"ፍትህን የሚሹት በወጡበት እየቀሩ ያሉት የትግራይ ሴቶች"
https://www.bbc.com/amharic/articles/cpe34g9vnevo አዳነሽ አብርሃ፣ ማኅሌት ተኽላይ እና ዘውዲ ሃፍቱ 9 ሀምሌ 2024, 06:42 EAT በትግራይ ክልል በሴቶች ላይ የሚፈጸመው አፈና፣ ግድያ እና ፆታዊ ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የተጎጂ ቤተሰቦች እና የሴቶች መብት ተሟጋቾች እየገለጹ ይገኛሉ። በመቀለ ባለፉት 11 ወራት 12 የሚሆኑ ሴቶች መገደላቸውን የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ለቢቢሲ ተናግሯል። * ማሳሰቢያ፡ ይህ ታሪክ የሚረብሽ ይዘት አለው። ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ በምሥራቅ ትግራይ ዞን አዲግራት ከተማ ነዋሪ የነበረችው የ 44 ዓመቷ አዳነሽ አብርሃ አስከሬኗ ከከተማዋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው በደቡብ ትግራይ መኾኒ ውስጥ ነው የተገኘው። “ የልጄን አስከሬን ከስድስት ወር በኋላ አገኘሁት ” ያሉት እናቷ ስምረት ተክሉ፣ አስከሬኗ በጎመን ማሳ ውስጥ ተጥሎ እንደነበር ይናገራሉ። ቢቢሲ በአዳነሽ አካል ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ጥቃት፣ አስከሬኗ የተገኘበት እርሻ እና በዚያን ጊዜ የለበሰችውን ልብስ የሚያሳይ ምስል አይቷል። ለሦስት ወራት የጠፋችው የ 16 ዓመቷ የማኅሌት ተኽላይ አስከሬንም በአድዋ ከተማ በሚገኘው ቻይና ካምፕ ውስጥ ተቀብሮ መገኘቱን ፖሊስ አስታውቋል። ሌሎች የፆታዊ ጥቃት እና አሰቃቂ ግድያ ሰለባዎች የሆኑ ማንነታቸው እንዲሁም ያሉበት ሁኔታ ያልታወቁ ሴቶች እንዳሉ በሴቶች ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ለቢቢሲ ገ...