ዴሞክራሲ ቃሉ ሳይሆን የህሊና ማሳው ነው ዕውነትነት።
ቁልፍ።
„እንሆ አፌን ከፍቻለሁ
አንደቤተም በትናጋዬ ተናግሯል።“
መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ ፴፫ ቁጥር ፪
ከሥርጉተ ሥላሴ 08.08.2018
ከጭምቷ እናትዬ ሲዊዝዬ።
v መክፋቻ።
የእኔዎቹ እንዴት ናችሁ ዛሬ የሰነባባቱን ቃለ ምልለሶች ጹሑፎች ቅኝት ላይ ነበርኩኝ እና ይህን ደግሜ በአዲስ እርእስ ማቅርብ ፈልግሁኝ። ስለምን? ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ስለተዘነጋ፤ በዛ ላይ የተስተዋሎት አትኩሮት ስሌለ ነው።
አቤቱታዬ ለጠ/ ሚር አብይ አህመድ የነበረ ሲሆን በግልባጭ ለዶር ለማ መግርሳም ነበር፤ የጻፍኩት በ01.06.2018 ከሁለት ወር በፊት ነበር። እርእሱ አብይ ሆይ! ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሆንኩኝማ እኔም ዘለግ ያለ ህላዊ አቤቱታ አለኝ፤ የሚል የነበረ ሲሆን ረጅሙን አቤቱታ ለእርገት ያልኩበት ቁልፍ ጉዳይ ይህን ይመስል ነበር።
መጪው የምርጫ ዘመን ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ከብክነት የጸዳ ትውልድን ለመገንባት ወሳኙ ቦታ ወሳኙ ቢሮ ላይ ነበር አትኩሮቴ። እውነት ለመናገር አሁን ያሉት የለውጥ መንፈስ የእኔ ብዬ ከዬትኛውም ተቋም ሆነ ግለሰብ ቀድሜ ብቀበለውም ይህን ለውጥ ወደ ዘላቂ አሳታፊ ሥርዓት ለመለወጥ ግን ዋነኛው አንኳር ጉዳይ ለዴሞክራ ግንባታ መሠረት የሆነው የቢሮ አደረጃጃት፤ አወቃቀር አሰራር የሰብዕና አገነባብ ከሁሉም ድርጅት በላይ በዚህ ድርጅት ውስጥ ሥርነቀል መሆን ካልቻለ ዛሬ ያዬናቸው ወይንም የምናያቸው ሐሤቶች በፍጹም ሁኔታ ቀጣይም አይሆኑም፤ ትውልዳዊም አይሆኑም። መንፈሱ ይቀለበሳል።
ዴሞክራሲ ምርጫ በራሱ እንኳን ግብ አይደለም። መዋቅራዊ ህሊናዊ መርሃዊ ለውጥ ካልኖረ በስተቀር። እንኳንስ የሁሉም ነገር ጭንቅላት እንዲህ ተዘሎ ቀርቶ። እስከ አቤቱታ 17 ያሉትን ለምትፈልጉ እዚኸው ብሎግ ላይ ታገኙታለችሁ።
ግን የ100 ሚሊዮን ጥያቄዎች መመለስ ይጀመራሉ ተብሎ የሚገመተው ከሁሉም ነገር ባለይ በዚህ መዋቅር በሚወሰደው ግልጽነት፤ ተጠያቂነት እና ሃላፊነት የሚወሰን ይሆናል። ጉሮሮ ነው ይህ መዋቅር። የፈለገ ድል ይነባበር የፈለገ ሳቅ ይደርደር፤ የፈለገ ሐሤት ይከመር ዘላቂ ያሚያደርገው ይህ ተቋም ብቻ ነው። አሁን የነፃነት ፈላጊው ጉዳይ አጀንዳ ሊሆን የሚገባው በዚህ መዋቅር ሥር ነቀል አደረጃጃት እና አመራር መሆን ግድ ይል ነበር ግን ያው እንደተለመደው በእለታዊ ሰናዮች ተጠምደን አንዳችንም ባሊህ አላልነውም። እነሆ … በድጋሚ ቀርጬ ነው በድጋሚ ያቀርብኩት።
v አቤቱታ አስራስምንት። ከሆድ ውስጥ ስለታሰረው የግማድ ገመድ ።
ክቡር ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ሆይ! ይህ መንፈሴን እንደ ዱባ የቀረደደው ጉዳይ ነው።
ዴሚክራሲ ጥሩ ቃል ነው። ይጥማል። ይመስጣል። ያጓጓል። እርስዎ በአዋሳው ጉብኝተዎት ላይ ስለ አውሮፕላን ማረፊያ ተጨማሪነት ሲጠዬቁ „ በቅርብ ቀን አይመስለኝም፤ አያለሁ ብዬ ሄጄ ሳላዬው ከቀረሁስ?“ ብለው ነበር። እኔም እላለሁኝ በቀላል ቃል ልቤ የተቀረደደበትን የሹመት ሁኔታ መግለጽ አውዳለሁኝ። ያልታዬኝ ነው ብዬም ስለማስብ።
በወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚብሄር የመሪነት መንፈስ ዴሚክራሲን አይመስለኝም። አይታዬኝም። ተስፋን መሠረት ለማስያዝ ስላልመሰለኝ። ለአላዛሯ „ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ያስፈልገናል ይገባናልም“ ያሉትን በባዕለ ሹመተዎት ጊዜ አሁን በሹመት አሰጣጡ ላይ „አያስፈልግም በተለይ በዴሞክራሲ አግባብ አይገባንም፤ ከወያኔ ሃርነት እጅግ ከዛገ መንፈስ መውጣትም የለበትም፤ ለዛውም ሌብነት ደረቱን ገልብጦ ዴሞክራሲን ይምራ፤ ከማረተው የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ዝገት ጋር እንቀጥል“ የሚል ውሳኔ ቀጣይነት ታትሞበታል ባይ ነኝ።
ስለዚህ ባለራዕዩ ዴሞክራሲ አልጋ ላይ ውሏል። ታሟል። 1% እንኳን ተስፋ የለውም። ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ መሆን? የዚህ የመኖር ጉሮሮ ወሳኝ ሰው መሆን ነው? የሰውነት መሪ መሆን? የነፃነት አውራ ልሳነ ሙሴ መሆን? ለሞት ሁለተኛ መግደያ የተሰናዳለት ግዞት ነው። ግዞት እና ሞት። ሞት እና ግዞት በጣምራ።
ፈጣሪ ሰውን ፈጥሮ አፍ ባይሰራለት ኖሮ ምግብ የሰው መዳህኒት ይሆን ነበርን? ይሁን አፍም ይሥራለት እንበል፤ መውጫ ባያበጅለት ሰው አይፈነዳም ነበርን? አሁን ወይ አፍ ወይንም የመጻዳጃ አካል መፈጠር የለበትም ነው የዴሞክራሲ ህልም በአልዛሯ ኢትዮጵያ። ዴሞክራሲ መጀመሪያ ሰው ሆኖ መገኘት እንጂ ጫካ ሆኖ መገኘት አይደለም።
ለነገሩ ለእኔ ከዴሞክራሲ በላይ ነው ሰዋዊነት እና ተፈጥሯዊነት ነው የሚልቅብኝ። ሴት መሆን ወለደችም አላወለደችም አንዲት ሴት // ሴት የሚለውን መስፈርት ለማሟላት „እናት“ የሚለውን እዮራዊ ጸጋዊ የፈጣሪ ቅብዕ አላት። ነገር ግን መፈጠሩ በራሱ በመፈጠሩ ውስጥ እንዲኖር ካልተፈቀደለት ጨለማ ነው። ጨለማ በህሊና ውስጥ ሲከትም እንደ ማለት። ህሊና በጨለማ ሲዋጥ በእዝነ ህሊና ሲታሰብ ሰው የሚለው ስብዕን ማሰብ አቁሟል ማለት ነው። ጨለማነት ሰውነት ሆኖ የዴሞክራሲ መሪ?!
v ክቡር ሆይ!
ግን ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር እንደ ሰውም እንደ ሴትም ማዬት ይቻላልን? ትግሬ ስለሆኑ አይደለም። እኔ ምኞቴን ብነግረዎት አውስትራልያ ፐርዝ የሚኖሩት ቅዱስ የትግራይ ሰው በቀጠታ ሹመት አቶ ገ/ መድህን አርእያ ዶር ሙለቱ ተሾሞ ወርደው እሳቸው ፕሬዚዳንት ሆነው በቤተ መንግሥት ማዬት ይናፍቀኛል። ሰብዕናቸው የዕውነት ሥነ - መዘክር ስለሆነ።
ሄሮድስ መለሰም ዜናዊም ቢሆኑ ትግሬ መሆናቸው እኔን ቅንጣት ታክል አይረብሽኝም። እኔን ፈጠረኝ የምለው ታቦቴ ጓድ ገ/ መድህን በርጋ ጉራጌ ነው። ሰብዕናቸው ነው የእኔ መለኪዬ። ስለሆነም እሳቸው እራሳቸው ወ/ሮዋ ደም በተነከረ እጃቸው ዴሞክራሲን ያህል፤ ሰብዕዊነትን ያህል ግዙፍ የመንፈስ ሃላፊነትን፤ እናትነትን ያህል ቅዱስ ነገር እሸከማለሁ ብለው መረከባቸው ገርሞኛል። ሰብዕናቸው ይህን ታሪካዊ ድርሻ የመሸከም አቅም / አቅልም በህልሙም ሊያስበው አይገባም።
እንደ አቶ ደመቀ መኮነን እራሳቸውን ከጠ/ ሚር በፈቃዳቸው እጩነት እንዳገለሉት ብልህነት፤ እንደ ቀድሞ ጠ/ ሚር ሃይለማርያም ደስአለኝ በፈቃዳቸው መልቀቅን እንደ ወደዱት ብሩኽነት አልመጥንም ብለው ሥልጣኑን መመለስ ይኖርባቸው ነበር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሄር። ሰው ከሚለው ተፈጥሮ ጋር ለመተዋወቅ የማይፈቅዱ፤ በተዘጋ መንፈስ ውስጥ የሚኖሩ ዝምብሎ ሰው ናቸው። ፎቷቸው እኮ ይናገራል እንኳንስ ታሪካቸው።
v የተስፋዬ ክቡር ሆይ!
በዚህ ሹመት ተስፋችን መሞት ብቻ ሳይሆን የሥነ - ልቦና ጥቃትም ደርሷል። ከእስር የተፈታውን የአቶ አንዱአለም አራጌን ፎቶ እና ናዚዝም ሲያበቃ ከእስር የተፈቱትን አትሜ አስተያዬሁት አንድ ነው ተመሳሳይ። አሁን እኔ ብነግረዎት አርበኞቼን፤ ጀግኖቼን አቶ አንዱአለም አራጌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን እያዬኋዋቸው ማድመጥ አልችልም። መጻፍ አቅቶኝ አይደለም ከተፈቱ በኋዋላ እማልጽፈው ሳሰባቸው ዕንባዬን መቆጣጠር ስለማልችልም ነው።
ኢሜል እንኳን በእነሱ ጉዳይ የማከብራቸው ወዳጆቼ ሲልኩልኝ ከአመሰግናለሁ ውጪ ቀጥዬ መጻፍ አልችልም። እነኝህ የነፃነት አርበኞች እኮ ልጅ አላቸው። አሁን በቅርቡም አርበኛ አንዳርጋቸውን ጽጌን ሳይ ከሙሉ ሰብዕናቸው ህሊናቸው በነበረበት ቦታ መሆኑን የሰማይ ታምር ነው። ቆራጣ ተስፋ ህሊናቸው እንደ ተፈጥሮው እናገኘዋለን ብዬ አስቤ አላውቅም። ከድንቅ በላይ ነው። ስንብት ነበር አማስበው።
አካላቸው ግን እጅግ ተጎድተዋል። ሞልቼ ለማዬት አቅም አንሶኛል። ይህ በህፃናት አእምሮ ውስጥ በምን መልኩ ሊቀመጥ እንደሚችል ፍች የሌለው በትረ ጉዳይ ነው። እኔ እራሴ እንዴት አድርጌ ልያቸው? እኔ ፎቶ ውስጡን ነው የማዬው። ለእኔ ፎቶ ማለት ራዲዮሎጂ ሁለመና ማለት ነው።
እራሳቸው የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ልጆች ምስላቸው በወያኔ ሃርነት ትግራይ በአልአዛሯ ኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን ጭካኔ በሥነ - ቅርስነት ደረጃ ምንም ነገር ሳያስፈልግ በሥነ- ዝክረነት ማስቀመጥ ይበቃል። የኢትዮጵያን የ27 ዓመት የመከራ ዘመን ዝም ብለው ወንበር ላይ እነኝህ አርበኞች ቢቀመጡ በዓለም አደባባይ ቁጭ ቢሉ አንደ ቅርስ ሊታይ የሚገባው ጥቁሩ ታሪክ ነው። በዬዘመኑ ይሄው ነው የኢትዮጵያ እናቶች የመከራ ተራራ።
ሦስቱም የዕንባ ዘመን ቅርስ ናቸው። አሁን በቤንሻጉል ላይ የተፈጠረው ወገኔ ሲታይ ራሱ ቅርስ ነው ዓይን የሚወጣበት ዘመን። የሰው ልጅ በአላዛሯ ኢትዮጵያ መሞከሪያ ጣቢያ ነው የሆነው። በቃ ስለ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሌላ ማብራሪያ አያስፈልገውም። እና ከዛ መንፈስ ውስጥ ለዛውም ጫካ የነበሩ ሴት ከመጠን ባለፈ በትግራዊነት ያበዱ ሴት የአላዛሯ ኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ተስፋ ያሟላሉ ብሎ መታሰቡ ራሱ ለተስፋ የተፈረደበት የሞት ፍርድ ነው። ቅጣት ነው።
ለተበደለው ህዝብ ተጨማሪ መቅጣጫ ሳንጃ ነው። ያን በደል እስኪ እንርሳው ቢባል እንኳን እሳቸውን ከዚህ ቦታ አስቀምጦ በፍጹም አይሆንም። እንዴት ታሰበ እራሱ? 50 ሺህ ወጣት አንድ ወር ባልሞላው ጊዜ የታሰረው ለወ/ሮ ፈትለወርቅ የዴሞክራሲ ሚ/ርነት ማዕረግ ለመሪነት ነበርን? ይሰቀጥጣል። ይጎመዝዛል። ያንገሸግሻል።
v ክቡር የኢትዮጵያ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ሆይ!
ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ የት ነው ያሉት? ቀደሞ ነገር ይህ መዋቅር የፖለቲካ ድርጅት ሰዎች የሌሉበት በነፃ የሚያስቡ ሰዎች ብቻ ሊሆኑ ይገባል። ከጽዳተኛ ሰራተኛ ጀምሮ አወቃቀሩ በዚህ መልክ መሆን አለበት። ጠረኑ የቢሮው የስታሊን መንፈስን የተጠዬፈ መሆን አለበት።
ቢሮው የጫካዊነት አረመኒያዊ መንፈስ መሞከሪያ የምርምር ማዕከል መሆን አይገባውም። ዓውዱ ሰው የመሆንን ተፈጥሯዊነትን የሚገልጽ ሆኖ መደራጀት አለበት። ልክ ክብሩነተዎት ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን ከቅጽር ግቢው ጀምሮ እንደ አደራጁት።
ስለ ሰው አፈጣጠር ዕጹብ ድንቅነት የሚያዘክሩ የቅርስ ተቋም መሆን ይኖርበታል። በአዲሱ ቋንቋ ሰው ሰው የሚል ጠረን። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚልን ጠረን መሆን አለበት። ኢትዮጵያዊነት ለወ/ሮ ፈትለወርቅ ምናቸው ነው? ሰው ማለትስ? ተፈጥሮ ማለትስ? ሴት መሆን ማለትስ? ርህርናስ ምናቸው ነው? ደግነት ምናቸው ነው? ምንም ነው።
ሴት የትግራይ መርማሪ እኮ የወንድ እሰረኞችን የዘር ማፍሪያ ደፍራ የምታንኮላሽበት ዘመን? ለዛውም ለወግ አጥባቂው ለትግራይ ማህበረሰብ። የወያኔ ማንፌስቶ ትርፉ፤ የግንቦት 20 ትሩፋቱ ይሄው ነው። ይህንን ነው ድላችን የሚሉት።
ለዚህ ሥፍራ ከፖለቲካ ውጪ የሆኑ ግን ሰለሰው ግድ የሚላቸው ሩሁሩሃን ብቻ ነው እዚህ መግባት ያለባቸው። ደግ ሰዎች በዬተቋሙ ተመርጠው። ባልደረቦቻቸው ራሳቸው ድምጽ የሰጧቸው መሆን አላባቸው። ግን ዕውቀቱ ያላቸው። እጅግ በበሰለ፣ በተጠና በጥንቃቄ መከወን አለበት።
ሰው ስለመሆን ህጋዊ ዕወቅና የሚሰጥ ተቋም እኮ ነው ይህ ቢሮ። ከታች ጀምሮ በመልካም ሥነ - ምግባራቸው፤ በማህበረሰቡ ኑሮ ተቀባይነት፤ በኢትዮጵያዊነት ኩራታቸው፤ በተፈጥሯቸው ህግ አዋቂነታቸው፤ በዜግነት ተቆርቋሪነታቸው ርህርህና ያላቸው መሆን አላባቸው። ኢትዮጵያዊነታቸውን የማያፍሩበት፤ የማይሸማቃቁበት።
ኢትዮጵያዊነትን የክብሬ ተክሊል የሚሉ ዜጎች መሆን አለባቸው። ከዚህ ቅዱስ ስፍራ የሥራ ባልደረባ መሆን ያለባቸው ንጹሃን እንጂ የዘራፊዎች ማህበር መሪ፤ የጭካኔ መሪ፤ የሰው መንፈስ ሰራቂ መሪ መሆን አይኖርባቸውም። ለዚህ ቦታ ምቀኞች፤ ቂመኞች፤ ዘረኞች፤ ኢ - ሰባውያን፤ ኢጎ ውስጣቸው የሆነ ሳይሆኑ በፍጹም ሁኔታ የአውንታዊ አርበኛ የሆኑ ቅኖች መሆን አለባቸው ለዚህ ቦታ የሚታጩት።
የተቀደሰ መንፈስ ነው ዴሞክራሲ። ዴሞክራሲ የሰባዐዊነት ቤተ - እግዚአብሄርም ነው። ዴሞክራሲ እኮ የወንጌልም/ የቁራንም አካል ነው። መልካምነት። መደማመጥ። መምራት፤ ለመመራት መፍቀድ ቅድስና ነው ዴሞክራሲ። ራስን ለመምራት ለመግዛት መፍቀድ - እራሰን ማሸነፍ ነው።
ለዚህ ቦታ ይመጥናሉ የሚባሉ ዜጎች በሰብዕናቸው ውስጥ ምንም እንጥፍጣፊ ምቀኝነት የሌላቸው፤ ህግ የማይተላለፉ፤ በዬትኛውም ሁኔታ በግድፈት እና በጉድፍ ሰብዕና የማይጠረጠሩ፤ ፈርሃ እግዚአብሄር ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋል።
ህግን ከተፈጥሮው የተረዱ። ሀገር በቀል ይሉኝታን ያከበሩ የወደዱም መሆን አለባቸው። በመንፈስም ሌቦች ያልሆኑ። ሌብነት ያልተጋባባቸው፤ ሌብነትንም የማይናፍቁ፤ የእነሱ ያልሆነውን ማናቸውንም የክብር ቁርጥራጭ የማያጩ መሆን አለባቸው።
ለዚህ መዋቅር ካድሬነት፤ የማንፌስቶ ማህበርተኝነት፤ ጎሰኝነት መስፈርት ሊሆን አይገባም። የሚያስፈልገው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ብቻ ነው። የሚያስፈልገው የመዳፍም የመንፈስም ንጽህና መኖር ብቻ መሆን ይገባዋል። የዴሞክራሲ ቁመና ለማኒፌስቶ ኢጓዊ መስመር አይገጥምም። መዋቅሩ ከላይ አስከታች በዚህ መንፈስ ነው መደራጀት የሚገባው።
v ክቡር ሆይ!
አንድ ምሳሌ ልስጠወት እኔና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሄር በምን ቋንቋ እንግባባለን? ድልድዩ መገናኛው የተሰበረ ነው። እኔ እና ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ ግን በመንፈስ ቤተኛ ነን በሚደንቅ ሁኔታ። ዛሬ አይደለም በቀደመ ሁኔታ። እኔና የዶር ምህረት ደበበ ቤተኛ ነን በመንፈስ ዕጹብ ድንቅ በሆነ ሁኔታ። እኔ የተዋህዶ አማኝ ነኝ። ጠንከር ያልኩ አማኝ። ዶር ምህረት ደበበ ደግሞ የፕሮቴስታንት ዕምነት ሰባኪም ናቸው። ግን እኔ በስብከታቸው ውስጥ ያለው የህሊና ንጽህና እና እኔ ላለኝ የፍቅራዊነት አንስተኛ ፕሮጀክቴ ቅርብ ስለሆነ ተመችቶኝ ነው የማዳምጠው። ሰብዕናቸው በዛ ውስጥ ስላለ።
ዶር ገመቺስ ደስታም በፍቅር ነው እመከታተላቸው። የማንተዋወቅ ሰዎች በአካል ግን የመንፈስ ንጽህና ራህብተኞች ስለሆነ ማህበርተኞች ነን - በቅንነት ጋላሪ። እነሱ አያውቁትም ከዚህ ሲዊዝ አንዲት ድሃ ማህበርተኛ እንዳለቻቸው። ሌላም ልጠቀስ የቡድሃ ሃይማኖት ተከታይ በስደት ህንድ የሚኖሩ የቲቤት ዜጋ የፍቅር አባት Dalai Lama (Tibetan spiritual leader) ጀርመን ካለው ንጹህ መንፈስን የመፍጠር ዩንቨርስቲ ጋር የሚሰሯቸው ድንቅ ተግባራት የልቤ ስለሆነ እከታተላቸዋለሁኝ። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ይህን ጉማም፤ ጎማማ ዓለም፤ ወደ እኛም እንዳይመጣ ኢትዮጵያንም ሊለውጡ ስለሚችሉ። ሰውን የሚመራው መንፈሱ እና ረቂቅ ንጹህ ስሜቱ ነው። ያን ቅጥ ማስያዝ ከተቻለ ማመጣጠን ይቻላል። መከራ እንኳን ቢሆን ይቻላል።
ፍቅርን ተፈጥሮውን የማያውቁ ሰዎች ለማድመጥም ጊዜ የላቸውም። በፍቅር ውስጥ ለመኖር የፈቀዱ ሰዎች ለእኔ ሃይማኖታቸው፤ ዘራቸው፤ የቆዳ ቀለማቸው፤ የሚኖሩበት አህጉር ቦታ የለውም። ፍቅር ፍልስፍና ብቻ አይደለም ሰማይ እና መሬት ማለት ነው። እርእስ ጉዳዩ የዘመናት የመኖር የትምህርት ክ/ ጊዜ ነው ፍቅራዊነት።
በስፋትም፣ በመጠንም፣ በቅርጽም፣ በይዘትም፣ በቀለም፣ በቁመናም ልንለካው አንችልም - ፍቅራዊነትን። ፍቅር ተፈጥሮው ክስተት ነው። አያልቅም፤ አይቆምም። ሰሞኑን የተካሄደውን የታላቋ ብርታንያን የልዑል ሄሪ ቻርለስን ጋብቻ እንውሰደው።
ጠይም ዕንቁ ተዋናዊት ሜገን ማርክል በህጋዊ ደረጃ አግብታ የፈታች፤ ወላጆቿ በጋብቻ ጸንተው ያልኖሩ፤ በቤተሰብ አመራር አደረጃጃት ወስጥ የጎደለ በብዙ ሁኔታ ያለበት፤ በዕድሜም ባለቤቷን የምትበልጥ፤ የታላቋ ብርቴን ሙሉ ደም የሌላት፤ የአፍሪካዊነት አማሪካዊነት ዝርያ ያላት፤ ከልጅነት እሰከ አሁን ባለው ጊዜ ውስጥ በትጋት ውስጥ በሰዋዊነትን የኖረችበት፤ በወጣትነት ዕድሜዋ ባላት ዕወቅና ደረጃዋ ሰውነቷን አጋልጣ የካሜራ ራት ያላደረገች፤ ስለሴትነቷ ጠበቃ የሆነች፤ ስለድሃ የዓለም ዜጎች ዋቢ የሆነች፤ ያን ወግ አጥባቂውን የታላቋ ብርታንያ ቤተ መንግሥት ታሪክም ደግሞ የማያገኛቸውን የማጅስቲን ይሁንታ አግኝታ ጋብቻ ፈጸመች።
በማን ሃይል? በማን አቅም? በማን ችሎት? በፍቅር ተፈጥሮ እና መርህ። ፍቅር የሌለው ሰብዕና በኢትዮጵያ የዴሚክራሲን ሥርዓቱን አይደለም ህልሙንም ማሰብ ይከብዳል። አቅሙ ደሃ ነው። ድህነት የፍቅር ያለበት ሰው የነቃው የህሊና ክፍሉም ደሃ ነው። ፍቅርን ተፈጥሮውን የማያውቅ ማንኛውም ሰው የህሊና ድርቀት ያለበት ነው።
የፈለገ ይማር፤ የፈለገ ሥልጣን ይኖረው፤ የፈለገ ዴታ ይሁን፤ የፈለገ ተመክሮ ይኖረው፤ ፍቅራዊነት በመንፈሱ ውስጥ ባሉ ንጥረ ነገሮች ገላጭ ሁኔታዎች ከነጠፉበት ወና ነው። ኮትም፣ ሱሪም፣ ገበርዲንም፣ ከረባትም፣ እጀ ጠባብም፣ ግብግብም፣ ቁምጣም፤ ሽብሽቦ፤ ሙሉወርድ፤ ሱሪና ኮት የለበሰ ሰው እንዲሁ፤ ሰው ሁኖ በመፈጠር ውስጥ አለመፈጠርን የወሰነ ማለት ነው የፍቅርን ተፈጠሮ የከዳ።
እኒህ ሴት እንዲህ ናቸው። ለራሳቸው ሳቅን የነፈጉ የዕድሜ ልክ የጸጸት ቤተኛ። ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሄር የመኖርን ተፈጥሮው አልኖሩበትም። ኖርኩ ቢሉ በጥበት በጥብቆ በተቸነከረ መርዛም ዘረኝነት፤ ከቀለሃ ጋር እና ከዛ ድፍን ካለ የማረተ ርዕዮት ዓለም ጋር ነው። ልባቸው ጥቁር ነው። ለወደፊትም ከሰብዕናቸው ስነሳ ወደ ተሻለ ሰብዕና ለመምጣት ፈቃጅም አይደሉም። የሴት ጨካኝ ሴት መሆንን ይደምስሰዋል። ሴት ጨካኝ የሆነች እለት ጾታዊ ክብሯ ተገፏል።
የፈለገ ይሁን ቦታ ጊዜ፤ ሁኔታ የሚሰጠው ዕድል አሹላኪ ከሚያደርገው ዋነኛው አመክንዮ ታላቁ ይህ ወሳኝ ቦታ አለቦታው መቀርቀሩ ነው። የተገባ ውሳኔ አልነበረም። ሁሉም ቦታ ተግኝቶ ማስተካከል አይቻልም። ሃላፊነት ሲሰጥ የራስንም ሃላፊነት በተወሰነ ደረጃ የሚቀንስ፤ የሚረዳ መንፈስ መሆን ይገባል። መቼስ ጥሬ ተስጥቶ ሙሉ ቀን ዶሮ ሲጠብቁ ዓይነት ከሆነ የአቅም ብክነት ነው፤ ለሌላ ትኩረት ለሚሻማ አጣዳፊ ጊዜንም ይሻማል።
ውጪ ጉዳይ ሚ/ር ላይ ስጋት የጠ/ ሚር ቢሮ ላይኖርበት ይቻላል። በአምሳሉ የፈጠረው መንፈስ እዛው በመልካም ሁኔታ ሰሞኑን ስላደላደለው። በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ሚ/ርም ተከታዩ ዲኤታ ሹሙ ወደ ውጪ ጉዳይ ሚ/ር ቢዛወሩ ችግር የለበትም አናቱ ተመሳሳዩ አቅም ስላለ ብዙ ሃላፊነቶችን ያቃልላል። ይህ እሸታዊ ዕድል ግን በዴሞክራሲ ግንባታ ላይ መታሰቡ፤ መወሰኑ ግን ፈጽሞ ሊታሰብም ሊገመትም ሊታለም አይችልም።
ሌላ ቦታ ወስዶ እኮ ሚ/ር ማድረግ ይቻላል። መቼም ያ መከረኛ ህዝብ መመኮሪያ ነው እንደ ጥንቸል ስለሆነ። ይህ ግን ፈጽሞ ሊሆን ያልተገባው ውሳኔ ነው። ራሱ ከኢህዴግ ግንባር አባልተኝነት ለዚህ ቢሮ መታሰብ አይኖርበትም። ጠቅላላ ቢሮው መጽዳት አለበት። ሽግሽጉ የሚ/ር መስሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆን ከላይ እስከ ታች ያለውም በጥራት እና ሰው በመሆን መንፈስ በአዲስ መልክ መገንባት ከሁሉ ቀዳሚው ተልዕኮ በሆነ ነበር።
የኢትዮጵያ እንደ ገና መወለድ ማህተሙ ይህ ቢሮ ባለው አቅም እና ልክ ይወሰናል። ተስፋው ተስፋውን ከማያገኝበት ቦታ ነው የተቀረቀረው። የዴሞክራሲ ፍልስፍናው እኮ ነፍስን ማስቀጠል ነው። ለነፍስ ነፍስን አጥፊ መድቦ እና ሃላፊነት ሰጥቶ አይሆንም። ይሄ እርምጃ ኦህዴድንም ከነመርኩቡ የሚያሰምጥ ነው። እንደ ገና በእነ አቦይ ስብሃት ነጋ የፖለቲካ አማካሪነት? ታጥቦ ጭቃ ነው። ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። ተስፋውን ቀራንዮ ላይ ብቻ ሳይሆን ጎለጎታንም ያከለ ነው። ሞት እና መቃብር።
v ቢሆን? ከተቻለ?
ከት/ ተቋማት፤ ከጤና ተቋማት፤ ከመምህራን፤ ከኪነ ጥበብ ሰዎች፤ ከፈጠራ ሰዎች፤ ከህግ ባለሙያዎች፤ ከሽምግሌዎች፤ ካባህላዊ ዳኞች፤ ከህግ ባለሙያዎች የተውጣጣ ህብረ ቀለማት በእውቀት፤ በተምክሮ የተመሰረተ አካል ነው ለዚህ ቦታ ሊሆን የሚችል። እዚህ ቦታ ላይ ርፍራፊ፤ ቅንጥብጣቢ የኢህዴግ መንፈስ ወይንም የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እንዲኖሩበት አልሻም እኔ በግሌ። ነፃ ሆኖ የሚያስብ፤ ነጻ ሆኖ የሚሠራ ንጹህ መንፈስ እንዲኖር ነው ምኞቴ። ስለሆነም ጥያቄው ጊዜ ተውስዶ፤ ተጥንቶ ጠቅላላ የመዋቅር ለውጥ ያስፈልጋዋል ባይ ነኝ።
ጥገናዊ ለውጥ ለሌሎች ተቋማት ይሁን። እዚህ ግን እእ። እኛ እናንተን አብይ ለማ ገዱ አንባቸውን መንፈሳችን የፈቀደነው እኮ ሰዋዊ መንፈሳችሁ እንጂ የግንባር ድርጅታችሁ ትዝ ብሎን አያውቅም። እሱን እማ ብናስብ አንቀራረብም ነበር። ብሄረሳባችሁ እና ሃይማኖታችሁ አስታውሰነው አናውቅም። የምናስበው መልካምነታችሁን፤ ምህረት መሆናችሁን ብቻ ነው። ለተስፋ የተላካችሁ ሐዋርያ መሆናችሁ ብቻ ነው የሚታሰብን - ለቅኖች።
ይሄን መንፈስ ዕውን ለማድረግ አዲስ መዋቅር መሥራት ያስፈልገዋል ትላላች ትቢያ ላይ ያለችው ሥርጉተ ሥላሴ ዜጋ ከሆነች፤ የአላዛሯ ኢትዮጵያ ሴት ልጅ ከሆነች፤ እኔም ከቤተሰቦቼ የወረስኩት ባድማ አገር አለኝ ብዬ ካመንኩኝ፤ መሪም አለኝ የምለው፤ እኔንም ሩቅ ነው የምትኖር ደሃ ናት፤ ታዋቂ አይደለችም ሳይል ሊያደምጠኝ ሲፈቅድ ብቻ ነው። መዋለ ዕድሜያችን የባከነበት አመክንዮ እንደ ገና ከሳጥናኤል ሥር ወድቆ ፈቃድ ዴሞክራሲ አቧራ ለብሶ ተንበርክኮ ይለምን? ግፍ ነው። የእውነት ዱላ ነው።
· ለነፃ ሚዲያ፤ ለነፃ የሲቢል ድርጅት፤ ለነፃ የፍርድ ሥርዓት፤ ለነፃ አስተሳሰብ፤ ለነጻ የምርጫ ቦርድ፤ ለነጻ የመጻፍ፣ የመናገር፤ የመደራጀት፤ ለነፃ መኖር፤ ለነፃ መተንፈስ፤ ለነፃ በመኖር ውስጥ ለማይቀረው ለሞት ለራሱ ይህ መዋቅር ሰቁ ቅስቱም ነው። ስለዚህ በሹመቱ ተከፍቻለሁኝ። ልቤም እንደ ዱባ የተቀረደደበት ሹመት ነው።
ተስፋዬን ባይረስ እንዲፈታተነው አድርጎታል። ሴት አቅም ከሌላት ሴት በመሆኗ የሚ/ር ደረጃ ቢሰጣት አያረካኝም። ስለዚህ ገዳይ፣ ጨካኝ፣ አረመኔ፣ ሌባ፣ ዘራፊ ስብዕና ሴት ስለሆነች ብቻ ትምራኝ አትልም ሥርጉተ ሥላሴ፤ ወ/ሮ ሄሮዳዳይ ዘራፊዋ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ሴት ናቸው እኮ ላዛውም እሳቸው ቢክዱትም የቃብቲያ ሰው ናቸው ሌላው ቢቀር። ግን ስታገላቸው ነው የኖርኩት።
እኔ መላ ይፈለግለት አይደለም የምጠይቀው የታቃዋሚ ድርጀቶች ተፎካካሪነት፤ የሲቢክስ ድርጀቶች ነፃነት፤ የሴቶች ተፈጥሯዊ የማድረግ አቅም እኩልነት ከተፈቀደ ይህ ድርጅት በጠቅላላ በአዲስ መንፈስ አዲስ መልክ ይዞ ይዋቀር ነው። ቢያንስ የዶልፊን ያህል አቅም ይኑረው።
የወንዶች የፖለቲካ ዓለም ሲያረጁም እስከ እነ እርጅናቸው ፖለቲካዊ ሥልጣን እንደ ጠማቸው አኖሯቸዋል። ስለዚህም ኢትዮጵያ ተስፋዋ ሁሉ በጎድን የተለካ ነው። ግን ሴቶች በፖለቲካው ዓለም እኩል ዕውቅና እንዲኖራቸው እምታገለው ለእኩልነታቸው እንጂ ሰውነታቸውን ለሰረዙ ለጥቁር ልቦች፤ ለጨካኞች አንስት አይደለም።
ሰብዕናቸው የተሟላም ሆኖ ግን ለቦታው ካልመጠኑ ሴትነታቸው ይጋርድላቸው የሚል ልፍስፍስ ራሱን ያልቻለ ፍልስፍናም የለኝም። ሴት እኩል ለመሳተፍ አቅሟ ሴትነቷ የሰጣት ጸጋ ሳይሸራረፍ ተግባራዊ ለማድረግ የምትጥረዋን ነው እንዳትገለልብኝ የምፈልገው። ቁጥር - ኮታ - ተዋፆ - ይህን ያክል የሴት ሚ/ር ተሾመ በእኔ ቤት ቦታ የላቸውም። ራስን ማብቃት ያስፈልጋል። የጣረች፤ የተጋች፤ በተግባር የተፈተነች ምስጉን ሴት ማለትም በሶሻሊዝም አቅመ ቢስ ፍልስፍና የተደቆሰች ሁለገብ ሴት አቅሟ ዕውቅና አግኝቶ በልኳ፤ በመጠኗ፤ ፈጣሪ አምላክ ለይቶ በመረቃት እናታዊ ጸጋዋ፤ ስለእናቷ በእናትንት ትሁንላት ነው።
አቅም ላነሳትም ናሙና ሆነ ህይወቷ አንዲስተምር ሆና ትግኝ ነው። ሴትነት ሲባል ብቻ ያለ ቦታዋ፤ ያለ አቅሟ፤ ያለ ክህሎቷ ሹመት ይቆለልላት አይደለም ሙግቴ። አቅሙን እንድታመጣ ሁኔታ ይመቻችላት። ስትበቃ ደግሞ ከምትመጥነው ቦታ ፆታዋ ሳይገፋ አቅሟ የፈቀደው ደረጃ ይሰጣት ነው። በዚህ ኦሮምያ ላይ የተሻለ የአቅም እንክብካቤ ነበርው። አሁን ቦታ ለመስጠት ችግር አልሆነበትም። ሌላ ቦታ ግን የከሳ ነው። አማራ ተቀብሮ የኖረ ነው። እንኳንስ አንስት ተብዕቱም ፍዳውን ሲከፈል ሲከረኮም ነው የኖረው።
አቅም እና ችሎታ ሳይሆን መለኪያው ጎሳ ስለነበር፤ እድሉንም ያገኙት አቅምን በማጎልበት ሳይሆን ያው የጎሳውን ትክሻ ተጠልለው ስለሆነ ወደ ፊት የመራመድ አቅማቸው ሰላላ መላላ ነው።
እኔ የህልሜ ቀንበጥ እምላቸው አንስታዊት አንበሳ መሪ „ምን ይታዬናል? ድመት ሆነን አንበሳ? ወይንስ አንበሳ ሆነን ሰው? ወይንስ ሰው ሆነን ሰው?“ የሚሉትን ነው። እኒህ ብቁ ለግላጋ ወጣት ሙሁር፤ ትሁት፤ የሰውነት ታታሪ አንስት ይንፍቁኛል። ዴሞክራሲ ታጭቶ በወረቀት ኮታ አይሆንም።
የመጀመሪያው የዴሞክራሲ ጥያቄ ሰው መሆን፤ ሴት ከሆነች ከጭካኔ ጋር ያልተነካካች፤ እጇ ደም ያልነካው፤ መንፈሷም ደምን የማያልም፤ ርሁሩህ እናታዊ ሰብዕና ያላት መሆን አለባት። ቢያንስ የኢትዮጵያ ህጻናት በሙሉ ልጆቼ ናቸው የምትል። ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ እኮ „ሳይንቲስት ለመሆን ሰው ብቻ መሆን ይበቃል፤ ከቶ ምን ይታዬናል? ድመት ሆነን አንበሳ ወይንስ አንበሳ ሆነን ድመት? ወይንስ ሰው ሆነን ሰው? መምህር ሆነን ተማሪዎቻችን፤ አለቃ ሆነን የበታቾቻን ለማብቃት ምን የጎደለን ነገር አለ? ሁላችንም አድገን አልጨረስንም“
ክቡሩ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ይህ እኮ ቃለ ህይወት ነው። ይህ እኮ ለእስልምና ዕምነት አማንያንም ቁራዕን ነው። በምድራዊ ሲተረጎም የተፈጥር የሰው ሥነ - አቅም፣ ሥነ - ሰብዕና፤ ሥነ - ሞራላዊ ፍልስፍና ነው። ይህችን የመሰለች የድንቆች እንቁ ያለቻት አላዛሯ ኢትዮጵያ ስለምን የገዳይ መዳፍ ናፈቃት? ስለምንስ የጭካኔ ፍታውራሪት ሴት፤ የዘራፊ ሴት ተምሳሌን መሾም አሰኛት?
ዴሞክራሲ እኮ ለነጻነት ጉሮሮው ማደሪያው፤ ማደራደሪያውም ነው። አላዛሯ ኢትዮጵያ ስለምን ወደኋላ ለመመለስ አለመች? ለመሆን የኢ - ሰብዕዊነትት መሪ ራህብተኛ ሆነችን? ጭካኔ እንደ ገና እንዴት ትናፈቅ ኢትዮጵያ? ደንብልብል ብሎብኛል። ጥገናዊ ለውጥ ሰጥቶ መቀበል ስለመሆኑ አውቀዋለሁኝ። ግን ጉሮሮ ተዘግቶ አይደለም። የወያኔ ማንፌስቶ ጽንፈኛ ሴት እንዴት ለሰብዕ ቀረፃ ይሾማሉ? እንዴት ለዚህ ቦታ ራሱ ይታጫሉ? መርግ ነው።
በፍጹም ሁኔታ የወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሄርን የዕውነተኛ የዴሞክራሲ መሪነት ጉዳይ አንዲት ቅንጣት መንፈስ ይህን ውሳኔ አይደግፈውም። አንዲት ራፊ የህሊና ርስት አያገኝም ወሳኔው።
ቅብዕ ሹመት ለመልካም ሆነ ለመልካም ላልሆነም ነው። የወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሄር ደግሞ የ27 ዓመት መከራ እንዲያገረሽ፤ በቀል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በስውር እንዲፈለፈል ለጥ ባለ ሜዳ እና ሰጋር ሰረገላ ተሸልሞ መጪ በል ተብሎለታል። ይህ ጥያቄ የሚሊዮኖች ድምጽ እንደሚሆን አስባለሁኝ።
አንድ መልካም ነገር ብዙ ቁስሎችን እንደሚፈውስ ሁሉ አንድ ወደል የበደል መጨመሪያ ግድፍት ደግሞ የመቁስል አይደለም የመግደያ ባሩድ ነው። የተሰባሰብ ቅን መንፈስ መበተኛም መሳሪያ ነው። እንኳንስ ይህን መሰል የተጨማሪ ቁስል ማመርቀዣ ሹመት ቀርቶ በሰላሙ አገር የነበረውን መታመስ ያሉበት፤ የነበሩበት ነው። ያን ሚዛኑን ለማስጠበቅ „ከጣና ኬኛ“ ጀምሮ የደከሙ ሰዎች ያውቁታል። አሁን በወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሄር ሹመት ተጨማሪ ግዳጅ የማንችለው ግማድ ደረበብን የጠ/ ሚሩ ቢሮ።
ይገባኛል የክቡርነትዎትን ንጽህና አስበው ነው ከመዳፍ አይወጣም ብለው ሊሆን ይችላል። ሰው ጥንቸል አይደለም። ሁልጊዜ ዜግነት መሞከሪያ ጣቢያ እንደ ጥንቸል ሊከፈትለት አይገባም። ወያኔ ሃርነት ትግራይን ማንፌስቶ በቃኝ ማለት ይሔው ነው። ዴሞክራሲ ታንቆ ፍትሃዊ ምርጫ የለም። ይህ ሹመት ሌላ ቦታ ነው የሚሰራው 50 ሺህ የአማራ እና የኦሮሞ ወጣቶች፤ አዛውንታት፤ ጎልማሶች፤ ባህታውያን፤ ህጻናት ደም ገብረበውታል። አንብተውባታል። ዋጋው ተመጣጣኝ አይደለም።
አንባ ጊዮርጊስ ጎንደር ወገራ አውራጃ ነው የሚገኘው። ይህ የድሆች ከተማ 26 ህጻናት ከሱዳን በታገዙ ወታደሮች ተጨፍጭፈዋል። እናቶች እናታችን ድንግል ማርያም ልጇን አዳኛችን ለማዳን ከእስራኤል ወደ ግብጽ የተሰደደችበት ዘመን በዛ ደሃ ከተማ ተፈጽሟል።
የረባ በር ያለው ቤት እንኳን የለም። ህጻን ወንድ ልጅ ያላቸው እናቶች ሁሉ እስከ ቆላ ወገራ ድረስ በመዝለቅ ጫካ ገብተዋል። ወጀቡን ለማሳለፍ። ታዲያ እኒህ ሴት ለዚህ ለተጋፋ ማህበረሰብ ድምጹን የመስማት ቀጥተኛ አቅም አላቸውን? ግፍ ነው? እጅግ ግፍ ነው። ከበደልም የከረፋ ግፍ ነው። ይጎፈንናል።
ቢያንስ የእነኛ ምንም ሳያውቁ ሙሉ አካላቸውን መሸፈኛ የሌላቸው ህፃናት ደም እንደ አቤል ደም ይጮኸል! በእስር ቤትም የሚፈጸመውን ሰምተውት የማያውቁትን ክፉ ነገር፤ ዘር የሚነቅል ታሪክ በአካል ባገኘዎት እነግረውት ነበር። ቤተሰቦቼም አያውቁትም፤ እዚህ ያሉ ሁለት ነጭ ጓደኞቼ ብቻ ነው የሚያውቁት።
ያ የራህብ የዴሞክራሲ የተስፋ ጊዜ እንደ ገና ለገዳይ ሲሸለም ያሳብዳል። ዕውነት ያሳብዳል። መጀመሪያ ሰው ይሆኑ ዘንድ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሄር ሱባኤ ይግቡ፤ ይጠመቁ፤ ለነገሩ ሃይማኖት የላቸውም። ይህም ቢቀር ሰው እንዲሆኑ ት/ ቤት ይከፈትላቸው። ሰው ያልሆነ ሰው ምስል ብቻውን ልብስ ስለለበሰ ሰብዕና አለው ማለት አይቻልም። ሰውን ለመምራት ሰው መሆን ይጠይቃል።
ዴሞክራሲ በባህሪው ግሎባል ነው። ሰብዕን በሚቀርጽ ታላቅ ግሎባል ተልዕኮ ሰው የገደለ፤ አሁንም ለመግደል የሚናፍቅ፤ በደም የዘለበ ሰብዕና ይህን ታላቅ ዓለምዐቀፋዊ የሥልጣኔ መሰረት ግዳጅ ሊሰጠው ከቶውንም አይገባም። ሙሉ ለሙሉ ከወያኔ ሃርነትም አገር እና ትውፊት ገዳይ ማንፌስቶ ክፉ ጠረን፤ እንደ ግንባርም ከኢህአድግ መንፈስ ውጪ አዲስ ንደፍ እና ፕላን ያስፈልገዋል ቢሮው።
ኢህአዴግም እኮ በመጪው ምርጫ እንደ ድርጅት ተወዳዳሪ ነው። በጓዳ ጅብ አስሮ አይሆን። ከዚህ በተረፈ አይደለም አንድ የሚ/ር ቦታ ጣምራም ሌላ ቦታ ቢሾሙ ክቡሩነታዎት ለሚሸከሙት ጥያቄ የለኝም። ይህ ቦታ ግን በቀጥታ የሞተ አስነስቶ ዲሞ የሚያስወጣ ነው። ስለ ዲሞክራሲ ፍልስፍና እና አፈጸፀም ከእንግዲህ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ከወ/ ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሄር ከአቦይ ስብሃት የሴራ መረብ ተንበርክኮ፤ ተጎንብሶ የሚለምንበት ቅርጥምጣሚ ትዕግስት የለውም። አካሉን እዬፈቱ መንፈሱን ማሰር ለሞተለት ተጋድሎው ሌላ ሞት ሊታወጅለት አይገባም። መኖር ሙቷል፤ ለሞቱ ሌላ ሞት አያስፈልገውም። ሰው ስንት ጊዜ ይሞታል? ስንት ጊዜስ ይገደላል? መኖር ማለት ነፃነት ማለት ነው። ስንፈጠር የተሰጠን የነፃነት እዬር የሸለመን የተቀማን ምንዱባን ነን። ያልታደልን!
አውራ ጥያቄው ቢሮው ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን ሥር - ነቀል ለውጥ ይደረግለት ነው። ጠረኑ ሰውኛ ተፈጥሮኛ ይሁን። ጭቆና፤ ግድያ፤ እስራት፤ ዝርፊያ፤ ወራራ የሚያወግዙ ፓስተሮች፤ ትእግስትን፤ መቻቻልን፤ አክብሮትን፤ ትውፊትን፤ ቅርስን፤ መቻልን፤ ፍቅርን፤ ትህትናን፤ ምስጋናን፤ ህሊናን የሚከብሩ ፖስተሮች አውዱን ይቀኙት።
አዳራሹ ስለ ሰው ልጅ ነፃነት የሚያውጁ የጥበብ ሥራዎች ይንግሥባቸው። ከዛ ቢሮ ሲገባ ገነት የተገባ ያህል የሳቅ - የፍሰሃ፤ ጭንቅና ችግር የሚረሳበት ሁኖ ይደራጅ። አዲስ ቀን፤ አዲስ ቀለም፤ አዲስ ተስፋ ፤ አዲስ ራዕይ፤ አዲስ ሰብዕና የሚናፍቅበት ዓወድ ምህረት ይሁን።
ቤተ መጻህፍቱ ሲደራጅም በደጋግ ሰዎች መንፈስ፤ በተፈጥሮ ጸጋዎች ላይ ምርምር ያደረጉ ጸሐፍት ብቻ ማህበርተኛ የሚሆንበት ሆኖ ይደራጅ። ሁሉም ሰው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከአዕምሮዬ ጋር ነበርኩኝ ብሎ መቼም ራሱን መዋሸት አይችልም። ሁሉም ሥነ - ልቦናው ተጎድቷል። ሁሉም ስጋት ላይ ነበር፤ አዋሳ ላይ አቶ አባተ ሲናገሩ „ቤቴ በሰላም እንደምገባ ተስፋ አለኝ“ ነበር ያሉት። የዜጋው መንፈሱ ተቀምቷል። ዜጋው ሥነ - ልቦናው ስጋት - ፍርሃት - እርግጠኛ አለመሆን ወሮታል።
የወያኔ ሃርነት ትግራይ እኮ ያልቀማው ነገር የለም። በቁመናው ሰዉ መሄድን፤ መልቀቅን እያሰበ ደመንፍሱን ነው የሚንቀሳቀሰውም ለዚህ ነው። መቀመጫ ስላጣ። መቆሚያ ብትን አፈር ስለተነፈገ። ስልጣን ላይ ያለውም የዘረፈውን፤ የገደለው፤ ያደማውም አራሱም ጭንቅ ላይ ነው እሱም ሽሽትን ያለመ ነው።
ከመጋቢት 24 ቀን 2010 በፊት እኮ በመንፈስ 100 ሚሊዮኖች የሚኖሩበት ባዕት አልነበርም። ምድረ በዳ እኮ ነው የነበረው የአላዛሯ ኢትዮጵያ ልጅ የመንፈስ ቀዬ ሁሉ። ስለዚህ ኢትዮጵያዊው ዜጋ ወደዚህ ቢሮ ሲገባ፤ በደብዳቤ ግንኙነት ሲያደርግ፤ በስልክ ሲነጋገር፤ እንግዳ ሲቀበል፤ የመጣን እንግዳ ሲሸኝ ሁሉ ከመንፈስ የሚቀር መልካምነት መኖር ይገባል። ህሊናው በአግባቡ እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል። እዚህ ቢሮ ሰው ሲገባ አቀባበሉ ራሱ ፏ ያለ ቧ ያለ „ርግብ በር“ ያስፈልገዋል። በሩ እራሱ ጠረኑ ሰውኛ - ሳቅኛ - ፈገግተኛ መሆን አለበት። የመንፈስ እርጋታ የሰፈነበት አዬር ቅጽር ግቢውን በሙሉ መሙላት አለበት።
የሎሬቱ ተስፋ እዚህ ቢሮ ውስጥ ዓርማ መሆን አለበት። የመጀመሪያው የአብይ የተሰባሰበ የአትኩሮት አቅማዊ መዋለ መንፈስ ማዕከል መሆን ያለበት ይህን ቢሮ በጥራቱ፤ በጠረኑ፤ በቋሚ ቅርጽነቱ መሰረት ማስያዝ ሊሆን ይገባል። የትውልድ ብቸኛ ቤት ነው ይህ ቢሮ።
ይህ ቢሮ የአብይ መንፈስ የታሪክ ቀን ሃውልት መገንባት ያለበት እልፍኝ መሆን አለበት። ይህ ቢሮ የሰዋዊ ቀረጻ ቢሮ መሆን አለበት። የሚጎበኝ፤ ሊያዩት የሚናፍቁት ተቋማዊ ህይወቱ የሚያስተምር የሚናፈቅ መሆን አለበት። ለተከፉት ፈጣኖ የሚደርስ መሆን አለበት። ቢያንስ መከፋትን ሊያደምጥ የሚችል። የመንፈስ ሃብታት ሁሉ የነፃነት እናት ምድር ሊሆን የሚገባው ይህ ቢሮ ነው። ዲቢሎስን እዛ አስቀምጦ፤ ለሳጥናኤል ዙፋን ሰርቶ ግን አይሆንም፤ ሊታሰብብም አይገባም።
ይህ ቢሮ የአማካሪዎች ሸንጎ ሁሉ ሲዳራጅ አንቱ የሚባሉ የሞራል አባቶች/ እናቶች መነኮሳት ሳይቀሩ፤ ሸኾች ሳይቀሩ፤ ፓስተሮች ሳይቀሩ፤ ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ሙሉ መብታቸው ተከብሮ አቅማቸውን ወደ ተግባር ሊያሸጋግሩበት፤ ሊመክሩበት እና ሊዘክሩበት የሚችል የትውፊት ጉልላት መሆን አለበት። ለመልካምነት፤ ለቅንነት ሰፊ እልፍኝ መሆን አለበት። ዜግነት፤ ሰዋዊነት፤ ህላዊነት፤ ነባቢትነት፤ ልባዊነት፤ እርቃዊነት፤ እኛዊነት፤ ምህረታዊነት፤ መቻቻላዊነት፤ ፍቅራዊነት እስኪ በዘመነ አብይ ወደ ክብራቸው ይመለሱ። የአብይ ት/ ቤትም ይባል።
ይህ ቢሮ እንዲመጡልን ይናፈቃሉ፤ ሲመጡ ደግሞ ፍቅርን ከነሙሉ ክብሩ እና ተፈጥሮው ያገኙታል፤ በመስተንግዷችን የመልካምነት ስንቅን እናካፍለወታለን፤ ሰዋዊ መከበርን ሰነቀው ይመለሳሉ። የሚል መሆን አለበት።
ክቡር ሆይ! ይህ ለነገ የሚቀጠር አይደለም። በሃሳብ ደረጃ ተግባሩ መጀመር አለበት። ፍቅር በነጠፈበት ህሊና ውስጥ ዲሞክራሲን ማንጠፍ አይቻልም። በአንድ ወቅት የዓለም ትልቁ ሃብት የትነው ለሚለው የዓለም ተመራማሪዎች ቡድን የደረሱበትን አምክንዮ መረጃ ገልጸው ነበር። ኑሮው መቃብር ውስጥ እንደሆነ። እኔ ደግሞ እንዲህም እላለሁ የዓለም ትልቁ የመኖር ንጥረ ነገር መቃብር ውስጥ ነው የምለው የፍቅር ተፈጥሯዊ መርሆዎችን እንደ አንድ የእውቀት ዘርፍ ልናመረው አለመቻላችን፤ ልንመረቅበት አለመቻላችን ነው።
የፍቅር ተፈጥሮ ዕውቅና ማጣት የሰው ህሊና በክፉ ነገሮች የሚያጠፋው ጊዜ ራሱን በልቶታል፤ ወይንም መቃብር ልኮታል። በዓለም አንድም ቦታ የፍቅር ተፈጥሮ የምርምር ማዕከል የለም። አንድም ሳይንቲስት በፍቅር ተፈጥሮ የተጠበበ የለም። ፍቅርን ተፈጥሮውን መርምሮ ትውልድን የማዳን ተግባር ያልተሰራበት ፍጹም አዳኝ አምክንዮ ነው። አንድም ተቋም፤ ድርጅት የለም ስለፍቅር ተፈጥሮ ዓለምን የሚሞግት።
አንድም ት/ ቤት፤ ኮሌጅ፤ ዩንቨርስቲ የለም። ፍቅር ትምህርትም፤ ሙያም አይደለም ለፕላኔታችን። የትምህርት መማሪያ መሳሪም ካሪኩለምም የለውም፤ መጸሐፍትም የለውም። የሰብዕና መለኪያም አይደለም። አቅሙ መለኪያ ያልተሰራለት፤ ፍልስፍናው ዳርቻ የሌለው ሳይንስ ነው የፍቅር ተፈጥሮ። አንድም ቀን ዓለም በፍቅር ተፈጥሮ ላይ ወርክሾፕ፤ ፓናል ዲስከሺን፤ ሰሚናር ህግ ራሱን አስችላ አዘጋጅታ አታውቅም።
ዓለምአቀፍ የፍቅር ተፈጥሮ ህግጋት ወላዊ ፌስቲባል፤ የመንገድ ላይ ትርኢት ዓለም አሰናድታ አታውቅም። „ማቻቻል፤ አክብሮት፤ ታጋሺነት፤ ፍቅራዊነት፤ ማድመጥ፤ ማዬት፤ ህላዊነት፤ እኛዊነት፤ ታማኘንት“ የሚል ሥያሜ ያለው ት/ ቤት እንኳን የላትም እመቤቲቱ ገሃዲቱ ዓለም። ዛሬ የሰው ልጅ ከሰው ይልቅ ማሽን አምላኪ እዬሆነ ነው። የቤተሰብ ዕሴት በድርቅ እዬተመታ ነው። ለዚህም ነው ዓለም አስፈሪ እዬሆነች የመጣችው። በ2015 አመልክቼ አድማጭ ሳጣ በ2017 የቃላት ፖስተራዊ ቻናል የጀመርኩትም ለዚህ ነው።
ወ/ሯ ከዚህ መንፈስ ጋር አስታርቆ ወደ ሰው የመሆን ፍልስፍና ለማምጣት የኢትዮጵያ ህዝብ መመኮሪያ ከሚሆን፤ ምጥ ላለው መከራ ገላጋይ ወ/ሮ ጽዮን ተክሉን ሌሎችንም በዬቢሮው ያሉትን ደጎች ግን ማንፌስቶ አምላኪ ያለሁኑት ንጹህ ዜጎች ዕድሉ ተስጥቷቸው ቅንነታቸው፤ ቸርነታቸው፤ ፍቅራዊነታቸው መዋለ የመንፈስ ሃብታቸው ወደ ተግባር የሚያሸጋግሩበት ቢሮ ቢሆን የተሻለ ነው።
ይህ ለወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሄር እና ለአቦይ ስብሃት ገጸ በረከት የተሰጠው ቦታ ሰብዕናው ሙሉ ለሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሰጠት አለበት እላለሁኝ፤ የተስፋ የፍቅር እልፍኝ ሰዋዊነት ነው። ለናሙና መውሰድ ይቻላል ገጣሚ ፍጹም አስፋው፤ አቶ ውብሽት ሞላ /የህግ ባለሙያ/ ዶር ደረጀ ገረፉ /የፖለቲካ ተንታኝ/ አቶ ታዬ ታዬ ደንዳዓ /የህግ ባለሙያ/ ወ/ሮ አለምጸሐይ መሰረት ታላቅ ሁለገብ ሙሁር፤ ኢንጂነር ሚኬኤል ሽፈራው የሎሬቱ ታቦት በልባቸው የታተመ ድንቅ ኢትዮጵያዊ አሉ።
v እነዚህ በተለያዬ አጋጣሚ ሚዲያ ላይ የማዬቸውን ነው፤ ለዚህም ዕድሉን ያላገኙ ብዙ በርካታ ደግ ወገኖች አሉ። ለዚህ ቦታ እናታዊ አንጀት ነው የሚያስፈልገው። ተብዕት ከሆነ ሴት አንጀት የሚባል ዓይነት። ኢትዮጵያ አኮ በደም ዝናብ የበቀለ እህል እዬበላች „የእንባ ጠባቂ በሚ/ር“ ደረጃ ነበራት። ሴት ልጅ ጥፍር፤ ወንድ ልጅ የዘር ማፍሪያ በሚከስምበት አገር፤ ሴት ልጅ ተዘቅዝቃ ተስቅላ ሌት እና ቀን በምትደበደብበት፤ ሴት ልጅ ደም በምትሸናበት አገር። ሌላም አለ „የህጻናት እና የሴቶች በሚ/ ር“ ማዕረግ። ምስል ይባል የተቃጠለ ካርቦን ይባል አይታወቅም። አላዛሯ ኢትዮጵያ የልጇቿ ተፈጥሯዊ ስብዕና አንደ ጥንችል የመሞከሪያ ጣቢያ ሆኗል። ግንቦት 20 ድሉ ይሄው ነው¡ሰው አልባ አገር፤ ህዝብ አልባ መንግሥት … የተኖረው እንዲህ ነው።
v ማጠቃለያ።
ዴሞክራሲ የተፈጥሮ መኖር ፍልስፍና ነው። የመኖር መሪው ደግሞ ሰው ነው። መሪው ሰው ፍጥረት ነው የፈጣሪው። በፍጥረቱ ውስጥም መፈጠረም ተፈጥሮም አለ። ተፈጥሮም እንዲኖር ተፈቅዶለት የተፈጠረ ነውና። መቼም ዴሞክራሲ ለቀልሃ እና ለድንጋይ ወፍጮ ካልተፈጠረ ለሰው እና ለተፈጥሮ ከተፈጠረ በሰው ውስጥ ያለ ሰብዕና እንጂ በብረት ውስጥ ያለ ጨካኝ እና አረመኔ ሰብዕና ለዴሞክራሲን ግንባታ አይመጥነውም። ያነጥረዋል ወይ አውርዶ ይፈጠፍጠዋል።
ሁለቱንም ከሞት የሚያድነው ህሊና ያለው የሀገር ብሄራዊ የቢሮው ተጠሪ ሲኖር ነው። የሰብዕዊነት ታታሪዎች ትንታጎች ሰርተው የማይደክሙ ዜጎችም ሰራተኞች ሲሆኑ ነው። ለገሃዱ ዓለም ሳይሆን ሰማያዊ ዓለምን የሚያልሙ ህይወታቸው የሚያስተምር የቸርነት አንበሎች ሲመደቡበት ነው። ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን ልሙጥ ነው።
ክቡር ጠ/ ሚር አብይ አህመድ ሆይ!
መልካም ብሩህ፤ ብሩክ የስኬት፤ የመደማመጥ ዘመን ለጠ/ ሚር ቢሮ እንዲሆን ከህሊናዬ እመኛለሁኝ። ለነበርን ዘንካታ የመደማመጥ ጊዜ እና ለሚሰጠኝ በቂ የልባዊነት ጊዜ ህሊናዊ ምስጋናዬን ዘለግ ባለ ትሁታዊ ቅንነት አቀርባለሁኝ። ድንግልዬ ጥላ ከለላ ትሁነዎት። ይኑሩልን።
የኔዎቹ የ አቤቱታዬ ማሰረጊያ ይህ ጭብጥ ነበር። ነገር ግን ገፈቱን እንጂ ሥሩን የነካ መጠይቅ በውል ሲቀርብ ስላላደመጥኩኝ ነው ደግሜ ማቅረብ የፈለግኩት። የሁሉም ነገር መሰረት የዴሞክራሲ ግንባታ ቢሮ ነውና፤ ለዛ ደግሞ ሚኒስተሯ ወ/ሮ ፈትለውርቅ ገብረ እግዚአብሄር ናቸው። መዋቅሩም በወያኔ ማንፌሰቶ የጠጠቀለለ ነው። ይህን ተሸከሞ ጉዞ የማግስት መርዶ ቤት ነው። ምክንያቱም ሳቃችን፤ ደስታችን ዘላቂ አይሆንም … የወንዝ ሙላት ውሃ አይነት ነው የሚሆነው … ጥሎ የሚሄድ
ዴሞክራሲ ቃሉ ሳይሆን የህሊና ማሳው ነው ዕውነትነት።
ውዴቼ ኑሩልኝ መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ