የዶር. ደብረጽዮን "አንጠልጥለን እንሰጣለን?"

የዶር ደብረጽዮን „አንጠልጥለን
እንሰጣለን“ ከምላስ
       ወይስ
ከአንጀት ተረቡ?
„ከቁጣው ጢስ ወጣ ከፊቱም የሚባላ
እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ።“
መዝሙር ፲፮ ቁጥር ፰
ከሥርጉተ©ሥላሴ
 16.11.2018
ከጭምቷ ሲወዘርላንድ።


                              ዘመን ሲሰጥ።

እንዴት አላችሁልኝ ውዶቼ? ትናንት አንድ ዜና ሽው አለኝ እና የውነት ይሆን ብዬ ስፈታትሽ እውነት  ነው ተባለ። ዶር ደብረጽዮን ገብረሚኬኤል ከህግ በላይ ማንም ስሌለ አንጠልጥለን እንሰጣለን በእነሱ ሥማችን አይጎድፍም ማለታቸው ነው የተደመጠው እድምታው በትርጉም ሲቃና። ግን ይህ የአፍ ወለምታ ነው ወይንስ የልብ?

እኔ አኮ እውነት ተናገሪ ብባል ዶር ደብረጽዮን በራሳቸው ፈቃድ ራሳቸው ጠይቀው አባታችን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቀሪዮስን ሄደው በአካል ሲጠይቁ ከህሊናቸው ጋር ምህረት አውርደዋል ብዬ ነበር። በረከት ይዘው ተመልሰዋል፤ ተባርከዋል፤ ተቀድሰዋል፤ ምርቃታቸውን ሳያባክኑ እንደ ሰው ተፈጥሮ ይሆናሉ የሚል ሙሉ ዕምነት ስለነበረኝ በሐሴት ራሱን አስችዬ ሁሉ ጽፌያለሁኝ።

ታዲያ ምን ይሆናል ከዛ ከተባረከው ተግባራቸው ማግስት እትጌ ትግራይ ጎራ ሲሉ ያው የለመደበዳቸውን ፉከራ ቀጠሉ፤ ይባስም ብሎም በራያ ሌላ ደም ፈሰሰ። እናም ደነገጥኩኝ። በወቃይትም ሌላ ርግጫ ቀጠለ።

በውነቱ እኔ ነገሮችን በቅንነት ስለማይ እግዚአብሄር ፈቅዶ ነው ይህን መልካም ነገር ሊያደርጉ ያነሳሳቸው ብዬ አስቤ ሰልነበር ከዛ ከቀደመው ትዕቢታዊ ጭካኔ ጋር ይፋታሉ የሚል እምነት ነበረኝ። የወሰዱት እርምጃ ደፋር ነበር። ብፁዕን አባቶቻችን እንኳን አገር ገባችሁ ለማለት ካለምንም ገፊ ሃይል ራሳቸው ጠይቀው ነበር አብረው ከጠ/ ሚር አብይ አህመድ ጋር የሄዱት እናም ያዮዋቸው።

አሁን ደግሞ እጅግ የሚገርም የሚደንቅም ድብልቅልቁ የወጣ መግለጫ በወጣ ማግሥት ደግሞ የወንጀል ተጠያቂን "አንጠልጥለን እነሰጣለን" ሲሉ አዳምጥኩኝ። ከሆነ እስዬው ነው የሰቲቱ መቀሌ ላይ ከተደገመ። በነገራችን ላይ የሰቲትን አወሮፕላን ማረፊያ ሳዬው ወልቃይት ጠገዴ ከወረራ እና ከሰቆቃ ነፃ የወጣ ያህል ነበር የተሰማኝ። ከቶ ዋዜማ ልበለው ይሆን? ትዝታው መጣብኝ። 

የሆነ ሆኖ መቀሌ ላይ ብቻ ሳይሆን የትግራይ ህዝብንም ከእስር ይልቀቁት በተምታታ መግለጫ አያዋክቡት፤ በተምታታ መግለጫ ማህል መንገድ ላይ አይገትሩት። መግለጫው እራሱ ሙሉውን ባላገኘውም የተሻለ ነው የሚባለው ማዘናጊያ ይባል ትጥቅ ማስፈቻ ተቆራርጦ የወጣው የሚገርም ነው የቃላቱ አነባበሮ ቁሮው። ራሱ ቁር ነው። 

ወደ ቀደመው ምልስት ሲሆን ከሁሉ በላይ ግን የለውጡ አካል እና አምሳል ከሆኑ? እስኪ ለዘመናት ለ40 ዓመታት የሰቆቃ መናህሪያ የሆነውን ኦሽትዝ ባዶ 6 ነፃ ያድርጉት? ባዶ 6 እኮ አንድም እስረኛ ተፈታ ተብሎ አልተሰማም። 

አዲስ አበባ ላይ ያልታወቀ 7 እስር ቤት የተገኜ ትግራይ ላይም  የወልቃይት እና የራያ በተለያዬ ቦታ የሚኖሩ የጎንደር እና የወሎ ልጆች እዬታፈኑ ተወስደው የተከዘኑበትን ቦታ እስኪ ይፍታህ ይበሉት። 

ዶሩ ሰው ለመሆን እስኪ ራሳቸውን ይድፈሩት። ጊዜ ታሪክን ይሠራል እና ከዛ ጭምልቅልቅ ካለው የሃጢያት ጉሮኖ ወጥተው ለራሳቸው ይፍታህ ይበሉት፤ ንስሃም ይግቡ እንደ ቀደሙት ...  

ጭካኔን ለትውልዱ ለማውረስ ከመባተል እስኪ የትግራይ ትውልድ እኛን አትውረሰን ቀደምቶችን ደጎችን ብቻ ውረስ ብለው እስኪ ይፍቀዱለት። እግዜሩ እኮ አዘቅዝቆ ያያል። የአሁኑስ ሰውኛ ነው፤ ተጠርጣሪዎች ብቻ ነው ተልይተው የሚታሠሩ እዮራዊ ቁጥ ከመጣ ግን ተራፊ የለም። 

በዚህ ውስጥ ህፃናት፤ ነፍስጡር እናቶች፤ አቅመ ደካሞች፤ ንጹሃን ዜጎች የመከራው ቤተኛ ይሆናሉ። በመጋቢት ወር እዮር ምልክት መቀሌ አቅራቢያ አሳይቷል። እኔም „ምልክት“ በሚል ስለ ራስ መንገሻ ዮሖንስ ታሪክን አጣቅሼ ዘለግ ያለ መጣጥፍ አቅርቤ ነበር። 

እዮራዊ ቁጣው በዚህም መልክ ላይሆን ይችላል፤ መሬት እሾህ ልታመርት ሰማይም እሳት ሊያዘንብ ይችላል። የሴት ልጅ ማህፀንም ለሰሚው የሚከብድ ነገር ፈጣሪ ሊሆን ይቻላል? እንሳሳ ሳይሆን ሰው ነው እንደ ጥንቸል ቤተ ሙከራ የሆነው? ለዛውም የራስ ወገን። ለሰሚው እኮ ግራ ነው?

ቢያንስ ዶር ደብረጽዮን ገብረሚኬኤል ለድርጅታቸው ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ሳይሆን ለራሳቸው ታማኝ ይሁኑ። በተጨማሪ የሚሰጡትን ውጥርጥር ያለ መግለጫ ደግመው ያንብቡት። ጊዜ ወስደው ይመርምሩት። የተጋሩ ሊሂቃኖቻቸው የሚሰጡት፤ የሚያረቁት ጹሑፍ ሳጅን በረከት ስምዖንን ጨምሮ ለቀጣዩ የትግራይ ትውልድ ጠቃሚ አይደለም። የተቃጠ ካርቦን ነው። 

የበዛ ግፍ እና መከራ ለልጅ ልጅ ልልጅ ተራፊ ነው። የዞግ አመራር መከራው ለራስ ብቻ ነው የሚቆለለው። ዜጋዊ ቢሆን ግን ለሁሉም ተደራሽ ይሆናል አሉታዊ ሆነ አዎንታዊ። አሁን የደረግ ዜጋዊ ስለነበር ተጠቂነቱ ሁሉም ነበር። እርግጥ ነው ሙሉው ስለፈረሰ አገር ተጎድታላች ምክንያቱም ጠቃሚና ጎጂ መለያ ማንዘርዘሪያ እንደ አሁኑ ብልህ መሪ ጥበብኛ መሪ ጠፍቶ። ለዚህም ነው አላዛሯ ኢትዮጵያ ተንበርክካ የዳኽቸው። 

ብቻ ብቻ ዶር ደብረጽዮን እስኪ ይሁንባቸው እና ባዶ ስድስትን ባዶ አድርገው ሙዚዬም ያድርጉት። በህይወት ዘመናቸው አንዲት ሽራፊ ታሪክ ይሥሩ እስቲ። እስኪ ይሁንባቸው እና የሰበሰቧቸውን የወንጀል ተጠርጣሪዎች ሁሉ ለማዕከላዊ መንግሥት ያስረክቡ ልዑል እግዚአብሄር ይቅር እንዲል፤ ልዑል እግዚአብሄር ፍርዱን እንዲአቀል። ቁጣውን ከላከ መቋጣሪያ፤ ማስቆሚያ አንዳችም ሃይል የለም እና።

ሁልጊዜም እንደምለው እኔ የላይኛው የእዮሩ ቁጣ ነው የሚያስፈራኝ። እስኪ አሁን እንኳን ራስን ቀጥቶ ተስተካክሎ ለመቆም ይሞከር። እስኪ ዶክተርነቱ በሁለት እግሩ የሚያቆም ሰብዕና ያላብስ። ከእንግዲህ በገዳዳም፤ በቀዳዳም፤ በወልጋዳም፤ በጋድምም፤ በሸንጣራም፤ በሾጠጤም አይቻልም ኢትዮጵያን እንደ ቀድሞ ወሮም ሆነ በጥርቆ ለመግዛት። ዙሪያ ገባው የተዘጋ ነው። ተደግሞ ጫካ አይገባ ነገር ይህ ሁሉ ምቾት ተለምዶ? እንዴት ተብሎ? ታሪኬ ባጭሩ ሁሉ ምን ሊሆኑ? አንድ የልጅ ልደት እኮ ዛሬ ስንት ወጪ ይጣበታል?

 ወደ ኤርትራ እንዳይታሰብ የማይሆን ሂሳብ ነው መሽቷል። ወደ ሱዳንም ቢባል ዓለም ዓቀፉ ህግ ዛሬ ከሰብዕዊ መብት በላይ ጉዳይ የለውም። ዘመኑ አልቋል።

የትግራይን ህዝብ የጅዋጅዊት ቤተኛ አድርጎ ከማንገዋለል ይልቅ ፉከራን ተግ አድርጎ ጥፋትን ገልፆ፤ ቧልትን ማቆም ነው ህይወት ሊያሰነብት የሚችለው። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ማናቸውንም ነገር ቢያቆም፤ በጀቱን ቢዘጋ፤ መንገዱን የ አፈራን፤ የወሎን እና የጎንደርን ቢዘጋ ምን ይኮናል? ተያይዞ ማለቅ እኮ ነው። እራሱ ጣና ላይ የተሳበው የኤሌትሪክ የነጻ አገልግሎት ቢቆም ምን ሊኮን ነው? እስከ አሁን ድረስ የትግራይ ክልል ለተገለገለበትም የአግልግሎት ክፍያ የአማራ ክልል ቢጠይቅ ምን ሊባል ነው? 

መቼስ ኢትዮጵያ የጠላት አገር እንጂ እንደ አገር የማትታይ ስለመሆኗ እኛ 27 ዓመት ሙሉ ተናግረናል፤ ጽፈናል፤ ለማለደኛው ነው አሁን አዲስ እዬሆነ ያለው፤ የተቻለው ፍዳ ምድርም ሰውም ህዝብም ፕላኔትም ከሚችለው በላይ ነው።
  
ይህ ዘመን ከማንም በላይ እና በላይ ለማን ይደላል፤ ለማን ይመቻል ቢባል ለትግራይ ህዝብ ነው። ይህ የጥገናዊ ለውጥ ባይመጣ ኖሮ ሌላ አካል እና ሃይል ዕድሉን አግኝቶ ቢሆን ኖሮ? ይህን ያህል መዘባነንም፤ ቀልምጥም ባልተገኘ ነበር። ምክንያቱም የለመድብን አጥፊውንም ደህናውንም ቀላቅሎ መቀቀል ስለሆነ። 

አሁን ግን አጥፊዎች ለዛውም ህግ የሚጠይቃቸው ብቻ በተጠና አኳኋዋን ተጠያቂ መሆናቸው ለሁለችንም እረፍት የሚሰጥ ነው የሆነው። ለንጹሃን የትግራይ ልጆች ወይንም ከትግራይ ለተወለዱ ልጆች አብዩ የሰማይ ሥጦታ ሽልማታቸው ነው። ለውጡን የሚመሩትም አጋሮቻቸው ድንቅ ስጦታ ናቸው። 

ኢህድግ የሚባለው ድርጅት እራሱ ዕድለኛ ነው፤ ይህን የመሰለ የዳዊትን ጥበብ የሰጠው አካል አግኝቶ መላውን በመላ ቀስ አድርጎ እየመለለው ነው። አድኗችሆዋል ከብዙ አይነገሬ ፈተና እና ውርዴት።

... እና አቤቶ ዶር ደብረጽዮን ገ/ሚኬኤል በነካ አፍዎት እስኪ ሁሎችንም የህዝብ የአገር የወገን የታሪክ የትውፊት ወራሪዎችን አንጥልጥለው ለመስጠት ድፈረቱን ያሳዩን፤ እህ ሹመት እኮ ሰጥታችኋዋል? የሆነው ነገር የታዬው ነገር የነበረው ነገር ሁሉ  የትውፊትም የታሪክም ድፍረትም ነበር። 

እና እስኪ እጅዎትም ደፍር ብሎ እንደ ማዕከላዊው ትግራይ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን ውጠው ያስቀሩትን ዋጮ ከመሬት በታች ያሉ የስቃይ ጉድጓዶችን ሁሉ ነፃ ያውጧቸው? 

መልካም ነገር ሰርቶ የተዋረደ የለም። ታማኝ ሆኖ ከስሮ የቀረ የለም። ጭብጨባ ላይኖር ይችላል ግን በህሊና ኖሮ በህሊና መሞት ግን የጽድቅ መንገድ ነው። አብሶ የነገ ትውልድ የእናንተን ዕዳ ተሸካሚ እንዳይሆን ቢመሽም እስኪ ባለቀ ሰዓትም ቢሆን ልብ ይስጣችሁ። አሜን!

·      ትግራይ እናቶች እናትነታቸውን ያወያዩት።

እኔ ጉዳዬ የድምጽ አልባዎቹ የኢትዮጵያ እናቶች ዕጣ ፈንታ ስለሆነ ለዚህ ዘመን ውብ ያልታሰበ ሎተሪ ዕድል ሁሉም የኢትዮጵያ እናቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እሻለሁኝ። 

የትግራይ እናቶችም አምርሬ በአዲግራት ዩንቨርስቲ መከራ ላይ ጽፌባቸው ነበር፤ አሁንም እምለው ያን ነው፤ እናትነታቸውን እንዲጠይቁት፤ እናትነታቸውን እንዲያወያዩት፤ እናትነታቸውን እንዲያነጋግሩት እና እናትነታቸውን እንዲያስወስኑለት።

ስለ ነገ ልጆቻቸው፤ ስለነገ የልጅ ልጆቻቸው ዕዳ ተሸካሚነት፤ ጎብጦ መኖርነት እንዳይኖር ይታገሉ። ዕድሜ ልክ 27 ዓመት ሙሉ መለመን የለባቸውም፤ የታሠሩበትን ገመድ በጣጥሰው ከዕውነት፤ ከሰብዕዊነት እና ከተፈጥሯዊነት ጎን ሳያወላውሉ፤ ሳያዋላዱ መቆም ይኖርባቸዋል። የሰው ልጅ አይደለም ለሰው ለአምሳሉ ፍጡር ላሳደገው እንሰሳ እንኳን ታማኝ ነው። እስኪ የተጋሩ እናቶች ለሰው ተፈጥሮ ታማኝ ለመሆን ይቁረጡ!

ሴቶች ትውልዳዊ ሃላፊነት አላባቸው። ሴቶች የመጀመሪያው የህይወት ት/ቤቶች ናቸው። መምህር ደግሞ ለትውልድ ብክንት ቀዳሚው ተዋጊ አርበኛ መሆን ይኖርበታል። ቀኑ እያጠረ ነው፤ ባጠረው ቀን ወስጥ ጊዜ ሳያባክኑ ሆኖ መገኘት  የእናታዊ ድርሻን ያጎለዋል፤ ስኬታማ ያደርገዋል።

ስለሆነም የተጋሮ እናቶች ሽፍንፍኑን ገለጥለጥ አድርገው ከእውነት ጎን ይቆሙ ዘንድ አሁንም አሳስባለሁኝ - በትህትና። ባዶ 6 ቀድመው ማዘጋት ይኖርባቸው የነበረው እነሱ ነበሩ። 

እጅግ ቢዘገዩም አሁንም ግርዶሹን ገልጠው ባልሆነው ነገር ሳይሆን በሆነው ነገር መሆንን ያሳዩን - በአክብሮት። የፈንግጪው ገበጣ ነፍስን መኖርን ተስፋን አያስቀጥልም። 

ግን እትዬ ትግራይ ቆሞስ ኢንጂነር ሰመኘውን ያስገደሉት የራሷ ገመናዎች ቢሆኑ ምን ትል ይሆን?ማተብ ይኖራት ይሆን?! ቀን ይፍታው።

መሆን ይቅደም!

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን 
አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

ውዶቼ ክብረቶቼ አዱኛዎቼ ቅኖቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ። 





አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።