አደብ ለወዘተረፈ።

ወዘተረፈ።
„የእግዚአብሄረ ቃል ወደ ሰለሞን መጣ፤ --- እንዲህ ሲል
ስለዚህ ስለምትሠራው ቤት በሥርዓቱ ብትሄድ፤ ፍርዴንም ብታደረግ
ትመላለሰብትም ዘንድ ትእዛዜን ሁሉ ብትጠብቅ ለአባትህ ለዳዊት
የነገርሁትን ቃል ከአንተ ጋር አጸናለሁ።“ መፅሐፈ ነገሥት
ምዕራፍ ፮ ከቁጥር ፲፩ እስከ ፲፫
ከሥርጉተ©ሥላሴ
31.10.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።


  • ·       ነሻ።

„Hiber Radio: የአቻም የለህ ታምሩና የሁንዴ ዱጋሳ ሞቅ ያለ ውይይት(ክፍል አንድ )ያድምጡት ያሰራጩት“

መነሻዬ ይህ ነው። በዚህ ቃለ ምልልስ መነሻነት ውስጤ የሚለኝን ነገር ለማለት ነው የፈለግኩት። በክርክሩ ላይ አልታደምም። ነገር ግን በዚህ ውስጥ ያሉ ቁምነገሮችን በማስተዋል ማዬት ይገባናል ብዬ አስባለሁኝ። ክፍል ሁለትን መጠበቅ አላስፈለገኝም።

ምክንያቱም ሙግቱ ጠቅላላ ይዘቱን አይደለም እኔ ልሄድበት የፈለግኩት። እኔ አስተያዬት ልሰጥ የምፈልገው የሥር - ነቀል ለውጥ ፍላጎት እና ያለው ተጨባጭ አቅም ስለገረመኝ ብቻ ነው ይህን መጻፍ የፈልግኩት። የምንፈልገው እና አለን የምንለው ነገር ይገረመኛል ሁልጊዜ።

የውይይቱ መንፈሱ ኢህአዴግ ራሱን አፍርሶ እንዬው ስለሆነ ያ በመዳፋችን ካለው አቅማችን ጋር ሚዛን ውስጥ ለማስቀመጥ የሚቸግርበት አመክንዮ መኖሩ ብቻ ሳይሆን በመቻቻል እና አፍርሶ በመገንባት ያለውን የራሴን ዕድምታ ለማቅረብ ነው።

ይልቅ የአክቲቢስት ሁንዴ ዱጋሳ የጭብጥ መነሻ ለእኔ ስሜት ቅርቤ ሆኖ አገኝቻለሁኝ። አሁን ኦነግ አረካሁም ስላለ ትጥቅ አልፈታም ብሏል፤ ውጤቱን አብረን እምናዬው ይሆናል። 27 ዓመት ሙሉ አንድም የነጻነት ሃይል አንዲት መንደር ለሳምንት ተቆጣጥሮ አያውቅም። ይህም ሃቅ ነው። የሁሉንም ዕድምታ ማዳመጥ መልካም ስለሆነም ይህንን ህብር ራዲዮ በማድረጉም አመሰግነዋለሁኝ። 

አላዛሯ ኢትዮጵያ እና ዕንባዋ ለ50 ዓመታት ተኑሮበታል። ዴሞክራሲ ስለሚባለውም ነገር ከሆነ ያዬነውን ዓይተናል፤ የሰማነውን ሰምታናል፤ የኖርንበትን ኑረንበታል።

ዴሞክራሲ የቃሉ ቅለት እንጂ እያንዳንዱ በራሱ ላይ እንዲፈጸም ፈጽሞ የማይፈቅደው ነገር ነው። ለሌላው ውግዝ የነበረው ሌላው ዕድሉን ሲያገኝ ያንኑ ተጫኝነት፤ ጠቅላይነት ሲደግመው ዘመኑ የእሱ ከሆነ ትክክል ሆኖ ይታዬዋል።
ወቀሳ መሰንዘር ቀላል ነው። ወቀሳ የመቀበል አቅም ነው መከራው። ወቃሹም ሆነ ነቃሹ በእጁ ባላቸው ሥልጣን ተወቃሽነቱን መቀበል ይችላል ወይ ሲባል አያደርገውም። ሁሉም አሁን ባለሥልጣን ነው በከፈተው ሚዲያ ይሁን በሚያሳትፈው መድረክ ሁሉ።

በዛ ለሁሉም እኩል መብት ሰጥቷል ወይ ቢባል። የለም። ታናሽ እና ታላቅ ጠይም እና ዳማ የተማረ እና ያለተማረ፤ የማህል አገር ሰው እና የዳር አገር ሰው እያደረገ ሸንሽኖ በዛች ባለችው መድረኩ የክት እና የዘወትር ሲለይበት ውሎ ማደሩ አልበቃ ብሎ ዛሬም በዛው ላይ ተሁኖ ሲተች ሲመነጥር ደግሞ ይታያል። ይህ ተደፍሮ እከሌ ተከሌ ተብሎ ቢነገር ደግሞ ሌላ ዘመቻ ሌላ ሞገድ ያስነሳል።
አላዛሯ ኢትዮጵያ ወዘተረፈ ችግር አለባት። ወዘተረፈ ችግሩ ደግሞ ሁሉም የድርሻውን በሚያዋጣው መከራ የተከመረ ነው። ሳቅ እራሱ፤ ደስታ እራሱ፤ ምህረት ራሱ፤ ይቅርታ ራሱ ከራስ አይጀመርም። ይልቅ ሥርነቀሉ ለውጥ የሁሉም ዜጎች ግዴታ ሊሆን ይገባሉ ባይ ነኝ።

እኩልነት ተባደግ ነው። አንዱ የቅርብ ሌላው የሩቅ ነው። ዕውቅና ያለው ሌላው ዕውቅና እንዲያገኝ አይሻም። አንዱ ጀግና ሲባል ሌላውን ጀግና እንዳይወጣ ክትር ሰርቶ ነው። ለራሱ የሰጠውን ነጻነት ለሌለው እንዲሆን አይሻም። ንፉግ ነው። እኔ ይሄኛው ተዚኛው፤ ተቺውም ተተቺውም ይሻላል ማለት አልችልም።

ዝምታ ወርቅ ነውን ቤተኛ ማድረግ ስለሚሻል እንጂ ይነገር ቢባል ጉዱ ብዙ ነው። በመገንባት ላይ ሳይሆን በማፍረስ፤ ተጠያቂ ሌላውን በማድረግ እንጂ እኔም ተጠያቂ ነኝ ብሎ ሃላፊነት የሚወሰድ ደፋር ምድሪቱ አላፈራችም።
  
በአላዛሯ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ለውጥ፤ ለውጥ አለ ለምንለው ለሞኞች ማለቴ ነው ጥገናዊ ነው። አብዮታዊ ለውጥ አይደለም። አንድ የነፃነት ሃይል በውል ተደራጅቶ፤ ባቅሙ በቅሎ፤ራሱን ችሎ አገር ለመምራት በቅቶ አቅም ኑሮት ያን ፈንቃቅሎ ጥሎ ነፃ አላወጣንም። ይህ ዓለም የሚያውቀው፤ ታሪክም የሚያውቀው ሃቅ ነው።

አብዮት የሚባለው ነገር ጽንሰ ሃሳቡም ሆነ ድርጊቱ ደግሞ የነበረውን ነገር በሙሉ ደርምሶ አሸናፊው የራሱን በትረ ሥልጣን ማቆም የሚችለው በራሱ አምሳያ ነው። ይህን ደግሞ በተደጋጋሚ ሲከሽፍም ሲሳካም ታሪክ አሳይቷል። የተተረፈበት ነገር አለመኖሩንም ታይቷል።

የዛሬ 50 ዓመት እንደ እኛ የነበሩ አገሮች ዛሬ ዓለምን እዬተገዳደሩ ነው እኛ ግን ከነበርንበትም ወርደን ሰውን በድንጊያ ወግረን፤ ገድለን ሰቅለን፤ አቃጥለን … ፌስታ እንደርጋለን --- ምጥ።

ወደ ቀደመው ሃሳቤ ምልሰት ሳደረግ አሁን በደርግ ጊዜ በዘመነ ኢሠፓ ሁሉም ይቅር የመንፈስ አቅሙ ልዑቅ ነበር። ያን እንኳን በቅጡ ማስተዳደር አልቻል ብሎ ባክኖ ነው የቀረው። ተበትኖ። ስንት ጥንቁቅ ሰዎች ነበሩበት። ስንት ሊቀ ሊቃውንት ነበሩበት። ሁሉ ነገር ይጠላል ሁሉ ነገር ይወድማል ሁሉ ነገር የማርያም ጠላት ነው። 

በዚህ አላዛሯ ኢትዮጵያ አተረፈች ወይ ሲባል በዓለም ካሉት ደሃ አገሮች የመጨረሻው ተርታ ላይ ትገኛለች። የትናንት ዛንጊባ ዛሬም እንደ ዘመመ ነው፤ ትናንት የነበሩ የኤሌትሪክ የስልክ ምሶሶዎች ኑዛዜ ላይ ናቸው። ትናንት ደማቅ የነበሩ ከተሞች የነፍጠኛ የሚል መለያ ኮድ ተሰጥቷቸው ድቅቅ ብለው አቧራ ለብሰው ይገኛሉ። ትናንትም ገጠር በኩራዝ ነው ዛሬም እንዲሁ።

አብዮት በሚባለው ጉድ ከሁሉ በላይ የሰለጠነው ሰው አለቀ፤ ተሰደደ፤ ትወልድ ባከነ። ትውፊት መቅኖው ደቀቀ። ሌላው ቀርቶ እኛ ቅርስ ውርስ መስራት አቅቶን በመንፈስ ደህይተን የዛሬ መቶ ዓመት ያሉም ቅርሶች ራሳቸውን ሳይጥሱ በመገኘታቸው ጠላት ናቸው ማፈርስ መደምሰስ ያልተቻሉት እንኳንስ መልካሙ ነገር ቀርቶ፤ ቋሚ ምስክሮች ቆመው እንዳይታዩ፤ ቆመው እንዳይመሰክሩ እንዲከስሙ ሰፊ የሆነ ዘመቻ ነው ያለው። አለመታደል።

ወንዞች እራሱ የመከራ ተሻካሚዎች ናቸው። ሃይቆች የፍዳው ታጋሪ ናቸው። የተፈጥሮ ሃብቶቻችን ብክነት ታቅዶ የተከወነ ነው። አላዛሯ ኢትዮጵያ ጠላቷን ነው አቅፋ የምትኖረው። ህልውናዋን ያመሳቀለውን ነው ልጄ ብላ ሸክፋ የምትኖረው። ጦሱ ደግሞ አብዮት የሚባለው ጉድ ነው።

አሁን ውይይቶችን ግርም እያለኝ ሳዳምጥ ሥር - ነቀል ለውጥ አልመጣም እዬተባለ ነው ሙግቱ። የነበረው ሁሉ ተደርምሶ ሰራዊቱም ሰራተኛውም   ማሳደደ፤ በከፋ ሁኔታም በጅምላ ማሳር፤ በውል ቤተሰብ መበትን፤ የተገነባው ሁሉ ፍርስስርስ ብሎ ከዜሮ ካልጀመረ ለውጥ የለም ነው ለዘመኑ ተንታኞች።

እናንተስ ዕድሉን ብታገኙስ ቢባሉ አይደለም ወዘተረፈ ችግርኛዋን አላዛሯን ኢትዮጵያ ችግር መሸከም መፍታት ቀርቶ በመዳፋቸው ባለው መድረክ እንኳን ከሰው ሰው ሲለዩ ነው የሚታዬው። የማይመቸውን ሃሳብ ለማስተናገድም ደፍረቱ የለንም - ሁላችንም።

አሁን ያሉት መሪዎች ግን በዬዕለቱ እንሱን ገድለው ሥልጣን ለመውሰድ ቤተሰባቸውን አፍነው ለቅድመ ሁኔታ ይዘው ሥልጣኑን መያዝ እየፈለጉ  በአደባባይ ሲያብጠለጥሏቸው እርቃናቸውን ሲያስቀሯቸው እያዩ፤ እያዳመጡ፤ መከራ ሲደግሱላቸው ቀውስ ሲያደራጁላቸው ውለው ለሚያድሩት ባላንጣዎቻቸው ጋር አብረው ለመሥራት ፈቅደዋል። ይህን እያዬን ነው።

ይህንን እያዬን እንኳን እኛ መማር አንችልም። ለእነሱ የሰጠውን አቅም፤ ለእነሱ የሰጠውን አደብ፤ ለእነሱ የሰጠውን አቅል ያህል ቀርቶ ብጣቂውን እንኳን ለመሆን አለመቻል አለመታደል ነው። 

በአንድ ወቅት የተፈጠረ የፖለቲካ ትርምስ ለዘላለም የትርምስ የህውከት መድረክ እንዲሆን ይፈለጋል። እሳት ማስነሳት ቀላል ነው። የተነሳውን እሳት ማስታገስ ነው ፍዳው። ፍቅርን ተሰጥቶህ ፍቅር ለመስጠት መንፈግም አለመታደል ነው። ይህንንም እያዬሁኝ ነው። 

ፍቅሩም ይቅር ዕድሜ ልክ በማያድግ ጎልቶ ሃሳብ ብቻ ተከዝኖ መንፈስን  ለአድማ፤ ለቅሬታ ማነሳሳትም ሌላው መበደል ነው። እስኪ እያንዳንዱ መሪ ነኝ የሚል ሁሉ ራሱን አሸንፎ መጀመሪያ ይነሳ። ለይደር መቼም "ሳል ይዞ ስርቆት ቂም ይዞ ጸሎት ነው፡ የሚሆነው።

በሌላ በኩል ብዙ ጊዜ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሲወቀሱ እሰማለሁኝ። መውቀሱ መንቀሱ መሪነቱን እስከ ፈቀዱ ድረስ ግድ ይላል። ድክመቶችን፤ ጉድለቶች ተንቅሰው ቢነገራቸው ይጠቅማቸዋል እንጂ የሚጎዳ አይደለም። ነገር ግን በስፋት እና በጥልቀት ሊታዩ የሚገባቸውን፤ ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን እና ሙያዊ አቅምን የሚጠይቁትን በውል መለዬት ያስፈልጋል። ችግሩ ወዘተረፈ ነው የ50 ዓመት ድርድር ችግር አለ። 

አሁን በባዕለ ሹመታቸው ጊዜ የተናገሩት ተጓድሏል የሚል ጉዳይ ይነሳል። አንደኛው ይህ የበዕለ ሹመት ንግግር ፖሊሲ አይደለም። ትልቁ ችግር የግንዛቤ ይመስለኛል። አቅጣጫ አመልካች ብቻ ነው። አቅጣጫ አምልካችነቱ ደግሞ በአንድ ወር ወይንም በመንፈቅ ብቻ የሚከውን ድርጊትን አመላካች አይደለም። ተስፋን ለማግኘት ያለ የሩቅ ጊዜ ምህንድስና ሃሳብ ነው። ሃሳቡ ዲዛይን ነው። ምናብ ነገር። ያ ሃሳብ ደግሞ ምን አልባትም እስከ 50 ዓመትም ሊወስድ ይችላል። ማስፈጸሚያ መዋቅሩም ያን ያህል መከራ ተሸካሚ ነው። 

እያንዳንዱን ቃል እያንዳንዱን ስንኝ እያወጡ ቢተነትኑት በራሱ ባህሪ፤ በራሱ መዋቅር፤ በራሱ መንፈስ ውስጥ የጊዜ- የሁኔታ - የቦታ - የመዋዕለ አቅም መጠንን ይወስናል። ከዚህም በተጨማሪ የውጭ እና የውስጥ ተጨባጭ ሁኔታዎችም አሉ። ዘመኑ ዲጅታል ዘመኑ ሉላዊም ነው። በሌላ በኩል ከሰብዕና የሚመነጩ የማድረግ አቅም እና ያለው መዋቅራዊ ግንኙት ያን ሃሳብ የመሸከም አቅሙም ሥልጣኔ ደረጃም ይወስነዋል። እንዲሁም ኢትዮጵያ የምትመራው ፕሬዚዳንታዊ አይደለም። 

የሆነ ሆኖ ቱማታ ለሽሮ እንጂ ለአገር ግንባታ መርህ ከቶም ሊሆን አይችልም። እንዲያውም ከተጠበቀው በላይ ፈጣን ለውጦች ታይተዋል። ይህም የሰብዕና ብቃት ያሰገኘው ነው። ያለው ነጻነት እና መጠራቅቅ ደግሞ የዲሞክራሲያዊ ማዕላዊነት መከራም አለበት።

ለዛውም ራሱ ኦዴፓ ላይ ያለው ኦነጋውያን መንፈስ ያላዬነው፤ ያለሰብንበት ረቂቅ ፈተናም አለበት። ዘርፈውም ሰርቀውም ገድለውም ሳይጠዬቁ አሁንም ሥልጣን ላይ ያሉት የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ማህበርተኞች ዬየደቂቃው የሰራ መረብ ተችሎ አሁንም እነሱም አብረው ይሾማሉ ይሸለማሉ። ይህም ተችሎ አብሮ ይኖራል። 27 ዓመት እኮ አንድ ትውልድ ነው። ከላይ እሰከታች  በአንድ ብሄረስብ የበላይነት እና ያን በደገፉ ሃይሎች ነው የተዋቀረው። 

በዛ ላይ በ27 ዓመት ቦታውን በመለስ መንፈስ ለማስያዝ የፈሰሰ የአገር ሃብት እና ንብረት አለ። ተጋሩ መሆናቸው፤ ደጋፊም መሆናቸው አይደለም። ለእነኝህ ሊሂቃንም አንጡራ የአገር ሃብት ፈሷል በዚህ መስክ። ስለዚህ ግድ ይላል መዋለ አቅማቸውን የመጠቀም። 

በሌላ በኩል አንዱ አሳዳጅ ሌላው ስደተኛ የሚሆንበትን ዘመን ለማምከን ይህን መራር ነገር መሸከም ግድ ይላል። ያለው የሥራ መስተጓጎል እኮ ምንጩ የኽው ነው። የሚያሳዝነው በኦሮምያ ብቻ ከ40ሺህ በላይ እስረኛ የነበሩ ወገኖች በዚህ ዕድል ተጠቃሚ መሆን በሚገባቸው ሰዓት እንሱም በልባቸው የቱን እንደሚደግፉ አይታወቅም። ሚስጢር ነው ግራ የሚያጋባው። የኦሮሞ ሊሂቃን በውነቱ አላወቁበትም። 

የኦሮሞ ሊሂቃን ዛሬ ባዶ ካዝና እና የፈረሰ መዋቅር ተረከበ አብይ ይሉናል እነሱ አሁኑ ኦሮምኛ የፌድራል ቋንቋ ይሁን ብለው በማህበራዊ ሚዲያ ሰፊ ዘመቻ ከፍተውበታል ለራሳቸው በትረ ሥልጣን። ይህን እንግዲህ ቀደምት የፖለቲካ ሊሂቅ ናቸው ይህን ሁለት የማይገናኝ ነገር የሚነግሩን። የ እኛ ፍላጎት ይፈጸም ነገር ግን ሌላው ጫና አይፍጠር። ጎደሎ ነው። 

በሌላ በኩል የአገር የባለቤትነትም ጥያቄ በአደባባይ የተሰማ ተደሞ ነበር። ምን ያህሉ መንፈስ ይህን የኦሮሞ መንፈስ ጎልቶ የወጣበትን ዘመን ደግፎታል ሲባል ከቁጥር የሚገባ አይደለም።

 ለዚህ በትረ ሥልጣን ያበቃው የኦህዴድ ዓርማ እንኳን ባለሙሉ ሥልጣን ሳይሆን የአቶ ዳውድ ኢብሳ መለያ አርማ ነው ዓርማችን ብለው ነው የወጡት። ራሳቸው የደከሙበትን አፍስሰው አሁን ደግሞ እንለቅማለን ብለው እዬታከቱ ነው … እኛ እንዲህ ነን። መተማመንን ለማምጣት ከእነሱ ይልቅ ቀን ከሌት የደከምን እኛ ነበርን። በዛ እንኳን አልነበሩበትም አይዟችሁ በርቱ ለማለት።

የሆነ ሆኖ የጠ/ሚር አብይ አህመድ ሙሉ ጨዋ ሰብዕና ያመጣው የአቅም ጥሪትን ለመቀልበስ፤ ለመቀማት፤ ለመንጠቅ በ6 ወር ውስጥ ሦስት ጊዜ የመግደል ሙከራ፤ አራት ጊዜ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተካሂዷል። ድርጊት ፈጻሚዎች ላይ እንኳን ኮስተር ያለ እርምጃ ለመውሰድ አልተደፈረም። ይልቁንም የአብይን ሰብዕና ደግፈው በወጡት ላይ እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ተካሂዷል ታሪክ ይቅር የማይለው። የዚህ ምንጩ ምንድን ነው ብለን አደብ ገዝተን ማስታረቅ ይገባል። 

የሆነ ሆኖ ለውጡ አፍርሶ በመገንባት መርህ ላይ ሳይሆን ባለው ላይ መልካም የሆነውም መልካም ካልሆነው በአደብ በመለዬት፤ መልካም ያልሆኑት በጥናት በበቃ፤ በስክነት ወይ እንዲሻሻሉ ወይ ደግሞ እንዲወገዱ የሚደረግበት ሁኔታ ለመፍጠር ጊዜ ይጠይቃል። አርምሞ ይጠይቃል። ስምምነት ይጠይቃል። ህሊናችን እኮ አለመሞረዱን አንድ ሁለት ብሎ ማንሳት ይቻላል። 

አንተ ማለቱ ቅርበትን ይጠይቃል ግን አዎንታዊው በይትባሃል ባህልና ትውፊቷ አክብሮ መንሳትን ይጠቅማል። ዶር አብይ አህመድ ለማለት እንኳን ድፍረቱ የለም። ይህን እንታዘባለን። ይህን እዬመረረንም እናስተውላለን። ተተኪ ልጆችን ለማስተማር ፈቃዳችን እስከዚህም ድረስ ነው። አክብሮ መነሳት ምንም አይታጠበትም። ምንም አያጎድልም።

በዛው በለውጡ ውስጥ አሉ ስለሚባሉት አገር ቤት ያሉ ሊሂቃንን እራሱ ቃለ ምልልሱን አዳምጡት - ውዶቼ ቅኖቹ። አንዲት ጊዜ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ማለት እንኳን አይደፍሩትም። ጠ/ሚሩ ነው የሚሉት። ይህ ማለት በውስጡ የጎረና ነገር እንዳለ ያሳዬናል። ስለዚህ ፈተናው ግዙፍ ነው። 

ሌላ የሰሞናቱን የሹመት ጉዳይ እንመልከት። በጀት ለመቆጠብ ታጠፉ የሚ/ር መ/ቤቶች ተባሉ 55 ሚኒስተር ዲኤታ ደግሞ ተሾሙ፤ „አልሸሹም ዞር አሉ“ ነው። ሌላው ቀርቶ የሥም ዝርዝሩን እንኳን ለማውጣት መንግሥት አልደፈረም። ስለምን? ትችን ለመቀበል አቅሙ ገና መሆኑን እናያለን። በሌላ በኩል ፍልሚያው በራሱ ውስጥም እንዳለም ያሳዬናል። ይህ የጥገናዊ ለውጡ ባህሪ ያመጣው ጉዳይ ነው።

በሌላ በኩል ለውጡን ተግተው ያመጡት ተገለው ደግሞ እናያለን፤ ይህን ዶር አንባቸው መኮነን ላይ የታዬውን ትዕይንት በራሱ ስትመረምሩት ከ66ቱ የርዕዮት ማዕባል ወስዶ ፍቱት ይላችኋል። የማን መንፈስ ጎላ፤ የማን መንፈስ ዝቅ አለ፤ የማንስ ደበዘዘ ሁኔታ መስታውቱን አቅርቦ ይሞግታችኋዋል። በዚህ በራሱ እጅግ ብዙ መንፈሶች ከማዕቀፉ ይወጣሉ። ስለምን? በዛ በጭንቅ ጊዜ ያ ተማላ መንፈስ መከራውን አብሮ ተቀቅሎበታል እና። 

ሌላም ምሳሌ ላንሳ አንደበት በተዘጋበት ሰዓት አርቲስት አስቴር መዳኔ ድምጻችን ነበረች። ቀኑ በማለፍ ላይ እያለ እሷም የፊት ለፊት ተጠቂ ነው የሆነችው። አሁን መድረክ ለአዲሶቹ ተዋናዮች ነው። ይህን ስትመለከቱት ፍትህ እና ዕውነት አደጋ ላይ ስለመሆናቸው ታያላችሁ። ይህም ማለት ህሊና ቅኖችን የማቅረብ አቅሙ ውሱን መሆኑን ትመለከታላችሁ። የሚገፉት፤ የሚገለሉት ውግዘ ከአርዮስ የሚባሉት ቅኖች እና ዕውነተኞች ብቻ ናቸው። ለዚህም ሌላ ተቋማዊ ተግባር ያስፈልገዋል። ተቋም ብቻውም አይረዳም የሰው የራሱ መለወጥ ያስፈለጋል። ቅን መሆን። ለዛስ ብቁ ነን ወይ ሲባል ራስን መፈተሽ ነው።
 
በሌላ በኩል ሁሉንም ሰብስቦ ማስር ቢጀመር የሚቀር የለም። መሪም ይጠፋል። አስተዳዳሪም ይጠፋል። ምክንያቱም ሥርዓቱ ራሱ ተጠያቂ ስለሆነ በሥርዓቱ ውስጥ የነበሩ የመዋቅር ቤተኞች ሁሉ አነሰም በዛም ተጠያቂ ይሆናሉ። እርምጃው ቢወሰድ ደግሞ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘንል። ብዙ ሰው ይሰደዳል። ብዙውም ኑሮውም ይፍርሳል። ግዙፍ ስጋትም ይከሰታል። ከሁሉ የሚከፋው የደርጉ ዜግነት ነው መሰረቱ የወያኔ ሥርዓት ግን ዞግ ነው።

ህውከት በተፈጠረ ቁጥር ህውከቱ የሚቀጣጠለው ዘውገኛው ባሰላው ልክ ነው። መከራው የሚፈጥረው ምክንያታዊ ሁኔታ ስላለ ማለት ነው። በዚህ እኔ ነኝ ያለ አንቱ የተባለ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተጠቂ አልሆንኩም ብሎ ሊፎክር አይችልም። ምክንያቱም አደባባይ የወጣውን ሁሉ ከእነ ማስረጃው የምንይዝ የምንሞግትም ስላለን። 

የማንፌሰቶ አምላኪም ቢሆን ከእኔ ወዲያ ካለ እሱ እራሱ የማንፌስቶ ከራራ ወገንተኛ ነው። አቅም የማባከኛው አንዱም ይሄው ፍልስስፍና ነው። በማንፌሰቶ ተቋማት የራሱን ዘር ከሰበሰብ የወንጀሎች ሁሉ ቁንጮ ነው። ከይፋዊው ስውራዊው የከፋ ስለሆነ። ዝርጓ ዓለማችን ደግሞ ዕድሜ ለእጬጌው ጉግል እንጂ መጎልጎሉን እንደ ተዝረከረከ መረጃው ከች ይላል በዬቤቱ።

ሌላው መከራ ሰው ሰው መሆን ለመቻል አለመጀመሩ ነው። ጭካኔ እኮ ጀግንነት ሆኖ የተቆጠረበት ጊዜ ነው። ሚሊዮን መፈናቀሉ የሚጠበቅ ነው፤ በሽግግር ጊዜ ይላሉ፤ እራሳቸው የሚሹት የሚፈልጉት ስለሆነ።

የሰው ልጅ ሞት በቃ ተራ ነገር ሆኗል። አንድ ሰው ከሰው ይልቅ ለውሻው ያዝናል ዛሬ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ። ለዚህ ነው እኔ ፍቅራዊነት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ከመዋለ ህጻናት ጀምሮ ይሰጥ። በዬቤተሰቡም የፍቅራዊነት ክበብ ይደራጅ የምለው። ሰው ለሰው መተዛዘን ቀረ። መከነ። አንዱ ገድሎ ዘቅዝቆ ሲሰቅል፤ ሌላው በእሳት ያቃጣላል፤ ሌላው ደግሞ በድንጋይ ወግሮ ይገድላል። የሃሞራቢ ህግ እንደ ገና በስንት ዘመኑ በቀደምት ስልጡኗ ኢትዮጵያ እዬታዬ ነው። 

ይቅርታ ተብለህ ይቅርታ ማድረግን አትፈቅድም፤ ይህን ይዘህ ደግሞ መሪ መሆንን ትመኛለህ። ሴረኞችን ተጸይፈህ አንተ ደግሞ መንፈስ እንዲኮረኮም ትተጋለህ። ታዲያ እንዴት እና እንዴት ተኩኖ ነው ብሩህ ዘመን ሊታሰብ የሚቻለው?

ይህ እንዲሆን የሚፈለገው ለውጡ በጀመረው መሰመር እንዳይቀጥል እንዲሰናከል ሌላው መሳናዶ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡ ሥር ነቀል አይደለም ተብሎ ተከሳሽም ነው። በሚታዬው ነገር እንኳን መተማመን አልተቻለም። ከእስር ወጥተህ፤ ስብሰባ ላይ ተገኝትህ መናገር ችለህ እደራጃለሁም ብለህ በተወሰነ ደረጃ እዬተንቀሳቀስክም የምን ለውጥ ትላለህ? ይህ ዕድል ባይገኘስ ኖሮ ማለት አልፈጠረብን።

ሌላው ትልቁ የፖለቲካ ክስረት ተፎካካሪው እራሱ የራሱ መንግሥት የሚሰራው እስኪመስል ድረስ ይህ አልተሟላም፤ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ እያለ ይተቻል። እሱ ራሱ የሰራው ለውጥ አለመሆኑን ፈጽሞ ሊያሰበው ፈቃደኛ አይደለም። ሌላው ደግሞ ህገ መንግስቴ ፌዲራሊዚም እንዳይነካብኝ ብሎ ከወያኔ ሃርነት ትግራይ የ27 የመከራ ቁልል ጋር ማህበርተኛ ሆኗል ተፎካካሪ ተብዬው።

ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ ሁሉ ዕድሉን ተጠቅሞ የራሱን ሞጋች አመክንዮ በፖሊሲ መልክ ነድፎ ራሱን መንፈሱን አደራጅቶ ራሱም ሰዋዊ ባህሪን ተጎናጽፎ ይቅርታን፤ ምህረትን፤ መቻቻልን፤ ሰጥቶ መቀበልን፤ አገልጋይነትን፤ ማድመጥን፤ መተቸትን ተቀብሎ ተግባርን አህዱ ማለት ሲገባ ኢህአዴግ ይህን አደረገ፤ ያን አላደረገም እጅግ የሚገርም የዘመኑ የጉድ ቁንጮ ነው። አሸንፎ ነው ያን የፈቀዱትን ያለሙትን ነገር መከወን የሚቻለው። ኢህአዴግ እማ የራሱን ተግባር የራሱን ትልም አስፈጻሚ እንጂ የተፎካካሪው/ የ ተቀናቃኙ/ የተቃዋሚውን መርሃ ግብር የማስፈጸም ግዴታ የለበትም።

የራሱን ሰው ካልሾመም በአፈጻጸም ላይ ከባድ ፈተና ነው። አሁን የክብርት ፕ/ ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ሹመት ስለምን ጠ/ሚር አልሆኑም የሚል ሙግት ይነሳል። የማይታሰብ ነው። ምክንያቱም ክብርቷ የኢህዴግ አባል አለመሆናቸውን ነው እኔ የሰማሁት። ይህን ተጨባጭ እና አስገዳጅ ሁኔታ ካለማገናዘብ የሚመጡ ግድፈቶች ይመሰለኛል። ለገዢው ድርጅት ውጭ ጉዳይ ጭንቅላቱ ነው። 

ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ 27 ዓመት ፓርቲ የሚባል ኑሮ አይውቅም። መቼም አንድ የፖለቲካ ድርጅት ፓርቲ የሚባለው ነገር በደጋፊ ሃይል ፓርቲ ነኝ ካለ ከጅሎች ጎራ ነው የሚመደበው።

ራሱ ኢህአዴግ ፓርቲ አልነበረም። አይደለምም። ደጋፊ ማለት እኮ የገብያ ውሎ የፊልም - የቲያትር - የሙዚቃ ታዳሚ ማለት ነው። ኢቤንቱ ሲያበቃ የሚበትን። የፓርቲ አባላነት እኮ ከገብያ ተሂዶ የሚሸመት ሰብዕና ማለት አይደለም። የአደራጃጃት፤ የአመራር መርህ አለው።

በጥቅሉ ሲታይ የፖለቲካ ፓርቲም ሳይኖር አሁን ያለው ለውጥ ከሚገባው በላይ፤ ከአቅሙ በላይም ማለት ይቻላል፤ ከሚጠበቅበትም የተሻለ ተግባር እዬከወነ ነው። አንድ የፖለቲካ ድርጅት ፓርቲ መሪ የመሆን አቅሙ የሚመጣው ከአባላቱ ጥንካሬ ነው። ይህ ደግሞ አሁን እኔ ሁሉንም ሳይ ስገመግም ፓርቲ የሚባል የለም። ደጋፊው ነው እንደ ፓርቲ አባልነት የሚታዬው። ደጋፊ ደግሞ ውልም የለውም። ውል አልባ ግዴታ የለም። ውል አልባ መብት ሊኖር ቢችልም ግዴታ ከሌለው ምሰሶ / ወይንም ፒላር የሌለው ቤት ማለት ነው። አላዛሯ ኢትዮጵያ ለእኔ እንዲህ ናት።

ትችትን ለማስተናገድ የሚችል የአንድ የፖለቲካ ድርጅት አቅም ያለው መሪ የፖለቲካ ድርጅት ይሁን ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት አላዛሯ ኢትዮጵያ የላትም። ተዋህዱ፤ ተጣመሩ፤ ተቀናጁ የሚባለውም እማይሰክነውም፤ ረግቶ፤ ጽንቶ ለውጤት የማይበቃውም እራሳቸው የሚቀናጁት የሚጣመሩት የሚዋህዱት በሥርዓት የሚመሩት የፓርቲ አባል የላቸውም፤ ይህ ማለት ጥንካሬው ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ነው። 

ጥንካሬ ስሌላቸውም ውህደታቸው ታች ወርዶ በአባላቶቻቸው ታሽቶ በስሎ ውሳኔ አግኝቶ ሳይሆን በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ብቻ የሚከውን ድርድር ነው የተኖረበት። የማይበርከተውም ለዚህው ነው።

በሌላ በኩል የአንድን የፖለቲካ ድርጅት አቅም ከሚያመነጩት ዋንኞቹ፤ ማገር የሆኑ ችግርን መሸከም የሚችሉ ነጻ የሲቢክስ ድርጅቶች መኖራቸው ነው። ይህም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ህልም ነው። 

ዛሬም እንኳን በማረተው መንፈስ ነው ለቀጣዩ ምርጫ ቦርድ መሰናዶ አደረኩ እያለ ልባችን የሚያወልቀው ኢህአዴግ፤ የፈለገውን ይሰርዛል፤ የፈለገውን ይቀባልል፤ የፈገውን በራሱ ጊዜ ያሰናበትል፤ የተደራጀውንም እንደ ጠላት አጋር ያፈርሳል። የዴሞክራሲ ግንባታ ምንትሶ በሚ/ር መ/ቤት ደረጃ እንዳለ አዳምጫለሁኝ ይህም በአዲስ መልክ በገለልተኛ ወገኖች ለማደራጀት ሃሳቡም ፈቀዱም የለም። እኔ አብይ ሆይ አቤቱታዬ ላይ በስፋት አቅርቤው ነበር። ለነገሩ ኢህአድግ ተብዬው መቼ ፓርቲ ሆነ እና።

በዚህ ሁሉ ጥልቅ በሆኑ ንድፈ ሃሳባዊ ሚዛን ሲታይ የጠ/ ሚር አብይ አህመድ መንፈስ ጥረቱ እና ውጤቱ አንቱ ነው። ነገር ግን አሁንም ገና እራሱን እንደ ፓርቲ ሳይቆጥር መጀመር ካለበት የፖለቲካል ፓርቲ አደረጃጃት መሰረተ ሃሳብ ላይ ተነስቶ ራሱን አሂሶ ትክክለኛውን መንገድ መከተል አለበት ብዬ አስባለሁኝ። በዚህ ስሌት መሪ ነኝ የሚለውም ኢህአዴግም ሆነ ተፎካካሪ / ተቀናናቃኝ / ተቃዋሚም ይባል እኩል ናቸው። የሚበልጥም የሚያንስም የለም። ልዩነቱ አንዱ ባለጠበንጃ ባለ ባጀት መሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ይህ የሌላቸው መሆኑ ብቻ ነው።

ስለዚህ ቀጣዩ ምርጫ ላይ ሁሎችም በዚህ መስመር ከቀጠሉ የደጋፊዎች ፉክክር እንጂ የፖለቲካ ድርጅት ፉክክር አይሆንም። ስለ ፓርቲ አደረጃጃት መርህ እና ሂደቱ ሊሆንም ስለሚገባው ነገር በቀጣዩ ሳምንት የምለው ይኖርኛል። 

ምክንያቱም ደጋፊዎቹ እራሳቸውን እንደ የፓርቲ አባላንት ስለሚቆጥሩት። ብዙ ሰውም ለአሳር እና ለፍዳ የተጋለጠው በዚህ ምክንያት ነው። የፓርቲ አባልነት የጫጉላ ሽርሽርም አይደለም። ግዴታ ውል የሌለበት የፓርቲ አባልነት ፕላኔታችን አስተናግዳ አታውቅም።

ለወዘተረፈ ችግራችን ደግሞ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጀት ያስፈልጋል። የቆረጡ፤ የወሰኑ፤ ለዓላማቸው ሌት ተቀን የሚተጉ፤ ህዝባዊ አገልግሎትን እንደ ጸጋ የሚያዩ።

አባልነት የጀምላ ተመልካችንት አይደለም። አባልነት ህይወትን መስጠትም ነው። ኑሮን መስጠትም ነው። በዚህ ዙሪያ የቀደሙት መርህ የተከተለ የታወቀ አባላት እንደሚኖራቸው አስባለሁኝ። የአንድ የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊ ማለት አባል ማለት አይደለም፤ አባል ማለትም ደጋፊ ማለት አይደለም። የሰፋ ልዩነት ነው ያላቸው።

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሽንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
ውዶቼ የእኔ ክብሮች ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።