ለመሆኑ አማራ እንደ ኢትዮጵያዊ ሙሉ ዜጋ ይታያልን?

ዕውቅና ያልተሰጠው
ችግር መፍትሄ ያገኛል
 ብዬ አላስብም።
„አቤቱ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም፤
ችግረኛና ምስኪን ነኝና።“ መዝሙረ ዳዊት ፹፭ ፩
ከሥርጉተ© ሥላሴ
ለመሆኑ አማራ እንደ ኢትዮጵያዊ ሙሉ ዜጋ ይታያልን? 
ከጭምቷ ሲወዘርላንድ።

  • ·       መነሻ።

በመጀመሪያ ነገር በአማራ ፍልስፍና ላይ ጠ/ሚር አብይ አህመድ እምነቱም ፍላጎቱም የላቸውም። አማራ የሚለው መጠሪያ መስማትም አይፈልጉትም። ይህን ባህርዳር ላይ በቅኔ ተናግረውታል። እኛ አጠቃላዩን ስለምናይ ብቻ ነው ውስጣችን፤ ፍቅራችን፤ አክብሮታችን የምንሰጣቸው እንጂ በነገረ አማራ ያላቸው አቋም እጅግ ከረር ያለ ስለመሆኑ በተለያዬ ጊዜ በሚያደርጉት ንግግር ይገልጡታል።

የሚገርመው በቀደመው ጊዜ እንዲያውም ተቆርቋሪነታቸው አመዝኖ ነበር የማዳምጣቸው። እጅግም የሚያሳሳ አቅም ነበራቸው። በአዲሱ ማንነታቸው ውስጥ ግን ልዩ ተልዕኮ የተሰጣቸው ያህል ፊት ሲነሱት ነው እኔ የምመለከታቸው። ከውስጤ አላዝንም። ይህም ለበጎ ስለመሆኑ ስለማምንበት። አንድ ቀን እንደሚጸጽታቸውም ልብ ልክ ነው።

የመጀመሪያ 6 ወር ሥራቸው ላይ በጫን ተደል የቤት ሥራ ክልሉን ሲያጣድፉት ነበር የባጁት። መተንፈሻ እስኪታጣ ድረስ። ሌላ ቦታ የማይሞክሩትን ሁሉ የለማ አብይ አካቢኔ የመሞከሪያ ጣቢያው ለሁሉም ነገር አማራ ክልል ላይ ብቻ ነበር። ይህም ሆኖ እንደ ሰውም አይተው ዕንባውን ለማድመጥ መፍቀድም የአባት።

እኔ እንደማስበው እራሱ አዴፓ የሚበላውን ድርጅት ሥሙ ራሱ አሁን ከሆነ የሚመቻቸው አይመስለኝም። እነሱ እራሳቸው ከዞግ ድርጅት ወጥተው ያን ያህል የተንጠራሩ የኦሮሞ ሊሂቃንን ተሸከመው፤ እያባበሉ፤ እያቆላመጡ ሠርግና መልስ እያስደረጉ የራሳቸውን ወገኖች አማራ ግን አማራ ነኝ አትበል ባይም ናቸው። ብቻ ይህ መከራ ሄዶ ሄዶ ክሩ ከተበጠሰ የኢትዮጵያዊነት አከርካሪ እንዳያበቃለት እሰጋለሁኝ። ሲከር ይበጠሳል ሲሞላም ይፈሳል እና።

የአማራ የማንነት ተጋድሎ ደሙን ጠብ አድርጎ ያመጣው ለውጥ በምንም በዜሮ መባዛቱን ይህ ምስል ያሳያል።
አማራ በመሆናችን ነግደን መኖር አልቻልንም- ከወልቃይት ጠገዴ ተፈናቅለው አዲስ አበባ አቤቱታ ለማቅረብ ከመጡት ወጣቶች መካከል
·         October 31, 2018

እኔ አገርም መንግሥትም አለ ብዬ አንችም ዜጋ ነሽ ስባል ዕውነት መስሎኝ ለጠ/ሚር አብይ አህመድ በቀጥታ፤ ለጠ/ሚር ጽ/ቤት እና ለዶር ለማ መገርሳ በግልባጭ አብይ ሆይ! ብዬ አቤቱታ በጥዋቱ ብዙም ስራ እና ሃላፊነት ሳይደራረብባቸው አቅርቤ ነበር።

ቢያንስ በወፍ በረረ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለወልቃይት፤ ለጠገዴ፤ ለመተከል፤ ለራያ አካባቢ ለሚኖሩ በመንፈስ ለተሰረዙ ኤትዮጵያዊ ዜጎች። ሁለቱም ሊያዳምጡኝ አልፈቀዱም።

ከሌላው አካባቢ በተለዬ ሁኔታ በአፓርታይድ ሥር ስለመውደቃቸው ጠቅሼ አበክሬ ጽፌ ነበር። የሚገርመው በዘመነ ኦህዴድ/ አዴፓ እንዲህ አማራ ተመሳሳይ መከራን ያስተናግዳል የሚል ምንም ግምት አልነበረኝም። እንዲህም አማራ ይገፋል ብዬ አስቤም አላውቅም ነበር።  በፍጹም። ለአማራ ጤነኛ መንፈስ አላቸው፤ በዛም ይዘልቃሉ ነበር ጽኑው ተስፋዬ። ነገር ግን የማዬው ነገር ሁሉ ተስፋዬን ወና አድርጎታል። 

እስከ አሁን ድርስ አቤቱታዬን ባሊህ ባይ ባለማግኘቱ ይኸው ከራያ የተፈናቀሉት ወሎ ላይ ከወልቃይት ከጠገዴ የተፈናቀሉት ደግሞ አዲስ አባባ ይገኛሉ። ራያ አላማጣ ያን ሁሉ መስዋዕትነት ባልተከፈለ ነበር የቀደመውን አቤቱታዬን ማድመጥ ቢችሉ። ለነገሩ ባዶ 6 ያሉ ፍደኞችን ማስፈታት አልተቻለም፤ ፌድራሉ በጀቱን ቢያቆም አልታዘዘም ከለ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ይችል ነበር። ግን ማን ደፍሮ?! አሁን ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምን እዛ አስቀምጦ ምን ፍትህ ሊገኝ ነው። የውርንጫ ድካም ነው። 

ሰሞኑን አንድ ትልቅ የፍትህ የምሥራች ሹመት ሰማን ግን ክብርት ወ/ሮ ማዕዛ አሻናፊ እና ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በምን የዕውነት መስመር ስምረትን ፈጥረው ሊሠሩ ይሆን? የማይለያዩ አካላት ናቸው እና። አንዷ ሉላዊ ሌላዋ አጢቢያ ደብር ላይ ያሉ ... 

ወደ ቀደመው ቁምነገሬ ምልሰት ሳደረግ እጅግ ሰቅጣጩ ነገር ከመነሻ መንደራቸው እስከ አዲስ አባባ ከ1000 በላይ ኪሎ ሜትር ተጉዘው እነዚህ ታዳጊዎች ከወላጆቻቸው ተነጥለው፤ ነፃነት ፍለጋ ክልትምትም ይላሉ። ነፃነትን ፍትህ ፍለጋ በአብይ ለማ ካቢኔ? ባለቤት የሌለው ህዝብ እንዲህ ነው።

የጠ/ሚር ቢሮ ደግሞ የኤርትራውያንን ቤት ለማስመለስ ደፋ ቀና ይላል፤ በሌላ በኩልም አፍሪካውያን የቢዛ ችግር እንዳይገጥማቸው አዲስ ፖሊሲ ለማስተዋወቅ ደፋ ቀና ይላል። „የራሷ ሲያርባት የሰው „እንዲሉ … እነዚህ ታዳጊዎች ደግሞ ዜጋ አይደላችሁም ተብለው፤ ብትን አፈር አጥተው እንዲህ ይንከራተታሉ። መውጫ መግቢያውን በማያውቁት አገር ባዶ እጃቸውን።

ነፃነት ማለት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምን አፈ ጉባኤ አድርጎ መሾም እና እንዳሻቸው የህዝብን ሥነ - ልቦና እንዲጠቀጥቁ መፍቅድ ነው። ነፃነት ማለት አቤቱታ ለማቅረብ የመጡ ታዳጊ ወጣቶችን በፖሊስ ማዋከብ ነው። „ጣና ኬኛ!“ ማለት አማራን መርሳት ማለት ነው። „ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው“ ማለትም አማራ ዜጋ አይደለህም ማለት ነው። ይኸው ነው ትርጉሙ አማራን በማግለል በዬአቅጣጫው የሥነ - ልቦና ስብራት ማድረግ። አንዱ ሰቆቃ ሲያልፍ ሌላው ደግሞ በእጥፍ ድርብ በአዲስ አቅም እና ጉልበት እንዲህ የሽታ ሽቶ መሰለቅ መከትከት።  

እኔ እስቅ ነበር ጠ/ሚር አብይ አህመድ በርሊን ላይ ላቀባበል የተገኙትን ወገኖቻችን አገራችሁ ግቡ እያሉ ሲስሟቸው። ምን አገር ኑሮ ነው የሚጋባው? ለመሆኑ አማራን ዜጋዬ ብሎ ያውቀዋል የጠ/ሚር ቢሮ? ለመሆኑ አማራ አገር አለውን? ለመሆኑ አማራ ሰው ነውን እንደ ሰው እንታያለን?የት ነው ያለው ዕንባ ጠባቂ የሚባለው ሚኒስተር መ/ቤት? የት ነው ያለው የሰብዕዊ መብት ኮሚሽን የሚባለውስ? መቼም የሴቶች የህጻናት እና የወጣቶች የሚባለው አይጠዬቅም የት እንደሆን መነሻው ስለሚታወቅ?

እነዚህ ሁለት ታዳጊ ወጣት ሴት ልጆች ነገ የጾታ ጥቃት ቢደርስባቸው ማነው ሃላፊነቱን የሚወሰደው? ለመሆኑ አቶ ደመቀ መኮነን ምን ይሰራሉ? ለመሆኑ ምክትል ጠ/ሚሩ የት ነው ያሉት? ቢያንስ ይህን የወታደር ወከባ እንኳን ማስቆም እንዴት አይችሉም? እነዚህ ወጣቶች የት ይድረሱላችሁ? የትስ ይግቡ? ምንስ አገር አለኝ ይበሉ? ተመልሰው እንኳን መግቢያ የላቸውም። ቢመለሱም አይናቸው እያዬ ዓይናቸውን ያወጡታል ጨካኞች አረመኔዎች። ስለነገ አያስቡና።

ሰሚ ሲገኝ አማራ እንደ ዜጋ ሲታይ ነው ፍትህ የሚገኘው። አማራን እኮ ለማዬት ሳይፈቀድለት ነው እዬኖረ ያለው። አዎን! አማራ የሚባል ማህበረሰብ መኖሩ አይፈቅዱትም ሊሂቃኑ ሁሉ። አማራ በዛች ምድር ውስጥ የተሰረዘ ማህበረሰብ ነው። የአማራ ሊሂቃን ባላተፈቀደላቸው ዘመን መገኘታቸውን አራሱ አያውቁትም። ተደፍኖባቸዋል። አማራ መቻሉ ትናንትም አስጠቅቶታል ዛሬም እያስጠቃው ነው። ነገም ይጠቃል። ያልፋል መስሎኝ ነበር ግን እማዬው ሁሉ ሬት ነው። 

ውዶቼ በዚህ አድራሻ ነበር ሰፋ እና ዘርዘር ያለውን አቤቱታዬን ያቀረብኩት።
  • ·       አድራሻው ይህ ነበር …

ለክቡር ዶር. አብይ አህመድ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር
አዲስ አበባ፤
ግልባጭ

ለጠ/ሚር ቢሮ
አዲስ አበባ፤
ግልባጭ ለክቡር የኦሮምያ ክልላዊ ፕሬዚዳንት ለአቶ ለማ መገርሳ።
አዳማ።
አቤቱታ የቀረበበት ቀን ... 01.06.2018    
https://sergute.blogspot.com/2018/06/blog-post_19.html

  • አቤቱታ ሦስት ላይ ይገኛል ስለ አማራ አቤት ያልኩት። ዜጋ አለመሆኔ እዬተነገረኝ ነው ያው እንደ ተለመደው ሁሉ።
የአማራ ሊሂቃን የማይረዳው አማራ አማራነት በኢትዮጵያ መንግሥት ህሊና ውስጥ መሰረዙን ነው። ማንም መስማት አይፈልግም ስለ አማራነት። ማንም ስለ አማራነት አጀንዳ እንዲሆን አይፈልግም። ይህ መራራው ሃቅ ነው። 

ዛሬ ገና በመባቻው ይህ የሆነው ነገ ሲውል ሲያደርግ ዘመኑ በምን እንቆቆ እንደሚዋጅ እግዜሩ ይወቀው። ምን አለ የአብይ ለማ ካቢኔ እነ አቶ ጃዋር መሃመድን በሸራትን ያንፈራስስ … 

ምን አለየደላው ገንፎ ያላምጥ እንዲሉ፤ እነዚህ ምስኪኖች ጫማ ጠርጎ ማደርን ተነፍገው አስፓልት ላይ ይነከራተቱ … ስለምን አማራ ናቸዋ!

ቁርጡ ነገር ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ የአማራ ተጋድሎን አጠናክሮ በተከታታይ መቀጠል ነው። አስፈላጊ ከሆነ የሎቢውን ተግባር ደግሞ አጠናክሮ እንደ አዲስ መጀመር ነው። ምን ይሁን ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል እና። መታገስ ለመላ ሲሆን መልካም በሆነ ነበር። ታሪካችሁን አትንገሩንም እያዳመጥ ነው እኮ አሁን አሁንስ። እም!

በተጨማሪም ግፈኞችን ፍርድ ሰጪው የላይኛው ስለሆነ ሰውኛውን ትቶ በመንፈስ ከልዑል እግዚአብሄር ጋር በትጋት መገናኜት ነው። ጸሎት አቅም አለው። አሁን ደግሞ ለእመቤቴ ወዳጆች ጽጌ ጾም ነው። እሷ  በእነዚህ ምንዱባን ልጆቿ አትጨክንም፤ ትራራለችም።

„አማራነት ይከበር!“

የኔዎቹ ኑሩልኝ።
ማለፊያ ጊዜ።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።