ዳማዊ ቀን እና ጠይም ዕንቁዎች ያሉበት የቤልጀሙ ቡድን ለሩብ ...
ጠይም ዕንቁዎች ያሉበት የቤልጀሙ ቡድን ለሩብ ፍጻሜ አለፈ።
ከሥርጉተ ሥላሴ 03.07.2018
(ከገደማዊቷ ሲዊዘርላንድ።)
ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዕን ናቸው፡
መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
(የማቴወስ ወንጌል ምዕራፍ ፭ ቁጥር ፲)
የቀኑን ጨዋታ አልተከታተልኩትም። ብራዚል ለሩብ ፍጻሜ እንዳለፈ ፊፋ ሪፖርት ላይ አንብቤያለሁኝ። የምሽቱን ግን በርጋ ተከታትዬዋለሁኝ። ቤልጀም እና ጃፓኖች ነበሩ የተጋጠሙት። የመጀመሪያው የእረፍት ክ/ ጊዜ ላይ ጀፓኖች በሚገርም ብቃት ተንቀስቃሰዋል። እስኪገርመኝ ድረስ። ፈጽሞ እንዲህ አለጠበቅኳቸውም ነበር። ፍጥነታቸው፣ የመከላከል ሆነ የማጥቃት ውህደታዊ እንቅስስቃሴያቸው በአግራሞት ነበር የተከታተልኩት። ለዛውም ከቤልጄም ጋር … ህም!
እርግጥ ነው ከ2014 የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ጀምሮ ቤልጀሞች የተከደነ ብቃት እንዳላቸው አስተውያለሁኝ። በ2016 ፈረንሳይ አገር ተካሄዶ በነበረው የአውሮፓ የዋንጫ ጨዋታም አስደሳች የአጨዋወት ስልት እና ሙሉ ሞራላዊ ሥነ - ምግባር እንዳላቸው በተጨማሪነት አይቻለሁኝ። እንዲያውም ያን ጊዜ ቤልጀም እና ፈረንሳይ የቦን ጥቃት ሰለባ ስለነበሩ ብዙ መከራ ያሳለፉ ስለሆኑ ከሁለቱ አገሮች ለአንዱ ዋንጫው ቢሆን የህዝቡን መከፋት ሚዛናዊ ያደርገዋል የሚል ህልም ነበረኝ።
ነገር ግን ዋንጫውን ፖርቹጋል ወሰደ። ፈረንሳዮች አጅግ ብርቱዎች ነበሩ በለስ ሳይቀናቸው ቀረ።
ዘንድሮም እኔ ለቤልጄም ያው መስል ህልም አለኝ። ያው ከሲዊዝሻ ባይበልጥብኝም። ነገ ቀን ላይ ሲዊዝሻ ከሲወዲን ጋር ግጥሚያ አለባት። በሻማ ብርሃን ነው እምታደመው። መቼም መነኩሲያዋ ሲወዝ ቆቧን አውልቃ ለሩብ ፍጻሜ ካለፈች የእኔውም አይቀርለትም ...ፌስታው ከልክ በላይ ይሆናል።
በዛሬው ጨዋታ ቤልጀሞች መጀመሪያ ላይ እጅግ የተዳከመ ነበር የማጥቃት ቆይታቸው። አብሶ ከእረፍት መልስ በ4 ዲቃቃ ውስጥ በጃፓኖች ሁለት ሲቆጠርባቸው እጅግም ደንግጬ ነበር። ጎል ጠባቂያቸው እኮ ጠንካራ ነበር፤ ቁመቱም የሰጠ ነው። ተመረብ እስተ መረብ።
በመጨረሻ ግን አንድ ጎል አስቆጥረው አንድ ለሁለት በሆነ ሂደት ላይ እያሉ ሁለተኛውን ደገሙና እኩል ለእኩል በሆነ ውጤት የ90 ደቂቃው ጨዋታ ተጠናቀቀ። በጠፉ ደቂቃዎች ላይ ትንሽ ምራቂ ደቂቃ ታከለላቸው። ያው የታዳሚው ሁኔታ እና ዕሳቤ እኔም ጨምሮ የነበረን ግምት ጨዋታው ለ30 ደቂቃ ይራዘማል፤ ያም ካልተሳካ የፔናሊቲ ቆይታ ይኖራል ነበር። ጥቂት ሰከንዶች ሲቀሩ ሦስተኛውን ደገሙት እና ለሩብ ፍጻሜ አለፉ። ያ ነበር አቅማቸው፤ ያን ነበር ዛሬ ጠብቄ እንዳያቸው እኔ ፕሮግራም ያደረኩት እናም አለፉልኝ። ደስም ብሎኛል።
ጨዋታው እጅግ ሰላማዊ የነበረ ሲሆን አንድ ቢጫ ብቻ ነበረው ጃፓን። ያው የእስያ አገሮች ይሄ ሜድቴሽን፤ ዮጋ የሚባለው አርት እጅግ ገርቶ ነው የሚያሰድጋቸው። ከዬትኛውም የቲም ወርክ እኔ ሳያቸው ቀስ ያሉ ሆነው ነው የማገኛቸው።
ጨዋታው በቆይታው አጓጊ ነበር ማለት ባልችልም፤ ግን መጨረሻ ላይ የነበረው ፉክክር እና ባለቀ ሰከንድ ላይ የገባው የቤልጄሙ ሦስተኛ ጎል አየሩን ሙሉ ለሙሉ በፍሰሃ ቀዬረው እና የተለዬ ስሜት እና ሞገስ ለጨዋታው ቸረው።
- ዕድልን ስለመጠቀም እኛ ምን እንማር?
ኢትዮጵያም የሞት ዳመና በአንዣበባት ወቅት ነው የሙሴው አብይ አሜኑ መንፈስን እዮር ያደላት። ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ሰፊውን ተስፋን ማስቀጠል የባለቤተኞች የእኛው ይሆናል። ያቺ ተጨማሪ ደቂቃ ናት ነፍስ ዘርታ ለቀጣዩ ጨዋታ ለቤልጄም ቡድን ነፍሱን የመለሰችለት።
ኢህአዴግ እንደ ግንባርም በማስተዋል ሆኖ ይህን ከእጁ የገባ ወርቅ ቀልጦ እንዳይፈስ ሊጠብቀው፤ ሊንከባከበው፤ ሊጨነቅለት፤ ሊጠበብለት ይገባል። ዕድል ካመለጠ ተመልሶ አይገኝም። ይህ እድል ለሁላችን የመንፈስ እርካታው እኩል ነው። ጥቂቶች የአሉታዊ አርበኞች የተፈጠሩበት ስለሆነ ይታክቱ። ምልዕቱ ግን ዕድሉን ለመጠቀም በፆም፤ በጸሎት፤ በሱባኤ፤ በድዋ፤ በአርምሞ፤ በተደሞ ከአብይ አሜኑ መንፈስ ጋር አዋህድን ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መንፈሳዊ ድጋፉን መፈጸም አለበት ብዬ አስባለሁኝ።
ለዚህም ነው ቤልጄም ያሸነፈው። በአለቀች ሰከንድ ያገኛትን ዕድል ቡድኑ ተጠቀመባት ጨዋታው ሳይራዘም፤ ሳይንዛዛ። 30 ዲቂቃ ቢራዝም እንደ ዛሬው አያያዙ ለሩብ ፍጻሜ ላይልፍ ሁሉ ይችሉ ነበር። ጃፓኖች እንደ ጥንግ ነበር ሲበሩ የነበሩት።
ይህን የተስፋ ብርሃን የቤልጄሙ ጨዋ ቡድን ተስፋውን ሰንቆ ቀጣዩን ጨዋታ ይፋለማል። ቤልጄም ጠይማዊ ዕንቋዎቿም ከህብር ቀላማቸው ከነጮች ጋርም ዳማዊ ዛሬን እንደ በራላቸው ነገም ይርዳቸው … ሥነ ምግባራቸውን እጅግ አድርጌ እወደዋለሁኝ።
ፍቅር በልጽጎ የሚገኝበት ዓውድ ለባርባሪያውያን ሳይሆን ለሠለጠነ ህሊና እስፖርት ብቻ ነው!
የኔዎቹ ርትህ ክፍል አምስትን ነገ እንቀጥለዋለን። ኑሩልኝ። መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ