"ፍትህን የሚሹት በወጡበት እየቀሩ ያሉት የትግራይ ሴቶች"

 https://www.bbc.com/amharic/articles/cpe34g9vnevo

 

 አዳነሽ አብርሃ፣ ማኅሌት ተኽላይ እና ዘውዲ ሃፍቱ

አዳነሽ አብርሃ፣ ማኅሌት ተኽላይ እና ዘውዲ ሃፍቱ

9 ሀምሌ 2024, 06:42 EAT

በትግራይ ክልል በሴቶች ላይ የሚፈጸመው አፈና፣ ግድያ እና ፆታዊ ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የተጎጂ ቤተሰቦች እና የሴቶች መብት ተሟጋቾች እየገለጹ ይገኛሉ።

በመቀለ ባለፉት 11 ወራት 12 የሚሆኑ ሴቶች መገደላቸውን የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ለቢቢሲ ተናግሯል።

*ማሳሰቢያ፡ ይህ ታሪክ የሚረብሽ ይዘት አለው።

ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ በምሥራቅ ትግራይ ዞን አዲግራት ከተማ ነዋሪ የነበረችው 44 ዓመቷ አዳነሽ አብርሃ አስከሬኗ ከከተማዋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው በደቡብ ትግራይ መኾኒ ውስጥ ነው የተገኘው።

የልጄን አስከሬን ከስድስት ወር በኋላ አገኘሁትያሉት እናቷ ስምረት ተክሉ፣ አስከሬኗ በጎመን ማሳ ውስጥ ተጥሎ እንደነበር ይናገራሉ።

ቢቢሲ በአዳነሽ አካል ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ጥቃት፣ አስከሬኗ የተገኘበት እርሻ እና በዚያን ጊዜ የለበሰችውን ልብስ የሚያሳይ ምስል አይቷል።

ለሦስት ወራት የጠፋችው 16 ዓመቷ የማኅሌት ተኽላይ አስከሬንም በአድዋ ከተማ በሚገኘው ቻይና ካምፕ ውስጥ ተቀብሮ መገኘቱን ፖሊስ አስታውቋል።

ሌሎች የፆታዊ ጥቃት እና አሰቃቂ ግድያ ሰለባዎች የሆኑ ማንነታቸው እንዲሁም ያሉበት ሁኔታ ያልታወቁ ሴቶች እንዳሉ በሴቶች ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ባለፈው የካቲት ወር በሰሜን ምዕራብ ዞን ውስጥ ወደ ሰለኽላኻ ከተማ በሚያስገባው ድልድይም እንዲሁ የአንድ ሴትን አስከሬን ፖሊስ አግኝቶ ነበር።

ማንነቷን የሚገልጽ መታወቂያ ማግኘት ባለመቻሉ ስሟን፣ እድሜዋን እና የመጣችበትን አካባቢ ማወቅ እንዳልተቻለ የላዕላይ ቆራሮ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር አለነ አስገዶም ለቢቢሲ ገልፀዋል።

መጋቢት 19/2016 .. በመቀለ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ ከተደረገ በኋላም ፖሊስ የተገደልችበትን ሁኔታ እና ምክንያት ማወቅ አልቻለም።

እኛ አላወቅናትም። ሬሳዋ ለረጅም ጊዜ ተጥሎ ስለቆየ ማንነቷን ለይቶ ማወቅ አልቻልንም። ለብሳው የነበረውን ልብስ ይዘን ወደ አጎራባች ወረዳዎች ሄደን ነበር። እስከ አክሱም እና አድዋ ድረስ በመሄድ የሚያውቃትን ለማግኘት ብንሞክርም አልተሳካልንም። ስለዚህ ከሌላ ቦታ አምጥተው ጥለውታል ብለን ነው የምንገምተውብለዋል።

በትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳይ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር ዓለም ምስግና፣ ወንጀሎቹን በቁጥር ለመለየት እንደሚያስቸግር እንዲሁም ፖሊስ ወንጀሉን የፈጸሙ ሰዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ ይናገራሉ።

ከእነዚህ ሰለባዎች መካከል አንዳንዶቹ እነማን ናቸው? ቤተሰቦች ስለልጆቻቸው ምን ይላሉ?

'ልብሷን፣ ጫማዋን እና ፀጉሯን አቆዩልኝ'

የምስሉ መግለጫ, አዳነሽ አብረሃ ነሐሴ 12 ቀን 2015 .. ከባለቤቷ ጋር 530 ላይ 'ጸበል ተጠምቄ እመለሳለሁ' ብላ ከቤቷ እንደወጣች አልተመለሰችም።

እድሜያቸው 85 የሆኑት ወይዘሮ ስምረት ተክሉ፣ መኖርያ ቤታቸውን የሞሉት የተለያየ ቀለማት እና መዓዛ ያላቸውን አበቦች ሲያዩ ልጃቸው አዳነሽ አብረሃን አስታውሰው ያነባሉ።

ነገር ግን አሁንም ድረስ በፍርሃት እና በድንጋጤ ውስጥ ያለችውን ሌላኛዋ ልጃቸውንአታልቅሺእያሉ ሊያጽናኑ ይሞክራሉ።

አዳነሽ አብረሃ ነሐሴ 12/2015 .. ከባለቤቷ ጋር 530 ላይጸበል ተጠምቄ እመለሳለሁብላ ከቤቷ እንደወጣች የቤተሰቧ አባላት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስልኳ እስከ ቀኑ 800 ሰዓት ድረስ ሲሠራ ነበር፤ ከዚያ ግን ተዘጋ።

አርብ ጸበል ተጠምቄ . . . ቅዳሜን ደግሜ ለእሁድ የሚሆን ይዤ እመጣለሁ ብላ ለሠራተኛ መልዕክት ትታ ሄደች። የእሷን መምጣት ስጠባበቅ ብዙ ቅዳሜዎች አለፉይላሉ እናቷ።

አዳነሽ ተወልዳ ያደገችው አዲግራት አካባቢ ነው። የቤተሰቧ አባላት እንደ አንድ ደግ፣ ታታሪ፣ ለውጥ ወዳድ፣ ልጅ እና ሰላማዊ ትዳር የምትመኝ ወጣት ሴት ያስታውሷታል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ የትግራይ ወረዳዎች በመምህርነት አገልግላለች። ሙያው ውስጥ ባሳለፈቻቸው አምስት ዓመታት የተዋወቀችውን የሥራ ባልደረባዋ አግብታ ነበር።

በመቀለ ዩንቨርስቲ የሒሳብ ትምህርት ተምራለች።

በትዳር 15 ዓመታትን ያሳለፈችው አዳነሽ ከማስተማር ሙያ ወጥታ የራሷን ሥራ ትሠራ እንደነበር ቤተሰቦቿ ተናግረዋል።

አዳነሽ ሕይወቷን ለማሻሻል ከአምስት ዓመት በፊት ወደ እስራኤል ሄዳም ነበር።

ሆኖም ከስድስት ወራት በኋላ በጤና ችግር ምክንያት ወደ አገሯ መመለሷን እናቷ / ስምረት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ወደ እስራኤል ሄጄ አመጣኋት። እዚህ ለአንድ ዓመት ከአምስት ወር ተንከባከብኳት - ከዚያም ከእኔ ጋር መኖር ጀመረች።

ጤንነቷ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ሲመለስ አዳነሽ የጭማቂ መሸጫ ሱቅ ከፈተች። ራሷን ለመደገፍ የአገር ውስጥ እና የውጭ ችግኞችንም ትሸጥ ነበር።

ከዚያም መስከረም ወር ላይ እንደወጣች ስተቀርባቸው ጊዜ፣ ያያት ሰው ካለ መረጃ እንዲሰጣቸው ምስሏን እና ስሟን በፌስቡክ ላይ አካፈሉ። በተለያዩ ገዳማት እና አድባራትም ሲያፈላልጓት ቆዩ።

ከዚያም መኾኒ በሚገኝ የማሽላ ማሳ ውስጥ ተጥላ የተገኘች ሴት እንዳለች በደረሳቸው መረጃ ማምነቷን ለመለየት ለብሳው የነበረውን ልብስ እና ጫማ ለፖሊስ አሳውቀው ልጃቸው መሆኗ ተረጋገጠ።

ነገር ግን በደንብ እስኪጣራ ድረስ አዳነሽ ስለመሆኗ ለቤተሰቡ አልተናገርንምይላል አጎቷ ኮማንደር ፍትሃነገሥት በርሄ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ እናቷ ደውለው ገንዘብ የጠየቁ እና የባንክ ሒሳባቸውን የላኩ ግለሰቦች ነበሩ።

በጥር ወር. . . 100,000 ብር ስጡን አሉን። . . . ግን እሷ አልነበረችም። በግንቦት ወር መተማ ውስጥ እንዳለች ነገሩን። አሳዩን ብንል ግን ምንም የለምይላል።

በዚህ ሁኔታ ለወራት በጭንቀት ያሳለፉት / ስምረት ቀደም ሲል የአዳነሽን ሞት የተረዱት የቤተሰብ አባላት ከስድስት ወራት በኋላ መርዶውን እንዳረዷቸው ይናገራሉ።

ከስድስት ወር በኋላ ነበር የሰማሁት። እዚያ ስሄድ ይህች ሟች የኔው ናት አልኳቸው። ቀሚሷን ጫማዋን ፀጉሯንም አቆይተውልኝ አየሁት። ነገር ግን ተጠርጣሪው እስካልተያዘ ድረስ አስከሬኑ እንደማይሰጥ ስለነገሩኝ እንዳላየሁ እንዳልሰማሁ ቀን ከሌሊት ሳለቅስ ከረምኩ።

የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት ኮማንደር ዓለም እንደተናገሩት ተጠርጣሪው መያዙን እና የአስከሬን ምርመራ ተጠናቆ ውጤቱን ለዐቃቢ ሕግ እንደሚተላለፍ ተናግረዋል።

የአዳነሽ አብረሃ የቀብር ስነ ስርዓት ሰኔ 6 ቀን 2016 ተፈጽሟል።

የምስሉ መግለጫ, የጓደኛዋን ልደት ልታከብር ወጥታ ያልተመለሰችው 32 ዓመቷ ዘውዲ

የቤተሰባችን ጧሪ ነበረች

ነሐሴ 2015 .. አጋማሽ ላይ አዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ፣ መቀሌ አዲ ሓውሲ በተባለው አካባቢ ከምሽቱ 130 ላይ ብዙዎችን ያስደነገጠ ግድያ ተፈጽሟል።

በወቅቱ ታርጋ የሌላት መኪና የያዙ ሰዎች ግለሰቧን ከነቦርሳዋ ለተወሰነ ርቀት እየጎተቱ ከወሰዱ በኋላ ጥለዋት ገድለዋት ጠፉ የሚሉ መረጃዎች መሠራጨት ጀመሩ።

ከእሷ ጋር ነበረች የተባለችው ጓደኛዋ ራሷን ስታ ወድቃ አይደር ሪፈራል ሆስፒታል ገብታ ነበር። ከዚያ በኋላ በምርመራ ላይ ከሚገኙ አምስት ተጠርጣሪዎች መካከል አንዷም ሆና ነበር።

ግድያውን የፈፀመው ማነው? ቤተሰቦቿስ ለምን ግልጽ መረጃ እስካሁን አላገኙም? ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።

ነገር ግን ግድያው አሰቃቂ በሆነ መንገድ መፈጸሙ ግልጽ ነው። ዘውዲ ሃፍቱ በዚህ መልኩ ከሞተች 11 ወራት አልፈዋል።

እስካሁን ፍትህ አላገኘንም። በፍርድ ቤት ቀጠሮ ከመመላለስ የዘለለ የሚጨበጥ ነገር አልተነገረንም። ምን እንደተፈጠረ አናውቅም፤ ምንም መረጃ የለንም። ይህ ሆነ ብሎ የነገረን የለምስትል ታናሽ እህቷ ብርቱካን ሃፍቱ ለቢቢሲ ተናግራለች።

ከተጠርጣሪዎቹ አንዷ የቀድሞ ጓደኛዋ በዋስ ስትለቀቅ ሌሎች አራት ሰዎች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።

32 ዓመቷ ዘውዲ ተወልዳ ያደገችው መቀሌ ማይ አንበሳ በሚባለው አካባቢ ነው።

ወላጆቻችን ተቸግረው ነው ያሳደጉን። እናታችን ሻይ እየሸጠች ነው ያሳደገችን፤ አባታችን ደግሞ የጥበቃ ሠራተኛ ነውትላለች።

ዘውዲ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በፎክሎር የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘች ሲሆን፣ በሼባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አካውንቲንግ ተምራለች።

ዘውዲ ምሥጢራዊ በሆነ ሁኔታ በተፈጸመባት ግድያ ከመሞቷ በፊት ሥራዋ ዕለታዊ ዕቁብ መሰብሰብ ነበር።

በተገደለችበት ዕለትም እንደተለመደው ዕቁብ ስትሰበስብ ውላ ምሽት ላይ የጓደኛዋን ልደት ለማክበር ነበር ከጓደኛዋ ጋር የወጣችው።

ገንዘቡን ተቀብያት ልብሷን ቀይራ ወጣች። ነገር ግን ከሄደች አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አይደር ገብታለች ተብሎ ተደወለልኝ።

ከዚያ በኋላ ቃሏን ለመስማት አልታደለችም።

እነዚህ ተመሳሳይ ጥቃቶች በሴቶች ላይ ሲደጋገሙ አስደንግጦኛል። ወደ ሥራ ወጥቼ እስክመለስ ድረስ እፈራለሁ። ይህ የሁሉም ሴቶች ፍርሃት ይመስለኛልትላለች።

 

የምስሉ መግለጫ, 16 ዓመቷ ማህሌት ተኽላይ

እንደወጣች የቀረችው ታዳጊ

በመኝታ ክፍሏ ውስጥሁሉም ነገር ቆንጆ ነው፣ ግን ማንም አያስተውለውም፣ ሁልጊዜ አዎንታዊ አስብ፣ ማንንም አትነቅፍ . . .” ወዘተ የሚሉ ጥቅሶች አሉ።

ተምራ፣ ከታላቅ እህቷ ጋር ንግድ ለመሥራት እና በስማቸው የሚጠራ ነገር ለመትከል ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት፤ ሁሌም ስለ አዳዲስ ፈጠራዎች ይነጋገሩ ነበር።

16 ዓመቷ ማኅሌት ተኽላይ ዘንድሮ አገር አቀፍ የስምንተኛ ክፍል ፈተና ለመውሰድ እና ጥሩ ውጤት ለማምጣት በዝግጅት ላይ ነበረች። ከትምህርቷ ጎን ሌሎች የትምህርት ዓይነቶችን እና ቋንቋ በማጥናት ጥሩ ውጤት አስመዝግባ ነበር።

ነገር ግን 16 ዓመቷን በያዘች በአንድ ወር ውስጥ መጋቢት 10/2016 .. ከሰዓት በኋላ ከቤቷ ወጥታ ወደ ቋንቋ /ቤት ስትሄድ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታገተች።

በዕለቱ ቤተሰቦቿ በግል ስልኳ ተደውሎሦስት ሚሊዮን ብርእንዲከፍሉ እንደተጠየቁ ያስታውሳሉ።

ከዚያም ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ደውለው ቤተሰቡ ገንዘቡን ለመክፈል ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ጠየቁ።

ነገር ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ባሉት ሦስት ወራት ውስጥ የማኅሌት ድምፅ አልተሰማም፤ የጠለፏት ሰዎች ያሉበት ቦታም አልታወቀም።

የማኅሌት ቤተሰቦች ግን ከዛሬ ነገ ትገኛለች በሚል ተስፋ ፖሊስ እና ማኅበረሰቡ ትብብር እንዲያደርጉ ጥረት ማድረጋቸውን ቀጠሉ።

አብዛኛው የአካባቢው ማኅበረሰብ ጥቁር ልብስን ከሞት እና ከመጥፎ ዕድል ጋር ስለሚያያይዘው በቤቱ ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ጥቁር እንዳይለብስ አያቷ ከልክለው ነበር።

ከማኅሌት እገታ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ስለነበር፣ ትገኛለች የሚል ትልቅ ተስፋ በቤተሰቧ ዘንድ ነበረ።

ማሂ ስትመጣ ነጭ ለብሰን ፎቶ ተነስተን የሁላችንም ፎቶ ቤት ውጥ እንሰቅላለን። ስለት ወደ ገባንባቸው ገዳማት ይዘናት እንሄዳለን፤ አእምሮዋ እንዲታደስ እናደርጋለንእያሉ በተስፋ ውስጥ እንደነበሩ እህተዕ ሚሊዮን ትገልጻለች።

ሆኖም ፖሊስ ከሦስት ወራት በኋላ ማኅሌት ተኽላይ ተገድላ እንደተቀበረች ተጠርጣሪዎች ማመናቸውን የአድዋ ፖሊስ አዛዥ አቶ ተስፋይ አማረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስለ ግድያው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት የተቆጠቡት አዛዥ፣ ተጠርጣሪዎቹ የተቀበረችበትን ቦታ እንደጠቆሙ እና አሁንም ምርመራው እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በሰጡን መረጃ መሠረት አስከሬኑ የተቀበረበት ቦታ ሄድንበማለትቻይና ካምፕየሚባል ቦታ ላይ ሬሳው እንደተገኘ አስረድተዋል።

የቤታችን ድምቀት ነበረችስትል ማኅሌትን የምታስታውሳት ሚሊዮን፣ ከታናሽ እህቷ ጋር ስታደርጋቸው የነበሩ የዕለት ተዕለት ንግግሮች፣ ሳቅ እና ጨዋታን ትናፍቃለች።

አሁን የምንፈልገው ድምፃቸው የተፈኑ ብዙ ሴቶች ፍትህ እንዲያገኙ ነውትላለች ማኅሌት መኝታ ክፍሏ ውስጥ የሠራቻቸውን የተለያዩ የግድግዳ ጽሑፎችን እና ቅርጻ ቅርጾችን እያሳየች።

የከተማው ፖሊሲ የአስከሬን ምርመራው ውጤትወራትንሊወስድ እንደሚችል እና በአሁኑ ጊዜ አስተያየት መስጠት እንደማይችል ይናገራል።

ፍትሕ የሚጠይቁ የትግራይ ሴቶች

በተለይ ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ በትግራይ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ እንደመጣ ሲገለጽ ቆይቷል።

ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ በመቀሌ እና አዲግራት ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደው ነበር።

ሰልፎቹ ላይ የተገኙ የሴቶች ማኅበር እና የትግራይ ፍትህ ቢሮ ተወካዮችበሴቶች ላይ የሚደርሰውን ዘግናኝ ግፍእንደሚያወግዙ ተናግረዋል።

የሴቶች ማኅበር ኃላፊ ወይዘሮ አበባ ኃይለሥላሴፍትህ ሊረጋገጥ ባለመቻሉወንጀሉ ጭካኔ በሞላበት ሁኔታ እየቀጠለ እንደሆነ ይናገራሉ።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐዲሽ ተስፋ በበኩላቸውሕግ እና ሥርዓትን ለማስጠበቅ እና አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ እየሠራን ነውማለታቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ከትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ኮማንደር ዓለም ምስግና ከጦርነቱ በኋላ በክልሉ የፀጥታ መዋቅር ላይ ክፍተቶች እንዳጋጠመ እና በግለሰቦች ላይ ግድያን ጨምሮ ከባድ በጦር መሳሪያ የታገዙ ወንጀሎች ሲፈጸሙ እንደቆዩ ይናገራሉ።

በሴቶች እና በሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃትንም አውግዘዋል።

በመቀሌ ከተማ ብቻ ባለፉት 11 ወራት ወደ 12 የሚጠጉ ሴቶች መገደላቸውን የሚገልጹት የፖሊስ ኃላፊው፣ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን በደል በትኩረት ለመከታተል ከፍትህ አካላት ጋር እየሠሩ እንደሆነም ገልጸዋል።

ከተፈጸሙት ግድያዎች መካከል ከአንዱ በስተቀርሁሉም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ ነው። . . . ዐቃቤ ሕግ አንዳንድ ማስረጃዎችን ከፌዴራል መንግሥት እየጠበቀ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ሁኔታዎች ተመቻችቷልብለዋል።

በጦርነቱ ወቅት በሁሉም የፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጉዳት መድረሱን እና በጦርነቱ የተወሰኑ የኮሚሽኑ መርማሪ እና የወንጀል ምርመራ ባለሙያዎች መሞታቸውን በመግለጽ ይህም ወንጀሎችን በሚመረመሩበት ፍጥነት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩንም አስረድተዋል።

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።