የልብህን ማድረስ የምትችለው በራስህ ጥረት ውስጥ ነው።

ሚዛን።
„በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢያተኛ
በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ አልሁ።“
መዝሙር ምዕራፍ ፴፰ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
24.08.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።


  • ·     ያያዥ።


ፈጽሞ ለውጥ የለም የሚሉ ወገኖች አሉ። ይህም መብት ነውና አከብራለሁኝ።

ለውጥ ማለት ለእኔ ሰኔ 29 ወደ ሰኔ 30 ሲቀዬር ለውጥ ነው። መናገር በተዘጋበት ምድር መናገር ሲጀመር ለውጥ ነው። በዓዋጅ የታሠረን ብሔራዊ ሰንደቅዓላማ ሁለመናህ አድርገህ ካለ አጋጅ፤ ካለ ከልካይ ይዘህ ስትወጣ ለውጥ ነው። 

እንደ ጠላት ይታዩ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ተፎካካሪ ይባሉ ተቀናቃኝ ኢትዮጵያ የእናንተም ናት እና የድርሻችሁን አበርክቱ ተብለው መጠዬቃቸው ይህ መጀመሩ በራሱ ለውጥ ነው። ለእነሱም አዲስ የተመክሮ ማሳ ነው፤ አዲስ የአስተዳደር እና የአማራር በር መከፈቻ ነው፤ አዲስ የአገልግሎት መስመር መከፈቱን ያበስራል።

ህዝብ ከጠ/ ሚሩ ጋር ፊት ለፊት ጥያቄዎችን አቅርቦ ሲሞግት ማዬት ትልቅ ለውጥ ነው። ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ያሉ ወገኖቼ ጋር የተደረገው ውይይት እኔ ኢትዮጵያ የገባሁ እስኪመስለኝ ድረስ በጥሞና ተከታትዬዋለሁ ብቻ ሳይሆን የትኛው ጥያቄ የትኛው ክልል ላይ ስለመሆኑ ሁሉ ልክ እንደ አንድ የትምህርት ክ/ ጊዜ አጥንቼዋለሁኝ።

አልፎ አልፎም በእንባ ነበር የተከታተልኩት፤ ይሄም  ለውጥ ነው እንደ አንድ የህዝብ አደረጃነቴ ቁምነገሬ ነው። ህዝብና መንግስት በቀጥታ የተገናኘበት አንድ ሃዲድ ነው ለእኔ።

ከውጭ አገር የፖለቲካ አሳታፊነት ይልቅ በተሸላ ሁኔታ በተቻለ መጠን ሴቶችን ቦታ ለማስያዝ የሚደረገው ጥረትም ከወንዶች የፖለቲካ ዓለም ለኖርንበት የድቅድቅ ጨለማ ዘመን ብርሃን ፈንጣቂ ነው። ይህን ውጥን በማስፋት፤ በማደረጀት ሴቶች ራሳቸውን በማብቃት እረገድ ተግተው መሥራት ከጀመሩ ነገን በተሟላ የእኩልነት መንፈስ ያበጃል። ይህም አንድ የለውጥ ፍንጪ ነው …

አንድ መሪ የአፍ ወለምታ ብሎ እራሱን ሲያሂስ ማዬትም ለእኔ የሰማይ ታዕምር ነው፤ 43 ዓመት ሙሉ አንዱ በአንዱ ሲያላክክ ተጠያቂነት እና ሃላፊነት በላነበረባት ኢትዮጵያ፤ አጥፍቻለሁኝ ተሳስቻለሁ ጉዳዩ የተነሳበት አግባባ ይሄ ነበር ማለት በራሱ ፍጹም ልባዊ እና ዘመንን ያናገረ የመጀመሪያው አብነታዊ ጉዞ ነው። ሥልጣኔም ነው። ሰው መሆንም ነው። ስህተት አልሰራሁም እኮ ሮቦትነት ነው።

ግብር ይገበራል ያውም የሰው፤ ከግብር በኋዋላ አክተሮች ይኖራሉ ለዛ ግብር ከፋይ ያ ጨርቅ ለባሽ ወገን ይረሳል። ጥፋተኛ ነን ይቅርታ ተብሎ አያታውቅም ነበር፤ አሁን ግን ጅምሩ አበረታች ነው … ለተደፈነው ገማንም መፍቻ ነው።

መመረጥ የፈለገ ማጥፋቱን አምኖ መቀበልን ማስቀደም ይገባል፤ ያን አትንኩት ነገን ብቻ ተመልከቱ አያዋጣም። እርግጥ ነው ይህ ጥፋት በመንግሥት ደረጃ ከሆነ ተባዳይን የሚክሱ፤ በዳይም ይቅርታ የሚጠይቅበት በአንድ ሰው ውክልና ሳይሆን አገራዊ በሆነ መልኩ ለመከወን ሌላ የሚጠይቀው አግባብ ቢኖርም፤ በቅጽበት ለተፈጠረችው ግድፈት ግን ያን የመሰለ እርምጃ መውሰድ እኔ ከጠበቅኩት በላይ አስደስቶኛል። ይህም ለውጥ ነው።
  
ሌላው እኛ አቅም በሌለነ ሰዓት፤ የነፃነት ፈላጊው ማለት ነው አቅምን ፈጣሪ ፈጥሮ ከጨለማው ማጎሪያ መውጣት በራሱ ለውጥ ነው።

አይደለም ከመሬታችን ውጪ አገርም ቢሆን የታሰሩ ወገኖችን ለማስፈታት መደራደሩ በራሱ ልዩ መንፈስ ነው። ዜጋ አገር አለኝ፤ መሪ አለኝ እንዲል አስችሏል።

በሆነ ባልሆነው ይህቺ የኤርትራ ችግር ፈጠራ ናት እያልን ውስጣችን እምናቆስለበት ሂደትም በልዑል እንግዚአብሄር ሃይል ምህረት እና ቸርነት እኛ ባላሰብነው መልክ መከወኑ ልዩ የሆነ የመንፈስ ዕሴት ነው። ይህም ለውጥ ነው። ህዝብ ለህዝብ ማገናኘት። የተለያዬን ቤተሰብ በአንድ ማዕዶት ማቀራረብ።
  • ·      ያላን ተቋማት!

የሁለቱ ሃይማኖቶች የእስልምና እና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት መሃል የነበረው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በአግባቡ መፍትሄ እንዲያገኝ የተሰጠው አትኩሮት፤ ለዚህ የዋለው መዋለ ጊዜ፤ ማዋለ መንፈስ፤ መዋለ ንዋይ እና ውጤቱ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማስቀጠል ታላላቅ ተቋማት፤ የአገር ባላዎች፤ የሁለመና ማገሮች እንደ ተሰናዱ ያመላክታል። ብዙ ጊዜ ተቋማት አልተገነቡም ሲባል እሰማለሁኝ። የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተቀሟነት ከልብ ሆኖ መመርምር ያስፈልጋል።

„የድምጻችን ይሰማ“ ተጋድሎው እና ውጤቱንም መንፈሴ ማለት ይገባል። እነኝህ ሁለት ባላዎች ናቸው። ታላላቅ ተቋማት ናቸው። ተቋምነታቸው ደግሞ ለገሃዱ ዓለም ሳይሆን ለመንፈሳዊ ስለሆነ ማህበረ ምዕማመኑን ሞራላዊ አድርጎ በመቅረጽ እረገድ ታላቅ ድርሻ አላቸው።

ሌላው ቀርቶ ኢትዮ ሱማሌ ላይ በደረሰው የቅድስት ተዋህዶ አደጋ መሳደድን እና አገልጋዮችም ምዕመኑም መሰዋት መሆን፤ የቅድስት ኦርቶዶክ ተዋህዶ ማህበር ምዕመን የሰጠው መልስ ኢድ ላይ በዬአካባቢው የተደመጠው የፍቅር ዕሴታዊ ሂደት ለቀጣዩ ትውልድ ፍቅርን በማወረስ ትውፊት ከመሆን አልፎ ለውጡ በመንፈስ ደረጃ መሰረት መያዙን አመላካች ነው። 

የታሰበው ግን በቀጥታ ሁለቱን ሃይማኖቶች ጦርነት ለማስገባት ተብሎ ነበር። ግን ትልሙ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። ይህ የመንፈስ ለውጡ ጥልቀቱ ሲመረመር የአዲሱ ለውጥ ተሳታፊነትን በሙሉ ልብ ከመቀበል መቻቻል የመጣ አቅም ነው። 

በኢትዮ ሱማሌ የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት የመከላከያ ሠራዊቱ ልክ እንደ ቀደመው ጊዜ የህዝብ ጠባቂነቱ መንፈስ እጅግ የተመሰጥኩበት፤ ሻማም ያበራሁበት ልዩ ዜና ነበር።

ብሥራት ልበለው። መከላከያ ሠራዊቱ 27 ዓመት ሙሉ ያው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ አስፈጻሚ ስለነበር የእኛ ለማለት አንደፈርም ነበር። ብለነውም አናውቅም ነበር። እነሱም ወያኔ ሃርነት ትግራይ የበላይነቱ ካበቃ የእኛም ማክተሚያ ነው ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ሲተጉ ነበር። ከሰሞናቱ ባደማጥኳቸው ቃለ ምልሶች ግን ተስፋ ሰጪ ጅማሬዎች አሉ።  

አሁንም ቀጣይ ተግባራት ሊሠሩ የሚገባቸው ቢኖሩም ባዬኋዋቸው መልካም ጅምሮች ግን ነገን ማሰብ ችያለሁኝ።
ችግሩ ምንጩ የማንፌስቶ ተጠሪነት እንጂ የህዝብ ለህዝብ መሆን ያልቻለ የኢትዮጵያ የሚባል ሠራዊት አለመኖር አናት የሌለው ፍጡር የመሆን ያህል ነው የነበረው። በዚህ ዘርፍ ጅምሩ መልካም ነው።
  • ·      ናፍቆት እና ምኞት።

አሁን ሊሂቃኑ ወደ ወጪ ስደተን አይታሰብም ያው በዘራፋ እና በወንጀል እራሳቸውን የዘፈቁት ብቻ ይሆናሉ የሚሰደዱት። አገር ገቢው ግን በርከት ብሏል። ከስደት ወደ አገር መግባት ጉዞ እና ሃላፊነትን ለመውሰድ የግንባር ቀድም ተሳትፎ ሂደት በሚመለከት …. አበረታች ነው። እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ላይ ያለው አያያዝ እና የደህንነት ጉዳይ ግን ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ይመስለኛል።

መልካም ነገር ነው አገር መግባት። ቸር ወሬም ነው አገር የሚገባው ሰው በርከት ብሎ ሲደመጥ። አቀባበሉ ሴሪሞኒያዊ ነው። ያ በመንፈሱ ውስጥ ምንም ለሌለው ነው የሚያስፈልገው። ህዝብ ወስጥ ለመኖር ለፈቀደ ምንም የሁካታ፤ የቻቻታ ሂደት አስፈላጊ አይደለም።

የሚያስፈልገውኢትዮጵያ አዬር መንገድ ሲደርሱ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባባል፤ ፈግግታ ብቻ ነው ተፈላጊው ነገር። አገር ገቢው ታክሲ ውስጥ፤ መንገድ ላይ፤ ሱቅ ውስጥ፤  ለአንዳንድ ጉዳዮች ወደ ቢሮ ብቅ ሲባል ትህትና፤ ፈገግታ ፍቅር ከተሰጠው ያ በቂ ነው። አገር ማለት ሰው እንጂ ዴኮሬሹን አይደለምና።
ለሥም - ለዝና - ለንግሥና ላሰቡት  ሴሪሞኒያዊ አቀባበል የልባቸውን ታንቡር ምት ይጨመርላቸዋል። 

በትክክል መከራው ራህቡ - ጥማቱ ለገባው ግን የህዝብን ጎስቋላ ኑሮ ለመጋራት ከህዝብ ችግር ጋር መሬት ላይ መገናኘቱ በቂ ነው።
እርግጥ ነው ለህይወታቸው የሚሰጉ ዜጎች እውቅና ማግኘቱ ለደህንነታቸው መሰረታዊ ነው፤ ከዚህ ባሻገር ያለው ነገር ግን 2 ሚሊዮን ዜጋህ በክረምት ሜዳ ላይ ፈሶ ድንኳን ተጠልሎ የቅንጥ ነው ለእኔ ቻቻታው ይሁን ሁካታው።

ደግሞስ ለስንቱ አቀባበል ተደርጎ ይዘለቃል? ዛሬ ፌስ ቡክ፤ ዩቱብ ያለው ሁሉ አክቲቢስት ነው፤ ጋዜጠኛ ነው፤ ጸሐፊ ነው። የሆነ ሆኖ ክድን ያለ ህይወት የሚኖሩ ሰዎች እኔ ይመስጡኛል። የታይታዎች ደግሞ ያቅለሸልሹኛል።

  • ·      ትዮ ሱማሌና ተስፋ ሰጪ ጅምሩ።

ከሰሞናቱ ኢትዮ ሱማሌ አዲስ አመራር እንደ መረጠ ተዘግቧል። ይህም መልካም ዜና ነው። አዲሱ ተመራጭ ሰብዕናቸው ሰባዕዊ ስለመሆኑ አዳምጫለሁኝ ከBBN። ተመስገን ነው።

ከሁሉ የሚልቀው ደግሞ የኢትዮ ሱማሌ አክቲቢስቶች አገር ቤት መግባታቸው ነው።  አክቲቢስቶቹ በራሳቸው ሙሉ እምነት ያላቸው፤ በትክለኛው መርህዊ ጉዳይ ላይ ሲታገሉ የነበሩ፤ በፊትም በኋዋላም ችግር የሌለባቸው፤ የበታችነት ስሜት የማይሰማቸው፤ ኢትዮጵያን ያስገኘኋዋት ያቆዬኋዋት እኔም ነኝ፤ አባቶቼ ናቸው፤ እርስቴ ናት አገሬ ነው የሚሉት። 

እኔም  የኢትዮጵያ ኢትዮጵያም የእኔ የሚሉ ብርቱዎች ስለሆነ አገር የሚገቡት የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ አለህ ሊባል ይገባል። አብሶ እንደ አክቲቢስት አቶ ጀማል ዲሬይ ኸሊፍ ላሉት።
እኒህን የሰባዕዊ መብት ተመጓች ለረጅም ጊዜ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ እከታተል ነበር። እናም እመሰጥ ነበር። ዛሬ ከጋዜጠኛ ሳዲቅ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ሳዳምጥ አክቲቢስቱ ኢትዮጵያ እንደ ገቡ አዳመጥኩኝ ደስም አለኝ።

እርግጠኛ ነኝ በፍቅራዊነት አብሮነት ዙሪያ የተለመደውን ተግባራቸውን ይከውናሉ ብዬ አስባለሁኝ። አሁን ኢትዮ ሱማሌ ያለው ችግር አያያዙ አበረታች ነው። 

መሪ አካሉን የሚያግዙ በሰብዕ መብት ተኮር ላይ ሲታታሩ የነበሩ የመርህ ሰዎች፤ ቅኖች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ልዩ አቅም ነው ለተስፋችን ብዬ አስባለሁኝ። እነኝህ ብርቅዬዎች በመገንባት፤ በማገዝ፤ በመርዳት፤ በማስተባባር እንጂ በማፈረስ እና በማግለል ያተከሩ ስላለሆኑ አጅግ አስደሳች ዜና ነው ወደ አገር መግባታቸው።
  • ·         ማራ።

በሌላ በኩል አማራዊ ጉዳይንም ስንመለከት የመአህዱ ዶር አፈወርቅ ተሾመ አንድ ልዑክ ይዘው ኢትዮጵያ እንደገቡ አዳምጫለሁኝ። ይህ እንግዲህ ትልቁ የአማራ ድርጅት በውጪ አገር መሆኑ ነው። ዶር አፈወርቅ ተሾመ የዛሬ ሰው አይደሉም።  የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ስለተወለደ አይደለም ስለ አማራ መታገል የጀመሩት። በቀደመው መአህድ ጊዜም ንቁና ብርቱ ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው።

በሌላ በኩል መአህድ ህልውናው ካበቃ በኋዋላ ደግሞ  በአቋማቸው ጸንተው፤ ወለም ዘለም ሳይሉ፤ ጃኬታቸውን እንደ ሌላው ሳይቀያይሩ በጥሞና ነበር የቆዩት። እንዲህ ዓይነት የማይበገር መንፈስ ያላቸው ሰብዕናቸው ለማናቸውም የሃላፊነት ቦታው ብቁ ናቸው። እንደ ሽንበራ ቂጣ የማይገላበጡ። ፈተናን ታግሰው የሚያሳልፉ። ሰብሰብ ያሉ።

ስለሆነም ነው ሞረሽ ወገኔ ሲጀመር ደግሞ  ተሳትፏቸውን የቀጠሉት። ብዙ ጊዜ ከተሠወሩ በኋዋላ ነው ወደ መድረክ የመጡት በሞረሽ ምክንያት ነበር። ከዛም በዳግማዊ መአህድ ላይ ሲሳተፉ አይቻቸዋለሁኝ።

አብሶ የእሳቸው ሊቀመንበር መሆን ፋይዳው በመላ ኢትዮጵያ ለተበተነው አማራ ዋቢ፤ አሳቢ፤ ሰብሳቢ እንደሚያገኝ ይሰማኛል። ምክንያቱም እሳቸውም የዛ ሰላባ ስለሆኑ። አንድ ጊዜ ከግዮን ራዲዮን ጋር በነበራቸው ቆይታ ወስጣቸው መጎዳቱን አዳምጫለሁኝ። እንደ ተጨማሪ እንጂ እንደ ባለቤትነት አለመታዬት የተገባ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

አብሶ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ የጣሊያንን ስልስል ርዕዮት ተከትሎ ታላቋ ምንትስ እያለ ያሳለውን አማራ መሬት ከተባለው ቀዬ ውጭ የተወለዱትን በሚመለከት ያለውን ዕይታ ሲገልጹ ቁስል ያለ ነበር።

በተጨማሪም ውጪ ላይ ያለውንም መገለልን፤ በማህበራዊ ኑሮ የሚደርሰውን ጫና የኖሩበት ስለሆነ ውጭ ለሚገኙት የአማራ ልጆችም ማዕከላዊ ዕይታ፤ ተቆርቋሪነት ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁኝ። አማራነታቸውን ከውስጣቸው የመቀበላቸው አቅሙ ዝልቅ ነው፤ የእውነትም ተቆርቋሪ ናቸው። 

ለዚህም ነው በዬምድጃው ሳይገኙ፤ ሳይታዩ የቆዩት።
ስለሆነም የሳቸው አገር ቤት መግባት በአማራ የህልውና፤ የማንነት ተጋድሎ ላይ ብርቱ አቅም እንደ ተገኘ አስባለሁኝ። ለራሱ ለብአዴንም ቢሆን አቅም ካለው ድርጅት ጋር መፎካከሩ ክብሩ ነው ብዬ አምናለሁኝ።

ልዩ እምቅ ያለው፤ ሰፊ ተመክሮም ያለው ድርጅት ጋር ቀርቦ መነጋገርም መታደል ነው። በመሆኑ የመአህድ አገር መግባት  ሚዛኑንም እንደሚያስጠብቀው አስባለሁኝ።

የውነት የሆነ ድርጀት የውነት የሆነ መሪ ሲኖረው አፍ ሞልቶ ያናግራል። በነገራችን ላይ የአማራ ድርጅት በጀርመን በተለዬ ሁኔታ ነበር እምከታተላቸው። ጨዋዎች ነበሩ። ለቆሙለት ዓላማ እና ለራሳቸው የቤት ሥራ ብቻ ነበር የሚተጉት። ሰው የራሱን የቤት ሥራ ነው መሥራት ያለበት።

በሌላ በኩል በአማራ መከራ ላይ የፊት ለፊት ተጋፋጭ የሆነው የሥነ - ልቦና ሙሁሩ፤ የምርምር ጸሐፊና ጋዜጠኛ አክቲቢስት ሙሉቀን ተስፋውም እንዲሁ ነገ እንደሚገባ አሁን ሳተናው ላይ አንብቤያለሁኝ።

ወጣት ሙሉቀን ተስፋው ጨዋነቱን እውድለታለሁኝ። ሞራላዊ ሰብዕናውን ልዩ ነው። ለአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ጽላት ነው። የአማራ ጽላቱ ተሰዶ ነበር አሁን ወደ ባዕቱ ሲገባ የሚያስፈልገው እንደ ሥርጉተ ሥላሴ ጸሎት ብቻ ነው። ሌላ አስፈላጊ አይደለም።  

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው እንደ ገሃዱ ዓለምተኛ አቀባበልን ተመኝቷል። እኔ ደግሞ ህይወቱ እንዲሰነብት በጸሎት እንድርዳው ባይ ነኝ። ደህንነቱ አሳስቦኛል። ሳነበው ዜናውን ደንግጫለሁኝ። የሆነ ሆኖ ወጣቱ ብዙም የታዬታ ሰው አይደለም፤ ወደላይም የመንጠራራት ዝንባሌ አሳይቶ አያውቅም፤ ግጭትም ውስጥ ብዙ አይደፈርም፤ እላፊም አይሄድም፤ ክድን ብሎ ግን ተግባር ተኮር የሆነ ሰብዕና ነው ያለው። የተከደነ ሲሳይ ነው።

ታታሪው ሙሌ የአማራን ሶቆቃ በመሆን ውስጥ ልባዊነትን መግቦ ስለሆነ እድሜውን መለመኑ በቂ ነው። የተረፈው ብዙም አይበጀውም። ቀስ አድርጉ ሲያዝ ነው ሁለመና የሚያምረው። ለብአዴንም የጋዜጠኛ ሙሉቀን ወደ አገር መግባት መልካም ነገር ነው ብዬ አስባለሁኝ። መልካምነት የማይበት ወጣት ነውና።
አሁን አቀባባል ላይ ሳይሆን ህዝብ ያለው መሬት ላይ ስለሆነ መሬት ላይ ሊሠሩ የሚገባቸው ተገባር ተኮር የሆኑ የቤት ሥራዎች ላይ ቢሆን ይመረጣል።

ፉክክሩም፤ ቅባ ቅቡም፤ ልቅልቁ አርቲፊሻል የሆኑ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን በዕድሉ ለመጠቀም ህሊናዊ መሰናዶ፤ ድርጅታዊ አቅምን ማሳደግ እና ማበልጸግ፤ ዓላማ እና ግብ አውቆ መታተር፤ ጊዜውን መሻማት፤ ክፍተቶችን መሙላት፤ ስብራትን መጠገን ነው ተፈላጊው ነገር።

አብሶ ፍቅራዊነትን የወጣቱ ስብዕና ሊሆን ስለሚገባ ትውልዳዊ ድርሻውን ወጣቱ ለመወጣት ሥርዓትን መያዝ፤ ከህግ በላይ አለመሆን፤ ለሰው ልጆች እና ለተፈጥሮ አክብሮት መስጠት እንዳለበት ማስተማር በትጋት ያስፈልጋል። 

ወጣቱ መኖርን የሚጀመረው ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ላይ አክብሮት ሲኖረው ነውና። ሞራላዊ፤ ሥነ - ልቦናዊ ተግባር ላይ መትጋቱ ነው ፍሬ ነገር መሆን የሚገባው። ይሄ የፉክክር ጉዳይ ብዙም አይረዳም። ሙሌ አዬር ላይ፤ ሳይበር ላይ፤ ወይንም ሞባይል ላይ ሳይሆን ልባችን ውስጥ ነው ያለው።

ጽላታችንም ነውና። አለን የምንለው አፋችን ሞልተን የምንናገርለት፤ ሲያጠፍም ስለምን ብለን የምንሞግተው ባንጻሩም ዓይተን የማንጠግበው፤ የምንሰስትልት ተስፋችን ነው። 

ስለሆነም አቅሙን ሥራ ላይ የሚያውለበት ሁኔታ በማመቻችት እረገድ ብአዴን ታላቅ ሃላፊነት አለበት። ደህንነቱንም ጉዳዬ ሊለው ይገባል ባይ ነኝ ብአዴን። እሱም እራሱ በብዙ መልክ ፈተናዎች ሊገጥሙት ሰለሚችሉ ከአመጋጋብ ጀምሮ ብርቱ ጥንቃቄ ማድርግ ይኖርበታል። ከጥንቃቄ ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም። እንደነዚህ ዓይነት ወጣቶች ሚዛን ለማስጠብቅ አንድ መንገድ ናቸው።
  • ·      መደጋገፍ መደገፍም።

በሌላ ዜና ደግሞ ዶር መራራ ጉዲና በመንግሥት ተስትፎ እዬደረጉ ስለመሆኑ አንድ ዜና አዳምጫለሁኝ። በመጀመሪያ ነገር ሂደቱን አስደስቶኛል። ድርጅታቸውን አወያይተው፤ አስወስነው መቀጠላቸው፤ ሁለተኛው ነገር በንጹህ ልባቸው ሊያገልግሉ ማሰባቸውን ከመንፈሳቸው ተረዳሁኝ፤ እኔም እምለው ይህን ነው፤ የመንፈስ ንጽህና ከኖረ ማናቸውንም ችግር ማስወገድ ይቻላል።

የጎደለውን ለመሙላት መትጋት አንዱ የተጋድሎ ድርሻ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ ዕድሉ እንዲህ ከተገኜ። ኢትዮጵያ የምታስፈልገን ከሆነችም። አጋጣሚው ሲገኝ በራስ ጥረት እና ብርታት ብዙ ነገር ማረቅ ማስታረቅም ይቻላል። ሩቅ ሆኖ መናገር እና አባል ሆኖ መናገር መብቱ የተለዬ ነው። ውስጥ ከተሆነ ተጽዕኖ ለማሳደር ጉልበታም ሃሳብ አቅርቦ ህዝባዊ ለማድርግ ይቻላል።

መንግሥት ይህን ዕድል መስጠቱ ዕውነትም መለወጡን ለማዬት ለምንፈቅድ ሰዎች አንድ ምልክት ነው። ስለምን? እሳቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጎልተው የወጡ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ስለሆኑ ግብረ ምላሹ ትርፋማ ነው ለራሱ ለመንግሥት።
  
በሌላ በኩል ድርጅቱም የሳቸውን ቻሌንጅ ተቋቁሞ አብሮ ለመስራት መፍቀዱ በራሱ የሰጥቶ መቀበል መርህን ሚዛን ያስጠብቃል ማለት ነው። አዲስ የተመክሮም ማሳ ነው ለሳቸው።
ለዚህ ነው ሥርጉተ ሥላሴ ለማውያን የሆነችው። ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ያን መደገፍ ቀደማይ ተግባራችን ሊሆን ይገባ ስለነበር።

አንዲት እህቴ አትዮጵያ ሄዳ ተመልሳ ስትመጣ በጻፈችልኝ ደብዳቤ እንደገለጸችልኝ ድባቡ፤ ጠረኑ ጥሩ ነው የሚል ነው። እኔም እምሻው ይህን ነው። ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፤ የነፃነት ታጋዮች አገር እዬገቡ ነው። ቀሪውን ነገር የራስን ሥራ ሞጥሮ መሥራት ነው። ሜዳ ነበር የሚፈለገው፤ ሜዳ ተግኝቷል ከስሞታ ወጥቶ አሳምኖ ታምኖ መታገል ማታገል …

  • ·      ልብ የሚያደርሰው የራስ ጥረት ብቻ ነው።

ኢህአዴግ አይደለም የነፃነት ፈላጊውን የልብ የሚያደርሰው፤ ራሱ የነፃነት ፈላጊው በሚሠራው ልክ ነው ነፃነቱን ማስገኘት ወይንም ማዋለድ የሚቻለው። የልብህን ማድርስ የሚቻለው በራስ ጥረት ውስጥ ነው።

ዴሞክራሲን ለማለም በማይቻልበት ጠጣር ዘመን ዛሬ ያን ሥርዓት ለማምጣት ና እና እኩል ታገልና አሸንፈህ አምጣው መባል ቀላል አይደለም።

ድሮም ትግሎ ኢህአዴግ የዴሞክራሲ አዋላጂ ይሆናል አልነበረም። እንዲያውም ገፍቶ ሄዶ ብዙ ነገሮችን አመቻችቷል። ቀሪው ስንፍናን አስወግዶ ወገብን ታጥቆ ህዝብ አስፓልት ባለበት፤ አፓርትመንት ላይ ብቻ ሳይሆን በገደሉ አፋፍ ላፋፍ፤ በተራራው፤ በሸንተረሩ፤ በኮረኮንቹ፤ በኮረብታው ሰፍሮ ስለሚገኝ ወረድ ብሎ ወገብን ጠብቅ አድርጎ መሥራት ነው። ህዝብ የከተማ ብቻ ሳይሆን ገበሬውም ሰው ነው። ሰው ከሆነ ደግሞ የህዝብ አካል ነው።

በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ የራስን ሥራ መሥራት ነው። ያ አልነበረም ከዚህ በፊት። ኢትዮጵያ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነው የነበረችው። በዛ ድቅድቅ ጨለማ ማንበብ አይቻልም ነበር። አሁን ብርሃን አለ፤ የተፃፈበትን ካልተፃፈበት ለይቶ ልሙጡን አልተጻፈበትም ለማለት ይቻላል። 

ልሙጡ ላይ ለመጻፍ ደግሞ የራስ ጥረትን ይጠይቃል። የራስ ፈጠራን ይጠይቃል። በቃል ውስጥ ሆኖ መገኘትም ይጠይቃል። ውሸት እንቧይ ነው። ሃቅ ግን ወርቅ ነው።

ስልት ብልሃት የሚያስፈልገው ከዚህ ላይ ነበር። ኦህዴድ እና ብአዴን ያን ያህል በተጉበት ጊዜ ድጋፍ አልተሰጣቸውም ነበር። ተሰናክለው ቀርተው ቢሆኑ ኖሮ አገር መግባትም፤ ነጻ የሚዲያ ተቋማት ለመገንባት ማሰብም፤ ተነጥፎ ተጎዝጉዞ አቀባበልም፤ ያሻውን መናገር መጻፍም አይቻልም ነበር። ስለዚህ ሥርጉትሻ ትክክል ነበረች ሽንጧን ገትራ መሞገቷ።
  • ·         ምርኩዝ።

ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው የጀግና አቀበባል ሊደረግለት ይገባል! (ጌታቸው ሽፈራው)

የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት አመራሮች አዲስ አበባ ገቡ

ዶክተር አፈወርቅ ተሾመ እና የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንጅነር ታደሰ ከበደ

አዲሱ የሶማሊ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ኡመር ማን ናቸው? | ዛሬ ከጀርመን / የገቡት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ጀማል ዲሬይ ኸሊፍ ከሳዲቅ አህመድ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

Ethiopia: / መራራ ጉዲና ኢቲቪን የበለጠ ለማሻሻል እንደሚሰሩ ቃል ገቡ

 

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!


ፎቶ ጉግል ላይ ያገኘሁትን ብቻ ነው የለጠፍኩት። ሳለገኘሁት የቀረሁትም አለ ለምሳሌ የዶር አፈወርቅ ተሾመ ፎቶ።

የኔዎቹ ልባሞቹ ፍቅሮቹ ኑሩልኝ!

መሸቢያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።