ናፍቆትን መገደብ ለነፍስ ራህብተኞች ሃጢያት ነው ...

ሳቅን፤ ናፍቆትን ለመገደብ
የታደመው ዕሳቤ
ወቅታዊነት ይጎድለዋል።
„ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚች ዓለም
ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን።“
ወደ ቆረንቶስ ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፲፰
ከሥርጉተ©ሥላሴ
01.09.2018
ከጭምቷ ሰዊዘርላንድ።

  • ·        የጭብጥ መነሻ።

#EBC አድማ የመቱ የሲቪል አቪየሽን ሰራተኞችን በመተካት ለሰሩ ሰራተኞች እውቅናና ሽልማት ተሰጣቸው፤

 

·       መቅድመ ነገር።


የኔዎቹ እንዴት ናችሁ? ትናንትም ዛሬም ደምኗል። ትናንትም ዛሬም ልዕልተይ የለችም። ትናንትም ዛሬም ብትጠራ ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብላ፤ ጠላታችሁ እልም ይበል እልም ብላለች። ትውር አላችም። እናም እኛ ምናችን ሞኝ ነው ደረትረት ብለን ጉብ ብለናል። ግን ያው እንደ ዳሽን ተራራ ከንፈራችን በልዕልተይ ላይ ነፋ አድርገናል። 

ያካፋል፤ ያበራል፤ እንገናም ያካፋል እንደ ገናም ይባራል በቃ እንደ ወርህ ሚያዚያ ቅጥ አንባሩ ጥፍት ያለበት ቀን ነው ዛሬ። ብቻ በዚህ ዓመት የተሻለ የበጋ ጊዜ ስለነበር እንዳሻት ሙቀቷን አክስክሳናለችና አሁን ብትመጣም ብትቀርም እንደ ፍጥርጠሯ ብለናል ስለ አውሮፓዊቷ እሜቴዋ ጠሐይ።
  • ·       የወግ ገበታዬን እስቲ ዘለግ አድርጌ ላስኪደው… እንዲህ …

የአብዬሽን ሰራተኞች ካለፈው ሰኞ ጀምሮ የሥራ ማቀም አድማ ለመምታት አቅደው ነበር። መቼም ዜናው ሲሰማ ጎሽ፤ ደግ አደረጉ ልላቻው እልቻልኩም። ምክንያቱም ወቅታዊነቱ የሴራ ይመስል ስለነበር። ስለምን ዓውዳመትን ታክኮ አድማን ለመከወን ታሰበ?

እኔ የሠራተኛ ማህበር አደራጅ ነበርኩኝ። ያን ጊዜ በዘመነ ኢሠፓ ማለቴ ነው ወደ 13 የሚጠጉ ኢትንደስትሪ ማህበራት ነበሩ። እነዚህ ደግሞ ራሳቸውን አደራጅተው  መኢሰማን (የመላ ኢትዮጵያን የሠራተኛ ማህበርንም ) የሚመሰረቱ ናቸው።

መቼም የመኢሠማ ብሄራዊ ጉባኤ ሲመጣ ነፍስ የሚያጠፋ ሥራ ነው ለአደራጆች የነበረብን። እኔ ብቻ ነበርኩኝ በዛ ለጋ ዕድሜ ሴት የክ/ ሀገር የሠራተኛ እና የገበሬ ማህበራት አደራጅ የሆንኩት። ሪኮምንዴሹኑ ደግሞ ከ አርሲ ክ/አገር ኮሜቴ ነው። ያን ጊዜ ናፍቆቴ ጢቾ አወራጃ የሴቶች አደራጅ ነበርኩኝ። 

ይህ ማለት ፓርቲዬ ኢሠፓ አቅም ያላትን ሴት፤ አንስት ናት ብሎ፤ አሳንሶ ገምቶ ለገንዘብ ቤት እና ለሴቶች አደራጅነት የሚል ቀመር አልነበረው። ሴቶች የመምሪያ ሃላፊዎች ሁሉ ነበሩ። አውራጃ፤ ወረዳ ላይ ርዕዮተ ዓለም ጉዳይ ሃላፊ የሆኑ ሁሉ ነበሩ። ሴት የወረዳ አስተዳደሪም ነበረችን። አሁን የ እይ ካቢኔ የተሻለ ጣዕም ያለው ምግባር እዬከወነ ነው። ተመስገን!

ወደ ቀደመው ምልስት ሳደርግ የመኢሠማን አገራዊ ጉባኤን ለማሳካት ፈተናው በ13 አዳራሽ የኢንደስተሪ ማህበራት ጉባኤቸውን አካሂደው፤ ውክል አካላቸውን ከመረጡ በኋዋላ ነው የሚካሄደው አገራዊ የመኢሠማ ጉባኤ።

ይህም ብቻ አይደለም የዬክፈለሀገራቱም ቀደመው ምርጫቸውን ስለሚከውኑ፤ የራሳቸው ውክል አካል ደግሞ ይኖራቸዋል። የሁለቱ ድምር ነው ብሄራዊ ጉአባኤውን የሚያዋቅረው። ነገር ግን እዬንዳንዱ የሠራተኛ ማህበራት ውክል አካል የግድ በኢንደስትሪው ማህበር ተመርጦ መምጣት ይኖርበታል፤ ስለዚህ ነው የሠራተኛ ማህበር ጉባኤ ሰፊ የሥራ ድርሻን የሚጠይቀው።

የገበሬ ወይንም የወጣቶች፤ ወይን የሴቶች፤ የሙያ ማህበራት ከሆነ በአንድ ሰንሰለት ብቻ ነው የሚዋቀሩት። ጅረት ወይንም ገባሪ ወንዝ አያስፈልጋቸውም። እርግጥ የከተሞች የተለዬ የአውካከል ተጨማሪ ሥርዓት ሊኖር ይችላል።
  • ትንሽ ለማብራራት

ገበሬዎች ከቀበሌ ገበሬ ማህበር ጀምሮ ወረዳ፤ አውራጃ ክ/ አገር እዬለ በአንድ ሰንስለት ነው መኢገማን(የመላ ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማህበርን)መፍጠር የሚቻለው እንደ ሠራተኛው ማህበር  የኢንደስትሪ ማህብራት ስለሌላቸው። 

እርግጥ ነው ገበሬ መንደር ድረስ መውረድ ስለሚኖር በዚህ ዘርፍ እንደ ሠራተኛው ከተማ ላይ አይገኝም ገበሬው፤ ስለሆነም  የእግር መንገድም ተጨማሪ ድካምን የሚጠይቁ ነገሮችም ይኖራል፤ ነገር ግን የሌሎች ማህበራት አደረጃጅት የተሻለ ነው በአፈጻጻም ደረጃ ቀለል ይልላ። የሠራተኛው ግን ውስብስብ አደረጃጃት፤ ውስብስብ የውክልና ዘይቤ ነበረው።

ይህን የምገልጸው አሁንም ቢሆን የሠራተኞች የገበሬዎች፤ በኋዋላ ላይም የማህብራት የሙያውንም ጨምሮ የሁሉም አደራጅ ስለነበርኩኝ የማህበራት ጉዳይ የነፍሴ ያህል ቅርቤ መሆናቸውን ማጠዬቅ ግድ ይለኛል። 

በተለይ የሠራተኞች የአዋጅ አፈጻጸሞችን በትክክል መንግሥታዊ አካላት ካልፈጸሙ ሠራተኞች መብታቸው ይረገጣል፤ አሰሪዎች ባሻቸው ሁኔታ በቂም፤ በቁርሾ ከሥራ ባፈናቀሏቸው፤ ባባረሯቸው፤ መብታቸውን በተጋፉ ቁጥር የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጉዳያቸውን ተከታትሎ ከግብ ማደረስ አለበት በፍ/ ቤት። ህግ አስፈጻሚ አካላቸው ነውና።
  • ·       የተገባው ባልተገባ ጊዜ ከሆነ ያልተገባ ምላሽ ተመጋቢ ይሆናል።

የሠራተኛው የመብት ጥያቄ ችግሩን ስለማውቀው፤ ውስጤም ስለሆነ ለእኔ የማውቀው ስለሆነ የተጋባ አይደለም ከሚል እሳቤ አይደለም ይህን እይታዬን እማቀርበው። የመንግሥት ይሁን የግል ድርጅቶች ሠራተኞችን ሲበድሉ፤ ሲያሰናብቱ፤ ሲቀጡ በስውር ነው። አስሪዎች ህጉንም ስለሚያውቁት እንዳይቀጡ አድርገው መስጥረው በረቀቀ ሁኔታ ነው።

የመብት ረገጣው ታስቦበት በቅጡ ተደራጅቶ ነው የሚከወነው። ይህን አሳምሬ አውቀዋለሁኝ።  የኢትዮጵያ የአብዬሽን ሠራተኞች የመብት ጥያቄ ማንሳታቸው የተገባ ሆነ ሳለ የመረጡበት ጊዜ ግን የተጋባ አልነበረም። የተገባው ጥያቄ ባልተገባ ጊዜ ከሆኑ ምላሹ አሉታዊነትን ተመጋቢ መሆኑ አይቀሬ ነው። የታዬውም ይኸው ነው።

እኔ እራሴ አደራጅ ሳለሁኝ በሠራተኛ ወገን ሆኜ ነበር እምሟገተው። የሞራሉ ካሳ ሲቀር፤ ሲፈረድባቸው እንኳን ሰራተኞች ምን ያህል በሥነ - ልቦና እንደሚጎዱ ጠንቅቄ እረዳለሁኝ። አሁንም ስሜቱ አለና። ነገር ግን የአብዬሽን ሠራተኞች ቅዱስ ዮሖንስን ይዞ፤ ሰፊው ዴያስፓራ ወደ አገሩ ለመመለስ ባሰበበት ጊዜ ይህን አድማ ለማድረግ መወሰናቸው ፈጽሞ ወቅታዊም፤ የተገባም አይደለም - አልነበረም። 

እንደገናም የዲያስፓራው ዜጋ ፈቃዱን የሚያገኝበት ሁኔታም በሰው እጅ ነው ያለው። አንድ ግዜ ካመለጠው አያገኘውም። ለቀጣይ እንዲራዘም ሊልም አይችልም። ይህ ቀን ካለፈበት ደግሞ ሰው ነፍሱን ቋጥሮ ስላልያዘው በቤተሰብም፤ በስደተኛውም ሊፈጠር የሚችለው ችግር አይታወቅም። ትንሽ ራቅ ሳብ አድርጎ ማሰብ ይገባል።  

የአብዬሽን ሠራተኞች እንደ ተወካዮቻቸው ገለፃ 8 ዓመት ሙሉ ጥያቄ ሲያቀርቡ መኖራቸውን፤ 8 ዓመት ሙሉ በደል እንደተፈጸማባቸው ተገልጦል። ታዲያ አሁን በምን ሂሳብ ነው በዚህ ወቅት ካልተመለሰ ሥራ እናቆማለን የሚሉት። ስለምን በአፍንጫ ካልወጣ አሁን ሞተን እንገኛልን ስለምን አሉ? 

ዶር አብይ አህመድ ጠ/ ሚር በሆኑ ማግሥት በዬዕለቱ የሚጻፉ ነገሮች ነበሩ በጦማርያን፤ አውሮፕላን ማረፊያ የትኬት ቆራጭ ችግር ሲገጥም፤ ወይንም አገሮች ቪዛ ሲከለክሉ ሁሉ ጠ/ሚሩ በዬቦታው እዬተገኙ እንዲያስፈጽሙ ይፈለግ ነበር። ትኬት ቆራጭ ቪዛም አስመቺ እንዲሆኑ...

ያው ስሞታ፤ ምሾ እና ማሳጣት እና ተጽዕኖ መፍጠር የተለመደ ሥራ ነውና፤ በዚህ ዙሪያ በፍጹም ሁኔታ የተደራጀ የደቦ ሥራ ተከውኖበታል። ዛሬ ታገደ ተብሎ የሰማነው ዜጋ ነገ ደግሞ ውጪ አገር ገባ ተብሎ ይደመጥ ነበር። ብቻ ፍርሻን የቆጣጠሩ አሉታዊ ዕሳቤዎች የለውጡን መንፈስ በማወክ በአጭሩ ቀጭቶ ለማስቀረት ሰፊ ዘመቻ በተከታታይ ተደርጓል። እሱ የወደደው ሆነ እና አሁን ካለንበት ተደረሰ። ተመስገን!

አሁን ደግሞ ቪአይፒዎችን አይመለከትም፤ ሌሎች ዜጎች ግን የዚህ ሰለባ ይሁን ማለት በራሱ ጨቋኝ፤ አግላይም ሃሳብ ነው። ቪአይፒውስ በግል አውሮፕላን መብረር ይችላል፤ ሌላው ለማይችለው ነበር ወገንተኛ መሆን የሚገባው።

የሆነ ሆኖ የተመረጠበት ጊዜ በውነቱ ትክክል አልነበረም። ዛሬ ከ40 ዓመት ላላነሰ ትወልድ አገራቸውን ያለዩ ሁሉ ወደ አገር የሚገቡበት ወቅት ነው። ወላጆች ያቺ መከረኛ እናት በህይወት ከኖረችም ቤት ያፈራውን የአቅሟን አሰናድታ ልጇን፤ የልጅ ልጇቿን፤ ምራትም አማችም ከኖረ ለማዬት ቀን ስትቆጥር ባጅታለች። እንዲያውም ቀኑ ረዝሞባታል። 

ያቺ 43 ዓመት ሙሉ ዕንባውን እንደ ጅረት ስትለቅ የኖረች ድምጽ አልባዋ ኢትዮጵያዊ እናት ቢያንስ አንዲት ቅዱስ ዮሖንስ ምን አለ ብትስቅ? ምን አለ ደስ ብሏት ተመስገን ለዚህ አበቃህኝ ብትል?ከርሞ በህይወት ላትኖር ትችላለች። 

መሬቷ እራሷ፤ አፈሯ እራሷ፤ ባዕቷ እራሷ፤ አሳድጋን ግን አጥታን ኑራለች። እንደ ወጣን ቀርተናል። ጠረናችን ከእኛ እርቋት ባዕታችን፤ የእሷ ጠረንም ከእኛ እርቆን ነፍሳችን ራህብ ሲፈጀን ኖረናል። የነፍስ ራህብተኞች ነን። ታዲያ ይህን ለማስታገስ የራህብም መዳህኒት ዘመን ሲመጣ እንዴት ይገደባል? እውነት ለመናገር ዘመንን የመገደብ ያህል ነበር ለእኔ የተሰማኝ።

8 ዓመት የተቻለ ችግር? „40 ዓመት ዓይኗን ያጣች ሸበላ አንድ ቀን እደሪ ቢሏት እንደምን ብዬ እንዳለችው“ ዓይነት ነው አሁን የሆነው። ሁሉም ነገር በአፍንጫ ይውጣ ነው የሆነው። ትእግስት የሚባል ስለመፈጠሩም አይታወቅም። እኔ አዝናለሁኝ እራሱ ለውጭ ሚዲያ የሚሰጡ ጠናና ዕሳቤዎችን ሳዳምጥ። 

ዛሬ ኢትዮጵያ መንግሥስት አላት። ቅሬታ - ብሶት - ችግር አይደለም ኢትዮጵያ ያደጉ የበለጸጉ አገሮችም ችግርን አልጨረሱትም። ችግርን በህግ ማስቆም አለተቻላቸውም። የእኛው ደግሞ አጀብ የሚያሰኘው የ43 ዓመት ችግር አትንነው አብይ ነው … ይገርም ነው።

በአንድ ሰሞናት ሊኖር የሚችል የመንፈስ የማሰባበስብ ተግባር ነው። ይህን ደግሞ ሙሴው በጥበቡ በምርቃቱ ከውኖታል። አብዛኛው የተበተነው መንፈስን በአሃቲ መንፈስ ክህሎትን አስታጥቆታል። ችግርን ለመፍታት ደግሞ የሁሉም ድርሻ ነው። አንድ ዕጣ ነፍስ እፍ ትንነልኝ ብሎ አቤቶ ችግርን ሆይ! በማለት  ሊያባርር አይችልም። ነገር ግን ተስፋ አለ።

መንግሥት አለን ብለናል። ኢትዮጵያ ሠራዊት አላት ለማለት ሁሉ ችለናል፤ ስለዚህ ስለምንድ ነው አሁን መንግሥታችን ለማሳጣት የምንሻው?ሁልጊዜ ስሞታ አቅራቢዎች ለመሆን ስለምንስ እንተጋለን? ይህ አዬር መንገድ ዓለም አቀፍ ነው። ኮሽ ባለ ቁጥር ሁሉ ነገር ሉላዊ ነው። በቀደመው ጊዜ እኮ መከራው ስለዋጠን ነበር። መተንፈሻ ስለጠፋ ነበር። 

በዬትም ሁኔታ ለነፃነት የሚደረጉ ተጋድሎዎች ሲደገፉ የነበሩት። ማጥፋት - ማቃጠል ከሌለባቸው በግሌ እደግፋቸው ነበር። … አሁን ግን የለውጡ አሳታፊነት እና አቃፊነት ጅምሩ እጅግ አበረታች ነው። እንዲህ በሙሉ አቅም እና ክህሎት የጠበቅነውም አይደለም … በዬለቱ ያሉ መልካምነት የታምር ነው … ቸርነቱ ገድል ነው። ከእንባ ወጥተን እዬሳቅን እኮ ነው ያለነው …

አሁን ለውጪ መንግሥታት፤ ለውጪ ሚዲያ ማሳጠት እኔ አላደርገውም። ደግሞም ቃልም ገብቻለሁኝ። ዶር አብይ አህመድ ጠ/ ሚር ከሆኑ ደግሜ አላመለክትም ሃዘኔን አልክም ብዬአለሁኝ። ምክንያቱም ለሳቸው በቀጥታ በፈልግኩት መልክ አቤቱታዬን፤ ቅሬታዬን፤ ሙግቴን መላክ እችላለሁኝ። ማን ከልካይ አለብኝ እና። አቅርቤአለሁኝ እኮ አብይ ሆይ! ብዬ እኔም ዜጋ ከሆንኩኝስ ዘለግ ያለ አቤቱታ አለኝ ብዬ። በሃሳብም እሞግታለሁኝ። 

ሌላው ስፈልግ ደግሞ ለውጪ መንግሥታት ከማመለክት በቀጥታ ፋክስ ማድረግ እችላለሁኝ። በፖስታ ቤት መላክ እችላለሁኝ። ደግሞም ያዳምጡኛል። ማድመጥ ማለት እሺ ብቻ አለማለት እንደሆነ አውቃለሁኝ። አይም መልስ ነው። ሃላፊነትን ስለማውቀው። ግን መሪ ያላት አገር አሁን አለችኝ። ችግሯ ግን ወዘተረፈ ነው። የግል የገዳይ እስኳድ እስከ መፈጠር የዘለቀ ...

በዬትኛውም ዘመን ይሆናል ብዬ ባላሰብኩት ሁኔታ ጥሩ አዬር ነው ያለው አገሬ ላይ። ቀጣይ እንዲሆን ደግሞ ቅንነት ያስፍልጋል። እዬባዊነትን ይጠይቃል። ቀጣይ እንዲሆን ራስ ማሸነፍ ይጠይቃል። ቀጣይ እንዲሆን ከእኔ ምን ይጠበቃል ማለትን ይጠይቃል። ቀጣይ እንዲሆን ከአፍራሽነት ራስን መግታትን ይጠይቃል። ለለውጡ ቢያንስ ታማኝ ለመሆን መወስን እና መቁረጥን ይጠይቃል።  

አሁን ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳሻቸው ተደራጅትው ሞግተው፤ ተወዳድረው፤ ተፎካክረው ማሸነፍም፤ መሸነፍም የሚችሉበት ብሩህ ዘመን ላይ ነን ያለነው። ብዙ ያጣናቸው የመብት ጉዳዮች ደረጃ በደረጃ እዬተስተካከለ ነው። ነገም ሌላ ቀን ነውና አጤ ሂደት ደግሞ የሚፈታቸው ችግሮች ይኖራሉ … ጊዜ ያስፈልጋል። ሆደ ሰፊነት ያሰፈልጋል። ቅድሚያ ሊተኮርበት የሚገባው ነገር እንደ እኔ የዶር አብይ አህመድ ህልውና ነው። የካቢኔያቸው ቀጣይነት ነው። ሌላው ይደርሳል። በ አንድ ቀን ልጅ ተጽንሶ ዩንቨርስቲ ተመራቂ አይሆንም። 

ከሁሉ በላይ በበጎ አድራጎት ዘርፍ ባለቤት የሌላቸውን ለመንከባከብ እንደ ኩሬ እውሃ ረግቶ የኖረው የፕሬዚዳንት ዶር ሙላቱ ተሾመ ቢሮ ሳይቀር እራሱ እንቅቀስቃሴ ጀምሯል። ይህ አበረታች ነው። ሥራ አልባው ሁሉ ሥራ እዬተፈጠረለት ነው፤ ለገሃዱ ዓለም ብቻ ሳይሆን ለመንፈሳዊ ህይወትም የአውሮፓውያኑን የበጎ ምግባር ጠረን አለ አገር ቤት …  ይህ ሞገሳችን ነው። የኢትዮጵያ የብሮድ ካስት ባለስልጣን እንኳን 7 ተማሪዎችን እስከ መጨረሻው ለማስተማር ቃል ገብቷል። ይህ የምሥራች ነው። ለእኔ ይህ ለውጥ ነው። 

በአላዛሯ ኢትዮጵያ ታምር የሚመስሉ ነገሮች ናቸው ያሉት። እና በዚህ ወቅት የኢትዮጵያን ጉሮሮ ለመዝጋት፤ ኢኮኖሚዋን ለማድቀቅ እንዴት ይታቀዳል? በአንድ ሰዓት ስንት የውጭ ምንዛሬ ታጣላች አገር? ትንሽ ማሰብ ያስፈልጋል። ትርፍ ሰዓት ተስርቶ ነው በዬአገሩ የሚኖረው። ጡረታ የወጡ ሰዎች እዚህ አያርፉም፤ የነፃ አገልግሎት ይሰጣሉ፤ ባለሙያዎቾ ዝቅ ባለ ክፍያ ያገለግላሉ። አገር እንዲህ ነው የሚገነባው። 

እስራኤሎች አገራቸውን ድንቅ አገር ያደረጉት በዚህ መስመር ነው። ጽዮናዊነት ብዙ ገድልን ተጫውቷል። ሠራተኛው ሰዓቱን ሳይሆን ሥራው ማለቁን ነው ማዬት ያለበት። 7 ቀን ሙሉ የሚሠራ ሙሴ ነው አሁን ኢትዮጵያ ያላት። እኔስ ማለት ይጠይቃል። 

ዶሮ ቤት የሚኖሩ ልጆች እኮ ነው ያለን? ቆሻሻ ውስጥ ለቅመው የሚበሉ ልጆች እኮ ነው ያለን? ትራፊ ተሰልፈው የሚበሉ ልጆች ነው ያሉን? ስንት ሺህ ልጆች ናቸው ጎዳና ቤታቸው የሆነ ያለን? አለመተዛዝን ያስተዛዝባል።

የሆነ ሆኖ የአብዬሽን ሠራተኞች ጥያቄቸውን እያቀረቡ ግን ሥራ ያቆሙቱን ተክተው ለሠሩት ክብር ለእነሱ ይሁን። በዚህ ቀውጢ ወቅት እና ፈተኝ ጊዜም ይህን ሃላፊነት ለመወጣት ስለቻሉ እኔም እንደ ዜጋ እነኝህ የክፉ ቀን ጥቃት አውጪዎች ለኢትዮጵያ አዬር መንገድ ብቻ ሳይሆን ለእኔም ጀግኖቼ ናቸው።

የታላቋ ሱማሌ ህልመኛ ሲያድባሬ እኮ ኢትዮጵያን ለመውረር ሲነሳ ሠርጋቸውን ትተው፤ ሞፈር ቀንባራቸውን ፈተው፤ ልጆቻቸውን ለቤተሰብ ሰጥተው፤ ጎጇቸውን አፍርስው፤ ትዳራቸውን ትተው፤ ወገኖቻችን ዘመተው እኮ ነው ኢትዮጵያን ጀግኖቻችን ያቆዩን።
ያን ጊዜ በተሟላ ሁኔታ መጠለያ - ስንቅ - ልብስ - ትጥቅ እንኳን ማሟላት አቅም አልነበራትም ኢትዮጵያ። አብዮቱ ጮርቃ ነበር። አሁን ያለንበት ወቅትም ጮርቃ ላይ ነን። አሁንም ያለንበት ወቅት እንደዚያ ተመሳሳይ ነው።

የተደራጀ ሴራ ጦርነት በለውጡ ላይ ከፍቷል። ባዶ ካዝና ነው አዲሱ ለውጡ የተረከበው። ሳቦታጁ ልክ የለውም። አጥፊዎችን መቅጣትም -  ማሰረም - ማበረርም ይቻላል ግን ያ አልተፈለገም።

በእዮባዊነት ቅንነትን እያስተማሩ - ፍቅርን እዬመገቡ ጎባጣን ማቃናት ነው የተያዘው። ያ ደግሞ ለቤተሰብም ለትውልድ ተቋም ነው። በዚህ የመልካምነት - የአርቆ አሳቢነት - የሚዛናዊነት ሂደት ላይ ሳንክ መፍጠር እውነት ለመናገር ህሊና ቢስነት ነው። እንደ አገር እንደ ዜጋ ድርሻዬስ ማለት ይገባል። እኔም የድርሻዬን ማለት እንዴት አይቻልም?

የተመረጠበት ጊዜ የጠላት ያህል ነው። እኔ በግሌ ሲያድባሬ ኢትዮጵያን ለመውረር ካደረገው አሳንሼ አላዬውም። ማንኛውም የሴራ ዓይነት የተስፋ ጠንቅነቱ በጥልቀት ሊመረመር ይገባል። ይህ ጉዳይ አንድ አገሬን ከሚል ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም።
ዓለም አቀፍ ህግጋትን ማስፈጸም የሚቻለው አገር ስትኖር ነው። ህዝብ ሲኖር ነው። 

ህዝብ ወደቡ ከተያዘ እኮ በአንድ ቀን ስንት ሰው ለበሽታ ይዳረጋል። እንዲያውም በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መዳህኒት መግዣ ሁሉ የለም። እና የአብዬሽን ሠራተኞች የፈጸሙት ግድፈት ለታሪካቸው ጥቁር ነው ባይ ነኝ።

ለውጡን ማገዝ አገርን ቀጣይ ያደርጋል፤ ትውልድን ቀጣይ ያደርጋል። አገርና ትውልድ ቀጣይ ከሆኑ ደግሞ አሁን ጥሩ መሪ ኢትዮጵያ ስላላት ደረጃ በደረጃ ችግሮቻችን ማስወገድ ይቻላል።

ይህም ማለት ግን ኢትዮጵያ ችግር ፈጽሞ የማይፈጠርባት አገር ትሆናለች ማለት አይደለም፤ ዘመን እራሱ የሚያስረክበው ችግር አለ። አሁን ብዙ ሰው ከሰው ይልቅ ከኔት ጋር ነው ቤተሰብነቱ። በሌላ በኩል ኋላቀርነታችን የብዙ ነገር ነው። የአስተሳብ ድህነት እራሱ … ወደ መልካምነት ለመምጣት ያለው ግብግብ፤ ከሴራ ጋር ለመፈታት ያለው ጦርነት … ስንቱ፤ ፍሬ ነገሩ ዛሬ በቸርነት ላይ ይጀመር በቅብብል ቀጣዩ ትውልድ ያስቀጥል ነው የሚለው  የአብይ ሌጋሲ  …

በአደጉ አገሮች ራሱ ስንት ወዘተረፈ ችግር ነው ያለው። የበለጸጉት አገሮች እራሱ ሁሉን ሰው አስተደስተው አያድሩም። እንደዛ ቢሆን የጭንቀት በሽተኛ ባልበዛ ነበር። ተመስገን ማለት እንደ ኦክስጅን ልንማረው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ፍርሻ ሆኖ ቢሆን ኑሮስ? ጦርነት እኮ ህግ የለውም?አቅጣጫው ያለታወቀ ነገር ናፋቂዎች ሁሉ ነበሩ … ዛሬም ይኖራሉ … 

በትጥቅ ትግል ሲሉ የነበሩት ትጥቅ ፈተው አገር እዬገቡ ሌላ የማዕቀብ አደጋ በዚህ ጮርቃ እና ለጋ የለውጥ መንፈስ ላይ መዶል አንጀተ ደንዳነት ነው።

የአብዬሽን ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ የሚደገፍ አልነበረም። የከሸፈ፤ ወቅቱን ያልጠበቀ አድማ ነበር። ስለዚህም እነሱን ተክተው የሠሩት ባላሙያዎች የአገርም የወገንም ኩራት ናቸው። መሸለማቸውም የተገባ ነው። አሁን የአብይን ካቢኔ የምናሳጣበት ምንም ምክንያትም፤ ምንም አምክንዮም የለም ጊዜው ገና ልጅ ነው፤ በዛ ላይ አያያዙ ጤነኛ ነፍስ ያለው ነው … ክህሎቱም ሙሉዑ ነው …

ይህ ማለት ዶር አብይ አህምድ 6 ክንፍ አለው እያልኩ አይደለም።  ነገር ግን እንደ መሪ፤ እንደ ሰብዕዊ ፍጡር፤ እንደ አንድ አገሩን ቁምነገር ለማድረግ እንደሚታትር መሪ ግን እንክብካቤ፤ እግዛ ሊደረግለት ይገባል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። ለነገሩ የሰብዕዊ መብት አክቲቢስቲነት ብቻ ሳይሆን ፓን አፍሪካነዚም መንፈሱ ያለው መሪ ነው ያለን።
  • ·       አለመተዛዘን?

2 ሚሊዮን ዜጎቻችን እኮ ላዩ ውሃ ታቹ ውሃ በሆነ ሁኔታ ሰው በሰራው ሴራ ጎዳና ላይ ናቸው ያሉት። „አንድ ሰኔ የነቀለውን አስር ሰኔ አይተክለውም“ ይባላል። ገበሬዎች ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለዋል። ማረሻ ቦታም የላቸውም።

በዚህ ማህል የተደፈሩ ሴት ልጆች ይኖራሉ። ከወላጆቻው የተለዩ ልጆች አሉ። በምግብ እጥረት በሽታ ላይ የወደቁ አሉን። አዛውንቶች፤ ነፍስጡር ሴቶች አሉን። መከራችን ወዘተረፈ ሆኖ ሌላ ፈተና ተመርቶ ነው ደግሞ ሌላ ትንፋሽ የሚያሳጣ ጫን ተደል ጭንቅ ተሸከም የተባለው አዲሱ ለውጥ።

ህሊና፤ ሰው መሆን፤ ዜጋ መሆን፤ ምን ማለት እንደ ሆነ ግራ አስኪገባ ድረስ የወገን ሰቆቃ በራችን ላይ እያለ ሌላ ደግሞ ማምረት የተገባ አይደለም። አሁን የኢትዮ ሱማሌው እልቂት ፊርማ ሳይደርቅ ደግሞ ሌላ ወጣሪ ችግር አመራችነት? 

ጊዜው እኮ አላለቀም፤ የዘመናት የተቆለለ ችግር፤ የተከመረ ችግር በአንድ ሰሞናት ካልተፈታ እዬተባለ ያለው ነገር ዘመናይነት ነው - ለእኔ። መኖር በራሱ ብዙ ነገሮች አሉበት። እስቲ የረጋች አገር መጀመሪያ ትኑረን። 

እስኪ የረጋ መንግሥት መጀመሪያ ይኑረን። እሲክ ለሴረኞች፤ ለተንኮለኞች መጀመሪያ ወደ ልቦናቸው ይምልስልን ብለን ከፈጣሪ ጋር እንምክር። ለነገሩ አሁን እኮ ማድረግ የሚገባን ሱባኤ ነበር። ጊዜው ሁኔታውን ቸርነቱን በሱባኤ መቀበል ይገባል። ምርቃት እኮ በሱባኤ በጾም፤ በሳላድ፤ በስጊድ ነው መሆን ያለበት  … 

ብናውቀው ቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ ነው ኢትዮጵያ ያለችው … ለዚህ ተባባሪ መሆን መቼም ኢ-ሰብአዊነት፤ ኢ- ሰላማዊነት ወይንም ራስ ወዳድነት ነው …

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

የኔዎቹ ኑሩልኝ።

ማለፊያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።