ነፃነት ከኖረ ድል ከሃሳብ አቅም ይመነጫል።

ሃሳብ የማያቋርጥ ጅረት ወይንም ፏፏቴ እንጂ የታቆረ የኩሬ ውሃ አይደለም!
„እሱን እግዚአብሄር ስለመረጠው ጌትነቱ
እንደ እጁ ሥራ ነውና ባለመድኃኒትን አክብረው።“
መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፴፰ ቁጥር ፩

ከሥርጉተ©ሥላሴ
31.08.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ


                                 ትውልድ በፍቅር ማዋህድ የአብይ ሌጋሲ ነው! 
ስለዚህም ሊከበርም- ለወደድም ደሊደነቅም ይገባል። 
ነገን በፍቅር ማሰብ፤ በእዮባዊነት መቀመር መክሊቱ የእዮር ነው። ተመስገን! 

43 ዓመት የተባከነበትም የተተረፈበትም፤ የተጎዳንበትም የተጠቀመንበትም ዘመን ታይቷል - ተፈትሿል። እግዚአብሄር በቃችሁ ሲለን ይህን ዘመን አመጣልን። በዚህ ዘመን ያኮረፉ እንዳሉ ይታወቃል። በዚህ ዘመን ምንም ለውጥ አልመጠም የሚሉ ወገኖችም እንዳሉ ይታወቃል። በዚህ ዘመን የተሻለ ዘመን መጥቷል የሚሉም አሉ። 

በርከት ያለነው ደግሞ የተሻለ ሳይሆን የ43 ዓመቱን ዘመን የሚያስንቅ ብሩህ ተስፋን የሰነቀ ነው የምንል ደግሞ አለን። ሰዎች እንደመሆናችን ስለምን ሬድ ሜድ ሃሳብ አልኖረንም ሊባል ግን አይገባም።

በሌላ በኩል መልካም ነው በርቱ የምንል አለን፤ መልካም አይደለም የነበረው ይሻል ነበር የሚሉም አሉም። ከነበረውም ከአሁንም ያልሆኑ ወገኖችም አሉ። ወለሌ ገበታ ላይ ያሉም አሉ። ይህም ቢሆን የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ስለመሆኑ ስለሚያጠይቅ ተስፋ አስቆራጭ አይደለም። 

በሌላ በኩል ደግሞ ፍጽና የሚጠይቁ ሰዎች አሉ፤ ሌሎች ደግሞ ፍጹም የሆነ የተባረከ መንገድ ነው የሚሉም አሉ፤ ጥቂት የማይባሉም ፍጹም ነውም አይደለም የማይሉ አባ እና እማ ዝማታዎችም አሉ። ማዕዶታችን ሰፊ ስለሆነች ሁሉንም የማስተናገድ አቅም አላትና እንደ እናት እንደ ባህሪያችን ይዛናለች። ነፃነት ካለ ድል ግን ከጉለበታም ሃሳብ ነው የሚመነጨው ተስማማንም አልተሰማማንም ... 

ከእንግዲህ በምን አጀንዳ እንወያያለን፤ ስለምንስ ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣል፤ ስለምንስ ህዝባዊ ስብሰባ መካሄድ ይኖርበታል የሚሉም አሉ። ይህም ትክክል አይደለም። ዴሞክራሲ ሂደት ነው። ለሂደት ደግሞ የሃሳብ ፍጭት፤ የሃሳብ ፍትጊያ ያስፈልጋል። ዛሬ ጠንካራ የሆነው ነገ ሊደክም፤ ደካማ የነበረው ሊጠነክር የሚችለው በሃሳብ መደጋገፍ እና ወደ ተግባር በሚቀዬሩ የሃሳብ ቅምጥ ሃብቶች ነው። መዋለ ንዋይን አንድ ነገር ላይ ለማዋል የሃሳብ መዋለ ንውያ ያስለፈልጋል፤ የተደራጀ፤ የተቀናጀ፤ ቅደምተከተሉን የጠበቀ። 

ሰው ሃሳቡን አውጥቶ ካልተናገረው በዝምታው ወስጥ ከሰከነ የተቀበረ ፈንጅ ማለት ነው። ስለዚህ ሃሳብ እንዳሻቸው ወጥተው እንደፈለጉ ሆነው ግን ከህግ በላይ ሳይሆኑ በራሳቸው ማሳ ሃሳቦች በነፃት ሊፎካከሩ ይገባል። የሃሳብ ጥራት በሃሳብ ፍትጊያ ነው የሚገኘው። ሃሳብ መፈራት አይኖርበትም። ሃሳብ በተደፈረ ቁጥር አቅጣጫው የለዬለት ጉዞ ላይ ስለመሆናችን ተረገጡን ማግኘት ያቻላል።

የተኖረበት የሃሳብ ተፋስስ በበላይነት እና በበታችን፤ ወይንም ባይነካም እና በይነካል፤ ወይንም ማን ደፍሮኝ እና እንደፈረዋለን በሚሉ የሃሳብ ማህበርተኛ ወገኖች ማሃከል ነው የተኖረው። በዬትኛወም መስፈርት ቢሆን ሃሳብ ሳይፈራ የተኖረበትን ዘመን አላስታውሰውም። ደፋር ሃሳቦች ከአጀንዳ ውጪ ናቸው። ደፋር ሃሳብ አቅራቢዎችም ከማህበረሰቡ ተገለው እንዲኖሩ የተበዬነባቸው ምንዱባኖች ናቸው።

ሃሳቤ ይብልጣል የሚለው አካል ሃሳቡ ስለመብለጡ የሚረጋግጠው ባሰለፋቸው የሠራዊት ቁጥር ልክ እንጂ በሃሳቡ አቅም ልክ አልነበረም። ይህም ምን ማለት ነው? ሃሳቡን ሌላው እንዲሸምተው የሚደረገው ባለው የሚዲያ አቅም እና ባለው የወታደር ብዛት እንጂ እሱ በሃሳቡ ልክ ፍሬአዘል ስለመሆኑ ሚዛን ላይ ተቀምጦ አልነበረም። ይህ እከሌ ተከሌ ሳይባል ከሊቅ አስከ ደቂቅ አገር ውስጥም ውጬ አገርም የአላዛሯ ኢትዮጵያ ህልውና ሲታመስበት የኖረው ገማና ነው። ሃሳብ ህልውና ሳይኖረው በደመነፍስ ነው አለሁ አለ ሲባል የተኖረው። 

እኔ በግሌ ለናሙና የማናሰው የፖለቲካ ድርጅትም፤ የፖለቲካ ሊሂቅም ወይንም ሚዲያ የለኝም። የሃሳቦች ገዢነት የንጥረ ነገሩ ጥራት ሳይሆን ባሰለፈው የደጋፊ ቁጥር ነበር የሚወስነው። በዚህ ዘመን ያዬነው ደግሞ ሁሉም ሃሳቡን የሚያቀርብበት ገብያ ይኖረዋል፤ አበጣሪው፤ አንተርታሪው፤ አጣሪው፤ የህዝብ የህሊና አደባባይ ብቻ ነው። 

ይህ ዘመን ከቶውንም ይመጣል ብዬ ያለሳብኩት እና ያላለምኩት ነበር። ለነፃነት መታገሌን ያላቆምኩት ተስፋ የማያልቅ፤ የማያቋራጥ መሆኑ እንጂ መቼውን ቢሆን ይህን ዘመን ጋር እንገናኛልን ብዬ አስቤው አልነበረም። ምክንያቱም ሰው ከራሱ ስለሚጀመር እራሴን እንደ አንድ የምርምር ማዕከል ወይንም ኦብጀክት አድርጌ ስወስደው፤ ስደግፍም ስቃወምም ምንግዜም ጠላት ነኝ። ተሳዳጅ ነኝ። ተገላይ ነኝ። ሁለቱንም ተደጋፈውም የተቃውሞ ሃሳብም ቀርቦ እኩል ነው የሚያስተናግደው - በግለት። ማንተርተሪያ፤ ማበጠሪያ፤ ማንዘርዘሪያ የለውም። ስለዚህ ማንዘርዘሪያ የሌለው ትግል ነፃነት ያመጣል የሚል ተስፋ ብጣቂ እልነበረኝም።

በሌላ በኩል ደፋር ሃሳብ በቀረበ ማግስት እታገዳለሁኝ። ስለዚህ ተስፋ የሚባለው ነገር ወደ መቃብር መላኩን አያለሁኝ። ደፋር ሃሳቦች ቢያጠነክሩ፤ ድክመትን ቢያጠሩ፤ ጎባጣን ቢያቀኑን፤ ቀናውን ቢመክሩ፤ ኮረኮንቹን ልገው ለስላሳ አስፓልታ ቢፈጥሩ እንጂ የሚያጠፉት፤ የሚያከስሉት አንዳችም ነገር የላቸውም። 

ነገር ግን የተኖረው በዚህ መሰል ዝንቅ ድቅድቅ ጨላማዊ አቋም ነበር። ስጽፍ ራሱ ጨለማ ወስጥ እንደሆንኩኝ እዬተሰማኝ ነው። እርግጥ ነው ነገ ምን እንዴት ይሆናል ለሚለው ከ እንግዲህ በራሴ ማሳ ስለሆነ ወክ እንዲህ እንድትል ብዕሬ የሚፈቀድላት ደረጃውን መመዘን አልችልም። በቀደመው ግን ጭፍን ያለ ዘመን ነው የታለፈው ... 

ወደ የፖለቲካ ድርጅቶች ወላዊ የሃሳብ ተዋረድ ሲመጣ ሲመዘን ደግሞ አንድ ሃሳብ ተቀባይ ማግኘቱ የሚረጋገጠው እዬጨመረ እዬሰፋ ሲሄድ፤ እያደገ ሲሄድ፤ ተከታይ እያፈራ ሲሄድ ብቻ ነው። አንድ ወህድት ይባል - ጥምረት፤ ጥምረት ይባል ቅልቅል ማደጉን - መበልጸጉን ማዬት የሚቻለው ሳይቋረጥ ወይንም ሳይጎረድ ተጨማሪዎችን እያከለ ሁሉን አሳታፊ ፤ አቃፊ በመሆን የአብርሃሙ ቤት ሆኖ ሲታይ ወይንም ሲገኝ ብቻ እንጂ እዬተናደ ከሆነ በውስጡ የለም ማለት ነው። ሃሳቡም ተሸናፊ ሆኗል ማለት ነው። ይህ ሃቅ ቢመርም ስናዬው የኖርነው ጉዳይ ነው።

የሃሳብን ዘላቂ ፍሬ ማዬት የሚቻለው በጨመረው የቤት ቁጥር፤ በጨመረው የአባላት ቁጥር፤ በጨመረው እድገት ልክ ነው። እንደ ካሮት ከሆነ ግን እዬጫጫ ነው ማለት ነው። እዬከሳ ነው ማለት ነው። እዬፈለሰ ነው ማለት ነው። 

ስለዚህ ወይ መፍረስ ወይ ደግሞ ሥር ነቅል ለውጥ ማምጣት ግድ ይለዋል። ቢያንስ ጥገናዊ ለውጥ። ዛሬ ኢህአዴግ በሃሳብ ደረጃ ማለቴ ነው በቁስ ወይንም በፋይንስ አቅሙ ማለቴ አይደለም በሃሳብ ደረጃ ከዜሮ ደረጃ ተነስቶ በህዝብ ዘንድ ሊደመጥ የተፈቀደለት አውራ የመሆን ዝንባሌ ነው ያለው ግንባር እዬሆነ ይመስላል ... ተፎካካሪዎች ለመፎካካር አለቸው ዕድልም የዚያኑ ያህል ፈታኝ ነው። ለዛውም ከነበሩበት ምንም የተሻለ ሃሳብ የማፍለቅ ዝንባሌ አይታይባቸውም ... 

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የሚመራው ሚዲያውም ከዜሮ ተነስቶ የሚናፈቅ ለመሆን መንገድ ጀምሯል። እድገት ለውጥ ማለት በዚህ ይታያል። ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንመለስ ባዮች ከመጋቢት 24 ቀን 2010 በፊት የነበረውን የሚደያቸውን አድማጭ ቁጥር ብቻ ለናሙና መወስድ አለባቸው። ምን ያህል አዲሱ የለውጥ ሃሳብ በምጥቀት ላይ እንዳለ ይነግራቸዋል።

ሚዲያ የሃሳብ ገብያ ነው። በዚያ የሃሳብ ገብያ ፈቅጅ ተሳታፊው የአንድ ወገን ብቻ እንጂ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ አልነበረም። አሁን ግን አይደለም እኛ ዓለምም እያስተረጎመ እዬታደመበት ነው። ሌላ ማስረጃ ሳያስፈልግ ሚደያቸውን ማዬት ነው። የሚሰጡትን አስተያዬቶችን ቀናነት ሚዛንም መለካት ነው።

ባለፈው ሳምንት አንድ በድብቅ የተቀዳ የሚል የዶር አብይ አህመድ የክንውን ግምገማ ሪፖርት አዳምጬ ነበር። አንድ ጹሁፍ ጋርም አድማጮቼ እንድትከታተሉት ለጥፌው ነበር። ያን ያህል ዶር አብይ አህመድ መሄድ አያስፈልጋቸውም ነበር። ሚዲያ ላይ ያለውን ስታስቲክ ብቻ ማውጣት እና ምን ያህል አዎንታዊ አስተያዬቶች እንዳሉ መመዘን ብቻ በቂ ነው። ድምፃቸው ሲጠፋም ጭንቃችን ሰፊ ነበር።  

ያ ስለምን ሆነ ብሎ መመርመር ያስፈልጋል። ሰው የራበውን አገኘ፤ ሰው የጠማውን አገኝ። እናም ቤሰተብ ለመሆን ሲፈቅድ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ነበር። ወጀቦች ነበሩ ነገር ግን ወጀቦችን ጥሰው ያለፉት ጤነኛ ሞገዶች አሸነፊ ሆነው ለወጀብ ፈጣሪዎችም መቆሚያ መሬት ለጋሽ ሆነ የተገፋው፤ የተብጠለጠለው የአብይ ሌጋሲ።

እኔ እራሴ የኢትዮጵያን ሚዲያ በፖለቲካ ዘርፍ ተከታትዬ አላውቅም ነበር።  አልፎ አልፎ አዋጅ ነገር ሲሆን ለማገነዘቢያ ስፈልግ በቻ ነው እምከታተልው፤ በዓመት ቢበዛ 7 ቀን። ዛሬ በዬዕለቱ ታዳሚ ነኝ። ለዛውም እኔ ሞገደኛ ነኝ። ግን ይህን ለውጥ ገና ከመቅድሙ ጀምሬ ፊት ለፊት ወጥቼ ነበር የደገፍኩት። የተሟገትኩለትም። ጠረኑ መልኬ ነበር። ትንፋሹ ውስጤ ነበር። እኔ ከማስበው ከማልመው ጋር ግጥም ነበር። ስለሆነም ደቂቃ አላባከንኩኝም ስለሆነም መደበኛ ታዳሚ ሆንኩኝ "ከጣና ኬኛ፡ ጀምሮ።

ወደ ቀደመው ስመሰል እርግጥ ነው ይህን የሃሳብ ቅቡልነት እንደ እዳ፤ እንደ ሽንፈት፤ እንደ መነጠቅ የሚዩት የራሱ የግንባሩ ወገኖች አባሎቹ እና አካሎቹ መሆናቸው ይገርም ነው። እነኝህ የድርጀታቸውን መፍረስ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን መፍረስም የራባቸው የነበሩ ናቸው ማለት ይቻለኛል።

እንዲያውም ይህ ዘመን በሃሳብ ልዕልና ልቅና ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ድል አገኘሁ ቢል አህአዴግ ዛሬ ነው። እጁን መሰስ አድርጎ ነው አሜኑ አብዩ ያወጣው። ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ጀምሮ እንደገና የተፈጠረበት ወቅት ነው ኢህአዴግ። 

ይሄ የኮፒራይት ጉዳይ ሳይሆን እንደ ግንባር ቁመቀሩ የኢህአዴግ ዓላማ እና ግብ ወደ ተሻለ አቅጣጫ ለመራመድ የተሰናደባት እና ይህንንም ሚሊዮኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በህሊናቸው የፈረሙበት የትርፍ ዘመኑ ነው ለግንባሩ ለራሱ። መሃንዲሱ መንፈስ የተደላደለ ምቹ ሁኔታ በሌለበት ነው ይህ የተገኘው፤ ሰከን ተብሎ እርምጃው ሲቀጥል ደግሞ ሰብሉን አፍሪካም ተጠቃሚ ያደርጋታል። ይህ ሁሉ እሰቡት የነበረውን ሳቦታጅ እና የወል ሚደያዎች የከፈቱት የማጣጣል ዘመቻ ... 

ወያኔ ሃርነት ትግራይ በነፍሱ እያለ ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ በግልም በጋራም ሥርዓቱ አልተመቸነም የምንልበትን፤ የምናወግዝበትን መሰረታዊ አምክንዮ ጋር እንኳን በሂደት በተስፋ ሊስተካካል ይችላል ብሎ እምነት ማሳደር መቻል ግንባሩ ሽልማቴ ነው ማለት ይገባው ነበር። እራሱ ግንባሩ ዶር አብይ አህመድን ሊሸልማቻው ይገባል። ከጉድ እና ከገማና ነው ያወጣቸው። ይህም ብቻ አይደለም ሌሎችም አማራጮች ቢሆኑ ሁላችን አሳታፊ ሊሆኑ ይችሉ ነበር ተብሎ በፍጹም አይታሰብም ነበር። እና ከጨለማ ወደ ብርህና የተደረገ ጉዞ ነው።  ለዚህ ነው የሽግግር መንግሥት፤ የተጽዕኖ ፈጣሪ አንድነት መንግሥት አሁን ከመሼ ደግሞ የሆነ ኮሚሺን ይቋቋም ሲባል ከልቤ የማይገባው። በ አለት ላይ ውሃ እንደማይፈልቅ አሳምሬ አውቀዋለሁኝ። 

የኢህዴግ የግንባሩ አኩራፊ አካላት ሴራ አደራጅተው አዲሱን መንገድ ለማስናክል ከመታታር ይልቅ መዳኛቸውን መንከባበከብ ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባ ነበር። ምክንያቱም ትንፋሽ ስለሆነ። ይህ አብያዊ ጉዞ ንጹህ ኦክስጅን ነው ለሁሉም። ተፎካካሪውንም ከውርደት ነው ያደነው። ምክንያቱም ትግሉ በረዘመ ቁጥር መሰልቸት እና ጭራሹን እርግፍ አድርጎ የመተው የሰው ልጅ ባህሪ ነው። 

በሌላ በኩል በአዲሱ ለውጥ አልተመቸንም ይህ ቀረ ያ አልሆነም ለሚሉት ስሞታ ለሚያቀርቡትም እራሱ አኩራፊው የግንባሩ አካላት ስንቅ እያቀበሉ ስለመሆኑ ልብ ሊሉት አልፈቀዱም። እራሳቸውን የሚድነው መንገድ እራሳቸው ታገሉት እስከ ግድያም ሄዱ። ሥርዓቱ ሙሉ ለሙሉ ቢፈርስ በኢሠፓ ጊዜ እንደታዬው ሁሉም ለማኝ ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ የጎሳ ስለሆነ ተጠቂው ሙሉ ለሙሉ ጎሳው ነው። ይህን ግን በማስተዋል መመርምር አልተቻላቸውም። ከሁሉም በላይ የማይነገሩ እጅግ አስጊ መካራዎችም ነበሩ። 

ይህ ከምን መጣ ቢባል የሃሳብ ልዕልና የባለቤትነት በሽታ ከሚያመጣው ተወሳክ ነው። የሰሞናቱ የሳጅን በረከት ስምዖን ያዙኝ ልቀቁኝም በሽታ ይኸው ነው። አብዮታዊ ዴሚክራሲ ይባል፤ ልማታዊ ዴሚክራሲ ይባል የሃሳብ ልዕለና ከሌለው ተሸናፊ ነው የሚሆነው። የአብይ ሌጋሲ የሚለዬው በራሱ መንፈስ ውስጥ የወጠነው አዲስ መንገድ የሃሳቡን ደረጃ ከፍ አደረገው ቅቡልም ሆነ።

አብያዊ ምንፈስ በቀጥታ ወደ ልብ ገብቶ ህሊናን የመቆጣጠር ጉልበታም አቅም ኖረው። ስለዚህም የሞተውን የኢህዴግ እሬሳዊ ሃሳብ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ጥሶ በአዲስ መንፈስ ሰውኛ እና ተፈጥሯዊ አድርጎ በልዩ ጥበብ አቀረበው። እናም አሸነፊ ሆነ።

ለዛሬ ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ይህን የሚመጥን ሃሳብ ማቅረብ እስካልተቻለ ድረስ ተወዳዳሪም፤ ተፎካካሪም ለመሆን የሚያስችል አቅም የማምንጨት ዘመኑን መቼ የሚለውን ለመለካት አይቻልም። ምክንያቱም አዲሱ ሃሳብ ሞገዱ ቅባዕ አለበት እንደ ንጉስ ዳዊት፤ እንደ ንጉሥ ሰለሞን። አይሰለችም ሁልጊዜም እሸት ነው፤ አያልቅበትም አዲስ ሃሳብ የማፍለቅ ተስጥዖው እጬጌም ነው። 

አሁን ነው እኔ መሪነት ተስጥዖ፤ መክሊትም መሆኑን እያስተዋልኩኝ ያለሁት። ለካንስ ለመሪነት መክሊት ከሌላ ምኞት ብቻውን ብላሽ ነው።

ብዙ ውይይቶችን እከታተላለሁኝ። አገር ቤት የሚካሄዱትን ነው እኔ እመከታተለው፤ የሚገርመው ነገር ተቀናቃኝ ሃሳቦች እኔን ወስጤን አሸንፈው የእነሱ ተከታይ ሊያደርጉኝ አልተቻላቸውም። እንዲያውም ያደክመኛል ማለት እችላለሁኝ። መድከም ብቻ ሳይሆን ይሰለቸኛል። 

ምክንያቱም እንደ ሰው የምናዬው ነገር አትዩት፤ እደሰው ደስ ብሎን እምናዳምጠውን መልካም ነገር አታዳምጡት፤ እንደሰው መስፊሪያ ተፈጥሯዊ የህሊና ዳኝነት እያለን አልሆንም አልተደረገም ቢባል ወይንም የ43 ዓመቱን ችግር አብይ እፍ ብሎ በማጅክ ያጥፋው ቢባል መንፈሴ ያነጥረዋል እንጂ በጅ ሊለው አይችልም።

ስለምን? የማዬው መልካም ነገር እዬራዊ ስለመሆነ ከልብ ስለማምነበትም። ቅዱስ እለታት፤ የተባረኩ እለታት እንዲህ እዬተበራከቱ ነገ አብይ ሊያብጥ ይችላል፤ ዲክታተር ሊሆን ይችላል ምስጋናውን በልክ አድርጉት ቢባል እሺ ባይ የለም። 

የአብይ መንፈስ እንዲህ የተንጠራራ አይደለም፤ ሲሆን ደግሞ ራሱ ካመጣው ሲመጣ እንጂ አሁን በገደብ ደስታችሁን፤ አክብሮታችሁን እሰሩት ምክር የማይሆን ነው። የሰው ልጅ ህሊናውን የሚገዛ የሃሳብ ጭብጥ ወቅትና ሁኔታን ባደመጠ መልክ ካልሆነ ተንሳፎ ይቀራል። ይሄው የትጥቅ ትግል እኮ ተንሳፎ ነው የቀረው። ኢትዮጵያ ከ ኤርትራ ጋር ስምምነት ስትፈጥር በራሱ ጊዜ መቅኖው አለቀ የትጥቅ ትግል። በቃ!

እኔ የማዬው ጥበብ የተሞላበት አመራር አለን - ለቅኖች። የማዬው ስለታዊ ጉዞ አለን - ለቅኖች። የማዬው በትእግስት የሰከነ ክህሎት አለን - ለቅኖች። የማስተውለው ከተኖረበት የሴራ ፖለቲካ ጋር ንክኪ የሌለው ጻዕዳ አመራር አለን - ለቅኖች። የማዬው ዓለማውንም ግቡንም የተረዳ ብቃት አለን - ለቅኖች። የማዬው ፍቅራዊነትን መርሄ ያለ ቅዱስ መንፈስ አለን - ለቅኖች። አብነቱ ደግሞ ለ አፍሪካም ጭምር ነው። ኢትዮጵያም ወደ ቀደመው ክብሯ እዬተመለሰች ነው። እኛምን እያስከበረን ነው። 

የማዬው መቻቻልን የእኔ ያለ ክብር አለን - ለቅኖች። የማዬው ባለቤት ሌላቸው ሁነኛ የሚሆን ተምሳሌነት አለን - ለቅኖች። የማዬው አቅራቢ ብቻ ሳይሆን አቀራራቢ ንጹህ ሃዲድ አለን - ለቅኖች። የማዬው የሳቅ ማህበር ልዩ ሙሴ አለን - ለቅኖች። 

የማዬው ችግሮችን የማጥናት እና የማያዳግም መፍትሄ የመስጠት ልቅና አለን - ለቅኖች። የማዬው ሁኔታዎችን በማጥናት ጠቃሚ ሃሳቦችን የማቀናጀት ብልህነት አለን - ለቅኖች። እና ከዚህ አፍንግጦ የሰማይ መና መጠበቅ ለእኔ ጊዜ ማባከን ወይንም ሥራ ፈትነት ነው።

ይልቁንም ይህን ድንቅ ብሩህ ዘመን ቅንነት መመገብ፤ ቸርነት ሳይስቱ መስጠት፤ ርህርህናን ሳይቆጥቡ መፍቀድ፤ እራስን ማሸነፍ፤ አይዞህን በገፍ መለገስ ይጠይቃል ከእያንዳንዳችን በግል ከሁላችንም በጋራ። ቀሬ ነገሮችን ለማለም ወቅትን - ሁኔታን - ጊዜን ማሰብም ይጠይቃል። ወቅቱን ያልጠበቁ ጥያቄዎች እራሱ አፍራሽ ናቸው። መንፈስን ይበትናሉ። 

አሁን ሃሳብን የመሰብሰብ ዘመቻ ላይ ነው የአብይ ሌጋሲ … እራሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መሪ አልነበራቸውም። አሁን ግን አላቸው። ይህ በራሱ ለእኔ የድል መባቻ ነው። አሁን እኮ ዶር መራራ ጉዲና ፍጹም ሌላ ሰው ሆነዋል። እንደግፈው ለውጡን፤ እንርዳው ለውጡን እያሉ ነው። በቄሮ ከሥርዓት መውጣት እራሱ ተከፍተዋል። እሳቸው እንግዲህ የፖለቲካ ሳይንስ ሊቀ ሊቃውንት ናቸው። የሳቸውን ህሊና ወደዚህ አቅጣጫ የመራ ልዑል እግዚአብሄር የተመሰገነ ይሁን አሜን!

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

የኔዎቹ አዱኛዎቼ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ።  

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።