የአማራ ተጋድሎና የኦሮሞ ንቅናቄ።

          ህም።
                                       ከሥርጉተ ሥላሴ 22.05.2015 (ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ)
                              „እናንተ ሴቶች ሆይ የእግዚአብሄርን ቃል ስሙ፤ ጆራችሁም የአፉን ቃል ትቀበል።“
                                                     (ትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ ፱ ቁጥር ፳)


  • ·         ጠብታ።

„ራዕይ የሌለው መሪ ነጂ መሆን እንጂ መሪ መሆን አይችልም። (ከባለቅኔው ጠ/ ሚር አብይ አህመድ የተወሰደ)“ ተመስገን ብላለች ሥርጉትሻ። ቃሏ „ነጂ“ እራሷ አቤት ቅቤ ስታጠጣ። ተመስገን።

ባለ ቅኔው ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ሰንበት ላይ ከውጪ ጉዟቸው ተመልስው እረፈት አላስፈለጋቸውም። ቀጥታ የሄዱት የውስጥን ቆሻሻ ጠረግ ለማድረግ በጋራ ከዶር ምህረት ደበበ ጋር ወደ አዘጋጁት ዓውደ የንጥህና ማስጠበቂያ ማዕከል ነበር 19.05.2018 እ.አ.አ። በቅድሚያ ግን ዶር ምህረት ደበበ እንኳን ደስ አለዎት። ምን ያህል ልቦናዎት ቅን ቢሆን ነው በጥረት ውስጥ ድል ዲል ያለለዎት። ለእርሰዎ የቀናችው ቀንም ትመጣልኝ ዘንድ እስቲ እባክዎትን ለአማኑኤል ይንገሩልኝ። „ኢትዮጵያ የአንተም የአንችም የእኔም ናት“ ተመስገን። „የኢትዮጵያን የቀደመ ክብሯ ይመለሳል!“ ተመስገን! ሌላም አንድ ተጨማሪ ተመስገን ላንሳ የዛሬ ሁለት ዓመት በአማራ የማንነት የህልውና አብዮት ላይ በተከታታይ እጽፍ ነበር። መቼም ለእኔ ቀላሉ ሥራ መጻፍ ነው። እንደ ቧንቧ ውሃ ስፈልግ መክፈት ሲያሻኝም መዝጋት እምችለው።

እና ያን ጊዜ የፖለቲካ ድርጅቶችን ለመሆኑ ማንፌስቷችሁ ስለ ህጻናት ምን ይላል? ብዬ ሞግቻችሁ ነበር። ከዛ በፊትም ተዳብዬ እሰራበት ከነበረው የራዲዮ ዝግጅት በ2005 ለመጀመሪያ ጊዜ የልጆች ፕሮግራም ጀመርኩኝ “አገር ማለት ምን ማለት ነው“ የሚል ነበር። አላስቀጠሉኝም። በጸጋዬ ድህረ ገጼ የቦርድ አባል የ7 ዓመት ልጅ በማድረግ በቀጣይነት „የሎሬት ተስፋ „ የሚል መምሪያ አደራጅቼም „አገር ማለት ምን ማለት ነው“ የሚለውን ለማስቀጠል ተጀመረ እሱም በጋራ ስለነበር በተለመደው የቅንነት ስብራት መቀጠል አልተቻለም። በመጨረሻ በግል ደግሞ ቢሻል ብዬ በጸጋዬ ራዲዮ ላይም „ፍቅራዊነት“ የሚል የልጆች ዝግጅት ጀመርኩኝ እሱንም የውጪ ሐገር ሰው በገንዘብ ገዝተው አልተቻለም እሱም ቀረ። ሌላም ነበር ለሌላ ቀን እሱ ይቀጠር …

ይህ ሁሉ አልሆን እያለ ሲያስቸግረኝ ከ2012 እስከ 2015 ድረስ ልጆች ተኮር የሆነ መጸሐፍ አንድ የግጥም „ፊደል“ የሚባል፤ ሌላ የክርክር ልጆች እዬተዝናኑ እያሰቡ የሚማሩበት „እንካ ሥላንትያ“ የሚባል ሌላም ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ያሳድጋሉ፤ የወደፊት ተስፋቸውንም እንዴት መንገዱን ቀድመው ይጠርጋሉ የሚል በንድፍም ጭምር የተሰራ ሲሆን „ጽናት እና ትዕግስት የሰራሁበትን መንገድ በ4 ኪሎው ገለጻቸው በባለቅኔው ጠ/ ሚር በስላይድ ሲያብራሩ አዬሁ፤ መጸሐፉ ላይ እኔ እንደዛ ነው የሰራሁት „የተስፋ በር“ የሚባለውን ለወላጆች / ለአሳዳጊ ድርጅቶች / ለአሳዳጊ ግለሰቦችም። ከዚህም ባለፈ እኔ ወላጆቼ በመለያዬታቸው ምክንያት እኔን እራሴን የሞገተኝን የኑሮ ፈታና መነሻ በማድረግ፤ እንዲሁም ወላጆች ቤት ውስጥ በክፍትነት የሚተዋቸውን መስኮችም በማከል ሌላም የልጆች ነገር ጭንቄ ስለሆነ ትዳሩ በቅጡ ካልተያዘ ማግስት ይፈርሳል፤ ከፍርሰት በኋዋላ ደግሞ ልጆችን በተሟላ ሰብዕና ማሳደግ ስለማይቻል „ርግብ በር“ የተሳካ ትዳርን እንዴት? የሚል ተጣፈ ሁሎችም ታግደው መጋዝን ያሞቃሉ። ገና ሲወጠን መልካም ነገር አዬር ላይ በሾታላዮች ታምሶ የትቢያ መደበር ያደርጉታል። አሁን የህፃናት ጉዳይ ባለቤት አገኘ ለዛውም በመንግሥት ደረጃ። ትንሳኤ የምለው እኔ ይሄን የሃሳብ ልቅና ነው። ኢትዮጵያዊነት ታስቦ ወራሽ ልጅ ተዘሎ አይሆንም። እንዲህ ለረጅም ጊዜ ስታገልበት የቆዬሁበት ጉዳይ ባለቤት ሲያገኝል፤ የእኔ ባይ ሲያገኝልኝ ተስፋው ሐሤት ነው።

እርግጥ ነው አሁን ሽግግር ላይ ስላለን አውሬው መንፈስ 100 ሚሊዮን ህዝብ ገድሎ ሳይጨርስ ስለሆነ ይሄ የምህረት አደባባይ ቀን የወጣለት እዬተጣደፈ ነው በቀጣይነት ለማጨድ፤ ስንት ዓመት ይቀጥልበት ይሆን? ብቻ ዛሬ ላይ ሆኜ እጽፋቸው የነበሩትን፤ መጨረሻ ላይ አሳርጋቸው የነበረባቸውን ስንኞች ምልሰት ሳደርግባቸው አቤቱታዬን መዳህኒዓለም ሰምቷል ማለት እችላሁ „ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል“ ባለኩት ጹሑፌ ላይ አንድ መፈክር ነበር „እኔስየበቀልና የባይታዋርነት ዘመን የሚያከትምበት ጊዜ ናፈቀኝ! ብዬ ነበር። ዛሬ ባለቤት የሌላቸው ማህበረሰቦች፤ አቅሞች ሁሉ ዕውቅና እያገኙ ነው። እኔም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆኔን እያዳመጥኩኝ ነው። ታማሚውም፤ የአካል ጉዳተኛውም፤ እንግዲህ ተዚህ የነፃነት አውራ ፓርቲዎች ያልሰጡኝን ተዛ ተባድማዬ መንፈሱ እዬተናኘ ነው። ግን በእርግጥ ለሥርጉትሻ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ይሰጣታልን? እሷ እኮ አንድም አይቀራት ከሊቅ አስከ ደቂቅ የወጠነው የሃሳብ ተዋረድ አልተመቸኝም ስትል፤ የሚሄድበትን አካሄድ ትክክል አይደለም ብላ ስታምን የሚሰማትን በብዕሯ በግንባር ሥጋነት እከሌ ይከፋዋል፤ እክሌ ደስ ይለዋል ሳትል ስትወቃው ነው የኖረችው። ግን ይቻላልን ለእኔ ዜግነት መስጠት? አይመስለኝም? 
  • ·         ዘንድሮ!
አሁን ወደ ተነሳሁበት … የሚገርሙኝ ነገሮች ይበራከታሉ በዘንድሮው ዘመን። የጠላ ጥንስስ አህዱ ሲል በትንሽዬ እንስራ ወይንም ገንቦ ሊሆን ይችላል፤ እንስራውም ሆነ ገንቦው አንድ ጆሮ ወይንም መንትዮሽ ሊሆን ይችላል። ብቻ አዎን ብቻ ምን በመሰለ እርጥብ ብሳና እና እንዶድ ልቡ ውልቅ እሲክል ድረስ ታጥቦ፤ ልቡ ጥፍት እስኪል ድረስ በክትክታ እና በአባሎ ወይንም በወይራ ታጥኖ ከንጡህ ውሃ ጋራ ደጃዝማች ጌሾ ለሦስት ወይንም ከዛም ለዘለለ ቀናት አብረው ሦስት ጉልቻ ይጎልታሉ። „ማቋጠሪያ“ ይባላል ጥንስስ እንደማለት ነው። ያው እኔ በጎንደርኛው አማርኛ ነው የማስኬደው፤ ወደ 24 ዓመት ሆነኝ እነዚህን አንገታቸውን ደፍተው የተቀመጡ ሙሽራ ቃላትን አደባባይ የማውጣትን ተግባር በፕሮጀክት ደረጃ ይዤ መሥራት ከጀመርኩኝ። ካልቸገረኝ በስተቀር ከቀበልኛ ዘዬ የወጣ ርዕስ ለህትምት ከበቁት 613 የአዋቂዎች የግጥም መድብል ውስጥ አልተጠቀምኩኝም። እነኛን ቄንጠኛ፤ ለዘኛ፤ ዜንጠኛ፤ ቅኔኛ፤ ፈሊጠኛ፤ ዘዬኛ፤ ጥዑመኛ፤ ዘዴኛ፤ ትውፊተኛ፤ ትንቢተኛ፤ ሸበልኛ፤ ሚስጢረኛ ሽሙንሙን ሆነው የተፈጠሩ ኢትዮጵያዊ ግን አንገተ ደፊ አፋርተኛ የቤት ልጅ ቃላትን የምጠቀመው ሀገራዊ ሃብትነታቸው የጋን ውስጥ መብራት ሆነው በመቅረታቸው አንጀቴ ስፍስፍ ልውስውስ ስለሚልላቸው ነው። አዝኘላቸው። እኔን ባይሰጣቸው ማን ያስታውሳቸው ነበር? „ተባረኪ ሥርጉትሻ“ ሹክታ መጣችልኝ በውስጥ መስመር። አሜን! አሜን! እንደ አፋችሁ ብርክ ብዕሬን ያደርግልኝ አማኑኤል። አቤት! እንዴት እንደምወዳቸው እኮ። እነሱም ዜጎች ናቸው - ቃሎቹ። ያምራሉ፤ ይስባሉ፤ ስላልነፈሰባቸው፤ ከነክብረ ድንግላቸው ስላሉ ደግሞ ውበታቸው የውስጥ ነው። ጣዕማቸው - ዜማቸው - ምታቸው ልዩኛ ነው። አይጠገቡም። ታድለው እነ ማራኪሻ! ትንሽ ነገር ተዝች ላይ የማስታውሰው ከአዲሱ ብሎጌ Kenebete ከቀንበጥ ላይ ታገኙታላችሁ ጥቂት ግጥሞችን፤ አምላካችሁ አለ ሞድ ያስፈልገናል ብለው ዲል ያለ ዲሞ ቢጤ በእኔ ላይ አድማ ስላደረጉም በቄንጥኛ የተጠለፉ ናቸው ትንሽ ግራ እንዳይገባችሁ። ሌላ ምን ነበር ጎንደር እኮ አማርኛ ሆኖ የቤተሰብ ቋንቋ ሁሉ ነበረን። አዎን የሚስጢር። ቀን የሰጠው እለት በዘይቤው አመጣላችሁአለሁኝ። ከኖርኩኝ። እኔ እንደ ሆነ ሞቴን እያሰብኩ ነው የምኖረው።
  • ·         ምልስት ወደ „ማቋጠሪያው“ …
ወደ ቀደመው ምልስት ሲሆን „በማቋጠሪያ“ የሰነበተው ጥንስስ እንደ ነገ አብሽሎ ሊጨመርበት በዋዜማው ቸረቸራ ይሁን ጉርድ በርሚል ሆነ ሙሉ በርሚል በተመሳሳይ ሁኔታ እስቲበቃው ታጥቦ፤ ታጥኖ፤ በረድ ብሎ ያመሽና፤ ማምሻ ላይ የኔታ ብቅል ደጃዝማች ጌሾ በተጨማሪነት ታክለው ከነባሩ ጋር በአዲሱ ቸረቸራ ዘለግ ብሎ ውሃ ይጨመርበትና ጎጆ ያዋዝማሉ። በዚህ ጊዜ „ተበራከተ“ ይባላል። በማግሥቱ የቀኝ ጌታ አብሽሎ ሠርግ ነው። ከሠርጉ መልስ ቅልቅል አለ። እሱ ደግሞ እነ ፊታውራሪ እንኩሮ፤ እነ ባላንባራስ ዶሮቄት ናቸው፤ ማስተካከያም ዲል ባለ የጉልበት ፍሰት እልልታውን አብረው ያስነኩታል የጫጉላ ጊዜውን። ሰነበትበት ይላሉ በጉባኤ አደራሻቸው - እዬዶለቱ። የዋዛ! ታዲንላችሁ ወጉ በሹክሹከታ ነው ተክ ተክ፤ ቱክ ቱክ ዋንኛ ቋንቋቸውን የተክና ቱክቱክ አንደበት። ተዚያ በስለናል ብቅሉም አብቅሎናል፤ ጌሾውም አለምልሞናል እንኩሮ ሆነ ዶረቄቱ ውበታችን በወሸቤ አብርቶታል ውበታችን አደምቆታል፤ ተጣምረን ደርጅተናል፤ ወጉም ደርሶናል እስቲ እንተያይ ብለው ጠረናቸውን ብቻ ይልካሉ። ማጀቱ ሁሉ አልባብ ባልባብ ነው። ብቅ ሊሉ ሲሽሞነሞኑ ከሰፈረ ወሸቤ ድፍድፍ ቅመሱ ከች ይላል። ምን አነሰ? ምን በዛ? ይባልና ማስተካከያ ካስፈለገ ተመጥኖ ይጨመርበታል። አሁን ምርጌቷ በወጭት ድስት በልኳ ተስተካክላ ትከወናለች። ከዛማ ሰንበትበት ብሎ ዝለላው ጉሽ ቅመሱን ገፈቱን በእፍታ አስከትሎ ከች። አዬ ጣሙ - ይምጣብኝ። በሁለተኛው ወይንም በሳልስቱ ማላፊያ ሆኖ ኮለል ሲል በአይዋ ወሸቤ ባሳበደው ጋን ከአተላው እዬተለዬ ወደ አዲሱ እልፍኙ ኮራና ደልደል ብሎ ስንዴ ከእንክርዳድ እንዲሉ ይኮኑበታል። ይህን ጊዜ ኮለል ያለው „ጥሩ“ ሲባል ቀሪው ደግሞ „አተላ“ ይሆንና ውሃ ይዘለስበታል። ለአሰር ውሃ ወይንም ለቅራሪነት ቦታው ይደለደላል። ለማተከዣ - ለኩታራ፤ ጊዜው እያለፈበት እዬነፈሰበት ሲሄድ እንትኑ የነፈሰበት እዬቆመጠጠ እዬሻገት ተስፋ አጥነት እዬበላው ግባዕቱ ለእንሰሳት መኖ ወይንም ለመሬት ግብዕት ይሆናል። አይጣል! አታዳርስ!

ተዛ „ለጥሩ ነጭ ለባሹ“ ግን ማነው ባለተራ ተብሎ ሲጠራ አይዋ ማንቆርቆሪያ አቤት ወዴት ይላል። በቀኛዝማች ብርሌ // ብርሌው ባለሹሩባ ሊሆን ይችላል ይንቆረቆራል፤ በግራዝማች ብርጭቆ ወይ ደግሞ በሊጋባው ዋንጫ ለድል፤ እንዲያም ሲል ከቅል በተሰራው አገርኛ በአሳላፊው አንኮላም ሊሆን ይችላል ወደ ቤተ ድምጽ ፈሰሱ ከትከት እያለ እዬተፍለቀለቀ ይምችህ የሚባለው። የጉሮሮ ማርጠቢያ ቆረር ይደረግለታል። ታዲያ ግን ተዚህች ላይ ካለበዛ እርካታ ከበዛ ደግሞ መንዘላዘል ያመጣል። ሲከር ይበጣሳል ሲሞላም ይፈሳል እንዲሉ …

አብሶ ጥሩ ጠላ የጎንደሬዎች ወይንም የጎጃሜዎች ከዓራት አይናማ ሴት አረቂዎች ከሆነ እስከ መንፈቅም ይዘልቃል። በቅቅል ዶሮቄት የተዘጋጀ ከሆነ የጌሾው አልኮላዊ ጣሙ እዬጠፋ መልኩም ጣዝማ፤ ጣሙም ጣዝማ ሆኖ ቁጭ። እንዴት ነው የኔዎቹ ሽው አላችሁን? ከገዳማዊቷ ብቅ ብትሉ … አይጠፋም ነበር … ተራራቅን … ምን ይሁን? ጠላውም ለእኛ ያው ፓለቲካ እና የሚያጣለ ስለሆነ። ተዚህች ላይ ብቃት ያለው ጥሩ ነው እያመረበት የሚሄደው እንጂ አተላው የአሰርውሃ ዕጣ ፈንታማ አምላካችሁ አለ ጆሮ ቁርጥ ከማድረጉ ራሱ ለዓይንም ቀፋፊ ነው። ኮምጣጤ። ሽግት ነው የሚለው። ሲያልቅ አያምር እንዲሉ። ጊዜም ሁኔታም የሚሰጠው ክብር ልዕልና በወጉ ካልተያዘ እንደዚሁ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።
 
  • ·         ዘሃ ብቻውን ሸማ አይሆንም።

በዛ ሰሞን አይዋ ለውጣዊ መንፈስ ተጊዜው ይባላል ሥሙ ቄሮን፤ አማራ ተጋድሎን አዲስ አበባን አንድ በማድረግ አንድ የተጋድሎ አዲስ ምዕራፍ የመጀመር እሳቤ እንዳለው አዳመጥኩት። ብቻ ይህን ራዕይ በሁለቱ አንጋፋ የተጋድሎ ጉልበታም ልብ በኦሮሞ እና በአማራ በተቀጥላ እሳቤ ሊሰራ ስለማይችል እንዲያው በዕድሜ ታናሼ በቁም ነገር የኔታዬ አይዋ የለውጥ የመንፈስ ሃሳብ አፍላቂ ተጊዜው መንፈሱን ባያባክነው መልካም ነው ባይ ነኝ። ማያያዝ አይቻልም። አሁንም መሰሉ ጉዳይ በአንድም በሌላም ይሄንኑ አዳምጣለሁኝ። ያው ሥር ነቀል ለውጥ ፍላጎትም መነሻው ይኸው ይመስላል። ሥር ነቀል ለውጥ እና ጥገናዊ ለውጥ አቅምን በማመጣጠን ባለማባከን እና በውርርስ አቅሙ ያለውን ጥቅም እና ጉዳት ራሱን ያቻለ አምክንዮ ነው። በሌላ በኩል በተለያዬ ጊዜም እንዳሳሰብኩት ወቅት ራሱ የሚሰጠው ዕድል አድማጭ ካገኘ እና ከባከነ ጥቅምና ጉዳቱንም ተዚህ በፊት ጥፌበታለሁኝ። የአሁኑ ወቅት ደግሞ ከኖርንበት ዘመን ይለያል። እንደ ቀደመው የተቃጠለ ካርቦን አይደለም።


·         የተጋድሎ ማያያዝ ተስፋ ሙት መሬትነት።

ስለምን ነው የማይሰራው? በመጀመሪያ ከቀደመው „ከድምፃችን ይሰማ“ ልነሳ። ያ ተጋድሎ ታምረኛ ነበር። ስልቱ ወጥ ነበር። ይህን ተጋድሎ ወደ ህዝባዊ ሁነት ለመለወጥ በግንቦት 7 በኩል ሰፊ ሽፋን፤ ሙሉ ዕውቅና፤ ሙሉ ቀረቤታ የተቸረው ነበር። ግን አልተሳካም። ንቅናቄው የራሱን እስረኛ ሙሉውን እንኳን ማስፈታት አልቻለም። ስለምን? ከተነሳበት ዓላማ ውጪ ሌላ ተጨማሪ ግዳጅ የመወጣት፤ ሆነ የመሸከም አቅም በባህሪው ሊኖረው ስላላስቻለው። ምኞት ከልካይ አልነበረውም፤ ኮፒ ራይቱን ሳይንፍጉ ተጨማሪ ተልዕኮ መስጠትም ክፋት አልነበረውም። ግን ምኞትን የሚያሳከው የፖለቲካ ፍልስፍናው ከተነሳው ህዝባዊ ባህሪ አቅም መነሳት ሲችል ብቻ ነው። ማገዝ ቢገባም ወያኔን ሥርዓት ይለውጣል ተብሎ አቅም አላቅሙ እና አላቅጣጫው ማፈሰስ ግን የፖለቲካ ፍልስፍና ግጠት ነው። በተጠማኝ ተጋድሎ የሌላ ድርጅት የማንፌስቶ ዓላማ ሆነ ተደራቢ ራዕይ አይሳካም። ሎጅክ።

ወደ ሁለቱም እንቅስቃሴዎችም ሲመጣ ሁለቱም ህዝባዊ ተጋድሎዎች በተጠማኝ ሃይል የተሳትፎ ታሪክ ቤተኛ ለመሆን ሳይሆን በራሳቸው አመክንዮች የተነሱ፤ ራሳቸውን የቻሉ ጉልበታም አብዮቶች ናቸው። ሁለቱም የታጋድሎ ሂደቶች የራሳቸው ውስጣዊ ገፊ ማንነት አላቸው። የእኔ የሚሉት። የእኔ የሚሉት አታጋይ መርህ አላቸው። ንክክኪ የላቸውም ከዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር። በትውስት ሃሳብ አመንጭነት የተጠነሰሱ አይደሉም። ሁሉንም የነፃነት ራህብ ለሽ ብሎ ከተኛበት ያባነኑ ቅጽበታዊ ግን ታማራዊ ስጦታዎች ናቸው። የእዮር! ሁለቱም ውስጣቸው ነፃነት ቢሆንም የዬራስ የአካሄድ ንድፍ፤ ቅደም ተከተል እና ጥያቄ አላቸው። የግንጪው ንቅናቄ የራሱን ነገሮችን ይዞ ነበር የተነሳው “የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን“ ማቀጣጠያ ማናሻ ነበር፤ ከሁሉም የቀደመ ሌላ የጎንደር የመይሳው ልጆች ድንቅ እርሾ ነገርም ነበረ። 

የእሱ ደግሞ ለዬት ያለ ነበር።  „የፈራ ይመለስ“ የሚለውን ይዘው አቶ ሞላ አስገዶም ትጥቃዊ ተጋድሎውን ትተው ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ 500 ወጣቶች በራሳቸው ወጪ ቲሸርት አሰርተው ፊት ለፊት በአደባባይ ወጥተው የወያኔ ሃርነት ትግራይን የሞገተው የመይሳው ትንፋሽ ነበር። ከዚህ በኋዋላ ነው የግንጪው ንቅናቄ የመጣው። ይሄ እዬተዘለለ ነው ግንጪ ላይ የሚኬደው እንጂ የቀደመው የተጋድሎ ጎኽ አነቃቂ - ጉልበታም - ቀስቃሽ - ልበ ሙሉ አቅጣጫ አማላካች የማይሳው ልጆች „የፈራ ይመለስ“ ድማሜ ነው። እኔ እንደማስበው እነኛ ሳተናዎች ነፍሳቸው ያለ አይመስለኝም። ልቅምቅም ተደርገው የታሠሩት ታስረው፤ የተገደሉት ተገድለው፤ የተሰደዱት ተሰደው፤ የታፈኑት ታፍነው፤ መድረሻቸው ሳይታወቅ የቀረ፤ የቀሩትም ከሥራ ተፈናቅለዋል። እኔም እዚህ የኢሳት የገንዘብ ማሰባሰብ ዝግጅት ላይ በ2015 ጥቅምት ላይ የተገኘሁበት ምክንያት የአንበሶቼን ሥም ስለማስታወስ ነበር። እግረ መንገዴንም ጎንደሬነቴን አስረግጬ በመናገር ያ ስብሰባ የመጨረሻዬ መሆኑን ለማተም ነበር። ካለ ቦታ አያምርም።
  • ·         ከቤተ ሳኦሎች ጋር የተካሄደ ህዝባዊ ተጋድሎ!


የ500 የዘለቀን ጀግንነት እንደ እርሾነት፤ ግንጪውንም ከእርሾነት ከፍ ባለ እንደ ማናሻ ማዬት ይቻላል። ከዚህ ቀጥሎ ያለው የጎንደር ጎጃም የአማራ የማንነት አብዮት ሥርነቀል ለወጥንም የጠዬቀ ስለነበር ከእሱ የቀደመ በምክንያታዊነት የሚነሳ አመክንዮዊ አብዬት በ25 ዓመት ውስጥ አልተነሳም። አልነበረም። ቀድሞ ነገር ብሄራዊ ሰንደቁን በድፍረትና በልበ ሙሉነት በመሬቱ ያወጣውም ያ ገድለኛ አብዬት ነው። መሬቱ ላይ ሻብያ በአደባባይ ብሄራዊ ስንደቁን ረጋግጦ ተጋድሎው የእኔ ማለቱ ጮርቃነቱን ብቻ ነው የሚያሳዬው። እሱን ራሱን ሻብያን አውግዞ የተነሳ ህዝባዊ አብዬትም ነው፤ በጠላቱ ተከሳሽ ሆኖ በወያኔ ሃርነት ትግራይ የታረደው። ታሪክ ይዳኘው። አዲሱ የዶር አብይ ካቢኔም ካሳውን፤ ፖለቲካዊ ወሳኔውን በምን ሊከውነው እንደሚችል በተደሞ ይጠበቃል። ሜድሮክስን በአንድ ቃል ጸጥ ያደረገ የጠ/ ሚር ቢሮ አማራ በግንቦት 7 ሥም የመከሰሱን፤ የመታረዱን እንቆቅልሽም መግቻውን ሥርጉተ ሥላሴ እዬጠበቀች ነው።
የአማራ የተጋድሎ አብዮት መሰረታዊ የሥርዓት ለውጥ የጠዬቀ ደረጃውን የጠበቀ፤ በውል የተደራጀ፤ በተሟላ ቅደመ መሰናዶ የታሰበበት፤ ራዕይ የነበረው፤ የመንፈስ ውህደት በመላው ዓለም የፈጠረ መሬት አንቀጥቅጥ የሰማይ ትንግርት መንፈስ ነበር።
ዓለምአቀፍ የሆኑ ግፎችን፤ መደፍጠጦችን፤ መጨፍለቆችን በሥርዓት ፈትሾ በህብራዊነት እና በህላዊነት ያዋደደ ለዘለዓለምም በአዕምሮ ውስጥ ቤተኛ ቢሆን የማይጎረበጥ መሬት አንቀጥቅጥ የጀግኖች ውሎ ነበር። መፈክሮቹ አሰራራቸው፤ ጥራታቸው፤ ኪናዊ ውበታቸው፤ ሊያስተላልፉ ያሰቡት ምህረታዊ መልዕከቶቻቸው፤ የተሳታፊዎች የህሊና ብቃት ሥርዬት ናፍቆት እና የህዝብ ሙሉ ድጋፍ እና እርካታ ወደርም አቻም፤ ብዕርም ብራናም አይችለውም። ህዝብ ነው ይሄን ያዘጋጀው። ሙሉ ሃላፊነቱን ወስዶ በቅኔ አቅልሞ። ስለሆነም በዬትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ተለጣፊ ወረቀት ሊጠቀለል ከቶውንም አይችልም። ጥያቄዎችም እንደ ተፈጥሯዊ ባህሪያቸው እስካልተመለሱ ድረስ ተጋድሎዎቹ ቀጣይ ይሆናሉ። ዝምታም አብዮት ነውና። ጸሎትም አብዮት ነውና።



ያ ገድላዊ የሰማይ ሽልማት ለዛሬ የፍቅርዊነት አብሮነት ድል ያበቃ የመንፈስ ጥሪት በገፍ ያተረፈ እጅግ ስኬታማ፤ ውጤታማ ሁልአቅፍ ዕሴታዊ ተጋድሎ ነበር። „የቡርቃን ዝምታን ሰይጣናዊ የ666 ግንብ“ አፈር ድሜ አስግጦ እንጦርጦስ የላከ ገድለኛ ነበር። ከዚህ በኋዋላ ቀጣዩ የሬቻው ዕልቂት እና የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ „በቃ!“ ያነሳው፤ የሃዘን፤ የጥቁር ልብስ የራሄል ዕንባ የወል ነበር። የተቃውሞ ገድልን በምክንያታዊነት አቅሙ በጉልበታማነቱ ማዬት ይቻላል። በዚህ ውስጥ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ርህርህናው የተፈተሸበት ፍጹም በሆነ መልኩ ሰው የመሆንን አቅም የፈተነ ሁኔታ ነበር የተፈጠረው። ይህ በሃዘን - በለቅሶ በመከፋት ውስጥ ያለፈ ዘመንን አንባቢ ህዝባዊ ተጋድሎ የነፃነት ህግ የረቀቀበት ነበር ማለት እችላለሁኝ።  „ሰከን“ በል የታላቁ አርቲሰት የይሁኔ በላይም ተግባር አንቱ ነበር። በዚህም ሥርጉትሻ የተገባትን ስለከወነችበት ሰዋዊ ስብዕናዋ ለመንፈሷ ስንቁ የዕድሜ ልክ ጥሪቷ ይሆንላታል። የተባበሩት መንግስታት የቀደሙት ጸሐፊ ያውቁታል ሁለታችን ተመሳጥረንበታል። 

እሳቸው እና ሥርጉተ የመንፈስ ትርጉመኞች ነን። በዚህ ተጋድሎ ውስጥ የሰከነ ጥበብን ያፈለቀ ምሳሊያዊ የልብ መሰባሰብ፤ ልዩ የውስጥነት ድምጽ፤ ገናና የነፃነት አርበኛው፤ የሰብዕዊ መብት ተሟጋቹ፤ የሎሬቱ ታቦት ቤተኛው የአትሌት ሊሊሳ ፈይሳ ዘመን  ተሻጋሪ ዓለም አቀፍ የተጋድሎ ጥበብ አያያዥ ነበር። ቅኔዋ ከጎንደር ተነስቶ ጎጃምን ይዞ ስሜን አሜሪካ አድርጎ አንቦ! ይሄ የሶላዳሪት እጅን ወደ ላይ አድርጎ መጣመር እዛው በጎንደሩ አብዮት ላይ የታዬ ነበር። ደግነቱ ይሄን ዓለም አቀፍ ማድረግ ውርስ አንቦ ተረክቦ ብርሃን አደረገው። ከሁሉም የተጋድሎ ድምጽ እጅግ ረቂቁ ገድል ሃዲድም የነበረው፤ የሰማይ ቃል ኪዳን ደግሞ የጎጃም የደም ግብር ነበር። ጎጃም ታሪክን በደሙ የጻፈ የታሪክ የኔታ ነው - ለሥርጉተ ሥላሴ። ለደቂቃ እኔ መንፈሴ ከጎጃም ናፍቆት ወጥቶ አያውቅም።

 ሂደቱን እኔ ስመለከተው ዛሬ ካለንበት ጋር ልክ በትንሽ እንስራ የማቋጠሪያ ጥንስስ የነበረው የ500 የመይሳው ልጆች „የፈራ ይመለስ“ ብለው የጀመሩት ተጋድሎ ሲሆን መበራከቻ የሆነው የግንጪው ንቅናቄ ነው። የሁሉም መንፈስ ስኬትን ለመፍጠር የነበረው ልፋት የውህደት ዕድምታ ደግሞ የጎንደሩ የአማራ የህልውና ተጋድሎ ነው ብዬ አስባለሁኝ። ከዚያ ዓዋጁ „የበቃን!“ የጸደቀው በሬቻ የዕንባ ጥቁር ልብስ ቀን ነው። በዚህ ሁሉ ሂደት የወያኔ ሃርነት ትግራይ የሰላ ሰይፉን፤ መሳሪያውን፤ ባሩዱን፤ የቂሙን ጥሪት ሁሉ በነዚህ ሞገደኛ ህዝባዊ ሞገዶች ላይ አፍሶ የቁርሾ መርዙን በአሻው ሁኔታ አወራርዶበታል። ዛሬም ቀጥሏል። መቼ ሊቆም እንደሚችል አይታወቅም። በወቅቱ ይህን ህዝባዊ ሞገድ ሊመራ የሚችል የተፎካካሪ ፓርቲ ሊሂቅ አልተገኘም። የህዝቡ ንቃተ ህሊና ከመሪዎቹ በላይ ነበር።

  • ·         ህዝብ የመራው ታሪካዊ አብዮት።
በዛ ላይ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ከተያዙ አጀንዳዎች ውጪ ሌላ ለአፍሪካ ሰላማዊ ትግል ማለት ምን ማለት እንደሆነ በጥበብ ያሰተማረው ለረጅም ጊዜ የዘለቀው „የድምጻችን ይሰማ“ ተጋድሎና የተከፈለው መስዋዕትነት የጎንደሩ የአማራ አብዮት ለዚህ የሃይማኖታዊ መብት መከበር ተጋድሎ የሰጠው ይፋዊ ዕውቅና እና ክብር ሌልኛው ህብራችን በውላችን፤ ድላችን ለመንበራችን በመሆናችን ስለመሆኑ መሬት የረገጠ ከፖለቲካ ድርጅቶ አቅም በላይ በሆነ ሁኔታ „ድምፃችን ይሰማን!“ መሪ መርሁ አድርጎት ነበር ተጋድሎው፤ ያ ዘመን ጠገብ ድርጁ እና ቆራጥ ተጋድሎ ህዝብ እማራለሁ ከሚለው ሙርቅርቅ የወያኔ ሃርነት ትግራይ የፖለቲካ ፍልስፍና አቅም ጋርማ በፍጹም ሁኔታ የማይመጣጠን ልዩ ፍጹም ልዩ የድንቅ ነሽ ድንቅ የልብ መሠረት ነበር። ስልቱ፤ ጥበቡ፤ አቅሙ፤ ጉልህነቱ የፖለቲካ ልቅናን ለማዋህድ የተሄደበት መንገድ ሁሉ የጎንደሩን የአማራ የማንነት አብዮት በተመሰጠረ ቅኔ ሲኬድ የጥቁር አፍሪካን የመጀመሪያም የመጨረሻም ታሪክ ነጋሪውን የፋሲል አግናባት ቀደምት ራዕይ ደረጃ ያስጠበቀ፤ ሥልጣኔውን ያበቃለ፤ የነዋሪዎችን የሥነ - ልቦና አቅም ሙሉ ለሙሉ ያስከበረ፤  የኢትዮጵያን የመንግሥት አመራር ብቃት ትውፊትን የተረጎመ፤ ጎንደር ማለትን ያነበበ፤ እና ያመሳጠረ የጉልላት ህብረ ነባቢት ነው። የመንግሥት ቅርጽ እና ይዘት ብቃት በህዝብ አቅም ህሊና ውስጥ ስለመሆኑ ተጋድሎው አመሳጥሯል ዓውጇልም።

  • ·         ነፋሻ ዝንቅንቅ አዬር።

በመሃል በኪናዊ አቅሙ የቅኔው ዕንቡጥ የቴወድሮስ ካሳሁን „ኢትዮጵያ“ መርህ ጸድቅ ዕንቁ ኪናዊ መለከተም ትሩፋቱን አስከብሯል። በዚህ ውስጥ ነው አዲስ የለወጥ ራዕይ መንፈስ በራሱ በገዢው ፓርቲ የባርነት ቀንበር በቃን የሚል ጭምጭምታ መደመጥ የተጀመረው። መነሻውም መድረሻውም የአማራ የህልውና ተጋድሎና የኦሮሞ ንቅናቄ ነው። በተፎካካሪ ሃይሎች ዕውቅና የተሰጠው ግን ለኦሮሞ ፕሮቴስት ብቻ ነበር። ከፖለቲካ ሊሂቃን ወገን አንድ ዕጣ ነፍስ ብቻ ነበሩ። እሳቸውም የመካከለኛው አፍሪካ ለእኔ ብቸኛ የምላቸው ጸሐፊ ፖለቲከኛ የዴፕሎማሲ ሊቅ አቶ የሱፍ ያሲን ብቻ ነበሩ። ለአማራ ተጋድሎ ሥያሜውን ህዝቡ አውጥቶለታል ሳለ። ህዝቡ „አማራነት ይከበር“ ብሎ ወጥቶ ሳለ። ህዝቡ „ወልቃይት አንችን ብረሳሽ ቀኜን ትርሳኝ“ ብሎ ወጥቶ ሳለ „የነጻነት ሃይል“ አደናገሪ ሞቶ ዘመን በማይሽረው የታሪክ ዝርፍያ እና ሌብነት በወሳኙ የህልውና ጥያቄ እንዲዋጥ እና ተትበስቦ እንዲቀር ሰፊ ዘመቻ እና ሰፊ የተጋድሎው የጸርነት ተግባር ተከውኖበታል። እንደ ብሄራዊ ሚዲያ ኢሳት እንደ ድርጅት በግንቦት 7። እንደ ጎረቤት አገር ኤርትራ። በአጋፋሪነት እና በጀሌነት ደግሞ ራስን ገዳዩ የጎንደሩ ማህበር። በማጣጣል መላ የትግራይ የፖለቲካ ሊሂቃን ከቅዱሱ አቶ ገ/ መድህን አርያ በስተቀር ሁሉም በክፉ ዓይን ነበር ያዩት። በወል እንዲከስም በነበር እንዲቀር የሙት በቃ የተፈረደበት ተጋድሎ ህዝባዊ አብዮት ቢኖር የጎንደርና የጎጃም የአማራ የህልውና ተጋድሎ ነበር።
ለወያኔ ሃርነት ትግራይም የአማራ ልጅ እንዲታረድ ምቹ ይለፍ የተሰጠውም በዚህ ምክንያት ነው። የሆነ ሆኖ ህዝባዊ እንቅስቃሴው መሠረቱ ይሄው ነው። ወያኔ ሃርነት የታላቋ ትግራይ የሥነ - ልቦና መሽሞንሞኛ መላበሻ የነበረው ቤተ - ሲኦል ሥነ ልቦናዊ ተራራ የተደረመሰው በእነኝህ ሁለት ተግባር ጠገብ የተጋድሎ ገድሎች ነው። በትግራይ የፖለቲካ ሊሂቃኑ „እንደ ገበያ ጫጫታ፤ እንደ ተራ የሰፈር ብጥብጥ፤ እንደ አልፈላ ቡብኝ ወይንም እንደ ጤፍ ጠላ“ ሲቃለል የነበረው የጎንደሩ የአማራ ተጋድሎ የህልውና አብዮት በወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥርዕዎ መንግሥት ሚዲያ የትሜና የተወረወረው ተጋድሎ ብቻ እና ብቻ ነው ለዛሬ የሚሊዮኖች የመተንፈሻ ቧንቧ፤ የክፉ ቀን እጂ አውጪ፤ የጀርባ አጥንት የሆነው። ተጋድሎው በግራ ቀኝ የታጠረበትን ግርዶሽ ጥሶ ታሪኩን መንበር ላይ ስለአዋለ ነው። ከዛ በፊትም ከዛ በኋዋላም የተካሄዱ ታጋድሎች ነበሩ፤ ግን ዛሬን ለመውለድ ወልዶም ለመራመድ አላስቻላቸውም። የመንፈስ ጋብቻ በሁለቱም ማህበረሰቦች ብቻ ሳይሆን ቅን በሆኑ ኢትዮጵውያን እውነቱን ያነጠሩበት ምስክር ነበር የአማራ ተጋድሎ። „ጋንቤላውም የእኔ፤ ኦሮሞውም፤ የእኔ፤ ድምጻችን ይሰማም የእኔ፤ እስረኛው ነፃነትም የእኔ“ ነበር ያለው። በነበሩ የተጋድሎ ሂደቶች አክተሮቹ ራሳቸውን ሲያተርፉ ህዝቡ ግን ያው መከራውን ተሸክሞ ራሱን በተስፋ ማጣት ሲገብር ነበር የኖረው ካለ አንድ አሰባሳቢ እና አለሁልህ ባይ። ይህ አብዮት ብቻ ነው ሁሉንም በመንፈስ ያጋባው ሞቶ በደሙ፤ ሞቶን ድል አድርጎ በአጥንቱ ፍላጭ ዛሬን በፍቅር በምህረት አምጦ ወለደ። መቱ ላይ እኮ 10 ሺህ ነዋሪዎች ወጥተው „ለማን አብይን አማራን እንዳትነኩ፤ በትነኩ ዋ!“ ነበር ያሉት። ይህ በምንም የፍልስፍና ቀመር እና ልቅና የማይለካ የማይሰፈር ንጡህ መንፈስ ቅዱስ ነው። 
  • ·         የምሥራች በጤና ጥበቃ ስልት።

ማንኛውም ህዝባዊ እንቅስቃሴ መሪ ከሌለው አንድ ቋት መግፋት አይቻለውም። እነዚህ ሁለት ተደጋጋፊ አብዮቶች አድማጭ አገኙ። በራሱ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ግርዶሼ ብሎ በለሰነው ማህበር ውስጥ የነፃነት ትግሉን ለማፈን በወሰደው እርምጃ ውስጥ በግርዶሽ የበላይነቴን አስቀጥዬ ተደላድዬ 100 ዓመት እገዛለሁ፤ ከዛ ዘረ ኢትዮጵያ ሥያሜውም „በህዳሴ ትግራዊነት“ ይተካል ሲል አዲስ ቀንበጥ ባለራዕዮች ጉዳያችን፤ አጀንዳችን ብለው ህዝባዊውን ተጋድሎ ማዳመጥ ጀመሩ። እንደ የራሳቸው ባህሪ አድማጭ የማግኘታቸውን ያህል ሁለቱ አድማጮች በጎንዮሽም መስመርም አዲስ ስልት ነድፈው መደማመጥ ጀመሩ። ልቅና ማለት ይሄ ነው። አዕምሮ ይሰራል የሚባለው ተረግጠህ ወይንም ጨፍልቀህ ወይንም ውጠህ ሳይሆን የተገባውን ዕውቅና ዕኩል በማድመጥ አክብረህ ነው። ኮፒ ራይቱን ለባለቤቱ ሰጥተህ። 

ስለሆነም አዲስ የጤና ጥበቃ መስመር ባህርዳር የደካ አዳማ፤ አዳማ የደካ ባህርዳር ተዘረጋ። ይህ የጤና መስመር ጊዜም ወቅትንም አላበከነም። ብልሃትን ሰንቆ ዳታ ሳያበዛ በፍጥነትን በልቅና መፍትሄን ቆጣጠረ። ይህ እንግዲህ እጅግ የበሰለ፣ የተራመደ፣ የሰለጠነ፣ የአቅም ብቃት መለኪያ ነው። ብልህነቱ ኑሮውን ለመምራት ከመነሳት ጀምሮ ብሄራዊ - አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን በተማከለ ሁኔታ ለመፍታት በሚያስችል ቁመና እና ወርድ እጅግ በራቀ በረቀቀም ራዕይ፣ በሙሉ መሰናዱ፣ በውል በተዳረጀ ህሊና ጠላት እና ወዳጅን በለዬ ምልከታ፤ ጥቃትን ለመከላከል በሚያስችል በተከደነ መንገድ፤ በከፍተኛ ጥበብ የተመራ ዕጹብ ድንቅ የሚያስብል የ21ኛው ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያ የፓን አፍሪካዊነት የአመራር የብቃት ኪናዋ ጥበብ የታዬበት፤ እጅግ ዘመናዊ ሥልጡን የሆነ የትግል ታክቲክ እና ስትራቴጅ ነው። ይህ ብቃት ዛሬ አይታይም፤ ለወግ የሚያበቃው በእጬጌው ሂደት ነው። ግድፈቶችን በመለቃቀም በጠላትነት ፈርጆ መታገለም፤ ግድፈቶችን በፍቅራዊነት ዕይታ ተስፋን ሰንቆ ነቅሶ አውጥቶ መሞገትም ሁለቱም መብት ነው። 

ፈራጁም ዳኛውም ህዝብ እና ጊዜ ነው። ቀኝም ግራም መንገድ ነው። ከልካይ የለም። ንግግር የተሰጠው ብቻ እንጃ የኔ ቢጤው የሚደፍረው የሙያ ዓይነትም አይደለም። መሪነት ከንግግር ዓዋቂነት ውጪ ድንጋይ አቅፎ መተኛት ነው። ይህን ጎንደሮች „ሲያጣ የጦመውን“ ይሉታል … የሆነ ሆኖ „ለሞኞቹ“ ይህ ታክቲክ እና ስትራቴጅ ህዝብን አቅፎ፤ ህዝብን ከሚያራቁቱ የመንፈስ ድህነት ድውዮችና ተወሳኮች ሁሉ ጋር ግብ ግብ ለመግጠም ቆረጠ፤ ወሰነ ፤ ለወሰነው እና ለቆረጠው መንገድ ደግሞ ጥበብን ምራኝ አለ፤ መቻቻልን ምራኝ አለ፤ ምህረትን ምራኝ አለ፤ ፍቅርን ምራኝ አለ፤ ትህትናን ምራኝ አለ፤ መሆንን ምራኝ አለ፤ ይቅር መባባልን ቅደመኝ አለ፤ በስሜት ሳይሆን በፍጹም በተረጋጋ መንፈስ በዕውቀት በበሰለ እና በዳበረ ክህሎት የሚመራ መንገድን አህዱ አለ። ዓላማውና ግቡ ኢትዮጵያን ቁም ነገር የማድረግ ሩቅ ራዕይ ስለመሆኑ ሂደቶቹ ብቻ እንዲገልጽ ይለፍ ሰጣቸው። መሰናዶው ዕለታዊ ሳይሆን የባጀ እና የበሰለ ብቁል ትልም መሆኑን አሳዬ። 

የብቃቱን ልክ በሚገርም ፍጥነት እና በተለዋዋጭ ስልቱ ሲያንቀላፋ የነበረውን ተስፋ አነቃቅቶ የጅም ደንምበኛ አደረገው። ኢጎይስቱ እና አውሬው ታወኩ፤ ቅናተኛው እና አራሙቻው ታመሱ፤ ደራጎናውያን የሚይዙትን የሚጨብጡትን አጡ። አውሬው መላ ጠፍቶት ሲወድቅ ሲነሳ ማጣፊያ ሲያጥረው አንዱ ሴራ ሲከሽፍ ሌላ፤ ሌላው ሲከሽፍ በሌላ እያከታተለ ቁርጭምጭሚትን ለመስበር ተጋ። ግን ፈጣሪ ያገዘው መልካምነት ወደ ፊት ገሰገሰ። መስዋዕትነትን ለውጤት በማብቃት እረገድ በታሪክ የኦሮሞ እና የአማራ ተጋድሎ ያደመጠው መንፈስ ነው። ዋጋም ዕውቅናም የማይሰጠው ምክንያት ትርፋማነቱ ልቁ በልጦ ስለወጣ ነው። የነበረውን አቅም አለኝ የሚለውን ሁሉ ፈተና ላይ አስቀመጠው። ከብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ እኮ በፖለቲካው ዓለም አንድ ዓመት ወይም ሁለት ዓመት መርታ አልታዬችም። ቢሮዋ እስር ቤት ነው የነበረው። ግን መንፈሷ ነው ክብር ያጎናጸፋት። ለወቅቱ። ይሄቺ ፖለቲከኛ በመንፈሳችን ጸድቃለች ለዘላቂ። ከእሷ የበለጡ ሙሉ ዕድሜያቸውን የባተሉ ሴቶች አሉ ግን ትቢያ ለብሰው የቀሩ። ወቅት የሚሸልመው የራሱ የሆነ ወርቅ አለው። መስዋዕትነት መክፈልና ስኬታማ መሆን የተለያዩ ናቸው። ያልገባን ይሄ ነው። ለዚህም ነው ይህን መሰል ጹሑፍ እስከ ቪዲዮ ላዘጋጅ የተገደድኩበት። ዕወቅና መንፈግ ዕዳም ነው። የፈጣሪ ቃልም ጥሰት። ካለ እርሱ ፈቃድ የሆነ የሰናፍጭ ነገር ስሌለ።

ይህ ሂደት በግርድፍ እና በሽርክት የተለሰነ ሳይሆን ወቅት ሰጥቶታል፤ አውቆታለም። ብቃቱ ስላለ። አበቃቀሉ ከውስጥ በመሆኖ፤ በታቀደ፤ አቅጣጫውን ባወቀ የእውነት ንድፍ ስለሆነ፤ በእውቀት ላይ በተመሠረተ ትጋት ስለሆነ፤ ዙሪያ ገብ እሾኽ ሆኖ የተነሳበትን የኢጎ ጃርታዊ አርበኛ ሁሉ እዬጣጣሰ ዛሬን ሰጠን። ሌላው ቀርቶ አቅጣጫውን የሚያስቱ ቀውሶችን ማምረት የማይሳነው ማህበረ ደራጎን ያጠመደው ወጥመድን እዬዘለሉ በፍጹም የአመራር ብቃትን እና በትዕግስት ወደፊት ገሰሰጉ ብልሆቹ። በዬተገኘችው ደቂቃ ሌት ተቀን ባተሉ። እርምጃውን ጠንቅቆ የሚያውቅ፤ አቅጣጫውን በሚገባው የተረዳው መሬቱን የሙጥኝ ያለ የለውጥ መሪ ሃይል የተዛነፍ ሆነ የጣልቃ ገብ እንኮሮዎችን እዬጣሰ በሰከነ ሁኔታ አዕምሮን ሳያባከን ሂደቱን እዬመራ ይገኛል። እነዛ ድንቅ 108 የራህብ መዳህኒቶች የሰጡት ዕወቅና ከተገባው ቦታ ላይ ስለሆነ እለቱ ፍርያማ፤ ፍሬውም የትውልድ እነጻ ስለመሆኑ የቆዬ ሰው የሚያው ይሆናል። እኔ እኮ ተናግሬያለሁ ብሄራዊ ቀን ሊያስወስን የሚያስችል አቅም ብዬ አብይ ኬኛ ክፍል ስድስትን ማዬት ይቻላል „ቀንበጥ Kenebete“ ላይ። እግዚአብሄርም የፈቀደው አለ። ቅብዕ ለበጎም ለጥፋትም ይሆናል፤ ልዑል እግዚአብሄር የፈቀደልን ግን የፍቅር ቅብዕ ነው። ይልቅ አቮ ጸሎት ይከሉበት።

ሃሳቡ፤ ከሌላ ድውይ እና ክልፍፍል የሥልጣን ጥመኛ፤ ወይንም የፋይናንስ እገዛ ለመያዢነት ሞፈር ዘመትኛ ላደረገው ማንፌስቶ፤ ሃሳቡ ከሌላ መጥቶ ደጋፊ ከሆነ ባለ ቻፕትር/ ደጋፊ በሚል ተቀጥላ የማይጫንበት ስለሆነ በአቅሙ ልክ በተለካ፤ ልቅም ብሎ በታሰበበት፤ በጥራት በተነደፈ የቅደም ተከተል የተግባር ንድፍ ርህርህናን፤ ትህትናን፤ አክብሮትን አክሎ ረጅሙን ጉዞ ተያይዞታል „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው።“ መሪ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፤ የመሪ ብቃት እስከ ምን ድረስ ሊከነዳ እንደሚችል፤ የመሪ ሰብዕዊነት፤ ስብዕና ምን እንደሆነ ጠረኑ በሰውኛ ፍልስፍናዊ ክህነት በራሱ ውስጥ በበቀለው ክህሎት፤ በራሱ ህሊና በጸደቀው አዲስ መንፈስ ነፍስን መልሶ፤ ነፍስን ሰጥቶ፤ ነፍስ ሆኖ ተስፋን አለሁልህ አይዞኽ ብሎታል። ተመስገን!  

  • ·         ማድመጥና ስጦታው።

ስለሆነም ይህን መንፈስ ለተፈለገው ዘላቂ አብነታዊ ጉዞ እንዲበቃ አቅም ከማዋጣት ይልቅ በማጣጣል እና አሳቻ ወይንም ዝንጥል መንገድ ሽቶ በዛ እሄዳለሁ ቢባል ራስን ለአውሬው የአጋጠመኝ አደጋ አጋድሞ ለማገዶነት ከመዳረግ ውጪ ተስፋ የለውም። በምንም ዓይነት መልኩ አማራ መሬት ላይ የተነሳው ጎመራ እና ኦሮሞ መሬት ያለውን ጎመራ በረዶ ላይ ያለውን የአዲስ አባባን መነቃቃት በመፍጠር ማያያዝ አይቻልም። አቅሙም የለም። አንዲትም ቦታም ትንሽ ነገር የለብታ ሽውታ ነበረች። ጥያቄዎቹም አይገናኙም። በትግል ዕድገታቸውም አይመጣጠኑም። ከሁለቱ ተጋድሎች ጋር አዲስ አበባን፤ ሆነ ሌላ የታሪክ ሽሚያ ግጥግጦሽ አምጥቼ እጨምራለሁ ቢባል በአንድ ድስት ወጥ ሩብ ኪሎ ጨው ጨምረህ ተበላ እንደማለት ይሆናል። ካለልኩ የተሰፋ ሽብሽቦ ከመሆን በላይ አንተ ማነህም ይመጣል? አዛዥም መሪም መሆንም አይቻልም - በፍጹም። ሁለቱም በመንፈስ ደረጃ መሪዎች አሏቸው። መሪነቱን ሚሊዮኖች ካተሙበት ቆዩ።

የሚቻለው አሁን በተቻለው መንገድ እዛው እቅርብ ያሉት የለማ አብይ ገዱ መንፈስ ከራሳቸው ማህበር ጋር በገጠሙት የጦር ቀጠና ውስጥ ጥሰው ማለፍ እንዲችሉ አቅም ማዋጣት፤ ወይንም ጎራን ለይቶ በወያኔ ትግራይ ማንፌሰቶ ሽብልል ግርዶሽ ተጠቅልሎ ማሸለብ። ቀጥሎም አብሮ መስመጥ ብቻ ነው። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ መሪ አለው። አሁን ባለቅኔው ጠ/ ሚር እያደረጉት ያለውም ይሄው ነው የ108ቱ ድምጽ አሸናፊ ሆኖ ይወጣ ዘንድ ነው ትጋቱ። ይህ ድምጽ አሸናፊ ሆኖ ሲወጣ ነው አዲስ ሥርዓት ሊዘረጋ የሚችለው። ሙሉ ለሙሉ ድሉም ያን ጊዜ ነው። አሁን ጮራ ብቻ ነው … ጨረር ነገር … ባይረሱ ያለበትን አካባቢ ፊት ለፊት በመግጠም ሳይሆን በጥበብ ፈውሳኛ ማድረግ። ይህ ደግሞ ለሁሉም አዳኝ መንገድ ነው።
  • ·         ሥር ነቀል ለውጥ እንዴት? 
ሥር ነቀል ለውጥ በቀጥታ ማምጣት የሚቻለው እራስህ በዳረጀኸው፤ ጠንከራ የፖቲካ ድርጅት፤ አቅም እና የማደረግ ብቃቱ ከሁለቱ ተጋድሎዎች በላይ በአዲስ የሃሳብ ልቅና ሙሉነት ባለው የህሊና ብቃት አቅም ብቻ ነው። ለዛውም ህዝብ ከተቀበለ። በብቃትህ ልቅና ለዛውም በትጥቅ ትግል የወያኔ ሃርነት ትግራይን ማንፌስቶ ሙሉ ለሙሉ ደርምስህ የበላይነትህን አረጋግጠህ አንተ ገዢ መሬቱን ስተቆጣጠር ብቻ ይሆናል ሥርነቀል የሚባለው የሚገኘው። በዚህ ሂደት ወያኔ ሃርነት ትግራይ ከነቅል ቋንቁራው ጥርግርግ ሲል ብቻ ነው። ይህን ለማድረግ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ሜዳ ላይ በሰላማዊ ትግል ታግለህ ከሆነ በህልምም አይታሰብም። ወያኔ ሃርነት ትግራይ የማንን ጎፈሬ ያበጥራል። አሁንም እኮ ባለድርሻ ነው። ሰላማዊ ትግል አገር ቤት እንታገላለን ሲባልም ተፎካክረን የወያኔ ሃርነት ትግራይን አውራነት እናሸንፋለን ነው። ለዚያ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ታምረኛ መንገድ የለም። አብራችሁ ኑራችሁ አይታችሁታል እኮ እነ ተፎካካሪዎች ድርድር ተብሎ በረዶ ሲጋገር። ፈቅ የሚል የሌለው።
  
እርግጥ ነው በህሊናህ ትጥቅ ልክ ብቃቱ ከኖረ፤ የፖለቲካ ብስለቱ ከኖረ እስከ አሁን ድረስም እኮ የሚያስጠብቅ ነገር ባልበረ። 27 ዓመት እኮ ከአንድ ትውልድ በላይ የዘለለ ነው። በታቆረ አምክንዮ። በማያድግ ዱካክ ማንፌስቶ። ወቅትን መምራት በማይችል የህሊና አቅም። አርቆ ይመጣልን በማይተልም ኮሳሳ ግንዛቤ። ለዛውም አንተ አታድግ ሌላው እንዲያድግ አትፈቅድ። አንተ የለህ ያለው እንዲያኖር አትፈቅድ። የአጃቢ ብዛት ህሊናን ሊያዳብረው ወይንም ሊያፈልቀው አይችልም። ጥሪት የህሊና አቅም የጥረት ውጤት ነው። ይህ ነው ስኬት። ይህም ቢሆን ተደራጅተህ ማሸነፍ ስትችል ያን ጊዜ የአሁኑ ቅልጣን እና ፈስስ ልበልን ማሳነካት ይቻላል። ይህ ሲሆን መላዕክታኑ ከሰማያ ሰማያት ወርደው ኢትዮጵያ በአንድ ትንፋሽ ራስ እግሯ ወርቅ በወርቅ ያደርጓታል፤ በልጅነት „አዲስ አበባ ላይ ወድቄ ብነሳ የሰራ አካላቴ ወርቅ ይዞ ተነሳ“ ይሆናል ማለት ነው። አሁን ያው እፍ ተብሎ ችግሩ ሁሉ ብን እንዲል ስንብተከተክ ውለን ስለምናድር እንጂ በራስ ሃሳብ ጸንቶ ቢያንስ ወጥ የሆነ አቋም መያዝ በተቻለ ነበር። 

አሁን አቤቱ ሰማያዊ ፓርቲ እንደ ጀመረው መሬት ላይ ማነው ጸሐፊ፤ ማነው ተጽዕኖ ፈጣሪ እያልክ ሰው እዬለቀምክ የሚሆን ሥር - ነቀል ለውጥ አይታሰብም። „ከሦስቱ አንዱ ይሻላል“ ይሻላል ካለከው የበለጠ አቅም አምጠህ ወልደህ መሆን አለበት ሥር ነቀል ለወጥን መተንበይ። አዲሱ ሰማያዊም መጥቻለሁ እያለ ነው። አማራ ሥም በተለወጠ ቁጥር ደም አይገበርም። ይልቅ ለሁሉም የሚጠቅም የአብይ የአስተዳደር፤ የአማራር፤ የቁጥጥር፤ የግምገማ  ት/ ቤት 4 ኪሎ ላይ ስለተከፈተ ያችን ከፈት እያደረጉ ገልብጦ ማንበብ የሚሻል ይሆናል። ኮፒ ራይት ባለቅኔው ጠ/ ሚር የሚጠይቁ አይመስለኝም። ትግል ሞናትነስ ሲሆን ነፃነት ይሞታል። ይህ ዶግማ ነው። አሁን እህቶቼ አሜሪካን አገር የሚኖሩት የዶር አብይ አህመድን ንግግር በሥርዓት ያዳምጣሉ። እኔ ሳስበው ወደ አዲስ መንፈስ ገብተዋል ማለት ነው። ከቃለ ወንጌል፤ ከመዝሙር፤ ከሀገር በቀል የሥነ ጥበብ ቤተሰብነት በመሪነት የያዙት የመሪያቸውን ንግግር ማድመጥ ነው። ቀድመው እንደ ጀመሩም ነግረውኛል። የሌላ መሪ ንግግር አዳምጠው አያውቁም። አማራነትን ወደውታል፤ ጎጃምን ጌጣችን ብለዋል። ለውጣቸው አስገርሞኛል። ወቅት እንዲህ ህሊናን ይገዛል። 
  • አዬህ እናቱ የእኔ አንበሳ ኢትዮጵያዊው ለውጥ ፈላጊው መንፈስ ሆይ!

አዲስ መሬት ያልነካው ሃሳብም አፍልቀህ፤ ከማንም ሳትጠለል ራስህን ችለህ፤ የህዝብን ልብ እና ቀልብ ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ ለመግዛት የሚያስችል ቁመና ኖሮህ፤ ደሃዋም ዜጋ ናት ብለህ ተቀብልህ፤ ጤና ያጣውም ጣዕሜ ነው ብለህ አቅርበህ፤ የከፋውን አባቱ የታሠረበትን ብር ብለህ ጠይቀህ አብረህ ተጫውተህ፤ የትዳር አጋሩን በቅርበት አጽናንተህ፤ ማትብህን ጠብቀህ በቃል ኪዳነንህ ጸንተህ፤ እናመሰግናለንም አውቀህበት፤ ቃል ኪዳኑን በውን ሁነህበት እንጂ በእግረ መንገድ ፖለቲካ የተነገረህን በኮፒ እየደገምክ እና እዬሰለስክ እንደ ካሴት፤ በሥም የመቀዬሬያ ሱቅ ከፍተህ እዬተገላበጥክ አይደለም ድል የሚሉት ቁምነገር። እንኳንስ አሁን አዳዲሰ ሃሳቦች በገፍ በ„ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ባለመቋረጥ እዬጎረፈ ቀርቶ በዘመነ ደመመንም፤ በዘመነ ቆፈን ቢሆን  እንደ ኩሬ ውሃ የረጋውን ግን ጣሪያ ላይ የተንጠለጠለውን ፍላጎትህን ለማሳካት ከልብ ጠብ የሚል፤ ሊደመጥ የሚፈለግ ሃሳብ ማፍለቅ፤ ገና ይሆናል ብለህ ቀድመህ መተንበይ ካልተቻለ ባቡሩ እዬጠላህ ዋዜማ ብቻ ሆነህ ትቀራለህ። ወይም ሥም ብቻ። ወይም ነበር ብቻ። ከቶ እዬተደማመጥን ነው የኛው ሥም አይጠሩ የለወጥ ፈላጊው መንፈስ? እንደዚህ ነው ነገሩ … „እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል“ ጎንደሬዎች ሲተርቱ „ጉልቻ ሲለዋዋጥ፤ ከዝንጀሮ ቆንጆ“ ምን ማለት እንደ ሆነ ቁጭ አድርጎ እያናዘዘ ነው ህሊናን አቤቶ ችሎት።

  • ·         የቀን እንጥሽታ፤
አማራ የጀግኖች ማርከሻ መሪ አለው። አንበሳ፤ ደልዳላ፤ ምራቁን የዋጠ፤ ብቁ የረጋ፤ ስክነት የረበበት፤ እንኳንም የእኔ ሆንክ የሚባልለት፤ የማይክለፈለፍ አንበሳው ኮ/ ደመቀ ዘውዱ የሚባል። ባለ ግርማ ባለ ሞገስ። ስኩን - ብጡል! ሌላውንም የታሰሩ የተንገላቱ፤ ቤተሰቡን የገበረ፤ ትዳሩን ያጣ ከ30 ሺህ በላይ መሪዎች አሉት። የሌላ ወርቅና ጨርቅ አድማቂ ከእንግዲህ አይሆንም። መስፈርቱ ይሄው ነው አማራ መሬት ላይ መሪ ለመሆን። ሌላው ማለገጥ ነው።

በተለይ የአማራ ልጅ ሲከሰስበት የኖረውን መሰረታዊ ጉዳይ እንውቃለን፤ አሁን ቢሆን ክሱ እሳቱ እዬነደደ ነው። ነገር ግን ለስለስ ያለው „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ያን ሁሉ መከራ ተሸክሞ ተረጋጉ እያለ ነው። ከማንም በተሻለ፤ ከዬትኛውም ሊሂቅ በበለጠ ለጉዳዩ ቅርበት ከተባለ ከአሁን ጊዜ የተሻለ ለአማራ ሁነኛ ባሊህ ባይ ጠበቃ ጊዜ የለውም። ስለአማራ ከአብይ መንፈስ የተሻለ መሪ በዘመኑ አያገኝም። ከሁሉም በላይ ለአማራ አዲስ ቀኑ ነው። እሱ ነዋ ዋናው የሁለገብ የጥቃት ተዋናይ ሆኖ በስውርም በግልጥ እስተዚህች ደቂቃ ድረስ ያለው። ሁሉም መስጥሮ ከምንጠራ አልተቆጠበም፤ ለአማራ ህሊናም በግለት ሽበር ከመልቀቅ አልታቀበም። የአሁኑ መታመስም ምንጩ ይሄው ነው። „ፋርጣ“ እንዴት አዲስ አበባን ይማራል ሲባል ቤተ መንግሥት ሲገባ ነደደ። ይሄው ነው ሚስጥሩ።
ይህን ቀረብን ብለው ከሚታመሱት ጋር አብረን ቆራጣ የሰው ያህል ክብር ሳንሰጥ ስናብጠለጥል፤ ስናጣጣል ለበለጠ መከራ እና ማጎዶነት ህዝባችን መንፈሱን ስንከፋፍል እንገኛለን እኛው እራሳችን። 

በሌላ በኩል ተጨማሪ በጥርጣሬ እንዲታይም፤ እንዳይታመን አሉታዊነትን እዬሸመትንለት ነው። ከቶ ከሥንቱ ነገር ጋር ይሆን አማራ ማህበረሰብን የምናጣለው? ከቶ አማራ ከስንቱ ጋር ነው የቂም ቤተኛ እንዲሆን የሚታጭለት? ከማንስ ጋር አማራ ይሠራ? ስልቱ ውሎ ግዞው የጠፋብን ነው። አልገባነም። ተደፍኖብናል። የማናውቀው ሐገር ናፋቂነት ከዘመነ ወያኔ ሃርነት በእጥፍ እንደሚጠብቅን አላወቅንበትም፤ በተዋህዶ ሃይማኖትም ሊመጣ የሚችለው ሰቀቀንም አልገባንም። እነኝህ ሊብራል የሆነ አቋም ይዘው የተነሱ ብሩህ ባለራዕይ ወጣቶች ይዘው የተነሱት መንፈስ ፍቅርና ምህረት ብቻ ነው። የበላይነት የገዢነት ስሜት በፍጹም ሁኔታ የለባቸውም። ማሰቡ ራሱ ፈጣሪ ይከፋብናል። ህጋዊ መሠረት እንዲኖረው መጣር የተገባ ነው። ሰው አላፊ ነውና። አቮ ለማ መግርሳ በራሳቸው ላይ የወሰዱት እርምጃ በራሱ የፖለቲካ ሸህም፤ ጳጳስም ነበር። ሚዲያ ቀረ አሁን ደግሞ አዲስ ፓርቲ ለአማራ የግድያ ገመድ …

እልቂቱ አሁንም አለ። ባለፈው ሰሞን እኮ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ከኢትዮጵያ ሱማሌ ወጥቶ ወላይታዎችን በአሰተዳደራቸው ቦታው አዳማ ይመስለኛል ተከፍተናል፣ ተሳደናል ብለው አስነስተውባቸው ነበር። ያን ጊዜ የዕጩ ጠ/ ሚር ውድድሩን ለማጨናገፍ፤ የሙያሌም ዕልቂት የዛኑ ሰሞን ነበር። አቦ ለማ መግርሳ እኮ ጥቁር ቲሸርት ለብሰው ነበር ስበሰባ ሲሳተፉ የነበሩት። ዶር አብይ አህመድም ድብ ያለ ገጽ ነበራቸው። ግን ዋጥ አደርጉት እና በዋናው ግባቸው ላይ አተኮሩ፤ ያን ቢስቱ የባሰ እንደሚቀጥል ያውቁታል። ያን ለመግታት ባይችሉ እንኳን ማመጣጠን እንዲቻል ቁልፋቸው ላይ ብቻ ተጉ። ይህ ማለት ግን ትጉሃን መከራውን አዳፍኑት ማለት አይደለም። ማጋለጥ ይገባል። እኔ እራሴ የዕዬለቱን እዬመዘግብኩኝ እይዛለሁኝ … ቀጥዬ ስለምሠራበት … አንኳንስ የሰው ልጅ ኢትዮጵያ ያለው አዬር እረፍት ያስፈልገዋል። ወፍራም ሙግቶች ሁሉ አሉኝ የጠ/ ሚር ቢሮ ጋር እምተጋበት ግን በአክብሮት ነው። እኔም ዜጋ ነሽ መባሌን ስለሰማሁኝ ትናንትና መደመጥ አለብኝ። እኔን ebc ያደመጠኝ አግባብ ነበር።
  • ·         መፍትሄ። 

ፍቅር ነው የሚከስውን ክሶ፤ የሚያቻችለውን አቻችሎ፤ ጊዜ የሚሰጠውን ጊዜ ሰጥቶ፤ ይቅርታ የሚጠይቀውን አስጠይቆ አስማሚ ድልድይ ሊሆን የሚችለው። ለመሆኑ የአማራ ተጋድሎ ባይነሳ ይህ የኦሮሞ እና የአማራ ዓይን ለዓይን መገናኘት እንኳን ይቻል ነበርን? ተስፋዬ ከይሲም ሆነ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶም አለያይቶን ነበር። ከሁሉም ቀድመው እኮ የተሰዉ ወገኖች አሉን። እነሱ እኮ ይህን ዕድል ይህን ትንፋሽ አላገኙም፤ እነ ሻ/ አጣናው ዋሴ እኮ እዛው አስር ቤት ነው ህይወታቸው ያለፈው። ለዛሬው ሰቀቀን ዛሬ ያልገባን መቼውንም አይገባንም። ኦህዴድ አኮ ችሎቱ ልክ የለውም። ያን ያህል ህዝብ ተጨፍጭፎ፤ ተፈናቅሎ በጣምራ አራቱንም መንትዮሽ የፈተና መንገድ የተሻገረው በአማራር ብቃት እና በሰብዕና ብቃት ነው። አሁንም ለማቋቋም ዕድሉን ሁሉ ለመጠቀም አንቱ ነው።

ኦህዴድ ከ700 ሺህ በላይ ህዝብ ሲፈናቀል የሚይዘውን፣ የሚጨብጠውን አጥቶ ተርበትብቶ ቢሆን ኖሮ፤ የመከራውን ውቅያኖስ የምታሻግረው መርከብ ሰምጣ ትቀር ነበር። ነገር ግን ዕለታዊውን ሳይሆን በዛ መልክ ቢቀጥል ሊመጣ የሚችለውን የከፋውን መራር ቀን አስልቶ፤ መግቻውን ርካብ ላይ አትኩሮቱን አድርጎ፤ ችግሩን በመቻል ችሎት አድርጎ ሊታመን በማይችል የግል እና የጋራ ሃላፊነት ውህደት የኖኽ መርከብ ወጀቡን ተሻግራ ብርሃና አበራች - ለሁላችንም ለሞኝ ቅኖች። የተረፈው ለዘር ነገን ይሠራል። ነገም ቢሆን አውሬው የተፈጠረው ለጥፋት ስለሆነ የእፉኝት ተግባሩን ባለሰብነው፣ ባላቀድነው ሁኔታ ይቀጥላል፤ በመኪና ግጭት፤ በምግብ ብክለተ ወዘተ … እሱ በነደፈው ልክ እንቅፋት በፈጠረ ቁጥር እዬተደናቀፉ መሃል መንገድ ላይ መቅረት ሳይሆን ያን የዴያቢሎሳዊ ሥራውን ለእሱ የቤት ሥራ እዬሰጡ፤ ዘላቂና አስተማማኝ የህዝብ አንድነት መገንባት ከተቻለ አረም አረም ነው በራሱ ጊዜ ይከስማል። ሙጃም ሙጃ ነው በራሱ ጊዜ ጠውልጎ ይሞታል። ጥላቻም በረከት የለውም … ከትውልድ እና ከዘር ይነቅላል „ልጅ አይውጣልህ“ እኮ ከባድ እርግማን ነው። ሚሊዮኖች በዬእለት ኑራቸው ይሄን ማለታቸው አይቀሬ ነው። ህ!

ቁጭ ብሎ ሂደቱን ላጠናው እኮ አፍሪካ ላይ ለዛውም ቁጥር ስፍር በሌለው ችግር ከሰመጠች ሐገር ውስጥ የተከወነ ብልህነት አይመስልም። እኔ የመቀሌውን፤ የጎንደሩን፤ የጅጅጋውን፤ የአሶሳውን፤ የአዋሳውን ስብሰባ በተደጋጋሚ ሳዳምጠው፤ የሚነሱ አንከሊስ ሃሳቦችን ሳስተውል፤ የሚገናኝ የሃሳብ ተፋሰስ እንኳን የለም። ኢትዮጵያ ያላት የብሄር ብሄረሰባት ብዛት 80 ሳይሆኑ፤ ኢትዮጵያ ያላት የብሄር ብሄረሰብ ቁጥር 100 ሚሊዮን ነው ከማለት ደርሻለሁኝ። ሁላችንም እያንዳዱ ዜጋ የራሱ የእኔ የሚለው በአሻራው ልክ የኢጎ ብሄረሰብ አለው። የውጥንቅጥም ዓይነት አለው፤ የዝንቅንቅም ዓይነት አለው፤ የድብልቅልቅም ዓይነት አለው፤ የመቀዬጥም ዓይነት አለው የሃሳባችን - የፍላጎታችን - የተፈጥሯችን፤ የራዕያችን ምኑ ቅጡ ዥንጉርጉር ነው። አገራችን ደሃ አገር መሆኗን ሁለ ረስተነዋል። ከሰው አቅም በላይ። ይህን ዕድል አሹልከን በእንጥሽታ አስም ካሰኘን መቼውንም አናገኛውም። ለዛውም እኮ እንተዋወቃለን። ህም! ይልቅ ጋንቤላ ላይ በሆስፒታሉ ጉዳይ የተነሳው ደስ ብሎኛል እኔም ጽፌበት ነበር። ሌላው የቀብር ቦታ የተገባ ጥያቄ ነበር። ሰው በመሬቱ መቀበሪያ የለህም እዬተባለ መኖር፤ „ወላጆች ልጆቻችን ለማን ጥለን እንሂድ“ የሚልም ተነስቷል ይሄ እንደ ዜጋ ሊሞግተን ይገባል። እያለ መኖር ያልተፈቀደለት ህዝብ „የብሄር ብሄረሶበች ቀን መከበር?!!!! የአፍሪካ ነብርነት¡“ ገድሎ እንግዚአብሄር ይማርህ። ይህ ሲታሰብ አንዴት ተዘለቀ 27 ዓመት?  እም!
  • ·         ምን?

ከቶ ምን አለን? የህሊና አቅም፤ የመተንበይ አቅም፤ ወቅት የማድመጥ የመተርጎም ችሎታ? ወቅትን የመቀዬስ ተስጥኦ? ወቅትን የማብራራት ክህሎት? የማደራጀት ክህሎት? ረዥም ጊዜ ተቀምጦ ጉዳዮችን አጥንቶ የመፍትሄ መንገዶችን የመተለም ጸጋ? ማደራጀት ቂጥ ይፈልጋል። ለቁንጥንጥ ሰብዕና ማደራጀት ክፈሉ አይደለም። ለስልቹዎችም ማደራጀት ክፍላቸው አይደለም።ማደራጀት ጆሮ ይፈልጋል። ማደራጀት መክሊትም ይፈልጋል። ማደራጀት ሙያ ነው። ማደራጀት በግብር ይውጣ፤ በለብለብ፤ በግርግር በሁካታ የሚደፈር አይደለም። ለመሆኑ ዘላቂና ጊዚያዊ ፍላጎታችን አበጥረን አንተርትረን እናውቀዋለን? ምን አለን? ምርጫ ሲመጣ በሥም ተዥጎርጉረን ፓርቲና ውህደት? እንቅስቃሴ ሲመጣ ፓርቲና ጥምረት? አዲስ ሃሳብ ሲመጣ ተቦድኖ ማብጠልጠል፤ በቃ ይሄው ነው ያለን? ህዝቡ እኮ መትረዬስ እዬረገጠ የተቀቀለው እኮ ብስል መሪ አጥቶ ነው። ጥበበኛ መሪ አጥቶ ነው። አሻግሮ አመላካች መሪ አጥቶ ነው። 

50 ሺህ የአማራ እና የኦሮሞ ወጣት ወር ባለሞላ ጊዜ እኮ ነው ለካቴና ነው የተዳረገው። ሥንት ትዳር ነው የፈረሰው? ያን ጊዜ ከሥራ የተፈናቀሉት ብቃት ያላቸው ማናጀር የነበሩ ሁሉ ከሥራ እንደ ወጡ ነው የቀሩት። ለበለጠ መከራ ህዝብ እንዲዳረግ ማሰብ ማለት አቅም ሳይኖር ዘመናይነት ማለት ነው። ያን ሥር ነቀል ለወጥ ይመጣል ብሎ የሚያስበው መንፈስን መጠበቅ ጉምን መዘገን ነው። ይህም ከታሰበ እንደ ቀደምቶቹ በራስ ጫካና ዱር ተሞክሮ እንዬው። ይህን መሰለ አጋጣሚ ከዚህ በኋዋላ በ100 ዓመትም አይመጣም። ስለምን? ለመለወጥ ራሱ አቅም ስሌለን፤ ለማድመጥ ራሱ ልምዱ ስሌለን። መበለጥን ለመቀበል ችሎቱ ስለሌን? „ከአውር ቤት አንድ ዓይና ብርቁ ነው“ ሆኖ ለነገሩ እራስን ከእኔ በላይ ማን አለ ያለ „አቶ ሀ፣ለ“ አሁን ጨርቁን ጥሎ ቢያብድ በፍጹም አይደንቅም። አልሰማህም አይል ሙሉ ቀን አዲስ ሃሳብ፤ ሙሉ ቀን አዲስ ራዕይ፤ 45 ቀናት በሙሉ አዲስ ተስፋ ነው የሚደመጠው። ሚዲያው ሁሉ ምስሉ ዜናው እሱው ነው አዲስ ነገር። ለጠሉትም መቼም ከበሽታ ላይ የሚጥል ነው ወይንም የሥነ - ልቦና በሽተኝነትን የሚሸለም። ህም!
  • ·         ህም!
የችሎታን ደረጃ በልክ የማወቅ አቅም ስለሌለ፤ አንድ አጀንዳ ለማጽደቅ ምን ያህል ጊዜ ይሆን የሚወሰድብን? ከአጀንዳ በኋዋላስ በምን ነው የሚጠናቀቀው? ቁስለቱን አውቃዋለሁኝ በዘጋቢነት ተገኝቼ አይቸዋለሁኝና። ያን የመሰለ የጎንደር አብዮት „የኦሮሞ ደም ደሜ ነው፤ በቀለ ገርባ መሪዬ ነው፤ የጋንቤላውም የኔ“ ብሎ ሲወጣ እንኳን ኦፌኮን በአጀንዳ መወያዬት እና አቋም መያዝ፤ አውሮፓ ህብረት ዕድሉ ተገኝቶ ተግቶ የእኔ ብሎ ፊት ለፊት ተጋፍቶ ዕውቅናውን ማስጠበቅ ሲገባ የታዬ ነገር አልነበረም። ዜሮ! ያ እኮ የሰማይ ስጦታ ነበር ለህብራዊ መሪነት። የሌለው፤ ያልተወሳው፤ ያልተነሳው እኔ መራሁት እያለ ጦርነት ሲከፍት የተፈቀደለት ደግሞ ልዕልናውን ዳጠው። ኦፌኮን አረና ላይ መንፈሱን አበቅላለሁ ብሎ ሰያስብ ሰማይ ሲያንጋጥጥ፤ ሲደከም፤ ያለተለፋበትን ጎንደር ደሙን ገብሩ ክብርህን ተረከብ ሲለው አሻም አለ። ያልተወጣ ያልተወረደበትን ቅንጣት መንፈስ ያልፈሰሰበት ሎተሪ በአማራ ተጋድሎ ሲታደል፤ ሲቸር አቅምን የመተርጎም የብልህነቱ ደረጃ ታዬ። በጣም የሚገርመው ዐጤ ቴወድሮስ ሃውልት ላይ ፎቶውም ላይ ታዬዩታላችሁ ቪደዮወም ሰርቼለታለሁኝ ከተሰዉት ጎን ለጎን ማማው ላይ „የአቦ በቀለ ገርባ ምስል“ ነበር ጫፉ ላይ እዩት። ይሄን ያክል ሰማይ ጠቀስ ልቅና በጠላት ከተፈረጀ ማህበረሰብ፤ ከተጋፋ ማህበረሰብ፤

አሁን ጊዜ መልካሙ ነገር ሥሙን ለማንሳት ያልተቻለበት ዘመን ታልፎ „የአማራ የህልውና ተጋድሎ“ በይፋ ትንሳኤው በምዕራቡ ዓለም ሳይቀር ታወጀለት። ቁጭ ብለው አርበኞቻችን ከዓለም አቀፉ ልዑክ ጋር እኩል መከሩ። የዓለሙ የመቻቻል እናት ጠ/ ሚር አንጂላ ሜርክል ኢትዮጵያ በመጡበት ጊዜም ተፎካካሪዎች ጋር የነበረው የወል ቆይታ፤ ተከታታይ ቋሚ ክትትል ምንጩ፤ ዘሃ ግራው የአማራ ተጋድሎ ሰብል ነው። በዚህ እርምጃ እኔ አላፍርበትም። ወገኖቼ እዛ ቢታረዱም እዚህ ሥርጉተ እና ታቦቷ ሎሬቱ አላረፉም። ባትለዋል። ስኬታማም ናቸው።

የሆነ ሆኖ ኦፌኮ ዕድልን እንዲህ ነው የሚሾልከው። በማንኛው ጊዜ አዲስ ቡቃያ ሃሳብ ይዘው የሚመጡ ሰዎች የሉም ማለት የጸሐይን ሙቀት ተፈጥሯዊነት መካድ ማለት ነው። ለእኔ ከዬትኛውም ፖለቲካ ድርጅት በላይ አቅም እንዳለ ዛሬ ሳይሆን ቀደም ባሉተ ጹሁፎቼ ሁሉ ተግቸበታለሁኝ። ኢትዮጵያ ላይ አሁን የሚበልጥ ብቁ ብጡል መሪ ነው ያለው። ገናና ሥም ገናና መሪነት ማለት አይደለም። ገናና መሪነት ሃሳብ አፍላቂነት ለዛውም ከቻለ ብቻ ሳይሆን ያፈለቀውን ሃሳብ ማዝለቅ ማለት ነው። የቀደመው ሃሳብ ሥራ ላይ አውሎ በጣምራ ሌላ አዲስ ተከታታይ ሃሳብ ማፍለቅንም ሂደት እራሱ ያስገድዳል። አዲሱ ወቅት ሽሁራር የበላውን የታቆረ ሃሳብ ሙት መሬት ላይ ታጣፊ አልጋ ገዝቶለታል። ስለዚህ ያልተቋረጥ አዲስ ሃሳብ ማፍለቅ እና መንቀሳቀስ ይጠይቃል ትግል የሚሉት ሞገደኛ ከልሞገተ የማያስተኛ። 
  • ·         አዬ!
ወደ ቀዳሚው ሃሳቤ ስመለስ የተጋድሎውን ባህሪ አጠቃሎ ለመምራት የሚያስችል ተጨባጭ ሁኔታ መሬት ላይ የለም። አልሆነ ቦታ ተቀርቅሮ ግብር ለአውሬ ከመሆን በስተቀር ምንም ትርፍ የለውም። እውነት ለመናገር አቅምም የለም። አቅም እኮ ማለት ወቅትን ማድመጥ ማለት እና ለወቅቱ የሚመጥን ምቹ ሁኔታ ህሊና ውስጥ እንዲበቀል ማስቻል ማለት ነው። ይህ በራሱ የለም። የሚናፍቁትን አዲስ ፊት ለማዬት ብራና ላይ ጹሑፍ በመጻፍ ሳይሆን መሬት ላይ ያሉት ድርጅቶች እንኳን ሚዲያ ከማሳደድ፤ የሌላ ሃሳብ ተዳባይ ሆኖ በራስ ለመቆም ከመማሳን ይልቅ ቢያንስ አዲስ አባባ ላይ የተጠናከረ ተግባር ከሴራ - ከሸር - ከተንኮል እና ከደባ የወጣ ንጹህ መንገድ መከተል ይኖርባቸዋል። አዲስ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ተጨማሪ መቼም አዲስ አንደሚኖርም አስባለሁኝ ጠረኑ እሱን የሚሸት ነገር አለው ከተፈጠረ ያው ያለው መታገያ መሬት አዲስ አበባ ብቻ ነው። ያ መከረኛ አማራ ከእንግዲህ በእክሌ ፓርቲ እዬተባለ ዘር አልባ መታጨዱን የቆረጠበት ስለመሆኑ አዳምጠናል። እንኳስ አማራ ነኝ አትበል ተብሎ ቀርቶ አማራ ነህም፤ እኔም የደምህ ክፋይ የአጥንትህ ቁራጭ አማራ ነኝ ተብሎ እንኳን ቢሆን ከእንግዲህ ዬትኛውንም ድርጅት ራዕይ ተሸክሞ ለሌላ የሥም ግንባታ ተቋም አማራ ገንቢ አይሆንም። ቢታሰርም፤ ቢሞትም በሥሙ በራሱ በአማራነቱ ስለመሆኑ እንቅጩን በአንድ ድምጽ ገልጧል ድፍን ጎጃም ድፍን ጎንደር። እስክንደነግጥ ድረስ። ያን ያህል ቁርጠኝነት የሚገርም ነበር። 

መቼም ኦሮምያ ላይ የማይታሰብ ነው። ኦሮምያን የሚደፍር የለም። ስለሆነም ኤክስፖርት በሚደረግ ራዕይና ግብ አማራን መምራት ከእንግዲህ የውድቀት ዋዜማ ነው። አንደበትም የለውም። የትኛውም ፓርቲ ካለ ማንፌስቶው መንቀሳቀስ አይችልም። አማራን ለምምራት አማራ ነኝ ማለትን ይጠይቃል። አማራንም አጀንዳ ማድረግን ይጠይቃል። በአዲሶቹ ዳርዳር አይቀሬ ነው። መሽሎክ ነው። ህዝቡ ተፈልጎ ግን አማራዊ መንፈሱ ተጠቅጥቆ ድምጹ የሚሆን አይደለም። አማራ አምርሯል። ይገባዋልም። 

                 
43 ዓመት ሙሉ መሬቱን እያቃጠለ፤ ትውልዱን በቀየው አስመንጥሮ የሰው ሥም በመውድሰ ታሪክ ሲገነባ ነውና የኖረው። የሌላው ቤተሰባዊ ዓውድ አልባብ ባልባብ ሆኖ ባቡርና ኢንደስትሪ ፓርክ ሲጠይቅ ልጆቹ የሚማሩበት ት/ቤት እንኳን የላቸውም። ለመኖር ያልተፈቀደለት ነው። ለመሆኑ አማራ አገሩ የት ነው?  አዲስ አባባ እራሱ በዝምታ ውስጥ የኖረው አማራ እንደ እሳተ ጎመራ ታምቆ የኖረውን ቁስሉን እያፈነዳው ነው። ብዙ ቁጥርም እንዳለ ይገመታል። ወቅቱና ፍላጎቶ፤ ወቅቱ እና ምኞቱ በፍጹም አልተገናኙም። አቅም ሲሳሳ ታዛ ለታዛ የተለመደ ነው። አሁን መንግሥት አለ በአግባቡ በግል ደረጃ ጥያቄዎች ይቀርቡለታል። እንሞግተዋለን።
  • ·         ዐጤው ጎጃም!
እኛ ያለንበት፤ የነበርንበት፤ የሄድንበትን ጎዳና ሁሉ ታዛቢው መስታውቱ ህዝብ በብልህነት እንደሚከታተለው መታወቅ አለበት። እኛ ስለፈለግን እኛ ስለወደድን ሳይሆን በራሱ በነጠረ የፍላጎቱ ቀለም ውስጥ የሚኖር ህዝብ አዲስ ፓርቲ በመሠረትን ቁጥር ና ልጎትትህ ቢባል በጅ አይልም ከአንግዲህ። እኛም እንተጋበታለን። የአማራ ተጋድሎ ብዙ ነገር አስተምሮታል - እኛንም። ዩንቨርስቲ ቢገባ የማያገኘውን የእውቀት ገብያ አግኝቶበታል። መልካሙን መልካም ያልሆነበትን አንዘርዝሮበታል። የጥሞና የሱባኤም ጊዜው ነው ይህ ዘመን ለአማራው። ሚዛኑ ሜዳ ላይ በወደቀ ጊዜ አለሁልህ ላለው መንፈስ ብቻ ነው የሚያደላው። የገረመኝ ነገር ጎጃምን ውጭ የሚኖሩት ጎንደሬዎች ጌጣችን ነው የሚሉት። ጌጣቸው መሆኑ የተረጋገጠው ዐጤው ጎጃም ደም ገብሮ ነው። የገበረው ደም ደግሞ ለአማራነቱ „ወልቃይት ጠገዴ አንችን ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ብሎ ነው“ ይህ ቃለ ወንጌል ነው። ዶግማ ነው። ለነገሩ „ተጋድሎም“ ቃለ ወንጌል ነው። ከዚህ ማዕቀፍ ውጪ የሚሆን ነገር ማሰብ አሽዋን አበጥሮ የማጣራት ያህል ነው። የጎንደሩ አብዮት እኮ ነው ራሱን
የሰዬመው „የአማራ ተጋድሎ“ ብሎ።  እነ አቤቱ ቅዱሳን¡ እኛ በሰጠንህ ቢሉት በድምጽ አልባው ተደሞው ክው ያደርጋል። ፈጣሪም አለ የማያዳላ። ትግሉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ይቀጥላል። አሁን እኛ እያለን ብናኝ ብትን አፈር የሌላቸው የአማራ ልጆች እኛ ስናልፍማ አብረው ነው የሚያልፉት። ስለዚህ በፍጥነት ወደ ራስ ተመልሶ የራስን የቤት ሥራ መሥራት ግድ ይላል። „አኖሌ“ አጀንዳችን ልትሆን አይገባም። በህሊናው ሞጋች ከቂም ጋር የተጣለ ግን የራሱን ክብር በሙሉ አቅም የሚያጠበቅ ጨዋ ጽኑ ሆደ ሰፊ አማራዊ መንፈስ መገንባት አለበን - ለትውልዱ። የዚህ ሰንደቅ ዓላማችን ሙሉ ክብር እና ሞገሰንም ማስመለስ ቀዳሚው ትውልዳዊ ድርሻችን ይሆናል።
  • ·          አማራነት ደም ነው።

የአማራ ልጆች በከረፋው የወያኔ ሃርነት በደል ተበድላችሁም „በማንነቴ“ ከማለት ይልቅ ድፈሩት እና „ በአማራነቴ“ በሉት። በስተቀር የትውልዱን የመኖር ርካብ እያሰመጣችሁት ስለመሆኑም ልታስተውሉት ይገባል። ተበዳዮቹ ምስክር መሆን ካልቻላችሁ በዳዩማ ጮቤ ነው የሚረግጠው። በዛ ላይ ለአማራ ቀና የሚያስብ አንብዛም ነው። ተኖረበት ተረጀበት እኮ … ነገም ዛሬም ዘመንም እንዳይበደል „አማራ ነኝ“ ማለት ቢከብድም „አማራ“ ተብዬ ተበደለኩ፤ በአዳባባይ በዳኝነቴ የተደበደብኩት በአማራነቴ ነው ማለት ዓለም አቀፍ ዕውቅናው ካጎላው እሲክ ከአርበኛ ሊሊሳ ፈይሳ ተማሩ። ይሄ እኮ ፈጣሪ አምላክ ወርዶ የሰራው ታምር ነበር። ግን ሾለከ። „ጥፍሬ ወለቀ፤ አካሌ ጎደለ፤ ዓይኔ ወጣ“ ይባል እና „በማንነቴ“ ማለት ይገባልን? በኢትዮጵያዊነት እንዳልሆነ ይታወቃል። ይህን መድፈር ሰውን ማትረፍ ሰብዕዊነትም ነው። አማራ ስለሆንክ አማራ ስላልሆንክ አይደለም። በዛ ላይ አማራም ኢትዮጵያዊ ነው። ይህ የፍትህ ዋቢ መሆን ህግ አዋቂነትም ነው። ይህ የሰብዕዊ መብት ተሟጋችነትም ነው። ይህ የፖለቲካ ሊሂቅነትም ነው። ራስን ስቶ የምንም ዓይነት ነገር ተጠሪ ውክል አካል ለመሆን ከባድ ነው። መነሻ ቤት አለው ሁሉም። ካለዘር የሚፈጠር ሰብል አለን? ለቤቱ ባለቤቱ ደግሞ ባለቤቱ ነው። መቼስ ቤት ሳይጸዳ በረንዳ አይጀመር ነገር …

ፊፋን ያህል ዓለምአቀፈፍ ባለአቅም ድርጅት በአደባባይ የተደበደበት አምክንዮ „አማራነት“ ነው። ይህን ገመና ማጋለጥ የአማራን ቀጣይ የስፖርት ተስፋ ጠባቂ ጠበቃ ማቆም ሆኖ ሳላ እንደዛ ማሽሞንሙኑ ግን ከ35 አስከ 40 ሺህ የሚገመተውን የአማራ ማህበረሰብን መግደል ነው። በተጨማሪም አፍሪካዊው የእግር ኳስ ቀንዲል ክቡር የይድነቃቸው ተሰማን የተጋድሎ ታሪክ በእሳት ማንደድ ነው። እሳቸው ለዚህ አልነበረም የታገሉት። የደከሙት። ዓመቱን ሙሉ አማራ በእግር ኳስ ምክንያት ተደበደበ፤ ሽንት በኮዳ ተደፋበት፤ በኤልኮፈትር በተደገፈ ጭፍጨፋ ተካሄደበት፤ ሃይማኖቱ ተደፈረ፤ የዩንቨርስቲ ተማሪ ልጆቹ በፎቅ ተወረውሩ፤ ይህ ሁሉ ከፊፋ ህግ ጋር በመጣሱ ምክንያት ነበር። ያ ድንቅ አርበኛ ሊሊሳ ፈይሳ እኮ ቀልብ የሳበው ወቅትን፤ ጊዜን፤ ሁኔታን፤ ቦታን በወጉ ስላደመጠ እንጂ ከእሱ በፊት መሰሉን የፈጸመ አትሌት ሁሉ ነበር። ብቻ ልብ ይስጠን! አላወቅንበት ስናሾልክ ስንሾልክ ግን እስከ መቼ? ሳይነኩ እነ ቤቮሻ እስከ አጃቢዎቻቸው ኡኡታ አሰምተው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያሳውጁ እኛ በአደባባይ ተዋርድን፤ ዘር አልባ ፍሬ አልባ ሆነን ማፈር¡ ማለጋጥ። ምህረትም መፍትሄም ሥርዬትም ንሰሃም በዚህ ግልብጥ መንገድ አይገኛም።

  • ·         ቪዲዮ የኦሮሞ እና የአማራ ተጋድሎ በምልሰት።
ቅኖቹ … የፎቶወቹን ቪዲዮ በፖስተር መልክ ሰርቻቸዋለሁኝ ይቀጥላልም። የተጋድሎ ታሪክ ስለሆነ ብታዩት አይከፋም፤ እንደ እኔ „ሞኞቹን“ እጋብዛለሁኝ በትሁት መንፈስ።

Freedom! ነፃነት! 05.22.2018

በማህበረ ሳጥንኤል በተስፋዬ ከይሲ፤ የቡርቃ ዝምታ፤ በኦንጋውያን፤ በሻብያ እና በወያኔ ፍርሻ የቁቤ ትውልድ እናቱን ላቆዩት አያት ቅድመ አያቶቹ ዕውቅና ሳይሰጥ አዬር ላይ የተፈጠረ አደርጎ እራሱን ተቀበለ። ታሪኩን የራሱን ፈራው። በተመሳሳይ ሁኔታ ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ አዲሱ የአማራ ትውልድ የአብይ መንፈስ ከጎረበጠው ደም የገበረበትን የራሱን ታሪክ አሳልፎ ለጮሌዎቹ መሸለሙን አልተረዳውም። ያጡት፤ ሾልከው የቀሩት ይነሰታሉ ይወድቃሉ፤ በደሙ ግብር አስቀድሞ መጪውን የትውልዱን ዕጣ ፈንታ በመተንበይ ልቅና እና ጥበብ አማራ ዛሬን ያሰገኘው አንጡራ ድሉን በግንጥል በቄሮ ብቻ እንደ ተገኘ አድርጎ ራሱን ገፍቶ ከዕንቁዊ ገድሉ እያወጣው ነው። ይህ የአብይ መንፈስ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ እኮ የአማራ ገድላዊ ታግድሎ እና ብሄራዊነት ዕሴት ያሰገኘው ረድኤት ነው። „የአማራ ተጋድሎ“ የተፈራበት አመክንዮ እኮ ይሄው ነው። ሌላ ሚስጢር የለውም። የአማራ የማድረግ አቅም በሌላ ሥም ተጋርዶ እንጂ በአማራ አቅም ጎልቶ እንዲወጣ ስለማይፈለግ ነው። መደራጀቱም የሚፈራው ለዚህ ነው። ስለሆነም አሁን በአለው የለውጥ መንፈስ ከታሪኩ ራሱን እንዲያገል አማራ በጣምራ እዬተሠራበት ነው። ይህ ገናና ታጋድሎ እዚህ ይደርሳል ተብሎ ስላልተገመተ ቁስል መግሉ ንፍርቅ ያደረጋቸው ኢጎኢስቶች ይዳክሩ የተፈጠሩበት ነው በሳጅን በረከት አምሳል ስለሆኑ። የሚያስፍረው አማራ ደግሞ ሰባራ ሰንጣራ እዬፈለገ አጃቢ ሆኗል። ዛሬ ያልተቀበለውን የማድረግ ብቃት ማንነት ነገ እየጣለው፤ ባይታዋር እዬሆነ እንደሚሄድ አላወቀውም።

አማራ ሆይ! የለማ አብይ ገዱ መንፈስ የራሰህ የደምህ ዋጋ ንብረትህ አዱኛህ ነው! ልብ ግዛ! ተጋድሎህ ባይኖር ዛሬን አታገኘውም። አንድ ጊዜ ልሳነ - አማራ የሚል የወጣቶችን ውይይት እከታታል ነበር። በህግ ዘርፍ ጠንካራ አወያዮችም ተወያዮችም አሏቸው። ግን የሚመቻቸው መሪ የለም። ስለዚህም ይህ ኢሜል ይሰራልን ብዬ ጠዬቅኩኝ። ይሠራል ወንድም ተባልኩኝ። ሴት ነኝ ብዬ የነበረኝን የቀደመ ሃላፊነት ጨምሬ ጻፍኩላቸው ራሴን ገልጬ፤ እና እስኪ „መሪ የሀገር ይሆናል የምትሉትን ጠቁሙኝ“ ከዚያ ቀጣዩ ጥያቄዬ ይቀጥላል ብዬ አንዲት ጥያቄ ብቻ ላኩላቸው። አልተመለሱም። ወጣቶች ናቸው እኛ ካለፍንበት ኢንትሪግ መውጣት ካልቻሉ ነገም ታማሚ ነው። ማግስትን በጣም አዘንኩለት። መርጨት ብቻ ነው ያ የሚረጨው ምን ያህል መንፈስን እንደሚበትን አይታወቅም። ሚዲያ ከፍተህ ሙግት ፈርተህ አይሆንም። አንዳንድ አገር መሪ ነን የሚሉ ሚደያዎች አስተያዬት አይቀበሉም፤ ቢቀበሉም ወዲያው ነው የሚሰርዙት መልካሙን ሳይቀር። ማዬት አይፈልጉም ሥሙን ራሱ። ነፃነት ፍለጋ እንዲህ ነው የሰው ዘር ጠልተህ። ይሄ ከሰብዕዊነት ውጪም ነው። አልተገናኘነም እኛ እና ራዕያችን ቀርቶ ሰው መሆናችን። ወቀሳ እኮ አዳኝ ነው። መዳህኒትም ነው። ፈዋሽ። ሌላውማ ያሽሟጥጣል፤ ያማል፤ ቀን ጠብቆ ቂም ያወራርዳል። ቅኖች እና ግልፆች ናቸው የሚናገሩት። የአብርሃም በጎች፤ ክብር ይቅርብን ያሉ ቅራኔ የደፈሩ፤ በራሳቸው ላይ ሙሉ ዕምነት ያላቸው፤ ልብ እንዲገጠምላቸው የማይፈቁዱ። ለራስ ነው ወቀሳ ለተወቃሹ፤ ጉድፍን ማድመጥ ጠቃሚ ነው። የሆነ ሆኖ እስቲ ሲያሸኝ የከረመው ጡሁፍ ይቋጭ።

 „አማራነት ይከበር!“
ነፃነትን ብቁና ብሩህ ህሊና እንጂ እልህም ኢጎም ንፋስም አይመራውም!
„ትግሬ እንጂ ትግራይ ተከዜን ተሻግሮ አያውቅም። ኢትዮጵያዊ ሙሁራን ይፍቱት!“
(ከጎጃሙ የአማራ ማንነት አብዮት የተወሰደ። መጨረሻ ላይ ያለውን ፎቶ ስታተልቁት ይመጣላችኋል)

የኔዎቹ መሸቢያ ጊዜን ተመኘሁ። እግዚአብሄር ይስጥልኝ - ኑሩልኝ።  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።