መቼ ይሆን አሉታዊ ቁርቁሱ የሚያበቃው? ይንፍቀኛል ...

„አማራነት መንፈስ ነው።“

„ብዙ ነገርን እንናገራለን፤ የነገሩ መጨረሻ እሱ ብቻ ነው፤
እንጂ ነገር ግን መጨረስ አንችልም።“
„መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ ፵፫ ቁጥር ፳፯“
ከሥርጉተ©ሥላሴ
04.09.2018
ከጭምቷ ሲወዘርላንድ

  • ·       ራሞተ ተሰሞናተ።

የሰሞናቱ ትርምስ ግርም ይለኛል። አሁን ጠ/ሚር አብይ አህመድ እና ዶር ለማ መገርሳ መድረኩን እስቲ እንዳሻችሁ ሁኑበት ያሉ ይመስለኛል። ምክንያቱም የስሜን አሜሪካ የነበረው የመሰናዶ ውጣ ውረድ ብዙ እንዳሰተማራቸው አስባለሁኝ። በዝርዝር ሥም አቀማማጥ ሁሉ ቦክስ እንደነበር የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ሪፖርት አስረድቶኛል።

የሆነ ሆኖ በቤተመንግሥትም ደረጃ የአደባባይ ሥራ እንብዛም ኑሯቸው የማያውቀው ዶር ሙሉቱ ተሾም ሳይቀር ብዙ ጊዜ ብቅ እያሉ በቴሌቪዥን መስኮቶች እያዬናቸው ነው - አሁን አሁን። እንኳን ለዚህ አበቃቸው ያሰኛል። መቼስ መነቃነቅን የመሰለ ነገር ስሌለ ….

ተነቃነቅ
ስንፍናን ነቅንቅ
ሞራልን አድምቅ
ኢትዮጵያን አልቅ>> 

አማራ ተጋድሎ እና ቄሮ ነፃ አውጥቷቸዋል ፕ/ ዶር ሙላቱ ተሾመን። የቀድሞውን ጠ/ ሚር ኃይለማርያም ደሳለኝንም ታጋድሎው ገላግሏቸዋል። ግንቦት ሰባቶችንም „የት ናችሁ? የት ደረሳችሁ? ምን ያዛችሁ“ ከሚለው ፈተና ገላግሏቸዋል። ተመሰገንም ሊሉት ይጋባል። ማጣፊያው ያጠረ መከራ ነበረ እና በዬጊዜው የመልስ ቀዳዳ ማጮለቅ… 

በሌላ በኩል የአንዱ ሥም ላይ ለልዕለና የሌላው ደግሞ ታች ወድቆ ሲፈጠፈጥ፤ የሌላው ደግሞ „የእኔ የእኔ“ እዬተባለ ሽሚያ ላይ - ለወረት ከፍ እና ዝቅም ሲባልለት ይታያል። ሌላው ደግሞ ግራው እና ቀኙ ማህል ላይ ሰቅዘውት እንደ ገመድ ጉተታ  ሲጓተቱት መንፈሱን ሲቦጫጨቁት እምለከታለሁ፤ እታዘብምአለሁኝ።

የነፃነት ትግሉ ሥም እና ዝና ብቻ ሆነ መከተቻው መቼም ዕንባ ሆይ! ወደ እዮር ላዳግም አቤቱታ ብቅ ሳይል ተሰሞናቱ አይቀርም … አክብሮትም ልክ መጠን ሲኖረው ህሊና ቦታ ይኖረዋል። እዛ አፈር ድሜ የጋጡት እንኳን አሁን በሚታዬው ደረጃ አልተመሰገኑም … አልተከበሩም፤ አትኩሮት አልተሰጣቸውም … ብቻ ዘመኑን እና ሁኔታውን መተርጎም እያቃተኝ ነው። የጉዞውም አቅጣጫ እና መድፊያውም እዬናፈቀኝ ነው ምንድን፤ ምን ይሆን ነገሩ ያሰኛል ... ሚስጢሩ ድንብልብ ...   

ብቻ የአብይ ካቢኔ ለመድረክ ተዋናዮች እንካችሁ - እንዳሻችሁ ስግሩበት፤ ሲያሻችሁም ዘምኑበት ብሎ ሚዲያውን ለቆታል፤ ለውጪው የፖለቲካ ትኩሳት ጥሩ ክኒን ነው። ታስታውስ እንደሆን እስረኞች ከእስር ሲፈቱ እንዲሁ መሰሉ ተከውኖ ነበር። በተለይ ለኦሮሞ ሊሂቃን በሩ ቧ ብሎ ተከፍቶ እንደ ሙሽራ በቢብ ቢብ ሲታጀቡ ሰነባበቱ። ነገር ግን የአማራ ተጋድሎ መሥራች እና አብሪ ኮከብ እንደ ነገ ሊፈታ ማማሻውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ።

ሞት አይፈሬው ጎንደሬ ግን ፊት ለፊት ወጥቶ አንበሳውን እንኳን ተፈታህልን ብሎ አቅፍ ድግፍ አድርጎ ይዟል። እሱ በሚገኝበት ሥብሰባ ሆነ ተቋምም ክብሩ ማዕረጉ ይህ ነው አይባልም። ገንዘብ ተከፍሎት ወይንም በመመሪያ በደብዳቤ ተጠርቶ አይደለም። ወይንም በሚዲያ አንቃር እስኪነቃ ተፎክሮለት አይደለም።

ለጎንደር ከውስጡ የገባ ጀግና እኔ በዕድሜዬ እንደ ኮ/ ደመቀ ዘውዱ አላዬሁኝም። ከሊቅ አስከ ደቂቅ እኩል ጀግናዬ ነው የሚላቸው። እኔም ጀግናዬ ነው የምላቸው፤ ተተኪዬ ወጣት ንግሥት ይርጋንም እንዲሁ … ለዛም ነው አብዝቼ በሁለገብ ሁኔታ የተጋሁላት። እሷን እናፍቃት አለሁኝ … በስክነት -  በጥንቃቄ - በማስተዋል ነፍሷን እንደትይዛት እሻለሁኝም። ከሁሉም ደግሞ ኢትዮጵያዊነቷ ላይ ያላት አቋም ፍጹም ሐሤት ሰጥቶኛል። እርግጥ ነው በ አጠገቧ ስሌለሁኝ ፖለቲካዊ ሰብዕናውን በማበልጸግ እረገድ የድርሻዬን ልወጣ አልቻልኩኝም። ባላት ላይ እኔን ጓድ ገ/ መድህን በርጋ እና አንባሳደር ወንድወሰን ሃይሉ እንደቀረጹኝ ስብዕናዬን አንደገነቡት፤

የሆነ ሆኖ የሰሞናቱን የሥም ፋሲካ ልባለው እኔ እንደማዬው እንደ እነ አቦ በቀለ ገርባ እንደ ተፈቱበት ዘመን ነው። ታጀቡ ተብሎ መታወጁ። ጳጉሚትን መስከረምን አክሎ በዚኸው ስንዛለል ባጅተን ከዚያ በኋዋላ ግን ልባሙ የልቡን ይከውናል። 

ጫና በጫና የተሰጠህን ተቀበል፤ አጨብጭብ፤ አሸብርቅ የተባለው የአማራ ክልልም ተራው ህዝብ ማለቴ ነው ፍንክች ሊል የሚችልው በጭብብጫው ላይ እንጂ በውስጥ ሃዲዱ ንቅንቅ የሚል አቋም አለዬሁኝም።

ጭብጨባው ግን እጅ እስከ አለ ምን ገዶኝ ብሎ ይለዋል፤ ይለዋል፤ ይለዋል። ውጣ በተባለበት በነቂስ እዬወጣ አድርግ የተባለውን ሁሉ እያደረገ ነው። ተገኝ በተበላውም ስብሰባ እዬተገኜ ሁን የሚሉትን እዬሆነላቸው ነው። አድንቅለት፤ ከብክበው የተባለውን ሁሉ ታቦቴ እያለ ነው። ሌላ ክልል ይህ ጫን ተደል ጫና የለበትም … ብአዴንም ሥራውን ትቶ ሲሸኝ እና ሲቀብል እናያለን …

የአፋር ሊሂቃን አገር ገብተዋል ይህ መሰል ድራማ የለም። የኢትዮ ሱማሊ ሊሂቃን እና አክቲቢስቶች አገር ገብተዋል ይህን መሰለ ትዕይንት የለም። የኦሮሞዎችም ቢሆኑ የተላኩት ደቡብ እና አማራ ክልል ላይ ብቻ ነው። ገባ አገር የሚባለው ሁሉ አማራ ላይ ነው የሚሰፍረው። ይህ ሁሉ ሂደት ስለምን እንዴት ማለት አይገባም። መሆን ያለበት እና የነበረበት ነው። የአማራ ሊሂቃን ጉባኤ ላይ አንድ ከሥራ የተባረሩ የዩንቨርስቲ ታላቅ ሙሁራን „አማራነት መንፈስ ነው“ ሲሉ አሳርገውታል።
  • ·       ቃውነቱስ ምን እያሉ ነው?

ከብአዴን ከፍተኛ አማራሮች ጀምሮ ከመላ ኢትዮጵያ የተውጣጡ እና የማከብርቸው እጅግም የምሳሳለቸው ዶር ካሳ ከበደ ከውጪው ዓለም የተሳተፉበት የአማራ የሊሂቃኑ ጉባኤ ሰሞኑን ነበር በባህርዳር። ሊሂቃኑ የቀደመው ብሂላችን እኛ እንግዳ ተቀባዮች ነን፤ እኛ መለኪያችን ሰውነት ነው። ሰውነት በመሆናችን ለደረሰብን በደል ብሶተኛ ሳንሆን ወደ ሰውነት ሊመጣ ላልፈቀደው ሌላውን የመቀዬር የአባቶቻችን/ እናቶቻችን ሌጋሲ ነው። 

ስለዚህም የአማራነትን ፍልስፍና አጥብባችሁ - ወጥራችን - አሳናችሁ አትዩት፤ ዘና - ፈታ - ሰፈ - ፈካ ያለ ፍልስፍና ነው ይላሉ አወያዮች ረ/ፕ አባባው አያሌው፤ ዶር ዳኛቸው አሰፋ እና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት። ተወያዮችም የዋዛ አይደሉም። ውሳጣቸውን በውስጣቸው በርቁቅ ቅኔ የተቃኜ ስለሆኑ ትምክህት ባይኖርብኝም ተባረኩልኝ፤ ኑሩልኝ ማለቴ ግን አልቀረም።

ምን ያህል ዘመን ይጓዝ እንደሆን አላውቅም እንጂ የአማራን ልብ ለማግኘት ዲካው ምንያህል እንደሆነ ከእንግዲህ እንደ ወትሮው ጋልበኝ ለመባል „እባብን ያዬ ..“ እንዲሉ ሆኗል። በዬትኛውም ፕሮፖጋንዳ እና መላሾ መናጆነት የቀረ ይመስላል። ለዚህ ነው እኔ አማራነት አሞሌ ጨውነት አይደለም የምለው። በልኩ ሲሆን ነው ሁሉ ነገር ቤት የሚመታው ሥነ - ግጥም። እንደዛ …

አወያዮቹም ሆኑ ተወያዮቹ  ሊቀ - ሊቃውንታት ኢትዮጵያዊነት መሆን ያቀተው ለብሶ የሚመጣውን ግርዶሽን ገለጥ አድርጋችሁ ብታዩት ከአማራነት መንፈስ ጋር መሆን ባይችል መስሎ ለመታዬት የሚያደርገው ጥረት ነው፤ አትፍረዱበት ባዮች ናቸው። 

ኢትዮጵያን በፀርነት የጠላት ግለሰብ ይሁን ቡድን ይሁን ተቋምም አማራን መጥላቱ ምንጩ ከዛ ነው ይላሉ ሊሂቃኑ። ሰንደቁ ኢትዮጵያ ለሆነች ለአማራ ግን ኢትዮጵያዊነትን ለማስተማር መሞከር መጃጃል ነው ባይ ነው ቅኔው ሲተረጎም። ቅኔው በገሃዱ ዓለም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም ልይህ - ልገናኝህ ቢባል ዝክረ ውስጡ ተፈላጊነት እና ተፈሪነት መሆኑ ነው የአማራው ሊሂቃን አድርገው ነው የገለጡት። ግን ተነጥሎ ሳይሆን በእኛነት ውስጥነት ጥበብነት - በሰልትነት።

ስለዚህም ማስተዋልን ገበር ማድረግ ይገባዋል አማራ ነው ፍሬ ነገሩ። አማራነት አቧራ ዘመን ቢያላብሰውም አቧር ሲገለጥ ግን ወርቅነቱን ማንም ሊወስድበት፤ ማንም ሊነጥቀው አለመቻሉ ብቻ ሳይሆኝ አማራ በቁመናው ልክ ማስብ እና መሆን ይጠበቅበታል የሚል በሳል አመክንዮ ነው የአማራ ሊሂቃን አገር ቤት ያሉት የተዋያዩበት አመክንዮ። 

በሊሂቃን ደረጃ እንኳን የሚካሄዱት ውይይቶች ለወቅታዊ ችግር መፍቻነት ባይሠራም ምክንያቱም ዞግ ስለሆነ ፖሊሲው ሁሉም ጉልቻውን ደራድሮ ስለሆነ አንድነት ህብረ ብሄርም ነኝ እያለም የሚሰብከው።

የሊሂቃኑ ትንተና እና ተደሞ በንጥረ ነገር ጥራቱ ከልብ የሚገባ ውስጥነት አለበት ትንተናው - ተዋህደናል አዋህደናልም ነው። ስለዚህም ይህ የቅኔ ጉባኤ የሚደፋ ሳይሆን እዬመነዘረ አዲሱ የአማራ ትውልድ እንደ ሪፈረንስ ሊጠቀምበት ይገባል ባይ ነኝ። ማወቅ መልካም ነው።

የ13ኛው መቶ ክ/ ዘመን የአማራ ሊሂቃን ፍልስፍና ዛሬ በ21ኛው ክ/ ዘመን ካለው ግሎባል ዓለም ፍልስፍና ጋር በጥራቱ፤ በብቃቱ፤ በምጥቀቱ፤ በጥልቀቱ፤ በብልሃቱ፤ በሚዛናዊነቱ፤ በማስተዋል ልኩ፤ በመቻቻል አቅሙ፤ በአክብሮት ልቅናው፤ በፍቅራዊነት ጣዝማነቱ፤ በፍትሃዊነቱ፤ በእኛዊነቱ ሰውን ተፈጥሮን ማዕከል አድርጎ በመነሳቱ ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ በፍጹም አይደለም።  

ስለሆነም የፈለገ ነገር አማራ መሬት ላይ ጫና ቢኖርም፤ በላይ በላይ እዬተደራረበ በመሰረታዊ የራሱ ጉዳይ ላይ አማራ እንዳያተኩር የማድረግ የቤት ሥራው ቢበዛም፤ ግን መሬት ላይ ያለው ፍሬ ነገር እጅግ የሚመሰጥ ነው። ጥንታዊነት ከዘማናዊነት ጋር አዋህዶ በኩራትነት ያሰበለ ያጸደቅም ነው። ስለሆነም አማራው በግልብ ፖለቲካ በመታመስ እና ከሞራላዊ ተፈጥሮ ባፈነገጡ ሥራትን ከሚዳፈሩ ነገሮች ላይ ጊዜን ማባከን በፍጹም ሁኔታ የማይገባ ስለመሆነ መሬት ላይ ያለው ጭብጥ ያስተምራል። 

በመንፈስ ልዕልና፤ በሥነ - ልቦና ድል ላይ የሚገኘው የአማራ ህዝብ ሰው እና ተፈጥሮ ማዕከሉ ማድረግ ቀዳሚው ተግባሩ ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ። ሰው እና ተፈጥሮን ማዕከል አለማድረግ ነው የአላዛሯ ኢትዮጵያ የ43 ዓመቱ ግራ ዘመም የፖለቲካ ችግር ብቻ ሳይሆን ወድቀትም። ዛሬ ላለው ሉላዊ ዓለም መነሻን ሲያስቡ መድረሻውን ማለምም ይገባል።

አማራነት የአውሮፓን ሥልጣኔ ትናንት ገንብቷል። ሚስጢር ነው ፍልስፍናው። ያ ፍልስፍና ግሎባል ዓለምን እንዲፈጠር አድርጓል። ባዕቱ ደግሞ ከዛው ከአማራት ነው። „አማራነት መንፈስ ነው“ ሲሉ እኒያ ዕድሜ ጠገብ ሊሂቅ በሁሉ ቦታ፤ በሁሉም ሁኔታ አለን ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ በእኛ ውስጥም ሌላውም አለ ማለት ነው አማራነት ፍልስፍናው አቃፊነት እንጂ አግላይነት አይደለም ነው።

ለእኛዊነት ፈጣሪነት የአባቶቻችን፤  የእናቶቻችን ሌጋሲ ነው ስለዚህ ለእኛዊነት አባቶቻችን / እናቶቻችን የነበራቸው ፍልስፍና እዮራዊ ሲሆን፤ እኛም የእነሱ ልጆች ስለሆን ሐዋርያ አያስፍለገንም ነው ፍሬ ሃሳቡ። ነገር ግን ይህን የጥበብ ምህዋር ዛሬ ካለው ችግር ጋር በመመዘን የቀደመው የሥልጣኔ ዘመናይነታችን ውስጣችን እንድርገው ነው ፍስልፍናው።

ስለሆነም የእናንተ አይደለንም የሚሉት ቢሆን፤ በመንፈስ የእኔ ብሎ መቀበል ከተፈጥሯችን ግዴታ የመነሳት ስለሚሆን ፍትሃዊ ነው። የትኛውንም የማህበረሰብ አባል መግፋት አይገባም። ጥንቃቄው መሆን ያለበት አንተ ቀልጠህ እኔን አኮፍሰኝ ከሆነ ብቻ ነው። ለዛ ደግሞ አሁን ጊዜው አለመሆኑ እዬታዬ ነው። በሌላ በኩል ግን ይህ ፍልስፍና በመቀበል እና በመሳቀብል ደረጃ ማዕከላዊ ማድረጉ እንጂ አማራ ላይ ብቻ መጫን አይገባም የሚልም ሙግት ተደምጧል፤ ሌላው እንግዳ ተቀብሎ ለተገኘው ዕሴት የህዝቡ ሃብት እንጂ የትውስት አለመሆኑን ሞጋቾቹ አሳምነዋል ገላጩን።  

አማራ በመንፈስ በሁለት ዓመት የተደራጀ ሲሆን ተጋድሎው ኢትዮጵያንም ነፃ አውጥቷታል። የቄሮ ትግል ትናትም ብቻውን ለድል አልበቃም ወደፊትም አንዲት ጋት መረመድ አይችልም። አማራም እንዲሁ፤

ሌላውም በከሰረ ሰጋር ቢሽቆጠቆጥ የጥንካሬ ሆነ የአንቱነቱ ምንጩ ያ ስለሆነ ነው የወረወረውን መልሶ አራግፎ እዬለቀም የሚገኘው። ስለምን? „አማራነት መንፈስ“ ስለሆነ። ነገረ ግን አማራም በእኛነት ውስጥ ለመኖር መፍቀድ ተፈጥሮው መሆንን መሳት የለበትም። የእኛነት ፍልስፍና ምንጩ አማራዊ ነውና።

Ethiopia: ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዶር ዳኛቸው አሰፋ ስለ ጠሚ አቢይ አህመድ የተናገሩት

/ ዳኛቸው አሰፋ "የፖለቲካው መንፈስ ወዴት እየሄደ ነው" - ክፍል 2

ድሮም ቢሆን አማራነት ዘረኝነት አይደለም ወደፊትም አይሆንም። አማራነት ዘረኛ መሆን ከጀመረ ራሱን አፍርሶ ይወድቃል። አማራነት የሰውን፤ የግለሰብን ይሁን የቡድን ነፃነትን መጋፋት ሲጀምር ራሱን ይንዳል። ስለምን? የአባቶቹን / የእናቶቹን አደራ በልቷል እና። አማራነት አቃፊነት - ተንከባካቢነት - ቻይነት እና ነፃነት ነውና።
  • ·       ነገረ እማዋይ።

አሁን ሰሞኑን በነገረ እማዋይ ያለውን አቲካራ አዳምጣለሁኝ። መቼ ይሆን ቁርቁሱ የሚአበቃው፤ በውነት ይናፍቀኛል። አሉታዊ ስለሆነ ነው የማይመቸው። እኔ የትናንት ጓዴን እማዋይን አውቃታለሁኝ። እውነት ለመናገር ተናዳፊ ሴት አልነበረችም። የረጋ መንፈስ የነበራት፤ የተሰጣትን ሃላፊነት በአግባቡ የምትወጣ፤ ለነፃነት ክብር ያለት ወጣት ሆና ነው እኔ የማውቃት። እንዲያውም እኔ እጅግ ዘግይቼ ነው እሷ መሆኗን ሁሉ ያወቅሁት።

በእኔ ዘመን ፊት ለፊት ከወጣነው ወጣት ሴቶች አንዷ ነበረች። እናም በዚህ ዘመን ተስፋ ሳትቆርጥ ይህን ያህል መከራ ለመቀበል መፍቀዷ ትልቅነት ነው - ለእኔ። ወጣትነታችን ፈተና የበዛበት መሆኑ ላይበቃ ጎልማሳነታችንም ለፈተና መጋለጡ ያው ለህዝብ በቅንነት አገልግሎት መስጠት የተፈጠርንበት ስለሆነ ነው። ሸር እና ተንኮል እኔ አላውቅባትም። እርግጥ ነው አንድ ቢሮ ውስጥ አብረን አልሰራነም ውስጧን በጥልቀት ለማዬት ዕድሉ አልነበረኝም፤ ቢሆንም ግን አሉታዊ መረጃ የለኝም በእሷ ሰብዕና ውስጥ።  

የሆነ ሆኖ ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙን ትልቅነቷ የሚታዬን ሴት ናት ብለን፤ ሰው ናት ብለን፤ የተፈጥሮ አካል ናት ብለን ከተነሳን ብቻ ነው እውነት የሚታዬን። በእኔ ዕድሜ፤ በእኔ የፖለቲካ አቅም ያለ ሰው የቤተሰብ ዘር መቁጠር ፈታኝ ነገር ነው። 

እኔ እራሱ አማራም ሰው ነው። አማራነትም ተፈጥሯዊ ነው ስለዚህ ስለምን የአማራ የህልውና ተጋድሎ ተገለለ በሚል መንፈስ ነው አማራ ነኝ ብዬ ለመውጣት የተጋሁት እንጂ፤ ለእኔ ቅርቤ አንደኛው አጀንዳዬ የድምጽ አልባዎቹ የኢትዮጵያ እናቶች ሴቶች ዕንባ የሚቆምበትን ቀን መናፈቅ ለዛም መትጋት ከበቂ በላይ ነው። አጀንዳዬም ይህው ነው። ሁለተኛው አጀንዳዬ የሎሬት ጸጋዬን ሌጋሲ ማስቀጠል ነው።

ነገር ግን በዚህ የድምጽ አልባ ሴቶች ተጋድሎ ውስጥም የአማራ እናት፤ የአማራ ሴትም አለች። በሎሬቱ ኢትዮ አፍርካኒዝም ሌጋሲ ላይም አማራዋ ሴት አለች። ልክ እንደ ኮንሶዋ፤ ልክ አንደ ኦሮሟዋ ወዘተ እህት እናት ለአማራውም አማራ ስልሆንኩኝ ብቻ ገና ለራሷ አደላች ይሉኛል ብዬ ገፋ ላደርገው አልችልም አጀንዳውን።

በሚገፉት፤ በሚያገለሉት፤ በተወገዙት የአማራ ሴቶችም ውስጥ እኔም አለሁበት። ባልገለል እንኳን እማደርገው ይህውን ነበር። እንኳንስ መከራውን እዬተቀበልኩት፤ መከራውም ውጦኝ ሰልቅጦኝ ቀርቶ። አንዲት የአረና ተመራጭ ሦስት ልጆቿ መንገድ ላይ ወጡ እሷ ስትታሰር ሲባል እዚህ ያሉ ግን አገር ቤት ካሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር የሚሠሩትን ሁሉ ተነጋግሬያለሁ፤ ኢትዮጵውያንም ያውቃሉ በዚህ ጉዳይ እታትር እንደ ነበር …

ምን ለማለት ነው? አማራ ባልሆንም ስለ ሰው መብት አታገላለሁኝ ካልኩኝ በአማራው የሚደርሰው ግለት፤ መገፋት ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲወጣ የሚፈለግበትን ሚስጢር አሳምሬ አውቀዋለሁኝ። ስለዚህም አሞግታለሁኝ። እኔም የዚህ ተጠቂ ነኝ እና። 

አማራም  ከእንጨት፤ ከሳር፤ አልተፈጠረም። አማራም ሰው ነው። ቢያንስ ሰው የመሆን የመኖር መብቱ መከበር ዕውቅና ማግኘት አለበት ይህ መቼውንም የማላቆመው ተጋድሎዬ ነው። ይህ ማለት ግን የፈለገ የአማራ ልጅ የፈለገውን የፖለቲካ ድርጅ ራሱ ቢያደራጅ እና ቢፈጥር፤ ከተደራጀው ጋር ቢቀላቀል፤ የፈለገውን ሰው ቢያድነቅ፤ የፈለገውን መሪዬ ክብሬ ኩራቴ ቢል ግድ አይሰጠኝም። 

ስለምን? ሰው ከሚል ማዕከል የሚነሳ መርሃዊ ትግል የሰው የመኖር፤ የሰው የማስብ ነፃነት፤ የሰው የማስተዋል ነፃነት፤ የሰው የመራመድ ነፃነት፤ የሰው የመናገር ነፃነት፤ የሰው የመደራጀት ነፃነትን፤ የሰው የመፍጠር ነፃነትን፤ የሰው የመወሰን ነፃነት፤ የሰው የመደራጀት ነፃነትን ወዘተ መቀበል ግዴታ ነውና። 

ሰው ከሚለው መነሳት ያቃታቸው የአስተሳስብ ድህንት ያለባቸው እኮ ናቸው ሰው በተፈጥሮው የማሰብ፤ የማድረግ፤ የመወስን፤ የመደራጀት ነፃነት አይገባውም ብለው የሚተናኮሉት፤ ዘመቻም የሚከፍቱበት።

የአማራ ማናቸውም ድርጅት፤ ሚዲያ ሁሉ „ሰውን እና ተፈጥሮን“ ማዕከል አድርጎ መነሳት ይኖርበታል። እኔም ሰው ነኝ፤ እኔም የተፈጥሮ አካል ነኝ ማለት አለበት አንድ የአማራ ልጅ። ሌላውም እንደ እኔ ሰው ነው፤ ሌላውም እንደ እኔ የተፈጥሮ አካል ነው፤ ስለሆነም ለእኔ እንዲሆንልኝ፤ እንዲደረግልኝ የምፈልገውን ሌላውም ሊሰጠው ይገባል ብሎ መሞገት ግድ ይሆናል።

ነፃነት ሰጪም ነሺም የለም። ነፃነቴ የእኔ ነው። እኔም የነፃነቴ ነኝ። ስለ እኔ „እኔ“ እንጂ ሌላው ሊበይንልኝ አይችልም። ስለዚህ ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ የማሰብ፤ የመወሰን፤ የመደራጀት፤ የፈለገችውን ቲ ሸርት የመልበስ፤ የፈለገችውን ድርጅት የመቀላቀል ሙሉ መብት አላት። 

በማድረግ፤ በማድነቅ እረገድ አማራ ስለሆነች ብቻ አድንቃችሁ፤ አክበራችሁ፤ እረድታችሁ ከሆነ፤ ወይንም ግንቦት 7 ስላልነበረች ንቃችሁ፤ አቃላችሁ፤ ዘምታችሁባት ልክ እኔን እንደምታደርጉት አድርጋችሁባትም ከሆነም ተጠያቂው ህሊና ነው። በውሽት ዓለም መኖር ትርፉ ትዝብት ብቻ ሳይሆን ውድቀትም ነው። የተደረሰበትም እዬታየ ነው። 

ከባዱ የሥነ - ልቦና ፍርሰት ነው …  ሽንፈትም ከባዱ የሥነ - ልቦና ሽንፈት ሲሆን ነው። „ጀግና“ መባል ሲመጥን ብቻ ነው ጀግንነት ሰጪው ሊመሰገን የሚገባው፤ „ጀግና ሥምም“ ተቀባዩ፤ ባልተገባው ከሆነ አይሰነብትም ጤዛ ነው።

አንድ በብቃት ክህሎት የተመለከ ከአገር መሪነት ወደ መንደር መሪነት የሚያወርደውም በይኽው ነው። ማንኛውም ሰው ሲደግፍም ሲቃወም ሰው ከሚለው ከተነሳ፤ የወረት ካልሆነ እና ለአገር የሚጠቅም ብሎ ከተነሳ ጅዋጅዊት አይኖርም። ሰዎች መልካም ነገሮች ሲሰሩ እንደሚመሰገኑ፤ መልካም ሳይሆን ደግሞ እንደሚወቀሱ መቀበል አለባቸው።

ፍጽምና ክንፍ አለን ከሆነ ግን የማይሆን ነው። ለዚህ ነው እኔ ከሚጽፉ ሊሂቃን ውስጥ ለኢኮኖሚ ሊቀ ሊቃውንቱ ለዶር ፈቃዱ በቀለ እጅግ የጠለቀ ክብር ያለኝ። ረጅም ጊዜ የጹሁፋቸው ታዳሚ ነኝ። የሊሂቁ ጹሑፍ ወቅትን፤ የኃይል አሰላለፍን የሚሞግተው ሆነ የሚደግፋው የቆሙበት የፋክት አርበኝነታቸው ብቻ እና ብቻ ነው። ሃሳባቸው ብቻ ነው ደጋፊውም ሞጋቹም። ከስሜት ብብዙ ማይል የራቀ ቃለ ምልልሳቸውንም ሳደምጥ ኢትዮ አፍሪካኒዝም ተኮር ነው። 

ስለሆነም የሳቸው ጹሁፍ ወጀብ በመጣ ቁጥር ዘንበል ቀና የሚል አይደለም። ጽኑ እና ቋሚ መንፈሱ ዕውነት ብቻ ነው። ዕውነትን የሚደፍሩ ሚዲያዎች ብቻ ናቸው የእሳቸውን ብዕር ደፍረው የሚያስተናግዱት። ፈሪዎቹ እውነትን ሲሸሹ የኖሩት ግን አይደፍሩትም የሳቸውን ጹሁፍ። ምክንያቱም ወጀቡ እንሱንም ስለሚያጥረግርጋቸው ይርዳሉ …

የፍርሃቱ ምንጭ ደግሞ ሌላ ምን ሳይሆን ማዕከሉና የራዕዩ መንፈስ ሰውና ተፈጥሮ ሳይሆን ወረቀትና ማንፌሰቶ ስለመሆን ነው። የማንፌስቶ ጣዖት አምላኪ ልቡን መንፈሱ ሥነ - ልቦናው አዞት አያውቅም። እራሱን ያስረከበበትን ቀን እራሱም ያውቃዋል። ዝት በል ሲባል ሆ! ብሎ በተቃውሞ መዝምት ነው፤ አክብር ሲባልም ሆ! ብሎ በዘመቻ ደግሞ ማክበር። እሱ ያመለከው ሰው አይደለም መላዕክ ነው። ስህትት፤ ግደፈት የሚባል አይነካውም።  

የ43 ዓመቱ ግራ ዘመም ፖለቲካዊ መከራ በዚህ መታመቀ ችግሩ ነው። አሁን እንኳን ኢትዮጵያ ባለው የአብይ አዲስ መንፈስ እንኳን እራስን ለመግራት፤ የተሄደበት መንገድ ስህተት መሆኑን ማረም አለመቻሉ የሚገርመኝ ነገር ነው።

ለዶር አብይ አህመድ እኮ ሚሊዮኑ ያን ያህል ፍቅር የሰጠው የተከተለው መንገድ ሰውን እና ተፈጥሮን ማዕከል ማድርጉ ራሱን ወቅሶ ትክክለኛውን የግሎባል መንፈስ ለመከተል መጀመሩ ነው … ነገም እሱን ተወዳድሮ ለማሸነፍ ጋዳ ነው። በዚህው መንፈስ ውስጥ በልጦ መገኘት ካልተቻለ። መብለጥ ደግሞ የማይታሰብ ነው። ምን አልባት ከወጣቶቹ ከተገኜ ተፎካካሪ ይታያል ጉዱ ነው በመጪው ምርጫ፤ 

በዚህ ዘመን አንድም መንፈስ እኔ የፖለቲካ ሊሂቅ ከሚባለው ላደምጠው፤ ውስጤ ሊሆን አልቻለም፤ ምክንያቱም ደረጃውን ያልጠበቀ ስለሆነ።

በተጨማሪም መሻሻል፤ መታደስም ሳይሆን የትናንቱ ጦርነት ዛሬም በባለተራው አና ብሎ እያዬሁት ስለሆነ። መሪነት መጀመሪያ ወታደርህን ቅጥ ማስያዝ ነው። ሥርዓት ያጣ ወታደር ሥርዓት ማጣትን መርሁ ሲያደርግ ነው የተሸነፈው። ተሸናፊ ሰራዊት ይዘህ ለማሸነፍ ደግሞ ማሰቡ በራሱ የወደቀ ነው። ማንም ይሁን ማን።

ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ አንዲት ነፍስ ናት። ስለሆነም እባካችሁን ተዋት። እስር ቤት ያዬችው ፍዳ ይበቃታል። ለነፃነት የሚታገል ግለሰብ፤ ተቋም ከዚህ መጀመር አለበት፤ የሌላውን ነፃነት አለመጋፋት። የሴት ፖለቲከኛ ችግር ያለበት ድርጀት፤ አዲስ መፍጠር መቅረጽ ያልቻለ ድርጅት ሬድሜድ ሰብዕና መፈለግ ግድ ነው። ተጽዕኖ ፈጣሪን መልቅም የግንቦት 7 ዋናው ስትራቴጅ እና ስልቱ ነው። ያ ተጽዕኖ ፈጣሪው የተፈጠረበት ነገር ሲዝል ደግሞ አብሮ መንፈሱ ይዝላል። ትናንት ያልጠቀመ መንገድ ዛሬ ስለምን ተመራጭ እንዲሆን እንደ ተፈለገ አላውቅም።

በወ/ሮ አማዋይሽ አለሙ ለነፍስ ራዕይ ወሳኟ እሷው ናት። እሷ ደግሞ ፈቅዳለች። መድረኩን ዕውቅናውን ፈልጋለች። ሚዲያውን ክብሩን ልዕልናውን ፈልጋለች። ምክንያቱም ሌላው ሊያስጠጋት አልቻለም። ሴሪሞኒ እንድታሞቅ ሳይሆን ያልበረደ የትግል ስሜት አላት ይህች ሴት፤ ይህን አቅሟን የምታፈስብት መደረክ አስፈለጋት። በዛ ላይ ጎንደሬ አማራ ናት። ስለዚህ ለግንቦት 7 ኢላማ ምቹ ነበረች። እና ምህረት ጠይቆ ይሁን ምህረት ጠይቃ ወስናለች መሪዬ የምትለውን።
  
ስለምን? አብን እራሱ ሊጠቀምባት ይገባ ነበር። አብን ከሰማያዊ ሰው ከማምጣትስ ወ/ሮ አማዋይሽ አለሙን መጠቀም ይገባው ነበር። እራሱ ብአዴን ሊጠቀምባት፤ ሊያከብራት ይገባ ነበር። ብአዴን አንድም አቅም ያላት ሴት የለውም። ከኦህዴድ እንደማዬው ዓይነት ተወዳዳሪ ተፎካካሪ የሴት የፖለቲካ ሊሂቅ የለውም ብአዴን። ቀሚስ መልበስ ብቻ አይደለም የፖለቲካ ልቅና። ወቅቱን መመዘን የሚገባው ዶር አብይ አህመድ ካካበቱት የእውቀት የውሃ ልክ ጋር መሆን አለበት።

ከዶር አብይ አህመድ የፖለቲካ ሊሂቅነት አቅም ጋር መድርስ ባይችልም፤ ተደማጭ ሰውን መፍጠር ግድ ይለዋል ራሱ ብአዴን …  ምክንያቱም ፖለቲካ አውዱ ሙግት ነው። ሙግቱ ደግሞ በአንደበትም ተደማጭነት እና ለዛም ጭምር ነው፤ ያን አቅም መፍጠር በአንድ ጀንበር ማምጣት አይቻልም። የተሰናዳ ከተገኜ ግን መቅደም የአባት ነበር። አልሆነም።

በአብን ሆነ በብአዴን  ያዬሁት ብልህነት የለም። ራሱ የአማራ ታገድሎ ታታሪዎችን ለማቀፍ ያለው ፈቃደኝነት ምንም ነው። ማሳተፍ ማለት ስብሰባ መጥራት አይደለም። ሃላፊነት መስጠትም ጭምር ነው። ወንበር ማካፍልም ጭምር ነው። መድረክ ሰጥቶ እንዲመሩ አጋጣሚ ማመቻችትም ጭምር ነው። እንደማስበው የድርጅት ዘርፉ ሰፊ የሆነ ክፍተት አለበት። አንድ የፓርቲ የድርጅት ዘርፍ ሥራው ሰው ማበጀት ነው። ከግንባሩ አባል ውጪ የትኞቹ የአማራ ሊሂቅ ናቸው አሁን ሃላፊነት ያገኙት ሲባል ምንም ነው።

 እራሱ አሳልፎ ዕድሉን የሚሰጠበት አግባብ ዘባጣ ጠፍጣፋ ነው የብአዴን። መቀሌ ላይ ተጋሩ ባህርዳር ላይም ተጋሩ ይወከላል ለፌድራል መንግሥቱ። ብአዴን እንደለመደበት ወያኔ ሃርነት ትግራይ ቀኝ እጅ ቢባል ይሻለዋል። ዕድልን አሳልፎ እዬሰጡ ቁጭ ብሎ የሰቀሉትን ቁሞ መለመን፤ ለዚህም ነው የትም ቦታ ያልተካሄደ በአማራ ወጣት ሴቶች ብቻ ላይ ባለፈው ወር ሙከራ ሲደረግ የነበረው ... 

በኦሮሞ ሊሂቃን ግን አንድ ሁለት ተብሎ መቁጠር ይቻላል አቅም ያላቸውን የኦሮሞ ልጆች። ቄሮ እኮ ተጋድሎው በብዙ ዘርፉ ተጠቃሚነቱ እዬታዬ ነው። ለዛ ደግሞ ኦህዴድ የከፈተው በር ነው። ትርፋማ ጉዞ እያዬሁ ነው በኦህዴድ በኩል። ብአዴን ግን ብአዴን ያሉትን አማራዎች እንኳን ወደፊት ለማምጣት አቅቶት ሲጠወር ነው የማዬው። እንኳንስ ከድርጅቱ ውጪ ያሉትን ለሃላፊነት ሊያሳጭ ቀርቶ።   

የሆነ ሆኖ ምንአልባት ጠይቀዋት አይሆንም ሊሆንም ላይሆንም ይችላል አላውቅም፤ በሌላ በኩል ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ የአብይ መንፈስ አልተመቻትም የእሷ አቋሟ የሽግግር መንግሥት ነው። መና ላይ የምታስበው መሪ አላት። እስክታዬው ድረስ።  ይህ ደግሞ ብዙው የፖለቲካ ገብያተኛው የሚፈለገው አፍንጋጭ መንፈስ ነው። ብአዴንም ቢሆን ይህን የልዩነት መንፈሷን ሊያሰተናግድላት ይገባል። ለግንቦት 7 ቢሆን ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ቀላል የምትሆንለት ሴት አትሆንም።

ምንአልባት ከተጠቀመባት በኋዋላ እንደሚሆን ሊያድርጋት አስቦ ካልሆነ በስተቀር ልክ እንደ ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዴቅሳ በቀሰተ ደመና አሻጋሪነት ቅንጅት እና ፍርሰቱ ላይ እንደታዬው … የሽሚያ ፖለቲካ …

ለግንቦት 7 ግን አማራ ሴት የሥ/ አስፈጻሚ አካል አግኝቷል። ያው ከአማርኛ ቋንቋ ውጪ ሌላ ቋንቋ ስላማትችል ለሷ ሲባል ደንቡ ይሻሻላል። በዛ ላይ ደግሞ አማራ ለዛውም ጎንደረ? መራራ ነው ይህ ሃቅ። 

እሷም የሽግግር መንግሥትን ስታስብ ግምቷ ምን ያህል ትክክል ስለመሆኑ መሬት ላይ በመሪ እና በተመሪነት ደረጃ ታዬዋለች ብዬ አስባለሁኝ። የሞባይል ጽ/ቤት ማለት ምን ማለት እንደሆን። የሚዲያ ፖለቲካ ማልትም ምን ማለት እንደሆን ገጥ ለገጥ ይተያያሉ። መለኪያው አላት፤ ታውቀዋለች የፖለቲካ ድርጅት ፋንክሽነሪ ሆና ስለሰራች ማንዘርዘሪያውን … ሲናሪዮ ቢጋር ኮመንድ ፖስት ታልፎበታል እና ...

ለግንቦት 7 ግን እስከ አሁን አማራን አግላይነት ለነበረው ጭቅጭቅ አንድ ይህ አለኝ ብሎ እንደ አንድ ጊዜያዊ ስልታዊ ታክቲክ መላሾ ይጠቀምበታል፤ የአብይ ካቤኔ ለሴቶች ክብርም ስለአለው በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሆንለታል ለግንቦት 7፤ እዛው መሬት ላይ የሰላ የትግል ፍላጎቱ፤ የሞቀ ነፍስ ሲያገኝ ሎተሪ ለዛውም ተንቦላ ነው  አባል ለመሆን ከፈቀደች እማዋይ እነሱም ከፈቀዷት። ኦሮሟዋ አንበሳማ ማን ይደፍራታል ጀግኒትን ጫልትሻን?!
 
ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ የተፈጠረች እንጂ ግንቦት 7 የፈጠራት የፖለቲካ ሊሂቅ አይደለችም፤ የቆዬ ልምዱ አላት። በዛ ላይ ውጪ አገር እኔ ስታዘበው እንደኖርኩት ድርጅታዊ አቅሟም በሞባይል ጽ/ቤት የተቀመረ ወይንም የተመረቀ አይደለም። በኢሠፓ አይደለም በዬትኛውም ደረጃ የሰራ አካላችን ቀርቶ ሾፌሮች ሳይቀሩ የትም ቦታ፤ በዬትኛውም ሁኔታ ፈተናን ተቋቁመው ኑሯቸውን መምራት እንዲችሉ ሆነው ነው የተቀረጹት። አርበኛ መስከረም አታላይ ምን ነበሩ ብላችሁ ጠይቁ?

የሆነ ሆኖ ነፃነት መጋፍት ጨቋኝነት ነው። ትናንት በከፋት ሰዓት ሥሟ ትዝ ብሎት ያላወቀው፤ እስር ቤትም መከራውን አብሯት ያያት ግን ከነፃነት በኋዋላ የነበረው የታቆረ ቂመኛ መንፈስ፤ ተፈታ እንኳን በበዛ ግለት ውስጥ ሳለች ያላቃናችኋት ዛሬ ደግሞ የእኛ የምትሏትም ብትሆኑ ማተብ ስለምን ተሠራ ብላችሁ ራሳችሁን ዳኙት። ኢትዮጵያዊነት እውነትነት እንጂ ዕብለትነት አይደለምና።

Ethiopian politics - ቶሎሳ ከነማስረጃው የእማዋይሽን ዘላፋ እና ሼር ለሁለቱም ወገን ይናገራል


ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ግን ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ የምንግዜም ጀግናዬ ናት። አማራ ስለሆነችም ጎንደሬ ስለሆነችም አይደለም። የከፈለችው መከራ ለሁላችንም ነፃነት ነው። ነፍሷ ተሰቃይታለች፤ ባክናለችም በብዙም ተጎድታለች። ሌሎች እኮ በእኛ ዕድሜ ላይ ያሉ አይደለም ሴቶች ተብዕቶችም በፖለቲካው ዓለም የሉም። ውጪ አገር ተቀምጠው አርቲክል እንኳን … ማንበቡን አይፈቅዱም እንኳንስ ትግሉን የእኔ ሊሉት ቀርቶ፤

…  የሃሳብ ልዩነት አለን ከእኔ ጋር፤ ወ/ሮ አማዋይ እሷ የሽግግር መንግሥት አራማጅ ናት እኔ ደግሞ የዚህ ተጻራሪ ነኝ። ለ እኔ የ አብይ መንፈስ ልዩ ጠረኔ ነፍሴ ነው። ቢታገዝ፤ የጎለደው ቢሟላ መልካምነት አለው በፖለቲካ ሊሂቃን ታይቶ የማይታወቅ ቅንነት አለ፤ ከዘለቀ ... እርግጥ ነው ቀላሎች ሆነው ግን ያልተደፈሩ አመክንዮዎች እንዳሉም ብረዳም በሚዛን ግን ውስጥ ለማድረግ የሚመች መንፈስ ነው። 

ስለሆነም ብንገናኝ ተወያይተንበት ባንተማመን እንኳን አብረን ለመኖር የሚያግደን አንዳችም ነገር የለም። በአንድ የፖለቲካ ድርጅትም የተለዩ ሃሳቦች ካልኖሩ የኩሬ ውሃ ማለት ነው የሚሆን፤ ትግሉም አሰልቺ፤ አዛይ አደንዛዥ ነው የሚሆነው። አሁን እኮ አዲሱ ለውጥ ይህን ያክል ድምቀት ያገኘው በቃ የነፃነት ትግሉ ሞናትነስ ሆኖ ስለነበር ጭምር ነው። የሰው ልጅ አዲስነት ክፉሉ ነው።
 
የሆነ ሆኖ በጣም በዘገዬ ሰዓት ነው የኛዋ ጓዳችን እማዋይ ናት ሲሉኝ ግርም ነው ያለኝ - ያደንቅኳትም። አንድ የጋራ ጓዳችን ካናዳ ያለ ነው የነገረኝ። ስለሆነም ለእኔ አንዲት አንስት መድረክን መድፈር መቻሏ ባራሱ ድሌ ነውና ከልቤ መልካም የትግል ዘመን እንዲሆንላት ለቀድሞዋ ጓዴ ለወ/ሮ እማዋያሽ አለሙ እንዲሁን እመኝላት- አለሁኝ።

ያው ታውቃለች የግንባር ሥጋ መሆኔን በእኔ ቤትም ወለም ዘለም አለመኖሩን። ስለዚህም ምኞቴ የውነት ስለመሆኑ ትቀበለዋለች ብዬ አስባለሁኝ። በተረፈ ግን ውሳኔዋ የማይጸጽታት እንዳይሆን ግን ጥንቃቄ ማድረግ የራሷ ጉዳይ እንጂ የሌላው ሰው አይደለም። ህሊናሽን ልምራ ወይንም ለተወሰነ ጊዜ እኔ ልምራው ግን ይህ ስስታምነት ነው። እኔ ህሊና አለኝ ለእኔ ብቻ የሆነ። ሌላውም ህሊና አለው የእሱ ብቻ የሆነ። 

ልብ እንዲገጠምልኝ አለመፍቀዴ ነው በፈተና ስታሽ የኖርኩት። ስለዚህም ለእኔ የማልፍልገው ነገር ለእማዋይም አልመኝም። መብት አላት የራሷን መንገድ የመወሰን። ተጎድታለች እኮ ይህች ሊሂቅ። ስለዚህ በቅንነት - በመልካምነት ነገሮችን በማስተዋል አድርጎ በራስ ተግባር ላይ መታተር ይገባል። አዲስ ብቁ ሴትን ለመፍጠር መፍቀድ። እሷ ግን ልትወቀስ አይገባትም ነፃነቷን ፕራክቲስ ስላደረገች። 10 ዓመት የታሠረችው እኮ ለዚህም ነው። ያን መከራ የተቀበለቸው እንዳሻት የፈለገችውን የፖለቲካ መስመር ለመከተል ነው። እስካገለገል ድረስ ተከብራ ትኖራላች ዝንፍ ስትል ደግሞ ... ታውቀዋለች።  

ሌላው የወ/ሮ አማዋይሽ አለሙ ብልህነትም ነው ውሳኔዋ። ምን ትሁን ይህቺ ሴት? የፖለቲካ ሊሂቅ ናት። ባዶ ሜዳ ታቅፋ እንዴትስ እንደምንስ ትዝለቀው ውስጧ እያረረ? እዬቻላች መምራትም መታገልም። ሱስ እኮ ነው በፖለቲካ ዓለም መኖር። ልልቀቅህ ብትሉት እሱም እይለቅ እኛም አንለቀው።

ስለዚህ መድርክ ያስፈልጋት ነበር አደረገችው። ከዚህ ላይ የፋክት ጋዜጠኛውን አቶ ሲሳይ አጌናን ለናሙና ከልባችሁ ሆናችሁ እሰቡት። ኢሳትን ባይቀላቀል እኮ በቃ እንደ ማንኛውም ጋዜጠኛ ነበር የሚታዬው። አሁን የጋዜጠኛ እና የአርቲስት አባባ በለውን ዕጣ ፈንታ ለኩት። ሥሙን እንኳን ማንሳት አልቻለም ሚዲያው ሁሉ። እሱም አብዝቶ የደከመ ሰው ነው። 

ስለዚህም ጋዜጠኛ አቶ ሲሳይ አጌና አቅሙን የሚሳይበትን አጋጣሚውን ሳያሾልክ ተጠቀመበት እናም ከአድማስ ባሸገር ክህሎቱን ማስተዋል ቻልን፤ ከአንግዲህ የግሉንም ቢጀመር ችግር የለበትም፤ እስከ ዕድሜ ልኩ የሚዘለቅ ዕውቅና እና ክብር አግኝቷል ያውም በሁላችን ዘንድ። 

የእሱን ልዩ የሚያደርገው ሁሉም የሚስማመበት ጋዜጠኛ መሆኑን ነው። ከእሱ በመለስ ነው ወቀሳ እንኳን ለኢሳትም ለግንቦት 7 ሲኖር፤ እሱ እያለ ስለምን ይህ ይሆናል? እሰከ ማለት እንደርሳለን። አዛውንት ሽማግሌ ባለግራጫ አድርግን ነው የምናስበው ከ እድሜው በላይ፤ የሃሳብ ልዩነቱ እራሱ ፈቅደነው ወደነው ነው። ይህን ዕድሉን አሽሉኮት ቢሆን፤ ባናውቀው ግን ይህን ያህል የውስጥ ትምክህት አይኖርም ነበር። አስተዋሽ አልቦሽ ነበር የሚሆነው። እንደ ብዙዎቹ። የቅንነት ጋዜጠኛው አቶ አንተነህ ከበደን ማንሳት እሻለሁኝ። በጣም አዎንታዊ የሆነ ሰብዕና አለው ግን ... ቦታ የለውም ሌሎችም ... 

ስለዚህ እማዋይ በግንቦት 7 መድረክ ደግሞ ዳግም ትነሳለች ማለት ነው … አቅሟንም ታሳያለች … ሌላው ያልተመቸኝ ግን ገንዘብ ማዋጣትን በሚመለከት ነው። እሷ እኮ ህይወቷን ሰጥታለች። ለአንዲት ሴት ልጅ እስር ቤት በብዙ ፈተና ውስጥ እንድታለፍ ግድ ይላታል። ደም እኮ ሸንታለች ይህቺ መከረኛ። ለዛ መከራ አላቂ ገንዘብ አይመጥነውም እንዲያውም። ማንሳት ራሱ ማፈሪያነት ነው። ቁስ ምንድን ነው? 

ሰው እንግዳ ጋብዞ አብልቶ፤ አጠጥቶ እንደገና ትፋው አይነት ነው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ባህላችንም አይፈቅደውም። እውነት ለመናገር ህሊናዋን ለመግዛት ከሆነ ባይወጣ ቢቀር ምን በነበረ፤ ለዚህ ነው እኔ አስከቻልኩት ብቻ የምሰራው፤ ከአቅሜ በላይ በሆነ የፋይናንስ ጉዳይ ዘው ብዬ አላውቅም። በዚህ የፖለቲካ ህይወት በአቅም ለመኖር መወሰን መልካም ነው። 
  • ·       „ልክን ማወቅ ከልክ ያደርሳል“

በሌላ በኩልም ግንቦት 7 ቀላል ድርጅት አይደለም። በቀላሉ ዘው የሚባልበትም አይደለም። በጣም ከባዱ አምክንዮ የፖለቲካ ማህደር የግንቦት 7 ውስጡን ከማግኘቱ ላይ ነው ለአላዛሯ ኢትዮጵያ ሆነ ለአብይ ካቢኔ። 

ግንቦት 7 የሚመርጣቸው ሰዎች፤ ዕውቅና እዬሰጠ የሚያሳድጋቸው ሰዎችን፤ የማናውቃቸው ተመስጥረው የተያዙት እንደተጠበቁ ሆነው የምናውቃቸውን ማዬት ነው ውስጣቸው ጣዕሙ ምንም ምን እንደሚል። ከአንድ ወንዝ እንዴት ተቀዱ እስከሚያሰኝ ድረስ። መስፈርቱ ረቂቅ ነው … ወደ ላይ ሲያወጣ፤ ቦታ ሲሰጥም ሲያሽቀነጥርም።  

በታሪክ በብዙ ሁኔታ እንደ ግንቦት 7 ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት በአላዛሯ ኢትዮጵያ ተፈጥሯባት አያውቅም። የዶር ለማ መገርሳ እና የዶር አብይ አብይ ብቃት የሚለካው ከግንቦት 7 ጋር በሚፈጥሩት የግንኙነት ደንበር ልክ ይወሰናል። እንዲህ እንዳሻ የሚተረጎመ፤ ተደመረ የሚባልለት፤ ተዋህደ የሚባልለት፤ ተደራደረ የሚባልለት ድርጅት አይደለም ግንቦት 7 በፍጹም።

ግንቦት 7 የራሱ መገለጫ ተክለ ቁመና አለው። ሌላው የፖለቲካ ድርጅት በቃ የፖለቲካ ድርጅት ብቻ ነው። በዓላማ የተሰባሰቡ ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች የሚፈጥሩት፤ ግንቦት 7 ግን እንደዛ ብቻ አይደለም። ከዚህ በላይ መሄድ አያስፈልገኝም።  

እስኪ እሰቡት ከኤርትራ ሊቀመንበሩ ወደ አውሮፓ የሚመጡበት ወቅት መቼ? የትኛው ወራት? ተመራጭ እና ተዘውታሪ ነው ብላችሁ መርምሩት። ጥልቅ ነው ውቅያኖስ። እራሱ የኤርትራ መንግሥትም ይህን ጥበብ አያውቀውም ወይንም አልደረሰበትም። ወይንም ገብቶት ይሁን ብሎታል ቀን እዬጠበቀለት ያቆዬው ጉዳይም ሊሆን ይችላል … ሰው „ሰው“ ስለሆነ ብቻ በመደዴ ሰብዕናው አይለካም፤ አይሰፈረም፤ የሚመሠርተው ድርጅትም ይሁን ተቋምም እንዲሁ። የመታገያ ዘመኑ እዬተራዘመ በሄደ ቁጥር ጊዜ የሚሰጠን ግብረ ምላሽ አለ። ከተማርንበት።

ለዬት ብለው የሚፈጠሩ ግን ሳናውቃቸው እኛን አሳምረው የሚያውቁን አሉ …. የግንቦት 7 ሊቀመንበር እሳቸውን ያውቃሉ ብዬ የማስበው አንድ የፖለቲካ ሊሂቅ ቢኖሩ አቶ ስዬ አብርኃም ብቻ ናቸው። ልባቸውን ለማዋስ ያልሞከሩ ይመስለኛል በርቀት ጠረኑን ሳሸተው፤
  • ·       ሃሳብ የገብያ አዳራሽ ቧነት።  

የሆነ ሆኖ የትግሉ መሰረት የፖለቲካ የገብያ አዳራሽ ማግኘት ነው። ያ ደግሞ በዘመነ አብይ ሜዳውም ፈረሱም ይህው ተብሏል። ተቋማዊ ሁኔታው ያው ደጋግሜ አምልክቻለሁ፤ በግንባሩም በመንግሥትም በጣምራ ቁልፍ ቦታ ላይ ያሉት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ - እግዚአብሄርን ይዘህ እሳቸውን መሪ አድርገህ ስለማይታሰብ ነፃ ዴሞክራሲያዊ ፍትሃዊ አገር። ይህ ዝበት መስመር ከያዘ፤ ከተስተካከለ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ሁላችሁም ሃሳብን ገብያ ላይ የቆጣጠራችሁን ይዛችሁ መቅረብ ነው፤ ህዝብ የፈለገውን ይሸምትና ይመርጣል። 

በሌላ በኩል ከ6ወራት በሆዋላ ሙቀቱ መጠኑ ትኩሳቱ ተለክቶ ስለሚፈጠረው ከንቅናቄ ወደ ፓርቲ የሽግግር ፍልስፍና ደግሞ አለ፤ ምክንያቱም ለወቅቱ ብቻ ተስማሚ የሆኑ ጉዳዮች ብቻ ናቸው ሁለመና ሆነው የሚቀረጹት፤ ሌላው በአሮጌው በተመደው መስመር ተብ ሲል ብልጡ ልክ እንደ ዘመነ ቅንጅት ደግሞ በሰላው መስምር መጪ ነው፤ እና  ያንጊዜ ዋናው ሙግት ሲመጣ ምን ሊኮን ነው አሁን ገና መሬት ባልረገጠ ሁኔታ ጦርነቱ?

እማይገባኝ አሁን የአብን እና የግንቦት 7 ቁርቁሶ ነው። ስለምን ሁልጊዜ ግንቦት 7 አዲስ ከሚፈጠር ድርጅት ጋር ጦርነት እንደሚገጥም ፍች ያልተገኘለት ጉዳይ ነው። የኦህዴድ አበቃና እና አሁን ደግሞ ከአብ ጋር መሆኑን አዳምጣለሁኝ። 

አሁን ምን ችግር አለው። የበለጠ ሃሳብ ይዞ መገኘት ብቻ ነው ተፈላጊው ነገር። በቃ። ለዚህ ደግሞ ለ6 ወር ተቀጥሯል አይደል? ተመስገን ማለት ሁለቱም ይገባቸዋል፤ አብን ለመደራጀት ችሏል፤ ግንቦት 7 ከአሸባሪነት ውግዘት ቀርቶለት አገር ገብቶ እንዲታገል ሁኔታው ምቹ ሆኖለታል፤ ለዛውም ሰው ሁሉም ነገር በተሰላቸው ጊዜ  አሽሉኮታል እና ሁለቱም ተመስገን ብለው እንደ መንገዳቸው መጓዝ ነው በቃ …. የሃሳብ ነፃነትን ሳናከብር ለነፃነት ስንት ዘመን ስንታገል እንደኖርን እራሱ ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው - ለእኔ። … ይብቃኝ …

ነፃነቴ የእኔ ነው። እኔም የነፃነቴ ነኝ።
ነፃነት የእሱም፤ የእሷም ነው። እሱም እሷም የነፃነታቸው ናቸው!

የኔዎቹ ውዶቹ ኑሩልኝ።

ማለፊያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።