አላዛሯ እምዬ ኢትዮጵያ እናቷንም አገኘች።
አላዛሯ ኢትዮጵያ
ራሷን አገኘች።
አላዛሯ ኢትዮጵያ
እናቷንም አገኘች።
አላዛሯ ኢትዮጵያ
ውስጧንም አገኘች!
„አድርገህልኛል እና ለዘላለም አመሰግንሃለሁ።“
መዝሙር ፶፩ ቁጥር ፱
ከሥርጉተ© ሥላሴ
26.10.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።
- · መቅድመ አንስት።
ኢትዮጵያ ዓለም ናት። ኢትዮጵያ መለያ ናት። ኢትዮጵያ ነባቢት ናት። ኢትዮጵያ ሥነ- ህይወት
ናት። ኢትዮጵያ አናባቢም ናት። ኢትዮጵያ ተነባቢም ናት።፡ኢትዮጵያ ሥህነ - ነፃነት ናት። ኢትዮጵያ ብጡለ -ክብር ናት። ኢትዮጵያ የመሆን እጬጌ ናት። ኢትዮጵያ ጥልቅ ናት።
ኢትዮጵያ የዕድማታ ቅኔ ማዕዶት ናት። ኢትዮጵያ ንጥር ትርጉም ናት። ኢትዮጵያ መነሻ መሠረት ናት።
ኢትዮጵያ ሉላዊ ህሊና ናት። ኢትዮጵያ ድርብ ግርማ ናት። ኢትዮጵያ ህላዊ ሞገስ ናት። ኢትዮጵያ ስመኝሽ ናት። ኢትዮጵያ ስናፍቅሽ ናት።
ኢትዮጵያ ተስፋ ናት። ኢትዮጵያ ተናፋቂ ፋና ናት። ኢትዮጵያ ትርጉም ናት። ኢትዮጵያ አዲስ አመት ናት።
አገር ሃይማኖት ነው። አገር አካል ነው። ኢትዮጵያም ሃይማኖትም አካልም ናት። ኢትዮጵያ ውስጥም
ናት። አዎን! ኢትዮጵያ ውስጧን እንሆ አገኘች። ውስጧን ብቻ ሳይሆን አላዛሯ ኢትዮጵያ እናቷን ጥበብ ሰጣት።
ለለበጣ ሳይሆን፤ ለፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን፤ ቀልብ ለማሳቢያ ሳይሆን፤ ለጊዜያዊ የሥልጣን ሹመት ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጧን ውስጥ ያደረገች እናቷን በእርግጥም አገኘች። ኢትዮጵያ የኖረ የተከመረ መከራ ቢኖርባትም፤ ችግሯ እፍ ተብሎ በአንድ ጊዜ
ባይተንም፤ ግን መተንፈሻ ቧንቧዋን አግኝታላች ብዬ አምናለሁኝ።
የራሄልን ዕንባ የሰማ አምላክ እንሆ አደማጣት እላለሁኝ። ኢትዮጵያ የሚለውን ሥሟን መቀበል ጋዳ
በሆነበት ዘመን፤ እንሆ አላዛሯ ኢትዮጵያ ብጡል ውጽፈተ- ወርቅን አገኘች። ብቁ ዋቢዋን አገኝች። ትንታግ ተቆርቋሪዋን አገኘች። ተመስገን!
አገር እንዲህ ለስኬት የበቃች፤ ጉልላት የሆነች፤ ልቅም - ክውን ያለች፤ ልጅ ኖራት። ያ ጉለበታም
አቅሟ ሳይባክን ከእነ ሙሉ አቅሙ እንዲህ ከፈለጋዊ ምህረት ጋር ሲገናኝ ታምር ነው። በክብርት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወረቅ ዘውዴ
ርዕሰ ብሄርነት፤ ርዕሰ መዲናነት፤ ርዕስ እኛዊነት፤ ርዕስ ትሩፋትነት፤ ርዕሰ ዐዕማዳዊነት ሐሴት አግኝቻለሁኝ - እኔ በግሌ።
እርምጃውም
ደፋር ማስተዋሉም ልዑቅ ነው እሳቸውን ለዚህ ቦታ ይመጥናሉ ብሎ ማጨት። አይን የተፈጠረበትን ተልዕኮ በብቃት አዬ የሚበላውን አመሳክሮልኛል። አመሳጥሮልኛል። አዲስ መጸሐፍ ተጻፈ።
መጸሐፉ ደግሞ በተደሞ - በህገ ልቦና ጸደቀ አስብሎ።
- · የሴቶች ፈተና ምኑ ቅጡ?
ሴትንት መልካም ቢሆንም፤ ተፈጥሯቸው ሁለ ነገራቸው ሳቢ እና ማራኪ ቢሆኑም፤ ሴቶች ጥብበ ቢሆኑም
ለራሳቸው ጉዳይ ግን እጅግ ሲባዛም ደካማ ናቸው። „ሴታዊነት“ መሆን መቻል ከባዱ ፈተና ነው። በሴታዊነት ውስጥ ብዙ ተወራራሽ ርቁቅ
ጸጋዎች፤ ምርቃቶች መክሊቶች አሉ። አንዱ ሴቶች ለእህቶቻቸው አቅም ዘብ መቆም ነበር። የብረት መዝጊያ መሆን። እኔ እማዬው ግን፤ እኔ
እምታዘበው ግን …
ሴቶች እራሳቸው ጠንካራ፤ አቅም ያላትን ሴት እህቶቻቸውን አጥብቀው ይታገሏቸዋል። ይፈሯቸዋልም። ሴቶች ራሳቸው
ብቁ ልቅና ያላቸውን ሴቶችን ፈተና ውስጥ አጥምደው ይጣላሉ። ከጉልበታም ወንዶች ጋር አብረው ተባብራው መሰናክል ይሠራሉ። ሴቶች ለሴቶች እኩልነት
ባላንጣ ሆነው ይቆማሉ። ስለዚህም የሴቶችን የክህሎት ቡቃያ ሥርዓቱ ከሚያደርሰው ጫና ባለነሰ እራሳቸው ሴቶች አቅም ያላቸውን ሴቶች
ታግለው የሚያመክኑበት ሁኔታ ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም።
ለሴቶች ብቃት ሴቶች መመስከር ቀርቶ፤ መናገር ቀርቶ፤ ዕውቅና መስጠት/ማጠትም ቀርቶ፤ ችሎታ ያላቸውን ባለመክሊት ሴቶችን አቅማቸውን ክትር
እዬሰሩ ማደናቀፉ ቢቀር ዕድለኛ በተሆነ ነበር።
በርቺ! አይዞሽ! ምን ልርዳሽ? ከጎንሽ ነኝ! የማይደፈር አመክንዮ ነው። እስከ አሁን በወንዶች
አለም በነበረው ፖለቲካ የደረሰው መበደል ድርብ መደረቢያ ራሳቸው ሴቶችም ነበሩ።
ሴቶች በአቅማቸው ልክ ዕውቅና ሲነፈጋቸው ወጥተው የሚሞግቱ ጠንካራ ሴቶች፤ ለእህቶቻቸው እራሳቸውን የገበሩ
ሴቶች ገጥሞኝ አያውቅም።
ሴቶችን ረድተው፤ አግዘው፤ አበራተው የሚታገሏቸውን ጉልበተኛ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሆነ የኢጎ አርበኞችን
ፊት ለፊት ሞግተው አጋልጠው፤ ለራሳቸው አቅም ዋስ ጠበቃ አክቲቢስት ሲሆኑ አይቼ አላውቅም - በፍጹም። ስለዚህ በወንዶች ፖለቲካ
ብቻ ሳይሆን ሴቶች ለሴቶች ያላቸው ቅናዊ ዕሳቤ ድርቀትም ጭምር ነው ኢትዮጵያ ለከፋ አደጋ ተጋልጣ የኖረችው።
ይህም ብቻ አይደለም ዘንቦ ተባርቆ ሴት ቦታ ስትይዝ በዘመድም ይሁን በብረት መዝጊያ ትዳር ይሁን
ወንድም ወይንም የዞግ አለቃ ኖሯት፤ ወይንም በራሷ ጥረት እና ብቃት ወፍ አውጥቷት በዛ በያዘችው ቦታ፤ በዛ ባገኘችው ዕድል እና
ዕውቅና አቅም ያላቸው ሴቶች፤ ባለቤት ያጡ ሴቶችን፤ አስታዋሽ የሌላቸው ሴቶችን፤ አድማጭ እንዲያገኙ ተግታ መስራት ሲጋባት፤ ለወንዶች
የፖለቲካ ዓለም ቀጣይነት ተግታ ትሰራለች።
ስለምን? ቢባል ዋናው እሷን የሚልቁ ሴቶች በቅለው - ጸድቀው አስብለው ማዬትን ስላማትሻ።
በዚህ
መሰል የጉድጓድ ጎድጓዳ የፖለቲካ ጉዞ የደቀቀው፤ ተሰብሮ የቀረው፤ አፍሮ የተንኮላሸው፤ጊዜው ባክኖ ያለፈበት የሴቶች አቅም ቤት ይቁጠረው። ስለዚህ
የሴቶች ፈተና የወንድ ፖለቲከኞች መቀናቀን ማዳፈን ብቻም ሳይሆን የሴቶችን አቅም አጀንዳቸው አለመሆን፤ የሴቶችን አቅም አብዝተው ወንዶች መፍራታቸው ብቻ ሳይሆን
ሴቷም እራሷ ለሴቶች እኩልነት ተጋድሎ ያልተፈጠረችም
ስለሆነች ጭምር ነው።
- · ምን ልበላው?
ባለፈው ጊዜ ልዕልት ጽዮን ግርማ ከመከላከያ ሚኒስተር ሚኒስተሯ ከወ/ሮ አንሻ መሐመድ ጋር ባደረገችው አክብሮታዊ ቃለ ምልልስ፤
ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሴቶችን በብዛት ካቢኔ ውስጥ ማስግባታቻቸው „ቀልብ“ ለማሳብ ነው የሚሉ አሉ የሚል ጥያቄ አቅርባ ነበር።
“ኢትዮጵያ ለሁሉም እኩል የሆነች አገር ናት”- ወ/ሮ አይሻ መሐመድ (የመከላከያ ሚኒስትር)
October 21, 2018
ጽዮን ግርማ/ጋዜጠኛ/
VOA
እኔ ደግሞ እንዲህ ልበላት … እስኪ ይሁንባችሁ፤ በመዳፋችሁ በሚገኘው፤ በምትችሉት፤ ቀልብ ለመሳብ የአሜሪካ ድምጽ የራዲዮ ፕሮግራም
በሴት ቃለ ምልልስ ተሳታፊዎች ጥልቅልቁን አውጡት
እና እንያችሁ። ሌላውም ሚዲያ እንዲሁ። ሌላውም ተፎካካሪ /ተቀናቃኛ/ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅትም እንዲሁ። የሲብል ድርጅቶችም
እንዲሁ።
ልዕልተይ ጽዮንሻ ጋዜጠኛ ይላሉ ተበላ ያማሉ ይተቻሉ የተለመደ ነው። አብዛኛውን ነገር ከራስ ለማራቅ ቢመስልም ሌላው ግን ውስጡ ለቄስ ነው። እኛ እምንፈልገውን አጠጋግተን መጠዬቅ የተለመደ ነው ልልሽ ነው። እኔው እራሴ ስላዬሁት። ማድነቅ የሚባል ነገር የለም። ያለው ምክንያት እና ሳቢያ መፈለግ እና መጣጣል ብቻ። ስንጥር መፈለግ ብቻ።
ዕድሜ ዘመን ሁሉ ተባዕት ነው ሲዳራደር የምናዬው። ሲሞገት የምናዬው ተባዕት ነው። እማናዬው ገብርዲና ከረባት ብቻ ነው። ድርቅ የመታው
ጉድ። በዚህን ያህል ዘመናቸው አቶ ሌንጮ ለታ እሳቸውን የምትተካ አንዲት ተማላ ሴት የላቸውም። አላፈሩም፤ አስበውትም አያውቁም።
ድርቅ። ዶር
አረጋይ በርሄ ቢሆኑ እንዲሁ። ድርቅ።
ዶር መራራ ጉዲናም ቢሆኑ እንዲሁ። ድርቅ። ፕ/ በዬነ ጵጥሮስ ቢሆኑም እንዲሁ። ድርቅ። ዶር
ነገደ ጎበዜ ቢሆኑም እንዲሁ፤ ድርቅ። አቶ መርሻ ዮውሴፍ ቢሆኑ እንዲሁ። ድርቅ። አቶ እያሱ አለማዬሁ ቢሆኑ እንዲሁ። ድርቅ። እስኪ
ቀለብ ለማስብም ያድርጉት እና እንያቸው። ይብጠልጠሉ /// ይታሙም። "ለቀልብም" ትዝ ተበሎ አያውቅም ደግሞም አይደፈሯትም። ራሱ ለኢተፖድህ ሁለተኛ ጉባኤ አንዲት ነፍስ ሴት አልነበረችምም። እጅግ በርካታ ድርጅቶች ነበሩ ጉባኤተኞች። ሴት የነጠፈበት፤ ሴት ወና የሆነበት። ይኸው የተኖረ ተኖረ ውጤት አልባ።
እንደ ሴቶች አቅም የሚፈራ የለም። ስለምን? ያውቋታል እንደሚገለበጡ። እንደሚበለጡም። ሞጥረው አይሰሩም እንሱ። ትንሽ ቀዳዳ ፈጥረው የነበሩትም ቢሆኑ ያዬነው አይተናል እኮ በዘመናችን።
አሁን ሰሞኑን አቶ ሌንጮ ለታ ሰው ልተካ ነው፤ እኔ ልለቅ ነው ብለዋል። እንኳን ለዚህ አበቃቸው። ተወዳዳሪ ወጣቶች
በዙ። ዶር ሌንጮ ባቲን ነው የሚያመጧቸው። በቃ። እዛው ዙር ተመለስ። ሲገላባበጡ እንደ አኩረባቲስት እነሱው በእንሱው ነው።
ሴት ደግሞ ዝም ብላ ሴት አይደለችም እንዲህ አፍን ሞልታ የምታናግር፤ የልብ የምታደርስ፤ አቅሟ የሰከነ፤ ክህሎቷ
ወደር የለሽ፤ ችሎታዋ ሉላዊ፤ ርጋታዋ ሥህን፤ ሰብዕናዋ ተፈጥሯዊ፤ ሁለመናዋ መረቅ የሆነች አንበሳ ሴት። በዚህ አሁን ኢህአዴግ
እዬበለጠ ነው። ቁንጮ ሆነ። ጉድ ሰራችሁ!
አብሶ የፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወረቅ ዘውዴ ሹመት ርዕሰ አምድ ነው።
ግርም ያለኝ እንግዲህ መከላከያ ሚኒስተሯ በዚህ እንዴት ሊወጡት ነው ይችሉታል ወይ ዝንባሌ
አዘል ቃለ ምልልስን አስተናገደ VOA ዛሬ ደግሞ ሌላ ቃለ ምልልስ አዳመጥኩኝ …. አዎንታዊ፤ ቅናዊ ተቆርቋሪያዊ ነው ...ግን ከቀደመው ጋር ሳያይዘው የት ላይ ይሆን የኛ ፍላጎት የሚለውን አጫረብኝ።
የአዲሷ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሥያሜ አንድምታ
October 26, 2018
አሉላ ከበደ – /አንጋፋ
ጋዜጠኛ/ VOA
ይህኛው ደግሞ የክብርት ፕሬዚዳንቷ ክህሎት፤ ተመክሮ
፤ ብቃት ዝቀሽ ስለሆነ እና ሹመቱ አይመጥንም ነው የዕድምታው ሙግት በትርጉም ሲቃና። ዕውቀታቸውን ሙሉውን እንቬስት ለማድረግ ሜዳው ጠባብ ነው አይነት
ነው ዕድምታው። አንሷቸዋል ይመስላል ዝንባሌው - እንደ መቆርቆር ዓይነት። ሌላው አይችለውም "ቀልብ" ለማሳብ ተብሎ ታማ ነው፤ ከሚችለው በላይ ነው፤ ሌላው ደግሞ የተሰጠው ቦታ ያንሳዋል … ከቶ እኛ ምኑ
ይሆን የሚያረካን?
የእኔ መልስ ደግሞ ይህም የተገኘው በዘመነ አብይ ነው። ስለሞኖራቸው፤ ስለብቃታቸው፤ ስለ ብልህነታቸው፤ ስለ ሁለገቡ
አቅማቸው ዕውቅና ማግኘቱ በራሱ ትልቅ የስኬት ልዕልና ነው። ሴቶች ለርዕሰ ብሄር ይመጥናሉ ብሎ ማሰቡ በራሱ ገድል ነው። እውነትም አይመስልም። ሌላ የፈጣሪ ጥበብም አለበት ምን አልባት ጸልዩበት ሚስጢር ሹክ ትባላላችሁ። ጥልቅ ነው። ዋስትና የመፍጠር ዕሴት ነው። እርሾውን አስተማማኝ የማድረግ። ለምነትነት በመሰናዶ። መሰናዶው እንዴት? ለመቼ? ሌላ ቀን ... ሌላው በዚህ ልክ የሚወጣው የታዳጊ ወጣት ሴቶች የመሪነት ፍላጎት ሥነ - ልቦናዊ አቅም እሸታዊ ፈልም ነው። አታስታውሱትም ጣይቱን ሙዚቃ ያ ይፈጸም ዘንድም ነው።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን እንዲህ
ዓይነት ሙሉዑ አንስት፤ አንዲት ዓይነት ሳንክ የሌለባት፤ እንዲህ ዓይነት የስክነት እምቤትን ፈልፍሎ ለዚህ ደረጃ ማወዳደር ራሱ
ታምር ነው። በዚህ ሹመት ውስጥ እናትነት፤ እህትነት፤ ሚስትነት፤ አክስትነት፤ አቀናጅነት፤ አማካሪነት፤ አስተዳዳሪነት፤
አደራጅነት፤ መምህርነት፤ ሐዋርያነት፤ ተመሳሌነት፤ በርካታ ማንነቶች ተቃቅፈው ተዋደው አሉ። መስኩ ሰፊ ነው።
ክብርት ፕሬዚዳንቷ ከሠሩበት ከሰላም በላይ ተፈላጊ የመተንፈሻ ቧንቧ የለም። ሴቶች ሰላሞች ናቸው።
መታጨቱ በራሱ በወንድ የፖለቲካ አለም ተግምዳ ተፈትላ ለኖረችው አላዛሯ ኢትዮጵያ ትልቅ የሥልጣኔ እምርታ ነው። መንፈሱ ራሱ ረቂቅ
ነው እሳቸው ከተሾሙ ጀምሮ በሥነ - ልቦናችን ያደረው እርካታ ያገኘነው አቅም አንቱ ነው።
ሌላው ባለቤት የሌለው፤ ያልተፈጠረለት፤
ቢፈጠረለትም ፋይዳው እዚህ ግባ የማይባል ሴቶችን ለትልልቅ ሃላፊነቶች አቅዶ የማብቃት ራሱን የቻለ ፕሮጅክት ሠርቶ የመከወን ጉዳይ አልተጀመረም።
ሴቶችን
በሚመለከት ህግ መንግሥቱ ተቆንጽላ የቀረበቸው ብቻ ሳይሆን ራሱን የቻለ ጉለበታም ድንጋጌም ይሻል። እንደ ኢባ ፔሩ የሰው ለውጥ መስራት። ጀግኒት ኢባ ፔሩ የሴቶችን አቅም እኩልነት
ያስከበረችው ህሊና ለውጣ ነው። አብዮት ነበር ያካሄደችው። ያ ደግሞ ከምንም የገዘፈ እና የሰፋ ነው። ዛሬ አርጀንቲና ውስጥ ማንም ወንድ ለዬትኛውም ቦታ ሲወዳደር
ሚስቱ/ እህቱ/ እናቱ ማን ናት ነው ዋንኛው ጥያቄ።
በነገራችን ላይ የዘንድሮ የኢትዮጵያ አዬር መንገድ የበረረ ጉዞ በሙሉ የሴቶች አቅም ላይ የተገነባ በሴት ፓይለቶች የተዋበም ነበር፤ የተመረጠው ቦታ ደግሞ አርጀንቲና ነበር። ዓለምአቀፉን የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ የነበረው ዝግጅት እጅግ
እኔን አርክቶኛል። ትክክለኛም ምርጫ ነበር። ክብርት ጀግኒት ኢቫ የምር የመንፈሴ ቤተኛ ናት ፎቷውም ቤቴ ውስጥ ይገኛል።
ብዙ አልተጻፈለትም እንጂ አርንጀንቲና ላይ ያለው የሴቶችን አቅም መንበር ላይ የማዋል ብቃት
የትም ዓለም የለም። አርመን የተለዬ ትኩረት ቢኖራትም የአርንጀንቲናን ያህል ግን ትውልዱ እንደ ትውፊት የሚወራረሰው አቅም ገና አልተገነባም።
በሴቶች የማድረግ አቅም ትውፊት የማድረግ ሰፊ ፕሮጀክት አለ በዚህ ዘርፍ ክብርት ፕሬዚዳንቷ ከሠሩበት ከሁሉም ሃላፊነት በላይ ነው። የችግራችን መፍቻውም
ይህው ነው። ሴቶች ሁሉንም መሆን ይችላሉና።
ሌላው ሚስጢራዊ መንገድ … ይፋዊ አይደለም ብቻ የተከደነ ሲሳይ ልበለው የካናዳ እና የአውስትራልያ
የመንግሥት አወቃቀር ትውፊቱን ባለመሳቱ፤ ትውፊቱን በማክበሩ በረከቱን አልተነጠቀም። ምርቃቱ አልተወሰደበትም። የአሁኑ የክብርት
ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዱ ሹመት ርቁቅ ጸጋ በዚህ መንፈስ ውስጥ አለ።
ምንአልባት በግርፉ ሳይሆን ውስጡን ላጠናው፤ ውስጡን ለመረመረው የመዳኛችን አውታርም ሊሆን ይችላል።
ፈቅደን ያጣነው፤ ትኩረት የነሳነው፤ ከአፍሪካ ተለይተን የተሰጠን ልዩ ምርቃት ነበር። ያን በራሳችን ፈቃድ ጠቅጥቀን ሰርዘን አፍረንበትም፤ ከሳወገድን
50 ዓመታት አሳለፍን።
50ዓመታቱ በሙሉ የደም መሬት አድርጓታል አላዛሯን እመቤት። ተረገምን። የእርግማን ዓመታትም ነበር የደም ዘመኑ። በቃ
ስንቀብር ስንካሰል፤ ስንወንጃጃል፤ ስናፈራርስ የኖርንበት ዘመን። እና እናማ ከሳቸው ሹመት ጋር አላዛሯ ኢትዮጵያ ወደ ነባሩ ክብሯ
እንደ ተመለሰች አስባለሁኝ እኔ። እርጋ! አለ ቢዚህ ጥበብ ውስጥ።
ምን አልባትም በቀጥታ እኛ ተርጉመነው ከብሄራዊ የዜግነት አራማችን
ጋር አያያዝነው እንጂ ያ እንጅባራ ላይ የታዬው የሰንደቅዓላማ ሚስጢር ይህ ነው ብዬ አምናለሁኝ። ቅብዕ እኮ የፈጣሪ የአንድዬ ነው።
ረቂቅ ነገር አለበት። ለእኛ ለጊዜው ያልተገለጠልን። ይህ እኮ መባቻ ነው። መባቻው ደግሞ ማግስትን ዋስትና እንዲኖረው ያደርገዋል።
ቤት ካለምሰሶ አይቆምም። አሁን ደጀን አላት አላዛሯ ኢትዮጵያ።
አሁን ኢትዮጵያ መሰሶ አግኝታለች። ጽናቱ ነገን አማትሮ፤ ተደሞን ቀምሮ፤ ትእግስትን ቀልቦ ለነገ ራሱን
ነገ አሰናድቷል። ይህ ቦታ ሴቶች ከያዙት ብዙ ጥብብ ያለው ተግባር ይፈጽሙበታል። እኔ እንዲያውም የድምጽ አልባዎቹ
የኢትዮጵያ እናቶች ዕንባ የእዮር መልስ ነው ብዬ አስባለሁኝ። ሚሰጢሩን በጥቅሉ ነው የምተዎው።
ክብርት ወ/ሮ ሙፍርያት ካሚል የደህዴን ሊቀመንበርነት ሲያገኙ አንድ ደፋር እርምጃ ወስደው አሳዩን።
ሦስት ወኪሎቻቸው በባህርዳር፤ በመቀሌ እና በጅማ የግንባሩ ድርጅቶች ጉባኤዎች ላይ ድርጅታቸውን የወከሉት ሦስቱም ሴቶች ነበሩ።
ይህ ያልተደፈረ አመክንዮ ነበር። ሴቶች ቦታ
ሴያገኙ ሴቶችን ቦታ ይነሳሉ።
እውነት ብናገረው እሳቸው ከውስጤ
ያለውን ነገር ነው የፈጸሙት። ነገም ዛሬ በተሰጣቸው እጅግ ግዙፍ ሃላፊነት ከዚህ የበለጠ በመሆን ውስጥ ሴቶችን በማብቃት እረገድ
ነፍስ ያለው ተግባር ይፈጽማሉ ብዬ አስባለሁኝ። ዕውነት ለመናገር እኒህ ሴት ክብርት ወ/ሮ ሙፍርያት ካሚልን ማለቴ ነው ለሴቶች
ለብቁዎቹ፤ ለሚመጥኑት አንስታት ምቀኛ አይደሉም። ለሴት ሊሂቃንም የኢጎም በሸተኛ አይደሉም። ሦስት አዲስ የፖለቲካ ሊሂቅ አንስቶችን
እኮ አሳዩን። አስተዋወቁን። ይህ መታደል ነው። በእኔ ትውልድ ይህን አላዬሁም።
ክብርት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ውስጣቸውን ሲሳዩን በዚህ ዘርፍ እንደሚተጉ ነው።
ይህ ንጥረ ነገር ነው። ይህ ንጥረ ነገር የትውልድን መሰረት ያንጻል። ጉዟችን ግንጥል ጌጥ አይሆንም። ሴት የሌለበት ፊልም እስኪ
እዩት። ውሃ ሲሄድበት የከረመ አለት ነው የሚመስለው። በቃ የፖለቲካችን መስክም እንዲሁ ... ሴት እኮ ጌጥ ናት። ሴት እኮ ልዩ ዜማ ናት። ከድምፆዋ ጀምሮ።
የሴቶችን አቅም በመገንባት እረገድ አንድ ትልቅ የሴታዊት አክቲቢስት በስንት የዕንባ ዘመኗ አላዛሯ
ኢትዮጵያ እንዳገኘች እኔ እቆጠረዋለሁኝ። ንግግራቸው ራሱ ፈውስ ነበረው። በቀጥታ ወደ መንፈስ ገስግሶ ቤተኛ ሲሆን ከልካይ አልነበረውም።
ሃብታሙ ክህሎታቸው የሴቶችን አቅም በማጎለብት ረገድ ትልቅ ነገር ተናገረዋል „ገና ምኑ ተነክቶ!“ ብለው። አዎን! „ገና ምኑ ተነክቶ።“
ቀድሞ ነገር የኢትዮጵያ ችግር ሳይታወቅ ነበር እኮ መፍትሄ ላይ ሲዳከር የተኖረው። የኢትዮጵያ
ይሁን የአፍሪካ ችግር አንድ ነው። ያም ሴቶችን ያገለለ ፖለቲካ አራማጅነታቸው። ይህ ማለት መሬት ሳይኖርህ ገበሬ መሆን ማለት ነው።
ወይንም ደፍተር እስክርቢቶ ሳይኖርህ ት/ቤት መሄድ ማለት ነው። ወይንም ትጥቅ አልባ ደንበሬ ተደፈረ ብለህ ውጊያ ወረዳ መሄድ ማለት
ነው። ወይንም መንጃ ፈቃድ ሳይኖር መኪና መግዛት ማለት ነው።
አላዛሯ ኢትዮጵያ ሹፌር የሌላት አገር ሆና የኖረችበት ዋነኛው አምክንዮ የሴቶችን አቅም ለመጠቀም አቅመ ልውስ በመሆኗ
ነው። አለመሳተፉ ይሁን፤ እንዳሻቸው ይሁኑበት ተብሎ የምንናገረውን ቢያደምጡን ስንት ነገር በተገራ። ቀደሞ ነገር ስለመፈጠራችንም
የሚያውቁት አግብተው ልጅ ሲወለድ ብቻ ነው። ወይ ደግሞ አይቀርም ያ ተፈጥሮ የሚባለው ፍቅር ሲይዛቸው።
የሴቶች በፖለቲካ መስክ ባይታወር መሆን አሁን በአቅማቸው ላይ ሰፊ አነጋጋሪ የሆነ አጀንዳ ሆኗል።
„አይችሉትም“ የሚል። አለመቻላቸው
የሴቶች ጉዳይ አይደለም። ሴቶች የሠሩት ችግር አይደለም።
የሴቶችን አቅማቸውን አጉልብቶ በሚገባ ቀርጾ ማውጣት የመንግሥት ተብዬው
ተግባር ነበር። ተፎካካሪ ነኝ የሚለውም ለሥልጣኑ ከመራኮት አገር የወንዶች ብቻ ሳላልሆነች በዚህ ላይ መትጋት ነበረባቸው።
አቅርቡም
ቢባሉ ማፊ ነው።
ቀድሞ ነገር መንግሥት ምን ሲሳራ ባጀ? የፖለቲካ ድርጅቶችስ? ትውልድ የሚባለው እኮ ሴቶች የፈጠሩት ነው። ካለሴት
ትውልድ አለን? ካለሴት የተፈጠረ ልጅ አለን? ሶፍያን መቸም አትሉኝም? ሴት እኮ የመጀመሪያዋ የህይወት ት/ቤት ናት።
ኢትዮጵያ ደሃ አገር ናት። የድህነቷ አንኳር ምክንያት የሥርዓት አለመስተካክል ነው። የሥርዓት
አለመስተካካል ያመጣው ችግር መሰረቱ የአስተሳሰብ
ድህነት ነው። ኋላቀርነት እኮ ማለት እኮ ያልተመጣጠነ እድገት ማለት ነው። አስተሳሰብም በተመጣጠን መልኩ ማደግ ካልቻለ
ድህነት አለበት ማለት ነው። ድህንት ኖረ ማለት ኋላቀርነት አለ ማለት ነው።
ያ ያልተመጣጠነ ዕድገት በፈጠረው መጠራቅቅ ውስጥ ሾልከው የወጡ ናቸው የዛሬዎቹ የካቢኔ አባላት፤
ስለዚህ ያላቸውን ይዘው ቀርበዋል፤ መደገፍ - መርዳት - አይዞችሁ ከጎናችሁ ነን ማለት ደግሞ የመንግሥት ተግባር ነው። በቅርበት
አብክሮ መርዳት። ልዩ አትኩሮት መስጠት። እነሱ ላልፈጠሩት ችግር እነሱ ተጠያቂ ሊሆኑ አይገባቸውም። ባይወጡትም እንኳን።
„የአይችሉትም“ ሟርቱም ቢሆን
የእነሱ የእጅ ሥራ ውጤት አይደለም። 27 ዓመት የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት፤ የሴቶች እና የህጻናት ሚ/ር የት/ሚር እያለ ልባችን
ሲያወልቅ ከርሞ የለንም ኢህአዴግ? እና ማብቃት የራሱ የመንግሥት ጉዳይ ነው። ለነገሩ ደራሹ ወንዝ ሲመጣ ማቄን ጨርቄን ነው የተሆነው።
ለሴቶች የቀረበ መሪ ኢትዮጵያ ይፈጠራል ብለን ሁላችንም አላሰብንም። አዲሱ የነጮች ዓመት 2018
እንደ ገባ ለአንድ የኢሚሌም ወዳጄ ጋዜጠኛ ነው ባለቤት ስለሌላቸው
ማህበረሰቦች ስንጻጻፍ ያው የአብይ አክቲቢዝም ነበር ያገናኘን፤ ሴቶች አቅማቸው ዕወቅና የሚያገኘው ዶር አብይ አህመድ ጠ/ሚር ከሆኑ
ብቻ ነው ብዬ ጽፌለት ነበር። ጹሑፌን ስለሚያነብ ይታዘበኛል። አሚመሉም አለ ከእጄ።
መቼም ሳይደነግጥ አይቅርም እንደዛ ስጽፍ ፤ ያን የመሰለ ቅጭም ያለ የውሳኔ ሃሳብ ስልክለት። የጠ/ሚሩ ውሹ ያን
ጊዜ ስላልነበረ። እሳቸው የኦህዴድ/ ኦዴፓ የጽ/ቤት ሃላፊ እያሉ ማለት ነው። አሁን የምናዬውም ያንን ነው።
ወደ ቀደመው ምልሰት ሲሆን በሴቶች አቅም ግንባታ ላይ በስኬት እና በውጤት ሲለካ ቀዝቃዛ፤ ለብ
ያለ፤ ተመጣጣኝ ሙቀት ያለው የመሆን ያለመሆን የደረጃው ጉዳይ የሚለካው በአንድ አገር ያለው መንግሥት የቤት ሥራውን በመሥራት እና
ባለመሥራት ይለካል።
ለዚህ ነው የአንድ አገር የዴሞክራሲ መጠን የሚለካው ያ አገር ለሴቶች በሰጠው የመብት ስፋት ወይንም በፈጠረው
መጠራቅቅ ይወሰናል የሚባለው።
አሁን ፊት ለፊት በወጡት ሴቶች
የአቅም ውስኑነት ቢታይባቸው እንኳን የእነሱ ጥፋት አይደለም። ሃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው። ሃላፊነቱን መስጠት ብቻ
ሳይሆን ተከታታይ ሙሉ እገዛ እና የሞራል ሙሉ ድጋፍ በቀጣይነት ባልተራራቀ ጊዜ መስጥት ያስፈልጋል። የሰው ግንባታ የሰሞናት አይደለም።
ተከታታይነት ያለው
መሆን አለበት ሁሉም ነገር፤ የወረት መሆን የለበትም። ሰው መገንባት ትልቁ እና ከባዱ፤ ፈታኝ እና አስቸጋሪው አመክንዮ ነው። ለዛውም 50 ዓመት ሴራ ሲዘመንባት ለኖረች
አላዛሯ ኢትዮጵያ ሲደመር ዞገኝነት - ፍዳ ነው፤ ውሃ ያዘለም ተራራ።
በ2013 በዚህ በሴቶች ዙሬያ በተከታታይ እስራ ነበር። ይባረክ እንጂ ዘሃበሻ ያወጣልኝ ነበር።
የተከከለ ፍቅር፤ ያልተደፈረ አምክንዮ በሚሉ ዕርዕሰ ጉዳዮች ወዘተ …አድማጭ ግን አልተገኘም ነበር።
ዛሬ ለቀኑ ቀን ወጥቶለት ሴቶች በኢትዮጵያ የሥልጣኔ ልክ፤ እናት
አገር በአላት የደረጃ የአቅም ልክ፤ እምዬ ባላት የሎጅስቲክ ፍሰት ልክ ያን ሁሉ ፈተና አልፈው የተገኙት ፊት ለፊት ቦታ ሲያገኙ
„ቀልብ ለመሳብ ነው አትኩሮት ለማግኘት
ነው“ ወዘተ ወዘተ … ሲያጣ የጦመውን ዓይነት ነው ለእኔ። መጀመሪያ
ዜጋ መባላችን በኖረልን። ብቻ ያልጀመርነው ነገር ያለ ይመስለኛል። ትናንትን ማሰብ ያስፈልጋል።
ሴት ልጅ ጥፍሯ በሚወልቅበት፤ ሴት የፖለቲካ ሊሂቅ ከእንግልቷ ስፋት ልክ ማጣት ደም የሸናችበት፤
ሴት ልጅ ተዘቅዝቃ ተሰቅላ የምትደበደበት ዘመን እኮ ነበር። ሴት ልጅ የመጀመሪያ በኽር ልጇን እስር ቤት አርግዛ ወልዳ፤ አባቱም
እዛው እስረኛ ሆኖ አሳልፈናል እኮ። ምነው ያ ተረሳ?
የጋንቤላ እናቶችስ ልጆቻቸው እያዩ አልተነጠቁም፤ የአንባ ጊዮርጊስ እናቶች
ወንድ ልጆቻቸውን ይዘው ጫካ አልገቡንም? ወ/ሮ ታደሉ ልጃቸው ተገድሎ እዛ ላይ ተቀመጥው አልተደበደቡንም?ስንቱ ይዘርዘር?
እኔ ሳስበው የሴት ሊሂቃንን ወደፊት ለማምጣት የተሄደበት ድፍረት እውናዊ አለም ያለሁኝ አይመስለኝም።
ልብ ወለድ ኪኖ ነገር ነው የሚስለኝ። በህይወት እያለሁኝ እንዲህ ሴት ርዕሰ ብሄር ለዛውም ይህ ይጎድልሻል የማትባል፤ አንገት የማታስደፋ፤
የኩራት ፏፏቴ አላዛሯ ኢትዮጵያ ይኖራታል ብዬ አስቤም አልሜ አላውቅም። በፍጹም።
ስለሆነም ለጠ/ሚር አብይ አህመድ ከፍ ያለ ትሁት ጀርጋዳ፤ ዘንካታ ምስጋና አቀርብላቸዋለሁኝ።
ይህ እርምጃ የአልጀርሱ ውሳኔን ወደ ተግባር ለመለወጥ ከተወሰደው ደፈር እና ጉልበታም እርምጃ በላይ ነው። እጅግ ጀግና እርምጃ
ነው። እጅግም ያልተጠበቀ እርምጃ ነው።
እጅግም የሚያረካ እና የሚያሰመሰገን ሁለገብ ጥቅም ያለው፤ የሚመሰጥ፤ የሚያጓጓ፤ ሁለንትናን
እርጋ! የሚያሰኝ ብልህ እና ብቁ
እርምጃ ነው።
አዲሳዊነትን አላዛሯን ኢትዮጵያ
እዬጎበኛት ነው … ይህ እርምጃ ለእኔ ይህ ይቀርሃል
የማልለው ከበቂ በላይ የሆነ እጅግ ጉልበታም እርምጃ ነው። መታመኑ በራሱ ወርቅ ነው። ስለሆነም መዋዕለ አቅማቸውን ለማዋል መስኩ
አነሰ የሚለው ዕድምታ ይህ ለእኔ ልበ - ገብ አይደለም። ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ ዕጹብ ድንቅ እርምጃ ነው።
ሌላው በሚ/ር ደረጃ የተመደቡት „አይችሉትም“ የሚለውም በአንጻራዊነት ሲታይ ስንት እኮ አቅመ
ቢስም ተባት አለ። ዶክተሬቱን ይዞ የዕለት ኑሮውን መምራት የተሳነው። በመጻህፍቶቼ ላይ አብሶ ትውልድ ግንባታ ተኮር ላይ „በተስፋ በር“ እና „በእርግብ በር“ ላይ የታዘብኳቸውን ሰነፍ ወንዶችን ለናሙና አቅርቤያቸዋለሁኝ።
ለዛውም ወንድ እኮ ሁልጊዜ በአንበሳ አምሳል የተሳለ ነው። በቃ ተባዕቱ ሁሉ በሙሉ ሁልጊዜ ጠንካራ፤
ሁልጊዜ ማድረግ የሚችል፤ ሁልጊዜ የሚሳካላት። ሁልጊዜ ውጤታማ። አይምሰላችሁ ስንት ጉድ እና ገማና ቤት ስለሚከውነው ነው። አንድ
ፋይል እንኳን ማደራጀት የማይችል፤ ለፋይሎቹ ማቀፊያ የሌለው ስንት ዝርክርክ አለ በዬቢሮው? ቤት ይቁጠረው?
ለኢትዮጵያ ሴት ባለቤቷም እኮ ልጇ ነው። ልጅ ደግሞ አለ እሱም/ እሷም ልጆቿ ናቸው። የሴት
ሰነፍ የለም እያልኩ አይደለም፤ ግን ሴቶች ቢያንስ የቤት ውስጥ ሃላፊነታቸውን፤ ማህበራዊ ኑሮ ተጨምሮ አሳምረው ነው የሚወጡት። ከቴማዋ
ትሁን ገጠሬዋ። እኔ የገበሬም አደራጅ ስለነበርኩኝ የገጠሯን ሴት በሚገባ አሳምሬ አውቃታለሁኝ።
- · አቅም ፎርሙላ አለውን?
የኢትዮጵያ ያልተጠናው ችግር፤ ምርምር ያልተደረገበት አመከንዮ „አቅም“ ማለት ምን ማለት ነው
የሚለው ነው። ግን አቅም ምንድን ነው? አቅም ከሜዳ ይታፈሳልን? አቅም ተዬት ይገኛል? አቅምስ ፎርሙላ አለውን?
እንደ እኔ አቅም ጥናት ይፈልጋል፤ አቅም አደራጅ ይሻል፤ አቅም አስተዳዳሪ ይመኛል፤ አቅም ትኩረት
ይፈልጋል። ግን አቅም በኢትዮጵያ ከቁጥር ያልገባ፤ ሲባክን የኖረ ንጹህ አንጡራ ሃብት ነው። ለዚህም የሴቶችን አቅም እንዲሁ እንደ
አባይ ወንዝ አግድሞሽ ሲባክን ነው የኖረው … ችግራችንም እልቀተ ቢስ የሆነው በዚህም ነው።
ትንሽ ለማብራራት ትንሽ ነገር ልከል። ይህን በ2016 ጽፌበታለሁኝ። ለምሳሌ አንድ ድርጅት ደጋፊ
ይኖረዋል። ከምንም አይቆጥረውም። ደጋፊው እኮ ወጭ አልባ ነው። ያለፋበት፤ ያልደከመበት፤ አቅም ያላፈሰሰበት። ግን አያያዝ ብሎ
ነገር አጀንዳ ሆኖ አያውቅም።
ሌላ ምሳሌ ልከል አንድ ሰው ፌስ ቡክ ይኖራዋል፤ ተከታዮቹን ከምንም አይቆጥራቸውም። እነዛ ተከታዮቹ
አንጡራ ሃብቱ ሳይደክም ያገኛቸው ናቸው። ግን ጉዳዩ አይደለም። በአገር ደረጃ ነፃነት እናስገኛለን በሚሉት ድርጅቶችም ደረጃም በነፃ
የሚገኝ ፍቅር ከወንዝ ዳር እንደሚታፈስ አሽዋ እንኳን አያዩትም …
ሰው ልገዝህ፤ ልርዳህ፤ ልታዘዝህ ብሎ የመጣውን አክብረህ እንኳን ደህና መጣህልኝ/ መጣሽልኝ
ማለት ሲገባ ዱላም አለበት። ቅጣትም አለበት። ቂም ማፍራትም አለበት። መበቀያ ማድርግም አለበት። እኛ ገና ነን።
መኖርን በመኖር
አስውበን አስጊጠን ለመጠበብ አልጀመርነውም።
አሁን ኦህዴድ / ኦዴፓ ያን የመሰለ የሰማይ የኤዶም ገነታዊ ፍቅር እንዲሁ እንዳልባሌ በረዷማ ፍሰት
ለቀቀበት … ካለ እድሜው አስረጀው። በስንት ዘመን፤ በስንት ድካም፤ በስንት ልፋት፤ በስንት ውጣ ውረድ የማይገኛውን የሚሊዮን ታማኝነት
በቃ ወፍዘራሽ አድርጎት ቁጭ አለ እጬጌው ኦዴፓ።
ሳይደክም፤ ሳይለፋ፤ ሳያወጣበት፤ ሳይከላተም በቃ ፍቅር ዘነበለት ከሰማያ ሰማያት፤ ፍቅር አረገደለት
እንደ ጉድ፤ መወደድ፤ መታመን ረበበለት፤ የትሜና አልፈስፍሶ፤ አጠውልጎ፤ አጠንዝሎ ወደ መጣበት በቁጣ መለሰው።
በመጨረሻ የምላው ለክብርት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሰህለ ወርቅ ዘውዴ ይህን አክብሮት፤ ይህን መሰል
ተቀባይነት፤ ይህን መሰል ውስጥን ፈቅዶ የመሸለም ምርቃት ሳያባክኑ ህሊናችን ሆነው ይዘልቁ ዘንድ አምላክችን ልዑል እግዚአብሄር
ይርዳልን። አሜን!
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው።
ሴቶች ቅኔዎች ናቸው!
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መልካም ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ