ኢትዮጵያ የየትኛውም አገር #ፖስተኛ አይደለችም። ፈላስፊቷ ኢትዮጵያ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት #አትወከልም፤ ልትወቀስም ይሁን ስሟ ሊጎድፍ አይገባም።
"አቤቱ ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ።" አሜን።
#ምዕራፍ ፲፰
የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ገዢ ይሁን መሪ፤ የትኛውም ተፎካካሪ ይሁን ተቃዋሚ፤ የትኛውም #ተጠማኝ ይሁን ተደማሪ የፖለቲካ ድርጅት #ቀንጣውን፤ ብቻውን ወይንም ያደራጀው ተቋም፤ የኢትዮጵያ ውክል አካል እኔ ብቻ ነኝ ሊል አይችልም። ቢያጠፋም ቢያለማም በፖለቲካ ድርጅቱ #ሥም እንጂ በአገረ ኢትዮጵያ ሊሆን አይገባም። ፈጽሞ። አገርን ማክበር እራስን ከማክበር፤ ከማስከበርም ሊነሳ ይገባዋል።
#ለምንድን አንድ ፖለቲካ ድርጅት ብቻውን ኢትዮጵያን ሊወክል የማይችለው? በስሱ እስቲ ……
1) አቅሙ ኢትዮጵያን ሊመጥን ስለማይችል።
2) ክህሎቱ ደረጃው በኢትዮጵያ ልክ ስለማይሆን።
3) የውስጡ ጥራት የኢትዮጵያን ተፈጥሮ ልክ ሊሆን ስለማይችል።
4) አንድም የፖለቲካ ድርጅት የሺ ዘመናት ታሪክ፤ ትውፊት፤ ባህል የሌለው ስለሆነ።
6) የፖለቲካ ድርጅት ፍልስፍና ኢትዮጵያዊ ሳይሆን #በትውስት ከሌሎች የተቀዳ፤ የተቀሰመ ስለሆነ ከኦርጋኒኳ ኢትዮጵያ ጋር ፈጽሞ ሊግባባ፤ እኩል ሊቀመጥ ስለማይችል።
7) ዕድሜ ዘለቅ ያልሆነ፤ ዛሬ ተገንብቶ መፈጠሩ ሳይጠናቀቅ፤ በአንጃ፤ በሽኩቻ፤ በቅናት፤ አሳሩን የሚያይ ተቋቷም የድንቂትን ኢትዮጵያ ማንነት ውክል ሊሆን ስለማይችል።
ስምንተኛ) የአንድ አገር ህዝብ ሙሉው የፖለቲካ ድርጅት አባል ሆኖ ስለማያውቅ፤ ጥቂቶች የብዙኃኑን ተፈጥሯዊ ማንነት ጠቅላይ ሊሆኑ ስለማይገባ።
9) ሃሳቡ በዝምታ ውስጥ ያሉ የሚሊዮኖችን ድምጽ #አፋኝ እና ጠቅጣቂ ስለሆነ።
10) በተፈጥሯዋ ኢትዮጵያ የነፃነት የፊደል ገበታ ሆና፤ ለራሱ ነፃነት ሌላ ነፃ አውጪ የሚመኝ፤ የነፃነት ፍልስፍና ኢትዮጵያዊ ማንነት እንኳን መሆኑን የግንዛቤው ደረጃ ድርቅ የሚመታው ተቋም ነፃይቱን አገር ብቻውን ሊወክል ስለማይችል፤ ስለማይገባም።
11) የኢትዮጵያ ፖለቲካ የኢትዮጵያን ሃቅ ክዶ ስለሚነሳ።
12) ኢትዮጵያ "ማኒፌስቶ" በሚባል የትውስት ዕሳቤ ስላልተበጀት።
13) ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ ቀንጣ ሰው፤ ወይንም በጊዜያዊ በሚግባቡ ሰወች መፈጠር ኢትዮጵያን ያህል ተመስጥራ፤ በህብራዊነት መስተጋብር የተፈጠረች አገርን ብቻውን ወክሎ ሊገኝ ስለማይችል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅት እራሱን ችሎ ከቆመ እንኳን በቂ ነው፤ አይደለም ኢትዮጵያን ጠቅልዬ ወራሽ ነኝ ከሚል።
14) አንድ ፖለቲካ ድርጅት ዛሬ ተፈጥሮ ነገ የሚፈርስ፤ ዛሬ ታጭቶ ነገ የሚናድ፤ ዛሬ አለሁኝ ብሎ ነገ የመራራ ስንብቱን ትዕይንት ሲያሳዬን ኖሯል። ይህን ስንታዘብ ስለኖርን ኢትዮጵያን #ማለካካት ፈጽሞ አይቻልም። ለየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ኢትዮጵያ በአቻው ሊፎካከራት አይችልም። በጥቂቱ ይህን ካልኩኝ። የኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች በላይ ነው።
አንድ የፖለቲካ ድርጅት ቀን ሰጥቶት ሊገዛ ይችላል። ሃሳቡ #የቀንጣ ወይንም የቡድን ሊሆን ይችላል። እሱ በሚያወይበው፤ በሚያጠነዝለው፤ በሚያዳምነው ኩነት የኢትዮጵያ ሥም ሊጎድፍ፤ ሊጣጣል፤ ሊንቋሸሽ፤ ሊገሰጽ ፈፅሞ አይገባም።
በሌላ በኩል አንድ የፖለቲካ ድርጅት ጥሩ ሰርቶ፤ ህዝብን አስደስቶ፤ ለህዝብ #ታማኝ ሆኖ፤ በሰባዊነት፤ በተፈጥሯዊነት አንቱ ቢባል እንኳን እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሊመሰገን፤ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ብርቱ ሊባል ይችላል እንጂ እኔ ብቻ የኢትዮጵያ ህሊና እና መንፈስ ነኝ ሊል ከቶውንም አይችልም።
ኢትዮጵያ ከቀንጣ፤ ወይንም ከጥቂት ሰወች አዕምሮ ከሚያፈልቀው የሃሳብ ማህለቅ #በላይ ናት። ኢትዮጵያኒዝም ፍልስፍናውም ይሁን የአፈጣጠር ዘይቤው ጥናት፤ ምርምር፤ ፍልስፍና በልዩ አቅል እና አቅም የሚጠይቅ ነው።
በአንድ ወቅት አንድ ቋሚ የኢትዮጵያ ይትበኃል ተነቅሎ፤ ሌላ ዘመን ሠራሽ ሁነት ሊተከል ይችላል። ያ ተፈጥሮን ነቅሎ የተተከለ ሁነት አይዘልቅም። ጊዜውን ጠብቆ ይገረደሳል። ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ፍልስፍናውም፤ ድርጊቱም #አና ያለበት ጊዜ ነበረ። ፈራረሰ ለዘር ሳይበቃ።
በትኩ ጭንብሉን አጥልቆ ዞገኝነት ገዛ። ተናደ። አሁንም ሌላ ትዕይንት ላይ ኢትዮጵያ ትገኛለች። ሃሳቡ ቀንጣዊ ነው። የሃሳቡ ውህደትን አቅሙን በራሱ አካሎች ሲተናነቃቸው የፋና የሰሞኑ መድረክ አብራርቶልናል።
በዚህ ሂደት የታዘብኩት ወይ መንፈሱ የበላይ፤ ወይንም ውክሎቹ የበላይ ተኋሁነው፤ ያልተጣጣመ፤ ያልተዋህደ ብስል ተጥሬ ጉዳይ ነው ያዬሁት። ውህድ የሆነ መስተጋብር አላየሁም። የአቅም ማነስ አይደለም ሚኒስትሮች ናቸው። የቀለሙ ልኬታ በመጨረሻው የዕውቀት ደረጃ ዶክትሬት። የቀንጣ ሃሳብ አመንጪነት ገዢነት ቀን #ሰጥ እንጂ ከውስጥ የደረሰ፤ ውስጥን አድሬስ ያደረገ የፕረዘንቴሽን ስስነት ወይንም መቋረጥ ሊሆን ይችላል።
ኢትዮጵያዊነት እንዲህ አይደለም። ለተቀበሉት ሰከንዶች፤ ደቂቃወች፤ ሰዓታት፤ ቀናት፤ ወራት፤ ወቅታት፤ ዓመታት፤ ዘመናት ቢፈራቀቁም ሁልጊዜ ህይወትን ይመራል። #ህልው ነው። ቋሚ የውስጥነት ቤተኛ ነው።
የት ቦታ እንደሆን አላስታውስም ክብርት ወ/ሮ ሙፍርያት ካሜል። "መደመር" አገር በቀል ነው ብለው ሲናገሩ አዳምጫለሁኝ። አገር በቀል የሚለውን ቃል ወድጀላቸዋለሁኝ - ድርጊተኛ ቢያገኝ። "መደመር" ቃሉ ግሎባል ነው። ምልክትም አለው። + ይህ የመስቀል ምልክት በሉላዊ ደረጃ ዕውቅና ያለው የቀመር ምልክት ነው።
አገር በቀል ልንለው አንችልም። "#መደመር" ሃሳቡ መታከል፤ መጨመር፤ ስለሆነ አወንታዊ ነው። እሳቸውን በአካል ባገኝ ወዲያው ነበር እማሸንፋቸው። በሌላ በኩል አዘውትረን ሁላችንም እምንጠቀምበት የለት ተለት ህይወታችን ነው ቃሉ። መፃህፍቶቼ ላይም አለ። እንደ ፍልስፍና፤ እንደ መሪ ሃሳብ ለመታየት ይከብዳል። መደመር ነፍሱ ቀጠለች አልቀጠለች የኖርንበት ስለሆነ እንደ ቃል እኛ፤ እንደ ዕውቀት ሂሳብ አሰልጥኖ ያስቀጥለዋል።
የሆነ ሆኖ መታከል፤ መጨመር ካልተጠላ ለምን የፖለቲካ ድርጅታቸው እሳቸው አባልም፤ አካልም ሆነው በኖሩበት ህወሃት መራሽ ኢህአዴግ፤ 27 ዓመታት የገነገነውን የክፋ ሃሳብ ውርስ ለማስቀረት አልታገለም። 8 ዓመት ብዙ ነው። ዛሬም ተጠልተው የሚገደሉ ነፍሶች አሉ እኮ ምስራቅ አርሲ ላይ። በማንነታቸው ክፋ ቃል እንዲያዳምጡ፤ መስቃ እንዲሰሙ የተገደዱ ዜጎች አሉ። የሚደመጡ ሰቆቃወች ሁሉ እኮ "ከመደመር" #በተቃራኒ የቆሙ ናቸው። ይህ ዝበት ለኢትዮጵያንም ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም #ዕዳ እያስቀመጠላት ነው።
"የመደመር"ዕሳቤው አገር በቀል ሳይሆን ሂሳባዊ ግሎባልም ቢሆን እንኳን አጽናኝ፤ እረጂ፤ አዋህጂ ማድረግ ይቻልም ነበር። ከዚህ በላይ ግን ጠቃሚ ጎዳና የሚሊዮን ፍቅርን በገፍ የቀለበው #ኢትዮጵያዊነቱ ሌላ ነገር ሳይቀየጥበት ለኢትዮጵያ የመዳኛ ፈውሷ ይሆን ነበር። ኢትዮጵያዊነት መንፈሱ ረቂቅ ብቻ ሳይሆን ኃያል አዳኝነትም አለበት - ለሚያውቀው።
ኢትዮጵያዊነትን የሚበውዙ ሁነቶች ለለት እንደ ስኬት ሊታዩ ይችላሉ። ለነገ ግን በረከት አይኖራቸውም። ኢትዮጵያዊነት የራሱ ማንነት ያለው ተፈሪ፤ ሁለገብ ማንነት ነውና እራሱን ለማዳን ለቀኑ ቀን ሲሰጠው ቀና ይልና የጎበጠውን ያቃናል። ተስፋው ያ ነው።
በሌላ በኩል ወ/ሮ ሙፈርያት ካሜል " መደመር + =" ? የሆነው አመክንዮ ይጠፋቸዋል ብዬ አላስብም። ከመደመር ጋር ተቀይጦ ያለው ኒዩክለስ ሁነትስ??? በዚህ በአለባሶ ጉዞ ሊሳኩም /// ሊጨነግፋም የሚችሉ ጉዳዮች ይኖራሉ። ዕድሜውን ከሰጠን እናየዋለን። ኢትዮጵያዊነት ባጣ ቆየኝ ሊባል አይገባም። ኢትዮጵያዊነት ቢከፋኝ ልመለስብህ ሊባል አይገባም። ኢትዮጵያዊነት በግርግር የተፈጠረ ማንነት አይደለም ና።
ኢትዮጵያኒዝም ቀና እንዳይል ተጫኝ መንፈስ አለ። ኢትዮጵያኒዝም ተቋሟት ላይ #ፍልሰት አለ። ኢትዮጵያኒዝም ጥሪት ላይ ነቀላ አለ። ግን ኢትዮጵያኒዝምን ለራሳቸው ሲሉ የሚጠብቁ፤ የሚንከባከቡ የፓን አፍሪካ አርበኞች ዘብአደሮች አሉ። ኢትዮጵያኒዝም ግሎባል ዜጎች አሉት። ኢትዮጵያኒዝም ከእኛ የተሻለ የሚያከብሩት፤ የሚሳሱለት፤ የሚናፍቁት ሚሊዮኖች አሉለት።
ሰሞኑን ስለቅኔው ልዑል ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ በኢትዮጵያ በመንግሥት ሚዲያ ሲቀነቀን ሰማሁኝ። እንኳን ለዚህ አበቃችሁ ማለት እፈልጋለሁኝ። እኔ #ለ፲፰ ዓመታት በባዕድ በስደት አገር በብዙ ፈተና ውስጥ ሆኜ ሆም ፔጅ፤ #ራዲዮ በጸጋዬ ሥም ያደረኩት በእሱ ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊነት፤ ፓን አፍሪካዊነት ጠርቶኝ ነው።
በዘመነ ብልፄው ሚዲያወች ፕሮግራሞችን ሳዳምጥ ደነቀኝ። ኢትዮጵያዊነት ሳይፈቀድለትም እንዲህ የሚያናግር #ጀግና መሆኑን አስተውየበታለሁ፤ አንዲት ስንዝር ተራምዶ፤ አንድ ቀጣይ እርምጃ ለመጓዝ አቅሙ የሚቀዳው #ከኢትዮጵያዊነት ነው። ተጠልቶም፤ ተርቆም፤ ተገሎም፤ አንይህ ተብሎ ፊትተነስቶሜ፤ ኢትዮጵያዊነት አይበገሬ መንፈሱ ያስገድዳል። ሊርቁት የማይችሉ ገናና #መሪ ነውና።
ሌላው ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ገዢው ፖለቲካ ፓርቲ ብልጽግና በሚገድፈው ይሁን በሚያሳካው ጉዳይ ለራሱ ስንቅ እና ትጥቅ እንጂ የኢትዮጵያ ውክል ብቸኛ ጌጥ፤ ወይንም ብልዘት አድርጎ ማዬት ከስህተት ያለፈ #ገደል ነው።
1) ስለሆነም ኢትዮጵያን አትዳፈሯት።
2) ለኢትዮጵያ የታረመ አንደበት ብቻ ነው ልኳ።
3) እሷን ከፍ እና ዝቅ ሲያደርጓት፤ እሷን ሲወቅሷት የሚያመን አለንና። #እናት እኮ ናት። መከፋቷ - መከፋታችን፤ ሳቋም - ሳቃችን የሆን። የማንነታችን ማህተም የላቀው ኢትዮጵያዊነት ለሆነው ለእኛ ክብሯ ሲነካ እንቆስላለን። ልንከባበር ይገባል እንደማለት።
ወሳኝ በሆኑ ግሎባል ጉዳዮች የኢትዮጵያ ጎዳና ሁሉ አይቅርብኝ አልነበረም። ቀደምቶች "ገለልተኛ" የዲፕሎማሲ መርህ ይከተሉ እንደ ነበር የታሪክ ድርሳናት ያስተምራሉ።
ኢትዮጵያ በከበረ - ማንነቷ፤ በከበረ - እሷነቷ፤ በላቀ - ጸጋዋ ልክ ሊኖር፤ ሊሆን የሚችል የፖለቲካ ድርጅት የለም። የፖለቲካ ድርጅት ታሪክ በኢትዮጵያ 60 ዓመቱ ነው። ለ፬ ሺህ ዘመናት ለኖረች አገር ሊመጥን አይችልም።
ስለሆነም ኢትዮጵያ በዘመን ውስጥ ዕድል ያገኜ የፖለቲካ ድርጅትን አስታኮ ኢትዮጵያን አቅላይ፤ ደፋሪ ቃል ከመናገር ፖለቲከኞች ሊታቀቡ ይገባል። አንድ ጊዜ ግድፈት ይሁን፤ ተደጋግሞ ሲደመጥ ግን ያማል። አሞኝ ነው የሰነበተው። ኢትዮጵያ የየትኛውም አገር "#ፖስተኛ" ሆና አታውቅም። ቃሉን ብደግመው የውስጤን ቁስለት ስለሚያመረቅዘው፤ በትርጉም አቃንቼ ነው ያቀረብኩት።
ዝም ብዬ የሰነበትኩት ማጋጋል፤ ማቀጣል ስለማልፈልግ ብቻ ነው። ጉዳዩ ረብ እስኪል የጠበቅኩት። ህመሙ፤ ቁስለቱ ግን እስከ አሁን አለቀቀኝም።
የአገሬ ልጆች እንዴት አደራችሁ? እንደምን አረፈዳችሁ።
ደህና ዋሉልኝ። አሜን።
ቸር አስበን፤ ቸር እንሁን፤ አሜን።
ቅን አስበን፤ ቀና እንሁን፤ አሜን።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። አሜን።
ኑሩልኝ። አሜን።
ሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
09/03/2026
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት፤ ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ