አላዛሯ ኢትዮጵያ አምላክ አላት።
የትውልዱ ብክነትን ለማስቆም ከቶ ለማን
አቤት ይባል?
„አቤቱ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ?“
መዝሙር ፲፪ ቁጥር ፩
ከሥርጉተ©ሥላሴ
08.10.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።
ከቶ የአማኑኤል አባታችን ሥጦታው እንዴት ይዞችኋዋል?
እኔ ፈጣሪ በቃቸሁ አለን የሚል ዕምነት ነበረኝ። ግን የሆነ አልመሰለኝም። ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል የሚስፈልገው የአዕምሮ ላውንደሪ ነው። የ50 ዓመት የሴራ ፖለቲካ ባህል አሁንም አለ እንዳለ። ይህን እንለውጣለን ብለው የተነሱት የለውጥ ሐዋርያት ትግላቸው ከራሱ ከሊሂቃኑ ህሊና ጋርም ጭምር ነው።
በምን ኦሞ አጥበው ከአዲሱ የአሰተሳሰብ መንፈስ ጋር ሊያዋድዱት እንሚቻላቸው ብርታቱን ይስጣቸው። እነኝህ የበቀልን ዓውደ ለመደምሰስ የተነሱ አዲስ ቡቃያዎች ያን የቆዬውን የታቆረ የሴራ የሽምቅ ውጊያ አስወግደው የእነሱን ንጹህ ድንግል አሰተሳስብ እንዴት ማዋለድ እንደሚችሉ ፈተናው ውሃ ያዘለ ተራራ ሆኖ እዬታዬ ነው።
ራሱ የፖለቲካ ሊሂቃኑ ለመለወጥ ያላቸው ፈቃድ ምን ያህል ይሆን? ራሳቸውን ማሸነፍ ቢችሉ አባሎቻቸውን፤ ደጋፊዎቻቸውን በዚህ አዲስ የአስተሳብ ባህል ለመቀረጽ እንዲህ አይችግርም ነው።
የዬትኛውም የፖለተካ ድርጅት ይሁን ንቅናቄ ይሁን ግንባር መጀመሪያ ከራስ የመነሳትን ተጋድሎ መጀመር ያለበት ይመሰላል። ራስን ሳይለውጡ ተከታይን ሆነ አባልን መለወጥ ፈጽሞ የሚቻል አይመስልም።
ለውጡ ወረቀት ላይ አይደለም። ለውጡ ከውስጥ መሆን አለበት። አንድ ሊሂቅ የዘመተበትን ሌላኛውን ሊሂቅ ራሱ ሄዶ ይቅርታ አድርግልኝ ካላለ አሁንም ቦክሱ ቀጣይ ነው የሚሆነው። ተጎጆው ደግሞ ሰላም የመናፈቀው ህዝብ ነው። አሁንም እንደ ትናንቱ መካሰስ ስሞታ ወዘተ ...
ታምቆ የቆዬው ቁርሾ እና ሴራ ነው አሁን ደግሞ ጭልጭል የምትለውን ብርሃን ለማጥፋት ፈተና የሆነው። ልምድ ተመከሮ የሚባለው ነገር ለዚህ የጭላንጭል ብርሃን መሆን ካልተቻለ ትውልዱ እንዴት ከብክነት ይድናል?
ሰማይ ተሂዶ ፈጣሪ እምጠይቅበት ሁኔታ ቢኖረኝ ይህን የሴራ ፖለቲካ መርዝ ከእያንዳንዱ የሥልጣን ፉክክር ከሚያደርግ የፖለቲካ ሊሂቅ ህሊና የሚወጣበትን ፈወስ እንዲያደርግ ልዑል እግዚአብሄርን ራሴ ሄጆ እጠይቀው ነበር።
በአንድነት ለውጡን እንደግፋለን ይባላል ነገር ግን ደግፈናል የሚው አካል ራሱ አልተለወጠም፤ ሴራውን ታቅፎ፤ ሸሩን አዝሎ፤ ተንኮሉን እሽሩሩ እያለ በተገኝችው ቀዳዳ ሁሉ ክፉ ነገር እዬረጨ ትውልዱ የብክነት ተጠቂ እዬሆነ ነው።
ከእኔ በፊት የነበረው ትውልድ ጠፋ በሴራ ፓለቲካ፤ የእኔ ትውልድም እያዬሁ በሸር ከሰመ፤ አሁን የሚፈለገውም አዲሱ እኛን የሚተካው ትውልድ ብክንት ናፍቆት እንዲቀጥል በሴራ ደቦ መተብት ነው። ዘመኑ የወጣቱ ነው፤ ዘመኑን እንደራሱ አደርጎ መቅረጽ እና መምራት ያለበት ወጣቱ ሆኖ ሳለ ያለፈው የተላለፍነው ዕድሉን ዛሬም እኔ ነኝ ብሎ ቸክሎ ይኸው ይታመሳል አይዋ የሴራ ተቸክል እና የሴራ እንቸክል በደቦ።
የሰው ልጅ ትውልድን ለማስቀጠል ነው የተፈጠረው እንጂ ትውልድን ለማባከን አይደለም። አሁን የሰሞናቱ የአቶ ዳውድ ኢብሳ ቃለ ምልልስ የሳቸው ትውልድ ተፍቶበታል ተበትኖበታል፤ ከሳቸው የቀጠለው ትውልደ ከስሎበታል አሁን ዘመናቸውን ጨርሰው አሁን ያለውን ትውልድ ዕድል በመሻማት ደግሞ ለማክሰም ተግተው እዬሠሩ ነው። እግዚኦ!
- · የትውልድ ብክነት በዬፈርጁ።
„ትጥቅ ፈቱ መባል አንፈልግም” - አቶ ዳውድ ኢብሳ የኦነግ ሊቀመንበር
ትጥቅ መፍታት የሚባል በጣም ሴንሲቲብ ጥያቄ ነው። ትጥቅ ፈታ አይባልም። ትጥቅ ፈታ ትጥቅ ፈቱ መባልንም አንፈልግም። ምክንያቱም ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለው ምንድን ነው? ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዱ ትጥቅ የሚፈታ አንዱ ትጥቅ የሚያስፈታ ይመስላል። አይደለም እንደ እሱ አይደለም የመጣነው። አጠቃላይ በሰላማዊ አገሪቱ ሰላም እንድትጠበቅ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ያለው ሚና „ፕሬዚላዊ ?“ እንዴት እንደሚሳተፍ በዚህ ውስጥ የእኛ ሚና ምን እንደሚሆን በዚህ ነው የተሰማማነው።“
ይህም ማለት ድርጅቱ ኦነግ በሰላማዊ እና በትጥቅ ትግሉን በሁለገብ መልኩ ይቀጥላል ማለት ነው። ይህ እንግዲህ ፍቱት በሚለው እርእስ ትናንት ያቀረብኩት ይህን መሰረት ያደረገ ነበር። ቀጣዩ የዛሬውን ሦስት ጉዳዮች እናያለን የሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃት፤ ነገረ ቡራዩ እና ነገረ ቤንሻንጉል በዚህውም ዕይታዬን እከውናለሁኝ።
- · የሰኔ 16 የቦንብ ጥቃት እና የአቶደ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ ዕይታ።
እንዲህ ይላሉ የኦነግ መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዋልታ ቴቪዥን አወያይ ለቀረበላቸው ጥያቄ
„ወ/ሮ ገነት የምትባል ወይንም ደግሞ ሳምበዲ ታምራት የምትባል ስሟም በደምብ አይያዝም ኤኒ ወይ ሚዲያ ላይ የወጣው አሁን ያልከው እንደዚህ የምትባል የኦሮሞ ኦነግ አመራር ውስጥም ይሁን ኦነግ አባል ውስጥም የለችም። እንደዚህ የሚባል በሚዲያ ከሰማን በኋዋላ ምን አልባት ደጋፊ ውስጥ ካለች ብለን ብዙ ፍተሻዎች አደርገናል፤ ናይሮቢ ኬኒያ ውስጥ ምንም የዚህ ዓይነት በእኛ አባል ደጋፊ እንደ ሌለ አረጋግጠናል አንድ እሱ ነው። ሁለተኛ ግልጽ በግልጽ አልሰማነም አላዬነም ይህንም በዚህም በተደረገው የቦንብ ጥቃት ውስጥ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር እጅ አለበት የሚል የመንግሥት ክስ አለሰማነም። እንዲሁ ወደዛ የኦነግ ሥም የመጠራት እንደዚህ ዓይነት „እንትን“ አለ ይህ ትክክል አይደለም ብለን ነው በእኛ በኩል እምንወስደው ምክንያቱም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በዚህ ውስጥ እጁ ንጹህ ነው። ይህን መቶ በመቶ እንተማመናለን።“
ይህ ማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ሊገልጸው ያልፈለገው ዕውነት አለ የሚል ዕድምታ ነው ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ጭብጥ እኔ ስነሳ። መንፈሱ የኦነግ የሆነ በራሱ በአንዱ በኦሮሞ ድርጅት ውስጥ ያለ ቡድን የፈጸመው ሊሆነም ላይሆንም ይችላል ነው እሳቸው የገለጹት። እሳቸው በራሳቸው ድርጅት ውስጥ ድርጊቱ ያልተፈጸመ ስለመሆኑ እርግጠኛ ሆነው ነው 100/100 የገለጹት፤ ስለዚህ የቀድሞው ኦህዴድ የዛሬው ኦዴፓ ራሱንም መፈተሽ ይኖርበታል ማለት ነው። ምክንያቱም ያን ጊዜ ከውጭ የገቡ ተፈካካሪ ፓርቲዎች አልነበሩም እና ከእነ አቶ ሌንጮ ለታ በስተቀር።
ከዚህ ጋር የማይታለፈው የቆሞስ እንጂነር ስመኘው በቀለ ህልፈትም አብሮ ሊንኩን መምርመር ያስፈልጋል። አቶ ዳውድ እሚሉት ይህን ነው። በኦነግ ሥም ማለት ኦነግ ማለት አይደለም ነው የሚሉት እኔም እንዲሁ ብዬ ጽፌያዋለሁኝ ግልጥ ሆኖ ይቅርብ ብዬ በጅምላ በ ኦነግ ሥም መባሉ አልተመቸኝም። የትኛው?
በሌላ በኩል ግን የኦነግ መንፈስ አንድነት እንዳለው በአቶ ዳውድ ኢብሳ አቀባበል ሆነ 5ቱ የኦሮሞ ድርጅቶች የሰጡት መግለጫ አንድም አምስትም እንደሆኑ አጢነናል። አክቲቢስቶቻቸውም እያዳለጣቸው የሚነግሩን ይህኑን ነው።
ኦህዴድ/ ኦደፓ በሚያሰተዳድራው የጸጥታ አካላትም የታዬው ይህው ነው።፡
አቶ ጃዋር ማህመድ ከዶር አብይ አህመድ እና ከአቶ ለማ መገረሳ ጋር ግንኙነት አለህ ወይ ሲባል ከሌሎቹ ጋር ነው ብሎ ፍርጥ አደርጎ ነገሮናል። ሌሎቹ እነማን ናቸው? ይህን ዶር ለማ መገርሳ እና ዶር አብይ አህመድ ከልባቸው ሆነው ሊመረምሩት ይገባል? ዕውነቱን በመግለጽ ቢያንስ ራሳቸውን ነፃ ማውጣት ይኖርባቸዋል። ያልጠራ ነገር አለ። የጎሼ እንቆቆ።
ሌላው የሚገርመው ጉዳይ ግርዶሽ ለመስራት የሚታትሩ ጸሐፍት ይሁኑ የኦዴፓ አካላት ዕውነት ራሷን አጥርታ የምትመጣበት ቀን ስለሚኖር ወንጀሉን አጥርቶ ማቅረብ ይገባል ቢያንስ ለህሊና። ጉዳዩን ከራሳቸው ለማረቅ ነበር ሲታገሉ የታዩት። "ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ" ... እንዲሉ።
ቀጣዩም አቅጣጫው የሚያመለክተው በግንባሩ ውስጥ ያሉ ግን የኦነግ መንፈስ የጠመቃቸው ወገኖች እጅ እንዳለበት ጥርጣሬ ያሳድራል፤ መክደኛው ተበራከተ።
መመሰጠሩም አና አለ። ማድበስበሱም አገር ገዛ።
… የኢትዮጵያ መንግሥት በቀን ሦስት ጊዜ ሲሰጥ የነበረው የመረጃ ቅጥ የለሽ ዝብርቅ ዝበት የፍርድ ቀን መራዘም ወዘተ ሁሉም ተዳምሮ ኢ- ታማኝነት ምንጩም ራስን በራስ ለማጋለጥ አቅም የማነስ ጉዳይ ይመስለኛል።
ወንጀል በታቀፈ ቁጥር ራሱን በራሱ እያጣፋ ከመበራከት አልፎ የሚከላከልለትንም ይውጣል። ቢያንስ ለወንጀሉ ተባባሪ አለመሆን የሚለካው ወንጀልን ለወንጀልኛው ማሸከም ሲቻል ብቻ ነው። የራሰም ወገን ቢሆን። አሁን ተዚህ ላይ ማን ይብለጥ? ፍትህ? ህግ? ኢትዮጵያ ወይንስ ህውከት ፈጣሪ የራስ ገበር?
- · ነገረ ቡራዩ እና ዕንባው።
አቶ ዳውድ ኢብሳ ቀጥለው ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ …
„ስለ ነገረ ቡራዩ መንግሥት ግልጽ አድርጎ አላወጣውም ይህ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች መንግሥት ነው ግልጽ አድርጎ ማውጣት ያለበት እገሌ እገሌ በዚህ ቦታ ተገኝቷል፤ ይህን ሲሳራ እግሌ ደግሞ በዚህ ቦታ እንደዚህ ይህ የፖሊስ „እንትን“ ነው ሌላ እንዲሁ የሰው ጡት ተቆረጠ እንደዚህ ዓይነት ብዙ ሰው ሞተ እንደዚህ ተብሎ ብዙ ይወራል። በዚህ ውስጥ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሩም ድርጅቱም ወይም ደግሞ አባሎቹም የዚህ ዓይነት ፖሊሲ የለንም አደርገንም አናውቅም“ ይህቺ "እንትን" የሚሏት ነገር ቃሉን ቢያወጡት መልካም ሲሆን በአገላላጹ ግን የእነሱ ጠረን እንዳለበት ይገልጻል አገዳደሉ ላይ ነው ግፋዊ፤ አሰቃቂ የሚለው ብዙም ያልተመቻቸው እንጂ …
ይህም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ ወደ መጀመሪያው ሃሳብ ይወሰደናል የኦህዴድ/ ኦዴፓ ፖሊስ ባለበት፤ የመንግሥት አካል ባለበት በአደባባይ የተፈጸመ ጭፍጨፋ ስለሆነ ይህም የኦዴፓ አመራር አካላትን በቀጥታ ተጠያቂ የሚያደርግ ነው ባይ ናቸው ይግለጡት የሚሉት ይህንኑ ነው።
እኔ በኦዴፓ ውስጥ ያሉ አካላት ከለውጡ ጋር ያላቸው መስተጋብር ጥርት ባለ መልኩ ራሱን የቻለ አብዮት ያስፈልጋዋል ብዬ ነው እማምነው። አሁን እኔ ቲም ለማ ለማለት ሁሉ አቅም እያነሰኝ ነው።
ሁለት ሰው ቲም ለማ ለማለት እየከበደ መጣ … በዛ ላይ ወንጀለኛን የመሸፍን ሁኔታ ከታሪክ ከትውፊት ጋር እንዳይጣበቅ ለጥንቃቄም መሆነን ብረዳም "ወትሮ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ" ያሰኛል።
አሁን በአቶ አዲሱ አረጋ ይሆን በአቶ ታዬ ደንኣ በዬጊዜው የሚሰጠው መግለጫ ይሁን የሚጻፈው አጭር የግርጌ ማስተዋሻ አንድም ቀን ከልቤ ገብቶ አያውቅም። ስልባቦት ነገር ነው። ምክንያቱም መደባቸው ከዬትኛው ጎራ ስለመሆን ዝንቅ መንፈስ ስለማይበት።
ስለዚህ ነው አጤ ዳውድ ኢብሳ ቁልጭ ባለ ቋንቋ ራሳቸውን ይጠይቁ፤ ደፍረው ለመናገር ምን አስፈራቸው ይናገሩት የሚሉት። የእኛም ወንጀል ከሆን ይነገረን ነው እያሉ ያሉት … ማን ምን የት ቦታ ብለው ዘርዘረው ግልጽ መረጃ ይሰጡ ባይም ናቸው። ትክክል ናቸው።
እኔ ከዚህ አገላለጻቸው እንደተረዳሁት ማህል አገር ብዙም የአቶ ዳውድ ኢብሳ አባል እንደሌላቸው ነው የተረዳሁት። ይህን የፈጸመው አሳፈጻሚው የፌስ ቡክ ፓርቲም ሊሆን ይችል ይሆን የሚልም ሌላ አቅጣጫ አመልካች ጉዳይም አለበት። ለነገሩ ይህን ያህል ዘመን አንዲት ቆራጣ እራፊ የመታገያ መሬት አልበረውም ራሱ ኦነግ በግዞት እንደ ኖረ ሁላችንም እናውቃለን። በፕሮፖጋንዳ አጥሚት ሞገድ ላይ ነው ነፍሱ ትርትር ስትል የባጀችው።
ጊዜ የሚሰጠውን የእናት ልጅ አይሰጥም እና የኦሮሞ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይሁኑ አክቲቢስቶቻቸው የመንፈስ ጋብቻ ከኦነግ ጋር እንዳላቸው ነው ወቅት እኛ ባልጠበቀነው በፈጣሪ ረቂቅ ክህለ ሥልጣን እዬተገለጸ ነው።
ሌላም ወቅት የሚገልጸው የየጠ/ ሚር አብይ አህመድ ሌጋሲ ያልተመቻቸው እና ሳንክ እዬፈለጉ ማጎሳቆል፤ መነሰት የራሳቸው ወገኖች መፈለጋቸውንም እያዬን ነው - እራሳቸው እራሳቸውን እዬታገሉት ነው። የዚህን ታሪኩን፤ ዕድሉን ለመስበር እዬታተሩ ነው። በኮፒ ራይት ሁኔታ ነው እዬታመሱ ነው የሚገኙት።
በጣም የሚገርመው ቸኮሉ፤ አደብ ነሳቸው፤ ተጣደፉ ሥልጣናቸውን የበላይነታቸውን ለማሳዬት እዮባዊነት ጎደላቸው። ይህ ችኮላ እና ጥደፊያ ነው ዶር ለማ መገርሳን ሆነ ዶር አብይ አህመድን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው። ይህን ሁለቱም ሊሂቃን በቅኔ ሲናገሩት ቆይተዋል ግን አድማጭ አላገኘም እና ነገን አስፈሪ አድርጎ አመጣው። ፉክክሩን የችግሩ ቁንጮ ደግሞ … የጦስ ዶሮ የሆነችው ኢትዮጵያ ናት። የተፈራው ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ነው። ይህ የ የአምክንዮ ጭንቅላት ማህበረ ኦነግውያንን በአንድነት በአንድ ሃሳብ እንዲሰባሰቡ አደረገ።፡
ቅደስት አገር ኢትዮጵያ ከውሳጣቸው ሳትኖር በለማ አብይ አሻጋሪነት ያን ተጠልለው ፕሮጀክታቸውን ለማሳከት ነው እዬታተሩ ያሉት። የተጸዬፉትን ማንነት በመቀበር ህልማቸውን ማሳካት ነው ትልማቸው።
አደብ በማጣቸው ምክንያት አሁን ሁሉም ወደ ራሱ ተመልሶ ሂደቶችን ማጥናትን ፈቀደ። አብሶ የብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ተጋድሎ ያደረጉ ከ1000 ሺህ በላይ የታሰሩ የአዲስ አባባ ወጣቶች እስር ባለቤት አልባ መሆን እና የቂም ማወራረጃ መሆን በተደሞ ዘመኑን እንመረምር ዘንድ ግድ ብሏል።
በዚህ ውስጥ ንጹሃን የደከሙለት መንፈስም ታመመ፤ አደብ ያጡት የኦሮሞ ሊሂቃን እና አክቲቢስቶች መልካሞች ያፈሩትን ንዑድ መንፈስ አብረው እያሾቁት ነው። ለዚህ ነው እኔ አማራ ክልል ማጥናት ያለበት ግዕዝ ቋንቋ ነው የምለው።
በዬትኛውም መስፈርት አማራ የአባቶቹን የፍልስፍና፤ የልቅና፤ የምርምር፤ የጥበብ፤ የጥልቅነት፤ የሚስጢር ሌጋሲ ለማስቀጠል እጬጌው ግዕዝን ማጥናት ለድርድር ሊያቀርበው አይገባም። ወላጆችም ከአሁን ይህን ማሰተማር መጀመር ይኖርባቸዋል። ነገን ለማደራጀት ከዛሬ መጀመር ያስፈልጋል።
- · ወጣ ገቡ የኦሮሞ ሊሂቃን …. ዕይታ
ዕውነት ለመናገር የመንፈስ ጫና በገፍ በዬአቅጣጫው መልቀቅ ሆነ በጠቅላላው ባዬነው ነገር ልባችን ከውስጡ እንኩት ብሎ ተሰብሯል። አንድ ዕውነት ግን መናገር የሚቻለው ጠ/ ሚር አብይ አህመድ እንሱ ባመረቱትም ይሁን በሌላ ገፊ ሃይል እና ጫና በሌጋሳያቸው ላይ የሚደረገው ጫና ሙሴናታቸውን ከህሊናችን በዬጓዳችን እዬተመጣ ማውለቅ የማይቻል መሆኑን ቢያውቁት መልካም ነው።
ከእነሱ ህውከት ብጥብጥ እና ልዩ ጫና በፊት ድንግሉን ሰብዕናቸውን እናውቀዋለን። ለምናውቀው ሰብዕና ህሊናችን ውስጥ ታትመዋል። ይዘልቃሉ ወይ የሚለውን ጊዜ የሚፈታው ይሆናል። ምክንያቱም ዕውነትን የሚወገን መንፈስ ዘመድ አልቦሽ ስለሆነ። ዕውነት ስታነባ ቢያንስ ጥግ መሆን ግድ ስለሚል። በሌላ በኩል ግን ከእንግዲህ በማመን እና በመታመን ያለው ድልድይ ስለተሰበረ በቸልታ የምናልፈው ጉዳይ አንድስም እንኳን አይኖርም። ዕድሜ ለእነሱ ትልቁን የማስጠንቀቂያ ድወል ደውለውታል። ለዚህ ላመሰግናቸው እሻሉኝ። ምስጋናዬ የለበጣ አይደለም። የሚሳዛነኝ ግን የቅኖች ድካም ነው።
በዚህ ውስጥ ሁሉንም ለማስደሰት ጠ/ ሚር አብይ አህመድ የመንታ እናት እንደሚሉት ነው የሆኑት ወይንም የሁለት አገር ስደተኛ እንደሚባለው … በራሳቸው ድርጅትም ውስጥ የሳቸውን ሌጋሲ ቀውስ ውስጥ ለመጨመር የማይተኙ መንፈሶች እንዳሉ ቀደም ሲል እኛ በግል ጠረኑን ቢሸተንም የአሁን የአቶ ዳውድ ኢብሳ ቃለ ምልልስ ፍንጩን አጠናክሮታል።
አብሶ የሰኔ 16 ሆነ በውሽማ ሞት እና የተከደኑት እሳቸውን የማስወገድ ድራማዎች በእዮር ወታደሮች ይመረመር ዘንድ የቤት ሥራውን መስጠቱ ይቀላል።
አሁን በራሱ በኦህዴድ / ኦዴፓ ያሉት አኩራፊዎች እዬተሸነፉ ሲመጡ ሁሉንም ነገር ጠቅልለው "በኦነግ ሥም" ማሳበቡ ብዙም ለእኔ ህሊና ወቄቱ ሊዳፋ አልቻለም። በማነኮሩ፤ በመደቆሱ፤ በመፍጨቱ ሁሉም አብሮነት አለበት ባይም ነኝ። ለዚህ የመስቀልን በዕል አከባበር እና የሬቻ በዓል አከባበር ዋንኛው ማመሳከሪያ ሰነዳችን ነው።
አንዱ በፋቲክ ሌላው በሰናይ ነበር የተከበረው። ሌላው የኦነግ አርማ እና የኢትዮጵያ ልሙጡ ብሄራዊ ሰንድቅ ዓላማ ጉዳይም እንዲሁ ነው። አንዱ በካቴና ሌላው በፍሰሃ። ይህ ማለት ቅንነት ጠፍቷል፤ አሸናፊ ሆኖ የሚታዬው የኦነግ ሥነ - ልቦና ስለመሆኑ እያዬን ነው።
በዚህ ውስጥ ግን የኦሮሞ አዲስ ትውልድ ብክነት ናፍቆት ያለባቸው እኩይ መንፈሶች ረፍት አጥተው እዬባተሉ ስለመሆኑ እያዬን ሲሆን አልፎ ተርፎ የቤንሻንጉል ጉምዝ ነዋሪዎች መከራም ከዚህ ቁጣ ጋር የበቀል ማወራረጃ መሆኑ ውስጥን በሰደድ እሳት የሚቀጣ ነው። ይህ የህዝብ መከራ ህጋዊ እውቅና ተሰጥቶ የልቡን ሲከውን ደሃ ደግሞ አሳሩን ይከፍላል።
- · ቤንሻንጉል ከፋ ወለጋ …
የኢትዮጵያ አዲሱ አጤ አቶ ዳውድ ኢብሳ እንዲህ ይላሉ … ለዋልታ ቴሌቪዥን ጠያቂ ...
„ከፋ አካባቢ የእኛ ሰራዊት የለንም። ስለዚህ የከፋው ምን ዓይነት እንደሆነ እንፎርሜሽኑ በትክክል ወደ እኛ መምጣት አለበት። ቤንሻንጉል ጉምዝ ያልከኝ የተባለው ያልከኝን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎች እነዚህ የቤንሻንጉል ጉምዝ „እንትኖች“ ላይ ጥቃት አድርሰው ሰው ገደሉ ነው። ይሄ ነው „እንትን“ ያለው ይሄ ሆኖ ከሆነ እኛ በበኩላችን ፎርማል ለእኛ ቀርቦ ምርመራ እናደርጋለን ከዛ በኋዋላ ለዬቲ ይቀርባል፤ ቅጣት ይቀርብበታል፤ ፔሬድ ከዚህ አያልፍም፤ አልፎ ተርፎ ግን በዚህ አሳቦ ጦርነት መክፍት ጦርነቱን አስፍቶ ብዙ ህዝብ መግደል እና ማፈናቀል ከዚህ ጋር አይገናኝም፤ ምንም ግንኙነት ሊኖረው አይችልም።“
- · ዕንባን እያዘራን እስኪ ትንሽ እንከፋፍተው … አዬር ይግባለት ይህ መታበይ …
„ከፋ አካባቢ እኛ ሰራዊት የለንም። ስለዚህ የከፋው ምን ዓይነት እንደሆነ እንፎርሜሽኑ በትክክል ወደ እኛ መምጣት አለበት።“ በዚህ ላይ ሁለት ነገር ይታያል፤ አንደኛ የአቶ ዳውድ ኢብሳ የጦር ማዘዣ ጣቢያ ተፈቅዶለት አዲስ አባባ ኮማንድ ፓስቱ መቀመጡን፤ እና መንግሥት ስለሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአቻው የኦነግ መንግሥት ደረጃውን የጠበቀ መረጃውን በትክክል መላክ እንዳለበት ትእዛዝ የሰጠበት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ „የከፋው አጥቂ ሠራዊት“ የሌላኛው የኦነግ ቅርንጫፍ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል፤ ይህም ብቻ አይደለም አፈንጋጮችም ወይንም አኩራፊዎችም ያደራጁትም ሊሆን ይቻላል። ማን ያውቃል?
ለዚህም አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመረጃ ውጪ እንደሆኑ እንደማያውቁትም ነው የሚናገሩት። ከካፋው ሠራዊቱ አዛዥ ጋርም ግንኙነት እንደሌላቸው ነው የሚናገሩት። በሠራዊት ደረጃ የኦነግ መንፈስ ተጋሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የ አብይን ሌጋሲ በማጥቃት በመወጠር ፕሮጀክት ላይ ገና ስምምነት እንዳልደረሱም ሚስጢር አለበት። ብቻ ዬትም ቦታ በዬትኛውም ሁኔታ የአብይን ሌጋሲ ማወክ እንዳለ ያሳያል። የጦርነቱ ቀጠና በጣምራ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የዓላማው ዓይነት ድፍን ነው። ለዚህም ነው ብንፈልግ "ኦሮምያን ለመገንጠል ዛሬስ ማን ያዘን" የተበለው።
- · ህም!
ወደ ቀደመው ምልስት ሲሆን „ቤንሻንጉል ጉምዝ ያልከኝ የተባለው ያልከኝን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎች እነዚህ የቤንሻንጉል ጉምዝ „እንትኖች“ ላይ ጥቃት አድርሰው ሰው ገደሉ ነው። ይሄ ነው „እንትን“ ያለው ይሄ ሆኖ ከሆነ እኛ በበኩላችን ፎርማል ለእኛ ቀርቦ ምርመራ እናደርጋለን ከዛ በኋዋላ „ለዬቲ“ ይቀርባል ቅጣት ይቀርብበታል፤ ፔሬድ ከዚህ አያልፍም፤“
„ሰው ገደሉ ነው“ ሰው ለእሳቸው ምንም ነው። በቃ ትንኝ። የት ላይ ነው ይሆን የሚነሩት? የትኛው ዘመንስ? ከ70 ሺህ በላይ ለተፈናቀለ ህዝብ አንድ ሰው ከቀጣንልህ ይበቃሃል ከዚያ በላይ ምን ትፈልጋለህም ነው። ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ፌድራዊ መንግሥት በአቶ ዳውድ ኢብሳ ለሚመራው የኦነግ ለመንግሥታችን በትክክል ሁኔታው በህጋዊ ሰርኩላር ደብዳቤ ያሳውቀን፤ ያቅረብ እና በእኛ ችሎት ይመረመራል፤ ጥፋት ከሆነ አጥፊው ይቀጣል ነው የሚሉት። የቤንሻንጉል ጉምዝ እንትኖች ነው የሚሉት … ፈጣሪ በአምሳሉ የፈጠረው ሰው እንትን? እም። „ዩቲ“ ቃሏ አልገባችኝም። „እንትንም“ የልሳናቸው መድፊያ ናት። የአንድ አገር መሪ … ህም!
ተዚህ ላይ ነገረ ቤንሻጉል አለይ ልባሙ ነገር የእነሱ እጅ እንዳለበት በትክክል ያመኑበት ይመስላል። ለዚህም ነው እነ አቶ አዲሱ አረጋ ግልጽ በሆነ አቋም ትጥቅ ኦነግ እንዲፈታ የሚፈልጉት። ግልጽ ሆኖ ስለወጣ፤ ከዚህ ውጭ ያለው ግን የውሽማ ሞት ነው። ደፍሮ የሚናገራት የለም። የሆነ ሆነ አቅም አለን መንግሥት ነን፤ እንከባባር ነው ጭብጡ የሚለው።
- · ይቅጥላል ማያያዝ ስለሚያስፈልግ የቀደመውን ልጨምር እና ...
„የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎች እነዚህ የቤንሻንጉል ጉምዝ „እንትኖች“ ላይ ጥቃት አድርሰው ሰው ገደሉ ነው። ይሄ ነው „እንትን“ ያለው ይሄ ሆኖ ከሆነ እኛ በበኩላችን ፎርማል ለእኛ ቀርቦ ምርመራ እናደርጋለን ከዛ በኋዋላ „ለዬቲ“ ይቀርባል ቅጣት ይቀርብበታል፤ ፔሬድ! ከዚህ አያልፍም፤ አልፎ ተርፎ ግን በዚህ አሳቦ ጦርነት መክፍት ጦርነቱን አስፍቶ ብዙ ህዝብ መግደል እና ማፈናቀል ከዚህ ጋር አይገናኝም፤ ምንም ግንኙነት ሊኖረው አይችልም።“
አሁን ከዚህ ላይ ለማስፈራራት፤ ጫና ለመፍጠር ያሰቡት ነገር ወደ አደገ ሁኔታ ተሻግሮ እንዳይመነጡሩ፤ የሚቆጣጠሩትን የተቆናጠጡበትን መሬት እንዳያጡ ስጋት አድሮባቸዋል። ገና እንቡጥ ነውና ሽምቅ ተዋጊያቸው። የሚያግዘንን የሚረዳነን ህዝብን እንዳትጎዱ፤ እንጎዳለን ብላችሁ ብትነሱ ዋ! ነው ቁምነገሩ።
ህዝብ አንዳይጎዳ ቢታሰብ እማ ኖሮ ከ50 ዓመት ያላፈራ ውጊያ በኋዋላ እንደ ገና ህዝብን ለውጊያ ማሰናዳት በውነቱ ህሊና ቢስነት ነው። ለመሆኑ ማን አስታጠቃቸው? ማነውስ ስንቅ የሚያቀርብላቸው? ማነው ሎጅስቲኩን የሸላማቸው? እንዴትስ አለፈላቸው?
የሆነ ሆኖ ለስንት ዓመት ለእነሱ ለማይድህ ዓላማ የኦሮሞ እና ልጅ ታቅርብ?
አብሶ የኢትዮጵያ መንግሥት ገና አልደረጁም ብሎ በዚህ ሁኔታ ተሸንግሎ በዝምታ ሁኔታውን አልፎ ጊዜ እስኪደራጁ የበለጠ እስኪሰፉ ጊዜ ከሰጣቸው ኢትዮጵያን በሰፊው ያሰጋታል።
በቀጥታ ገፈተው የሚሄዱት ወደ አማራ ክልል እና ወደ ቤንሻጉል ይሆናል። ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ጋርም አዲስ መስመር ይፈጥራሉ። ለዚህም ይመስላል በመንፈስ እኔ የማስተዳደረው ልዩ ክልል ቤንሻንጉል ላይ ይሰጠኝ ያለው የወያኔ ሃርነት ትግራይ። ቀደም ሲልም ካርታውን ሰርቶታል። ኦነጎች በቤንሻንጉል ቆርጠው ከገቡ ከሱዳን ጋር የሚገናኙበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው።
በኢትዮጵያ መንግሥት ያለው ቅጥ የለሽ መዘናጋት ኢትዮጵያን የሚያፈርስ ጥንስስ ሰለመሆኑ አጀንዳው ያደረገው አይመስልም። ደርግ እኮ ንቆ ንቆ ነው ወያኔ ሃርነት ለዚህ ድል የበቃው።
ሆኖም አያውቅም እኮ እንዲህ አይነት እንዝህላልነት። አገር አገነጥላለሁ የሚልን ቡድን በመዲናህ ማዘዣ ጣቢያ አስከፍትህ ኢትዮጵያን ለአደጋ መስጠት። ራስህ የሚወጋህን የሚያፈርስህን ዓርማውን ካለውለበለበ፤ በመዲናው ህዝብ ተስለፎ ካልተቀበለ ብለህ አውጀህ ማህል አዲስ አባባ የጦርነት ማዘዣ ጣቢያ ማድረግ፤ ለመወሰንም ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ ማቃት ይገርማል? የሚገርም የጉድ ክምር ነው …እዬታዬ ያለው ነገር።
ሌላው በጣም ስሜት የሚነካው ነገር ይህን ያህል ሰፊ ንድፍ ይዘው በሰላማዊ መንገድ ነው ልንታገል የመጣነው ደግሞ አሁንም ይላሉ። ከተማው ውስጥ ሽምቅ ውጊያ አለ ገጠርም ውስጥ ወደ መደበኝ ውጊያ ሊያድግ የሚችል አይነት ሁኔታ ነው ያለው። በዚህ ላይ የ ኢትዮጵያ መንግስት ቀበቶ ልል ነው። እግዚኦ!
የኢትዮጵያ መንግሥት እነሱን እያቆላመጠ መከራውን ተሸክሞ ተቀምጧል። በ ኢትዮጵያ መንግስት አቋም ዝንቅነት ደግሞ ሺዎች አሳራቸውን ብትን መሬት አጥተው ይንከራተታሉ?
ጊዜ የሚሰጠው የበለጠ እስኪደራጁ፤ የበለጠ እስኪፈረጥሙ፤ የበለጠ አቅም እስከሚያመርቱ ድረስ ይሆን? የእዮር የደህንነት ቢሮ ይመርምረው?
ቀድሞ ነገር የ ኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ግልጽነት የጎደለው ስለሆነ ለማመንም እኮ ከባድ ነው። በሌላ በኩል ለኦሮሞ ህዝብም ጠንቅ እዬተተከለበት ነው ያለው የፈረደበት ህዝብ። የ ኦሮሞ እናት በማረፊያዋ ጊዜ እንዲህ በግራ በቀኝ ታመሰች። በግልጽም ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አብዛኞቹ ሊሂቃን ለ ኦሮሞ እናት ዕንባ ግድ የላቸውም። ምክንያቱም ቅራኔ የሚያብስ እንጂ ቅራኔን የሚሸር አቋም የላቸውም። አቋሟቸውም ቋሚም ግልጽም አይደለም። ህዝብን ለፍትህ ማታገል እንዲህ አይገለጠም።
ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሆኖባት ኢትዮጵያም ፍዳዋን ከፈለች። ለዛውም ተፈቅዶላቸው፤ አትንኳቸው ተብለው እንደ ታቦት ተከብክበው። ይህ ግፍ ነገን እንዴት ሊያሰተናግደው እንደሚችለው እዮር ይወቀው፤ ኢትዮጵያ እንደሆን ከስማ የማትከሰም፤ ወደቃ የማትወደቅ አላዛር ናት። አምላኳ አላት …
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
የኔዎቹ ቅኖቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ