UEFA Champions League 2018.

       
        አሳዛኙ ስውር የራሞስ ሴራ አሸነፈ።

                                 ከሥርጉተ ሥላሴ 27.05.2018 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።)

               „ልጄ ሆይ በክፉ ሰዎች አትቅና፣ ከእነሱ ጋር መሆንን አትውደድ፣ ልባቸው ግፍን ታስባለች እና፣
                    ከንፈራቸውም ሽንግላን ትናገራላችና።“ (መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፳፬ ቁጥር ከ፩ እስከ ፪ ።)



የ2018 የአውሮፓ ሻንፒዮን ሊግ የዋንጫ ውድድር ፍጻሜ ቀን ነበር - 26.05.2018። እኔ ለሁለቱም ቡድኖች በተመጠነ ስሜት ለመከታታል ነበር ዕለቱን የታደምኩት። ምክንያቱም እኔ ወይ ከገዳመ አገር ከሲዊዝዬ አንድ ክለብ ወይ ከጀርመን ባዬር ሙንሽን / ዶርትሙንድ ቢኖሩልኝ ነበር ምኞቴ። የሆነ ሆኖ ያው ዘረ ዶርትሙንድ ስለነበር የተሻለ የስሜት ዝንባሌ ነበረኝ። የአስልጣኝ ዩርግን ክሎፕ አብነታዊ የውሳኔ ሰብዕና እጅግ ስለምመሰጠበት ዝንባሌዬ ለሊቨርፑል ነበር ማለትን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁኝ። ያው የጠይም ዕንቁ ቤተመንግሥታዊ የሰርግ ማግስትም ስለሆነም ወደ እዛ ወፍ ቢያዳላ ምርጫዬ ነበር። በዛ ላይ አፍሪካዊነትም በኮብነት ሴኒጋል እና ኢጅብት በጉልሁ አለበት። የስፔን ደጋፊ ሆኜ አላውቅም። በተለያዩ ሁነቶች በገጠሙኝ አመክንዮች የተጫኝነት መንፈስ አለባቸው።
  • ·         ንዲህ ነው የሆነው … እንዲህ

በኮከብነት ተጫዋችነቱ የስፔኑ ብሄራዊ ተጫዋች ራሞስ ከአገሩ ክለቦችም ለሪያል የረጅም ጊዜ ተጨዋች ነው። ዛሬ የሰራው ሴራ ግን ፈጣሪ አምላክ አንድ ቀን ብድሩን ይሰጠዋል። እንዲዚህ መሰል ከጨዋታ ህግ ውጪ በረቀቀ ሁኔታ ሴራን አቅደው የሚከውኑ ስፖርተኞች መጨረሻቸው በዝምታ የተከደነ ይሆናል። ዓለምም ከዚህ ቀደም ልብ አላለው ካልሆነ ታድሞበታል።
ጨዋታው በዩክሬን ነበር። ለአውሮፓ ሻምፒዮን ሊግ ፍጻሜ ውድድር የሁለቱም ተጫዋቾች ደጋፊዎች አኩል በሚያስብል ደረጃ ፉክክር ይኖራል የሚል መንፈስ ነበር - ሲጀመር። እርግጥ ነው በመጀመሪያው የጨዋታ ደቂቃዎች ውስጥ በተካሄደው የሁለት ዘውዶች ውድድር ላይ ተጽዕኖው አይሎ የነበረውን የሊቨር ፑል ቡድን የጀርባ አጥንት ለመስበር በታቀደው ትልም ተሳክቷል። መግቢያውም ተስፋውም ሙሉ ነበር። ሊቨር ፑሎች የተሻለ የጫዋታ አቅም አሳይተው ነበር። እውነት ለመናገር ሪያሎች በመጀመሪያዎቹ መቅድመ የጨዋታ ፍልሚያ ደቂቃዎች ተፎካካሪያቸውን ሊቨር ፑልን ፈርተው በለብታ ስሜት ነበር ሲባክኑ የታዩት - ለእኔ።

ልክ 26 ደቂቃ መባቻ ላይ በጸሎት ጨዋታውን አህዱ ያለውን የኢጅብቱን አፍሪካዊ የእኛዊነት ቀለም ብሄራዊ ተጫዋች፤ የሊቨር ፑሉን አህመድ ሳላህን አድኖ የክርኒውን ጡንቻ አካባቢ ጉዳት በማድረስ ከጨዋታ ውጪ ያደረገው የሪያሉ የራሞስ ስውርነት ሴራዊ ትልም የሊቨር ፑሉን የማሸነፍ ድባብ ጉም ያለበሰ ክስትት ነበር። ያ ቅን ተጫዋች ጨዋታውን ለመቀጠል ትንሽ እንደ ተንቀሳቀሰ አለመቻሉን ያረጋገጠ ገጠመኝ ምልክት ሰጠና ዕንባውን እያፈሰሰ ከጭዋታ ሲወጣ ወፏ እንዳላወጣቻቸው የነገረቻቸው ጀርመናዊ የዶርት ሙንድ አሰልጣኝ ዩርግ ክሎፕ ፊታቸው የሃዘን ማቅ ለበሰ። ደመመን ተጫናቸው።

እኒህ አሰልጣኝ የዶርት ሙንድ የቢጫ ጥቁር ማልያ አውራ የነበሩ ሲሆን፤ ዶርትሙንድ ለትልቅ ደረጃ ያበቁ፤ ለራሱ ለጀርመን ብሄራዊ ቡድን የ2014 የፊፋ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድር ለዋንጫ ከአርጀንቲና ጋር በነበረው ፉክክር ጀርመንን ለድል እርካብ ያበቃው ማርዮን ጎትሰን እና ቁጥራቸው በርከት ያሉ ብሄራዊ እና የክለብ አንቱ ተጫዎችን ኮትኩተው በማብቃት ለዕውቅ ዝና ያበቁ ውጤታማ አስልጣኝ ናቸው። ልጆቻቸውን ማብቃት ነው ህይወታቸው። የጀርመኑ ዶርትሙንድ የማሸነፍ አቅሙ እዬሳሳ ሲመጣ፤ በብሄራዊ ጨዋታም፤ በሻንፕዮን ሊግ ጨዋታም ከደረጃው ዝቅ እያለ አቅም እያነሰው ሲሄድ፤ ጥረታቸው ፍሬው መባከኑን ሲመለከቱ ጉዳዩን በልባቸው መስጥረው በተመስጦ ሲከታተሉት የነበሩት ትንታግ አሰልጠኝ ዩርግ ክሎፕ ችግሩ እኔ ልሆን እችላለሁኝ የችግሩ ምንጭ እኔው ነኝ፤ እኔ የቡድኑን እድሉን ጋርጀዋለሁኝ የቡድኑን ብለው ካለምንም ቅድመ ሁኔታ የቡድን አስልጣኝ ሃላፊነቱን ሲለቁ ድንጋጤው ቀላል አልነበረም። ድንጋጤው ብሄራዊ ነበር ማለት ይቻላል። ድንገተኛም ነበር።

ስንበታቸውም ልብ የሚነካ የሚመስጥም ነበር። እኔ ከሥነ ጹሑፍ ባለነሰ ለእግር ኳስ የተለዬ ፍቅር እና ክብር አለኝ። የሰው መገናኛ የፍቅርም መገለጫ ዕልፍኝ ነው እግር ኳስ። የፍሰሃ፤ የሰናይ፤ የሳቅ እና የዕንባም ቤተኛ ነው። በፍቅር ውስጥ ሳቅ ብቻ ሳይሆን የፍቅር ዕንባም አለ። በፍቅር ውስጥ አዎ ብቻ ሳይሆን አዎንታዊ አይም አለ። ስፖርት ውስጥ የሚፈሱ ዕንባዎች ሰውኛም ተፈጥሮኛም ናቸው። የፍቅር ተፈጥሯዊ ዕውነተኛው ባህሪ ገላጭ ቢባል እናት እና የስፖርት ማልያ ናቸው - ለእኔ።

ወደ ቀደመው ስመለስ እኒህ በእግር ኳስ ዓለም ውስጥ ከኢጎ እና ከፍቅረ -ንዋይ ፍቅር የሌላቸው፤ በራሳቸው ማንነት የሰከኑ ታላቅ ጀርመናዊ የእስፖርት አሰልጣኝ ዩርግ ክሎፕ ለዓለም ያሰተማሩት ታላቅ ነገር፤ ባዶ እጅም ተሁኖ፤ ምንም ሌላ የመንፈስ ማሳረፊያ ሳይኖር ክብርን፣ ዝናን፣ ማህያን ንቀው በፈቃድ አጓጒውን ዕውቅና መልቀቅን ነበር። ለቲማቸው የበለጠ ዕድገት እና ዕድል ራስን ሰማዕት ማድረግ። እኒህ ታላቅ ሰው የግል ኢጎን የተዋጉ አስልጣኝ ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ የግሎባል ጀግና ናቸው። ለጀርመንም ታላቁ ሽልማት ናቸው። ከዚህ በኋላ ነበር የሊበር ፑል አሰልጣኝ ሆነው የተቀጠሩት። እርግጥ ነው ዶርትሙንዶች ከፍቷቸዋል። መከፋታቸውን በአደባባይ ከሊቨር ፑል ጋር በነበራቸው ጨዋታ ሜዳ ላይ ሁሉ ገልጸዋል። ያም ከፍቅር፤ ከመውደድ፤ ከመታመን፤ ከመሳሳት የመጣ ስለሆነ አዎንታዊ ነው። ሰው የሚወደውን ሲያጣ፣ መከፋቱ ከፍቅር ተፈጥሮ የመነጨ አዎንታዊ የመልካምነት ቤተኝነት ነው። አትሂድብን፤ አንጣህ፤ እንይህ ሁልጊዜ፤ ልናገኝህ እንፈቅዳለን ነው። ይህ ተፈልጎም አይገኝም።

የሆነ ሆኖ እኒህ ዕውቅ አስልጣኝን ፊፋ ራሱ ሊሸልማቸው እና ሊያከብራቸው የሚገባ ልዩ ሰው ናቸው። የግል ኢጎን ለማልያ ፍቅር በማስገዛታቸው። ክብርን አልፍልግህም ብሎ ገፍቶ ቤት መቀመጥ። ካለ ሥራ። እኒህ ሰው ታሪካቸው ሊዘከር የሚገቡ ታላቅ ሰው በፈቃዳቸው ያን ሙሉ ሥልጣን እና ተወዳጅነት ሲለቁ ያዘጋጁት የሥራ ቦታ አልነበራቸውም። እኔም ያን ጊዜ ይህን ናሙናዊነት እርምጃን መሰረት አድርጌ በኢትዮጵያ እንደ ሙጫ ሙጨጨ ያለውን ሥልጣን ከወንበር ጋር መጣበቅ ሁኔታ በተመለከተ አንድ ጹሑፍ መጻፌን አስታውሳለሁኝ።

ዛሬም እኛ እንደ ቀላል አዬነው እንጂ የቀደምው ጠ/ ሚር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ያደረጉት የዘመናት የማይደፈር አይነኬ አመክንዮ ይህን መሰል በራስ ላይ የሚወሰድ ቆራጥ እርምጃን ነው። እኛን የሚጨንቀን የጋህዳዊ ዓለም ውርክብ ሆኖ እንጂ መንፈሳዊ ሃብቱ ጥልቅ ነው። ለቀጣዩ ትውልድ አንተም / አንቺም ነገ ይህን ቦታ በጥረትህ / ሽ፤ በብቃትህ / ሽ፤ በችሎታህ / ሽ ልክ ታገኘዋለህ / ሽ ነው። ትውልድን በፖለቲካ ተሳትፎ ተስፋ የመገንባት ታላቅ ትውልዳዊ ድርሻቸውን ነው የተወጡት። ይህን ት/ ቤት ከፍተህ፤ መጸሐፍ ዘርግተህ 100 ዓመት ብታስተምረው ተግባር ከሌለበት ወና ነው። 43 ዓመት እኮ የዴሞክራሲ ቃለ ምህዳን በአላዛሯ ኢትዮጵያ እኮ ዝንጥ ብሎ ግድግዳ ላይ በቄንጠኛ በፍሬም ተሰቅሎ ኖሯል። ስለሆነም የቀድሞው ጠ/ሚር አቶ ሃይለማርያም ደስአለኝ በፈቃድ ከሥልጣን መልቀቅም ሆነ የአሸኛኝት ሥርዓቱ ሂደት የቁስ ጉዳይ አይደለም። የትውልድን ሞራል የማነጽ ነው። ነገንም ማሰናዳት ነው። ይህ የመኖርን ትርጉም ለታዳጊ ወጣቶች ያመሳጠረ እርምጃ ነው። አኔም ነገ የሚል ታላቅ መነቃቃት ይፈጠራል። አሁን እኮ በጠ/ ሚር አብይ አህመድ ሥር እንደ አንድ ዜጋ እዬተመሩ ነው የቀድሞው ጠ/ ሚር አቶ ሃይለማርያም ደስአለኝ። አልሸፈቱ፤ አገር አለቀቁ፤ አልተሰደዱ።
  
ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ጀምሮ በነበረው የመንፈስ መሰባሰብ ጥረት 84% ደስታ መገኘት ቀላል ትርፍ አይደለም። ይህ ከሥነ - ልቦና ስጋት መዳንም ነው። የሥነ - ልቦና መዳን ነው የውስጥን ሰላምን መልሶ ሰውን ወደ ኑሮው፤ ወደ ተስፋ ማድረግ የሚመልሰው። ሰው መናገር ካልቻለ በሽተኛ ነው የሚሆነው። ከ27 ዓመት በኋዋላ ቢያንስ „መሬት ደም ጠጥታ ኖረች፤ ደም አበቀለች፤ ያበቀለችው ምርትም ሰብልም እዬተመገብን መኖር ተገደድን“ አንድ ወንድሜ ጋንቤላ ላይ የተናገሩት ነበር „ስሞት ልጆቼን ለማን ትቼ ልሂድ፤ የትስ ነው የምቀበረው“ ሌላው ወገኔ የገለጹት ነው። ማስተዋሉ ላልተነፈገ ዜጋ ይህ ሥጋዊ አይደለም መንፈሳዊ ነው። ድምጻቸውን የወገኖቻችን መስማት። ገፃቸውን ማዬት ሌላ የዜግነት ማህሌት ነው። እራሱ ሂደቱን ከወትሮው በተለዬ ሁኔታ ዛሬ ምን አዲስ ነገር አለ ብለን ህሊናችን ሸልመን፤ ለማድመጥም አቅም ኖሮን መትጋት ትርፉ ረቂቅ ነው። መንፈሱንም ወደ ራሳችን ለማስጠጋት ያሳዬነው አዎንታዊ መንፈስም ሌላው አዎንታዊ ታሪክ ነው።

በሌላ በኩልም አቦ ለማ መገርሳም እዬቻሉ የእሳቸውን ክብር ለዶር አብይ አህመድ አሳልፈው መስጠታቸው ሌላው የታምር ምዕራፍ ነው። ሰሞኑን በጋንቤላውም ህዝባዊ ስብሰባ ላይ አቦ ለማ መግርሳ እታች ቁጭ ብለው፤ ዶር አብይ አህመድ ደግሞ ሰብሳቢ ሆነው የሚሰጡትን መመሪያ ለማድመጥ መፈቀዳቸው የትኛው ዓለም ውስጥ ኢትዮጵያ እንዳለች የምግባር፤ የሞራል፤ የመሆን አብነታዊ መንገድ ነው።

በሌላም በኩል በሌሎች የሰብዕና ስስነት እና አማራዊ በሆኑ የህልውና ወሳኝ ጉዳዮች ላይ በፍጹም ሁኔታ የማይመቹኝ አቶ ደመቀ መኮነንም ራሳቸውን ከጠ/ ሚርትርነት እጩነት ፈቅደው ማግለላቸው ብቻ ሳይሆን ጠ/ ሚር አብይ አህመድ በሚመሯቸው ልዑኮች ሁሉ ከሥራቸው ሆነው መመሪያ ለመቀበል የሚያደርጉት ጥረትም መልካምነት ያለው የለውጥ መንፈስ ነው። ከዚህ ቀደም በእስራኤል አገር በነበረው የኢትዮጵያ የልዑክ ቡድን በመሪነት አቶ ደምቀ መኮነን፤ በልዑክ አባልነት ደግሞ ዶር አብይ አህመድ አብረው ሄደው እንደ ነበረ የሚታወስ ነው።

ያን ጊዜ ነው „የዛሬ 25 ዓመት እምታልማት ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች?“ ሲባሉ „እኔ እማልማት ኢትዮጵያ 25 ዓመት ይረዝምባታል፤ ካዛ ባነሰ ጊዜ እኔ አማልማት ኢትዮጵያ ዕውን ትሆናለች። ይህን የምልበትም ተጨባጭ፤ መሬት የያዘ አምክንዮ ስላለ ነው“ በማለት ለቀረበው ጥያቄ ተስፋዊ መልስ የሰጡት ዶር አብይ አህመድ የዛሬው የኢትዮጵያ መሪ ናቸው። ስለዚህ ላይ እና ታች፤ ታች እና ላይ ሲኮን ያለው መንፈስ በእነዚህ አራት ኢትዮጵውያን የፖለቲካ ሊሂቃን ጤናማ አብነታዊ ጉዞ ላይ የተለዬ ረቂቅ የሆነ ትውልድን፤ ማግሥትን የማዳን ቅዱስ መንፈስ አለ ብዬ አምናለሁኝ - እኔው።

አሁን ወደ ቀደመው ነገረ ስመጣ ከራሞስ ሴራ በኋዋላም የሪያል አንድ ተጫዋችም ከሴራ በጸዳ የጨዋታ መገፋፋት ተፈጥሮ ጨዋታውን ሳይቀጥል ሲወጣ፤ ለእረፍ እስከ ወጡበት የግማሽ ጨዋታ ክፍለ ጊዜ ድረስ ግብ አልተቆጠረም። መረብ እና ድንቡልቡል ቡና አልተጣጡም ነበር እንደ ማለት።

ከእረፍት መልስ እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ይህን ገጠመኝ ያዬሁት 51ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ድራማ ተፈጠረ። ጎል ለማግባት የሪያሉ ተጫዋች ቤንዚማ ሞክሮ ሳይሳከለት የቀረውን፤ የሊቨርፑል ጎል ጠበቂ ሎሪስ ካርዮስ በተረጋጋ መንፈስ አርቆ ከጎሉ ደንበር በረጅሙ መምታት ሲገባው ትንፋሹን ሳይሰበስብ፤ ለራሱ የቡድን አባል እንደሚያቀብለው አመቻችቶ ኳሷን መልሶ መረቡ አጠገብ ላለው ለተፎካካሪው ቡድን በቅርቡ ለሚገኘው ጥቃት ለሰነዘረበት ለቤንዚማ አቀባይ ሆኖ ከፔናሊቲ በላይ ደልድል ያለ፤ ኮራ ያለ፤ የልብ አድርስ ጎል ሰማያዊ ድል ለሪያል በመሸለም በራሱ ላይ አንድ በማስቆጠር አንድ ለባዶ መምራት ጀመሩ ሪያሎች። ቅጽበቶ ፖዝ አልነበረውም። ጠይሙ ዕንቁ ሴኒጋላዊው ህብራችን የሊቨር ፑሉ ባለ 19 ቁጥሩ ዛዲዮ ማነ እልሁን ዋጥ አድርጎ ፈጣን ጥቃቱን የተወጣበትን የመጀመሪያ ብሥራቱን በ54 ደቂቃው ላይ ዓወጀ። የሪያል መረብም የጥቃት አዬር ጎሰማት።

ከዚህች ቅጽበት በኋዋላ የጨዋታው አዬር ሙሉ ለሙሉ በሚገርም ፍጥነት ተለወጠ። እኩል ለኩል ሆነ ድባቡ። የኔዎቹ ቅኖቹ እስኪ ….  የዚህን ጊዜ የራሞስ ዓይን ጨዋታውን በምለሰት ተከታተሉት እና እዩት። ሴራዬ ከሸፈ በማለት ነብር ሆኖ ነበር። እራሱ ክርስቲያኖ ሮናልዶም ጭስ ፊቱ ላይ ይታይ ነበር። ምን ነበር ፆመ ረመዳን ይህን የአፍሪካ ዕንቁ የሳላህ አላህ ቢታደገው? ምን አለ በመንፈስ የአፍረካ የእግር ኳስ አምድን መንፈሳቸው ክፍት ብሎት የሰነበተውን ጉልላቱን፣ ድንቁ ዝክረ አፍሪካን ይድነቃቸው ተሰማ በመንደረ አጸደ አርያም ደስ ቢላቸው ምን በነበረ? ኢጂብቶች ለ አፍሪካው የእግር ኳስ ቀንዲል ልዕልና አክብሮታቸው የሰንደቅ ያህል ነው። ለቅዱስ አባታችን ለአቡነ ተ/ ሃይማኖትም እንዲሁ።

የሆነ ሆኖ ይህን እኩል የመራመድ ያልፈቀዱት የቀደምው የፈረንሳይ ኮከብ ብሄራዊ ተጫዋች የነበሩት፤ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የሪያል አስልጣኝ የሆኑት ጭምቱ የሲዳን መንፈስ የተጫዋች ለውጥ ጆክር አመጡ። ያም የዌል ዝነኛ ተጫዋች ለግላላው ቤል ነበር። ቤል የፊፋም ተሸላሚ ነው። ቤል ጎልቶ የወጣው በፊፋው የ2016 አውሮፓው የእግር ኳስ የፈርንሳዩ ብሄራዊ የጨዋታ ሜዳ ላይ ነበር። ያን ጊዜ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደፊት ከገሰገሱት አውሮፓዊ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል አንዱ ዌል ሲሆን አውራውም ቤል ነበር። ቀልብ የሳበ፤ መንፈስን የሚገዛ የአጨዋወት ብቃት ያሳዬ ተጨዋች ብረት መዝጊያ ነው ለዌል።

የሪያሉ ቢል በጨዋ ደንብ ተለውጦ ገብቶ ያገኛትን ኳስ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ዕድሉን በአግባቡ በላቀ ክህሎት ተጥቅሞ በረጅሙ ለግቶ በተክሊል ከመረብ ጋር አጋባት እና ድንቡልቡሊትን አፍነከነካት። ፈረንጆች ድሪም ላይክ የሚሏት ዓይነት ነበር። ድንቅ ፍጹም የቅልቅል፤ ዲል ያላለ ድንቅ ትዕይንት ነበር። አሁን ሪያሎች 2 ለ 1 መምራታቸውን ቀጠሉ። እኩል በእኩል የነበረውን መንፈስ ላቅ ወደ አለ ደረጃ ጨዋታውን አሻገረው ቤልሻ። የዳኛ ዩርግ ገጽ ወደ መክሰል አዘነበለ። የሊቨር ፑል ደጋፊም ቀዘቃዛ መንፈስ ተርከፈከከፈበት እዬጎመዘዘው። ከዛም ቢል ቀጣዩን የግጥግጦሽ ማጥቃት ሰነዘረ እና የራሞስ ልብ በድርብ ድል አደነደነው፤ እናም ዋንጫውን ይዞ 3 ለ 1 በሆነ ግብ ታሪኩንም ቀድሶ አሰልጣኝ ሲዳንን አስፈንድቆ ወደ እስፔን፤ ዳኛ ዩርግም የከሰለውን ተስፋ ይዘው ወደ ለንደን።

ያ አብሪ ኮከብ ተጫዋቹ መሃመድ ሳላህ የራሞስ ሴራ ሰለባ ባይሆን ኖሮ፤ በትክክልም ዛሬ አሸናፊውን ለማወቅ ቢያንስ ተጨማሪ የጨዋታ ደቂቃ ይኖር ነበር። የፔናሊት ድርብ የጨዋታ ህግም በተጨማሪ ደቂቃዎች ይከሰት ነበር። አፍሪካም የይድነቃቸው ህልም ብርሃኑን ይሰማ ነበር።

  • ·         ግን የሆነው …

ሴራ ተስፋን ተቀናቅኖ አሸንፎም ዕለቱን እጬጌው ፊፋ ዋናጫውን እና የወርቅ ሜዳሊያውን አክሎ አነባብሮ ደራርቦ ወደ እስፔኑ የዘውድ ዙፋን ልኳል።

የሊቨር ፑልን ጥቃት የመለሰውም ጠይም ዕንቁ ጎል አግቢም የሊቨር ፑሉ 19 ቁጥሩ የእኛው አፍሪካዊ ሴነጋላዊ ቀለማችን ሁለት ጊዜ ወደ አካባቢው ደርሳሃል በሴራው መንፈስ በአቤቶ ራሞስ ተብሎ በቢጫ ማስጠንቀቂያ ተስጥቶታል። የመጀመሪያው ንክኪ አልበረውም ፍርሃት ካልሆነ በስተቀር። በሌላ በኩል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የክንድ ጨዋታ ግድፈት የፈጸመው ሪያል ግን ምንም ሳይቀጣ የወርቅ ሜዳሊያውንም ዋንጫውንም፣ ሳቁንም፣ ፍሳሃውን በገፍ ሰናንቆ ጭፈራውን አስነካ። ልዩ ጉርሻ ለአቤቱ ራሞስ በስውር ሳይሸለምም አይቀርም።

እርግጥ ነው በዛሬው ጨዋታ ብዙ ቅጣት አልነበረበትም፤ ዳኛውም እጅግ የተራጋጉ ቢሆኑም ራሞስ ግን አልተቀጣም፤ በሌላ በኩል ቀደም ብየ እንዳነሳሁት በክንድ ጨዋታ ላይም ለዛውም መረብ አካባቢ ስለነበር ዘለውታል። እዩር ግን አንድ ቀን ይሰጠዋል ቅጣቱን ለራሞስ። ሴራ የግል ኢጎ ከመጠኑ ሲያልፍ የሚመጣ ረቂቅ የበሽታ አይነት ነው። ምንም መዳህኒት የሌለው፤ ከጸጥታም፤ ከደህንነትም፤ ከህግም ቁጥጥር በላይ የሆን ግን ከእዮር ቅጣት የማያመልጥ ድውይ ሰብዕና ነው። አቅም የሌላቸው፤ በራሳቸው አቅም ድፈረት የሚያንሳቸው የፈሪ ሰዎች መለያ ስንኩል ስብዕና ነው።
 
ጨዋታው እስከ ዛሬ ከተከታታልኳቸው አውሮፓዊ ሆነ ዓለም ዓቀፋዊ ጨዋታዎች ሁሉ መንፈሴ በቀዘዘ ሁኔታ የተከታተለው ነበር። ጨዋታው ሴራ ስለነበረበት ማራኪ ነው ማለት አልችልም። በብዙ ድራማዊ ትርኢቶች የተከውነ ቢሆንም ሴራ ባለበት ሁሉ መንፈሱ የጨላማው ነው። ስለዚህ የጨዋታ ህጉ በሴራ መርዝ የተለወሰ በመሆኑ ልብ አንጠልጣይም ነበር ማለት አልችልም።

ለምሳሌ የቤል ሁለቱም ጎሎቹ ታምረኞች ነበሩ፤ ግን የልቤን ምት አልጨመረውም። ጨዋ ጨዋታ አዬሁ ማለትም አልችልም። በሌላ በኩል ኳስና ክርስቲያኖ ርናልዶ ብዙም ልብ ለልብ ሳይገናኙ ነበር 90 ደቂቃው የተጠናቀቀው። አለቀናውም። ከእሱ ይልቅ የተሻለ ንቁ የነበረው የፈረንሳዩ ብሄራዊ ተጫዋች የሪያሉ ቤንዚማ ነበር። በዛሬው ጨዋታ ቤንዚማ ተከታታይ የጨዋታ ንቃት ብቻ ሳይሆን አዕምሮን ሰብሰብ አድርጎ ያገኙትን ዕድል በፍጥነት ለመጠቀም ያሳዬው ታታሪነት ኢትዮጵውያን እያሸሎክን ቆሻሻ ውስጥ የምንጥላቸውን ማናቸውም አይነት አዎንታዊ ዕድሎችን ሁሉ በምለስት በመቃኘት፤ ማግስትን ለመሥራት እጃችን የገባውን ዕድል አጠቃቀሙን ለማዋቅ ብንትጋ መልካም ስለመሆኑ ትምህርት ሰጪ ነበር ማለት እችላለሁኝ።

ያቺ ቅጽበታዊ የሊቨር ፑል ጎል ጠባቂ ለተቀናቃኙ ቡድን ለቤንዚማ በራሱ እጁ ያቀበላት ኳስ እና አእምሮውን ቀጥቶ ሰብሰብ ሰከን ብሎ ድሉን ያጣጠመው ወጣት ቤንዚማን ለአውሮፓው የ2018 የፊፋ የሻንፒዮን ሊግ ዋንጫ ሪያልን አበቃው። ታሪክን ያህል የሰፊ ተጋድሎ ክብር ደረበለት።፡አንዲት ቅንጣት ገጠመኝ ከተሳታች ብዙ ነገር ይዛ ትሰምጣለች፤ አንዲት ቅንጣት ገጠመኝ ከተደመጠች ደግሞ ብዙ ፍሬ ታመርታለች። ጨዋታው የሥነ - ልበና ነው። መዘናጋት፤ ትንፋሽን አለመሰብሰብ፤ የጥቃት አካባቢን ለይቶ አለመረዳት፤ መቸኮል ያመጣው ግድፈት የሊቨር ፑልን ተስፋ ገደል ጨመረ።
ድካሙም በተገባው ልክ ዕሴታዊ ሊሆን የሚገባውን ታሪክን አባከነ። ለዋንጫ ውድርድ 3 ለ 1 በመደበኛ የጨዋታ ጊዜ ሲጠናቀቅ የሰፋ ልዩነት ነው። ይህ ውጤት ለሊቨር ፑል እቅማዊ ሞራል ሰባሪ ነው። ተጨማሪ የጨዋታ ጊዜ ተጨምሮ፤ ያም ሳይሳካ፤ በፔናሊቲ ቢለያዩ እንኳን የተመጣጠነ ሞራል መገንባት በተቻለ ነበር። የኔዎቹ … ኳስ ፍቅር ነው። የፍቅርን ተፈጥሯዊ ባህሪ ያስተምራል። ጊዜን፣ ዕድልን፣ ድካምን፣ አለማባክንም ያስተምራል።

ይከውን፣ --- እኔ ሪያል እንዳሸነፈ ሳይሆን የራሞስ ሴራ እንዳሸነፈ ነው እማስበው፤ በውስጡም ኮከብ ግብ አግቢዎችን ልቀው እንዳይወጡም የተሸፈነ ሸፍጥ አለበት። የታገለው ከአፍሪካ ጋርም ጭምር ነው። እኔ በግሌ በዚህ ውድድር ጨዋ የኳስ ጨዋታ አዬሁም ማለት እልችልም። ኢጎ አይቻለሁኝ፤ ሴራ አይቻለሁኝ። ይሄው ነው … ተዛሬ ለዛሬ።








ዓለም ከሴራ የምትወጣበት ቀን ይናፍቀኛል!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።