሁሉ ለሌሎች የትግል ነፃነት ለመስጠት ንፋግ ሊሆን አይገባም። አገር ውስጥ በሰላማዊ ትግል መታገልን ለመረጡ ድርጅቶች ጫና መፍጠር #መሰናክልነት ነው። ከሁሉም ለሁሉም ሳይሆን ይቀራል ትጋቱ እና መስዋዕትነቱን። ለትውልዱም መከራን ማጨት ነው። ጥረቶች የዝምተኛውን ማህበረሰብ ህሊናን የመግዛት አቅም ሊኖራቸው የሚችለው #ስክነትን ከዋጡ ብቻ ነው።
ሌላው "የኢትዮጵያ ህዝብ እኛን ካላመነ፤ እኛን ተስፋ ካላደረገ ማንን" የሚል የቤቴ ጣሪያ ሞቅ እስኪለው ድረስ የሳቅኩበት ክሊፕ አዳመጥኩኝ። ከሁሉም በላይ አማንያን እግዚአብሄርን አላህን ያምናል፤ የማይለወጠውን፤ የማይቀየረውን አልፋ እና ኦሜጋ የሰማይ እና የምድር ንጉሥ፤ የሰማይ እና የምድር ልዑልን፤ የሰማይ እና የምድርን ጌታን።
በውነት ፈጣሪያችን ተስፋ እናደርጋለን እንጂ ተስብስቦ ሲበተን፤ በትኖ ሲለቅም፤ የለቀመውን ሲያፈስ፤ ተገናኝቶ ሲለያይ ወይንም ሲካሰስ የሚውለው የኢትዮጵያ ፖለቲካን ለማመን አቅም ይጠይቃል። 60 ዓመታት ሙሉ ለዲሞክራሲ ሚሊዮን ተገበረ፤ እኮ ዛሬም እውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው። አንድ አንጃ ያልፈጠረ የፖለቲካ ድርጅት መቅረብ አይችልም ባልፍንባቸው የትግል መስመሮች። በሌላ በኩል የሰው ልጅ አምላክ አይደለም የሚመለክ።
እልህ
ብስጭት
የኮፒራይት ግብግብ
ኮሽ ባለቁጥር ከልክ በላይ ምኞትን ከፍ ማድረግን መከርከም ጥሩ ይመስለኛል። ለትውልድ ቋሚ መምህ አሻራ መፍጠር ለሚያስብ። ቀላሉን ቅንነትን እንኳን ደፋሪ የለም። ቀላሉን የመከባበር ባህልንም ለማስቀጠል ፈቃዱ የለም። ንቀት ሞራላዊ ትውልድን የመፍጠር አቅም የለውም። ከአቶ ጃዋር መሃመድ በስተቀር ጥሞናን የደፈረ ፖለቲከኛ አላውቅም። ሁልጊዜ ችኮላ፤ ሁልጊዜ ጥድፊያ። "የቸኮለ አፍሶ ለቀመ" የኢትዮጵያ ሐዋርያዊ ፍልስፍና ነው። መጠሞን መርህ ማድረግ ይጠቅማል። ለግል ህይወትም። የታረመ አንደበትን ቢያንስ ለትውልድ ለማበርከት ትጋት ቢኖር ምርጫየ ነው።
#እህሳ።
#የሁለገብ ትግል አደጋው አገርቤት ላሉ ቀንበጦን፤ ሸበላወች ነውና ቀንበሩን ለሚሸከሙ ወጣቶች ከውስጣችሁ እሰቡበት፤ ተነጋገሩበት፤ ሰው የማዳን ብሂልንም አህዱ ብትሉ ስል በትህትና አቀርባለሁኝ። ህዝባችን ባልተሳኩ፤ በማይሳኩ፤ ጨንግፈው በሚቀሩ ሁነቶች ብዙ በጣም ብዙ መከራ አይቷልና። ርህራሄ ያስፈልጋል።
በግልም ይሁን በጋራ መታገሉ፤ መትጋቱ፤ መበርታቱ መሞገቱ የአቅምን መሞከሩ ግን ጥሩ ነው። #ጥረት ነው የዓላማ #ጥራት ፈጣሪውና። ሌላው በገዢውም፤ በተቃዋሚው፤፦በተፎካካሪ፤ በተጠማኝ፤ በተደማሪም ፖለቲካ ውክልናም፤ ፖለቲካ ዕውቅናም የሌለው አባ ዝምታ፤ እመ ዝምታ ናቸው። ሙሉ አቅም፤ ክህሎት እና ጨዋነትም ዝቀሽ ነው ከእነሱ ዘንዳ።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን። አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን። አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
25/12/2025
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
ዕውነት ሽሽት አያውቅም።

አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ