የአቶ ዳውድ ኢብሳ "የእንትን" ፍልስፍና።
ልብ።
„አቤቱ በቁጣህ አትቅሰፈኝ፤ በመ ዓትህ አትገስጸኝ።“
መዝሙር ፮ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
10.10.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ
- · መነሻ።
ሰበር
መግለጫ ኦነግ ትጥቅ ፈቶ ለመግባት ነው የተስመማው
ጤና ይስጥልኝ እንዴት ናችሁ ደህና ናችሁ ወይ ክብረቶቼ። ዛሬ የኢትዮጵያ መንግሥት ኦነግን
በሚመለከት ግልጽ አቋሙን አሳውቋል። እጅግም ዘግይቷል። ቢሆንም ግን እኔ በገባኝ እና በጻፍኩት ልክ በሁሉም መስክ በተበራራ መልኩ
በመንግሥትም ተገልጧል። ቆፍጠን ኮስተር ያለ መግለጫ ይመስላል መሬት ላይ ድፍረቱ ከኖረው። በዚህ እኔ ደስ ብሎኛል ደስ ያለኝ ግን እኔ የተረዳሁትን ያህል ስለገለጸው ነው። መግለጫውን የሰጡት አቶ ካሳሁን
ጎፌ መ/ጉ/ኮ/ጽ/ቤት ም/ዴኤታ ናቸው።
እኔ ብዙ ጊዜ በአዎንታዊነት ሥማቸውን አነሳዋለሁኝ።
ለዬትኛውም ጥያቄ ግልጽና ጭብጥ ነክ ምላሽ ለመስጠት አቅማቸውን ያዬሁት አቶ ዳውድ ኢብሳ በኦነግ መሪነት ኤርትራ ላይ እያሉ ፤
ዶር መራራ ጉዲና በኦፌኮ መሪነት፤ አቶ ካሳሁን ጎፌ ኦህዴድን ኦደፓን ወክለው በዶቼቨሌ ዲቤት ሲያደርጉ በተመስጦ ነበር የተከታተልኩት።
ያን ጊዜ እጅግ ነው የተደነቅኩት።
ዲቤቱ ለእኔ 70% በአቶ ካሳሁን ጎፌ አሸናፊነት ነበር የተጠናቀቀው። ያን ጊዜም አቶ ዳውድ ኢብሳ 30 ሺህ እስረኛን
መፈታትን በሚመለከት እምነታቸው ስስ ነበር ሰራን የምትሉትም በቂ አይደለም ብለው ነበር ያቃለሉት፤ ያበጨሉት። ያው ኦፌኮንም „ጉልቻ ቢለዋወጥ
ወጥ አይጠፋጥም“ አቋም ነው የነበረው።
ሌላ ጊዜም በዶር አብይ አህመድ ወደ ኦህዴድ ሊቀመንበርነት ሲመጡም እንዲሁ አቶ ካሳሁን ጎፌ ተጠይቀው እጅግ ጠንቃቃ
መልስ ነበር የሰጡት። አብሶ ቀጣይ ጠ/ ሚር ቦታን ሲጠዬቁ በብልህ አቅም ነበር የመለሱት። ሌላ ጊዜም እንዲሁ በዶር ለማ መገርሳ
እና በዶር አብይ አህመድ መካከል ስላለው ግንኙነትም ተጠይቀው ምህንድስናው የዶር ለማ መገርሳ መሆኑን ገልጸው ዶር አብይ አህመድ
በሚመለከት ክህሎታቸውን ሲገልጹ ምቀኝነት፤ ቅናት፤ ኢጎ፤ የበታችነት ስሜት በሌለበት ሁኔታ በድንግልና የገለጹ ሰው ናቸው። እንደሳቸው ደፍሮ የተናገረ እኔ አላዬሁኝም።
እንዲያውም እምሳታውሰው
የኦህዴድ ጽ/ ቤት አንድ የኮንድንዬም ቤት ይመሰል እንደ ነበር እና እሳቸው ግን ለቱሪስት መስህብ በሚሆን መልኩ እንዳደራጁት ገልጸው
ነበር። አያይዘውም የሳይንስ ቴክኖሎጂ ሚ/ር በነበሩበት ወቅትም ያሳዩትን ልህቅና በአድናቆት ነበር የመሰከሩት። በሌላም በኩል በሥራ ዓለም ዶር አብይ አህመድ ያላቸውን ቤተሰባዊ አቀራረብ
እና አብሮ ለመስራት ምቹ መሪ ስለመሆናቸው በአጽህኖት አብራርተው ነበር።
እኔ ሁልጊዜ ይህ የመንግሥት አንደበት የሚባለውን
በሚር ደረጃ እንዲይዙ የምፈቅዳቸው ነበሩ። አብሶ ኦህዴድ ውስጥ በግልጽ በዶር አብይ አህመድ ብቃት ጎን የቆሙ እሳቸው እና አቶ
ታዬ ደንደኣ መሆናቸውን ስሜታቸውን ተረድቻለሁኝ። ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫው ላይ የመንግስትን ግልጽ አቋም ገልጸዋል። ዝረዝሩን
ውዴቼ ታዳምጡት ዘንድ በትህትና እግልጻለሁኝ። እንዲሁም የአቶ ዳውድ ኢብሳም በተወሰነ ደረጃ ሙሉ የሚባለው ቃለ ምልልስ ወጥቷል።
የተቆረጠ ግን አለ። ቢሆንም በዚህ ውስጥ አትኩሮቴ የሳበውን አምክንዮ ብቻ አነሳሳለሁኝ።
በአቶ ካሳሁን ጎፌ ገለጣ እርግጥ ነው ግድፈት አይቻለሁኝ።
ኤርትራ የነበሩ የታጠቁ ሃይሎችን በሚመለከት ከሳቸው የማላስበው ግድፈት ነገር ገጥሞኛል። ጠንቃቃ መሆናቸውን ስለማውቅ ዕውቅና መንፈግ
የፈለጉት ሃይል እንዳለ ተረድቻለሁኝ። ኦነግ፤ ግንቦት 7፤ የአቶ ሞላ አስገደሙ ገና ትናንት እዬገባ ነው የተባለውን የዴ.ም.ህ.ት ሌላው ቀርቶ ቤንሻንጉልን
ሲያነሱ የአማራ ዴሞክራሲ ሃይልን ዘለውታል። በዚህ አጋጣሚ ዴምህት
መንገድ ላይ የገጠመው አደጋ ነፍሳቸው ላላፉ ወገኖቼ ነፍሳቸውን ይማር ልጄ ይመጣል ብላ ለጠበቀቸው ያቺ መከረኛ እናትም መጽናናቱን
ይስጣት አምላኬ። አሜን!
ወደ ቀደመው ምልስት ሲሆን የአቶ ካሳሁን ጎፌ አንድን
የአማራን ታጣቂ የተደራጀ ሃይል መዝለል ይህን አብሬ እማዬው የአዲስ ዓመት ዋዜማ ምሽት ላይ ጠ/ ሚር አብይ አህመድም ሰላማዊ ጥሪውን አክብረው
ወደ አገር የገቡትን የፖለቲካ ድርጅቶችን፤ ሊሂቃን፤ አክቲቢስቶችን ሥም በእጥፍ ሲጠሩ የአማራን አንድም ሊሂቅ አልጠቀሱም መድረክ ላይም ጎልተው እንዲወጡ፤
ዕወቅና እንዲያገኙ አልተፈለገም ያው እጅ ለእጅ በመያያዙም እንዲሁ። አማራ እንደ ዘመነ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ዛሬም ለ ኦዴፓ ዘመን ጋሬ ወይንም ግርባ ከሆነ ምን ይፈልጋል?
ስሜን አሜሪካ ላይም የአማራ አክቲቢስቶችን አንዳቸውንም
ዕውቅና ሲሰጡ አልተደመጡ ዶር አብይ አህመድ ራሳቸው። እንዲያውም የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ የሚድጡ ነፍሶችን ነው እንደ
ታቦት ሲከበክቡ የሚታዩት - አሁንም። ዛሬ የኢህአዴግ ለውጥ ነው ብሎ በመግለጫው ዓይኑን በጥሬጨው አጥቦ ግንባሩ ቢያወጣውም
ዓለም በሙሉ ይመሰክራዋል የአማራ ተጋድሎ መሰረታዊ የለውጥ ውጤት ስለመሆኑ። ልባቸው ያውቀዋል ራሳቸው ዶር አብይ አህመድ ይሁኑ
ዶር ለማ መገርሳ።
ይህም ብቻ አይደለም ኤርትራ ያሉ በትጥቅ ትግል የሚታገሉት
ጋር የኢትዮጵያ መንግሥት ውክል አካላት ነው ሁሉችንም ያነጋገረው፤ አማራው ላይ ሲደርስ ግን አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ደረጃ እንኳን አተልደረሰም።
ግንቦት 7 በጠ/ ሚር አህመድ፤ ኦነግ በጠ/ ሚር ደረጃ፤ በውጭ ጉዳይ ሚር እና በኦሮሞ ክልላዊ መስተዳደር ፕሬዚዳንት፤ በተጨማሪም በዛሬው በአቶ ካሳሁን ጎፌ መግለጫ ፕሬዚዳንት የሚልም ተጥቅሷል ዶር ተሾመ ሙላቱን
ይሁን ዶር ለማ መገርሳን አላውቅም ብቻ የክብሩን ደረጃ ማዬት ይቻላል።
ዴ.ም.ህ.ት
በፌድራል ደረጃ የፌድራል የደህንነት መሪ ነው ያነጋጋራቸው ሲሆን አማራውን ደግሞ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው። ምን ማለት ነው ይህ? ምን ተብሎ
ይተርጎም? „እንዳያማም ጥራው እንዳይበላም ግፋው ነው“ ይሄ እሰከ አጥንት ገብቶ የሚመረምር ረመጥ አመክንዮ ነው። ግንቦት 7 በትክክል የፌድራል ደረጃ ቢሰጠው የተገባ
ነው፤ ህብረ ብሄር ንቅናቄ ስለሆነ፤ ሌላው ግን የዞግ ድርጅት ነው። የክት እና የዘወትር እንዲህ ገና በመባቻው የለማ አብይ ሌጋሲ
ካዘወተር ነገ ገና ከመምጣቱ በፊት ጠንዝሎ ይታዬኛል።
…. ዛሬ ደግሞ እማከብራቸው አቶ ካሳሁን ጎፌ የአማራን ዴሞክራሲያዊ ሃይልን ንቅናቄን እንዲሁ ዘለውታል። ባለማወቅ ነው ማለት አልፈልግም። ምክንያቱም እሳቸው እጅግ ጠንቃቃ ሰው መሆነቸውን በቀደመው ጊዜ አስተውያለሁ
እና። እራሱ ድርጅቱን እንዳለም አልቆጠሩት። ሰርዘውታል።
መጪው ጊዜ ድቅድቅ ነው …. ለአማራ። ማናቸውም አማራ ነክ የሆኑ አክቲቢቲዎችን ዕወቅና ለላለመስጠት የተማማሉ ነው የሚመስሉት።
ለዘለለ
አማራን እንደ ዜጋ የማዬት፤ አማራን በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ለማዬት ፈቃድ ፈጽሞ የለም። አማራነት ተለጣፊነት ወይንም
የማደጎ ልጅ አይነት ሆኖ ነው የሚታዬው። ይህ እኔን እንደ አማራ ይጎረብጠኛል። መጎርበጥ ብቻ አይደለም ወደዚህ አቅጣጫ እንዳተኩር
እዬተገፋሁኝ ነው ያለሁት።
ሌሎቹም ወገኖቼ መሰሉን አቋም እንዲይዙ እዬተገፉ ነው። በዚህ አያያዝ መጪው ዘመን ቆምጣጣ ይመስለኛል። የሚደንቀው፤ የሚገርመው
አማራ ክልል ኢትዮጵያ ሄደው የነበሩ እንደሚነግሩኝ ከሆነ በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ አብይ አለ እኔንም ጨምሮ። ነገር ግን ይህን የተሰጠውን
ንጹህ ፍቅር የአብይ ሌጋሴ ዕውቅና ሊሰጠው አልፈቀደም። እንዴያውም አልፈልግላችሁም ውስዱት እያለን ነው ፍቅርን፤ አክብሮትን፤ ትህትናን።
ለምን? እዮር ይመርምረው። ብዙ ግራ የሚገቡኝ አመክንዮዎች አሉ።
አሁን የኢህአዴግ የግንባር መግለጫ ኦህዴድ እንዳይከፋ፤
ደቡብ እንዳይከፋ፤ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በቁልምጫ ላይ ነው፤ ኦህዴድ ላይ ቁልምጫ ነው፤ ደቡብ ላይ ቁልምጫ ነው የለማ አብይ ሌጋሲ
አማራ ላይ ሲደርስ ግን ወገቤን ነው የሚለው፤ ድርብ ጫና ድርብ ግለት ነው እያደረገ ያለው። እንዲያውም ኦሮሞ አፍሪካን ሲመራ
ለማዬት አማራ በአማራነቱ ሳይሆን በህብረ ብሄር ጋሻ ጃግሬነት ድርሻውን ይወጣ ዓይነት ነው - ተቀብሮ። ይህ ነገር ነገን ያከስለዋል። አደባባያዊ
ግለት እና ጫና ነው ያለው። ይህን ደፍረን እንናገራለን። ምክንያቱም ጠበንጃ ተሸካሚነት ቀጣዩ ትውልድ ዕጣው መሆን ስሌለበት።
50 ዓመቱ የአማራ ቀንበር ፖሊሲ በዚህ ዘመን መቀጠሉ
ለዛውም ሰዋዊነት እና ተፈጥሯዊነት ማዕካላቸው ነው ለተበሉት ለለማ አብይ ሌጋሲ አሰንጋላ ነው። ለእኔ ጠ/ ሚር አብይ ክህሎታቸው ነው ሥልጣን ላይ ያለው ብዬ
አስባለሁኝ፤ የመወስን አቅም ያለው ሌላ እንደሆነ ይረዳኛል። ምክንያቱም ወንበሩ ባዶ ሆነ ነውና ያዬሁት - በህልሜ። ዶር አብይ አህመድም ከስሜን አሜሪካ መልስ በሙሉ
የፈጠራ ክህሎታቸው ልክ እንዲንቀሳቀሱ ራሱ የተፈቀደላቸው አይመስለኛም። ቆጥበው ተብለው የተገሰጹ ዓይነት፤ ያ ዬዕለቱ የምስራች ኮሰመነ እኮ ያ አዳዲስ የተስፋ ጉዞ … ከሳ። ኢትዮጵያዊነትም
አሻቅበን የምናዬው ምስል ብቻ ነው የሆነው። በቃ ዛሬም ትናንትም በአብይ
አንደበት ብቻ ያለ …
- · አቶ ዳውድ እና ዋልታ እንዴት ተኋኋኑ?
የዋልታ አወያይ ሙከራው ሁሉ ሳይሳካ እንዴት አሁን
ተሳካ ብሎ ለጠዬቀው አቶ ዳውድ ኢብሳ ሲመልሱ ሲመልሱ ቃል በቃል አልጻፍኩትም ዕድምታው ግን የሰላም ጥሪውን ላለመቀበል አለመፈልግ
ሳይሆን ተገፍተው እንዴት እንደ ወጡ ገልጠው የለማ አብይ መንግሥት
ከመለሰም ሌጋሲ ከሃይለማርያም መንግሥት ሌጋሲ በተለዬ ሁኔታ ተሰናድተው ተዘጋጅተው ስለመጡ ነው ያሉት።
የቀደመው ትጥቅ ትግል የማስፈታት፤ ግልጽነት አለመኖር፤ ጉልበት የማሳዬት፤ ወደ ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ለመመለስ አለመፍቀድ እንደ ነበር
ገልጸው አቶ ዳውድ ኢብሳ ሲዊዲን ኖሮይ አሜሪካ ወዘተ ለማስማማት
ጥረት እንዳደረጉ እንዳልተሳከ ነው የገለጹት።
አሁን በዚህ እሳቤ የቀደሙት ስምምነቶችን ያለተሳኩበት
ሁኔታ የለማ አብይ ሌጋሲ እንደ ተሰናደ፤ በበቂም እንደ ተዘጋጀ ነው የገለጹት። ከቀደመው ስምምነቱን ከሚያፈርሱ ነገሮች በተቃራኒ
ዝግጅት ሰላለ ነው ማለት የቀደመውን ስምምነት የፈረሰበትን የለማ አብይ ሌጋሲ ተስማምቶበታል ማለት ነው። ይህ እንግዲህ „የራስን
ዕድል በራስ መወሰንንም“ ይጨምራል ማለት ነው። ዝቅ ብዬ ሙሉ ቃሉን ስለጻፍኩት ከልብ ሆናችሁ ትከታተሉት ዘንድ በትሁት መንፈስ
አሳስባለሁኝ። የትጥቁም ጉዳይ እንዲሁ ነው።
ሌላው የተጠዬቁት የበደኖ የአርባጉጉ የአማራ ህዝብ ጭፍጫፋ ነበር። እሱንም
የእኛ እጅ የለበትም ብለው፤ ስለምን ወተር ላይ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጠረው ጭፍጨፋ ተሸፈነ? የበደኖን እና አርባጉጉን ያህል
የወተሩ አልጮኽም ባይ ናቸው? በዚህ አገላላለጽ ወተር ላይ እጃቸው እንደ ሌለ ነገር ግን አርባጉጉ እና በደኖ ላይ ደግሞ ከፍተው
ትተውታል መቼም ክፍት በመተው የቃላት ዳማ በመጫወት ሊሂቅነታቸው ብጡል ነው። አሻሚ ቃላትን ነው የሚመርጡት። የቃላት ፈንጣጣ ግጥማቸው ነው። "የእንትን" ፍልስፍናም።
የሆነ ሆኖ ነፃ እና
ገለልተኛ አካል ይመርምረው ባይ ናቸው። ህም! የዘር ጥፋት አልተካሄድም የሚል ሌጋሲ ባለበት ሁኔታ እንዴት ተብሎ ነው ገለልተኛ አካል
የሚፈጠረው? ቀድሞ ነገር አማራ ዜጋ ሲሆን ነው ይህ ጥያቄ መልስ የሚያገኘው።
እጅግ አሳዛኙ ነገር ሃላፊነት የሚወስድ አካል አለመኖሩ
ነው። ይህም ብቻ አይደለም አማራ ኢትዮጵያዊ ነው ብሎ ለመቀበል እስከ አሁን ድርስ በመንግሥት ደረጃ የሚደፈር አለመሆኑ ነው።
- · ዛሬም የተቆረጠው …. አለ።
ዛሬ ሙሉ ነው ቃለ ምልልለስ ወጥቷል፤ የሰኔ 16 ጉዳይ ግን ተቆርጧል።
በአቶ ዳውድ ኢብሳ ቀደም ብሎ ተቆራርጦ፤ ተቀጣጥሎ በቀረበው ቃለ ምልልሳቸው የሰኔ 16ቱ ጉዳይ በዛሬው ሙሉውን መቆረጡ
ለምን? እሳቸውም አቶ ዳውድ ኢብሳ 100/100 እኛ የለንበትም እራሳቸውን ይጠይቁ በማለት በግልጽ እርግጠኛ ሆነው ነበር የተናገሩት።
እኔም እራሱን ኦህዴድ ይመርምር ብዬ ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ደም ከልብ የሆነውን ነፍስ፤ ዜግነትን የተነፈገቸውን የቆሞስ
ኢንጂነር ስመኛው በቀለን ጉዳይ አብሮ ሊታይ እንደሚገባውም ገልጫለሁኝ። ውዴቼ ይህን ቁልፍልፍ ያለውን ነገር ደጋግሞ ማዳመጡ ስለሚበጅ ደግማችሁ አዳምጡት።
„ትጥቅ ፈቱ መባል አንፈልግም”
አሁን በዋልታ ቴሌቪዥን ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ሙሉው ወጣ ሲባል ያች ከቀደመችው ተቆርጣ ከቀረበችው የሰኔ 16 የግድያ ወንጀል
ላይ ሌላ መንግሥትን የሚታገል ሌላም ስኳድ ከኦነግ ውጪ የሆነ ኦህዴድ ውስጥም ሊሆን ይቻላል ሥውር መንግሥት እንዳለም
ፍንጭ ይሰጣል።
የሆነ ሆኖ ጠ/ ሚር አብይ አህመድ እና ካቢኔያቸው የሰይጣን
ጆሮ ይደፍን እና አንድ ነገር ሆነው ቢሆን ኖሮ የቆሞስ ኢንጂነር ስመኛው ዕጣ ፈንታ ይገጥማቸው ነበር፤ ደመ ከልብነት። ዜግነታቸውም
ይሻር ነበር ማለት ነው በዚህ አያያዝ። ምን አልባትም እንደ ቆመሱ ቀባሪም ላይፈቀድ ይችል ነበር። እሳቸው ቆመው ይህን ዕውነት
መድፈር ያልቻሉ አንድ ነገር ቢሆኖ ኑሮስ? ወደፊትም ቢፈጠርስ?
ድብቆሹ መገለጥ እስካልቻለ ድረስ ነገም ሞቱ ቀጣይ ነው። ህግ ደግሞ
ለባለጊዜ ማድላቱ ቀጣይ ነው። ነገር ግን ማንም ሰው ከህግ በላይ ሊሆን አይገባም ነበር። ይህም የተጠያቂነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ትውልዱ በዬጊዜው ስለሚከፍለው መስዋዕትነት
ሃላፊነት የሚወሰድ አካል ባለቤት የለሽ መሆን መራራ ገጠመኝ ነው - ለእኔ። ለድምጽ አልባዎቹ የ ኢትዮጵያ እናቶችም የማህጸን እሳተ ጎመራ።
- · ቁልፋ ቁልፍ //// ሲፋታታ
ሌላው እጅግ ያስደሰተኝ ግልጥንት ቀደም ባለው ጊዜ
በዬትኛው ዘመን እንደሆን አላውቅም ብቻ „ኦሮሞ“ ማለት ወንጀል ነበር ይላሉ አቶ ዳውድ ኢብሳ። እኔ በደረግ ጊዜ የተለያዩ ኮርሶችን፤
ሰሚናሮችን፤ የተለያዩ ጉባኤዎችን ተሳትፌ ነበር፤ አርሲም ነበርኩኝ ምንም ቅንጣት የልዩነት ነገር አይቼ አላውቅም ነበር። አዲሱን
ትውልድ ለማሳመጽ የተነሳ ነጥብ ነው።
በፍጹም ሁኔታ ምንም ልዩነት አልነበረም። እኩል እንማራለን እኩል እንመደባለን።
እንዲያውም ከፍ ያለውን ቁንጮ እነሱ እና ኤርትራውያን ነበር የሚቆጣጠሩት። አሁን እኮ ሦስት ትውልድ ያዩ የተማሩ የተመራመሩ የኦሮሞ ሊሂቃን በሁሉም የዕውቅት ዓይነት አሉ መሬት ላይ።
ሌላው ይህን ቁልፍልፍ ዓላማውን ይዞ በአቶ ዳውድ
ኢብሳ የሚመራው ኦነግ መንግሥት ባወቀው ስምሪት አዲስ አባባ ላይ ሁለት ጊዜ ስብሰባ እንዳደረጉ፤ የባንክ አካውንት እንደከፈቱ፤
የአመራር አካላት ስምሪት ሐረር፤ ወለጋ፤ ቦረና፤ አርሲ ስብሰባ እንዳደረጉ፤ በቀጠይም ለህዋሳቾቻቸው ሰሚናር በዬደራጀው ለመስጠት
እንደተዘጋጁ ሥራ ላይ እንደሆኑ ነው የገለጹት። በዚህ ላይ ም/ ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ደግሞ ወጣቶቻቸውን እዬሰበሰቡ እዬሰበኩላቸው ነው።
ሌላው ልብ ያላት ጉዳይ ከህውሃት ጋር ያላቸውን ቀረቤታ
ልዮዋን የአቀባበልን መሰናዶ በሚመለከት „መንግሥት ራሱ ነው ያዘጋጀው" ነው የሚሉት።
እኛ እንዲያውም አናውቀውም ነው ያሉት። "እኛ ከኢህአዴግ ጋር ይሁን ከቲፒኤልኤፍ ጋር የጦርነት ግንኙነት ነው ያለን። መራራ የሆነ ጉዳት አድርሰውብናል።" ይህም "በአንድ ጀንበር አይልቅም።"
አቀባበሉን ያዘጋጀልን
የዶር አብይ መንግሥት ነው ያዘጋጀው ቲፒኤልፍ ደግሞ ከግንባሩ ውስጥ ነው ያለው ብለዋል። እስከ አሁን ምንም ዓይነት ግንኙነት የተለዬ የተመሰጠረ ግንኙነት የለንም
ነው ያሉት። ይህም ክፍት ነው „እስከ አሁን“ ነው ያሉት ነገ የሚያስማማቸው ነገር ቢገጥም? አይታወቅም።
በሌላ በኩል ደግሞ እርቀ ሰላሙ ያን
መራራ ዘመን አሳልፍን በአንድ ጀንበር አይከወንም ነው ያሉት። ይህ እጅግ ከባድ ነገር ነው። በዚህ ወስጥ የመደመር፤ የይቅርታ፤ የምህረት የሚባሉት የለማ
አብይ ሌጋሲ አንጎል አምክንዮዎች በኦነግ ዘንድ ገና ያልተደፈሩ ስለመሆነቸው ታውጇል። እስቲ ትደገም። „በአንድ ጀንበር አይልቅም።“ ህም።
የገረመኝ ግን የለማ አብይ ሌጋሲ የኦነግ ሠራዊት
ወደ አገር ሲገባ ትግራይ ላይ አቀባባል እንዲሰናዳ ሲያደርግ ስለምን ይህን ለግንቦት 7 ይህን ለአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ እንዲያደርገላቸው
አልተፈቀደም? በተለይ ከቲፒኤልኤፍ ጋር የተናጠል እስከ አሁን ግነኙነት
እስከ ሌላው ድረስ ኦነግ? ይህም ቋጠሮው የበዛ አመክንዮ ነው።
ልዩ እንክብካቤ፤ ልዩ አያያዝ፤ ልዩ ጥበቃ እኔ ከአብይ ሌጋሴ አልጠብቅም።
እኔ የአብይ ሌጋሲ እንደ ተፈጥሮው እንደ ወትሮው ለሁሉም እኩል መሆንን ቢደፈረው መልካም ይመስለኛል። የአስጨንቀው፤ የሚጫነው
መንፈስ ከኖረም ደግሞ ለህዝብ ግልጽ ያደርግ። አኔ አሁንም አብይን ፍለጋ ላይ ነኝ …
- · የአቶ ዳውድ ኢብሳ የቃላት የዳማ ጨዋታ አበሳ። „የእንትን“ ሌጋሲ ….
መቼም የሳቸው ሌጋሲ መራሹ ቃል "እንትን" ነው፤ ጭብጡን
ግርዶሽ ሊሰሩለት ሲፈልጉ "በእንትን" ያወራርዱታል። ጭብጡን ቀብረው ለማለፍ የሚጠቀሙበት ቃል ነው 'እንትን'።
ስለመገንጠል አቋሙ ኦነግ አሻሽሎት
ይሆን ብሎ የዋልታ ቃለ ምልልስ አድራጊ ሲጠይቅ፤ አቶ ዳውድ ኢብሳ „ትጥቅ መፍታት“ የሚለውን እንደፈሩት ሁሉ „መገንጠል“ ጽንሰ ሐሳቡን አልወደዱትም።
አዲስ
መዝገበ ቃላት አዘጋጅተውለታል። ሊሂቃኑ ሁሉ የአማራ የህልውና የማንነት ጥያቄ የሚለውን መድፈር እንደተሳናቸው ዓይነት ማለት ነው "ፋኖ" „የነፃነት ሃይል‘ ቅብጥርሶ ምንትሶ እንደሚሉት ቅጥልጥል ጉድ። ብቻ በዚህ አንድ ዓመት የተማርኩት ታላቅ ነገር የኦሮሞ ሊሂቃን ልብን ለማግኘት ዳገት መሆኑን ነው። ደገት ብቻም ሳይሆን መራራም ነው። ዶር መራራ ጉዲናም እንዲሁ
ናቸው፤ ወዘፍ አድርገው ነው የሚተውት፤ በቃል መቆዬትም የእርግማን ዓይነት እዬሆነ ነው፤ ፍላጎታቸውን ሰም ለብስ ወርቅ፤ በአለባሶ
አሽሞንሙነው ነው የሚገልጹት ድፍንፍን ድብልብል አድረገው።
እንደዚህ ዘመን በፍጹም ሁኔታ እኔ አልተማርኩም፤ ሁሉንም በቅንነት ነበር የማዬው አሁን ግን ዕውነትም
እንደሚባሉት ነው ወይ እያልኩኝ ነው ከራሴ ጋር ሙግት ላይ ነኝ። ኢትዮጵያ ለማለት ይሁን ኦሮምያ ለማለት ይሁን አይታውቀም ሊሂቃኑ
አጋድመው በአገሪቱ ተጀምሮ በአገሪቱ ይጠናቃል። እስኪያልቅ
ይህን ሳስብ የግንቦት 7ቱ አገራዊ ንቅናቄው ትውስ አለኝ። የሆነ ሆኖ እንዲህ ይላሉ አቶ ዳውድ ኢብሳ …
„ይህ ኦሮምያ መገንጠል ኤርትራን መገንጠል ኮንሴፕቱ
ወይንም ደግሞ ጽንሰ ሃሳቡ መገንጠል የሚለው በእንግሊዘኛው የፖለቲካ ጽንሰሓሳብ የትኛውን እንደሚወክል ብዙ አመት የተቸገርንበት
„እንትን“ ነው። ወይ ኢንዲፕንደት ጥያቄ ነው ይዘን የተነሳነው፡፤ ያ ከሆነ ነፃነት ነው እንጂ መገንጠል አይደለም። መገንጠል የሚለው
ኮንሰፔቱ ዋነኛውን የትኛው የእንግሊዘኛ የፖለቲካ ኮንሴፕት እንደሚወክል ለመረዳት ብዙ የተቸገርንበት ነው መገንጠል የሚለው „እንትን“
ይዘን ተንቀሳቅሰንም አናውቅም፤ እዬተንቀሳቅስን ያለነው ይህ የታወቀ ነው የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ መንግሥት በጉልበት በጠበንጃ ነው የተያዘው የቅኝ ግዛት ማለት ነው። ይሄ ብዙ ቦታ ማሰረዳት ይቻላል። ከዚህ
የኦሮሞ ህዝብ ነፃ መውጣት አለበት ብለን ነው የተነሳነው። የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ፕሮግራም ይህ ነው።
ይህን ደግሞ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ብሎ ነው
ያሰቀመጠው። ይህን
የሚወስነው የኦሮሞ ህዝብ ነው። ይህ እንዴት ነው ነፃ አገር መመስረት ነው ወይ ደግሞ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ሌላ አይነት ፖለቲካ
ግንኙነት አድርጎ ሌላ አይነት አዲስ መንግሥት የፖለቲካ ግንኙነት መፍጠር ሁሉን አሳቃፊ ሁሉን አሳታፊ የሆነ ማድረግ ነው ይህ የኦሮሞ
ህዝብ በተዋካዮቹ የሚወስደው ውሳኔ ነው። ይሄው በቂ ነው።“
ከአገር ምስረታው በኋዋላም ቢሆን እንደ ጎረቤት አገር ወይንም በኮንፌደሬሽን
ወይንም ኦሮሞ ኢንፓዬር የሚመራት ኢትዮጵያ ወዘተ ክፍት የሆነ ነገር ነው …. ዝንባሌው አዝማሚያው ጠረኑ አዬሩ ሁሉ ይህን ይህን
የሚልም ይመስላል …. ዘትንሳኤከ ...
ከጠ/ ሚር አብይ አህመድ መንግሥት ጋር ይሁን ከዶር
ለማ መገርሳ እንዲሁም ከዶር ወርቅነህ ገበዬሁ ጋር ስምምነቱ ይህ ነው። የአብይ መንግሥት ተሰናድተው ተዘጋጅተው ስለመጡ ነው የተቀበልናቸው የሚሉን፤
ሟቹ የአቶ መለስ ዜናዊ ይሁን የአቶ ሃይለማርያም ደስላኝ መንግስት፤ ሲዊዲን፤ አሜሪካ፤ ኖሮውይ ወዘተ ሞክረው ሳይሰካ ቀርቶ አሁን
የተሳከው ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት በሚያችሉት ሁሉገብ ትግል መንገድ ይታገሉ ዘንድ ነው የተፈቀደላቸው።
አገር ምድሩ
አትንኳቸው ተብሎ የአገር መምስረቻ ዓርማቸውን በመዲናይቱ ተውልብልቦ አቀባበል እንዲደረግ የተደረገው ለዚህ ነው። ከላይ እስከታች ያለው የጸጥታ ሃይልም ያረገረገው ለዚህ ነው።
ትግራይም ትእዛዝ ተሰጥቷት አቀባባሉን በታቀደው ሁኔታ
የፈጸመችው ለዚህ ነው ራስን በራስ የማስተዳደር ፕሮግራም። ይህን የተቃወሙ ደግሞ ከ1000 ሺህ በላይ የሆኑ ዜጎች በሺሻ፤ በጫት፤
በዘረፋ፤ በደረቅ ወንጀል ተሳቦ በግፍ ጦላይ ላይ ባለቤት አልባ ሆነው አሳራቸውን ይከፍላሉ። ፍትህ ትጮኻለች።
ዛሬ መግለጫውን የሰጠው የኢትዮጵያ
መንግሥት ኢትዮጵያዊ ነኝ ያለውን ህዝብ አስሮ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ኢትዮጵያ ቅኝ ገዝታኛለች የሚል አካልን በቢአይፒ ደረጃ እያንፈራሰሰ
ነው። ለዛውም በትጥቅ የተደገፈ ጥቃት እዬፈጸመ፤ ሺዎችን አፈናቅሎ፤ ታሪክ ይፍረደው? ለመሆኑ አንድ አገር ሌላውን ቅኝ ለማድረግ
ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው? ለመሆኑ መቼ ዘመን ነው ኦሮሞ መንግሥት መሥርቶ የሚያውቅ? ካሰኜኝ ሌላ ጊዜ እጽፈበታለሁኝ። የፈጣሪ ቁጣንም ማሰብ ይገባል።
ወደ ቀደመው ሃሳብ ምልስት ሲሆን „መገንጠል“ የሚለውን የፈሩበት ምክንያት ከአንድ ሙሉ አካል የተወሰነው ሲነጠል ወይንም ሲለይ፤ ሲዘነጠል ማለት ነው መገንጠል፤ ከትክሻ እጅ ሲገነጠል ወይንም ሲነጠል። አብሮ የኖረ አገር ሲለይ የሚለውን መቀበል አልፈለጉም።፡
በሳቸው
በአቶ ዳውድ ኢብሳ ግንዛቤ ኦሮሞ የምትባል አገር ነበረችን ያችን አገር ኢትዮጵያ የምትባል አገር በጠመንጃ በሃይል ቅኝ አድረጋት
ኑራላች አሁን ከቅኝ ገዢያችን ኢትዮጵያ ነፃ መውጣት እንፈልጋለን። ቀድሞውንም አካል አልነበረንም ነው የሚሉት። መገንጠል የምትለዋን ነፃነት በምትል ቃል እንድትወራረድ
የፈጉበት መሰረታዊ ምክንያት ይኸው ነው።
አንድ ጊዜም አቶ ጃዋር መሃመድ ያን የ5 ቀኑን የቤት መዋል አድማ ሰሞናት
ቃሉን ተጠቅሞበታል ራስን በራስ መሳተዳደር በሚል፤ ሌላ ጊዜ ሲጠይቅ ደግሞ አባጭሎ አልፎታል። እንደ አሳ ነው ሙልጭልጭ የሚለው ቃላቱ ከእነሱ ሲደርስ። የሆነ ሆኖ ይህ ሌላ የታሪክ
ፍተሻ ስለሚያስገባ አሳ ጎርጓሪ ይሆንባቸዋል። እኔም ልለፈው የፍቅርን ትውልድ ክው አድርጎ ስለሚያደርቅ። ክፉ ቃል ለህሊና አይመችም
እና … ለዬትኛውስ ዘመን …
እንደ አቶ ዳውድ ኢብሳ ህልም አገራዊ ማንነታችን
በህዝብ አስወሰነን ከኢትዮጵያ መንግሥት፤ ወይንም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋርም አይደለም የሚሉት ከተለያዩ ህዝቦች ጋር አብረን የምንወስንበት ሁኔታ በቀጣይ
ዕድሉን እናመቻቻለን ነው የሚሉት። ሌሎችም እንዲሁ የዬራሳቸውን ትናንሽ ቁርጥራጮ ይፍጠሩም ባይ ናቸው። ወደ 80 አገሮች። የትኛው ፕላኔት ላይ ይሆን የሚኖሩት?
እራሱ ቃሉ „ኦሮምያ“ የሚለው ወያኔ ሃርነት ትግራይ
ሰራሽ ነው። እንዲያውም አንድ ጊዜ ወ/ሮ አዳነች ፍሰሃዬ የVOA ጋዜጠኛ ቃለ ምልልስ ስታደርግ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ችሮታ „ኦሮምያ“
የሚባል ክልል ተፈጥሮላችኋዋል ቀድሞ ኦሮምያ
የሚባል ክ/ አገር ነበራችሁ ነበር
ያለችው።
ግርም ነው ያለኝ አንዲት ዓለም አቀፍ ጋዜጠኛ ከወያኔ ሃርነት መምጣት በፊት ስለነበረው የአገራችን የአሰተዳደር እና የአመራር አደረጃጀት ብጣቂ ዕውቅት ፍርፋሪ ግንዛቤ እንደሌላት
ተረድቼ ነበር። ብቃት ማለት የዞግ ማህበርተኛ
መሆን ብቻ ነው። የነበረው ክ/ ሐገር ወለጋ፤ ባሌ፤ ጎጃም፤ ትግራይ፤ ሐረር፤ ኢሊባቡር፤ ስሜን በጌምድር/ ጎንደር/ ሽዋ፤ ጅማ፤
ጋምጎፋ፤ ወሎ፤ ኤርትራ፤ አርሲ፤ ሲዳሞ 14 ክፍላተ ሐገራት ነው የነበሩት። እሷ ታዲያ ቀድሞ „ኦሮምያ“ የሚባል ክ/ ሐገር ነበራችሁ
ዛሬ „ኦሮምያ“ የሚባል ክልል ሰጥተናችኋዋል ምን ትፈልጋላችሁ ዓይነት ነው ነበረው … ዕድምታዋ። መሳቂያ!
የሆነ ሆኖ ልኣላዊ አገር ነበርን፤ ሉኣላዊ አገርነታችን
የቀማን የኢትዮጵያ መንግሥት ነው ስለሆነም የእኛ ጥያቄ አብረን ካልነበርንበት ልንለይ ወይንም ልንገነጠል ሳይሆን እንደ ቀደመው
አገርነታችን ነፃነታችን አስመልሰን ልዑላዊ አገር መሆን ነው እድምታው። ለዚህ ነው „መገንጠል“ የሚለውን ቃል ማንሳት ያልፈልጉት።
በዚህ ውስጥ ያሉ የቃላትን፤ የሥንኛት፤ የሐረጋት ወዲህ እና ወዲህ እያምታቱ ሃቅን ላለመድፈር የሄዱበት መንገድ እንደ ተመክሯቸው
ራሳቸውን አስገምቷቸዋል።
ልባቸው ሚዛኑ - ወቄቱ - ልኩ የማስተዋል ደረጃው ምን ያህል ስለመሆኑ ማዬትም አስችሎናል። ለእኔ እራሱ
ቃላት ምርጫው ትልቅ የፖለቲካ ክስረት ነው። አጀንዳ አልባ መሆነቸው አስደንግጧቸዋል ብዬ ነው የማስበው። ሃቅን ክዶ እና ጥሶ ትቢያ
አልብሶ እና ጠቅጥቆ ቢሄዱት የኢትዮጵያ አምላክም አለ። በቀጣይ የትግል
ዘመን ህይወታቸው ስለመቀጠሉ ራሱ አያውቁትም።
እንደ አዲስ ኦህዴድም የተወሰነውን/ ኦፌኮም/ ሌሎች ከኦነግ
ሥም የፊትም የኋላም እዬቀጣጠሉ ያሉ ድርጅቶችን አሰባስበው አንድ ኦሮምያ የምትባል አገር የመፍጠሩን ሴራ በተደላደለ መሬት ላይ
በሰላም ወጥተው በመግባት ለማስፈጸም ነው የተሰናዱት። አዲስ አባባ፤ ሐረር፤ አርሲ እና ወለጋ እናም ቦረና ሥራ እንደጀመሩ፤ የባንክም
አካውንትም እንደከፉት ነገረውናል። ይህም በመንግሥት እንደሚታወቅ
ገልጸውልናል።
- · የተደሞ ፈንጣጣ።
ቀደም ባለው ተቆራርጦ በወጣው ቃለ ምልልስ „ትጥቅ
አልፈታም አላለም ኦነግ“ የሚል ዕድምታም የነበራቸው ወገኖች ነበሩ። የዛሬው የኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠው መግለጫ ለእነዛ የዕድምታ
ተደሞ የግንዛቤ ደረጃ መልስ ቁልፉን የሳጣቸው ሲሆን፤ በሌላ በኩል የአቶ ዳውድ ኢብሳ ያቃላት መረጣ የዳማ ጨዋታ በሙሉው ቃለ ምልልስ ላይ ማግኘት ይቻላል። „መገንጠልን“ ነፃነት“ በሚል የተኩበት
ዋናው አብይ አመክንዮ እኛ ሉዕላዊ መንግሥት የነበረን ወደፊትም ለዛ የምንታገል ነን ነው ዋናው ቁሙ ነገር። ይህን ከልብ ሆኖ በማስተዋል የእኔ ብሎ የልብ ማድረግ ይገባል።
የቃላት ምርጫቸው በጣም የታመቀ በብዙ ትርጉሞች የታጨቀ
ብቻ ሳይሆን ታዳሚውን አውላላ ሜዳ ላይ ከፈተው ነው የሚተዉት። በነገራችን ላይ ሁሉችም የኦሮሞ ሊሂቃን ይሆኑ አክቲቢስቶች ቃለ
ምልልስ ሲያደርጉ ቃለ ምልልሱ ዕወጃ ነው። ዓዋጁ ለኦሮሞ ህዝብ ነው።
ቃለ ምልልስ አድራጊው ለእሱ መልስ የሚሰጣቸው ይመስላዋል፤
አይደለም እነሱን በሚከተሉት ፍልስፍና አባሎቻቸውን ተከታዮቻቸውን አንዲሁም ደጋፊዎቻቸውን ማስታጠቅ ነው የሚሹት። ይህ የተለዬ ክህሎታቸው
ነው። ለጥያቄው መልስ ሲሰጡ ተከታዮቻቸውን ሰብሰብበው በአዳራሽ ይሁን ሜዳ ላይ የሚያነግሩ ያህል ነው የሚሰማቸው። የሚናገሩት ፊት ለፊት ለኦዲዬንሳቸው ነው። ይህን ልብ የሚለው መንግሥትም የፖለቲካም ሊሂቅ አላዬሁኝም።
ለውጡን በሚመለከት እኛም አለንብት፤ በከፍተኛ ደረጃ ተንቀሳቅሳናል የእኛም
ውጤት ነው ይላሉ። ይህ ከሆነ ለሻሸመኔውም ለቡራዩም አረመኔዊ ድርጊት እጃችን አለበት ብሎ መድፈር ግድ ይላል። ሃላፊነቱንም መወሰድ
ይገባል። አቶ ዳውድ ኢብሳ የኦነግ ሊቀመንበር አንዲት ቅንጣት ቦታ ላይ ሃላፊነት የወሰዱበት ቦታ የለም። ሽሽት ክፍላቸው ነው። እኔ የሚገርመኝ ይህን
እያዬ የኢትዮጵያ ወጣት አላስፈለጊ መሰዋትን መፍቀዱ ነው። አንድም ሊሂቅ ሃላፊነት ሲወሰድ ተደምጦ አይታወቅም። ትውልዱ ልብ ሊኖረው
ይገባል። ትውልዱ በራሱ ላይ ጢባ ጢቦሽ መጫወት የለበትም።
ሌላው ያዘንኩበት እሳቸው ታሰረው ወላጅ እናታቸው
እሳቸውን ሊዩ ሲሄዱ የደረሰው ሰቆቃ ነው። የሁላችንም እናቶች ደረጃው ቢለያይም በዬዘመኑ እስረኛ ልጆቻቸውን ሊዩ ሲሄዱ መሰሉ ይፈጸማል። ስለሆነም
እግዚአብሄር ደግ አምላክ ነው ለእናት ዛሬም ያው ልጅ እንዳ ህፃን ልጅ ስለምታይ እናታቸው ከዛ ሁሉ መከራ ዘመን አልፈው ደግሞው
ስላገኛቸው ዕድለኛ ናቸው። እንኳንም ለዓይነ ሥጋ አበቃቸው።
አሁንም ይበቃሻል መከራ ብለው ቀሪ ዘመናቸውን በትካዜ እንዳያሳልፉት ቢጠነቀቁላቸው መልካም ነው። አሁንም
የሳቸው እናት ፍደኛ ናቸው። ልጃቸው ሌላ እሰጣ ገባ መሆናቸው የእናትን የመጨረሻ ዘመን የባሰ ያጠቁረዋል፤ ከበፊቱም በከፋ ሁኔታ ሰቀቀን ነው እዛው ኤርትራ በሩቁ ቢሆን ይቀል ነበር። አሁንም እሳቸው ጫካ አሰኝቷቸዋል፤ ነገሩ ካለማራቸው ጫካ ሊገቡ ይችላሉ፤ ከገቡ ደግሞ መከራው ግዙፍ ነው።
ለሌሎች የኦሮሞ እናቶችም ለሳቸው ሥልጣን ክብር እና ዝና ሲባል ባያንገላቷቸው መልካም ይመስለኛል። የትናንቱ ላይበቃ በተዘጋ በተዳፈነ
እምቅ ፍላጎት እናት ዕድሜ ልኳን የኦሮሞ እናት እንድታለቅስ መፍረድ? እም።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ
ሚስጢር።
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ