የባድመ ዕድምታ በሥርጉታ ዕይታ ።

                         አይዋ አደብ ብትገኝስ ምን ይመስልሃል?

                                       ከሥርጉተ ሥላሴ 07.06.2018 (ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።)
                               „ልጄ ሆይ የእግዚአብሄርን ተግሣጽ አትናቅ፣ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር።“ 
                                                   (መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፲፩)



  • ·         ጥገናዊ ለውጥ እና ፈተናው።

አደብ ሲታደሉት ብቻ የሚገኝ ተፈጥሮ ነው። መልካም ስብዕና። የሆነ ለውጥ ነገር ፈልገህ የለውጥ ፍንጮች እና አቅጣጫዎች የሚያመጣቸውን ነገሮች ፈርተህ አይሆንም። አንድ ትወስዳለህ ሌላ ትሰጣለህ። አንድ ትሰጣለህ ሌላ ትቀበላለህ። አንድ ትጥላለህ ሌላ ታነሳለህ፤ በጥገናዊ ለውጥ ውስጥ ሁሉም ተጠቃሚ ሁሉም ተጎጂ አይሆንም። ተጎጂውም ተጠቃሚውም እኩል በኩል ነው። መስዋዕትነቱም እኩል ነው። ጥገናዊ ለውጥ ቡፌ አይደለም። የምትፈልገውን የምታነሳበት፤ የማትፈልገውን የምትተውበት። ከምትፈልገውም/ ከማትፈለግውም መታደም ግድ ይላል። ዴሞክራሲ የሚባለውም እኮ በድምጽ ለተወሰነው ውሳኔ ተሸናፊው የግድ ተገዢ ይሆናል። ሳያኮርፍ ደስ ብሎት ሥልጣኔው ካለ። 

ለዚህ ደግሞ ተፈጥሯዊ አደብ ሲኖር ነው - ከተገኜ። ድምጽ ላልሰጠህበት፤ ሽንጥህን ገትርህ ለተሟገትክበት ሃሳብ ተሸናፊ ከሆነ ላሸነፈው መገዛት፤ በዛ ሃሳብ መመራት የግድ ይላል። በለውጥ ውስጥ መራራ ሃሞት በማር በጥብጦ መጠጣት ማለት ነው። ኮሶ በሽታ የያዘው ሰው „አሳንጋላ // እንቆቆ“ የሚባል ባህላዊ መዳህኒት ሲወስድ እያንገሸገሸው ነው። ግን ከሚያወርደው የኮሶ ትል ለመገላገል ነው ያ መራራ አሳንጋላ ሆነ እንቆቆ ተደፍሮ የሚወሰደው። በጊዜው ካልተወሰደ ከተገኘው ቦታ ላይ እዬተለጠፈ ያዋርዳል። ወፌ የያዘችውም የሌሊት ወፍ ምን በመሰለ ቁሊት እብድ ብላ ተሰርታ በሽተኛው ሳይነገረው ይባለ እና ሲጨርስ ይነገረዋል። ለመዳን። 

በጥገናዊ ለውጥ ውስጥ እኩል መጠቀም እኩልም መጎዳት የግድ ነው። መበላለጥ የለም በጉዳቱ። በጣም ተጠቃሚ ሆኖ የቆዬው ወደ ማህል መምጣት ግድ ይለዋል። ለዚህም ነው ጎንደር ብቻውን የ100 ሚሊዮን ህዝብ ነፃነት የሰው ግብር ለ43 ዓመት አቅርቦት መደብርነቱ ይቁም የምንለው። የቀደሙት አባቶቻችን ጀግንነታቸውን በባዕታቸው ስለሚያደርጉት መስዋዕትነቱም ሆነ ድቀቱ እኩል በኩል ነበር። በዛ ዘመን ቢያንስ ጉዳቱ እኩል ይሆናል። አንድ ቦታ ላይ ብቻ አይደለም ህዝብ የሚያልቀው፤ ኑሮው የሚፈናቀለው። መከራው ለሁሉም ጢስ ይደርሰዋል። ስለዚህም የመተዛዘን ሚዛናዊነት ይኖራል። በስተቀር ግን ባልተወለደ አንጀቱ ነው የሚሆነው። አሁን አጋዚ በንጹሃን ነፍሳትን እንደሚርሰው መከራ ማለት ነው … ሌላውም እንዲሁ። ጎንደር ቢታጨድ ምን ሲገደው፤ የራሱ ጢስ ጤና ውሎ ይደርለት እንጂ …

እርግጥ ነው ቀደም ባለው ጊዜም ቢሆን መላ የኢትዮጵያ ህዝብ እኩል በፈጸመው ተጋድሎም በመጠቀም ላይ እንደ እጅ ጣታችን መበላለጥ ቢኖረውም ግን ጉዳቱ በቀደመው ጊዜ ከ43 ዓመት በፊት በነበረው ማለቴ ነው የኢትጵውያን ተጋድሎ ተመጣጣኝ ነበር። ተጠቃሚነቱ ግን እንደ ተዛነፍ የተራራቀ ነበር። ልክ እንደ አሁን ባለግርማው የቄሮ አብዮት ዕወቅናው መንበር ላይ፤ የአማራ ተጋድሎ ደግሞ ትቢያ ላይ አቧራ ለብሶ እንደሚገኘው ማለት ነው። ሰማያዊ ፓርቲም ቁንጮ ብቸኛ ተደራዳሪው እኔ ነኝ ብሎ የነጭ አደራዳሪ ያሳኘውም ይኽው ነው። በሌለበት ተጋድሎ ላይ ተንጠልጥሎ ደረቱን ነፍቶ የተኮፈሰው። ለዚህም ነው ጎንደሮች „ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም“ የሚሉት። የደከመው፤ የሞተው፤ የተወረረው፤ የታራደው እያለ ደርብና ምድሩ ለወፈኞች ምሪቱ የሚታደለው። „ምስጋና“ እንኳን የተነፈገው የአማራ ተጋድሎማ እስከ አርበኞቹ እጣው አይደለም ይኳትነው።
  • ·         ብ መርምሪው ጹሑፍ።

„የአልጀርሱ ስምምነት ህወሀትን ዋጋ ማስከፈሉ እንደማይቀር ሲነገር ነበር (መሳይ መኮንን)“

ልብ የሚመረምር ጹሑፍ ከጋዜጠኛ መሳይ መኮነን አነበብኩኝ - ዛሬ። መነሻዬም ይሄው ነው። አንድ በእሱ መላ ክንዋኔ ምርኮኛ የሆነ ወንድም ከወደ ካናዳ አለኝ። ዛሬ ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን ይህን የጻፈውን አንብበሽዋል ወይ? እያለ በጥያቄ ያጣድፈኛል። እኔ ደግሞ ጋዜጠኛ መሳይ እና ዶር መራራ ጉዲና ጎንደር ተወልደው ያደጉ ናቸው እለዋለሁኝ። ያው አጭር ግን ቅኔ ነው የሚናገሩትም የሚጽፉትም ለማለት።

ወንድሜ ከመደወሉ በፊት ቀድሜ አንብቤ ስለምጠብቀው ይህ ምን ማለቱ ነው እስኪ አብራራልኝ እለው እና እሞግተዋለሁኝ። እሱም የፖለቲካ ሙሁር ስለሆነ። የጋዜጠኛ መሳይ መኮነን ጭብጥ ከመጨረሻ ላይ ነው የሚገኘው። ሌላው ደግሞ እንደ ማካሄጃ ከእርሱ ላይ። እኔ ብተወው እንኳን ወንድሜ ስለሚጠይቀኝ ግድ ነው አጥምጄ አንብቤ ማስታወሻ ይዤ መጠበቅ - የተለመደ። የእሱን የጹሑፍ መንፈስ ለማወቅ ረጅም ጊዜ በፖለቲካ ህይወት የቆዬ ሰው መሆን አለበት። ሚስጢረኛ እንደማለት። ላይ ሲጀምረው ፍሰቱ 100% በአዎንታዊ ቀምሞ የሰጠውን ሃሳብ መጨረሻ ላይ 1% ሳይሰጠው ነው የሚቋጨው። ጫሪ ሃሳቦችን አንስቶ እንደ ፍጥርጥራችሁ ብሎ አጋግሞ እንደ ጣደን ሽው ነው የሚለው። ደፍሮ ሲወጣ ደግሞ ታይቷል ጉሮሮውን ዘግቶ፤ የእለት ክብሬ፣ ሞገሴ ይቅርብኝ ብሎ ወልድያ ላይ የነበረውን ጭፍጨፋ አውግዞ ወጥቷል። ድርጀቱን ግንቦት 7ትንም ፊት ለፊት ወጥቶ ሞግቶታል። ይህ በታሪክ የማይረሳ መልካም አቋም ነበር።

የሆነ ሆኖ ዛሬ በጻፈው ጹሑፉ ላይ መጨረሻ ላይ እርገቱን የቋጨበትን ብቻ ላንሳየጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር ከኤርትራ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት እነመለስ ዜናዊና ሃይለማርያም ደሳለኝ በመጡበት መንገድ የሚሞክሩ ከሆነ ትርፍ የለውም። ችግሩንም የአልጀርሱን ስምምነት በመቀበል የሚፈታ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ከሆነ ተሳስተዋል። ወይም ችግሩን ለመፍታት ከልብ ቆርጠው አልተነሱም። አልያም ኤርትራን ዲፕሎማሲያዊ ቅርቃር ውስጥ ለመክተትና ጊዜያዊ ድል ለመጨበጥ በሚል ብቻ የተወሰደ እርምጃ ሊሆን ይችላልከዚህ ላይ ለኤርትራ ተቆርቋሪነቱን ቢያሳጣበትም ኤርትራ እሺ ብትል ቀጣዩስ ዕጣ የሚል ስጋትም አድሮበታል እንግዲህ እኔ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ነው የምጽፈው፤ ወደፊት ወደ ኋዋላ የሚጎትተኝ ጣጣ ምንጣጣ የለብኝም። የጋዜጠኛ መሳይ መኮነን ግን ጣምራ መንፈሶች አሉበት። 

አንደኛው ሚዲያው ኢሳት፤ ሁለተኛው ግንቦት 7 ሦስተኛው የጋዜጠኛው ሥነ - ምግባሩ፤ አራተኛው ሰብዕናው። ከዚህ አንፃር ሲታይ ከራሱ ገፊ አመክንዮ ብቻ ቆንጥሮ፤ በስሜት ተጋፋፍቶ የሚያመጣው ነው ብዬ አላስብም። በዛ ላይ ጋዜጠኛ የውስጥ አዋቂ ነው የሚባለውም እውነታዊ መሰረት ያለው አባባልም አለ።
  • ·         ምን ነበር ይሆን ምክክሩ? ልብ ጥልጥል ታደርጋለች ይህቺ ነጥብ፤ ክፉኛ ሳበችኝ።

ችግሩንም የአልጀርሱን ስምምነት በመቀበል የሚፈታ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ከሆነ ተሳስተዋል።ተረገጥ አለበት። ከዚህ በላይ ስምምነት ነበር ወይ ከዛ ኤርትራ ላይ ድርጀቱ ግንቦት 7 የመሸገበት አምክንዮ? ይህን ጥያቄ ማንሳት ግድ ይላል። ከባድመ ጉዳይ በላይ ከፍ ያለ ሌላ የተመሰጠረ አንገብጋቢ ጉዳይ ከነበረ፤ በሱዳን እና በኢትዮጵያ ጠረፍ በመተማ የነበረው 23 ዓመት መከራስ እንዴት ይታያል ነው? ሱዳን ደንበር ጥሳ እዬገባች ወገኖቻችን ጨርሳለች፤ ወያኔ ሃርነት ትግራይም ስለምን ሱዳንን ትጋፋላችሁ እያለ ያን መከረኛ ህዝብ አሰቃይቶታል።

ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሬታችንም ለሱዳን በመሸለም የነበረውን ሂደት በመቃወም ዓለምአቀፉ የደንበር ኮሜቴ ጠንከር ያለ የተጋ ተግባር ይከውን ነበር። ይህ ድጋፍ አልነበረም በግንቦት 7 በኩል። ያን ጊዜ ፖሊሲ ስሌለው ሊጠዬቅበት አይገባም ግንቦት 7 ብዬ ሞግቼ ነበር። የሽግግር መንግሥት እና ትሳኤነት እኔ ነኝ ብሎ ሲመጣ ደግሞ ፖሊሲ የሌለው ድርጅት፤ ፕሮጀክት ነኝ ተልዕኮዬን ጨርሼ እፈርሳለሁ ያለ ድርጅት የሸግግር መንግሥት ሰነድ ሊያዘጋጅ አይችልም ብዬም ሞግቻለሁኝ። 

በዚህ ሂደት ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን ምን አቋም ነበረው? አውግዞታል ወይ? የዓለም አቀፉ የደንበር ኮሜቴ ፊርማ ሲያሰባሰብ ድርጅቱ ተነጥሎ ሲቀር ምን ነበር ምልከታው? ግንቦት 7 ሥልጣን ተረክቦ ቢሆንስ ለኤርትራ መንግሥት ከአልጀርሱ ስምምነት በላይ ምን ታጮቶለት ነበር? የናቅፋን የሙት መንፈስ ወይንስ የአፍረካዊቷን የሲንጋፖር የአንበሶች አገር ድርሻን በባለቤትነት ለማስፈጸም፤ ወይንስ የፖለቲካ የበላይነት ልዕልና ባለድርሻ፤ ባለ ሙሉ መብት አራጊ ፈጣሪነት ሥልጣነ - መንበር? በዚህ መንፈስ ውስጥ ብዙ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል። ጉዳያችን በአልጀርሱ ስምምነት ብቻ ነው ወይንስ የሥነ - ልቦና የማንነት ሽግግር የሚጠዘጥዝ አመክንዮ?
  • ·         ጊዜያዊ ድል“

ጊዜያዊ ድል“ አሁን የለማ ገዱ አብይ አንባቸው መንፈስን ለተከታተለ ለጊዜያዊ ድል ነበርን እዬባከነ ያለውን? አርበኛ አድንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በኦሮምያ ብቻ ወደ 40 ሺሕ እስረኞች የተፈቱት ያን ረጅም ተደጋጋሚ የታህሳሱ ግርግር ዳግሚያ የሙግት ረጅም ጊዜ ሲፋለሙ የነበረው ለጊዜያዊ ድል ነበርን? የጠ/ ሚር ሹም ሽሩስ ጉዳይ? ሌላ ታሪካዊ አደራ የለበትንም?

ባድመ አኮ ድሮም ተሰጥታለች። ሰራዊቱ ገፍቶ ቢሄድ እኮ ድሉ የኢትጵያ እንደ ነበር መኮንኖቹ ተናግረውታል። በዚህ ውሳኔ በዲፕሎማሲ ዘርፍ የኢትዮጵያ መንግሥት ያተርፍበታል፤ ግን ጋዜጠኛ መሳይ እንዳሰበው  „የኤርትራን መንግሥት ቅርቃር ውስጥ ለማስገባት“ ሳይሆን ቀጠናውን ወደ ሰላም በማምጣት የጠነከረ አካባቢያዊ ሰላምን አምጦ ለማስወለድ ነው።

ቀላል ውሳኔ አይደለም። እጅግ ደፋር ውሳኔ ነው ለዛውም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሰናዶው ቀድሞ ተጠናቋል ማለት ነው ለእኔ የሚሰጠኝ ግብረ ምላሽ። ውሳኔው በሌላ በኩል በፖለቲካም አትርፏል። ተፎካካሪዎቹ ኤርትራ የሚገኙትን አቅም ተፈታትኗል። ምክንያቱም የጀርባ አጥንት የኤርትራ መንግሥት እንደ መሆኑ መጠን ኤርትራን ከሁለት መንፈሷን ከፍሎ ማህል መንገድ ላይ ገትሯታል። አንዱን እንድትመርጥ። ለተፎካካሪዎችም ተጽዖኖ በዝማታው ውስጥ አሳድሯል። ሲያልቅ አያምር ከመሆን ለመዳን አሁኑኑ የሚል መልዕክት ልኳል። በተጠያቂነት እረገድ አዲሱ የጠ/ ሚር አብይ ካቢኔ ተጠያቂ የሚያደርገው ቆራጣ ምንም ነገር የለውም። ይህን ድፍን ዓለም ያውቀዋል። 

ስለምንይሄ ፎቶ ይመልሰዋል። ይህ አውሬያዊ መንፈስ ፈቅዶ እና ወዶ የሰጠው፤ የሸጠው፤ የለወጠው፤ የቀረደደው፤ ያቃጠለው ማንነት ነው እያመረቀዘ መፍትሄ አልባ  የኢትዮጵያን ልጆች ሲውጥ የኖረው። ጥላቻን እዬመረተ በዬዘመኑ ሲያናክሰን የባጀው። በዚህ ሰው ደራጎናዊ ሌጋሲ ነው ኢትዮጵያ መለመላውን ቀርታ በልጆቿ ሰቀቀን መሽቶ የሚነጋው። ልጆቿ ለዕለት ከፍን አጥተው መንገድ ላይ እንኳን ለማደር ስጋት እና ሰቀቀን የተሸለሙት። አንድ ወጥ ሃሳብ አሰባሳቢ ጠፍቶ ትውልድ ሲባክን የኖረው። በተነን።
  • ·         ስለ የኤርትራ መንግሥት።

የኤርትራ መንግሥት ለጽድቅ አይደለም ድህነቱን ተሸክሞ ሺህ ልጆቹን አጥግቦ ለማደር ሳይችል ባህር ውስጥ ሰምጠው እዬቀሩ፤ ግን  የኢትዮጰያን የተቃዋሚ ድርጅቶችን በጀት መድቦ ሲደግፍ የኖረው። በበዛ ተስፋ መዋለ ንዋዩን አፍሷል። ያለችውን ጥሪቱን ሁሉ እዬሟጠጠ የሚችለውን ያህል ተግቷል። ለወደፊትም በፈለገው ስምምነት ይደራደር የኤርትራ መንግሥት እንደ ኬንያ መንግሥት ልብ ጣል ተደርጎ ትራስን ከፍ ተድርጎ የሚተኛለት አይደለም። በፍጹም። በቁጫኑ ውስጥ ያለውን እልህ የሚያወራርድበትን አጋጣሚ ሁሉ ከመጠቀም አያንቀላፋም አይተኛም። 

በእነ አጅሬ ቤት ዘው ተብሎ ተገብቶ በቃችሁን/ ጨዋታው ፈረሰ ዳቦው ተቆረስ የሚያስኬድ መንገድ አይደለም። የረጅም ጊዜ የቆዬ ወደፊትም የሚዘልቅ ያልተመጣጠነ የበላይነት መንፈስ ሲንጠው የኖረ ነው፤ ወደፊትም ቀጣይ ነው። የኤርትራ መንግሥት እንደ ማንኛውም መንግሥት ጥቅሙን ተጻሮ ይቆማል ተብሎ አይታሰብም - እንደ እኔ። ከዚህ ያለፈ ፍላጎቱን ለመፈጸም ሆነ ለማስፈጸም እንደ መደራደሪያነት የሚያቀርባቸው ሌላ መደራደሪያዎች ሊኖሩት ይችላሉ። መከላከያ ሠራዊቱ የአቶ ሞላ አስገዶም ትንፋሽ፤ ሚዲያው ግራ ቀኙ። ሲሶ መንግሥትነት … የናቅፋ ህልም ወዘተ … ቀድሞ ከደገፋቸው ተፎከካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የነበሩ የጓሮ ፖለቲካዊ ስምምነቶች ፍንጭ የሚወጡት ያን ጊዜ ነው … ችግሩንም የአልጀርሱን ስምምነት በመቀበል የሚፈታ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ከሆነ ተሳስተዋል።የዚህች ጥያቄ መልስ ያን ጊዜ ትፈርጣለች።
  • ·         ያልተወለደ የአጥንት ጽንስ ህውከት።

የሄሮድስ መለስ ሌጋሲ የግንቦት 20 ባለድሎች የሙት መንፈስ  „ተገንጠሉልን፤ ወደብ አያስፈልገነም፤ ክብር እና ልዑላዊነት ከኤርትራ ፍቅር በላይ አያስፈልገንም፤ የፈለጋችሁትን ያህል አቅማችሁ እስከ ፈቀደ ድረስ የእኔ ለምትሉት ባድማ ሁሉ ፊሪማዬን ደስ ብሎኝ እልል እያልኩ እስጣለሁ“ በማለት የፈቀደው  የአውሬው መንፈስ የሄሮድስ መለስ ዜናዊ ሌጋሲ ነው። ከዚህ በኋዋላ ደግሞ ሌላ የእንግዲህ ልጅ አመረተ። ያ ሁሉ ውድመት ተከተለ - በጦርነት የአማራ እና የኦሮሞ ልጅ በብዛት እዬሄደ ተማገደ። መለያዬት ያለ የነበረ ሲሆን የእኛው ግን ለጠላትም አይስጥ የሚያሰኝ ነበር። ከጦርነቱ ማግሥት የነበረው ዓለምአቀፍ ውል ደግሞ ተንጠልጥሎ መቋጠሪያ ሳይኖረው፤ አሳካለሁ ያለውን ሁሉ እያደራጀ እርስ በርስ በሃሳብም፤ በመንፈስም፤ በነፍስም ሲያዋጋ ኖሯል የኤርትራ መንግሥትም በበኩሉ። የሚያልቀው የድሃ ልጅ ነው ለዛውም ያ መከረኛ አማራ። ባድማውም የሚቃጠለው ያው የአማራ። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ቁንጫን የሚወራረደውም ያው አማራ። እስከ አሁኗ ዕለትም አላባራም።
 
የመንፈስ፤ የሥነ - ልቦና መከፋፈል፤ የውስጥ ሰላም አለመረጋጋት እና የማስፈራሪያ ቆመጥ ተደርጎ የተወሰደው ጉድ ነበር በሁለቱም ወገን በወያኔም በሻብያም - ባድመ እና ጦሱ። ስምምነቱን በመርኽ ደረጃ ተቀብሎ ግን ህዝብ በወለሌ ገባታ ላይ አስቀምጦ በጦርነት ስጋት መናጥ ነው ተልዕኮው የሄሮድስ መለስ ደመነፍስ ሌጋሲ። ወይ ተገፍቶ ቅቤ አይወጣው፤ ወይ ረግቶ አይበላ ወገሜታዊ ኑሮ። ይህ ትልቅ የሥነ - ልቦና ጦርነት ቅርስ ነው የግንቦቶች 20¡ ስላቤ። የመከራ ስልባቦት። ሰዉ ሁልጊዜም ባድሜ በልቦናው ውስጥ የማይወለድ ጽንስ አጥንት ሆኖ ተሸክሞት እንዲኖር ማድረግ። የአጥንት ጽንሱ በተገላበጠ ቁጥር፤ በተግረጨረጨ ቁጥር፤ ጸባዬ በተቀዬር ቁጥር ስክነት ጠፍቶ፤ ስጋት ነግሶ ውስጡን ባር ባር እያለው እንዲኖር መወሰን። የሃሳብ ጉግስ መራገጫ። 

ሁልጊዜ የፖለቲካ ማስፈራሪያ ለግራ ቀኙ። በማህል ሁለት የጫካ አውሬዎች በሚያደርጉት የርግጫ ጨዋታ አላዛሯ ኢትዮጵያ እስከ ጽንሷ መረጋገጥ፤ በድንጋጤ ውስጥ መምከነ። ይህ ህሊናቸውን ፍሰሃ ሰጥቶ ውስጣቸውን የሚያፍነሸንሽው ነበር ለሄሮድስ መለስ ዜናዊ ሆነ ለአቻቸው። እንዲወለድ ያልተፈቀደለት ጽንስ ግን ከማህጸን ሆኖ የሚነስት፤ እርፍት የሚነሳ፤ ጤናን የሚያውክ ሃኪምም፤ ገላጋይም የሌለው፤ ፈዋሽ መዳህኒት ያልተገኘለት የመንፈስ የጋለ የፋመ የስቃይ ብረት ምጣድ፤ ወይንም ረመጣዊ ፋስ።

የተፈቀደለትን መብት ቀርቅሮ ወይ ይሆናል፤ ወይ አይሆንም ሳይሉ ባለዬለት ማቅ ውስጥ መስማቀቅ። በዚህም ሌላ መዋለ ንዋይ፤ ሌላ የቁስ ፍሰት፤ ሌላ የሰው ሃይል ብክነት። የመንፈስ መግደያ የፖለቲካ መጫወቻ ጥቁር ሜዳ የኢትጵያን ህዝብ አሻንጉሊት ያደረጉ መሪ ቢኖሩ ሄሮድ መለስ ዜናዊ ብቻ ናቸው። በዓለም ታሪክም አገርን ባህር በር ወደብ አልባ አድርጎ በማስገንጠል፤ ለሱዳን ተጨማሪ መሬት ቆርሶ በመስጠት ያልተቋጨ መከራ ከትወልድ እስከ ትውልድ እንዲቀጥል ያደረጉ የክፉዎች እሸኽ ቢኖሩ ሄሮድስ መለስ ዜናዊ ናቸው። ምን አለ ሞተው እንኳን ቢተውን? ጃርት! የጀርት ጉባኤ ርደት ይሄው ነውእያገረሸ የሚነስት ቁስሉ እያነፈረቀ የሚቦጫጭቅ - የሚያቦጫጭቅም። በዚህ ጦስ ደግሞ ጎንደር ታረሰ። የጎንደር ልጅ መከራውን ተሸከመ። የጎንደር የተቃጣው መከራም ጎጃምንም አሳጨደ። የልዑላዊቷን ኤርትራ በትረ ሥልጣን ለማስመለስ ትግራይ ላይ ሳይሆና አማራ ላይ ነዶ አመዱ አማራ ማህጸን እናት ውስጥ አረገ።
  • ·         የነፃነት ትግል እና መንፈሱ።

በነፃነት ትግል ውስጥ አውራው ጉዳይ የህግ የበላይነት ይኑር ነው። ሺዎች ደማቸውን የገበሩበት። የህግ የበላይነት ሲባልም የአንድ አገር ብሄራዊ ህግ እንዳላት ሁሉ ከአህጉራት ጋር፤ ከግሎባሉ ዓለም ጋርም ባላት ማናቸውም ግንኙነቶች ሁሉ የህግ የበላይነትን ማክበር ማስከበር አለባት ነው የትግሎ አንኳር የነበረው። ኢትዮጵያኢትዮጵያ“ ላይ እንደምትጠቀጥቀው ህግ መንግሥቷ፤ የወንጀለኛ መቅጫ እና ሥርዓቱ፤ የፍትብሄር ህግ እና ሥርዓቱ እዚህ ሲዊዝ ያለው ኢንባሲዋ ቅንጣት ታክል መተላለፍ አይችልም። ድፍረቱ አለኝ ቢል 24 ሰዓት ውስጥ እንደ ወንጀሉ ቅሌቱን አሸክሞ የሲዊዝ መንግሥት ህጉን ለመፈጸም ይገደዳል። መብት ቢኖራት እማ ጀግና / አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ ይህን ጊዜ ሁለመናው ለቀረመት ውሎ ነበር። ኢትዮጵያ ላይ እንደሚጠቀጠቀው ህግ እዚህ መብቱ አልተገኘም። ፎቶውን እንኳን የማግኘት መብት የለውም የወያኔው መንግሥት። ያለበትን ሁኔታ የማወቅ መብት እንኳን የሰማይ ያህል የራቀ ነው።

ኢትዮጵያ ላይ ግን ስለምን የህግ ባለሙያዎች በየዓመቱ ይመረቃሉ እስኪያሰኝ ድረስ ህግ የሌላት፤ ህግ የማይዳኘት አገር ሆና 27 ዓመት ሙሉ ኖራለች። ዓለም አቀፍ ህጉማ አንቀጽ በአንቀጽ አንድ ዓመት ላይ እኔ ሠርቼው ነበር። በባዶ የተባዛ ስለነበር። አሁን የጠ/ ሚር ለውጥ አለ። / ሚሩ የመርህ ሰው ናቸው ይሄን በቀደመው ንግግራቸው ሁሉ ቢጎጎ ይገኛል። ስለሆነም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሰላም አብሮ የመኖር ፖሊሲ ለማስፈጸም ከጎረቤቶቻቸው ጋር መነጋገር፤ የዲፕሎማሲያዊ ተግባር መጀመር ግድ አላቸው። ይህን ለመከወን፤ ሱዳን፤ ጁቡቲም፤ ኬንያም፤ ሳውዲም፤ የተባባሩት አረብ ኢምሬቶችን በሥፍራው ተገኝተው የተገባውን ተልዕኮ ፈጸሙ። አገር ውስጥም አንቦ፤ መቀሌ፤ ጎንደር፤ ባህርዳር፤ አሶሳ፤ ባሌ፤ ደንቢደሎ፤ አዋሳ፤ ጋንቤላ፤ በቤተ መንግሥታቸው፤ በሚሊዬነም አዳራሽም ተነቀሳቅሰው ከሚመሩት ህዝብ ጋር ተገናኙ ተወያዩ። 

ከቀረበላቸው ጉዳይ ውስጥ ከህዝብ የደንበር ጉዳይ ነው፤ ጋንቤላ ላይ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ፤ ትግራይ ላይ  የኤርትራ ጉዳይ፤ አማራ፤ አሶሳ ላይ የሱዳን ጉዳይ። ማዳመጥ ብቻውን መፍትሄ አይደለም። ያዳመጡትን ወደ ተግባር ለመወለወጥ የመፍትሄ እርምጃ ያስፈልጋል። የመተማውን ጉዳይ ከሱዳኑ መሪ ጋር እንደሚነጋገሩ ቢያንስ የሁለቱ አገር ዜጎች በሰላም የሚዘዋወሩበትን ሁኔታ የማመቻችት ጥረት እንደሚያደርጉ እዛው ላይ ቃል ገቡ። የጋንቤላውን መዝግበው ያዙ። ደቡብ ሱዳን ያረጋም ስለሆነ በሱዳን ቆይታቸው በነበራቸው የሁለትዮሽ ግንኙት ወደ ተሻለ መረጋጋት የሚያመራበትን ሁኔታ ፍንጭ አዳምጫለሁኝ። ከግብጽ ጋር የነበረው ውጥረትም ረገብ ብሏል። ይህን ጊዜ ክፈተት ቢኖር ለማስጮኽ አዳኞች በሆን ነበርን። ለማብጠልጠል፤ ለማቃለል። ተደፍረው የማያውቁ ስምምነቶች ሁሉ በሁለቱ አገሮች ተደርገዋል። አዲስ አበባ ላይ።

ሌላው የኤርትራ ጉዳይ ነው በቅርበት ያለው። ክፍት ሆኖ ያለው ይሄው መስመር ነው። ይህም በቀላሉ ቃልም የሚገባበትም፤ ማስታወሻ በመያዝ ብቻ የሚፈታ አይደለም። ጉዳዩ በዓለምአፍ ደረጃ የተያዘ ነው። በሙያቸው ሰላም እና ደህንነት ጨምረው ያጠኑ ናቸው። „ሰላም“ የሁሉም መሰረት ስለመሆኑ ዕውቀታዊ መሠረት አላቸው። ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ከተፎካካሪዎችም ጨምሮ ብቸኛው በባድመ ጦርነት የተሳተፉ መሪ ናቸው። እልቂቱን ያውቁታል። አስተርጓሚ አያስፈልጋቸውም። በሩዋንዳ ላይ የነበራቸው ሌላው ዝቀሽ የተመክሮ ሰብላቸው ነው ለጠ/ ሚር አብይ አህመድ። ዓለም አቀፍ ህግን በዓለም አቀፍ ግዳጅ በመወጣት ረገድ ያለውን ህይወት ኑረውበታል። ስለዚህ ከመሰሩት መፍትሄ ለመስጠት መርህን ማስከበር ይጠይቅ ነበር።

 የኢትጵያ እና የኤርትራ ጉዳይ ዓለም አቅፍ ውሳኔ መርህ ፊርማ ያለበት ነው። ህግ ይከበር ብለን ስንጮኽ እኮ ህግ በራሳችን ላይም ተፈጻሚ ይሁን ብሎ መፍቀድ ነው። አይደለም ወይ? ነው። ለህግ የበላይነት የሚታገል ሰው ባለ 30 አንቀጹ የ1948 የታህሳስ 10 የተባባሩት መንግሥታትን ውሳኔም፤ ተጨማሪ ዓለምአቀፍ ህግጋትም  በእኔ ላይ እንዲፈጸሙ መውደድ እና መፍቀድ ግድ ይላል። ስለሆነም የአልጀርሱን ስምምነት ተንጠልጥሎ፤ ደም ቋጥሮ፤ ቂም አብቅሎ፤ የጥላቻ ተባይ አፍርቶ ግን ባሊህ ባይ አጥቶ ዘሃ ያደረበትን ውሳኔ አቧራውን አራግፈው ስምምነቱን ባለመብት ለማድረግ ጣሩ። ድርጅታቸው ኢህዴግ በመርህ ደረጃ የተቀበለውን ውሳኔ፤ በዘመነ አብይ ወደ ተግባር በሚያስችል አቅሙ ዕውቅና አሰጡት። የሆነው ይሄው ነው ኤርትራ ላይ የመሸገ ማናቸውም የፖለቲካ ድርጅት ከዚህ ውሳኔ ስምምነት በመለስ ብትን አፈር ኤርትራ ላይ መቆሚያ አያገኝም። ሽራፊ መንፈስ ከፕ/ አሳያስ አፈወርቂ በችሮታ አያገኝም። ቁልጭ ያለው ሃቅ ይሄ ነው። በጠ/ ሚር አብይ አህመድ ሲፈጸም አብሶ እዛ ኤርትራ ላይ የመሸገ ሁሉ ይህ ውሳኔው ሊመረው ወይንም ሊያንግሸግሽው አይገባም። ከህግ በላይ ማንም የለም እና።

ማንም ዜጋ ከአገሩ፤ ማንም የዓለም ዜጋ ከዓለም ህግ፤ ማንም ስደተኛ በስደት ከሚኖርበት አገር መንግሥት እና ህግ በላይ  እና ውሳኔ በታች እንጂ በላይ ሊሆን አይችልም። የሚያሳድሩን ዜጎች እራሳቸው ከአገራቸው ህግ በታች እንጂ በላይ አይደሉም። ዝቅ ብለው ነው አክብረው የሚያድሩት። በዚህ ትዕቢቱ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ተንጠልጥሎ ጥላቻን፤ ጭቅጭቅን፤ ንትርክን በቦንዳ ሲያመርት ኖሯል። ዛሬ ግን ሌላ ቀን ነው እዛ ኤርትራ የመሸጉትም ቢሆንም እንደ ጋዜጠኛ መሳይ መኮነን ጹሑፍ እማ ከዚህም ያለፈ የተመሰጠረ ነገር ሊኖር እንደሚችል ፍንጭ እዬሰጠን ነው ኤርትራ እንደማትቀበለው ሌላ ተጨማሪ የመደራደሪያ ጉዳይ አላት ነው የሚለን ጹሑፉ
  • ·         ሂደት።

አንዲት ቀላል ምሳሌ ላንሳ … አንዲት ሙጎጎ ጥዳ እንጀራ እዬጋገረች ያለች እናት ልጇ ቢያለቅስባት አጠገቧ ያለችው ሴት ቀጥላ እዬጋገረች እንድትጠብቅ ታደርጋለች። እንጀራው በደመቀው ሁኔታ ሳይጓደል ይጋገራል፤ ሊጡም ሳያልፍበት፤ ቀጣይም ጎረቤት ካለች ትቀጥላለች ይህ ማለት ትውልዱ ዓለም ዓቀፍ ህግን በማከበር አላስፈላጊ ከሆነ ግጭት እንዲታደግም ይረዳዋል። በሂደትም ቂም በቅሎበት ያለው የጥላቻ አረማዊ አረማሞ ውርስ በተሻላ ሁኔታ መስመር ለማስያዝ ለቀጣዩ አሸናፊ ፓርቲ መስመሩ ይጠረግለታል። የቤት ሥራው ተሰራለት ማለት ነው። ሥራ ይቀልለታል። መከራውን ተሸካሚው ይህ ጥድፊያ ላይ ያለው ካቢኔ ነው። ግን ለነገ የሰላም ጉዞ አዲስ መንፈስ እዬፈጠረ ነውሌሎች ያነፋረቁትን እንዳነፋረቁት ሳይተው … ደፍሮ ገብቶበታል። 
  • ·         የተፎካካሪዎችን አቅም መፈተሽ።

ሌላው ይህ ውሳኔ የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን አቅም በቅጡ ፈትሿል። አጥንቶታል። የአቅማቸውን መሰረት አድርጎ ጎድቦ የያዘውን አምክንዮ በእጅጉ ተዳፍሮታል። ስለዚህም እትጌ ኤርትራ ከእንግዲህ ሰማይ ላይ መና ለማግኘት እስከ ዛሬ ካወጣችው በጀት በላይ መድባ መቀጠል፤ ወይንም ምንም ወጪ ሳታወጣ ያገኘችውን የሰማይ በረከት ተንበርክካ መዛቅ ለዛውም ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ምርጫው የባለቤቱ የአትራፊው ነው። በዚህ ሂደት እትጌ ኤርትራ እንደ አሻት የምትወላዳበት የመንፈስ ፖለቲከዊ መናህሬያ እንደሌለ ቀደም ብዬ ጽፌያለሁኝ። ኦህዴድ እስከ ዛሬ ባለው አቅሙ ከኤርትራ መንግሥት ጥገኛ የሚያደርገው ፍርፋሪ የውለታ ቅርጥምጣሚ ነገር የለም። ራሱን የቻለ፤ በራሱ ውስጥ የበቀለ ድርጅት ነው። የማያልቅ ሃሳብ ያለው አንቱ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ነው፤ ለዚህም ነው እኔ ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን ዕዕምሮም አለው ኦህዴድ የምለው። ይህ ማለትም ድርብ የፖለቲካ ጨዋታ የሚጫወቱ ራስከጂዎች ይጠፋሉ ማለት ግን አይደለም። ይኖራሉ አራጆች ከዬትኛውም ማህበረሰብ እንደ እስስት በዬዘመኑ የሃይማኖት አመጽ ሲነሳ ያነን ቀለም፤ ሌላ መንፈስ ላቅ ብሎ ሲመጣም የሚለዋወጡ የምስል አክሮባቲስቶች።
  • ·         ብሄራዊ ደህንነትን በማስጠበቅ የአቅም መመጣጠን።

አላዛሯ ኢትዮጵያ እስከ አሁን ይህን መሰል ዕድል አግኝታ አታውቅም። በደህንነት ሙያ ላይ መጠነ ሰፊ ተመክሮ ያላቸው መሪዎች ወደፊት መጥተው አያውቁም በታሪኳ። አሁን ግን በሲቢሉም በወታደራዊም ሙሉ አቅም ከሙሉ ሰብዕና ጋር ያላቸው ልጆች አሏት። ኦቦ ለማ መግርሳ እና ዶር አብይ አህመድ። ስለዚህ ድርድሩ የበታች እና የበላይ አይደለም። በእኩል መስመር ላይ ልክን አውቆ የሚሆን ነው የሚሆነው። ይህ ሌላው የኢትጵያ ወርቃማ ዘመኔ የምትለው ታላቁ ሽልማታዊ አምክንዮ ነው። አሁን ኢትዮጵያ በብሄራዊ ደህንነቷ ለዛውም 21ኛው ምዕተ ዓመት የዲጅታል ዘመን የሚመጥን ሥልጡን፤ ፈጣን ጭንቅላት ያለው፤ ለአፍሪካም የሚበቃ ሙሉ አቅም እና ክህሎት አላት - መዳፏ ላይ። ስለዚህ የፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሚያደረገው ድርድር በአንድ እጅ ብቻ አይደለም ጭብጨባው። በሙሉ እጅም ነው። 

እሳቸው ያላቸውን በደህንነት ተመክሮ ሆነ ክህሎት ያህል ያውም ዕድሜ የሚሰጠው ተጨማሪ የማድረግ አቅም ጋር ሲነፃፀር ኢትዮጵያ የተሻለ ዕድል አላት። ብሄራዊ ደህንነቷን አጽንታ የማስቀጠል ልበሙሉነት አላት። ልብንም የማያስደፍር። ብዙ ጊዜ የደህንነት ሰዎች ፖፕሊስቶችም ናቸው። የትግራዮች የደህንነት አበጋዞች እኮ የሚያምሱን ትግራዊነት በሽታ ስላለባቸው ነው። የዚህ ሁሉ መከራ ምንጩም ይሄው ነው። አብልጦ አግንኖ ትግራይን ማውጣት፤ ከፍ ማድረግ ይህ ነበር ጉዞው አሁን ተመስገን ነው። ሌላው ቀርቶ የሰሞኑ የኢህአዴግ ስብሰባ የወያኔ ሃርነት የዝገት ክብብ አልነበረም። ይህን ልብ ያለውም የለም።

ነገ ደግሞ እትጌ ትግራይ በልኳ የተመጠነ ውክልና ይኖራታል። ከአማራ እና ከኦሮሞ ጋር እኩል በ9 ቁጥር ፊጢጥ ማለት ይቀራል። ህግ ይምራ ከተባለ ይሄ ሁሉ መስተካከል አለበት። የዓለም አቀፉን የአልጀርሱን ስምምነት ለማክበር የደፈረች አገር የፓርቲ የውክልና ህጉን በመፈጸም እና በማሳፈጸም እማ ቀላሉ ይሁንላታል ተብሎ ይገመታል። ያ መያዣ መገረዣው የጠፋው ሙርቅርቅ የስብሰባ፤ ላንቁሳዊ ልብ መውለቅ የትርምስምስ ጨቀጨቅማ ጉዞም ልክኑ ይይዛል። አክብሮቱንም ያገኛል። እትጌ ትግራይም በበላይነት የምትታማበት ዘመን መስመር ይይዝላታል። ከ4% ህዝብ 9 ሥ/አ/ ኮሜቴ አባላት 27 ዓመት ተቀለደ፤ ጡረተኞች ሲጨመሩ እማ ከእኩል ለኩል በላይ ነው። ራሳቸውን የሸጡት ሲታከሉ ደግሞ ያው አባ ጠቅልል። ማለጋጥ ነበር።

ሌላው ቁም ነገር ግን ጠ/ ሚሩ ሲሞገሱ የሳቸው ተግባር፤ ወቀሳ ሲመጣ ደግሞ የወያኔ ሃርነት ሴራ አድርጎ ማቅረቡ አልተመቸኝም። እስከ አሁን ከወሰዷቸው ወሳኝ ደፋር እርምጃዎች ሳይ በወያኔ ልብ የተገጠመላቸው መሪ አይደሉም። የሃሳብ ተጠዋሪም አይደሉም። ቀድሞውንም እኔ ስል የነበረው የራሱ የማያልቅ፤ የማይነጥፍ ፏፏቴ ሃሳብ ያለው መንፈስ ነበር እያልኩ ስጽፍ የባጀሁት። በራሳቸው እምነት እና ዝንባሌ ግን በድምጽ የሚወሰነው፤ እያስወሰኑ እንደሚፈጽሙ ነው የማስበው። መግለጫዎችንም ሌሎች ጻፉላቸው የሚለውን አልስማማበትም። ስለምን? የቀደሙት ንግግራቸው ጋር ተወራራሽ መንፈሶች ብቻ ሳይሆን ቃሎችም ሳይለወጡ አሉበት። ያው እኔ የዕንቁ ቃላት እና የአገላለጽ ዘይቤ ምርኮኛ ስለሆንኩኝ። ስለዚህ ይህ ሁለት አውራ ውሳኔ የሳቸው መንፈስ የፈቀደው ነው ብዬ ነው እማምነው። ቢሮክራሲ ላይ፤ ሚደያ ላይ፤ ጸጥታ አስከባሪው ላይ ግን የታቀዱ ሴራዎች፤ ሸሮች አሉ። ቀጣይ ጥቃቶችም በተለያዬ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል ብዬ አስባለሁኝ። የወያኔ ሃርነት ትግራይ በራሱ መደበኛ የሴራ ተቋም ነውና።
  • ·         ጦርነት አመድ ማሳፈስ ነው አውሌያው።

ዛሬ ጦርነትን ማንም የዓለም ህዝብ ሆነ መንግሥታት አያበረታቱትም። አንድ የጭልጋ ገበሬ21ኛው / ዘመን እንኳንስ እኛ ወፎች ጦርነት አይፈልጉም፤ ስለዚህም ሰላማዊ ኑሮ ነው የምንፈልገው። ቅማንት አማራ እያለ የሚያዋጋን ብአዴን ነው፤ ተውን አርሰን እንብላበት“ ነበር ያለው። ከጦርነት የሚታፈሰው አመድ ብቻ ነው። ንብረቱ ቀርቶ ሰው የሰለጠነው ሰው፤ የሰው ሰው ነው የሚጠፋበት። ተኑሮበታል። አልጠቀመንም ባድመ ላይ ቀጣይ ጦርነት ቢከፍት እንደ አለፈው ጊዜ ሺሕ የአማራ ልጅ እና የኦሮሞ ልጅ ሄዶ ይዋጋል ተብሎ አይታሰብም። ሁለቱም ማህበረሰብ ሞተው አይተውታል። በተለዬ የስሜን ሰው በተለይም አማራ መሮታል። ወይፈኖች ይራገጣሉ ከሥር ያለው አማራ ይደቃል። 

የሁሉንም ክርኒ የሚያስተናግደው ለዛውም በጥርስ ተይዞ የአማራ መሬት እና ህዝብ ነው። ስለዚህ ሰላም የሚናፍቅ ህዝብ ወደ ሰላም የሚያደረገውን ጉዞ በጥሞና ማድመጥ ይጠይቃል። አደብ ገዝቶ ሁኔታውን፤ ቀጣዩን አፈጻጸም መከታተል አለበት፤ ጦርነት የማይናፈቀውም ሆነ በጦርነት አስተዋፆ ለማድረግ የማይፈቅደው ማህበረሰብ። በተለይ ዋቢ አልባ ለዬዘመኑ የሰው ቁርጥ አቅራቢውም ምሽግ እና አንጋቹ አማራ ጠንቃቃ መሆን አለበት።  

ትግራይ ላይ እኮ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ታይቶ አይታወቅም። በ27 ዓመቱ በህመሙ፣ በመከራው አብሮ አልተጋራም። ያው እኛ ነን ስለነገ ልጆቻቸውም እምንጨነቀው። አንድ ኢትዮጵያዊ ውስጥ የኖረ ህዝብ ሥነ - ልቦናዊ ጉዳቱ ቀላል ስለማይሆን። ይሄ እንዴት ይያዛል በተለመደው የጦር ምርኮኞች እንደተስተናገዱት፤ ወይንስ ልክ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ወልቃይት እና ጠገዴ ወሮ እንደሚድጠው፤ በጉድጓድ ውስጥ ተቀብረው ፍዳቸውን እንዳዩት ወይንስ በዓለም አቀፍ የሰባዕዊ መብት ህግጋት? ሃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ስላለን በአግባቡ ይከወናል ብዬ አስባለሁኝ። 

የመሬቱ ብቻ ሳይሆን በዛ ውስጥ የሚኖሩ ነፍሶች ምን እና ምን ይሆናሉ ነው የእኔ ጉዳይ? ዛሬ ኢትጵያዊ ነን ሊሉ ይቻላሉ እነ ተጋሩ ግን ሆነው አልነበሩም። ሁሉ ደም ሲፈስ፤ ሁሉ ህዝብ ሲፈናቀል፤ ሁሉ በታቀደ ሁኔታ ህዝብ ሲጨፈጨፍ በኤልኮፕተር ታግዞ ሁሉ ምናቸው አልነበረም። እዛው ባድማቸው ላይ በመቀሌ ዩንቨርስቲ፤ በአክሱም ዩነቨርስቲ፤ በአዲግራት ዩንቨርስቲ አንድ ለነፍሱ ያደረ ካህን፤ አንዲት የማህጸን ባላደራ እናት እንኳን አልተገኘም። ግን እኛ አሁንም ስለ እነሱ ይጨንቀናል። የሥነ - ልቦና ጉዳይ ስለሆነ። ሰው የመሆን ጉዳይ ስለሆነ።
  • ·         ያለምንም ቅደመ ሁኔታ

ለእኔ እጅግ የከበደኝ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ውሳኔውን ተግባራዊ አደርጋለሁ ሲል የጠ/ ሚር አብይ ካቢኔ ጉልበታም የሆነ ከሰው በላይ ምንም ነገር ስሌለ ሁሉ 70 80 ሺህ ለጠፋው፤ ለተማገደው ህዝብ፤ ለተማረከው ወታደር፤ አካሉ ለጎደለበት እና አስታዋሽ ላጣው፤ ለጠፋው የሥነ - ልቦና ቁስለት፤ ጥቁር ለለበሰው የእናት አንጀት፤ ከጦርነቱ በኋላም ከዛ አቧራ ለብሶ ሲባዘን ለነበረ ምስኪን የሚመክት ይቅርታ እና የህሊና ካሳ ላይ ምንም አለመባሉ እጅግ ነው ያሳዘነኝ። እኔ የድምጽ አልባዎቹ እናቶች ጉዳይ ውስጤ ስለሆነ። በሌላ በኩል እዛ ባድመን ሲጠብቁ ጉልበታቸውን ለታላቋ ትግራይ ታሪካዊ የልማት ልዕልና ሲበዘብዙ ለኖሩት የሠራዊቱ አባሎች ራሱ የእናመሰግናለን ግርማ በሚመለከት አንድም ነገር አልተባለም። ያው እናት አለች። ለውትድርና ሄዶ ሲቆፈር የሚወል ሎሌ አምራች … የህሊና ጉዳት ካሳን በሚመለከት ባለቤት ሊኖረው ይገባል፤ የህግ መሠረት ያለው ቋሚ እና ተከታታይ ተግባርም። 
  • ·         ህዝብ ድምጽ መስጠት ነበረበትን?

ህዝብ ድምጽ መስጠት ነበረበት የሚል አስተያዬት አንብቤያለሁኝ፤ ኤርትራ ስትገነጠል ማን እንደ ተጠዬቀው? የአልጀርሱ ስምምነት ጊዜ ማን ተከብሮ እንደ ተጠዬቀው? አንሄድም፤ አንገኝም፤ ቢገኙም አንፈርምም ማለት ይችሉ ነበር እኮ አነ ግንቦቶች 20 ዎች ስለጀግኖቻቸው አይደለም ጥዋትና ማታ እሚያዜሙት፤ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ በዜግነቱ መብት ኑሮት ያውቃልን? መቼ? የት ላይ? ስለዚህ ይህን የግንቦት 20 አምላኪዎች ራሱን ግንቦት 20 እና የሄሮድ መለስን አውሬያዊ ሌጋሲ ጠይቁ ነው መልሱ።
  • ·         መገንጠል እና ጦሱ።

ኦንግ ተሳክቶለት ቢሆን ምኞቱም ይሄው ነበር። እና ኦንግን ብለህ አንጥፈህ ጎዝጉዘህ ተቀብለህ ሻብያን እገፋለሁኝ ማለትም ከባድ ነው። ሁለቱም ባያምኑበትም ከኢትዮጵያ ማህጸን ውስጥ የበቀሉ ናቸው። የኢትዮጵያን ጡት አነሰም በዛም የጠቡ ናቸው። እነሱ ካህዲዎች ቢሆኑም። ለመርህ ሰው ብስል ከቀሊል አድርጎ ለማዬትም የሚፈትኑ ጉዳዮች አሉበት። በግማሽም ኢትዮጵያዊ በግማሽም ኤርትራዊ የሆኑ አሉ። ታሪክ በሚጠይቃቸው መሠረታዊ የአገር ጥፋት ተጠያቂ የማይሆን አንድም የፖለቲካ ድርጅት የለም ከቅርብ ጊዜዎቹ በስተቀር። ሁሉም በአነሰውም በበዛውም የአገር እና የህዝብ ጉዳት ተጠያቂ ነው። 

ሁሉም የኢትዮጵያ እናቶች ፍሬ ሲበሉ ነው የኖሩት  - ዛሬም። እነሱው ያነኮሩትን ነው አሁን መልክ ለማስያዝ ላይ እና ታች እዬተባለ ያለው። እነሱ በቁርሾ ያበቀሉትን ቡቃያ ነው አሁን ውስጡን ለማጥራት እዬተባከነ ያለው። እነሱ የጠነሰሱት የመከራ ሌሊቶች ነው ዘመን ከዘመን እዬተሸጋገረ ይሄው ትውልድ ሲባክን የኖረው። አሁንም ያው ይቀጥል ነው። ሥሩ ሲባል አቅም የለ፤ አቅም ያለው ሲደፍር ደግሞ እንቅፋት እዬፈጠሩ የውስጥ ሰላምን ማወክ። ሁሉም ነበረበት የኤርትራ እና የሻብያ ጋብቻ ጊዜ እነ ኦቦ ሌንጮ ይሁኑ ሌላውም። የፍቅር ሃኒሙን ጊዜ አብሮ ነው አዳሜ ሠርግና መልሱን ያስነካው። ያ ይመቸኛል ብሎ ነው ጠብ እርግፍ ብሎ እጅ ነስቶ ሲያገለግል ከሄሮድስ መለስ ሌጋሲ ጋር ተዳምሮ የነበረው …
  • ·         የቀጠናው ሰላም ስለማስጠበቅ።

ኢትዮጵያ ቀደምት አገር ናት ሲባል፤ ለአፍሪካው ህብረት፤ ለጥቁሮች ነፃነት፤ ፓን አፍሪካኒዝም ሆነ ለተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ምሥረታ ከፍ ባለው ሳይንሳዊ ፍልስፍናም የድንቅነሽ መሬት ስትሆን በመንፈሳዊው ዓለምም አውታር ናት። ስለዚህ አፍሪካን፤ መካከለኛው ምስራቅ አፍሪካን፤  የአፍሪካ ቀንድን ችግር መልክ ለማስያዝ ራሷን መገበር ግድ ይላታ ውቅያኖስ እያቋረጡ ትናንሽ አገሮች ሁሉ የቀይባህር ባለሟል ሆነዋል። አፍሪካውያን ደግሞ ከምንም አልቆጠሩትም። አጀንዳቸውም አይደለም። በመከካለኛው ምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ የጠነከረ አነቃቂ ውይይትም የለም እኮ። አሁን የአቶ ዮሱፍ ያሲን የመካከለኛው አፍሪካ ጠበብት ናቸው። ግን ተጠቅሞባቸው የሚያውቅ አንድም ሚዲያ የለም። አልፎ አልፎ DW ላይ አዳምጣለሁኝ። የዛሬ 20 ዓመት የአፍሪካ ቀንድ ተክለ ገጽ ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም።

ሌላው ግን የኤርትራን የማቅረብ ጉዳይ ጋዜጠኛ መሳይ እንደሚያስበው ወይንም እንደሚያሰጋው በብልጠት አይደለም። „አልያም ኤርትራን ዲፕሎማሲያዊ ቅርቃር ውስጥ ለመክተትና ጊዜያዊ ድል ለመጨበጥ በሚል ብቻ የተወሰደ እርምጃ ሊሆን ይችላልእንዲህ ዓይነት ጠማማ ሰው አይደሉም ዶር አብይ አህመድ። ምንአልባት ቅንነታቸው እና ንጽህናቸው አንዳያስጠቃቸው ነው ስጋታችን እንጂ ውስጣቸውን ላጠናው ሰው ለፖለቲካም ብልጣ ብልጥነት የሚሆን ሰብዕና የላቸውም። ያው ፖለቲካ ብልጥነትም ትንሽም ከሴራውም ከሸሩም ቀምስ ቀምስ ቀሰምም ያለ ነገር ስለሚያስፈልገው። እንደ ተፈጠሩ ናቸው። ፍቅር አለበት በተባለበት ቦታ የማይደክሙ የፍቅር ሊቀ ትጉሃን ናቸው። ቀድሞ ነገር ከሴራ የጸዳ የፖለቲካ ሊሂቅ መሪም ዓይናችን እንደናፈቀው ኖሮ አሁን ነው ለመዬት የበቃነው። ንፅህናቸውን አይቶ ነው አምላካችን ከዛ ሁሉ የውስጥ መከራ አውጥቶ ለዚህ የፈተና ጊዜ አሻጋሪ ሙሴ ያደረጋቸው - የቀባቸው። በሌላ በኩል ስለ አፍሪካ ቀንድ ያላቸው በጎ ምልከታ ይሄው ማያያዣ ምርኩዙ። ስለ ኤርትራም ያላቸው ቅናዊ ራዕይም ይሄው … የቀደመ ስለመሆኑ። 

„Dr. Abiy Mohammed ሕዝብን የሚያረጋጋ ንግግር ተናገሩ
ኦህዲድ በእድገት ውስጥ ያለ ድርጅት ነው። በርካታ ቻሌንጆች እዬገጠሙት ያነን እዬፈታ የመጣ ድርጅት ነው። ችግር ባይኖር ኖሮ መሰብሰብ ባላስፈለገ ነበር። ኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ባይኖራት ኖሮ 60/ 70 የፖለቲካ ፓርቲ ባላስፈለገ ነበር። መደማመጥ ስሌለ፤ መስማማት ስሌለ ነው እንጂ 60 ፓርቲ አያስፈልገንም ነበር። ይሄ ችግር ደግሞ የሚፈታው በማኩረፍ አይደለም። የእኔ ሃሳብ ካልተደመጠ ብቻ በማለት አይደለም። በመቀራረብ ነው። ማስተዋል የሚገባን ኦሮምያ 300 ሚሊዮን ህዝብ ማስተናገድ የሚያስችል ፖቴንሻያል አለው። የኢትዮጵያ ህዝብ 100 ሚሊዮን አይሞላም። እንኳን ብሄር ብሄረሰቦች ጁቡቲም፤ ኤርትራም ሱዳንም ቢመጡ በህግ፤ በሥርዓት እሰከ ሰሩ ድረስ አብሮ መኖር፤ አብሮ ማደግ አስፈላጊ ነገር ነው። ዱባይ ያደገችው ውሃ ኢንፖርት አድርጋ፤ አፈር ኢንፖርት አድርጋ፤ ድንጋይ ኢንፖርት አድርጋ፤ ሰውም ኢንፖርት አድርጋ ነው።" ይህን ነበር የተናገሩት።

ሌላው በራውንዳ ቆይታቸውም ያዬዩትን አይተዋል - ከጦርነት ትርፉ አመድ ብቻ መሆኑን። በባዕለ ሹመታቸውም ንጹህ የናፍቆት ፍቅራቸውን ነበር  ለኤርትራ መንግሥት እና ህዝብ የላኩት። አሁንም በውስጣቸው ቢኖር ነው እንደ አንድ አብይ ጉዳይ አድርገው የመጨረሻ መቋጫ ለመውስድ ደፋር እርምጃ ነው የወሰዱት ትርፍን በሚመለከት ፍቅር ነው የሚያተርፈው። ማሸነፍን በሚመለከትም ህግ እና ዓለም ዓቀፍ መርህ ነው ያሸነፈው። የህግ የበላይነት ነው የተረጋገጠው። እንደ ዜጋ ሊመር የሚችል ነገር ቢኖርም የብትን አፈር ነገር፤ ያው በመንፈስም መለዬት ከባድ ቢሆንም ነገን ተስፋ በማድረግ የተሻለ ቀን የተሻለ መስማማት፤ ተሻለ ሁለቱም በአዋሳኝ የሚኖሩት ዜጎች እንደልባቸው ወጥተው ገብተው ካለስጋት በቀደመው የአብሮነት ብሂል የሚሠሩበት ጤናማ ሁኔታ ሊፈጠር ከቻለም አንድ ነገረ ነው በፍቅር ፍለጋ ውርዴት የለምፍቅር ፍለጋ ሸንፈት የለም። በፍቅር ፍለጋ የመንፈስ ትርፍ እንጂ የቁስ ብልጠት የለም። በፍቅር ፍለጋ ክብር ነው ያለው። በፍቅር ጉዞ "ቅርቃር ውስጥ መጨመር" ሳይሆን የሚቀረቅረውን ዲያቢሎሳዊ ሴራ አክሽፎ ክፉውን መንፈስ አባሮ ቅርብትን ለዕልፍ መናኘት ነው። መኖርን ነፃ ማውጣት የፍቅር ፍልስፍና ነው።   
  • ·         ኢትዮጵያ አዬር መንገድ መርዶ።

የማከብራቸው አቶ አበራ የማን አብ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውን የለውጥ ውሳኔ ስሜታቸውን ገልጸዋል። እኔ ከባቡር ሃዲዱም፤ ከቴሊኮሙም ይልቅ ኢትዮጵያ አዬርመንገዱ ውሳኔ አስደንግጦኛል። መርዶ ነው ለእኔ።

አዬር መንገድን በሚመለከት ኢትዮጵያ ቀረኝ የምትለው ሌላ ቅርስ ከወያኔ ሃርነት የማወደም ጦስ የዳነ የለም። ይህም ቢሆን መንፈሱ ዞጋዊ ነው። የሥራ ቋንቋውም ያው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ የአዬር ሃይል፤ የምድር ጦር፤ የባህር ሃይሉ፤ ፖሊሱ፤ የአገር ደህንነቱ ፓፕሊስት ነበር። የኢትዮጵያ አዬር መንገድ ያው የኢትዮጵያ ከሚባል የተጋሩ የግል ንብረት ሆኖ ኖሯል። ያቺው ጅራቱ ምልክት ስላለበት አዬር ላይ አንድ ለእናቱ ስለነበር ፍቅራችን አልነፈግነውም። እርግጥ ነው በትግሉ ውስጥ እሱም የፈተናው ተጋሪ ነበር። ወያኔ ሃርነት በሚፈጥረው የህዝብ መብት ረገጣ ምክንያት በኢትዮጵያ አዬር መንገድ መሄድ ሁሉ ወንጀል ነበር። በኢትዮጵያ አዬር መንገድ መሄድ ወንጀል ከነበረ አሁን ተቆርቋሪ ሆኖ መነሳትም ያስገምታል። የሆነ ሆኖ ይህ ቅርስ በነበረው ትውፊቱ ለቀጣዩ ትውልድ ቢተላለፍ ምኞቴ ነበር። አንድ እንደ ወልዴ ስለሆነ። ከቁሱ ትርፍ የህሊና ትርፍ ስለሚበልጥም። ለኢትዮጵያ የሚጠቅማትም የመንፈስ ሃብትነቱ ነው።

ግን ለውጥ ተፈልጎ ለውጥ የሚያመጣቸው ወጀቦች ተፈርቶ አይሆንም እና ቢያንስ ለውጪ ባለሃብቶች አዬር መንገዱ እንዳይሰጥ አበክሬ ላስገነዝብ እሻለሁኝ። ውስጥን ሚስጢርን አውጥቶ የመስጠት ያህል ነው። ሆድ እቃን ማስረከብ። ፓተንቱም ይሰረቃል። ታረኩ ምርኮኛ ይሆናል። ቅኝ ግዛትንም መፍቀድ ነው። ብዙ ነገሮች ነው የሚበከሉት ባህላችን ወጋችን ልማዳችን ዕምነታችን ነፃነታችን የዓድዋ ድል ሁሉ ይደፈራል። በፈለገው ሁኔታ እና መስፈርት ይህን አዬር መንገድ ልምዱ ተመክሮው ተቀባይነቱ እኮ የሰማይ ነው የነበረው። እርግጥ ነው የአስተዳደር በደል እና ተጥቅልሎ በአንድ ጎሳ መያዙ ህመም ነበር።

በሌላ በኩል የሄሮድስ መለስ ዜናዊ ኢትጵያዊነትን በጠላትነት ፈርጆ ድራሹን ለማጥፋት ያደረገው የ27 ዓመት ብካዩን ለማጽዳት እዬታገሉ ሌላ ብካይ መናፈቅየኢትዮጵያዊነት ሱስ ነውን“ አቅምን ያኮስሰዋል። መንፈሱንም ይዳፈረዋል። የቀረው የመነሻ እርሾ እኮ በተቋም ደረጃ ይሄው አዬር መንገድ ብቻ ነው። እንዲያውም አንድ ጊዜ 20 የቻይና አስተናጋጆችን ስልጠና በሚመለከት የጻፍኩት ጹሑፍ ፖስት ሳይደረግ ቀርቶ ነው እንጂ መረር ያለ ጹሑፍ ጽፌም ነበር። ሁለመናችን ከተሸጠ ምን ይትረፍን? የኢትዮጵያ ንጹህ ሰንደቅዓላማ እኮ ለምልክት ያለው በዚህ ተቋም ብቻ ነው። እያንዳንዱ አገር ሲመጣ ድርብ ተልዕኮ ይዞ ነው። የመንፈስ ወረራ ይዞ ነው የሚመጣው። ከሆነም ቢያንስ ፖፕሊስት ለሆኑ ባለሃብቶች ቢሆኑ የተሻለ ነው። ግን መራራ ውሳኔ ነው። ለትወልድም አይበጅም። አሁን ደግሞ ብቅ ብቅ ሲል ኢትጵያዊነት አንድ ለእናቱን አስረክበን ምን ሊቀረን? ያለን ስለሚመስለን ነው እኮ የለንም እኮ … ለዚህም ነው እኮ ወጣ ገብ የሆነው ራዕያችን። በዚህ የሚገኘው ትርፍ ኢትዮጵያ ቢቀርባት እና በነበረ ጽናቷ ተግታ ብትቀጥል ምኞቴ ነው። የህመም አለው ዓይነት ይህ የዕድሜ ልክ ሆድ መርዘን ነው የሚሆነው። ነቀርሳ መትከልም ነው።
  • ·         ነገረ አማራ።

አማራ። ነገረ አማራ በጥሞና መከታታል አለበት ይህን መሰል ብሄራዊ ውሳኔ። መንፈሱን ማባከን የለበትም። እስከ አሁን ባያቸው፤ በታደመባቸው፤ በኖረባቸው ሂደቱ ውስጥ የኖረበትን የመከራ ቁልል ያውቀዋል። ስለዚህ የሌላ አጀንዳ አስፈጻሚ ላለመሆን፤ ክውን ሰብሰብ ማለት አለበት። እዬሄደ የሚማገደው ነገር ተግ ማድረግ አለበት። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ልቡን ስለፈተነው ሌላ ቀጠና ከፍቶ ደግሞ አቅምን የማባከኛ ስልት ሊኖረው ስለሚችል በተደሞ መሆኑ ይጠቅመዋል - ለአማራ። ለነገሩ እነሱም „ከቤተ አቧራ“ ምንም እንደማይጠብቁ ነው። የሆነ ሆኖ መቆስቆሻ ገል ከመሆንም መታቀብ አለበት - አማራ።

  • ·         እንደ ቅንጣቢ ወይንም እንደ ማከያ አሻቦዊ ድል የታዬው የአርበኞቻችን ከእስር መፈታት፤  

የፖለቲካ አርበኞቻችን እነሱም ግምት አልሰጡትም ወያኔም የውስጥ ቃጠሎው ጭስ አልበረደለትም። እነሱም ተመስገን አላሉትም የወያኔ ሃርነትም ንዴት አልበረደለትም። እነሱ እናመሰግናለን አያውቁበትም የወያኔ ቁጭትም እንደፈላ ነው። አሁን የአርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታት እኮ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ መብረቅ ነው የነበረው። በዛ ላይ ከጠ/ ሚር አብይ አህመድ ጋር በቤተመንግሥት ፖለቲካዊ ውይይትም ማድረግ የከፋው መርዶ ነው። ስንት መዋለ ንዋይ ያፈሰሱበት ነው። ስንት ደክመው ጥረው ግረው ያገኙት ድል ነበር አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌን ከእጃቸው ለማስገባት። ስንት ወጥተው ወርደው ለፍተው ከእጃቸው የገባ የበቀል ማወራራጃ ነፍስ ነበር። በጣምራ አገሮች መሃከል የተከናወነ የሸፍጥ ክንውን ነበር። 

ይህ እኮ ከባድም ባላነሰ ነበር ጉዳዩ ለእኔ። ስለዚህ አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ መፈታት እንደ ቀለል ነገር ማዬት ከፖለቲካ ውጪ መኖራችን ያሳያል። የተመክሮ ድርቀት። ከዛ በኋዋላ የድርጀቱን ሂደት እና ፈተናዎችን ቢጤን ከአልጀርሱ የውሳኔ አፈጻጸም ጋር ተመሳሳይ ነው። ከእነ ህሊና መገኘት በራሱ ምን ሊባል እንደሚቻል አላውቅም። ምክንያቱም ሁልጊዜ በስንብት ነበር እምደምድመው ጹሑፌን፤ ያ ህሊና ከነተፈጥሮ በመዳፍ ሲገባ ትልቁ የፖለቲካ መደራደሪያ ነው። ግን እሱም ዋጋ አልተሰጠውም። ያ ትልቅ መክፈቻ ከእጅ ገብቶም ዛሬም እናነኩራለን።

ሳይንቲሰት ኢንጂነር ቅጣው፤ አቶ አሳፋ ጫቦ፤ ፕ/ አስራት ወልደዬስ፤ አቶ አሰፋ ማሩ፤ ሻ/ አጣናው ዋሴ፤ ፕ/ ዶር እምሩ ስዩም … ዕድሉን አላገኙም። መኖርን አላገኙም። መሰንበትን አላገኙም። የመን ኢትዮጵያን ደፍራ ያን ያህል ስታስረግጠን አይቆጨንም፤ መደፈራችን አልኮሰኮሰንም። አያንገበግበንም ዛሬም። የመንም የእጇን አግኝታ አርበኛውም ከቤተሰቡ ጋር ከነሙሉ ሰብዕናው ጋር ተገናኝቶ እንደ አልባሌ እናዬዋለን። ግን ምን ቢደረግልን ይሆን እኛ የምንረካው? ሳውዲ ላይ ደማቸው የፈሰሱ ኢትጵውያን፤ ሊቢያ ላይ አነገታቸውን የታረዱ ወገኖች ያሉን ዛሬ ሳውዲ፤ ኬኒያ፤ ሱዳን ላይ ክብራችን ዝቅ ያለበት ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ ተለውጦ  ለአገራቸው መሬት ሲበቁ ለእኛ ምናችንም አይደለም። እኛ የሚጨንቀን የገበርዲን እና የከረባት እና የማልያ ጉዳይ ነው

ትግረኛ ቋንቋ ተነገረ ተብሎ ቀውጢ በተሆነበት መንደር ዛሬ ለኤርትራም፤ ለትግራይም ተቆርቋሪነት ያስተዛዝባል። በሌላ በኩል እነኝህን ወጣት መሪዎችን ለዚህም ነው አታውቋቸውም የምላችሁ። እንደነዚህ ዓይነት ወጣት ፖለቲከኛ ከትህትና ጋር ኢትዮጵያ ብህልሟም አስባው አታውቅም። ሊኖሩ ይችላሉ በግል እንደ ድርጅት ግን ኦህዴድ ለብልህነት ዲታ ነው ሁልአቀፍ አቅም አለው። አቅሙ ወጣ ገብ አይደለም። አቅሙ ወጥ ነው። በራሱ መንፈስ ላይ የቆመ ነው። ያለውን የሚያደርገውን ጠንቅቆ የሚያውቅ።
ምን ተጎዳ  የኦቦ ሌንጮ ለታ ቡድን ገናሀ“ ብሎ ኦህዴድ መግለጫ ሲያወጣ ጥሪውን ተቀበለ የውሳኔውን። በብሄራዊ ደረጃ ጥሪ ሲመጣ ማቄን ጨርቄን ሳይል አምኖ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እያለ ሄደ ክብርን አገኝ። ተደማጭነትን አተረፈ። እሸቱን ተቋዳሽ ሆነ። እነ ሳጅን በረከት ስምዖን ቅርሻ በሚደመጥበት ጉባኤ፤ ከበረዶ ግግር ጋር መላ ይገኛል ብሎ ከትሞ የነበረበው ኦፌኮንበጥንቃቄ ውሳኔውን እንዲህ ብለነዋል፤ ለማ ፊቱ ኦሮሞ ይመስላል፤ ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም፤ የታሪኩን ፈተና መወጣት አይቻለውም አህዴድበማለት ጊዜውን ሲያቃጥል እነሱ ብሄራዊ አህጉራዊ ጉዳያቸውን በድፍረት እያጣደፉት ነው። ከእንግዲህ በኋዋላ ሥራ ቦታም ስለሚደራረብ በነበረው ጊዜ ያልተጠቀሙት ሊያገኙት የሚገባውን አትኩሮት እና አክብሮት ያህልላይሆን ይችላል። ሁሉም ልቡ ተንጠልጥሏል። ቤት ኪራይ ፍለጋ ነውወደ አገሩ ለመግባት። ይህ ድርብ የመንፈስ አዲስ ጉዞ ላስገኘው የተስፋ ጉዞ አቅምን አጠናክሮ ጉልበት መሆን ሲገባ አሁንም ያው ነው በተለመደው መንገድ።
  • ·         ቅራኔ አያያዝ እና አፈታት ድርብነት።

አንዳንድ ውይይቶችን ሳዳምጥ የልምድ ማነስን ሲወሳ እሰማለሁኝ። እንኳንስ ዶር አብይ አህመድ ሄሮድስ መለስ ዜናዊ እኮ ምን ነበራቸው ጫካ መጥተው እኮ ነው የአገር ብሄራዊ መሪ የሆኑት። የሆነ ሆኖ በቅራኔ አያያዝ እና አፈታት እረገድ ዶር አብይ አህመድ የዳበረ ተመክሮ አላቸው። በተወለዱበት በቀያቸው የእስልምና ሃይማኖት እና የተዋህዶን ፈተና በድል ነበር የተወጡት። ከዚህም ባለፈ ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ካፒታል ቀውሶችን አፈታት እና ሂደት ከባህላዊ መተሳሰሮች አገር ሉላዊ የሆነ ጥናት አድርገዋል። የመመሪቂያ ጹሑፋቸው በዚህ ላይ ያተኩረ ነው። በሙያም ቢሆን መጨረሻው የእውቀት ደረጃ ላይ ያደረሳቸው የሰላምና የደህነነት የእውቅት ዘርፍ ስለሆነ ለብሄራዊ ሰላም እና መግባባት ድርጁ ትልቅ ልብ፤ ሰፊ ሆድ፤ መጠኑን መለካት የሚከብድ አደብ የገዛ ሁለገብ- ሁልአቀፍ ህሊና አላቸው https://www.youtube.com/watch?v=SMD2pmSYZ2k&t=398s Social Capital
እርግጥ ነው ከሰማይ የወረዱ መላዕክ ስላልሆነ እንደ ሰውነት ግደፈቶች ሊኖሩ መቻላቸውም ሰውኛ ነው። ማሽን ሰው ሰራሽ ሳይሆኑ የፈጣሪ ፍጡር ናቸው። ከሁሉ በላይ ንጹህ ልብ እና ፍቅርን የሚሻ መንፈስ አላቸው። ትሁት አንደበት አላቸው። ከዚህም በላይ የማይከብዱ አቅርቦ ለማድመጥ ቅልል የሚሉ፤ አቀራራቢ እና አግባቢ ገጽ ያላቸው ናቸው። 

የሰውን ልጅ እንደ ጸጋ እንጂ እንደ ጠላት፣ እንደ ተቀናቃኝ አይመለከቱትም። „ህዝብ መኖሩ በረከት ነው“ ብለው የሚያምኑ ናቸው። „ሰው የሌለበት ቅልጥ ያለ ከተማ በጠራራ ጸሐይ እንኳን ቢሆን ያስፈራል፤ ሰው የመኖር ጸሐይ ነው“ ብለው ነው የሚያምኑት። በሳቸው ቤት የኤርትራ ህዝብ የደሜ ክፋይ የአጥንቴ አካል ብለው የሚያምኑ ቅን ሰው ናቸው። በዚህ ክፋት በነገሰበት ዓለም ደግሞ እንዲህ ዓይነት መሪ ማግኘት ከፖለቲካ መሪነት ይልቅ ሞራላዊ መሪነቱ አድልቶ ነው የሚገኘው። እርግጥ ነው መሪዎችን የግድፈት መናህሪያ የሚያደርጉ ክፉ መካሪዎችን ፈጣሪ አምላክ መንገዳቸውንም ጉልበታቸውን ሽባ ያድርግልን ነው የዕዬለቱ ጸሎቴ። ምቀኞች፤ ቅን ያልሆኑ ሰዎች፤ መንደርተኞች፤ ስውሮች ብክላቸውን መሸጋገሪ እንዳያደርጉት ፈጣሪ ይርዳቸው። „አሜን!“ ጠረኖችን አበክሬ ስለመክታተልም የሚጨንቁ ነገሮች አሉበት። ሰው በተቀረበ ቁጥር ሰንሰለታማዊ ሃዲዱ ትብትብ ነውና። አብሶ አቅመ ቢሶች መንጠላጠያ ነው የሚሹት። ጥገኞች ስለሆኑ።
  • ·         ማጠቃለያ።

የወለዱት ልጅ፤ ያገቡት ትዳር፤ የሚገዙት ልብስ 100% አያረካም። ግን አንጻራዊ መርካት ካለ 50% እንኳን ቢሆን ከዜሮ ለተነሳ ገነት ነው። ለዛውም እስከ አሁን የተከፈለው መስዋዕትነት ለታሪክ ብልጽግና ለነፃነት ግብርነት ነው እንጂ በውጤት፤ በስኬት ደረጃ ለተከፈለው መስዋዕትነት የሚመጥን ብቁ አቅም ያለው የፖለቲካ ድርጅትም መሪም ኢትዮጵያ አግኝታ አታውቅም። ብታገኝም ሴራው ሰብሮ ይጥለዋል። ደግፎ ጎደሎን መሙላት ሳይሆን አብሮ የመውደቅ ህልመኛ ነው ሁሉም። ለዚህ ነው በኦህዲድም በዶር አብይ አህመድም አሳሩ ተባራክቶ የባጀው። የሁለቱ ብልህነት እና ጠንቃቃነት ልህቅናም የሚላካው ያን ዘመን ተሻጋሪ የሸር ሰንሰለት አልፈው እዚህ መድረሳቸው ነው። አልተበገሩለትም ለ66ቱ የሴራ ካቴና። መሪነት ማለት ይሄው ነው። ወጀብን አሸንፎ የሚወጣ ጀግና። በዚህ ላይ የገዱ መንፈስ ብረት መዝጊያ ነው፤ ለዛውም የሳጅን በረከት ስምዖንን ዘመን ጠገብ ሴራ ድል ነስቶ፤ ጀግኖች!

በቅንጅት ጊዜ ለተከፈለው ግብርነት ባክኖ ነው የቀረው። ስበብ ምክንያት አይሆንም። ዛላቂ መፍትሄ ለማምጣት አቅም አልነበረውም የወያኔ ሃርነትን ሴራ ተቋቁሞ ሆነ የ66ቱን የሴራ መቋደሻም መክቶ ወደፊት መራመድ አልቻለም። / ሚር አላስለወጠም፤ ካቢኔ አላስለወጠም ወይንም በተወሰነ ደረጃ እንዲቀዬር አለስደረገም፤ በህብረት፤ በአማራጭ ሃይሎች፤ በአንድነት፤ በመድረክ፤ በኦፌኮን፤ በሰማያዊ ቢባልም በተመሳሳዩ ነው። ራሳችውን ችለው ለመቆም ለመቀጠል እንኳን የተሳናቸው ናቸው።  ለተጨባጩ ሞገደኛ ለውጥ ቁልጭ ያለው ለፍሬ ያበቃው ገናናዎቹ የኦሮሞ ንቅናቄ እና የአማራ ተገድሎ ብቻ ናቸው። ለዚህም ባክኖ እንዳይቀር ዕድሉን ውል ላይ ያዋለው ይህን ያዳመጠው ለማ፤ የገዱ፤ የአብይ፤ የአንባቸው መንፈስ ነው። ተጋድሎዎቹ ደም ገብረውለታል - ሁለቱም። ትዳራቸውን አፍርሰዋል - ሁለቱም ተጋድሎዎች። ኑሯቸውን ቀቅለዋል - ሁለቱም ተጋድሎዎች። አካላቸውን ታርደውለታል - ሁለቱም ተጋድሎዎች።

እኔ ነኝ የሚል ድርጅት ካለ ሳተናው ብራና ላይ አለሁለት ይምጣ እና ይሞግተኝ። ብልጭ ድርግም በሚል የሞገድ ፉከራ አንዲት ጋት የመንፈስ ትርፍ እንኳን ለመሰብሰብ አልተቻለም። ይልቁንም የተሰበሰበው ተበተነ እንጂ። ያዳመጡት ብልሆቹም ሲሆኑ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሌት እና ቀን ከእነ ሪሞርኬው ስብሰባ ላይ የሚጣደውን የወያኔ ሃርነት ትግራይን፤ የሳጅን በረከት ስምዖንን፤ የአቦይ  ስብሃትን ሸር እና ደባ ጥሶ፤ የውስጥ አርበኞችን የእነ ሆድ አደሮችን ፍልሚያ ችለው እና ረትተው፤ ዓይናቸው ጉርሽጥ እስኪመስል ድረስ ሌት እና ቀን እንቅልፍ አልባ ተግተው፤ የህዝብ መፈናቀሉን እና ጭፍጨፋውን ተቋቁመው፤ በውጭ የሚኖረውን የመመሪያ ሰጪ እልፍ ትእዛዝ እና ግፊያ ችለውና ታግሰው ነው ትግሉን ከዚህ ደረጃ ያደረሱት። እኛ ደግሞ አቃቂር ስናመርት ውለን እናድራለን። ዘመናዮች።

ይህን አላረካንም የሚል ካለ ደግሞ ሜዳውም ፈረሱም ነው። ቀድመን ለመተንበይ አቅም እንኳን የለም፤ ቀድሞ ነገር የተተነበዬውም አይሆኑ ሆኖ ወርዶ ነው የተፈጠፈጠው። አዲስ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ጭራ እዬጎተቱ ማጓተት ብቻ። የለማ አብይ የአንባቸው ገዱ መንገድ የፖለቲካ አቅም እና የተፎካካሪው ፖለቲካ ድርጅት ሆነ የተንታኙ እንዲሁም የጋዜጠኛው አቅም ሁልጊዜም እንደምለው መመጣጠን አልቻለም። ጭራ መከተል እንጂ ቀንዱን መቅደም አልተቻለውም። ለዚህ ነው አቋራጭ መንገዱ እንደ መውጫ በር ተጠምዶ ያለው። እነ ኦቦ ለማ መግርሳ ሊጠኑ ይገባቸዋል የምለውም ለዚህ ነው። አላወቃችኋቸውም የምለውም ለዚህ ነው። በጣም የተራራቀ ጉዳይ ነው የማዬው። ይልቅ አገናኝ ድልድይ ሰው ማፈላለግ እንደ ተለመደው፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ወይንም ደግሞ ወፊቷን መጠያዬቅ ሳይሻል አይቀርም። የሚስጢር ቀዳዳም አልተገኘም። ይሆናል የሚባለው አይሆንም ግን ዱብ የሚል አንድ ሌላ አዲስ ነገር ደግሞ አለ። ለዛውም በዬዕለቱ፤ አንዳንድ ቀን እስከ ሦሰት አራት አዲስ ዜና ይኖራል። ይብቃኝ … የኔ ቅኖቹ መልካም ሰንበት።

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ።   


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።