ጭንቁ ሌቦቹ አቅም አገኙ ነው።

             
ጭንቁ ሌቦቹ አቅም አገኙ ነው። 
ለውጡን የመቀማትም
ዕድል ሊኖር መቻሉ
መጤን አለበት።
                                                                      ከሥርጉተ ሥላሴ 28.05.2018 (ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ )

„የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን አይተካከላትም፤ በጥሩ ወርቅ አትገመትም። እንግዲያሳ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው? ከሕይዋን ዓይን ሁሉ ተሰውራለች። ከሰማይ ወፎች ተሸሽጋለች። ጥፋትንና ሞት ወሬዋን፣---  በጆሮቻችን ሰማን ብለዋል።“ (መጽሐፈ እዮብ ምራፍ ፳፰ ከቁጥር ፲፱ እስከ ፳፪)
·        

                              መቅድም።
ታዲያ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የማንን ጎፈሬ እንዲያበጥር ይጥበቃል? የቡላ አጥሚቱን፤ የጎን አጥንት ሾርባውን አዘጋጅተን ስናገጠግጠው በጡጧ ሰነባብተን የለም። ለወያኔ ሃርነት ትግራይ እኮ አቅሙን ያደራጀንለት እኛው እራሳችን ነን። ለውጡ ሊቀለበስ እንደሚችልም ማሰብ ይገባል። ምክንያቱም ትግሉ ከለውጡ ጋር ነውና።
በተቃዋሚ ሥም ገንዘብ የከፈለ ሁሉ ምርጥ ዜጋ ነው።

 ስለሆነም በአገኘው ተቀባይነት እና ዕወቅና ሽንጡን ገትሮ ቀን ሲገነባ ሌሊት ሲያፈርስ ነው የከረመው። የትኛው ሚዲያ ነው ይህን ለውጥ ደግፎ የተነሳ? የትኛው? አንዲት ነገር እዬመዘዘ ሲታመስ አይደለም የተከረመው። እያንዳንዱ ሂደትን በስላቅ ሲዥጎረጎር አይደለም የተከረመው። ለውጡን የሚቃወሙ ሰዎች እዬተፈለጉ አይደለም ቃለ ምልልስ እንዲያደርጉ ሲደረግ የተከረመው። በምክንያቶች ላይ ሳይሆን በሳቢያዎች እና በዘሃቸው ላይ ብቻ ነበር ውርክቡ።

የትኛው ሰው ነው ለውጡን በጤነኛ መንፈስ የሚይ ቃለ ምልልስ የተደረገለት። አንድ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ብቻ ነው። ሲጀመር ትንሽ ሰሳ ያለች ክፈተት ነበረው። ያ ደግሞ የተገባ ነው። ማመዛዘን ማገናዘብ የተገባ ስለነበር። ከዚያ በኋዋላ ግን በፍጥነት እንደ ሰብዕናው ሙሉነት ደልዳላነት በስክነት እና በብልህነት „አናስደንግጣቸው“ ነበር ያለው። „ሌላው ቢቀር እስከ አሁን ያደረጉት ይበቃል“ ሲል ሁሉ አዳምጨዋለሁኝ።

አሁን እፍታ ላይ እሱ ስሌለ ታድሜ አላውቅም። አሁን ያለውን አቋሙን አላውቅም። ቀደም ባለው ሰሞናት ግን  በአቋሙ ውስጥ እንደ ነበር አንድ ቃለ ምልልስ ላይ አስተውያለሁኝ። አሁንም ተስፋዬ ሙሉ ነው ክብሩን የጠበቀ ጋዜጠኛ መሆንኑን ስለማምን በዛው „አናስደንግጣቸው“ አቋሙ ይቀጥላል ብዬ አስባለሁኝ። ከዕድሜው በላይ የተረጋጋ ሁለገብ ማስተዋል ያለው፤ ጋዜኛ ለሚለው ሚዛናዊ ሰብዕናም ናሙና ነው። ርግጥ ነው የራሱ ሚዲያ ስሌለው ሁልጊዜ ላዳምጠው እንደ ዶር አቦንግ ኢትዮጵያ ሜቶ ባለመቻሌ ተጎድቼያለሁኝ። በሁሉ ዕይታው መስማማት የግድ የለብንም። እኔም ሥርጉተ ነኝ እሱም ጋዜጠኛ ሲሳይ ነው። በመደገፍ እና በመቃወም ዝንባሌያችን ይለያያል፤ ተመክሯችን ሆነ ያለፍንበት የህይወት መስመርም እንዲሁ የተለያዬ ነው። የሆነ ሆኖ እንደ እሱ ያለ ምራቁን የዋጠ ጋዜጠኛ ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል። 
 
በተረፈ እንደ ሳጅን በረከት ኦርጅናሉ መጣ እስከሚባል ድረስ የታዬው መታመስ ታሪክ አንድ … ሁለት … ሦስት እያለ ቆጣጥሮታል። ለውጣዊ ሂደቱ እኮ ለወያኔም አንጡራ ጠላቱ፤ ለነፃነት ፈላጊውም አንጡራ ጠላት ነው የሆነው። አኩል ለእኩል። ሁሉም ሲያብጠለጥል አይደለምን የባጀው? የትኛው ሚዲያ የትኛው ጋዜጠኛ የትኛው የፖለቲካ ተንታኝ፤ የትኛው የፖለቲካ ድርጅት መሪ ለዚህ ለውጥ ቅናዊ ንጹህ ልቦና ቅርብ የነበረው፤ ካለ አንጋፋው መኢሶን በስተቀር። መኢሶን እንደ ድርጅት፤ ዶር ነገደ ጎበዜ እንደ ፖለቲካ መሪ እጅግ ቅን የሚባል ግልጽ አቋማቸውን ከግል ኢጎ በፍጹም ሁኔታ በራቀ መልኩ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። የተመክሯቸው አቅም ለዚህ የወቅት እቅም ጋር የሚመጥን ነበር።

እሳቸው ይሰበስቧቸው ከነበሩት ብሄራዊ ጉባያት ሁሉ በወጣትነት ዘመኔ ታድሜያለሁኝ። የረጋ መንፈስ እንዳላቸው አውቃለሁኝ። በዛ በማከብርላቸው ሰብዕና ውስጥ ስለመቀጠላቸውም ሰሞኑን አዳምጫለሁኝ እስኪገርመኝ ድረስ። ይህን ሰብዕናቸውን ጠንቅቄ ስለማውቅም አንድም ቀን በወቀሳ አንስቼው አላውቅም ድርጅቱን። የደነቀኝ የጠበኩትን ጥንካሬ በጽናት በቋሚነት ማግኘቴ ነው። ዛሬ እኮ አይደለም ሰው፤ ዕቃ ካኖሩበት አልገኝ ካለ ዘመን ተቆጠረ። የሃሳብ ልዩነት መኖሩ የተገባ ሆኖ ንጹኽ ተግባርን እንደ አመልማሎ የጥጥ መሰናዶ መደመጠጥ ግን የህሊና ሽፍትነት ነው።

ኢጎ አዎንታዊም አሉታዊም ቢሆንም አሉታዊ ብቻ እንዲገዛ መፍቀድ ጠረኑ የጨለማ ነው። ፕሮፖጋንዳ ለአዎንታዊ እርቅ፤ ለአሉታዊ ጠብ ወይንም አሉታዊ ግን ለሚያግዝ የሚጠበቅ ቢሆንም የሚታዩ ተጨባጭ ሰብሎችን አረም እንዲወጣቸው ለመፍቀድ መጣር ደግሞ ጎንድ ተ/ ሃይማኖት አንድ በለው ይህን የጸላዬ ሰናይ መንፈስ ያስብላል። አንድ ዕጩ ለምርጫ ሲወዳደር የምረጡኝ ፕሮፖጋንዳ ይኖረዋል ያ አዎንታዊ ነው። ተፎካካሪው ደግሞ እሱን ለማሸነፍ ተቃራኒውን ቢፈጽም ያም አዎንታዊ ነው። በሃሳብ ገብያ ሚዛኑ በህዝብ የሚዳኝ ነው የሚሆነው። አሁን የእኛ ተግባር ግን መልካም ነገር እያገኘህም፤ እያዳመጥክ አይደለም፤ ጭላንጭል ብርሃን ውስጥ አይደለህም፤ ጨለማ ውስጥ ነህ ቢባል የሚሆን አይደለም። ጥቅሙን የሚጻረር ተጠቃሚ ስለሌለ። 84% ግብረ ምላሹ ኢ - መልካምነት ዘመቻው እርቃኑን እንደ ቀረ አመላካች ነው። ስለዚህ ጨርሶ እርቃናችን ሳንቀር ስልት ቀይሮ ሊደመጥ የሚችል፤ ሸፍጥ የሌለበት የህሊና እጠባ ላውንደሪ ያስፈልገናል። እኔ ይገርመኛል በግል እማገኛቸው ሰዎች ሁሉ እርካታቸውን የሚገልጹበት ስንኝ ሁሉ። መጻፍ ጀምርኵኝ ያለችኝ እህት ሁሉ አለች። ለዛውም ከዘማሪነት ወጥታ ፖለቲካ ጉዳዮዋ ሆኖ። ይህ የመንፈስ ልዕልና ያመጣው የመንፈስ መረጋጋት እና ተስፋን ማግኘት ነው።
  • ·         ጥገናዊ ለወጥ እና ተስፋው።

ለውጡ እኮ ጥገናዊ ነው። ያውም በራስ ውስጥ ባለ የፖለቲካ የሥልጣን ሽግሽግ። በዚህ እንኳን እኩል ግንዛቤ ሊኖር አልቻለም። በጥገናዊ ለውጥ መርህ ሰጥቶ መቀበል፤ ተቀብሎ መስጠት፤ ማትረፍ እና መክሰር፤ ዕድል ከቀናህ ሦስት ትወስዳለህ ሁለት ትሰጣለህ። የምትፈልገውን ለማግኘት የማትፈልገውን ማስጠጋት እና የእኔ ማለት ግድ ነው። ኢህአዴግ ድርጅቱ የአራት ፓርቲ ስብስብ ነው። ድርድሩ ኮታዊ መሆኑ አይቀሬ ነው። ወሳኙ እኮ ድምጽ ነው። 4% እኩል ድምጽ ነው ያለው። ይህ ዝበት በራሱ መርህን ተጠዬቅ የሚያሰኝ ነው ለወደፊት። በዛ ላይ በሁሉም የበላይ የሆነ ልዕልናዊ አቅም አለ ከ4%። ይህን ወደ ተመጠነው ሁኔታ ለማምጣት አንተም አታስፈልግም ተብሎ አይሆንም። ለዚህ ፈቃጅም ነሺም አቅም ነው። የመንፈሱን አቅም ቤሳ ቤሲቲ ሳያወጣ በነፃ ለመሸለም ያልቻለ የነፃነት ፈላጊ ሌላ የኤዶም ጸጋን ይመኛል።

መጀመሪያ የማይከፈልበትን የመንፈስ ድጋፍ ለመስጠት ፈቃድ ይኑር፤ ከእያንዳንዱ በግል ከሁሉም በጋራ። መደገፍ ቢቀር ባንበጠብጥ፤ በራሳችን ተግባር ብንጠመድ ምን አለበት? ምን ሥንሰራ ነው ውለን እምናድረው። ጉድፍ ስንለቅም፤ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ዱላ ስናቀብል ነው። ከዬትኛውም ማህብረሰብ መልካም የሆኑ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ መልካም ያልሆኑም ይኖራሉ። ይህም መመጣጠን አለበት። ተጠያቂነቱ በሁሉም መስክ ሊታይ ይገባል። ሰው መሆን ህሊናዊነት ነው። የመኖር ስጋት የሁሉም ዜጋ ሆኗል። ጋንቤላ ላይ ያለው ኦሮሞ „ልጄን ለማን ጥዬ ነው እማልፈው“ እያለ ነው። „የትስ ነው እምቀበረው“ እያለ ነው። „ደም ስትጠጣ የኖረች መሬት፤ በደም ዝናብ የበቀለ ሰብል ስንበላ የኖርን“ እያተባለ ነው። ይህ መራራ ነገር ነው። ይህን አመጣጥኖ ለመምራት እና የውስጥ ሰላሙን ለመመለስ የግድ ለሌቦች የትንፋሽ ጊዜ መስጠት ግድ ይላል። በስተቀር ቁርሾ በእጥፍ ቀጣይ ነው የሚሆነው። ቁርሾ ከቀጠል በሁሉም ቦታ አንዱ ሌላውን መጨራረሱ አይቀሬ ነው። አደጋ ላይ ነን። ግን … ግን እግዚአብሄር መቼ ይሆን የሚታወቀው? ስላደረገው መልካም ነገርስ መቼ ይሆን ተመስገን የምንለው?

ይህም ሆኖ ኤርትራ ያህል በጎ የማታስብ ጎረቤት አገር አለችብን ይሄ አንድ ይባል፤ ሁለተኛ፣ --- የነፃነት ፈላጊው አዲስ ፋስ ገዝቶ የተያዘ የተረዘዘውን ሁሉ ባልራራ አንጀቱ እዬፈለጠው ነው ኔት ላይ፤ ሦስት፣ --- ማህበረ ደራጎን ሴራውን አደራጅቶ መሬት ላይ ትንፋሽን ሰቅዞ ይዟል፤ አራት፣ --- በራሱ በለውጡ ውስጥ ያሉ ማህል ሰፋሪዎች በዚህ ውጥረት ውስጥ ተሁኖ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ የለውጥ መንፈሱ ከሚጠበቀው የጥገናዊ ለውጥ በላይ የላቀ ኢትዮጵያን እናት አገሬ ያለ ድንቅ አዬር ነበረው። ማን አገዘው? ማን ደገፈው? ማን የእኔ አለው? ጥቂት አንድ ሁለት ሦስት የሚባሉ ሙሁራን ንጹህ ልብ ያላቸው፤ ሥልጣን፤ ማህበረ ፍቅረ ማንፌስቶ ምንትሶ ቅብጥርሶ የማይፈልጉ ኢትዮጵያ ደግማ የማታገኛቸው ሊሂቃን ፕ/ አለማዬሁ ገ/ ማርያም፤ ዶር ፈቃዱ በቀለ፤ ዶር ኦባንግ ኢትዮጵያ ሜቶ፤ ዶር ፈቃዱ እሸቴ፤ አቶ የሱፍ ያሲን በቃ ሌላ ማን? ከድህረ ገጽ ዘሃበሻ እና ሳተናው በትጋት አዳዲስ ሃሳቦችን ሁሉንም በእኩልነት የደጋፊውንም የተቃዋሚውንም ድምጽ ሲያስተናግዱ ታዝቢያለሁኝ።

በተደራጀ በተቀነባበረ ሁኔታ ማዕቱን ስናፈስ ነው የከረምነው። ህዝብን ለመምራት ከህዝብ መሃል ተገኝቶ የህዝብ ስሜት ማጥናት በራሱ ወንጀል ነው፤ ሽርሽር የጫጉላ ጊዜ፤ ድግስ ነው ነው የሚባለው። በቃ። የቀድሞ ሰዎችም ግብር ማብላት ልማዳቸው ነው። ስለሆነም ወደ ትፊውታችን ምልሰት እየተደረገ ነው። ቤተ መንግሥት የጥቂታን ሳይሆን የሁሉም ነው መሰረተ ሃሳቡ።
ዕድሜ ልክ እኛ ውጪ አገር ስብሰባ ስንጠራ ሽርሽር የጫጉላ ጊዜ አልነበረም? ማታ ላይም መንፈሳችን ስናዝናናው ያ የሱባዔ ጊዜ ነበር። በ27 ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ ላይ ከጥግ እስከ ጥግ ኢትዮጵያውያን ለማድመጥ የተሄደበት መንገድ ቢያንስ የወገኖቻችን ጠረን ለማድመጥ፤ ለእኛ ለአገር ፍቅር እራህብተኞች ምን ማለት እንደሆን ራሱ ሳንጠዬቅ ያ ተዘሎ የሚዲያ አቅም ያላቸው እንዳሻቸው ሲተረትሩት ነው የከረሙት። ተፎካካሪዎች የፖለቲካ ድርጅት መሪነታቸው አቻዊ ሆኖ አቅሙን አጠናክሮ በውስጥ ድርጅቱን ማብቀል ሲጋባ፤ የጠ/ ሚር ጉዞ ክንውን ዘጋቢ እና ገምጋሚ ሆነው ነው ያረፉት።

ማዘዝም መታዘዘም ባደራጀኽው፤ በደከመክብት፤ ባበቀልከው፤ በመረጥከው ማሳ እንጂ  ዘው ብሎ ገብቶ ሰብሌ ካልሆንክ፤ እኔ ካልመራሁህ፤ ይህን አድርግ // አታዳርግ እዛው ሥራ ሰርትህ ጠብቅን ምን ያለተዘረዘረ ጉድ አለ … ዛሬ ሁሉ ደክሞታል። አቅም አለኝ አለደከመኝም የሚል ካለ ደግሞ በራሱ አቅም ወጥቶ አዲስ ሃሳብ እብቅሎ ሰብልን መሰብሰብ ጌታ የለበትም። አሁን አቦ በቀለ ገርባ ጎንደሬዎች ቢፈቅዱልኝ የትግላቸው አጋራ ብሆን የሚል ውሃ ያልነካው ንጹህ ሃሳብ አብቅለዋል። ኧረ መከራን እቀበላለሁ ላለ ወገናችን ደግሞ የክብር አባልነቱን ማን ወስዶት ጸሎቱንስ ማን ነፍጎት ነው መልሱ።

ብቻ እንኳንም ከጎንደር የአማራ ተጋድሎ በፊት አልሆነ። ምክንያቱም የዚያን አብዮት የማሰብ ልቅና፤ ሚስጥራዊ የበቃ የአብሮነት ሥልጣኔ፤ የተዋጣለት የፍቅራዊነት ንጡር ሃብቱን አቅም ልክ ስለሚልጠው። አቦ በቀለ ገርባ በግላቸው ያላቸውን የመሆን ፈቃድ አሰምተዋል። ግልጽ አቋማቸውንም ገልጸዋል። ድሮም ያከበራቸው ህዝብ ነው ጠረናቸው ሳያውቀው፤ ዛሬም ያነን አሳድገው በውስጥ ሊደመጥ የሚገባ ዕውነት ሆነዋል። አቅምን ማምጣት በብልጠት ሳይሆን በቅንነት ነው መሆን የሚገባው። ያለው አይቸገረም አጋጣሚውን ሲያገኝ ያፈልቀዋል። ዕንቁ ነውና።

  • ·         ራሞት።  

አሁን በቅርቡ „ለማ እና ገዱን ልንደግፋቸው ይገባል፤ ለውጡን እኛ ካለመጣን አንልም“ የሚል መርህ ተኮር ነገር እዚህ ሳተናው ላይ አንብቤያለሁኝ ከግንቦት 7። የት ነበር ግንቦት 7 በሚዲያው፤ በጸሐፍቱ፤ በጋዜጠኞቹ፤ በተንታኙ የነበረው ያን ያህል ጉግስ፤ የአቶ ኤርምያስ ለገሰ ኢሳት ላይ „ለማም ገዱም ገዳይ ናቸውስ“  ያ አፍርሽ መንፈስ እንደዛ ኔት ላይ ሲፈረሽ? ኦህዴድ እንደ ድርጅት አቦ ለማ መግርሳ ወደ ፊት ሲመጡ ምንድን ነው የነበረው፤ ድምጹን አጥፍቶ የእጅ ውዝዋዜው ቢታይ እኮ ወይ መዳህኒተ ዓለም አባቴ ስንት የሰው ዓይነት ነው ያለን ያሰኛል? ለአንድ ለማከብረው የኢሜል ወዳጄ „ጋዜጠኛን ሀን“ ድምጹን አጥፍተህ የእጅ እንቅስቃሴውን ብቻ እዬው ብዬ ልኬለት ነበር። 

ከዚያ ቀጥሎ ዶር አብይ አህመድ ተዞረ። ወደ ፊት ሲመጡማ ምንድን ነው የነበረው? አብይ ኬኛ! ከክፍል አንድ እስከ ስድስት „ህሊና“ በጣም ብዙ ጹሑፎች የጻፍኩት እኮ በዚህ ምክንያት ነው። ሃግ የሚል፤ ተዉ የሚል መሪም ድርጅትም በመጥፋቱ። አይደለም ከተጀመረ ለወራት የዘለቀ ውጊያ ቀርቶ የአንዲት ሰከንድ የቃል ወለምታ ስንት ነገር እንደሚበክል አይታወቅም። ህዝብ መንፈሱ ተስፋ ሲያደርግ፤ ነፍሰ ጡር እናቶች በሰላም አምጠው ይገላገላሉ። እኔ ወያኔ ሃርነት ጎንደር ሊጋባ ዋዜማው ላይ ምጥ ላይ የነበረች እናቴ ብላት ይሻለኛል የአንደኛ ደራጃ መምህሬ የነበረች በስጋት እያማጠች አልፋለች። ልጁ ተረፈ። እናቴ ስተንገርኝ በህወቴ እንዲህ አይነት መረባባሽ አይቼ አላውቅም ነበር ያለችኝ። ጭንቀት እኮ ራስን መምራት ያቅታል። 

ሰው ሲደነግጥ የሚይዘውን የሚጨብጠውን ነው የሚያጣው፤ እና በዬቀኑ ያን ያህል ሚዲያ ላይ ጭንቅ መላክ መርዝ የመላክ ያህል ነበር። በዚህ ማህል ልጆችም አክሰሱ ያላቸው ያዳምጡታል። ፍርሻ እኮ ህግ የለውም። የምንጥብቀው ቀርቶ የማንጠብቀው ሰቀቀን ነው የሚመጣው። ልመናው ያ ነው የነበረው …

የትጥቅ ትግል አንዱ አማራጬ ነው ያለ ድርጅት በሚመራው ሚዲያ „ለማ እና ገዱ ገዳይ ነው“ ብለህ ህዝብ እንዳይደግፋቸው ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ሥራ ሰርተህ አሁን ይሄ ማለት ምን ማለት ነው? አይገባኝም እንዲገባኝም አልፈቅድም። መሽቷል። ውጪ አገር በሚዲያው በሽታሽቶሽ የተበተነው አቅም፤ አቅሙን በስውር ሲበሉ ሲገዘግዙ የኖሩ ሰንት ሰዎች ናቸው ያሉት?

የት አላችሁ ብሎ ደጋፊዎቹን ፊት ለፊት ስንሟገትለት የኖርነውን ጠይቆን፤ ሰብስቦን፤ አነጋግሮን፤ አይዛችሁ ብሎን ያውቃልን ግንቦት 7? ለመሆኑ ሥማችን ያውቀዋልን? በእሱ ምክንያት የወጣልነን አዲሱን ማንነት „ጉዲት“ የተባለ ሥም የተሰጠን ኢትዮጵያዊ ዜጎቹን። ለመሆኑ ሰው ስለሚለውስ ክብር አለውን? ዛሬ አንድ የሀገር መሪ እታች ድረስ ወርደው ህዝብን ሲያዳምጡ ነውር ሆነባቸው። እኛ ስላለደርገነው ብቻ። አቅም እኮ ሜዳ ላይ አይታፈስም ህዝብን የአንተ ነኝ ብለህ ተረገጡን መስጠት ብቻ ሳይሆን ዱላውን ለመቻል መሳናዳት ይጠይቃል። ምነው አቅሙ ጊዜው በኖራቸው እና ሙሁራንን አዲስ አበባ ላይ ራሳቸው ሰብሳቢ ሆነው ሰብብስበው ባነጋገሩ። ያን ያህል ካድሬዎች በሚሰበስቡት ስብሳባ ላይ ሃሳባቸውን የሚገልጹት ሊሂቃን በፍጥጫና በእርግጫ እንዲያቆርጡ ባልተደረገ ነበር። በአዲሶቹ የወያኔ ሃርነት ምላጮች ትንተና ተብዬውም በመርዝ ተስፋው ባልተደለዘ ነበር። እኔ አዲስ አበባ ላይ የተካሄዱ አገራዊ ስብሰባዎች ዓላማቸው ተስፋን ቀሚዎች ሆነው ነው ያገኘኋዋቸው። 

ስለሆነም በዬክልሉ በጠ/ ሚሩ ሰብሳቢነት የተካሄዱ ስብሰባዎች ዕንቁ ናቸው። ካድሬያዊ መንፈስ የሌለባቸው። ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ፍላጎት በእጅጉ የራቁ በብዙ ኪሎሜትር። የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እና የአዲስ አባባ ከተማው ግን አሳንጋላ ነበር። ያው የተመለደው ማለገጥ ዴሞክራሲያው ማዕከላዊነት የዘፈነበት ቤተ ዋይታ።
  • ·         ውቅና።

ሌላው „ኢትጵያዊነት ሱስ ነው“ ስላለለት ነው ሰማያዊ ስለ አርበኛ አንደርጋቸው ጽጌ አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ አካሄደ የሚልም አንብቤያለሁኝ። እንኳንስ በሥሙ ስብሰባ በዚህ ዘመን „ጽጌ“ የሚባል አባት አንዳርጋቸው የሚል ልጅ ማውጣት በማይፈቀድለት ወቅት። ስለ አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ ፊት ለፊት ወጥቶ መቀቀል ቅዱስ ቁርባን መስሎታል ግንቦት 7? ራዲዮ ፕሮግራሜ የቆመው „ላንቺ ነው ኢትዮጵያ“ መግቢያ ላይ ስለምጠቀም ነው። ስንት ኑሯችን እንዳፈነቀለው አያውቀውም ግንቦት 7? በእትብቴ መንደር የሰው እርድ አዬር ላይ ከፍቶ፤ ከዚህ ደግሞ የተሻለ የተስፋ ብርሃን ይሆናል የተባለው መሪው ሲታሰር ቢያንስ በሳምንት ሁለት ቀን ማንሳት የተገባ ስለነበር ስንት የሽብር የመንፈስ ግርፋት እንደ ደረስ የት አውቆን? ቀድሞ ነገር በመንፈስ አቅም ስለሚባለው ጥበብ ግንቦት 7 አልነበረበትም።

የግድ ነፃነት መፈለግ በማንፌሰቶ ከፈን መጠቅልል ማለት ነው። አሁን ነው አርበኛ አንዳርጋቸው እስር መፈታት ቀን ጊዜ ይቆጠራል፤ ሞት የተፈረደበት አቡነ ጵጥሮስ እኮ ነው። ለዛውም አሁን ዘነዘናውን ስለማግኘታችን እርግጥ የሚያደርግ ነገር የለም። ሴራ ስለሚጋለጥ። በዓመት አንዲት ቀን ሥሙ የማይነሳው ምንዱብ። አጀንዳ ሲጠፋ አጀንዳ ዛሬ ሆነ። አሁን ደግሞ እሱን ከነነፍሱ ለማግኘት ሰጥቶ በመቀበል የጥገናዊ ለውጥ መርህ እሳት የላሱ ሌቦች ከነበረው መረባቸው ጋር የተቋረጣው እንዲቀጥል ያስፈልግ ነበር፤ ሆኗል። አንዱን መምረጥ ነው። 

ወይ አንዲን ወይ ሌቦቹ ሳይፈቱ እንዲቀሩ። ሁለት እግር አለኝ ተብሎ በአንድ ጊዜ ሁለት ዛፍ አይወጣም። ይህ ዕድል የሚገኘው ቃብቲ ላይ ከፍትን የተባለው የወታደራዊ ማስልጠኛ ጣቢያ¡ በእጥፍ ድርብ ወታዳሩን አምርቶ፤ በዝናር ሙሉ ወኔ እና መትረዬሱ በአፋር አድርጎ አዋሽን ቆርጦ አራት ኪሎ በመንፈስ ሰረገላ ቁብ ሲል ብቻ ነው። ሌባም ፍርዱን የሚያገኘው የአራት ኪሎ ህልሙም የሚወራረደው። ለዚህም ያበቃው የቄሮ እና የአማራ ተጋድሎ አብዮት ነው እንጂ ያን ደንዳ የማህበረ ሳኦልን በር የሚደፍራት አንድስም እንኳን አቅም አለነበረም። ይህ ሁሉ በዬዕለቱ የሚደመጠው የምሥራች ለወያኔ ሃርነት መርዶ እና ራድ የላከው የዛ 50 ሺህ ልጁን ለእስር ቤት የገበረው ሺዎቹን ነፍሱን የሰጠው የሁለቱ ተጋድሎ ፍሬ ነው። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የነበረው መታወክም እነዚህ ሁለት ታጋድሎዎች ያስገኗቸው ፍሬዎችን ለመቀልበስ ነው። በቅንጅት እንደ ተለመደው … ድካሙ ተበትኖ እንዲቀር ነበር የተሰላው …
  • ·         ባጃው።

የተከረመው ክራሞት እኮ ወያኔ ሃርነት ትግራይ እርግፍ ተብሎ ተረስቶ በአብይ በለማ በገዱ በአንባቸው መንፈስ ላይ ነበር አሉታዊ ዘመቻው። አቃቂሩ ሲደረት የተከረመው። እነሱ ከዛ ከወያኔ ሃርነት ጋር ጉሩቦ ለጉሩቦ ተናንቀው እስረኛ ሲያስለቅቁ፤ የሥልጣን ሹም ሽር ሲያስደርጉ እንኳን የተፈቱት እንኳን ሽራፊ ዕውቅና ለመስጠት ፈቃዶኞች አይደሉም። የትሜና የተወረውሩት የነፃነት አርበኞች በክብር ከሚወዷቸው ህዝብ ጋር እንዲገናኙ ሲደረግ ምንም ነበር። የወያኔ ሃርነት ትግራይ መንፈስ ከእሳት የገባ ፕላስቲክ ሆኖ የሚይዘውን የሚጨብጠውን ሲያጣ እኛ ያ የሥነ - ልቡና ልቅና የፈጥረን አዲሱ ለውጥ ጋር ከጎኑ ልንቆም አልቻልነም። እስኪ ይነገረኝ ከዛ የሲኦል የበቀል ጉደጓድ የወጣ አንድ የነፃነት አርበኛ አብይን አይዞህ ከጎንህ ነን ያለነው በአደባባይ ያለ ካለ ይምጣ? ማን አለ? ከማሳጣት በስተቀር። 

ያልተገኘውን ነገር አጎልብቶ አጎልምሶ ከመግለጽ በስተቀር። ፈጠሪ ለሰጠው መልካም ነገር ምስጋና ካጣ ሊቀማም መብቱ ነው እራሱ አዶናይ። ክብር እኮ የፈጣሪ እንጂ የሰው ሥራ አይደለም። ስኬትም እንዲሁ። ይህን ዕድልስ ምነው  የአርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ ወላጅ አባት፤ ልጆች፤ ባለቤቱ እና ቤተሰቡ ባገኘው በነበረ።

 እኔ ስጋት አለብኝ … የወያኔ ብቻ አቅም አይደለም ይህን አንበሳ አሳልፎ ያሰጠው፤ አሁንም ከአንበሳ መንገጋ ስጋ የመንጠቅ ያህል ነው? ይቻላልን? አዳኖይ ይመልሰው። ቀንቶት ያ ሙሉሰው ለዓይነ ሥጋ ቢበቃ የሆነውን ሁሉ ዝቀሹ ተመክሮው በመቻል ይችለዋል። ስለዚህም ምህረቱ በሁሉም አቅጣጫ ይሁን እንላለን እኔ እና ብዕሬ። ሶሻሊዝም እና እኛ እንዲህ እና እንዲያ ነው … አንዱን አስውጦ ራስን ማውጣት። ለዚህ ነው እኔ አቦ ለማ መግርሳን የምዕት ቅኔ ያላኳቸው። እናትም ዘመንም እሳቸውን የመሰለ የምህረት ሰማይ አልፈጠረችም። 
  • ·         ም! 

ዶቼቨሌ እና ቪኦኤ በሁለት ጎራ ላይ ነው ቸክለው ነበር የከራረሙት። የሰከኑ የመኖራቸውን ያህል የሚያጣጥሉ፤ ምክንያት እዬፈለጉ የሚሰላቁም ተደምጠዋል። የለማ የአብይ የገዱ መንፈስ እኮ የፊናንስ፤ የጦር ሃይል አቅም እምጡ አላለም። እውነት  ለኢትዮጵያ የሚታሰብ ከሆነ፤ በቻፕተር ተደራጅታችሁ ገንዘብ አጠራቅማችሁ እርዱኝ አላለም። በመንፈስ መደገፍ ብቻ ነው የጠዬቀው። መልካም ነገርን አለመግለጽ መብቴ ነው መጠዬቅም መብቴ ነው ምን ማለት ነው ይሄ? አገር እኮ፤ ህዝብ እኮ የአሽዋ ቤት አይደለም። በያንዳንዱ ቃል ውስጥ መደርመስም ማቋጥቆጥቆጥም አለ። 

ቁልጭ ያለው ነገር የህዝብ ሳቅን አልናፈቅነውም። ማን በደልክ? ማን ተበደልክ? እያልን ቁርሾ እዬለቃቀምን እርስ በርስ መተላለቅ፤ የበላይ ሆኖ የኖረው መንፈስ መሬት ተነጥፎ ደግሞ ያው የተለመደው ዱላውን በዙር እንዲቀምስ ነው ፍላጎታችን። መቧከሱ እንዲቀጥል። የእልቂት ታንቡር እና መለከት መናፈቅ። በዚህ ውስጥ የበዳይም የተባዳይም እናት አለች አላዛሯ ኢትዮጵያ። ስንት ጊዜ ይቃጠል የማህጸን አንጀት። ሺዎች ሲፈቱ ደግሞ 4 ሚሊዮኑ ደግሞ መከዘን አለበት፤ ለዛውም በዘር ተነጥሎ። ዓይን ያወጣ ዓይኑ ይውጣ እንደሚለው የሃሞራቢ ህግ። አቦ ሌንጮ ለታን ተቀብልህ የወያኔ ሃርነት ፊታውራሪዎችን አስራለሁ ብትል አይሆንም። የጥገናዊ ለውጥ ባህሪም አይፈቅድም።

አንዷን ፈርኦኒት እና ሌባ በሚ/ር ደረጃ ላይ አስቀምጠህ ለዛውም ጉሮሮ ላይ ሰንቅረህ ገና ሙግት አለባቸው ከእኔ ጋር ጠ/ ሚር አብይ አህመድ በዚህ ጉዳይ አንላቀቅም፤ አንዷን ሌባ እና ፈርኦኒት ማግለል አይቻልም። ሁሉንም ለማግለል ደግሞ አንተ ራስህ ሞግተህ ያመጣኸው ለውጥ አይደለም። መሪዎች አልነበራቸው ህዝባዊ አብዮቶች። ዋጋ አሳጥተን ለወያኔ የበቀል ገጀሞ አሰናድተን በኮፒ ራይ ስናምሳቸው ነበር የኖረንው የራሳችን ወገኖች ግን ጥግ አስይዘን፤ ለወያኔ ሃርነትም በሥማችን የበቀል ቁርሾ ኩትኩት ያሰናዳንላቸው ናቸው የአማራ የህልውና ተጋድሎና የኦሮሞ ንቅናቄ አብዮት ያመጡት ለውጥ ነው። ለውጡን ማድመጥ መምራት የቻሉ ደግሞ ተፈጠሩ። እኛ ኔት ላይ ስንፋለም ሾለክን። እንዲያውም ዕድሉን በአግባቡ ስለተያዘ እንጂ ወያኔ ሃርነት ትግራይም መዳፉ ላይ ለማስቀመጥ ዕድሉ ሁሉ ነበረው። ምን አለን እኛ የምንመክትበት ሰራዊት? ምን? የህሊና አቅም እንዲህ 84% ሆ! ብሎ የሚያሰደግፍ፤ የአዲስ ሃሳብ ፍልቅት? እኮ ምን?

በዚህ ላይ አቤቶ ኤርትራም አለች። ኤርትራ አጀንዳ አይደለችም። በታሪኳ ገብታ የማታምስበት ድርጅት ቢኖር ኦህዴድ ብቻ ነው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ነገ አይታወቅም። ይህ የሰማይ ስጦታ ነው ልብ ላለው በዚህ አዬር ከቀጠለ። ጤና ስለማትሰጥው አገር አይታሰብም። ሌላ ሥራ የላትም ኤርትራ። ይህ ዕድል ልብ ላለው የሱባኤ ውጤትም ነበር። የኢትዮጵያ ቀና ማለት መቼውንም ስለማትሻ - እትጌ ኤርትራ። ኢትዮጵያ በሙሉ ሪሶርሷ አቅም ካገኘች ኤርትራን ማን ሲያስታውሳት። የተንጣለለ ወደብ ብቻውን አራጣ ይዛ አይታዋለች። ፈጣሪ ካልተጨመረበት የፈለገ ዓይነት ትምክህት አሽዋ ነው።

  • ·         ውጥ ተፈልጎ ለውጥ ተሸሽቶ።

በፍጹም ሁኔታ እንደ ሰው ቁጭ አድርገን ልገምግምህ ብንል የምንችለው አንድ አይደለም ሁለት አይደለም 43 ዓመት ሙሉ ራሱን በሁሉም መልክ ካደራጀ 666 ቡድን ጋር ተጋድሎ እዬተደረገ እኛ የገበርዲን ሽርሽር ላይ ነበር የከራረምነው። ወይ እኛ አቅም የለን፤ የሚችሉትን ሊያደርጉ የፈቀዱ ሲፈጠሩ ደግሞ ቀስቱን አነጣጠርን እንደ ለመደብን ውጊያ ላይ። ተጨማሪ ደም፤ ተጨማሪ ብጥብጥ ናፈቀን። ቀድሞ ነገር ዶር አብይ አህመድን ኢትዮጵያዊ አድርገን የራሳችን ወገን አድርገን ተቀብለናቸዋልን? ለመሆኑ ወገናችን ናቸው ብለናልን? ከውጭ አገር የሄዱ የሌላ አገር ዜጋ እኮ ነው ያደረግናቸው ልክ እንደ ደንቢ ዶሎ። ስለምን? ስለሚበልጡ ሙሉ እዮራዊ አቅም ስላላቸው። በቃ ይሄው ነው። ህዝብ አታነጋግር እንደ ድንጊያ ቢሮህን ዘግተህ ተቀመጥ እኮ ነው ጉዳዩ። ችሎታህን ሰው አይወቅ የጋን ውስጥ መብራት ሁን ነበር ዘመቻው። በቅናት ሲያሳብድን የከረመው ይሄው ነው። አሁን ፖለቲካኛ ያልነበረው ሰው ነው መደበኛ ንግግራቸውን ቃል በቃል እያደማጠው ያለው። ምክንያቱም ህሊናን በሁለገብ ዕወቀት የሚያበለጽግ ነፃ የአየር ላይ ት/ ቤት ስለሆነ። ስብከተ ወንጌልም ነው። 

  • ·         ወይ መዳህኒተ ዓለም አባቴ!

ኢትዮጵውያን ወገኖቼን በቀዬው እያገኘሁዋቸው ነው። አሁን ደግሞ ውጪ ያለችሁትን ላይ እፍልጋለሁኝ እከሌ ተከሌ ሳይባል፤ ከፈቀዳችሁልኝ ከእናንተ በላይ የሚበልጥ ጉዳይ የለም እና ልያቻሁ ነው የአሁን ጥያቄ። ለዛውም „ አታብዙት ይህን የነፍጠኝ ሰንደቅዓላማ“ የሚበላውን የጣሰ በዛ በልሙጡ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ብሄራዊ ሸማችን በሚያሸበረቀው ትዕይንት የዬዓመቱ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ለማዬት የናፈቀ መንፈስ ነው። ፍቅርን መሻት መልካምነት ነው። 

ይህን ዕድል ልጠብቅ ብል አንድ ዓመት ይቃጠላል። አጋጣሚው ተገጣጥሟል መጋቢት እና ነሃሴ ነው ነገርዬው። በማህልም ሳንገናኝ የሚሆነው አይታወቅም ነው ጉዳዩ። ከሳውዲ ሲመለሱ በቀጥታ የሄዱት ዶር ምህረት ደበበ ከሰበሰቡት መንፈሳዊ የህሊና የንጥህና ማስጠበቂያ አዳራሽ ነበር። „ሳላገኛችሁ ትሄዳላችሁ ብዬ፤ ታመልጡኝ አላችሁ ብዬ ነበር። ቆዬችሁኝ እግዚአብሄር ያክበርልኝ!“ ነበር ያሉት ድካማቸውን ገፍተው ፈገግታ ለግሰው። ያ ቅን ማህበረሰብ ደግሞ ልቡን፤ ህሊናውን ሸልሟቸዋል። „ከአነጋገር ይፈረዳል ከአያያዝ ይቀደዳል የሚሉት አቮውም ለዚህ ነው። በዛ ዓራትዓይናማ የንግግር ጥበባቸው ተስፋን የሰነቀ የልብ መንገድ ነበር የከፈቱት። ዕድሉን ለመጠቀም ማሰብ ብልህነት ነው። ሰው የህይወቱ ቀጣይነት በመዳፉ የለም። ግራ ቀኝ ሴራ በጣምራ አስፍስፎ ጦሩን መዞም እዬጠበቀ ነው። በፆም በጸሎት እባክህን ይህን ሰው እንደሚሆን አድርግልን ... የሚል አቅሙ ሽውህራር የበላውም አይጠፋም። መመጠን ካልተቻለ ይሄው ነው ጥቃት ማቀድ። በዛ ላይ ውጪ አገር እኮ ተለያይተናል። ማን ማንን ያምናል ዛሬ? ማን ሞኝ አለ ቤቱንም ልቡንም ከፍቶ የሚያስረክብ።

በስልክ እኮ ልብ ለልብ ከቀረ ስንት ጊዜው ነው። መቅጃ አዛጋጅተው ነው የሚደውሉት። ፈጣሪ በዬግላችን የሰጠን ነፃነት በዬፌርማታው ቀማኛው ብዙ ነው። ሰው በኢሜል ሲገናኝ አይተማመንም። ያ የመንፈስ የህሊና የቃል ዕዳ ነው። ሰው ሌላውን ሲያምነው ነው የውስጡን የሚነግረው ይሄ ይተብሃል ቀርቷል ዛሬ። አጋጣሚ ተጠብቆ ማጥቂያ እና ማስጠቂያ ነው። በተለይ ያ ሰው ጥሩ አጋጣሚ ከኖረው ያችን መዘዝ ተደርጋ ይከሰስበታል፤ ይወገዘብታል፤ ይገለልበታል። የተሰጠው ከበሬታንም ሙጃ እንዲውጠው ይደረጋል። በስውሩ መረብ ያለውንማ አማኑኤል ብቻ ነው የሚያውቀው ስንት ዜጋ ማህበራዊ ህይወቱ እንደ ከሰለ። ፍርዱን ይጠብቅ እያንዳንዱ እስተ ልጅ ልጁ ድረስ።

ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን ኢትዮጵያ ከብራ በምትንግሥበት ጃኗዋ ዕስር ባላታወጀበት፤ ድምፆዋ ከፍ ብሎ በዜማ በሚደመጥበት አገር የጠማኝን ፍቅር መጥቼ ላጣጥመው ከወገኖቼ ጋር ነው። ለእኔ እናንተ „አሸባሬ“ ምንትሶ ቅብጥሮስ አይደላችሁም ናፍቆቶቼ ናችሁ ነው አብዩ ጉዳይ። ሲያሰኛቸሁም ውቁኝ ዱላውን የምችልበት ትክሻ አመቻችቼ እመጣለሁ ከፈቀዳችሁልኝ፤ ራስን ዝቅ ያደረገ ትህትናዊ ጥያቄ ነው። ክፋት የለውም።

ለእኛ ሰውና ሰው፤ መንግሥትና ህዝብ ሲገናኝ ያመናል። ወያኔም በዘጠኝ መንግሥት የሸነሸናት ኢትዮጵን፤ በ100 ሚሊዮን አሉታዊ ኢጎ የከዘነን ለዚህ ነበር። እኛ ግን ይህ ቀን አስበን በዬዓመቱ ስብሰባ እያዘጋጅን ኖረንበታል። ለእኛ የሚፈቀደው መንፈስ ለሌለው ባዕድ ይሁን ነው። ግን እኛ ምኖች ነን? የቅናትም አለው ዓይነት። የምቀኝነትም አለው ዓይነት። ይሄ እኮ እኛ ያደራጀነው፤ የደከምንበት፤ በእኛ ማንፌስቶ የሚመራ አይደለም። እኛ ሳንፈጠር የተፈጠረ የራሱ መርህ ያለው ስፖርታዊ ድርጅት ነው። ስፖርት ደግሞ ፍቅር ነው ተልዕኮው። ሌላ ቦታ መርኽ ይጠበቅ ከሆነም ይሄም አያስኬድም። ለእኛ ሲሆን አይሰራም ለሌላ ሲሆን መርህ ይሰራል። „አማራ ተጋድሎ“ ብሎ የወጣው እኮ ህዝብ ነው። ያ የሚሊዮኖች ድምጽ መርሁ ይከበር የለም። ከሚሊዮኖች ፈቃድ የአንድ ሰው ቀንጣ ትዕዛዝ ለእኛ ህሊና ገዢያችን ዳዊታችን ነው። መብት እንጂ የግዴታ ህግጋት እንዲያስተዳድረን አያሻንም። ሰው ይታዘባል አለማለት።

ምን አለ ሰው እና ሰው ቢገናኝ። ምን አለ መሪ እና ህዝብ ቢገናኝ። አማራ እና ኦሮሞ በባህርዳር ላይ ሲገናኙ የካድሬ ስብሰባ ነው ነበር የተባለው። ያ እኮ ነው ለዛሬ የመተንፈሻ ቧንቧ የሆነው። ከቅንጅት በኋዋላ እኮ የማናውቀው ዕዳ ተሸክመን ቀበሪ አልባ እኮ ነው ያለነው። ልጆች እኮ የአገራችን ሰዎች የሚሏቸው በዬጓራው ያሉትን እንደ አቅሪያባቸው ነው። ያን ጊዜ ልጅ የነበሩት ዛሬ አድገዋል፤ ከዛ በኋዋላ ተወልደው ያደጉትን እኔ አላውቃቸውም። ተበትነናል እኮ። በሦስት መሪዎች ከሦስት ተሰነጣጥቀን እንደ ጠላት ነው የምንተያዬው። በሃይማኖቱም ይሄው ነው። የውጪዉ፤ የአገር ውስጡ፤ የማህሉ ሦስት። እኔ አሁን ከሁሉም አልሄድም። ለዛውም ወንድሜ ሙሉ አቅሙን የሚያፈስበት የውጩ ስደተኛው ቅዱስ ሲኖዶስ ሆኖ። ስለምን? እማውቃት ቤተክርስትያን አንድ ብቻ ናት። አንዲት ትንሽ አገር ሲዊዝ ሦስት የሰባካ ጉባኤ ነው ያለው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ። እና ሥርጉተ የት ትሁን? ሦስት አካል የለኝም ያለኝ አንድ አካል፤ አንድ ገጽ ነው። ከአንዱ ሂዳ ከሌላው ብትቀር ደመ መራራ ናት። ስለዚህ እኔ ከውጪ አገር የተዋህዶ ቤተክርስትያን አንድ በመሆነቸው አንድነታቸውም ታምር ከሰራው የሌላ አገር ተዋህዶዎች እሄዳለሁኝ ዓውደ ዓመት ሲሆን አቅም ሲኖረኝ። በቃ። ገዳማት በተወሰነ ጊዜ እሄዳለሁኝ። ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሰብሳቢ አልባ እንደተበተነ እኮ ነው ያለው።
  • ·         ክብር ሙቀት።

ዛሬ ያ አቧራ ላይ የወደቀው የፓን አፍሪካ የዓለም ማህበር መሥራች አቅሟ ወግ ደርሶት ኬንያ ላይ ኢትዮጵያ እንደዛ ስትከብር፤ ስትንገሥ ለነፃነት ራህብተኞች እሾኽችን ነው። ያን ያህል በግርማ እና በሞገስ አፈር ላይ የተጠቀጠቀው ኢትዮጵያ ኬንያ ላይ ትንሳኤዊ ከብረ ልዕልናዋ ሲታወጅ ባዕዳችን ነው። አጀንዳችን አልሆነም። ስለምን? የአማራ እና የኦሮሞ ተጋድሎዎችን ውጤትን ማድመጥም፤ ማዬትም ስለማንፈቅድ። ወያኔ ሃርነት ትግራይ የራሴ ድል ነው ብሎ ካድሬዎቹን አሰማርቶ በአፈረሳት ኢትዮጵያ ላይ የከንቱነት ሸቀጥ ቤት ከፍቶ፤ ዓይኑን በጥሬጨው አሽቶ ፊት ለፊት ሲሟገት፤ እኛ በተለያዬ ሁኔታ የተሳደድንበት ኢትጵያዊነት ከፍ ብሎ ሲልቅ የድላችን፤ የድካማችን አካል ልናደርገው አልፈቀድንም።  አላዛሯ ኢትዮጵያ ክብርት ኢትዮጵያ ስትሆነ ፍሳሃችን ሊሆን ሲገባ ሌላ ስንጠቃ እናመርታለን።

ስንት ሰው ነው ከሲኦል ጉድጓድ ኑሮ ወጥቶ ከቤተሰቡ ጋር የተቀላቀለው? ስንት ወገን ነው ስደት ላይ ታስሮ የነበረው ተፈቶ ለአገሩ መሬት የበቃው፤ ያ ዝም ብሎ ከመሬት የታፈስ፤ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ገዢዎች በደጋፊዎቻቸው ፈቃድ የተከወነ ድል ነውን? ኤርትራ ላይ በዘመነ ደርግ ጊዜ የታሰሩት እንኳን ከዛው ነው ያሉት፤ ከዛም በኋዋላ ትክ የሌላቸው መኮንነኖች ሁሉ ነፃነት እናመጣልን ብለው  የኤርትራ የሴራ ዋሻ ብልቷቻውል ግን የኤርትራ መንግሥት ተጠይቆ ያውቃልን? አጀንዳ ሆነው ወገኖቻችን ያውቃሉን? ዛሬ ሱዳን፤ ኬንያ፤ ሳውዲ አርብያ በተገኙበት ሁሉ እርዳታችሁን ሳይሆን ክብራችን መልሱ ብለው የሰማይ ታምር ባለቅኔው ጠ/ ሚር ለውጤት ሲበቁ የእኛ አይደለም። የአንድ ሰው ነፍስ እኮ አንድ ቀን አይመረትም። 

ያ ጀግና ኮ/ ደመቀ ዘውዴ ክብሩ ሳይደፈር ከእስር መውጣቱ ሳይሆን በስብሰባ ጥሪ አልደረሰውም ሌላው ሙግት ነበር በጎንደሩ ጉባኤ ያዳመጥኩት። ትልቁን ነገር ትተን። ከቁም እስር ይፈታ ነው መሰረታዊ ጉዳይ ሊሆን የሚገባው። ሺህ ሌባ ይፈታ አርበኛ አንዳርጋቸው ለልጆቹ ነፍሱ ይትረፍ። መከራውን ለተጋራች ለትዳሩ ይኑርላት። የሺብሬ እናት ምን ተጠቀመች? ማን ያስታውሳታል? የእኔ ስጋት ሌላ ነው ከእነ ሙሉ አካሉ መንፈሱ ያስረክቡን ይሆን? ወይንስ የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ቀደም ብዬ እንደ ፈራሁት ይሆን ነው የሚስጨንቀኝ። በእሱ እሰር ዙሪያ ብዙ ትብትቦች አሉ። ይህ ነው እንጂ ለእኔ ቁም ነገሬ የሌባ መፈታት፤ መሾም መሸለም አይደለም። አርበኛ አንዳርጋቸው እኮ መንፈሱ ጊዜ እና ሁኔታ አላገዘውም ከእኛ ተፈጥሮ እንጂ ከልቡ ብቁ ሰው ነበር ለዬትኛውም ሃላፊነት። መከራን የሚደፈር በመከራ የኖረ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነው ለቂም ማወራረጃ …. እ.

ሌቦች ተፈቱ የግድ ነው። አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌን ነፍሱን ለማግኘት የእነሱን ሰዎች መፍታት ግድ ይላል። ለዛውም አንድ አጋዚ ምን ሊያደርገው እንደሚችል አይታወቅም። አንድ ሰው በቂ ነው። ባህርዳር ላይ አንድ አጋዚ እኮ ነው 50 ነፍስን የጨፈጨፈው። አንድ ሰው ነው ደራሲ ምስባእከ ወርቁን ቀፎውን ያስረከበን። የጨዋታው ሜዳ እኮ በወያኔ ሃርነት ትግራይ መዳፍ ውስጥ ነው። አረበኛ አንዳርጋቸው ጽጌን እስኪ እኔ እተካለሁ የሚል አንድ የፖለቲካ ሊሂቅ ውጪ አገር የሚኖር ይምጣ እና እኔን ይሞግተኝ። ኤርትራ እያለ ነው እኔ አንዳርጋቸው ጽጌ ሽልማታችን ነው ብዬ የጻፍኩት። ዛሬ የሚታዩት ፎቶዎች ሁሉ እኔ ያሳባሰብኳቸው ፎቶዎች የነበሩ ናቸው። ሁለት ቀን ነበር ያገኘሁት ያን ታላቅ ኢትዮጵያዊ፤ በቅንጅት ምሥራታ በሲዊዝ እሱም እኔም ገላጭ ሆነን፤ በፍራንክፈርቱ ስብሰባ እሱ ገላጭ እኔ ሰብሳቢ ሆኜ። ኢሜል /ስልክ ቀጣይ ግንኙነት አላስፈለገኝም። ሥሜን አያውቀውም። ሥሜን ሳልገልጥ ነበር ስብሰባውን የመራሁት። በዛ በሁለት ቀን አቅሙን ሳዬው ልክ እኔን አንደ ፈጠረኝ እንደ ጓድ ገ/ መድህን በርጋ ያለ የድርጅት ብቃት ነበር ያዬሁበት። እኔ ወስጥን ነው ማዬት እምወደው።

ስለሆነም አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌን ህይወት ለማግኘት ሌባው ሁሉ ቢፈታ ለእኔ ቅጭጭ አይለኝም። ሴራም አለበት የእሱ እስር ዘመን የሚፈትሽው። ይህንንም በተለያዬ ሁኔታ ጽፌበታለሁኝ። ብቻ ያ መከራን የፈቀደ አፈር በልቶ፤ አፈር ለብሶ እንደ ልዑል አለማዬሁ ቴወድሮስ እንደ ወጣ እንዲቀር የተበዬነበት ቅን ዜጋ፤ ብቁ ዜጋ፤ ከበለሃሳቦች እጅ ወጥቶ መከራውን ለተሸከመች የትዳር አጋሩ እና ልጆቹ ለእኔያ ዘመን እንዳሰራቸው ለኖረ አርበኛ አባቱ ይኑርላቸው። እኛማ ወርቃችን መቼ አውቅንበት። እኔ አንዳርጋቸው ጽጌ ሽልማቴ ብዬ የጻፍኩትን ጹሁፍ የሚለጥፍ ድህረ ገጽ እንኳን በወቅቱ አላገኘሁም ነበር። የላኩበትም መድርሱም የተረጋገጠብት የመልሱ ኢሜል በእጄ አለ። ግን ደፍሮ ፖስት ማድረግ አልተቻለም። ለምን? ድንብልብል። ይልቅ ለእስር ከታደረገ በኋዋላ መኖሩን ዘሃበሻ ሳያግደኝ መንፈሱን ሙሉ አስተናግዶልኛል እና አመሰግነዋለሁ በዚኸው አጋጣሚ። ታሪኩም ነው ለድህረ ገጹ አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ በቀላል የፖለቲካ ትንተና ሰብዕናውን ሆነ ብቃቱን መግለጽ አይቻልም። ውስጡ የሚያበራ ዕንቁ የነበረ ሰው ነው። ከእስር ቢፈታ ይህ ታላቅ ሰው ደስታውም ፍሰሃውም ሁነቱም የተከዱኑ ጠጠርማ ጉዳዮች አሉበት። ስለዚህ እኔ እርግጠኛ የምሆንበት ነገር የለም። ተቀላቅለናል። ማን ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም። የሚያዋጣው ዘግቶ ገዳማዊ ህይወትን አህዱ፤ ክለቱ፤ ሦለስቱ … አርባዕቱ … ማለት … ኑ እስክንባል በተፈቀደው ሁኔታ። 

  • ·         በለውጡ አራማጆች የተደራጀ የሥነ - ልቦና የጥቃት በረዶ።

ሌላ ይህ ለውጥ ከተጀመረ ጀምሮ ያወረድነው ማዕት በሥነ - ልቦና ላይ ያደረሰው ጫና ግምት ውስጥ አልገባም፤ ለለውጡ አራማጆች በለማ አብይ ገዱ አንባቸው። እነሱን እኮ ሰላማዊ ህይወታቸውን ነበር ያወከነው። ጊዜያቸውን ተሻምተናል። አትኩሮታቸውን በትነነዋል። ተረጋግተው ከአውሬው ሴራ ጋር እንዳይጋፈጡ ተጨማሪ ጫና ፈጥርንባቸውል፤ ለዚህም ታሪክ እንደሚጠይቀን ልብ ልክ ነው። ዳኛው ፈጣሪም አዘቅዝቆ ይመለካታል። ልክ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ኢትዮጵያ ሱማሌ፤ ጨለንቆ፤ ሞያሌ፤ ወልድያ፤ ቤንሻንጉል ላይ እንደ ከፈተው ጣምራ ዘመቻ እኛም በኔት ሞጥረን ማጣጣሉን፤ ማቃለሉን ነበር ተያዬዝነው። አዲሱ ለውጥ ለግብ እንዳይደርስ ታገልነው። ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ደግሞ ከ27 ዓመቱ ከነፃነት አርበኛው ሲደርስበት የነበረው ዱላ ተግ ብሎ ካሳ ነው የተሸለመው። የተሰነጠቀው ተገጠም። በስክንት ወቅቱን መከሩበት። ከልባቸው ሆነው ዘከሩ። አቅማቸውን እንደ ገና አሳምረው አደራጁ። አሁን መልሰው በመቋቋም ላይ ናቸው። መቀልበስም ሊኖር እንደሚችል ማሰብም ብልህነት ነው። ሌላ ያልተጠበቁ የጥቃት አደጋዎችም ባልታሰበ መንገድ ሊኖር ይችላል በግልም በጋራም ሽብር።

ቀን ተመልሷል ብሎ ሃሳቡን የገለጠው ሁሉ በተጠና ስልት ከምድረ ገጽ ይጠፋል ለውጡ ካልቀጠለ። እዬተመዘገበ ሊስቱ ተይዟል። በዚህ ማህል ለመጀመሪያ ጊዜ በትረ የቁጥጥጥር ሴል አከረክሪዋ ባልታሰበ ሁኔታ የደቀቀው ኤርትራም የሰላ የደህንነት ስራውን በስንጥቁ ውስጥ ገብቶ ያሻውን ይከውናል። የፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂ ጸሐፊ ማህበረ አቦይ ስብሃት እኮ ናቸው። አቦይ ከሁሉም ለሁሉም ሴራ የተዳራጀ ፖሊሲ ቀማሪ ናቸው። ዘረ ብዙ መረበ ብዙ። ሳጅን በረከት ስምዖን ደግሞ ከሰሞናቱ አንድ ሹመት ጀባ እንዲልላቸው ሌላም ቅድመ ሁኔታ ይኖራል። ይህም መጠበቅ ድንቅ ነው … አዲስ ነገር ሲፈጠር ያዙኝ ልቀቀኙ ከመንል … ሰከን ያለ ጉዞ፤ የሃይል አሰላለፍን ጥበብ መኖር ለፖለቲካ እርካብ ጠቀሚ ስለሆኑ ፊደል ገበታ እንግዛ … መምራት እንደሚናፍቅ ሁሉ ለመመራትም ናፍቆተኝ መሆን ያስፈልጋል። ልክ እንደ ቀድሞ ጠ/ ሚር አቶ ሃይለማርያም ደስአለኝ።

  • ·         የሰው ብርንዶ … ናፋቂነት።

ቀድሞ ነገር መቼ ነፃነት እርቦን? መቼ የህዝብ ዕንባ አንገብግቦን? መቼስ የኢትዮጵያ እናቶች የ43 ዓመት የሰው ብርንዶ ማቀርብ እንገፍግፎን? እኛ ቀይ ምንጣፍ፤ ሥም፤ ዝና በቃ። ኤርትራም እንዳይከፋት ጥብቅናው አለ። አሁን ይህም በሽታሽቶሽ አሹልከን ሁሉንም አጥተን ድንኳናችን ጥለን ከዜሮ ጀምረን እንደ ዘመነ ቅንጅት በረድ ድግሙ ታቱ በበረደው ቁርጭምጭሚት ይቀጥል ነው። አቅም ስለሚባለው ነገር የትርጉም ንጠት አለብን። ይልቅ ሌላም ዱብ ዕዳም ይጠበቅ። ከዚህ የሌቦች ማህበር በላይ … ውጪ ያሉ የትግራይ ሊሂቃንም እርቀ ሰላም አውርደው አዲስ መሪ ይዘን መጣን በማለት ብቅ ብለው የአብይን መንፈስ የሚሞግት አከርካሪ የሚሰብር የ100 ዓመትን ዕውን የሚያደርግ ስልት እና ስትራቴጂ ይጠበቅ። አቶ ሰዬ አብርሃም ወደ አገር ቢመለሱ ምን ሊባል ነው? ወይንም ቋፍ ላይ ያለው መንፈስ ፈንድቶ ወደ አልታወቀ አቅጣጫ ለውጡ እንደ ግብጽ መጪ ቢልስ …
ለመሆኑ የደንቢደሎውን ህዝባዊ ስብሳባ በአደብ አዳምጣችሁታልን? ዶር መራራ ጉዲናም ቢመረጡም አይፈልጉትም። ሌላ ሦስተኛ መንገድ የያዘ መንፈስ ነው። ማቀራረብ አይደለም ማጠጋጋት አይቻልም። አክቲቢስቱም የኦሮሞ ማለቴ ነው፤ ፈርስቶችን ጨምሮ፤ ሊሂቃኑም ከሚሉት ውጪ ያለ ደሴት ነው …

  • ·         ላዛሯ ኢትዮጵያ … የሥም ትንስዔዋ!

እነሱ በህይወት እያሉ እኮ ነው ሥሟ ሞት የተፈረደባት ኢትዮጵያ ዛሬ ሺህ ሚሊዮን ጊዜ የምትነሳው። ከመጋቢት 24 ቀን ከ2010 ጀምሮ ሲቆጠር ሳትነሳ ውላ አታውቅም። ለዛውም በክብር፣ በልቅና በጥበብ ልክ እንደ ጥንቱ እንደ ጥዋቱ። „ከንባታነት፤ ዳውሮነት፤ ሃመርነት፤ ሲዳማነት ውብ ነው ግን ኢትዮጵያዊነት ከሁሉም ይበልጣል፤ ከሁሉም ያድምቃል፤ ከሁሉም ይጥማል።“ ማህበረ ደራጎን እና የኤርትራ መንግሥት ይህን ከሚሰሙ፤ ይህን ከሚያዳምጡ ቀብራቸውን ይምርጣሉ። ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ አታሳፍልግም ከሚለው ጋር ጊዜያዊ የሃሳብ እርቀ ሰላም ፈጥሮ የኢትዮጵያን የክብር ጉዞ መንገድን ለመጥለፍ ቋንጃ ሲከተክት ውሎ ያድራል። አብይን ከከተከተ ዘመድ ነው ሁሉም። ተዛመደ በአሉታዊ ሐረግ። ለመሆኑ የት ነው ያለነው? ግን ገብቶናል ኢትዮጵያን በሙሉ ቁመና ማቆዬት ማለት ምን ማለት እንደሆነ? ቀን ጥሩ ነው። ላለመደገፍ መብት አለኝ፤ „ለመጠዬቅ መብት አለኝ ግን ግዴታ የለብኝ።“ ሆኖ አያውቅም። በዬትም ሁኔታ ካለግዴታ የተፈጠረ መብት ከለመብት የተፈጠረ ግዴታ የለም። የትም አገር። ሁሉንም ጠልቶ የሚኖር ዴያቢሎስ ብቻ ነው።

  • ·         ሩ መንፈስ።

ኢህአድግ በ27 ዓመት ያልሰራው የለውጥ ዓይነት አቅጣጫ አለ ለዛውም ዘራፊውንም፤ ሌባውንም፤ ወራሪውም፤ ደም ሲጨልጥ የኖረውን፤ በሰው ልጆች የስቃይ ጩኽት ሙዚቃ ሲዝናና የኖረውም፤ አርዮሱንም፤ ደራጎኑንም፤ ሳኦልንም ሁሉም ተቻችለህ ኑር ተብሎ ተፈቀዶለታል። ለማን ሲባል? ትውልዱን ለማስቀጠል ሲባል። ስንቱ ሌባ፤ ስንቱ ዘራፊ፤ ስንቱ አሳሪ፤ ስንቱ አክራሪ፤ ስንቱ ገዳይ፤ ስንቱ ዳብዳቢ ስንቱ ስንቱ ታስሮ ይዘለቃል? ስንቱ? ቁንጮው ላይ ሆኖ፣ ዳኛ ሆኖ፣ አቃቢ ህግ ሆኖ፤ ፈራጅ ቀዳጅ ሆኖ፤ አሳሪ ሆኖ፣ ደብዳቢ ሆኖ፤ ታች ያለው ሌባ ደግሞ ተሳዳጅ? አዛውነቱ ሌባ፤ ከእሱ የሚያንስውን ድርጁውን ሌባ ሲያሳድድ፤ ተሳዳጁም ሌባ አሳዳጁም ሌባ? በዚህ ቅጥመጠኑ በጠፋበት ውል የለሽ ጉዞ ነው እኒህ መሪ የመጡት። እኛም አላስጠጋናቸውም፤ እነሱ አላስጠጓቸውም የሁለት አገር ስደተኛ ነው የሆኑት። 

ብቻ ፈጣሪ አይረሳቸውም። ጊዜው አልበቃ ስላለ ነው እንጂ እኮ በእያንዳንዱ ንግግራቸው ውስጥ ያለው የተስፋ ዘር ሌላ ኢትዮጵያን አምጦ ለመወለድ የታለመ ስለመሆኑ እግር እግር እየተሄደ ቢሰራበት ስንት ፍሬ በኖረው። ለብዙ ዘመን የሚያገለግሎ መጠነ ሰፊ ልቅም ያሉ አዳዲስ የፖሊሲ ሃሳቦች አሉበት። ብዙ መጸሐፍም ይወጣዋል - ለቅኖች በዚህች በተወሰነ ጊዜ ብቻ ባለቅኔው ጠ/ ሚር  ያቀኑት ቅንነት ዘመንንም ይካሳል ታሪክንም ያወርሳል።

ጥያቄ ሁላችንም አለን። እኔም አለኝ። በልቤ እዬመዘገብኩ እያስቀመጥኩኝ። ቀጣይም ነው ሙግቱ። ግን ኢትዮጵያ መንግሥት አሁን አላት፤ በዚህ ዘርፍም ጉድለት አለ፤ ይህ ላይ ስስ ነው፤ ይህ ደግሞ ጭራሹንም አልተሰበበትም ተዘሏል፤ ባለፉት ቀናት ሚዛኑን ያላጠቡቁ ክፍተቶች አሉ፤ ሚዛኑ ካልተጠበቀ ለጥገናዊ ለውጡም ቢሆን አደጋ አለው የሚል። ከዚህም አለፍ ያሉም ምኞቶች አሉኝ። አቤቱታዬ ይቀጥላል። ግን ዛሬ የተገኘውን ከቶውንም ያላሰብኳቸውን የመንፈስ መረጋጋቶቼን ጠቅጥቄ አይደለም። እጅግ ወርቅ የሆኑ ተገባሮች ከመጋቢት 24 / 2010 ቀን ጀምሮ እስከ አሁን በተከወኑት ላይ የእኔ ብዬ አስጠግቼ አክብሬ ነው።

መሪ ሰው ነው እንጂ መሪ ማሽን አይደለም። መሪ ሰው እንጂ ባለክንፍ መሪ የለም። መሪ ሰው እንጂ አስማት አይደለም። መሪ ሰው እንጂ ቁማር አይደለም። በሌላ በኩል መሪ አጋዥ ሲያገኝ እንጂ ብቻውን ከሆነ የፈለገ ዕንቁ ይሁን ይወድቃል። የአርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ አቅም የባከነው በዚህ መልክ ነው። እሱ ያደራጃቸው የመንፈስ ሃብቶች ዛሬ የሉም ፈልሰዋል። መሪ ማሽን አይደለም ወይንም ማጅክ። ለ6 ኣውሮፓ አገር ሦስት ወር ነው ለመሸፈን፤ አሁን ደግሞ በቀን ሁለት ቦታ ለዛውም ውጪ አገር እና አገር ቤት መባተል ነው የሚታዬው።

በመንግሥት ሚደያ ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ ሲመሰገን አዳምጫለሁኝ። ጥረቱ ዕውቅና አግኝቶ። እነ አቦ በቀለ ገርባ ሲፈቱ ገንቦ እንኳን ጆሮ አለው፤ የመንግሥት ሚዲያ ተብዬው አንጠልጥሎ ነበር የጠራቸው። ሎቱ ስብሃት ስለ ሃጢያተኞች፤ አሁን ግን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሽብር ተጠርጥረው ነው የሚል ነው የተደመጠው። ይህ ለውጥ ነው። „አቶ“ ብሎ መነሳቱ በራሱ ዕወቅናው ቃል ጠባቂ ነው። የሰው ልጅን ክብር መጠበቅ። ከሰው የተነሳ ራዕይ እንደ አለ ስለመኖሩ ያመለክታል። ግርዶሽ ከተሰራለት ግን አይታዬንም።

ለእኔ የአሜሪካኑ ጉዞ ተሳካም አልተሳከም እምታተርፈውም እምትከስረውም ኢትዮጵያ ናት። ቢቀሩም ለመልካም ነው ቢገኙም ለመልካም ነው። ፈጣሪ የወደደው ይከወን። ጠቃሚ ከሆነ ያሳካላቸው የማይጠቅም ከሆነ ምክንያት ፈጠሮ ይዝለላቸው። ይህም አጀንዳ ሆነ መታመስ ግን ቅናት እና ምቀኝነት ብቻ ነው። አቅማቸው ስለሚታወቅ የቀረው መንፈስ ደግሞ ከእኛ እጅ ይወጣል ነው። አቻውን ለመከወን መትጋት እንጂ ሃሳብ ያለውን ትልም እዬተከተሉ መባትል የአቅም ብከነት በዛ ላይ ትዝብት ነው። ስንቱን ነው መቃወም ይቻላል? እግዚአብሄር የወደደው የቀባው የፈለገ መጋረጃ ቢሰራ አይቀሬ ነው። ሳጅን በረከትን ያህል የመከራ ሌሊት፤ አቦይ ስብሃትን የመሰለ የበረዶ ሌሊት የተሻገረ መንፈስ አሁንም አዶናይ አለው። ቅኖችም በጸሎት ይተጉለታል። የአረብ አገር እህቶቻችን ግፍ በመቃወም በተደረገው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ የተገኘ የኢትዮጵያ ኢንባሲ የለም። መቼም ያ ሰው መሆንን ብቻ ነበር የሚጠይቀው። ለነገሩ ያነን ሰልፍ የተቃዎሙት እኮ ናቸው ዛሬ ተነጥፎ ተጎዝጉዞ ንጉሣዊ አቀባበል የተደረጋላቸው እነ አቦ ሌንጮ ለታ። አሁን ደግሞ እስኪ እንገናኝ እንተያይ ነው …

  • ·         ብዕር መርኽ ክወና።

ለሰው መልካም ሲታሰብ መልካምነት በገፍ ያተርፋል። ክፉ ሲታሰብ ደግሞ ባላሰብነው ሁኔታ ቅጣቱ የእዮር ይሆናል። አለመርካት መብት ነው። ያረካ ደግሞ ድርጅትን በፖለቲካዊ ፍልስፍናዊ አቅሙ እና መርሁን መካች አድርጎ፤ አብቅቶ ሌት ተቀን ባትሎ፤ ወጥቶ ወርዶ ራስን ማስከበር ከልካይ የለበትም። ሜዳውም ፈረሱም … ይብቃኝ ተዚህ ላይ … ቀጣዩ ከጠ/ ሚር አብይ አህመድ ቢሮ ጋር ጠንከረ ያል ሙግት ይኖረኛል፤ ምኞት እና የተስፋ አቤቱታ ይሆናል። ከተሰነበተ።

  • ·         እኔ ቅኖች ጊዜው ሲኖር እንዲህ ቢሆንስ?

„kenebete (ቀንበጥ)“ ብሎግን እንዲሁም „Sergute Selassie Youtube“ ብትጎበኙስ ምን ይመስላችሁዋል።
የፍቅራዊነት የቃላት ፖስተራዊ ቻናልን ይጎብኙልኝ። እስቲ ኑልኝ!

„መሪ ማለት መሪ እንጂ ነጂ ማለት አይደለም።“
(ከባለ ቅኔው ጠ/ ሚር አብይ አህመድ የተወሰደ።)
ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

መሸቢያ ጊዜ።   

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።