ፈሳሽ ፖለቲካ እና አደጋው። ሻማዋም ኑዛዜ ላይ ናት።

ጥምዝምዝ አመክንዮ።
„የእግዚአብሄር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፣---
የሰው ልጅ ሆይ፤ የወይን ግንድ፣ በዱር ዛፎች
መካከል ያለ የወይን አረግ ከዛፍ ሁሉ ይልቅ
ብልጫው ምንድር ነው?“
ትንቢተ ህዝቅኤል ምዕራፍ ፲፬ ከቁጥር ፲፪ እስከ ፲፫
ከሥርጉተ©ሥላሴ
24.10.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።



  • ·       ብጥ።

መሻገር በአዎንታዊነት ቢሆን ምንኛ መልካም በሆነ። ወንዝ ከላይ ከላይ ሌላ ቦታ ዝናብ ሲጥል በድንገቴ ወንዙ ይሞላ እና ብዙ አደጋ ያስከትላል። ማለትም እዛ አካባቢ ዝናብ ሳይኖር ማለት ነው። የችግሩ ምንጭ ከሌላ በሚነሳ እንደማለት። ሙላቱም ደራሽ ይባላል። ምንልባትም ከሰዎች ተሻጋሪዎች በተጨማሪም የጋማ ከብቶችም ሊኖሩበት ይችላል። 

አገር ሰላም ነው ብለው በተለመደው አኳሆን መሻገር ሲጀመሩ ድንገት ዶል ይልና ደራሹ የመጨረሻ ስንብት ይሆናል። የዋና ሙያተኛ የሆነው ግን ምን አልባት ከንፍሮ ጥሬ የሚያወጣው አምላክ ይድን ይሆናል። የኢትዮጵያ የቀውስ መነሻ ውስጣዊ ብቻ ነውን? እእ!የፈሳሽ ፖለቲካ አደጋ ይታዬኛል። 

ወደ ቀደመው ጭብጤ ምልሰት ሲሆን አካባቢውን አጥንተው ሰማዩንም አስተውለው ላይ ዘንቧል ብለው የሚያስቡ ጠንቃቆች ግን ከመግባታቸው በፊት ወደ ወንዙ በተረጋጋ ሁኔታ አደብ ስለሚገዙ ብዙም ለአደጋ አይጋለጡም። ደራሽ ሙላቱ ተግ ሲል ሁሉም በነበረው መልክ ሲረጋጋ ሁሉም ወደ ቦታው ሲመለስ ወንዙን አቋርጠው ወደ ቀያቸው ይገሰግሳሉ። ለዚህ ነው አበው „የሚያልፍ ዝናብ አይምታህ“ የሚሉት። ግን ኦዴፓ ይህን አስተውሎታልን? መሪው አገር መሪው አስተዳዳሪው አውራ ፓርቲ እሱ ስለሆነ።

አሁን እማያቸው ጉዳዮች እና መጪውን ጊዜ በእጅጉ ያሰስበኛል በ2017 ህዳር ወር ላይ VOA ከአቶ ያሬድ ጥበቡ እና ከፕሮፌሰር ዳንኤል ተፈራ ጋር አንድ ደማቅ ውይይት አካሄዶ ነበር። ራዲዮ ክፍሉ የሰጋበትን ነገር አንስቶ ሲጠይቅ „የእርስ በርስ ግጭት እኔን አያሰጋኝም ተጋምደናል“ ሲሉ አቶ ያሬድ ጥበቡ፤ በአንጻሩ ፕሮፌሰር ዳንኤል ተፈራ ግን ያሰገኛል ብለው እኔም ተያያዥ ጉዳዮችን አክዬ „መቋሚያ“ በሚል እርእስ ጉዳይ እርሰዎ እድለኛ ነውት አቶ ያሬድ ጥበቡን ማለት ነው እኔ ደግሞ እንቅልፍ አጥቼለሁኝ፤ የነገ ብቻ ሳይሆን የነገ ወዲያውም ያሰጋኛል ብዬ ሞግቼ ነበር።

አሁን በድጋሚ አቶ ያሬድ ጥበቡን VOA መልሶ ቢጠይቅልኝ ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ቃለ ምልልስ የሚያደርጉ ወገኖች የሚሰጡት አስተያዬት ለመንግሥት ሰፊ ጠቀሚታ ስላለው። መንግሥት ሳይሸበር ተመክሮዎችን ሥራ ላይ ሊያውላቸው ባይችል እንኳን እንደ ውስጥ ጠባቂ የመከላከያ የሃሳብ ሃይል ሊመለከታቸው ይችላል።

በሰል ያሉ፤ ጠንከር ያሉ፤ አሻግረው የሚመለከቱ፤ ማግስትን የሚተረጉሙ ዕይታዎች ሲኖሩ ከትወልድ ብክነት ይታደጋሉ። ያ የአቶ ያሬድ ጥበቡ መልስ ግን እንቅልፍ ለሽ አድርጎ የሚያስወስድ እጅግም አዘናጊ እናም ትጥቅ አስፈቺ ትንተና ነበር።

ዛሬ በአገር ውስጥ መፈናቀል ኢትዮጵያ ከዓለም አንደኛ የወጣችበትን መርዶ እዬተሰማ ነው። መፈናቀል የሌለበት አካባቢ የለም። በ2030 ደግሞ የሰይጣን ጀሮ ይደፍናን እና እንደ አሜሪካውያን ሊቀ ቃነት ትንተና ከሚከስሙት አገሮች ተርታ ትገኛለች አገረ ኢትዮጵያ። እግዚኦ! ተሰህለን! መሃከነ!

ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን ይህ ራሱ ከባድ ቢሆንም አሁን ባለው የህግ የበላይነት የማስጠበቅ አቅሙ ጋር ሲለካ ነገ ከዛሬዎች የከፋ ይሆናል የሚል ከፍተኛ ሥጋት ነው ያለኝ እኔ በግሌ። ተኝተው የሚያድሩ ዕድለኛ ናቸው። ደራሽ ችግሮቹ ቢታከሉስ ብሎ ማሰብ አሁንም ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል።

አብሶ ከኤርትራ የሚገቡ የነፃነት ታጋዮች ጉዳይ ባልተፈተገ የጥራት ዕሳቤ እንዲህ በመደመር ፖለቲካ መቀላቀሉ ነው አሁን አደጋውን የባሰ እያደረገ ያለው። ወትሮ በርቀት ነበር። አሁን ደግሞ በአካል ከዛው ናቸው። እያንዳንዷን ደቂቃ በምን ሁነት እንደሚጠቀምቡት ፈጣሪ ይወቀው።

አቶ ጃዋር መሃመድን እሸከማለሁ ብላ በቀይ ምንጣፍ የተቀበለች ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ የኡጋዴ ነፃ አውጭን እቀበላለሁ ብላለች። ቀደም ባለው ጊዜ የእነ አቶ ዳውድ ኢብሳን አቋም በተወሰነ ደረጃ መረጃ እጦት የለብንም። የኡጋዴው ነፃ አውጭ ግን መንፈሱ ብዙም ቅርብ ስላልነበር ከመረጃ ውጭ ነን። ያው ከግንቦት 7 የፍራንክፈርት ስምምነት ውጪ፤ ያም ምን ስለምን ሰለመሆኑ ድፍን ነው የነበረው። ብቻ ስለ ኦጋዴን ነጻ አውጪ ድርጅትጊዜም አባክነን አናውቅም።

እና በዚህ ቀውስ ውስጥ ሆነ ኢትዮጵያ ምን አለ አደብ ብትገዛ ያሰኛል። አገር ውስጥ ያለው መከራ ገፈቱም ዋናውም እዬናጣት ያነን መልክ ሳታስይዝ አሁን ተጨማሪ ችግር ለማስተናገድ ወቅቱ አልነበረም። ጠ/ሚር አብይ አህመድ የ አማካሪ ድርቀት ያለባቸው ይመስለኛል። ይህ የመለዬት ሳይሆን ለወል አገራዊ መረጋጋት ሲባል እንሱም ትንሽ ተግ ቢሉ መልካም በሆነ ነበር። የተወሰነ ሃይል ስለገባ ያ በቂ ነበር ባይ ነኝ። ለዛውም የጓዳ ስምምነቱ በምን መልኩ እንደሆነ ራሱ አይታወቅም። 

እትጌ ኤርትራ ግንቦት 7 እና ኦነግን በመሬቷ ላይ አብራ ስታኖር ችግር ገጥሟት አያውቅም። እንዲያውም ግንቦት 7 በአውሮፓ ህብረት መልካም ፈቃድ ከኦዴግ ጋር አገር ለመግባት ትንሳኤ እና እኔ ህይወት ነኝ ብሎው በፍቅር እፍ ብለውም ነበር። ጫዋታው ፈረሰ ሆነ እንጂ ከላይ በወረደ ዶፍ። የጫጉላ ጊዜውን ያዬ፤ ከኦፌኮ ጋርም ቢሆን መሪዎችን አክባሪ  ነው ግንቦት 7 ለአውሮፓው ህብረት የምርጥ ዜጋ ጉባኤ ተመራጭ ነበር፤ ኢሳት ሚዲያው ኦሮምኛ ፕሮግራም አለው። ሊሂቃኑ የ ኦሮሞ ማለቴ ነው በሚዲያው ግርማ ሞገስነታቸው አምደኛ ነበር።  

ዛሬ ተፎካካሪ ሆኖ የቀረበው አቶ ጃዋር አህመድ ሆነ ቲም አባሉ ፕ/ ህዝቃዬል ግርማና ሞገሱ በዝቀሽ በኢሳት ላይም ነበር። እኛም ያወቅናቸው በዛ ነው። ያ ፍቅር አሁን የት ገባ?

እትጌ ኤርትራ ስትፈቅድ ብቻ ነበርን ፍቅሩ ያሰኛል? እትጌ ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ትጥቅ አስፈትታ ስትልክ ደግሞ አዲስ ጦርነት አስከፍታ ነው። አንደኛው ኢትዮጵያዊነትን ሌልኛው ደግሞ ኦሮሞነት አንጥራ፤ ቀምማም አጠናክራ ነበር። ብርቱ ሙግት ነበር። የ ኦነግ ዓርማ እና የዜግነት ዓርማው የቀዝቃዛው ጦርነት በ አፍሪካ መዲና አዲስ አባባ ላይ። ገዢ መሬት መቆጣጠር ይሉሃል እንዲህ ነው። ሙት መሬት ላይ ነው የነረበረው ኦዴፓ።

ለዛውም ቦንቡ የፈንዳው አዲስ አባባ ላይ ነው። ወያኔን አዝለን እንዳስገባን አንቀልባውን እንነሳዋለን ፍጥጫ ተግባራዊ ሊሆን ይሆን ያሰኛል? መቼም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቄን እንደ ሌላው የአገር መሪ ማዬት ትልቁ የፖለቲካ ክስረት ነው።

ለዛውም የኢትዮጵያ ህልም ፍቅር ሰላም ምኞት ቢሆንም ግን አያያዛቸው እንደ ኮነሬል ጎሹ ያሉ ጠበብቶችን በቅርብ ይዞ መሆን ይገባው ነበር። አሁንም ቢዘገይም አንድ መላ ቢሰጠው መልካም ነው። እውነት ለመናገር ልቁ ግንኙነት እንዴት ሰብሰብ ማለት እንደሚችል አንድዬ ይወቀው። 

ዓለም ፕሬዚዳንት ፑቲንን ማንበርክከ አልቻለም። አቶ ኢሳያስ አፈወርቂም አፍሪካዊ ፑቲን ናቸው። ዶር ለማ መገርሳም አፍሪካዊ ፑቲን ናቸው። የሁለቱ ድርድር ቁጭቱ ደግሞ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን የማዳን ወይንም የማጣት ጉዳይ ነው። ኦዴፓ ኦሮምያ ኦሮምያ ከሚል ታላቋን አገር እንዳያሳጣን ሊተጋበት ይገባል። ኦዴፓ አስኳል ጉዳይን የቤት ሥራውን ለማን እንደሰጠው አያታወቅም። ኤርትራ ጋር ዘው ብሎ ተግብቶ ዘው ተብሎ እንደማይወጣ አስቀድሜ ቸክችኬዋለሁኝ።

ከአዲስ አበቤዎችን ሰጥ ከማስደረግ፤ በሙሉ ልብ እና በፍጹም ቅነንት ፍቅርን ያጠነዘለ እርምጃ ማግስት አሁን ደግሞ ለአውራው ፓርቲ ለኦዴፓ ከቀደመው በባሰ ሁኔ ቤንሻጉል እና ኦነግም ተመሳሳይ ፍጥጫ ላይ ናቸው። ቤንን እና ኦነግ ኤርትራ ላይ ኮሽታ አለሰሙም። ምን ሲገድ ባለቤት የሌላት አገር እያለችላቸው። 

ቤንሻንጉል እንዲነሳ ነበር የቤንሻንጉል ጉምዝ ባለስልጣኖችን በአደባባይ ጥቃት የተፈጸመባቸው። ይህም ለእኔ ከእትጌ ኤርትራ ውጪ ማሰብ አቃተኝ። እነኝህ ደግሞ ሁለቱም የዞግ ድርጅቶች ናቸው። በምኑ ይሆን የሚራኮቱት? 

ኤርትራ ላይ በሰላም ኑረው አሁን ምን ወረደ ያሰኛል? ደግሞ የሚገርመው ኦሮሞዎችም አብረው ተጠቂዎች መሆናቸው ነው። ጠ/ሚሩ ኦሮሞ ናቸው፤ መሪው አውራ ፓርቲም  የኦሮሞ ኦዴፓ ነው፤ ተቃዋሚያቸው ደግሞ የራሳቸው ወገን የሆነ ኦነግ ነው በማህል የኦሮሞ እና የአማራ እናት ታልቅስ ምን ሲገድ? ከ80 እስከ 100 ሺህ የሚገመቱ ወገኖች ሞቱን ሳይጨምር በላይ በጣለው ዶፍ ወንዙ ገደቡን ጥሶ ሰቆቃ ታቅፈው ባለቤት አልባዎቹ ይማቅቃሉ ዕንባን ሰንቀው። ማው ባለተራ? ቀጣዩ ደግሞ አፋር? 

ምክንያቱም ያን የመሰለ የ100 ቀናት ውጤት እና ስኬት፤ ያን የመሰለ የአፍሪካዊነት ግርማ ሞገስ እዬተናደ እንዲህድ ሆን ተብሎ ታቅዶ እዬተሰራበት ነው። ቀስ እያለም ኢትዮጵያዊው ተስፋ እዬሟሸሸ ነው። ሻማዋም ኑዛዜ ላይ ናት። የወንዝ ሙላትን ነው እኔ ዛሬ ጭብጤ ያደረኩት፤ ባለቅኔዎች ይፍቱት "ወንዝ እያሳሳቀ እንደሚባለው" እዬሆን ነው … ቃል መታጠፍ በሁሉም ዘርፍ።

እንባን አይተህ ተስፋን ማቀድ ያቅታል ይፈትናል፤ ሰላም ናፍቀህ የታቀደ ሴራን ስታዳምጥ ራስህን ይሞግትሃል። የሚያሳዘነው በዘመነ ኦዴፓ አውራውን ሃቅ ለመድፈር ፍራሃቱ ነው። እጅግ የሚገርመኝ ነገር ይህ ነው። ግን አላዝንም ቅኑ ደጋፊው ነኝ፤ አስከመጨረሻውም እዮባዊነትን ታጥቄ ግን እውነትን እዬተናገርኩኝ አዬዋለሁኝ እንዲህ እያገላበጥኩኝ። ውስጡንም ሲሰኘኝ ጎርጎር እያደረኩኝ።፡

ሌላው ኦዴፓ በዚህ ቀውስ ውስጥ ቀድሞ የገባውን ቃል ለቄሮ ለማስፈጸም ብቻ ሳይሆን የቄሮን ጀግንነት ለማስቀጠል ገዳይነቱንም ደፍሮ ለፍርድ ለማቅረብ አለመቻሉ ትልቁ ሆገብ የተቀባይነት የቅቡልነት ተስፋውን ያጫጫው አመክንዮ ነው። ቄራዎቾ እራሳቸው እነሱንም ቢሆን ምን እንዲህ ከህዝብ ፍቅር ሊያወጣቸው ምን አታጋላቸው የሚለው በራሱ ሌላ መጽሐፍ ነው። ጀግንነትን ማዝለቅ ስለምን ፈሩት? ምነው እንደ አብዲሳ ቢሆኑ? 

ለዚህም ነው እኔ አማራ ክልል ተጨማሪ ቋንቋ ማጥናት አለበት፤ ለ አማራ ሆነ ግዕዝን ለፈቀደ የሚስጢራቱን እጬጌ ግዕዝን ማጥናት አለበት የሚል አዲስ ሙግት ይዤ የመጣሁት። ተስፋዬን እያሳሳው ያለው ራሱ ኦዴፓ ነው። ፍቅሬን እንዳላጣው ብታገለውም ግን ማግስትን ሳስበው መሮ ከስሎ ይታዬኛል። እናም ቆርጦ ከእውነት ጎን መቆም ግድ ማለቱን አምንበታለሁኝ። እንደ ትናንቱ ዛሬም። 
  • ·       ውነት ቢደፈር።

ግን ዕውን እትዬ ኤርትራ ኢትዮጵያ ብቁ መሬ ኖሯት ያ መሪም ከዕድሜ ጠገቡ አዛውንት ፖለቲከኛ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በላይ ልቆ እና ደምቆ የአፍሪካ መሪ እንዲሆን ፈቃድ ይሰጠዋልን? እኔ እሰጣ ገባውን ሁሉ ከኤርትራ ውጭ ለማሰብ አልችል አልኩኝ።
አሁንስ የኤርትራ መንግስት በጀት፤ የሎጅስቲክስ ድጋፍ ሲሰጥ የነበረውን መስክ  በኤርትራ በኩል ቁሟል ወይ? ትርፍ እኮ በዚህም ነው የሚለካው። ታጎርሳለህ በጉርስከው ልክ ትሰጣለህ። ለማወኩ ለብጥበጣው በጀቱ ድጎማው መዋል ካልቻለ ይቆምም ነበር። ይህም ያልተደፈረ አምክንዮ ነው። 

እትጌ ኤርትራ ትጥቅ ማስፈታቱ ለዓለሙ ማህበረሰብ እና ለዴፕሎማሲያዊ ትርፍ ሆኖ ግን አሁንም ሰላሟ የታወከችን ኢትዮጵያ የማዬት ህልመኝነቷ ቀደም ባለው ጊዜ ስንሞግት የነበረበት ጉዳይ አገረሸን ያሰኛል?

ምክንያቱም ስምምነቱ ለራሷ ለኤርትራ ነፍስም ለፈገግታዋም መልካም መሆኑን አይተን ወህ ባልንበት ማግስት የምናዬው መራራ ሆነ። ቆስቋሹ ማነው። ማገዶ አቅራቢው ማነው?እትጌ ኤርትራ እኛም እንኳንም መጣሽልን ብለናል። አቀባበሉም ከውስጥ የበቀለ ፍጹም እውነተኛ እና ቅን ነበር በሁለቱም ህዝቦች በኩል። በፕሬዚዳንት ኢሳያስ ልቦናስ ምን አለ? ሁለቱ አገሮች በቀጣይነት ወደ ሃሳብ አንድነት ለመምጣት ምን ቅደመ ሁኔታ እንዲያሟላ ተፈልጎ ይሆን? ብቻ ልቅ የሆኑ በር አልባ የሆኑ አመክንዮዎች በህሊናዬ ይፋተጋሉ።  

ሌላው የአሁኑ የራያ እና የትግራይ ጉዳይም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። በዚህ ዙሪያ የትግራይም ልጆች የአማራም ልጆች እዛው ድርጅታቸውን አቋቁመው ነበር። ቲፒዴኤምን በሚመለከት እዚህ ሲዊዘርላንድ የሚኖሩት ውዶቼ እንደ ነገሩኝ ከሆነ የኤርትራ መንግሥት ልዩ ጠባቂ እና ተንከባካቢም እንደሆኑ ነው አበክረው የገለጹልኝ። መዋለዱም ዝምንድናውንም አክለው በአርምሞ ነግረውኛል። ወደ አገር ሆሎችም ሲገቡስ ያን መንፈስ የት ሊጎልትቱት ይሆን ያሰኛል?

ሰሞኑን በከፊል ከኤርትራ የትግራይ ልጆች ገብተዋል። ከሚነገረው ግዙፍ የሠራዊት ቁጥር አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም እጅግ ጥቂት ነው። የአማራው ግን ጠቅልሎ ገብቷል። ኤርትራ የመሸገው ቀሪው የአቶ ሞላ አስገዶም ጦር ትጥቅ ስለመፍታቱም አይታወቅም የእሱም ሁኔታ ሌላው ራስ ምታት ነው። ድራማውም ጥልቅ ነው ውቅያኖስ። 

በሌላ በኩል በወልቃይት እና በጠገዴ እንዲሁም በራያም ቀውሱ ቀጥሏል። የትግራይ ሹማምንት፤ የአማራም ሹማምንት ተግ ብለው ሁኔታውን ማጥናት ያለባቸው ይመስለኛል። ከሁሉ የሚልቀው የአገር ሉዕላዊነት ጉዳይ ስለሆነ። ትንሽ አገር ስለሚባለው ህሊና ሊኖራቸው ይገባል። ከላይ የሚዘነበውን ዶፍ ወንዙን ሞልቶ መሻገሪያ እንዳያሳጣ ወደ አባቶቻችን የብልህነት፤ የጥበብ፤ ፍጹም የሆነ የሰክነት ሌጋሲ ምልሰት ማደረግ ይገባ ይመሰልኛል።

ኢትዮጵያ ለሁለቱም ታስፈልጋቸዋል። በመሃል ያሉ ያልጠሩ ባዕዳዊ ስሜቶች እንዳ አሉ ከልባቸው ሆነው ሊያዳምጡት ይገባል። ወያኔ ሃርነት ትግራይ እንደ ቀደመው ሁሉንም አስደገድጋለሁ አሁን ማለት አይችልም። አዴፓም እንደ ቀደመው ተኝቶ በለኝ የሚልበት ሁኔታ አሁን የለም። ሁለቱም ታጠቂ አላቸው። ሁለቱም ከኤርትራ የገቡ የታጣቂ ተጨማሪ ተፎካካሪ ድርጅቶች አሏቸው። የትግራይ በከፊል ነው የገባው ስምምነቱም ምን እንደሆን  ከእትጌ ኤርትራ ጋር አይታወቅም። አንድ ነገር ቢፈጠር ግን ዝግጁ ነው። 

የአማራው መንግሥት ደግሞ የጎንዮሽ ግንኙነት ከኤርትራ መንግሥት ጋር እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል። ይህ የላይ ዶፍ ወንዝ ሙላት ደራሽ የሆነ ከበላይ የዘነበ መከራ ያዘለ ጎማማ ጉመ ነክ ወጮፎ ይመስላል። ውዶቼ በስክነት ሆናችሁ ነገር ዓለሙን መርምሩት።
  
ልብ ቢኖራቸው ሁለቱም የመቀሌውም የባህርዳሩም ሊሂቃን እከሌ ተከሌ ሳይባል ትውልዱን ማሰብ ይኖርባቸዋል። ይህን የመከራ ጭጎጎታም ዘመን ተረዳድቶ፤ ተፋቅሮም ተዛዝኖ ተከባብሮም ማለፍ ከቻልን እድለኞች ነን።

ሁሉም እሳት ያምረዋል፤ ሁሉም ግጭት ሽው ይለዋል። ስክነት ብሎ ነገር የለም። አደብ ብሎ ነገር የለም። ችግሮችን በጭልፋ እንጂ ከልብ ሆኖ ለማዳመጥ ፈቃድ የለም። በስክነት ነገሮችን እንዳናይ የሚያደርገን፤ በበሰለ ሁኔታ አሽተን አጣርተን ሁኔታዎችን እንዳንመረምር የሚያደርገን ደግሞ ከልክ ያለፈው የአገር ውስጥ ሰበር ዜና ወጀብ ወይንም ሞገድ ነው።
  • ·       ርትራ እና ትውልዷ።

ከውስጤ እያዘንኩ ኤርትራ አዲስ ቡቃያ ትውልድ ፈልሶባታል ማለት ይቻላል። ይህን በአቀባበል ጊዜ ሳይ እጅግ አድርጌ ነው ከህሊናዬ ጥምንም ያልኩበት ጉዳይ ነው። ወጣት ወንዶቹ የሉም። ወጣቶች በጭራሽ የሉም። ካቢኔውንም አዬሁት። በእድሜ የገፉ ናቸው። ደስታቸውም ፍሰሃቸውም ቀዝቃዛ ነው። የበረደው።

 ኢትዮጵያ ደግሞ እስከንደነግጥ ድረስ የታዳጊ ወጣቶች አገር እዬሆነች ነው። ዘጋቢ ሪፓርተሮች የከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እጅግ ወጣቶች ናቸው። ከ20 እሰከ 30 ዓመት የሚገመቱ። ይህን እኔ ውጪ አገርም አይቼም አላውቅም። ዓለም ራሱ ጥናት ሊአደርገበት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል። ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የማዬውም ይህን ነው። ይህ ለእትጌ ኤርትራ ይመቻል ወይ፤ ምቾት ይሰጣል ወይ ሌላው ሞጋች ጉዳይ ነው። የተከደነ ኮሶ። 

ሌላው ቀርቶ እትጌ ኤርትራ ጠ/ሚር አብይ አህመድን ስትቀበል አብዛኞቹ ሴቶች አንስቶች ነበሩ። ሌሎችን ጥቂት ህጻናት እና ሴት ወጣቶች ነበሩ። ለጋብቻ ራሱ ፈተና ነው። ጋብቻ አልባ ትውልድ ለማስቀጠልም እንዲሁም የፈተና ሌሊት ነው። ስለዚህ ይህን ለማመጣጠንም ሌላም ተልዕኮ ይኖራል ብሎ ማሰብም ልባምነት ነው።

ኤርትራ ላይ ለላተቋረጡ ዓመታት የተካሄዱ ጦርነት አልበቃ ብሎ ሰፊ የሆነ ወጣት ስደተኛ አገር ናት። ራሱ አየሩ አሁንም የጦርነት አውድማነት ነው። እና እናማ ወጣት ሴቶች ትዳር በማግኘት እና ከዛ ቀጥሎ ዘር በመተካትም ሰፊ ችግር አይቻለሁኝ ኤርትራ ላይ። ስለዚህ ይህም ሌለው የስደተኛ ፍሰትን ቁጥር ኢትዮጵያ ላይ በስፋት ይጨመራል፤ ሌላ አዲስ ዴሞግራፊም ኢትዮጵያ ላይም ይፈጠራል። እነሱ ደግሞ በተለይ አንስቶች ፍጹም የሆኑ ልባሞች ናቸው። ፌያሜታን ማንበብ ነው። ደርግ ለዘር ሳይተርፍ የፈለሰበት አመክንዮም ይሕው ነው። ይህን ችግር ለማካካስ የአሁኖቹ ግጭቶች እና ቀውሶች በጥልቀት ስሄድበት ወደ ሸጎርጓራ ጥምዝምዝ አመክንዮ ወሰደኝ።

ግን ኢትዬ ኤርትራ አሁን በኢትዮጵያ ፓለቲካ ላይ ምን ሁኔታ ላይ ነው ያለችው? ዘለግ አድርጌ ስጠያይቅ ከርሜያለሁኝ። ከሰላም በላይ መልካም ነገር ባይኖርም ግን ሰላሙ ቀውስ ሰናቂ እንዳይሆን በሆነው ላይ ሳይሆን ወደፊት በሚታዩ ግራጫ አዬሮች ላይ የኦዴፓ ሊቃውንታት ባሊህ ቢሉት መልካም ነው። „በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ“ የሆነ ዓይነት የሚመስሉ ጉዳዮች አሉበት።

ምክንያቱም መለዬት ምን ያህል ስለመሆኑ እኔ እራሴ በማላውቀው ስሜት ሆኜ ነበር የኤርትራን እና የኢትዮጵያን ግንኙነት በፍጹም ሐሴት እና ሲቃ የተቀበልኩት። አሁንም ያ ፍቅራዊነት ስሜቴ ሙሉ ነው። ነገር ግን የግራ ፖለቲካ እና ሴራ ደግሞ ቃልኪዳነኛ ናቸው። ቅን የሆነ እራሱን ያሸነፈ ሊሂቅ ለማግኘት ይከብዳል። ዝርግ!

ፖለቲካ እና ፍቅራዊነት፤ ፖለቲካ እና አደራ፤ ፖለቲካ እና ታማኝነት፤ ፖለቲካ እና ሃቀኝነት፤ ፖለቲካ እና ከራስ በላይ ለሌላው ለመሰዋት መፍቀድን አገናኝቶ ለመራመድ የአፈጣጠራቸው ባህሪ ብዙም አያስኬዱም። አሁን እኔ ስጋቴ በእጅጉ ጨምሯል።
ዕውን ኤርትራ የኢትዮጵያ ሐሤት ያስደስታትል ወይ? ዕውን ኤርትራ ብቁ ክህሎቱ ሙሉ፤ ብዙ የመንፈስ ሃብታት ያለው ወጣት መሪ  ለኢትዮጵያ ትመኛለች ወይ ነውስ ሌላ እሷ የምትዘወረው ቧንቧ ያሰኛት ይሆን? የልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። ድንብልብል! 

እትጌ ኤርትራ ትጥቅ ብታስፈታም የመንፈሱን ፈንጅ ሳታስፈታ ነው የለቀቀችው። ቢያንስ ኤርትራ ላይ ለሠራዊቱ የተገባው ኮርስ ሊሰጥ ይገባ ነበር። ለረጅም ጊዜ በመንፈስ ያደራጀቸውን ሃይል የለቀቀቻቸው በግብር ይውጣ ስሜት ነው ብዬ ነው እያሰብኩ ያለሁት። የዘበጠ!

በታማኝነት ውስጥ የበቀለ መታመን ስለነበረም ፍጥነቱ እና የስኬት ፍጆታው ውህደታቸው አፍታ አልቆዩም። ጦሱ ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ ተርፏል። አዲስ እና አብረው ቅዱስ የሖንስን ለማሰለፍ በታለመበት ወቅት ነበር ፈንጁ የፈንዳው እዛው ከመዲናው ታፋ ላይ። ዛለ አንበሳ ፈንድሻ ቡራዩ ላይ ዋይታ። የራሄል ዕንባ …

ቡራዩ ለአዲስ አባባ ታፋ ነው። የእነ አቶ ጃዋር አህመድን የመታበይ አቅም ለተመለከተ እና የሐምሌው ዝምታ የቡና ፖለቲካ ሲታሰብ መረቡ ሁለገብ ሆኖ ይታያል። ሙልሙል ፈተና!

እና እናማ እትጌ ኤርትራም ረጅሙን እጇን ሰብሰብ ብታደርግ ለታይታ፤ ሌላ ቧንቧ አላት። በተዘዋዋሪ በአረብ አገሮች ያላትንም ተጽዕኖ ብታስታግሰው መልካም ነው ስምምነቱ የልብ ከሆነ። ኪዳኑም የእውነት ከሆነ። 

ኢትዮጵያም ልብ ቢሰጣት እና ፍቅሩን በልክ ብትይዘው መልካም ነው። የችግሮቿን ምንጭ ፊልስጤም ላይ አሽቀንጥራ እና ተሸቀንጥራ ከምትቆልል መዳፋ ላይ ቢያንስ ሊኖር ይችላል ብላ ትሰብ። ቢያንስ ይህም አለ፤ ሊኖር ይችላል ብላ ትገምት?

ሆድ ዕቃህን ዘርገፍህ መሸፈኛ መፈለግ ቢከብድም፤ ተጨማሪ ልብ ከማስገባት መታቀብ ግን ብልህነት ይመስለኛል። በዚህ ተጠያቂው ኦዴፓ ነው። ኦዴፓ ቅይጥ ችግሮችን በዓይነት እያስተናገደ ነው በዘመኑ። ኢትዮጵያንም ካለእርዕሰ መዲና ፈቅዶ በመንፈስ እንድትራቆት አያሰላ ነው። ይህንንም እያዬን ነው። ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አፍሪካንም ካለመዲና ለማስቀረት እዬተሰራበት ነው። ቀውሱ ከቀጠለ የአፍሪካ ህብረቱ ወደ ሰላማዊ አገር ሊሄድ ይችላል። ለነገሩ አቶ ተስፋዬ ገብሬ ምን ሥራ ሲኖረው?

ከእርቅ በፊት የኤርትራ መንግሥት ሲፎክር የነበረባቸው ሁነቶች እንደ ደራሽ ሙላት መከራው መላ ኢትዮጵያን እያጥለቀለቃት ነው። የቀረው አፋር ብቻ ነው። አፋርም በቀጠሮ ነው። ጋንቤላ የደቡብ ሱዳን መርግ መከራ ደግሞ አለ። እና እናማ ይህ ቀውስ አገራዊ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብዬም ስጽፍ እንደባጀሁት የውጭ እጅ እንዳለበት ይሰማኛል። ችግሩም ተሻጋሪ ነው። ኢትዮጵያ ሱማሌን እታደጋለሁ ያለችበት ዘመን ማክተሚያ ላይ ያለች ይመስላል? ሁሉ ቦታ መከላከያ ይምጣልን ነው ጥሪው። የራሷ ሲያርባት ከሆነ ደግሞ ሁሉም መካራ መክደኛ አልባ ቀጣይ ነው።፡

የሆ ሆኖ ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። የለማ ካቢኔ ወይ ኢትዮጵያን ማዳን ወይ ደግሞ ኢትዮጵያን መበተን አደጋ ውስጥ እንዳለ ይሰማኛል። የተዘጋን በር ከፍቶ ለዛም ስልት እና ሰፊ መዋቅራዊ መሰናዶ ሳያዘጋጅ በገፍ መከራን እያስተናገደ ይገኛል።  

ከኤርትራ የሚመጡ የስደተኞች ቁጥር በአራት እጥፍ አድጓል፤ በህጋዊ የመጡትም መመለስ አይፈልጉም። ብዙዎቹ እዛ ለመኖር መወሰናቸውን እዬሰማን ነው። ከዛ ውስጥ ንጹሃኑ ምን ያህል ናቸው በስለላ መስክ ያልተሰማሩ ሌላው ወጣ ገባ ጉዳይ ነው። ጋንቤላ ላይም ከደቡብ ሱዳን የሚገቡት ከነዋሪው በላይ ናቸው ከስደተኞች ውስጥ በስለላ ተግባር ያልተሰማራውን ለመለዬት ምን ያህል አቅም እንዳለው የለማ ሌጋሲ አላውቅም።

እዚህ እንኳን ተሰደው ኤርትራና ኢትዮጵያ ጦርነት ቢገጥሙ እንሄዳለን የሚሉ ገጥመውኛል። ለእኔም ለቤተሰቤም ቅርቦቻችን ኤርትራውያን ናቸው፤ ክፍሎቻችንም ናቸው። በጭራሽ ተተናኩለውኝም ሰላሜንም ነስተውኝ አያውቁም። ከፍቅር፤ ከትህትና፤  ከአክብሮት በስተቀር። እንዲያውም ሥም ሁሉ አውጥቼ ነው የምጠራቸው። ነገር ግን ብሄራዊ ስሜታቸው ፍጹም ልዩ ነው። የጽዮናዊነት ያህል ነው።

የእኞቹ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ሰዎች ደግሞ ወገናቸውን ማሰደድ ብቻ ሳይሆን አገራቸውን በቀውስ ሲያተራምሱ ይገኛሉ። አሁን  ከአማራ ክልል ጋር የሚያደርጉትን እሰጣ ገባ ተግ አድርገው ስለ ማግስት የትውልዱን እጣ ፈንታ ማሰብ፤ በመላ ኢትዮጵያ የተበተነው የተጋሩ ቤተሰብ ማሰብ ተስኗቸው ከራሳቸው ወገናቸው ጋር ጦር ይሰብቃሉ። እንደ አቶ ዳውድ ኢብሳ ዓይነቶችም በዚህው ሰርክል ውስጥ ናቸው። ለነገሩ ኢትዮጵያ እኮ የጠላት አገር ናት - ለግራ ቀኙ። 

የሚገዛው አገር ሲኖር ህዝብ ሲኖር ነው። አሁን ግን የሚታዬው እጅግ የከፋ ሲሆን የቀውሱን ሁኔታ ልብ ገዝቶ፤ አደብ ገዝቶ፤ ቀልብ ገዝቶ መቀመጫ መሬትን ማደላደል ሲገባ ለፍርሻ ለንድት ትጥቅ አቅራቢ መሆን አለመታደል ነው። 

ኦዴፓ እራሱ ከሥልጣን ማግስት የአማራ ጥያቄዎችን በመግፋት እና ትኩረት በመንሳት ሰፊ ድጋፉን አራቁቶታል፤ ይህም ሆን ተብሎ የተሴራ ነው። የራስ ተሰማ ናደው ሌጋሲ ምን ይሥራ? ለኦዴፓ የኢትዮጵያዊነት ጥንካሬ ቢጠቅመው እንጂ የሚጎዳው አልነበረም። በዛ ላይ ከፎቶ ፍሬም ያለፈ የተግባር አህዱ አይታይም በራሱ በኦዴፓ።

አብሶ አማራን በመንፈስ የማግለሉ፤ ለጥያቄዎቹ ትኩረት አለመሰጠቱ ምክሩም መልካም አልነበረም። አሁን አይታይም፤ ነገረ ግን ይታያል። ትዕግስት ሲያልቅ ፍቅር እንደሚሰደድ። ለ ኦዴፓ አዴፓ ላይ ብቻ ሳይሆን አማራ ህዝብ ላይ ነው ባለው ያለው። ግን አላወቀበትም ብቻ ሳይሆን  ያላወቃ መስሎ የቤት ሥራውን በጫና እና በሊጋባዎቹ ለማስፈጸም ሲተጋ መንፈስ እንዳይሾልከው ቢያሰብበት መልክም ነው። የ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ካለቀ በሆወላ ነው የሚስተውለው። ብቻ "ሞኝ ካመረረ በግ ከበረረ" እንዳይሆን በዚህም ዙሪያ ስጋቴ ልክ የለውም።

በሌላ በኩል ደግሞ የአማራ ክልል እና የኤርትራ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት የግብጦ ፍልፍቅልቅ እና ቅብጥ እና ቅልጥ የሙሽርነት ጉዳይም ከሉዑላዊነት አንጻር ለእኔ ያልተመቸኝ በእጅጉ የቀፈፈኝም አመክንዮ ነበር። ለዛውም  ከጠጣሩ ፓለቲከኛ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር? የምጡ ዓይነት የለውም? የህመሙም ፈወስ የለውም።

ኦዴፓ እራሱ በአገኘው አጋጣሚ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ የኦነግን መንፈስ ጫና በመፍጠር ለማስፈጸም ይህን ያህል ፋታ ከማጣት አገር እዬፈረሰች ስለሆነ በዛ ላይ ቢሰራ መልካም ነው። መሰረት የሌለው ቤት ይናዳል። አይቆምም። 

አሁን አዲስ አባባ የኦሮሞ ቋንቋን አስገድዶ የማሰጠት፤ የራስን ሹም አምጥቶ የመጫን፤ ተፎካካሪዎችን በስልት የማስወገድ፤ በዬቦታው የራሱን ሹማምንት ቦታ የመስጠት፤ ንጹሃን አስፓልት ላይ መረሸን፤ በገፍ ማሰር ይህ ሁሉ የበቀል ሂደት ከፈለገው ነገ ይችላል። ኢትዮጵያ የምትባል አገር ስትኖር። 

አሁን ግን በጥቅል በጥቅሉ በቦንዳ በቦንዳ የኮሶ የመርዶ፤ እንቆቋዊ የመፍረስ አደጋ ኢትዮጵያ ገጥሟታል። በዛ ላይ መስራት እና የሃይል አሰላለፉን መልክ ማስያዝ ያስፈልግ ነበር። ራሱ የሃይል አሰላለፉ ተላዋዋጭነቱ የገባው አይመስልም ኦዴፓ። 

ለዚህም ነበር እኔ ብልሁን ሊቀ ሊቃውንት ኮ/ጎሹ ወልዴ የጠ/ሚር አብይ / ዶር ለማ መገርሳ አማካሪ እንዲሆኑ እምሻው። ዶር አብይ አህመድም ሆኖ ዶር ለማ መገርሳ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተመክሮ በላይ ሄደው ቀውሶችን ሃንድል ማድረግ አልቻሉም። አልቀደሙም። ይልቁኑስ ተቀድመዋል። ፍላጎታቸው ሙት መሬት ላይ ነው ያለው። አንዲት ቀለሃ ስው አታጠፋም በተባለ ማግስት? ህም!

ኦዴፓ እዛው ጉልቻቸው ላይ ሲንደፋደፍ ቀውሱ አገር ምድሩን አካልሏል። ወያኔ ሃርነት ትግራይ አገር ሊገዛ እዬገሰገሰ መንበሩንም ጨብጦ ግን ስስቱ አላስቀምጥ አላስቆም ብሎት ወሎ፤ ጎንደር አሁን ደግሞ ከጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ እንዳደመጥኩት ከከፋ እዬነቀለ ሃብት ወሰደ። እንዲህ ዲታ ሆኖ አሁንም ዘረፋ ላይ ነው። ወያኔ ሃርነት ትግራይ የቁስ ነው። የኦዴፓ ደግሞ ረቂቅ ነው። የመንፈስ ልዕልና፤ ልቅና ላይ ነው እዬሰራ ያለው። አቅም አለን የማለት። አቅሙን ማስቀጠል የማያስችሉ ባይረሶችን ማስወገድ ካልተቻለው ልፋቱ የውርንጫ ድካም ይሆናል፤ ታጥቦ ጭቃ ...  

ነገ ህዝብ በቃኝ ብሎ አያድርገው እና መድፍ እዬረገጠ አብይ ይውረድ ቢል ተጠቃሚው ማን እንደሆን ማስላት ይኖርበታል ኦዴፓ። አቅጣጫም ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም። አይሆንም ማለት አይችልም። እትጌ ኤርትራ መሪዋ እኮ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸው። 

ኦዴፓ ከሥሩ እዬተነቀነቀ ነው። ባልቦላው የት ላይ ስለመሆኑ ልብ ያለው አይመስለም፤ ኦዴፓ አብይን ከመደገፍ ይልቁንም መንፈሱን ለሌላ ያወረሰበትን ዘመናይነትንም ተመልከተናል። ዓርማውን ማስከበር እንኳን አልቻለም። 

እንደ ደህንነት ሰው ችግሮችን በዬዘርፉ እና በጅረታቸው ልክ በጥበብ መያዝ ቢገባም ግን ከመሰረቱ ማፈንገጥ በፍጹም አይበጀውም። ስለሆነም ኦዴፓ ከህልመኝነት ትርምስ ወጥቶ በምክንያታዊ ችግሮች ላይ የሰከነ መነፍትሄ ማመንጨት ይኖርበታል። 

ለዚህ ደግሞ መድህኑ ኮ/ ጎሹ ወልዴ ብቻ ናቸው። ፈቃጆቹ ከፈቀዱለት ለአብይ ካቢኔ። ሌላው ከሀምሌው ዝምታ ጋር ንክኪ የለንም ስለተባለ ችግሩ ላይ መስማማት አልተቻለም። ችግሩ ላይ መስማት ከላተቻል መፍትሄን በወል መፈለግ አይቻልም። ሌላ ሃይል አለ … „አክ ወሬ¡“ አይደለም።

  • ·       ልቁንስ የተደራጀ ተግባር ለመከወን ኦዴፓ በፍጥነት ፈቃዳቸው ተጠይቆ ከፈቀዱ ኮ/ጎሹ ወልዴ ዕድሜም የራሱ የሆነ ስጦታ አለው፤ በዛ ላይ ሁሉም ያላቸው ቅን ሊሂቅም ናቸው እና እሳቸው ብቻ ይህን መጠራቅቅ ሊያሻግሩ ስለሚችሉ በዚህ ጉዳይ ከውሳኔ ቢደረስ መልካም ነው። መብሰል ማለት እንደዚህ ዓይነት ደፋር እርምጃዎችን መወሰድ ነው። ለዚህ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ብቁ ቢሆንም እኔ እንደ ሥርጉተ ከስሜን አሜሪካ መልስ በሙሉ አቅማቸው፤ በሙሉ መክሊታቸው እንዳይንቀሳቀሱ የኢጎ ፈረሰኞች አስረዋቸዋል ባይ ነኝ። 


ወደ ቀደመው ምልስት ሲሆን ኮነሬሉ ሁሉንም አስማምተው ሁሉንም በቅንነት አይተው በልክ በአቀም ልክ ኢትዮጵያ ትራመድ ዘንድ ቁልፍ ሰው ናቸው። አሁንም አልመሸም ይህን ወደ ተግባር ማሻገር ግድ ይላል። 

ለእኔ ያለጥርጥር የአሉታዊ ቦንብ የታጠቀ መከራ ነው ኢትዮጵያን እያመሳት ያለው። እትጌ ኤርትራም ራሷ ብትሆን በታሪክ በዘመኗ ለሻብያ የ ኢትዮጵያ ህዝብ ልባዊ ትህትናዊ - አክብሮት ሲሰጠው አሁን መሆኑን በማስተዋል ልትመረመረው ይገባል። „የቆጡን አውርድ ብላ የብብቷን“ እንዳይሆን …  መጪው መካራ ሁላችንም አናውቀውም። ኤርትራም ዕድሉ ሊያመልጣት ይችላል ... አቅጣጫ የለሽ ሞገድ ተፈጥሮ ሁሉም አብሮ ከሚሰምጥ። በመጨረሻ ለማህበረ ተጋሩ ልብ ይስጣቸው ባይ ነኝ። 

ለመሆኑ ምን ያህል ተጋሩ ነው ከትግራይ ውጪ የሚኖረው? ለስንቱስ ጥበቃ ሊያቆሙ ይችላሉ ህውሃቶች? ቢፈልጉስ ይችላሉ ወይ አሁን ህውሃቶች? ቄሮ ራሱ ንጉሥ ነው አሁን። ስለዚህ ገብቼ በዬቦታው ምርጥ ዜጋዎቼን አድናለሁ የኔዎቹን ነጥዬ ቢል ወያኔ አይመስለኝም?

ቁጭ ብለው የግንባሩ አመራር አካላት ከልባቸው ሆነው፤ ኢጓቸውን አስወግደው፤ መራኮታቸውን አቁመው፤ ፉክክራቸውን ለይደር ቀጥረው በስክነት በዘመናቸው ኢትዮጵያ የምትባል አገር እና ኢትዮጵያ የሚባል ህዝብ እንዳይከሰም ቆርጠው፤ ወስነው ሌት ተቀን ሊመትጋት ፊደል መቁጠር አለባቸው - በትህትና። 

ኢትዮጵያ የአብይ ብቻ አገር አይደለችም። የማዬው፤ የምታዘበው ነገር ግን ገብቶበታል ይወጣው ዓይነት ነው። የዝብሪት ቤት አገርን አያድንም። ህዝብን አይታደግም። ፍላጎትንም አያስገኝም። ጦርነት ህግም - ሥርዓትም - ሰባዕዊነትንም - መኖርንም - ነፍስንም አያውቀውም። ግዱም አይደለም። ጦርነት አመክንዮዎ መሃን ነው።

ጦርነት ቢገላገል ወይንም ቢወልድ በቀልን ብቻ ነው። በቀል ደግሞ ትወልድን በመንፈስ ማምከን ነው ተልዕኮው። ጦርነት የሞራልም አምካኝ ነው። ጦርነት ሃጢያትም፤ ወንጀልም ነው። ሰው መግደል የጽድቅ መንገድ አይደለም። እነ አቶ ዳውድ ኢብሳ የተከተሉት ይህን ነው። እስከመቼ ከሳጥን ጋር እስኪስማሙ ድረስ። በጀርባቸው ግን እትጌ ኤርትራ እንዳለች መቀበል ግድ ይላል። 

ወያኔ ሃርነት ትግራይም ወዮ የመጣሁ እንደሆን ፉከራም ይኸው ነው፤ በመድፍ ባይሆን እንኩሮውን ባሻኝ ሰዓት ደግሞ የኔ ነው ባይም የእትጌ ኤርትራ አዲስ ፓሊስ ይመስላል። „ነው“ አይደለም እያልኩ ያለሁት ይመስላል ነው። „አካሄዱን አይተው ሸክሙን ይቀሙታል“ እንዲሉ …

ብቻ መቼ ከ66ቱ የማሌ የግራ መከራ እንደሚገላገል ትውልዱ ይጨንቃል። የራሳቸውን ጊዜ አባክነው የዘመኑን ትውልድ ቀብረው አሁን ደግሞ የታዳጊ ወጣት አገር የሆነችውን የኢትዮጵያ ተስፋ ያምሱታል። ተቀራራቢ ዕድሜ ፈጽሞ የለም። በዛ ዕድሜ ውስጥ መኖር ባይቻል እንኳን ተቀራራቢ ካልተሆነ ጋዳ ነው ገድጋዳ። ይህ ሎጅክ ነው። እንዴት ክፍተቱ ሊሞላ ይችላል። ፈጽሞ እኮ እጅግ የተራራቀ ሁኔታ ነው እዬታዬ ያለው። 
  
ለነገሩ ትውልዱ እና አዛውንታት መሪዎች ሲተያዩ እንዴት ከልጅ ልጆቻቸው ጋር በፖለቲካ፤ በሃሳብ ልዕልና ተፎካክረው እንደሚያሸነፉም ግራ ነው። በቋንቋስ እንዴት ይገባቡ ይሆን ያሰኛል። በጣም ፈጣን ትውልድ ነው ኢትዮጵያ ያላት። ተፈቅዶላትም ነበር። ግን በጥባጭ ሳለ ሆነ ነገሩ ሁሉ ///

  • ·       ስከውነው እንደዛሬው ዕይታዬ።


ሁሉም ያጣውን እዮባዊነት ህሊናው ቢያደርገው መልካም ነው። ተፎካካሪ የሚባሉትም አደብ ይኑራቸው - በትህትና። ቀን እና ሌት አንድ ዓይነት ይሁኑ! በሰውነት ውስጥ ለመኖር ይወስኑ! በሚሉት ልክ ሆነው ይገኙ - በአክብሮት! 

ሥልጣን አላፊ ነው። አሁን ያለው ተጋድሎ አገር እና ህዝብን የማጣት ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ የቀደመ የሩቅም የውጭም የኢትዮጵያ ጠላቶች ህልም ነው። አሁን ክፍት በር ነው … ልቅ የሆነ ጉድ። ለዚህም ነው እኔ በህልሜ ወንበሩ ባዶ ሆኖ ያዬሁት።

ማገናዘቢያ መጋመድ ብቻውን አላደነንም። የ50 ዓመቱ መከራ ሊወጠን ታቃርቧል። ወገኖቼ ይህ እንግዲህ ከላይ ያነሳሁት የጭብጤ ልቦና ነው።  የእርስ በርሱ ግጭት አያሰጋኝ ም ነው ያሉበት የአቶ ያሬድ ጥቡቡ እና ያሰጋኛል ያሉት የፕሮፌስር ዳንኤል ተፈራ ሙግት ነው  በVOA ሜዳ። ተደግሞ ቢደመጥ ያስተምራል። በልቦና ቢያስቀምጡትም አይከብድም። ሌላው የእኔ የዛን ጊዜ ዕይታ ነው። 

 „ የአገር ጉዳይ:- ወደ የት እየሄድን ነው?ተወያዮቹ:-አቶ ያሬድ ጥበቡ እና ፕሮፌሰር ዳንኤል ተፈራ“
ህዳር 24, 2017
„መቋሚ /ከሥርጉተ ሥላሴ/“

ማስተዋል ከቀናው ብቻ የችግርን ሥረ መሰረት ማወቅ ይቻላል!
ችግር ከታወቀ አቅም ያለው መፍትሄም ማመንጨት ይቻላል።

ክብረቶቼ --- ጹሁፌን ስለፈቀዳችሁ ከውስጤ ባለው ድንግል ትህትና ምስጋናዬ ይድረሳችሁ - በትህትና ዘንክት ያለ ለዛውም።

ኑሩልኝ የኔዎቹ።

ማለፊያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።