የሰውን ልጅ መኖር በግፍ መቀማት #ስርቆት አይደለምን?
የሰውን ልጅ መኖር በግፍ መቀማት #ስርቆት አይደለምን?
"የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፦
እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።"
(ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱)
እንዴት አላችሁልኝ ክቡራት እና ክቡራን የልቦቼ። ደህና ናችሁ ወይ? ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩ አገዛዞች የሚቆሙት ባላ እና ወጋግራወች ኢትዮጵውያን በሚከፍሉት መስዋዕትነት ነው። የኢትዮጵውያን አብራክ እና ማህፀን ቄራ ነው ዘመን ከዘመን። እግዚኦ። በተለይ አማራ።
እኔ ከተፈጠርኩ፤ ነፍስ ካወቅኩበት ጊዜ ጀምሮ በተፈጥሮ አደጋ ከምናጣቸው ቤተሰቦቻችን በላይ በድህነት፤ በአስተዳደር ብልሹነት፤ በጦርነት የምናጣቸው ወገኖቻችን ይበልጣሉ። በተፈጥሮ ሞት የምናጣቸውም ቢሆን በድህነት የሚሞቱ ወገኖች አሉን። ድህነት እኮ የበሽታ ምንጭ ነው። ጭንቀት ይፈጥራል። ለበርካታ በሽታወችም ያጋልጣል ድህነት። በተስተካከለ የህክምና እጦት ምክንያት የምናጣቸው ወገኖች አሉን።
በእስራት፤ በአፈና የምናጣቸው ወገኖች አሉን። ይህ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሰው ልጅ መኖር ላይ የፈፀመው ስርቆት አይደለምን? የቀደሙትም ቢሆን ሊጠዬቁበት የሚገባ ነው። ሚሊዮን ተረጂ አልበቃ ብሎ ማደህዬትም ታቅዶ እዬተሰራበት ነው።
ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሰባዕዊ ጉዳዮች እያሉ ሚሊዮኖች ከጎርፍ ጋር እያደሩ አንድ አይሉ ሁለት #እዮቤል ቤተ- መንግሥት እና በዛ ዙሪያ ለሚሰባሰቡ ድሎተኞች ሽሙንሙን ቢሮ መገንባት የዜጎችን የመኖር ተስፋ መቀማት አይደለምን? ለዛውም ያለን በቂ - ቤተ መንግሥት እያለን።
በዓለም በአገር ውስጥ መፈናቀል አንደኛ የወጣች አገርን ሥርዓተ መንግሥትን እዬመራህ እነዛን ቀን በሐሩር፤ ሌት በቁር፤ ክረምት #ከጎርፍ ጋር የሚፋለሙ ወገኖችህን የተደላደለ መኖሪያ ሳታዘጋጅ፦ ለዲታ የመዝናኛ ማዕከል ማስመረቅ #ስሮቆት አይደለምን? ዘመን እራሱ እዬተሰረቀ እኮ ነው።
በአንድ ክፍለ ዘመን የሚኖር ህዝብ አለ። ያ ህዝብ የረባ መጠለያ፤ የረባ ከፈን፤ የረባ የለት ጉርስ ሳያገኝ፦ ሰላሙንም ተዘርፎ ከተማወችን በማንቆጥቆጥ ላይ ደፋ ቀና ብትል ለዛ ሊለምን ላፈረ ህዝብ ምኑ ነው? የፈለገ የዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ያድንቅህ - ያንግሥህ። ለእኔ ልሙጥ ነው። መጀመሪያ ዜጎችህ የገመና መከወኛ የለት ልብስ ይኑራቸው። ውራጅ ያጣ ህዝብ ይዘህ የዓለም - ተዋቂ ሰወችን ይዘህ ብትፈነጥዝ ዘመንህን እራስህ እዬሰረቅኽው ስለመሆኑ ሊገባህ ይገባል።
በድህነት ለመኖር ያልተፈቀደለት ህዝብ ይዘህ አዲስ ቤተ - መንግሥት????? ስርቆት ብዙ ዓይነት ነው። ለስርቆት ሳይንቲስትም // ፈላስፋም አልተፈጠረለትም። የገንዘብ ከሆነ ኤዲተር /// የመንፈስ ከሆነ የሰባዕዊ መብት ተሟጋቾች ነው ሊሞግቱት የሚችሉት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ #ፍፁም ደግ፦ ፍፁም #ሩህሩህ ህዝብ ምን ገጠመው?
1) መረጋጋቱ - ተሰርቋል።
2) ሰላሙ - ተሰርቋል።
3) ተስፋው - ተዘርፏል።
4) የመማር #ካንፓሲቲው -ተሰርቋል።
5) ደግነቱ - ተሰርቋል።
6) ቅንነቱ - ተዘርፏል።
7) አብሮነቱን - ተቀምቷል።
8)መተሳሰቡን - ተነጥቋል።
9) መሰባሰቢያው በፈቃዱ #የተደራጁ ባህላዊ መድረኮቹን ተነጥቋል። ወይንም ተስተጓጉለዋል። ዕሴታቸው ጓጉሏል።
ቁቤ - እድር - ማህበር - ወበራ ሁሉም ሰላማቸው ታውኳል። መንፈሳቸው ተበትኗል።
10) የጋብቻ ዕሴቱ ላይ ስጋት አንዣቧል።
11) የጉዞ ፍላጎቱ ላይ ጫና አለበት። ጉዞ ለዲታወች ብቻ ሆኗል። ያላቸው ጉዟቸውን #በአውሮፕላን ብቻ አድርገዋል። ይህም እራሱ አሸባሪ ሊደራጅለት ይችል ይሆናል። እንዳይቀጥል። እምናውቀው ነገር የለም። የሰው ልጅ ተገድሎ፤ መገደሉ አልበቃ ብሎ ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ እኮ አዬን። ተገድሎም የተቃጠለ አለ። ተገድሎም ለጅብ የተሰጠ አለ። #የባቢሎን ጥንስስ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ዕውን እዬሆነ ነው። አገር አቋራጭ አውቶብሶች ሥራ ፈት ሁነዋል። ማለት በአውቶብስ አገልግሎት የተሰማሩ ባልሃብቶች እና ሠራተኞች ችግር ውስጥ ናቸው። በተለይ ሹፌሮች፤ እረዳት ሹፌሮች እንደወጡም ቀርተዋል። ማት ነው ያለው።
12) የመኖር ፈቃዱ ላይ ጭንቅ ተጭኗል። የት ላይ ተሁኖ በምን እርግጠኝነት ቤተሰብ ይመስረት? ሃብትስ እንዴት ይፍራ???
13) ዜጋው ትውልድ የማፍራት አቅሙ ላይ ከፍተኛ ስጋት አለ። ልጆቹ እንደወጡ ነው የሚቀሩት። ይታገታሉ። ይገደላሉ። ይደፈራሉ።
14) ምርቃቱ ወልደህ ሳም፥ ድረህ ኩለህ ሳቅ እዬቀረበት ነው። ጋብቻ ሰብዕና አይደለም መሥፈርቱ ዞግና ቀበሌያዊ ስሜት። በዚህ ዕሳቤ ማግሥትን ደልድሎ በመቀበል ዕሴቱ ላይ ከፍ ያለ ግራጫማ ጫና አለ።
15) በጥበብ ዕድገቱ ላይ እንቅፋት ተደቅኗል። ብቅ ብሎ የነበረው የጥበብ ዓውድ ሙሉ ስድስት ዓመት #ደመመን ውስጥ ነው የባጀው።
16) ዘመን የሰጠው ማህበራዊ ግንኙነት ዘውትራዊ ዕጣ ፈንታው ዕቀባ ነው። ትውልድን የሚያርርቅ መንፈስ ሊታረም ሲገባ ዓመት ይዞ እስከ አመት ሥልጣኔን ገድቦ ኢንተርኔትን መዝጋት ዱድማነት ነው። ሥልጣኔ ጋር ግብግግብ? ከግሎባላይዜሽን ጋር ጦርነት?
17) ዜጋው በዕምነቱ፦ በትዊፊት ላይ ዲያቢሎሳዊ መንፈስ ጋር ነው ግብግብ ላይ ያለው።
18) ነፃነት ቀራኒዮ ተልኳል። የማሰብ፤ የመፃፍ የመሞገት ነፃነት ደንበር ተሻግሮ እኛንም እያሳደደን ነው። ከዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ግንኙነት በሌለን ላይም ሳይቀር። እንኳንስ አገር ላይ።
19) በታሪክ አንባወቹ ላይ ፋክክሩ ደርቷል ዝርፊያውም እንዲሁ።
20) በባህል ዓውድማወቹ ላይ ንቀቱ፤ ስላቁ፤ ማጣጣሉ ከእኛነት ጋር ያለው ፈተና ጎለጎታ ነው።
21) በፊደላት ምህንድስናው ላይ በተለይ በአማርኛ ቋንቋ ላይ የወረደው መከራ ሚዛን የለው። ከዕውቀት ዘርፍ እንዲወጣ ተተግቶበታል።
22) አዲስ ሃሳብ ማፍለቅ በኢትዮጵያ መሳደድን ያመጣል። እራስን ማፈን ደግሞ ያስከብራል።
23) በኢትዮጵያ ተተኪ በማፍራት ተፈጥሯዊ ሂደቱ ላይ ያለው ማዕቀብ ይህ ነው ተብሎ ሊመዘን አይችልም።
#ጎረቤት አገሮች ከአንከሯ ከፓን አፍሪካኒስቷ ኢትዮጵያ ምን ተስፋን በምልዓት አቅደው? ምን ተቸራቸው????
1) በኢትዮጵያ ሁለገብ አደጋ ጎረቤቶቻችን ምን ይሰማቸዋል? የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድን ወደ ሥልጣን መምጣት ሁሉም ጎረቤቶቻችን በደስታ እርችት የተቀበሉት ነበር። የኬኒያ ሙሁራን እንፀልይለት ሲሉ ሁሉ ሚዲያ ላይ አድምጫለሁኝ። ያ ዛሬ አለን?
2) የሱዳን ችግር ከመቼ ወዲህ እንዲህ ተባባሰ???
3) ሰላማዊቷ እህት #ኬኒያ፤ አንድም ቀን ኢትዮጵያን አጥቅታ የማታውቀው ኬንያ ስለምን በቀውስ ተናጠች?
4) ሱማሌ እና ኢትዮጵያስ ምን ሁኔታ ላይ ናቸው? በጋራ ብዙ ነገር የታቀደው ኤርትራን ጨምሮ ያ ስምምነት የት ደረሰ???
5) የቀረው #ዬጁቡቲ ዕጣ ፈንታስ በቀጣይ ምን ይገጥመው ይሆን???? አውራ ጥያቄ ነው።
#ጠቅላይ ሚር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ መደበኛ ዜና በኢትዮጵያ የለም። ሁልጊዜ #ሰበር ነው።
1) ሰበሩ ዜና መርዶ ነው።
2) ሰበሩ ዜና ዕንባ ነው።
3)ሰበሩ ዜና ዋይታ ነው።
3) ሰበሩ ዜና ጭንቅ ነው።
4) ሰበሩ ዜና ስጋት ነው።
5) ሰበሩ ዜና ማህበራዊ ሰላምን የሚያውክ ነው።
5) ሰበሩ ዜና ጤናን የሚጎዳ ነው።
6) ሰበሩ ዜና መከራ ነው።
7) ሰበሩ ዜና ተስፋን ቀሚ ነው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ #የኢሊት ብቻ ነው።
1) በኢትዮጵያ ፖለቲካ ህዝብ እንዲሳተፍ ፈቃድ አይሰጠውም።
2) በኢትዮጵያ ፖለቲካ በዝምታ ውስጥ ያለው ሳይለንት ማጆሪቲ ውክልና የለውም።
3) በኢትዮጵያ ፖለቲካ የኮሌጅ፦ የዩንቨርስቲ መረጃ ማቅረብ ያልቻለ ከሰውም አይቆጠር። የፈለገ ሁለገብ አቅም፤ ክህሎት ይኑረው።
4) በኢትዮጵያ ፖለቲካ እግዚአብሄር በሰጣቸው ቅንነት፤ መክሊት እና ፀጋ አገራቸውን በተመክሯቸው በነፃ የሚያገለግሉ ጭራሽ ከቁጥር ውስጥ ተመዝግበው ፈጽሞ አያውቁም። ሚዲያውም የረሳቸው ናቸው።
5) በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውህድ ማንነት // ከሁለት በላይ ከሆኑ ዞጎች የተወለዱ ምንም ዓይነት ትኩረት አይሰጣቸውም። መጠጊያም የላቸውም። ኢትዮጵያኒዝም ባለቤት የለውምና።
6) በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሌላ አገር ዜጋ ጋር ጋብቻ ተፈፅሞ ስለሚፈጠሩ ልጆች ዕሳቤ የለውም።
7)በኢትዮጵያ ፖለቲካ #በልጆች ጉዳይ ላይ ፈፅሞ ትኩረት የለም።
8) በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ኢትዮጵያ በኽረ አጀንዳ አይደለችም። ቢኖርም ፌክ ነው። የኢትዮጵያ የኢሊት ፖለቲካ አገሩን የረሳ ፖለቲካ ነው።
1) አሁን የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ፖሊሲ ምን እንደሆን አይታወቅም።
2) ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያላት አቋም ግልጽነቱ ምን ያህል እንደ ሆን እኔ በግሌ አላውቅም።
ኢትዮጵያ የምታራምደው ምን ዓይነት ርዕዮትዓለም እንደ ሆን አይታወቅም። ድፍን ወይንም ድንቡልቡል ነው።
#ተስፋ።
ተስፋን ለኢትዮጵያ ሳስበው ይከብደኛል። እኔ በተስፋ ዙሪያም ስለምተጋ፤ ተስፋም እግዚአብሄር ነው ብዬም ስለማምን።
የወደፊቷ #የኢትዮጵያ በሥርዓት ተስፋን ለመቅረጽ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ………
1) ከአንድ አክቲቢስት ህሊና በላይ ነው።
2) ከአንድ ጠቅላይ ሚር አቅም በላይ ነው።
3) ከአንድ ዩቱበር ባለሚዲያ ችሎታም በላይ ነው።
4) ከአንድ የፖለቲካ በሳል ተንታኝ ተመክሮም በላይ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተንታኙ ቁጥር ስፍር የለውም።
5) ከአንድ ጥሩ ተናጋሪ የንግግር ጥበብ በላይ ነው።
6) ከአንድ በጎ አሳቢ ችሎታ በላይ ነው።
7) አጋጣሚ ካገናኛቸው የተወሰኑ #ስብስቦችም ህሊና በላይ ነው።
8)ከተወሰኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከሚተጉ የሙሁራን የኢሊት ስብስብም ሙያዊ አቅም በላይ ነው።
9) ከአንድ ፕሮፌሽናል ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛም ህሊና በላይ ነው።
#ስጋት።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሥርዓት አልበኝነት ጀማምሯል ከምል ተላምዷል ብል ይቀለኛል። በመጠነ ሰፊ ከቀጠለ ለቀጠናውም እጅግ አስጊ ነው። የህግ የበላይነት ኢትዮጵያ ውስጥ ፈተና ላይ መሆኑን ሙሉ 5 ዓመት ጽፌበታለሁ። ሞግቸበታለሁ። ቅልቅል ነው። የወንጀሎች ዓይነት ያልተለመዱም አሉበት።
ወንጀሉን በመንግሥታዊ አካል፤ ወይንም ስውር በሆኑ ኃይላት ወንጀል በማን እንደሚፈጽም አይታወቅም። እኔ እንዲያውም እማዬው "#የሞገድ ጋዜጣ" ልበወለድ ትዕይንትን ነው እያዬሁ ያለሁት። ብዙም ጽፌበታለሁኝ።
ቅንነት። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በቅንነት ድርቅ የተመታ ነው። የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት የሚችለው አቅም ያለው በተፈጥሯዊው ቅንነት ብቻ ነው። ፖለቲከኞች ተቋስለዋል። ቅንነትን አምጦ ለመውለድ የሚያዳግታቸው ይመስለኛል።
………… ስለዚህ የእኔ ዕይታ።
1) በምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ያልነበራቸው ከዝምተኛው ሳይለንት ማጆሪቲ ውስጥ ያሉ፦
2) በተፈጥሯቸው አዛኝ የሆኑ ሩህሩኃን፦
3) በተፈጥሯቸው ቅን የሆኑ፦
4) በተፈጥሯቸው የሰው ልጆችን እና ተፈጥሮን የሚወዱ፤ የሚያከብሩ፦
5) የኢትዮጵያ ህዝብ በጭካኔ ተቀጥቷል፦ ስለዚህም አይዟችሁን የሚደፍሩ አጽናኞች፦
6) በመልካምነት ትጋት ያላቸው ወገኖች።
7) ግሎባሊስት የሆኑ፦
8)አወንታዊ የሆኑ ፖዘቲብ ቲንከሮች
ከእነዚህ የተውጣጣ ትውልድ እና አገር እልፍ ሲልም አህጉርን፦ ከዚህም በዘለለ ለግሎባሉ ዜግነት ክብር የሚሰጡ ቅኖች በቲም ኢትዮጵያን እንዲመሩ እመኛለሁ። እግዚአብሄርን የምጠይቀውም ለኢትዮጵያ ይህን ዕድል እንዲያመቻች ብቻ ነው። ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊም ሆነ እስከ አሁን ካዬናቸው የፖለቲካ ድርጅት ተሳታፊወች ባሻገር ማለም ይገባል። የሚል የፀና ብርቱ ዕምነት ነው እኔ ያለኝ።
ለጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ህሊናም ምቾት የሚሰጠው ይህ መንገድ ይመስለኛል። የሚያውቁት ሰብዕና ከሆነ ፈቃዳቸውን ማግኜት ይከብዳል። ተፈጥሯቸው ስስ ነው። ሚዲያ ላይ እኮ ቀርበው አያውቁም። በሎሬት የሽልማት ጊዚያቸውም አልደፈሩም። ቀውሱን ያውቃሉ። ይህ እንዲሞግታቸው ፈቃደኛ አይደሉም። ሚዲያን አጥብቀው ይፈራሉ። የራሳቸው ፋንታዚ ፈጥረው በዛው ውስጥ ሲፍለቀለቁ ውለው ያድራሉ።
#ኃይል እና ጉልበት ጦሱ።
ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እንደ ቀድሞ ጠቅላይ ሚር አቶ ኃይለማርያም ደስአለኝ አይደሉም። ወይንም ልቀቅ ተብለው ይሁን በፈቃዳቸው ይልቀቁ ይህን ለታሪክ ባለሙያወች ትቼ እንደ ኮነሬል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዓይነት አይመስሉኝም። ሥልጣናቸውን ከመልቀቅ ጋር ዓለም በቀውሱ የምትናጥበትን ሁኔታ ከማደራጀት ይቆጠባሉ ብዬ አላምንም። አሳቻ መሪ ናቸው። እሳቸውን ማንበብም፤ መተርጎምም ይከብዳል። ቅጽበታዊም ይመስሉኛል በርቀት ሳያቸው። ብስጩም ይመስሉኛል።
የዛሉ፤ የደከሙ፤ አቅም ያነሳቸው የሚመስሉት አቅደው ይመስለኛል። በሙያቸው ሰላይ መሆናቸውን መርሳት አይገባም። ሁሉም የመንግሥት ሚዲያው ኃላፊወች፤ ፤ ምክትል ጠቅሚሩ ሰላዮች ናቸው። ብዙ ነገር ቁልፍልፍ ነው። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ለሙሉ ዘመናቸው ቤተ - መንግሥት እዬገነቡ ነው። የራውንዳ ዓይነት ለዘለቀ ዘላለማዊ ገዢነት ነው እዬተጣደፋ የሚገኙት። ካቄሙ በቀላቸው ኪሎግራሙን መተመን አይቻልም።
መፈንቅል የሚጠማቸው አሉ። እኔ የዛን ሃሳብ አልገዛም። በ80 ከዛም በሚበልጡ ብሄረሰቦች ዕውቅና የቆመች አገር? በዚህ ላይ የሃይማኖቱ ኢንተግሬሽን ሲታከል፤ በተጨማሪም አካባቢያዊ ስሜት ታክሎ አደጋው ከቁጥጥር ውጪ ሊወጣ የሚችልበት ዕድሉ ሰፊ ነው። ለመሆኑ በጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ዙሪያስ ሰባዕዊ? አዛኝ? አጽናኝ? የአይዟችሁ አርበኛ አለን? ለማናውቀው ልሙጥ ዕድል አቅም ሊባክን አይገባም ባይ ነኝ። ተስፋዬ 0% ነው። የዚህም አቀንቃኝ አይደለሁም። ይተው ቢባሉ እኮ ዛሬ ካለው ደረጃ መከራው አይደርስም ነበር።
የሚያጨበጭቡላቸውም፤ የሚደግፏቸውም መንፈሱን የጭካኔው ስለተመቻቸው ነው። ስለዚህ ከዚህ ስብስብ ደግነት አላስብም። ሙሉ ዕድሚያችን ለከፈለነው መስዋዕትነት ከኢህአዴግ የወጣው የቲም ዶር ለማ እና የቲም አቶ ገዱ ቅንጅት ምን መዓት እንዳፈሰሰብን አይተናል።
ያ ሁሉ የተገበረ ህዝብም አስተዋሽ አልቦሽ ሆኖ ነው የቀረው። ሳናውቃቸው ሙሉ ድጋፋችን ሰጥተን ተቀጥቅጠናል። ኢትዮጵያም መፈራረጃ ሆናለች። እና መፈንቅለ መንግሥትን ተንተርሶ የሚመጣው ኃይል የባሰም ሊሆን ይችላል። ተሽሎ የሚታዬው በዋዜማው እና ለአጭር ጊዜ ብቻ ሊሆን ይችላል። እኔ በዚህ ፍፁም እምነት የለኝም። #በጨለማ ውስጥ መዳህ ጉምን መጨበጥ ማለት ነው ለእኔ።
#ምን መደረግ አለበት?
አቅም ያለው ተፈጥሯዊ፤ ሰባዕዊ ቲም ውጬ አገር ከተደራጀ፦ ይህም አገር ውስጥ ፈፅሞ አይቻልም። እስከ አሁን ልፍስፍስ በሚል ፕላን እና አነጋገር እሳት ውስጥ የተማገዱት ይበቃል።
የሆነ ሆኖ ሙሉ ስድስት ዓምት ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊም፤ ካድሬወቻቸውም ሁልጊዜ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መፈንቅለ መንግሥት ታሰበብን ነው። የዘወትር ሰበር ዜናው ይህ ነው። ኮሽ ባለ ቁጥር የሚደነግጥ// ያረገረገ ሥርዓት እንደ ጠቅላይ ሚር አብይ ዘመን አላዬሁም። ሥርዓቱ ደንጋጣ እና ተርበትባች ነው።
የዶክተር አብይ መንግሥት ረጋ ብሎ ያሳለፈበትን ጊዜ አላስታውስም። ብንን ብንን ነው የሚል። ይባትታል። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ በፓርቲያቸው በብልጽግና ጉባኤ የሚያምኑት ሰው አጥተው የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ እራሳቸው ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ነበሩ። ይህ በዬትኛውም ዓለም የፖለቲካ ድርጅት አደረጃጀት ፈጽሞ ሆኖ የማያውቅ፤ የማይፈቀድም ነው። እኔ በሙያዬ አደራጅ ነው የነበርኩት። ምርጫ በአስመራጭ ኮሜቴ፤ ጉባኤ ብሄራዊ ከሆነ በፕሪዚዲዬም ነው የሚመራው።
የሆነ ሆኖ የኢትዮጵያ የገዘፈ ውስብስብችግር ይሁን፤ የኢትዮጵያም ተፈጥሮ ከጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ ህሊና በላይ መሆኑን እሳቸውን ዶር አብይን ማሳመን ይገባል። ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ አሊ ለአህጉሩም፤ ለቀጠናውም፤ ለአፍሪካ ቀንድም እንደ ዓለም የሰላም አባትነታቸው፤ እንደ ሎሬት ተሸላሚነታቸው ሊያደርጉት የሚገባ ፍፁም የሆነ ተግባር ፈቅደው እና ወደው ሥልጣናቸውን በክብር እንዲያስረክቡ ማግባባቱ ነው ሊጠቅም የሚገባው።
ይህ ቅናዊ ርጉ ስልት ብቻ ዊዝደም ሆኖ ኢትዮጵያን ከተጨማሪ ጥቃት ሊያድናት ይችላል። የኢትዮጵያ ጉዳይ ከሱዳን ችግርም የበረታ ነው። ጠቅላይ ሚሩ ዶር አብይ ናቸው። ሥልጣናችን ከተነካ 100 ሺ ሰው በቀን እናርዳለን ብለው ደፍረው የተናገሩ መሪ ናቸው። ማዕከላዊ የአመራር ስልታቸው የሰው ልጅ አይደለም። የሆነ ሆኖ ነገረ ኢትዮጵያ አብዝቶ ማስተዋልን በአጽህኖት የሚጠይቅ ነው። ይህ ከቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አንኳር ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚር አብይ የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ በጽኑ ሊሠራበት ይገባል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ50 ዓመት በላይ ለዘለቀው ችግር መፍትሄው መሮጥ አይደለም። ተረጠ እኮ። ያዬሁት አፍሶ መልቀም፤ ለቅሞ ማፍሰስ ነው። በፖለቲካ ድርጅት ውስጥ አንጃ ይፈጠራል። ይበተናል። መልሰው ደግሞ እነዛው ሰወች በአዲስ ሥም ይመጣሉ።
በዚህ ለመሆኑ በንቃት የሚሳተፋት የኢትዮጵያ የፖለቲካ እሊት እስቲ እንስማ ጥሞና ላይ ናቸው ሲባል። የኢትዮጵያ ችግር በለብ - ለብ፤ በውሽልሽል፦ በድረስ ድረስ፦ በለበጣ ጊዜያዊ ስብስብ፦ በሽንገላ እና ጥዴፊያ ዘላቂ መፍትሄ ፈፅሞ ማምጣት አይቻልም።
መመኘት ይቻላል።። አብዛኛውን የሚያረካ ስኬት ግን በግርግር ፖለቲካ አይገኝም። ወይንም በደጋፊ ብዛት፤ ወይንም በተጽዕኖ ፈጣሪነት ዊዝደም አይፈልቅም።
ስክነት - እርጋታ - ማድመጥ - እራስን ማሸነፍ - ለውዳሴ ከንቱ ያለውን የፎቶ ሾው መግታት ይገባል። ከሁሉ ግን ዕንቁውን፤ አልማዙን ቅንነት መድፈር ይጠይቃል። እራሱን የገዛ፤ ምራቁን የዋጠ፤ በተመክሮው ያፈራ ኢትዮጵያዊ ቲም ብቻ እኔን ይናፍቀኛል። ጠረኑም ተግባሩም ከግል ዝና የዘለለ አቅም እና ክህሎት ያለው።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉ©ተሥላሴ
Sergute©Selassie
09/07/024
ጊዜ ራዲዮሎጂ ነው።።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ