የልጆች የህይወት ዳገታዊ ግማድ። እስጨናቂው ዕጣም።
ወላጃዊ ግዴታን በመወጣት እረገድ የትውልዱ ዕጣ መለጣ እንዳይሆን ቢታሰብበት መልካም ነው።
አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?
እኔን ከማዳን ከጩኸት ቃል ሩቅ ነህ?
(መዝሙር ምዕራፍ ፳፩ ቁጥር ፩)
ከሥርጉተ©ሥላሴ
04.08.2018
(ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ)
- · የመጓጓዣ ሃሳብ።
ይህ ርዕሰ ጉዳዬ ዛሬ ባለሁበት ዕድሜዬ ያሳብኩት አልነበረም። ይህን ገና ታዳጊ ወጣት እዬለሁኝ
ከውስጤ የነበረ አብሮኝ ያደገ ደሜ ነው። አብሮኝ እንዲያድግ የሆነበት ምክንያትም እብዬ እና አቨይ ሲለያዬ የማወቀው ታሪክ ስላልነበረኝ
አድጌ ነፍስ ሳውቅ እኔ ከእናቴ ጋር መሆኔን ሳረጋግጥ በራሱ ጊዜ በመንፈሴ የተጸነሰ ይመስለኛል። መራራ የደም ቅምረት ላረሳው ላይረሳኝ
ተዋደን በአንድ ማዕድ አብረን የኖርን ግማድ።
ከዚህ በተጨማሪ ከወላጆቻቸው ጋር በጋራ ከሚያድጉት ይልቅ እንደ እኔ ከእናታቸው ጋር የሚያድጉት
ዕድል ያሸለበችባቸው እጅግ በርካታ ህፃናት የመንፈስ ምሾም ህሊናዬን እንዳይተኛ አድርጎ ኮትኩቶ ስላሳደገውም ጭምር ነው። ከአደግኩ
በኋዋላ እንደተረዳሁት ማግባትም መፍታትም ገብያ ሄዶ እቃ እንደ መግዛት እጅግ ቀላሉ የህይወት ክፍለ አካል መሆኑንም ተገንዝቢያለሁኝ።
በህይወቴ ከሚያሥፈሩኝ ነገሮች ትልቁ ትዳር ሆኖ በልቤ ጽላት የተከተበውም በዚኸው የመከራ ጠመኔ
መሆኑ ዛሬ ዛሬ ይረዳኛል። ላም ጣም ለሌለው ሕይወት ስለምን የሰው ልጅ ጉልቻን አህዱ ይለዋል?
አሳዛኙ ነገር በእኔ አልበቃ ብሎ እህቶቼም በዚህ ውስጥ ኑሯቸውን መወሰናቸው ዛሬ ላይ ውስጤን ያርመጠምጠዋል።
ከማህበረሰቡም፤ ከቤተሰብም ያዬነው የትዳር ናሙና ባለመኖሩ ታላቁን እዮራዊ ጸጋ ሸሽተነው እንድንኖር ተገደናል።
በዚህ የውስጥ ቋያ ውስጥ እንግዲህ
ብዙ ማህበርተኞች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁኝ። ቢሞክሩት እንኳን ሳይዘልቁ በፈትነት ተጨምረው የከተሙ ብርኩት ናቸው። … ስናሳዝን እንደ
ትውልድ።
እጅግ የሚከረፋው ነገር አቨይ ናፍቆኝ ስሄድ እብዬ ትናፍቀኛለች፤ እብዬ ናፍቃኝ ስሄድ አበይ
ይናፍቀኛል፤ አንድ ጊዜ እዚህ ሲዊዘርላንድ ሁለተኛው የቲያትር ኮርሴ የመንገድ ላይ ቲያትር ስልጠና ነበረኝ፤ እና የተሰጠን የወል
እርእስ "የልጅነት ጊዜ በልጅነት ሰብዕና" የሚል ነበር።
ለመሥራት ስጀምረው ዕንባዬን መቆጣጠጠር አልቻልኩኝም። ትወናው በአማርኛ እና በጀርመንኛ ስለነበር
እንኳንስ ሊቀናበር ቀርቶ ሲቃው የትምህርት ባልደረቦቼንም አወከው እና ሌላ እርእስ ጉዳይ ለእኔ ብቻ ተነጥሎ ተሰጠኝ፤ ያም ቢሆን
ሌሎች ሲተርኩት መቋቋም አልተቻለኝም። እንግዲህ ሙሉ ዕድሜ ላይ ሆኜ ነው ይህን ሰቀቀን መሸከም ያቃተኝ። ምን ለማለት ነው ይሄ
አጀንዳ አብሮ አደጌ ሲሆን በመሪር ሃዘን ውስጥ አብሮኝም ያለ ነው … አባቴ እና እናቴ አብረው ጎን ለጎን ሲቀመጡ፤ ሲበሉ ሲጠጡ፤ ሲስቁ እንደናፈቀኝ የቀረ ህልሜ ነው።
... እናም ታዳጊ ወጣት ስሆን ምን አለ እግዚአብሄር ሁላችንም ሙተን ሰማይ ላይ አብረን እንድንኖር ብታደረግን
የማለት ሃሳብን እንደ ፍለስፍና ይዤው አደግሁኝ። አንድም ቀን በህይወቴ እግዚአበሄርን አኑረኝ ብዬ ጸልዬ አላውቅም። መኖርን በቃኝ
የማለት ሽል የተጸነሰው በእናት እና አባቴ አብሮ አለመኖር በደረሰብኝ የውስጥ ቁስለት ነበር። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር አብረው እዬሳቁ ሲሄዱ እራሱ አብሬ እስቃለሁኝ ጉዳዩን ሳልሰለማው ... ምን አልባት በመንፈስ አብሬ ብሆን በማለት።
እብዬ እናቴ እጅግ ደግ ናት ናት ማንም ጎንደር የሚያውቃት ሁሉ ካልዩነት ሃሳብ የሚፈርምላት
ሁሉንም እንደ እድሜው የምትይዝ ሰው ቤቱ የሆነች ናት፤ አቨዬ ደግሞ
ጭምት በዝምታው ወስጥ ዓለም ዜና እና ከመጸሐፍት ጋር የታደመ ገለል
ብሎ ለመኖር የፈቀደ ብዙም እሪካ ሪካ የማይወድ የሥጋ ፈቃድ የማይነካካው ጨዋ ነበር፤ ግን ስለምን ተለያዩ? ይህ ይጨንቀኝ ነበር።
ስለሆነም አቨይም እብዬም ለእኔ እኩል ናቸው። ሁለቱም ለትምህርት እኩል ግንዛቤ አላቸው። ሁለቱም
ይሳሱልኛል። ግን እኔ እና አፋቤት የቀረውን ታናሽ ወንድሜን አብሮ ለማሳደግ ምን አገዳቸው? ለያውም እኔ የስለት ልጅ ነበርኩኝ፤ በዛ ላይ ጤና አልነበረኝም?
እግዚአብሄር የጠዬቁትን ከሰጣቸው በኋዋላ ስለምን ተለያዩ? ለያውም አቨይ እጅግ ዘመናይ ስልጡን አንድም ቀን ከረባት ከአንገቱ ተለያይቶ
የማያውቅ በዛ ጀርጋዳ ቁመቱ ልክ ያ ገበርዲን ሞዴል ያደረገው፤ አኗኗሩ ዘመናይ፤ ቁመናው ልዩ ሲሆን እብዬ መደበኛ ት/ቤት አቋርጣ ነው ትዳር የመሰረተችው፤ አጭር ፍልቅልቅ ጉልላት
የመሰለ ዓይኖቿ የሚያበራ ገጽ ፎለቄ ሳቂተኛ ደማም ዓይነ ግቡ ናት ፍጹም ደጊት፤ ግን ስለምን ተለያዩ?
በመለያዬታቸው ምክንያት በሁለቱም ወገን ትደርሳላች ካሉበት ደረጃ ሳልደርስ መቅረቴ ሚስጢሩ ይህ
ነበር። እነሱ ሲለያዩ ህልማቸውም አንብሮ ተፋታ። አሳዛኙ ነገር በወድድር አሸንፎ የተጠራሁበት ሥም በራሱ የፈተና ቋት ነው የሆነላቸው። አዎን/ የእኔ ሥም በድምጽ ብልጫ
በቤተሰብ ዕድምታ የተወሰነ ነበር። ሩቅ አልመው ነበር ያወጡት ... ግን ምን ይሆናል ፈተና ብቻ …
የሆነ ሆኖ በማናቸውም ሁኔታ በዚህ አጀንዳ ላይ ሰፊ አትኩሮት አለኝ። የውጪ የትምህርት ዕድል
አግኝቼ የተውኩበት፤ ባለፈው እንዳጨወትኳችሁ ቁልፍ ከሆነ የመጨረሻው የመሪ አካል በትጋቴ ተመርጬ አብሬ ቁጭ ብዬ ለረጅም ጊዜ ተዋይቼ "ምን ላርግልሽ" ሲሉኝ ወደ ባዕቴ ልመለስ ከገበሬ ጋር ልኖር እፈቅዳለሁ ያልኩበት ሁኔታ ሳስበው ያው የሁለገብ ሃላፊነት ግዴታዬ ሰፊ
ስለነበር ነው። ብዙ ነገር ያሥራል ወላጆች ልጆቻቸውን አብረው ለማሳደግ ካልወሰኑ። አጭር እሳቤ ብቻ ይሆናል የህይወታቸው አውራ።
ለዚህም ነው በአንድ የኮሚኒቴ ራዲዮ የልጆች የራዲዮ ፕሮግራም እዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀመርኩት፤
ከዛም በጸጋየየ ድህረ ገጽ "የሎሬት ተስፋ" የልጆች ፕሮግራም እና የወላጆች የልጆች አገልግሎትን በሚመለከት አንዳንድ ነጥቦችን ለመነካካት
የሞከርኩት፤ በጸጋዬ ራዲዮም ሽልማቶቻችን በሚል አንድ የፍቅራዊነት ፕሮጀክት ጀምሬም ነበር።
ይህም ብቻ አይደለም ከዚህ በሰፋ ሁኔታ ለልጆች ሁለት መጸሐፍ፤ ወላጆች የልጆቻቸውን ተስፋ እንዴት
ቀድመው ማደራጀት እንዳለባቸው፤ እንዴትስ ማስተዳደር እንደሚገባቸው ጠቋሚ ሃሳቦችን የያዘ "የተስፋ በርን" የጻፍኩት፤ ከዚህም በዘለለ
ወላጆች ትዳራቸውን በሚገባ በያዙ ቁጥር የትውልድ ታላቅ ሃላፊነት መወጣታቸው ስለመሆኑ ያመሳጠረ ለባለትዳሮች፤ ትዳርን ለሚያስቡ
እጮኛሞች „ርግብ በርን“ የጻፍኩት።
ልጆች በጋራ ከወላጆቻቸው ጋር ከላደጉ የብዙ ፈተና ተጋፋጭ ነው የሚሆኑት፤ ትልቁ መከራ ህይወትን በቀላል የማዬት ችግር ይገጥማቸዋል። ህይወት
የማትፈታ የማትደፈር ሆና ነው የምትታያቸው። ምን አልባት ዕድል ቀንቷቸው የፖለቲካ ሰው ከሆኑ ብቻ የተሻለ ዕይታ
ሊኖራቸው ይችላል። ፖለቲካ ፈቅዶ መፈተን ቢሆንም ከብረት ቁርጥራጭ የተሰራ ሰብዕናን ያጎናጽፋል።
የሆነ ሆኖ የልጆች ነገር እሰከ ዕለቴ ህልፈቴ ድረስ ከውሰጤ የማይጠፋ ጉዳዬ ነው። ሌላው ቀርቶ
ከውጪ የተወለዱ ልጆችን በመያዝ እረገድ በአባቴም በእናቴም ጥሩ ተምክሮ ስላለኝ ያን የወረስኩበት መንገድ ስለምን ውጪ በተወለዱ
ልጆች ላይ እንጀራ እናት እንጀራ አባት የሚለው መንፈሱ አሉታዊ ሊሆን ይችላል የሚል ሁሉ ሰፋ ያለ እይታ አለኝ።
በልጅነት የሚቀረጹ ነገሮች ካለ
ነጋሪት ጋዜጠ በፈቃድ፤ በህሊና የሚታተሙ ናቸው። እናቴም ለእንጀራ ልጆቿ፤ የልጅ ልጆች ሳይቀር፤ እንጀራ አባቴም ለእኔ፤ እንጀራ
እናቶቼም ለእኔ ያላቸው ልዩ ፍቅር፤ አክብሮት አሰተዋይነት ብዕሬ ለመግለጽ አትችለውም። የታደሉ ናቸው ግራ ቀኙ። ሳነክም አላገኘሁባቸውም በእኔ ሰብዕና አያያዝ፤ ባይታዋር አድርገውኝ አያውቁም፤ ለደቂቃ። ስለዚህ ከውጭ ለሚወደሉ ልጆችም እድሉ የገጣማቸው የተገባቸውን ሰጧቸው ቁጥር ትልቅ አሻራ እንዳለው በዚህ አጋጣሚ ላሳስብ እወዳለሁኝ።
- · የመዳረሻ ጭብጥ፤
ዛሬ እጅግ ያዘንኩበትን የሰሞናቱ ሁኔታ ለማስቀኛት አስቤ ነው መጓጓዣውን ያስቀደምኩት። የቆሞሱ
የኢንጂነር ስመኛው ልጆች አንጀቴ ውስጥ አሉ። እኔ ወላጅ እናታቸው አሁን ያሉበት ድንገተኛ የሃዘን ሁኔታ ሆነ፤ የተከደነው ነገር ብዙም አጀንዳዬ
አይደለም። ባለሙያዎች ስላሉበት፤ ብቻ ግን እናት እናት መሆኗን አውቃለሁኝ አስገዳጅ ነገር ካልገጠማት በስተቀር። ነገር ግን አገራዊ ተልዕኮ ያለው የትዳር አጋር ያላት አንዲት አንስት ማስቀደም
ያለባት የራሷን የግል ፍላጎት መሆን አልነበረበት። ባትማረው ጥንቅር ቢልስ? ልጆቿ ናቸው ክብሯ ድግሪዋ ዕሴቷ። ግለኝነት እና እናትነት
አብረው አልተፈጠሩም።
ግለኛ የሆነች እናት ቀድሞ ነገር መክሊቷን ለዛውም የፈጣሪ ሥጦታዋን ገድላዋለች። ጀርመንኛ ለምትችሉ ወገኖቼ የ6 ደቂቃ ፊልም ስለ እናት የሠራሁት አለ። ብቻዋን ልጇን ስለምታሳድግ እናት፤ ለዛውም ስደተኛ ካንፕ ሆና ብቻዋን። ... ልጆች እኮ ከሁሉም የላቁ ስጦታዎች ናቸው። ስጦታ እንደ አልባሌ ነገር መታዬት የለበትም።
https://www.youtube.com/watch?v=vAJk4hYoaKE&list=PLBnaFEncxyNfuRqJSALv9zTCXJTUf0nOHd&index=2
Die Mutter (The mother - እናት ) Sergute Selassie.
በትውስት ሰብዕና የተለጠፈ ነው ግለኝነት ለእናት። „ለላም ቀንዷ አይከብዳትም የሚለውም ብሂል
ከዚህ የመጣ ነው። እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያን ሁሉ በርሃ ለበርሃ የተንከራተተችው ለልጇ ለአማኑኤል ነው። „ጎሺ ለልጇ ስትል ተዋጋች“
የሚባለውም ለዚህ ነው። ካንጋሯ አንቀልቧ ከሆዷ አብሮ የተፈጠረውም በዚህ ነው። እናትነት ጥልቅነት ነው። እናትነት ሚስጢርነት ነው።
እኔ እኮ ውጪ አገር ለፖለቲካል ሳይንስ ትምርት የጎንደር ክ/ ሀገር ኢሠፓ ሥ/አ/ኮሜተ ራሺያ
እንዲሄድ ሌሊት ነበር ስብሳበውን አካሂዶ ጉዳዩ አስቸኳይ ስለነበር ሲደወልልኝ አላቅማማሁም እህቶቼን ለማን ጥዬ አላደርገውም
ነበር ያልኩት። ሦስት እህቶች፤ አንድ ወንድም አንዲት እናቴን አስተዳደርን ነበር።
እኔ ነኝ የገቢ ምንጫቸው፤ መሃዬ ለ10 ቀን ቢዘገይ ማሰተዳደርም አልችልም፤ ያው በደሞዝ ነው
የምተዳደረው ዘርፎ መኖር ቀርቶ ሁሉ ለተመራበት የቀበሌ 16 የቦታ ምሪት እንኳን እኔ፤ ጓድ ገጻህኝ ወርቄ እና ጓድ ዘርጋው አስፈራ
ብቻ ነበር ቦታ ለመመራት ያላመለከትነው። ምን ሊያደርግልኝ? ሳልፍ አንዲት ሰኔል እና ቹቻ በቂዬ ናት። ቁስ ትርፍ ነገር ነው ሥም ግን ማህተም ነው።
የሆነ ሆኖ መከራ በእኔ ማብቃት ስለነበረበት እህቶቼ ተንከባክቦ ማሳደግ ትውልዳዊ ድርሻዬ ነበር። የዛን ቅን ታላቅ አካል ውሳኔውን ተላልፌ ቀረሁኝ። መብሉ ብቻ ሳይሆን ሰው አድርጌ ማሳደግ ነበር ህልሜ። ሄጄ ስመለስ ምን ሆነው
እንደሚጠብቁኝ አላውቀውም ነበር። ከጎበጡ በኋዋላ ማስተካከል አይቻልም።
በቅርባቸው ስሆን ግን እማላፍርባቸው አድርጌ ሰብዕናቸውን ሙሉ ሁለገብ በማድረግ ማነጽ ዋናው ሥራዬ ነበር።
በዛ ዕድሜ ማለት ነው። ያውቃል ሁሉ ምን ዓይነት ቀንበጥ እንደነበርኩኝ። ዛሬም አሜሪካ አገር ይመስክር ጎንደርም ይመስከር። መሳደግ
ማለት ማብላት ማጠጣት ብቻ ማለት አይደለም።
ሙሉ ሰው አድርጎ ኮትኩቶ፤ ስብዕናውን በሰብነት ቀርፆ ማሰደግ ነው። ሲናገርም ሲኖርም ሲያስብም
የማያሳፍር አድርጎ ማሳደግ። ያም ቀርቶባቸው እነኝህ ሚስኪኖች የቆሞስ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ልጆች ፍሬዎች የእናት
ፍቅር እንዴት ይነፈጋሉ? ወንጀል ነው ለእኔ ይሄ።
እንዲያውም እኔ በተስፋ በር መጸሐፌ ላይ የጻፍኩት ፈታነውን፤ ወጀቡን፤ አውሎውን ችለው ልጆቻቸውን
በጋራ ማሳደግ ካልቻሉ ተጋቢዎች አይውለዱ፤ ወልደው ከተለያዩ ግን ወንጀሎኞ ናቸው ብዬ ሁሉ ጽፌዋለሁኝ።
ስለምን? ወላጆች አብረው
ሳያሳድጉ የቀሩት እና በወላጆች እንክብካቤ ያደጉ ልጆች እኩል የሥነ - ልቦና አቅም የላቸውም። ይህን ክፍተት ለሞሙላት ነበር እኔ ለእህቶቼ እና ለወንድሜ ስል ያን የመሰለ ዕድሌን ያሳለፍኩት። ትዳርም አልሻም ስል የነበርኩት ፊቱ የከፋው እህት እና ወንድም
እንዳይ ስለማልፈልግ ነበር። የመንፈስ ተጠማኝ እንዲሆኑ እህቶቼም እና ወንድሜ አልሻም ነበር። አጋሬ ተሳስቶ እኔም ባዋጣሁት ገንዘብ ነው
ያደጋችሁት ብሎ መስቃ እንዲናገራቸው አልፈቅድም ነበር። ነፃነት በብዙ መልኩ ይገለጻል እና። ነፃ የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር የሚጀምረው በቤት ውስጥ ነው።
እነዚህ ምስኪን ልጆች ሁሉንም አጥተው አደጉ፤ አባትም እናትም። ከወላጅ አልባዎቹ በምንስ ይለያሉ? አሁንም ድምጻቸውን እንኳን ሁሉንም አጥተው ሀዘን ብቻ ተሸካሚ እንዲሆኑ ተገደዱ።
አይቸግራቸውም የሚል ሞቶ አዳምጣለሁኝ። የማይችግራቸው እህል እና ውሃ ነው። ግን የወላጅን ጠረን ማንም ሊተካው ፈጽሞ አይችልም። እሚታም/ አያትም ቢሆኑ እንደ እናት እና አባት አይሆኑም፤
ይህ እኮ የፈጣሪ ሥራ ነው። የፈጣሪን ጥበብ ሰው ሰራሽ ኩነት አይተካውም። አርቲፊሻል አባባ ተፈጥሯዊውን እንደማይተካው ሁሉ።
- · ወላጃዊ ዕሴት ድርቀት።
ሌላው ግልጽ ያልሆነልኝ መሰረታዊ ነገር ከአባታቸው ከእናቸው ጋር የነበራቸው የቆሞሱ እንጂነር
ስመኘው ጉዳይ ስለምን አሁን ለአዳባባይ በቃ የሚለውም ሌላው ጉዳይ ነው። የተለመደ ነው አንድን ወፍራም ወንጀል ለመሸፈን ሌላ
ሳንክ ፈጥሮ በዛ ላይ የቤት ሥራ መስጠት።
የሆነ ሆኖ ይህ የቃል ኪዳን ሰነድ በድርድር ወይንስ በፈቃድ የተከወነ ይሆን? በምን አስገዳጅ ሁኔታ ነው በተነጠለ መንፈስ ይህ ሁኔታ ሊፈጠር ያቻለው?ይህም ሌላ የማይታወቅ
አምክንዮ አለበት ግምሽ ጌጥ ህይወት ነበርን ድሉ? ደስታን ከቤትህ፤ ከቤተሰብህ፤ ከአካባቢህ ካልጀመርከው የት ይጀመር? እትብታቸው
የተቀበረው ጎንደር ነው ስለምን መነጠልን ፈለጉት?
እናታቸው መነኩሲት እንደላቀሱ አልፈዋል ይላሉ አባታቸው መንኮሲው። አባታቸው ደግሞ በመከራው በምርኩዝ ተገኝ ተብለው የሚዲያ ማሙቂያ
ሆነዋል፤ አንድም ቀን ለዓይነ ሥጋ ሳይበቁ፤ አንድም ቀን ምርቃት ሳይገኝ፤ አንድም ቀን አባታዊ እናታዊ ወግ ሳይደርሳቸው አሁን የ ዕንባ ቤተኛ መሆን። እንዴት ዓይነት አተሪክ ነው?
የሚዲያው አጀብ ከዛ በፊት በሽልማታቸው እንዲገኙ አልተደረገም። ግልገል ጊቢ አንድ እና ሁለት ሲመረቀም አባት የክብር እንግዳ አልነበሩም።
ወንድማቸው ቢያሳድጓቸውም ወንድማቸውን የሰጧቸው ወላለጆቻቸው ናቸው። አብዛኛው የጎንደር ልጅ በዚህ መልክ ነው የሚያደገው። የፖለቲካው ማገዶም ታክሎበት። ጎንደር ስጋት ስላለ ልጆችን ዘውር አድርጎ ማሳደግ የተለመደ ነው ...
የማይረሳው የሰው አብርክ እና ማህጸን ፍሬ ነው ሰው መሆን። እትብት መንደርም አለ። እንኳንስ የተወለዱበት በሥራ ምክንያት የሚያውቁት እንዴት ይናፍቃል፤ አሁን እኔ ጢቾ በቆጂ ይናፍቁኛል።
ስለምን? እኔ እነሱ ሚስጢራዊ ኑሮን ተጋርተናል።
ለነገሩ ትውልዱ ምን መርዝ እንደተረጨ አይታወቅም። ለምንም ነገር ጊዜ የለውም። ይህ መራራው
ዘመን የሚያሰኝ ነው። የ እህት ልጅ ማለት ምንም ነው። ምን የእህት ልጅ አህት ማለት ራሱ? ወንድም የ እናት ልጅ ማለት በራሱ።
ከቁጥርም መሰረዝም አለ። በዚህ ሁሉ ነገር መጪው ጊዜ የቤተሰብ ዕሴት እዬከሰመ ስለሆነ እጅግ ፈታኝ አምክንዮዎች ትውልዱን ይጠብቁታል። የተቋረጣ ነገር
አለ።
ቤተሰባዊ ማሳከፋት እና መከፋት። አስታራቂ እለተገኘላቸውም። ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ
ትልቁ ተልዕኮ ቤተሰባዊ እሴቶችን ቀስ በቀስ ሽርሽሯቸዋል። ብዙ ሰው ስለምን ሰለሰው አያስብም ይላል። ሰው ቢክተም ነው። አላውቅህም፤
አላውቅሽም፤ ምን ስታደርግልኝ/ ምን ስታደርልጊልኝ የሚል ሰፊ የሆን ግን ረቂቅ ስውር ደባ ተከውኗል።
ቤተሰባዊ ሃላፊነት፤ ማህበራዊ
ሃላፊነት፤ ትውልዳዊ ሃላፊነት፤ አገራዊ ሃላፊነት አልቋል። ቤተሰባዊ ዕሴት፤ ማህበራዊ ዕሴት፤ ትውልዳዊ ዕሴት ወልቋል። የሚያጽናናው
ተግባር ሃይማኖታዊ ዕሴት ዘሩ አለ። ግን ለእግዚአብሄር/ ለአላህ አገልግሎት የሚተጋ መነሳት ያለበት ሰውን ውደዱ
ከሚለው መሆን አለበት። ቤተሰብህን አክብር መሆን አለበት።
ብዙ ሰው ደርግን ሲያወግዝ እሰማለሁኝ።
እኔም እህቶቼም የዛ ዘመን ታዳሚዎች ነን። በዛ ዘመን ነው ያደግነው። ትልቁ የደርግ ቀመር የማይታዬው፤ የማይዳሰሰው ያልገባን ግን
በህይወታችን የነበረው ቤተሰባዊ ሃላፊነት የሚያከስም ነገር ሥርዓቱ ያልሰራ መሆኑን ብዙ ናሙማዎች ማቅረብ ይቻላል።
ከአጤዎቹ ደርግ ትውፊቱን እንዳለ ነበር የወረሰው። የቀረጣጠፈው፤ የቀነሰው ነገር አልነበረም። ከእሴታችን ለማፈንገጥ ቢክተም የሆንበት አንዳችም ነገር የለም።
ወያኔ ሃርነት ትግራይ ግን ያን ቤተሰባዊ ትውፊት ሊያወርስ አልተቻለውም። የትውልዱ መቋረጥ
የሚጀመረው ከዚህ እንብርታዊ ጉዳይ ነው። ብሄራዊነትን ላማምጣት ቤተሰባዊ ዕሴት መነሻ ነው። መጀመሪያ የገደለው ይህን ነው ወያኔ
ሃርነት ትግራይ። ስለሆነም እናት አባት ከዚህ ያለፈ ትውልዳዊ ሐረግ ከፋይዳ አይቆጠረውም። በጣም ረቂቅ ነው። እናት አባትም ቢሆኑ በተለመደው ዕሴት ልክ አይደለም። ትርፍ ናቸው። እነሱም በዚህ ውስጥ ናቸው። ያጣናቸው ብዙ ነገሮች ናቸው። ሾልከናል።
ዛሬ ላይ ቤተዘመድ ትርፍ ተለጣፊ
ጉዳይ ነው። ጎረቤትማ ከባዶ በታች ነው። ስለምን? በወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ መርዝ ሁሉም ቪክተም ስለሆነ። ለዚህ ነው ሲኖሩም
ካሳደጋቸው ማህበረስብ ወላጆች ጋር ተለይተው፤ ሲያልፉም እንዲህ ከሞቱ አሟማቱ ሆኖ ልጆች ባለቤት አልባ፤ ሜዳ በቀል ሆነው የሚቀሩት።
ይህ ማንም ሰው በውስጥነት ያለዬው፤ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በእኛ ላይ ድል ያደረገው ረቂቅ ጉዳይ ነው። በዚህ መስመር ያልተሸነፈ
የለም። እናት ሳትቀር የተፈተነችበት ክፉ ዘመን ነው።
ይህ ችግር መሆኑ ስላልታወቀ አጀንዳችንም አይደለም። አጀንዳችን ካልሆነ አሁን ዶር አብይ አህመድ በሚመሩት ካቢኔም ባለቤት አልባ ነው። ሳቢያዎቹ እንጂ መሰረታዊ ምክንያቱ
ደፋር አላገኘም። ለእኔ የህፃናት እና የሴቶች ሚ/ር
ፍሬም ውስጥ ያለ ግድግዳ ላይ የተንጠለጠለ ፎቶ ነው። በድን!
ነገም ከችግሩ አመክንዮ የመነሳት አቅም ስላልተጀመረ አደጋው ሰፊ ነው። ከችግሩ ያልተነሳ አመክንዮ
ሥራ ያለው ግን በሥራፈትነት 27 ዓመት ሙሉ የመዋቀር ሲሳይ ሆኖ የኖረ ነው።
ቢሆንማ ኖሮ የቆመሱ ኢንጂነር ስመኘው የግል ህይወት
ሰብዕና መስዋዕትነቱ እንዲህ ቀለም ጎደል አይሆንም ነበር። ለማን ነው የተጉት? ለትውልዱ ነው አይደል? ግን የራሳቸውን ዘር ትውፊት ርክክብ ሳያበጁ መሆን አልነበረበትም። ወላጆቻቸውን ረስተው፤ ትውልድ መንደራቸውን ላለማዬት ሃራም ብለው፤ ልጆቻቸውም እንዲህ በሆነ ሁኔታ አባትም
እናትም አጥተው … ይህን ስገልጸው መራራ ነው። እውነት ሁልጊዜም መራራ ነው።
አትቀመሽ መራራ ነሽ
አትጠጭም ሃይለኛ ነሽ
አትዋጭም ጎምዛዛ ነሽ
ዕውነት ደፋር ካላገኘሽ
ቃና የለሽ ትሆኛልሽ ሽሽሽሽሽሽሽሽ
ይህን አዲስ አባበ ድል ገብያ ገብርኤል እዬኖርኵኝ የተጻፈ ለህትምትም የበቃ ግጥሜ ነው። ያን
ጊዜ ግጥሞቼ በሙሉ ዕውነት ተኮር ነበሩ። ዕውነት በዬዘመኑ ፈተናዋ አያልቅም፤ ተወዳጁ ጉዳይ ብታሻነፍም ብትሸነፍም እሷ ግን
ከባለማሎቿ ጋር ትኖራለች።
ይህ መከራ ዘላቂ ነው። የኢንጂነር ስመኘው ልጆች ካለወላጅ ማደግ፤ ደመ ከልብ አባት መኖር፤
ቤተሰብ አልባ መሆን በሥነ -ልቦናቸው ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ቢያንስ እስከ ሦስት ትውልድ ድረስ ዘራቸውን ተጎጂ ያደርገዋል።
ልጆቹ
ሁሉንም ነገር ፈረተው ያድጋሉ። ልጆቹ ደስታ አልባ ሁነው ያድጋሉ። ልጆቹ ሁሉንም ሰው ተጠራጣሪ ሁነው ያድጋሉ። ልጆቹ ትዳርን ፈሪ
ሆነው ያድጋሉ። ልጆቹ የመኖር መርሃቸውን በግፍ ተነጥቀዋል።
የመጀመሪያ ልጃቸው ወጣት ነው እስከዚህ ዕድሜው ድረስ በእናቱ ወገን ያሉትን እንጂ የአባቱን
ወገን አያውቁም። ግንጥል ጌጥ ነው። አብሶ የአባታቸውን እናት፤ አባት የተፈጠሩባትን መሬት ታሪኩንም አያውቁትም። ግን ስለምን?
በምን ዓይነት የፖለቲካ እሰረኝነት እና ውል ነበር ይህ እንዲሆን ግድ የሆነው? ታሪክና ዘመን ይመርምረው።
- · ልመና በአጽህኖት!
እኔ ለወላጆች እጅግ ዝቅ ብዬ አማሳስባችሁ የፈለገው ፈተና ይኑር፤ አግብታችሁ ከወለዳችሁ በኋዋላ ግልኛ አትሁኑ። ፈተናውን ታግሳችሁ ልጆቻችሁን አብራችሁ አሳድጉ። አብሮ በማሳደግ ወርቅ
አይዘንብም ግን ነገን ማዬት ትችላላችሁ። እባካችሁን አትፋቱ? ወይንም ከገሃዱ ዓለም የትምህርት፤ የቀጣይ ዕድገት ብላችሁ ልጆቻችሁ
የእናንተን መስዋዕትነት ዕዳ እንዲሸከሙ እባካችሁን አታስገድዷቸው? ልጆች ያራሳቸውን ህይወት ይነሩ ዘንድ ፍቀዱላቸው። ቢያንስ ቤት ውስጥ
ወይ አባት ወይ እናት መኖር ግድ ይላል።
- · ባለ አራጣ ዕዳ።
በቤት ሠራተኛ እያሰደጉ ልጅ አለኝ ማለት? ገራሚ ዕዳ ነው፤ አደራውን መወጣት የተሳነው ባለ አራጣ
ዕዳ። ለዛውም ውስብስብ ፖለቲካ እኮ ነው ነገረ አባይ? ብዙ መመከር ብዙ መዘከር አለበት ከውሳኔ በፊት። ብዙ የሚተጉ ሰዎች በአገር
ጉዳይ ትዳር የላቸውም፤ ልጅም አይወልዱም።
አሁን አቶ ልደቱ አያሌው ፈንገጥ ያሉ ሰው ናቸው፤ በፖለቲካም ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ
ኑሮም፤ የግል ስብዕናቸው በመኖር ውስጥ ህይወታቸውን የሚመሩበት መርህ ደግሞ የሚገርም ነው።
እጅግ ያስደሰቱኝ ከዛ ከደግነት በኩራት አቶ ዮሴፍ ገበሬ ጋር በነበራውቸው ቆይታ ሲገልጹ አግብቼ ወልጄ ቢሆን ኖሮ ልጆቼ ያን
ማህበራዊ ቀውስ እንዲሸከሙ ይገደዱ ነበር ብለዋል። ልክ ናቸው። ትክክለኛ እርምጃ ነው። ግለኛ አይደሉም ማለት ነው። አቶ ልደቱ አያሌው ትዳር ባለመመሥረታቸው እና ልጆች ባለመውለዳቸው የሚያጡትን ሐሤት አስቀድመው የወሰኑበት መንገድ ትውልዱን አድኗል።
ልጅ መወለዱ ብቻ ሳይሆን በወላጆች የፖለቲካ፤ የማህበራዊ፤ የኢኮኖሚ ተሳትፎ ሳንክ ከኖረበት ሰብዕናው፤ ሥነ - ልቦናው ያልተሟላ ልጅ ከሆነ ሸክም ነው። ልጆች ሲያድጉ በወላጆቻው ቁርሾ ተወቃሽ፤ ተነቃሽ መሆን አይገባቸውምና። ካልተወለዱ ሸክም የለባቸውም። "አልወድም" ያለው ደራሲውም ለዚህ ነበር። ይህ ዘመን በምናብ ታይቶት ...
በዚህ ዘርፍ ያልተወለዱትን ልጆቻቸውን፤ ያላታሰበችውን የትዳር አጋራቸውን ከቀደመ መከራ የታደገ ብርቱ አብነታዊ ተግባር ፈጽማዋል አቶ ልደቱ አያሌው። የራሳቸውን ደስታ ቀብረው ማለት ነው። ለዚህም ነበር ቃለ ምልልሱን ወደ ሦስት ጊዜ ላዳምጠው የፈቀድኩት። ከዛ በኋዋላ በፖለቲካ አቋማቸው ላይ የማወርደው ማት በረድ አለ። እንዲያውም ረሳሁት ማለት እችላለሁኝ። ስለ ልጆች ማሰብ ስለ ትውልድ ነውና ... የቤትህን መከራ ሳታሸንፍ ማግስትን ማሰብ ህልም ነው ... የራስህን ሰብዕና ሳታርቅም ከጀመርከው ውርስህ እዳ ነው።
ለልጆች ህሊና አስቀድሞ ማሰብ፤ መጨነቅ፤ መጠበብ አስቀድሞ በርቀት መተንበይ ይገባል። ለትዳር አጋርም ከሚመጣው ፈተና
አስቀድሞ ማሰብ ይጠይቃል። ከወለዱ በኋዋላ ደግሞ የልጆችን ህሊና በአንድም በሌላም የማያሰቀቅ መሆን አለበት። ግለኝነትን ተግ አድርጎ ለትዳር ህገ ደንብ ራስን ማስገዛት።
በተቻለ መጠን ወላጆች በሰብዕናቸው
ውስጥ የልጆቻቸውን ነገር እንደ ማዕከላዊ አጀንዳ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ነገን ማሰብ። ልጆች እኮ ዘር አልባ ሆነው ሊቀሩ ይችላሉ። አገር የለኝም የማለት
መንፈስ ሊያድርባቸው ይችላል። ለነገሩ ይህን በሚመለከት ብዙም አልተሠራበትም። ለዚህ ነበር እኔ በዚህ ተኮር የሆኑ መጸሐፍትን ለመጻፍ
የተገደድኩት። ግን ምን ይሆናል በጉልበተኞች ታግቶ ካዝና ያሞቃል።
በልጆች ጉዳይ ላይ ብዙ የሚመረምሩ አመክንዮ አሉ። አሁን እነኝህ የተባት ፆታ ያላቸው ልጆች
ዕድሜ ልካቸውን የውስጥ ሰላም አይኖራቸውም። ሌላውም ገዳዩ ማለት ነው እነሱ አድገው ያጠቁኛል በሚል ሌላ የተከዘነ መከራ ይጠብቃቸዋል።
በዚህ ላይ ሁነኛ የላቸውም። ሁነኛ መኖሩ ብቻውንም በቂ አይደለም። መንገድ መሪ መሃንዲስ ካልኖረ …
ሲጠቃለል ማን ይግደል ማን?
ማን ያስገድል ማን? መከራውን ተሸካሚ እነዚህ ሦስት ልጆች ናቸው። መከራው ደግሞ የማዋለ ዕድሜም ነው። እና ከመፈጠራቸው ይልቅ
አለመፈጠራቸው የተሸለ ነበር። እድሜ ልካቸውን በመንፈስ ታሥረው ነው የሚኖሩት።
ዕድሜ ልካቸውን በህሊና ተቀፍድደው በካቴና ነው
የሚያሳልፉት። ይሄ የደም ጉዳይ ከልብነትም ከአንጀትም የሚወጣ ጉዳይ አይደለም። ሞጥረን እንርሳ ሊባል የሚችላው በሁሉም ወላዊ በሆኖ
ፖለቲካዊ ቀውሶች ችግር እንጂ የግል ህይወት ላይ ያነጣጠረው ከሆነ አደጋው እጅግ ሰፊ ነው።
እነኝህ ልጆች እሰረኞች ናቸው። የሚፈቱበት ቀን ሳይኖር ይኖራሉ። መኖር ታስሮ በታሰረ መኖር እንዲኖሩ የተፈረዳባቸው ምንዱባኖች
ናቸው። ከሁሉም የመጀመሪያ ልጁ የመከራ ቀንበሩ የፊት ለፊት ረድፈኛ ነው። የመሰናክል ሩጫ መዳራሻው መሰናከል … ያልታደለ ቤተሰብ፤ ባክኖ የቀረ … ሞቱ የአንድ ሰው ብቻ አይደለም እስከ ልጆቹ ድርስ ነው። ነገም የእነሱ አይደለም።
ምን ባደረጉ ነው ልጆች ለዚህ ውስብስብ የፖለቲካ ፍጆታ የሚውሉት? አባታቸው መነኮሰ ሞተ ስለሆነ
የሚመጣባቸው ምንም ነገር የለም። በዛ ላይ የለመዱት ነገር አለመኖረ ራሱ ጽናት እንዲኖራቸው ያደርጋቸዋል። ለልጆች ግን ከኢትዮጵያ
ህዝብ ንጹህን ፍቅር በገፍ ቢታደሉም ያን የውስጥ መከራ እና የወደፊቱን ረመጣዊ ዳመናዊ ህይወት ለመሻገር አሁንም አሁን ሁነኛ አለማግኘታቸው
እጅግ አሳዛኝ ነው። ቢያንስ እናት?
ለዚህ ነው እኔ የአቶ ልደቱ አያሌውን ውስኔ የተገባ የምለው። የማታሳድገውን ልጅ አለመወልድ ብቻ
ሳይሆን በውስብስቡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ ቀደመው በትዳር ህይወት ላይ ሊወሰኑ የሚጋባቸው ግዙፍ ተደሞዎች አሉ። ሁለት
ወዶ አይሆንም። ፈቅዶ ከቤተሰብ ጋር መለያዬት አንዱ የፈተና ፈርጅ ነው። ስልክ ባለመደወል፤ ግንኙነትን በማቋረጥ ውስኔ ላይ ናፍቆትን፤
ትዝታን ማሸነፍ ይጠይቃል ለተማለዎችም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሴራ ተፋቶ ለማዬት ሆድ ይፍጀው ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴራ ጠጥቶ ነው ያደገው።
ለዚህ መሰል ውሳኔ ደግሞ ድፍረትን ይጠይቃል። የራስን ዕዳ እራስ የመሸከም አቅም አምጦ ሳይወልዱ
በዚህ መሰል ችግር ውስጥ ልጆችን ካለ ዕዳቸው ካለ አቅማቸው ተሸክሞ ብሎ መፍረድ እንደ ሰው ፈታኝ ነው። ሃጢያትም ነው።
ከዚህ ላይ ለአማራ ሊሂቃን የማስገነዝበው አንድ ቁምነገር አለ። ይህ የቆሞስ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ህይወት ህልፈት ብዙ አስተምህሮት አለው ለአማራ የህልውና ተጋድሎ ብዬ አስባለሁኝ።
እኒህ ታላቅ ብሄራዊ አሳቢ የኖሩት ለአገር ለወገን ብቻ ነው። በርሃ ለበረሃ ክልትምትም ሲሉ የኖሩት ለ ኢትዮጵያዊነት ነው። ለራሳቸውም፤ ለልጆቻቸውም፤ ለወላጆቻውም አለሆኑም። ሲያልፉ ግን መከራው ለራሳቸው አሟሟታቸው እጅግ አሰቃቂ እና ክብርን የደፈረ፤ ለወላጅ አባታቸው እና ለልጆቻቸው ተስፋ አስቆራጭ አደጋ ነው የሆነው።
የሰው ልጅ መጀመሪያ ከራሱ መጀመር ከተሰናው መጨረሻው በዚህ መልክ ይደመደማል። አማራነት እና ኢትዮጵያዊነት ፈተናውም ይሄው ነው። አማራነትን ሳትቀበል ኢትዮጵያዊነቴ ካልክ ይህ ተመክሮ ተቋም ከፍቶልሃል። ኢትዮጵያዊነትህ አቅም ኑሮት የሚያስከበርህ አንተን አማረነትህን ማክበር ስተጀመር ብቻ ነው። ርግጠኛ ሆነህ እኔ አማራ ነኝ ማለትን ሳትደፈር ክብርና ኩራቴ ይቀጥላል ብለኽ አተሰበው።
ከራስህ መንፈስ ከሾለክ ከልብ ነህ። ልብ ካለህ፤ ህሊናህ ነገን ማሰብ ከተቻለው። ... ከዚህ በላይ መሄድ አያስፈልገኝም።
የልጆች ተስፋ ነገን ማቃናት ካልቻለ ትርፉ የውርንጫ ድካም ነው።
የኔዎቹ ለነበረን መልካም ጊዜ ኑሩልኝን ልሸልም።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ