ክርስትና እና እስልምና ዓይናችሁን አደራ ጠብቁ!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት + 
የኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖት 
ዓይናቸውን የመጠበቅ አምላካዊ 
ግዴታ አለባቸው። ክርስትና ማለት
 ሆነ እስልምና መታመን ነው።

„የሰው ልብ መንገድን ያዘጋጃል፤
እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል“
መጽሐፈ ምሳሌ ፲፮ ቁጥር ፱
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute ©Selassie
17.12.2081
ከጭምቷ ሲወዘርላንድ




ምሩቁ ይስህቅ!



·       ጠብታ

ጤና ይስጥልኝ ውዶቼ የማካብራችሁ እና የምናፍቃችሁ የአገሬ ልጆች እንዴት አላችሁልኝ። አውሮፓ ስሜን አሜሪካ ያላችሁ እንዴት ይዟችኋዋል ብርዱ? ዘንድሮ በጋውም እረጅም ነበር፤ ክረምቱም ቀለል ያለ ነው እዚህ እንደ ሲዊዝ ከሆነ። ለነገሩ ገዳማዊቷ አገር ሲዊዘርላንድ በጋውም ሆነ ክረምቱ በልክ ነው፤ እጁን ታጥቦ የፈጠራት ብጽዕት ናት እና። በረድ የሚጥለው ተራራ ላይ ነው። 

ሙቀትም በበጋ ምን አልባት ቢበዛ እስከ 5 ቀን ነው ከፍ ያለ የሙቀት ደረጃ የአዬር ንብረት ያለው እንጂ ቀሪው ለጤና ተመጣጥኖ እንደሚሠራ ምቹ ምጥን ነው። የገዳማዊት አገር ነገር እንዲህ ነው እንደ ህዝቧ ሁሉም በደንበር ነው፤ በልክ  …. የታደለች!
·       ዓይን።
ብሩካን!


ዓይን ፖስተኛ ነው። ዓይንም ብርሃን ነው። ዓይንም የምርምር ተቋም ነው ለአካላት ሁሉ። ዓይን በጥበብ ውስጥ የተቀመረ ተፈጥሮ ነው ያለው። ይህን ስል ግን ልበ ብርሃን የሆኑ ሉላዊ ዜጎችም እንዳሉን ነው እማስበው። የእነሱ አፈጣጠር ደግሞ ከማስተዋል ጋር ብልህነቱምን አርቅቆ ነው የፈጠራቸው። ልዩም ጸጋም ክህሎትም ነው ያላቸው።

የሆነ ሆኖ ይህ ዘመን ለሁሉቱም ሃይማኖቶች ለክርስት እና እና ለእስልምና ዓይናችን ሊሉት የሚገባ ዘመን ነው ይህ የምሥራች የምርቃን ዘመን ብለው ሥም ቢያወጡለት ምርጫዬ ነው። እንደዚህ ዘመን ለእኛ ትውልደ ሃይማኖት የከበረ ተቋሙነቱ በመንግስት ደረጃ ዕውቅና የተሰጠበት ዘመን የለም። በ50 ዓመት ውስጥ ሁለቱም ሃይማኖቶች የተመጠነ ዕውቅና ብቻ ነው የነበራቸው። እንደ ዓይንም፤ እንደ ህሊናም እንደ ብቁ ወታደርም አይታዩም ነበር።

                                                     አደባውያን!

አሁን ግን ክርስቶስ ፈቅዶ ሙሴ ሰጥቷቸው፤ እዮርም በቃችሁ ብሎ እንሆ ቋሚ አጀንዳ ሆነው ተከበረው፤ ተወደው፤ ተፈቅረው፤ ተቀርበው፤ እዘዙን ተብለው፤ ተስፋ ሆነው ተቀባይነታቸው ጎልቶ እንዲታይ የጠ/ሚር ቢሮ ሌት እና ቀን እዬበታለ ነው። በጠ/ሚር አብይ ህሊና ውስጥ ኢትዮጵያን ከነክብሯ ለመመለስ ዋነኛ ቁልፉን ቦታ አግኝተውታል ብዬ አምናለሁኝ። እግዚአብሄርን ባወቁት ቁጥር ጥበቡ እንደ ልብ አምላክ ዳዊት እንደ ልጁ እንደ ሰለሞንም ነው። ብቻ ልዑል እግዚአብሄር ይጠበቅልን መንፈሶቻችን ሁሉ።

ትሩፋት!


ይህ የሽልማት ዘመን እዮራዊ ስለመሆኑ የጸሎት፤ የሰጊድ፤ የድዋ ውጤት በመሆኑ ምስጋነው የሚረጋገጠው ሁለቱም ሃይማኖቶች ክርስት እና እስልምና፤ ወንጌል እና ቁርአን ለዚህ ዓይን ለሆናቸው የለውጥ ሂደት ምዕመኖቻቸውን የለውጡ ሠራዊት አድርገው ጥበቃ ሲያደርጉለት ብቻ ነው፤ ምስጋና ሰጠን፤ አስራት አቀረብን ለፈጣሪ የሚባለው። ተመስገን አልነውም ማለት የሚቻለው ይህን የምርቃት ዘመን ማከብረባቸውን ማረጋገጥ የሚቻለው። ዘመኑ መደዴ አይደለምና። ዘመኑ ብልህ እና የጥበብ ዘመን ነው።

ይህ ዘመን የምርቃት ዘመን ነው።  ሙሴ ምሩቆችን እስነስቶ እነሆ የአውራ ዕምነት ተቋማት የታሰሩበት ገመድ ተፎቶ በተለይ እስልም እና እና ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት መተንፈስ ጀምረዋል። የኢትዮጵያ የእስልምና ሃይማኖት ተጋድሎ በምድራችን በጣም ለረዘመ ጊዜ አንቱ የተባለ አፍሪካን ያስተማረ መምህር የሆነ የተደራጀ ብዙ የሰላማዊ ትግል አካሂደዋል። ሐዋርያ የሆነ የነጻነት ጠንካራና ብርቱ፤ እንዲሁም ጽኑ ተጋድሎ አደርገዋል ከሦስት ዓመት በላይ።

ተጋድሎው የአደባባይ ብቻ ሳይሆን በህገ ልቦናም፤ በጾም፤ በጸሎት፤ በሰጊድ ሰፊ የሆነ ተግባር ተከውኖበታል። እስልምና አዋቂ ልጆቹን፤ ሰማዕት ልጆቹን በእስር መንገላለት ብቻ ሳይሆን ህይወታቸውን ሰጥተውለታል ለነፃነተቸው፤ ለእኩልነታቸው።

እጅግ በርካታ የእስልማና እምነት የሃይማኖት ወጣቶች፤ አባቶች፤ እህቶች ሰፊ የሆነ የተግባር መስዋዕትነት ከፍለዋል። በዚህ ዙሪያ ቢቢኤን ራዲዮ ፕሮግራሙ፤ በአንድ ወቅትም የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ እጅግ በሚመሰጥ፤ እጅግም በሚገርም፤ እጅግም በሚየበረታት ሁኔታ ተግቶ ትግሉን መርቷል። ለእስልምና ሃይማኖት እና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አንድነትም የበኩሉን ጉልህ ድርሻ አብርክቷል ሚዲያው።


የዚህ ለውጥ አናት የሆኑት ሁለቱን ተጋድሎዎች የኦሮሞ ንቅናቄ እና የአማራ የህልውና ተጋድሎን በቂ ዕውቅና ሰጥቶ ቢቢኤን የተሟላ ተግባርን ፈጽሟል። አብሶ የአማራ የህልውና ተጋድሎ በተገለለበት፤ በኮፒ ራይት ጉዳይ እንግልት በደረሰበት ጊዜ ደጀን ሆኖ፤ መከታ ሆኖ፤ ግንባር ቀደሙን ደርሻ በሃላፊነት እና በሚዛናዊነት ስሜት ከውኗል ቢቤኤን።

የጎንደር አብዮት „የድምጻችን ይሰማን“ ጥያቄ ህሊናው ማደረጉ ቢቢኤን በእጅጉ የተመሰጠበት እና በጉልህ ከምስጋና ጋር ተጋድሎውን ለመደገፍ ከጎን የቆመበት ሁኔታ ታሪክ ሊረሳው የማችል ጉልበታሙ የቢቢኤን መኖር ያሰገኘው ሀገራዊ ትሩፋት ነው።

እኔ እራሴ ቀድሜ ነበር የድምጻችን ይሰማ ንቅናቄ ሲመጣ እንግልት፤ ግፊያ ሲያልበት እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ድምጻችን ይሰማ ነኝ ብዬ በድፍረት የወጣሁት። ምክንያቱን ንጹህ የሃይማኖት የእኩልነት ጥያቄ ይዞ የተነሳ፤ ልብ ሊሸለመው የሚገባው፤ የአመራር ጥበቡም ህሊናን የሰረቀ ልዩ የሆነ፤ አደረጃጀቱ ፍጹም ድንቅ የነበረ ተጋድሎ ስለነበር።

በሌላ በኩል የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌሰቶውን ሲቀርጥ ኢትዮጵያ እንደ አገር በማቆዬት እረገድ ብቻ ሳይሆን ታሪክ የካናቸውን  የሁለቱን ሃይማኖት ተፈጥሯዊ ጋር ትስስር እንቅርቱ ስለነበር በጥርሱ ይዞ በጸርነት አስቦ ቅደስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ነጥሎ በማውጣት ቀብረናታል፤ አከርካሪዋን ሰብረናትል እስከማለት የተደረሰበት መከራ ነበር። ይህ እርምጃው እስልምና የጸረ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጎን ለማሰለፍ ሆን ብሎ ያለመው ዲዲቲ ነበር።

ያ የ27 የድቅድቅ ጨለማ ዘመን የቤተክርስትያንዋ አገልጋዮች፤ ማህበረ ምዕመናንም ጨምሮ ልጆቿ በኢኮኖሚ፤ በማህበራዊ፤ በባህላዊ፤ በታሪካዊ፤ በትሩፋታዊ፤ በትውፊታዊ አቅሟ ልክ እውቅና እንዳያገኙ፤ ቀና ብለው እንዳይሄዱ በረቀቀ ሁኔታ አድሎና ጭቆና በመፈጸም በስፋትት በፖሊሲ ደረጃ የተሰራበት ነበር። ይህን ዛሬ ላይ ያለውን ውጤት በመንግሥት ተቋማት ያለውን የ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የልጆቿን ውክልና በማዬት ማነጻጻር ይቻላል። ለስሙ ግን የጠቅላይ ፓትርያርክ ጽፈ/ቤት ነበር። 

ምን ያህል በ27 ዓመቱ የወያኔ ሃርነት ትግራይ አዋራነት የአገር መንፈሷ በስልት ውስጧ ሲመነጠር እንደነበር ዛሬ ላይ በማስተዋል ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በማየት ማመሳከር ይቻላል። ሃይማኖቷ ሆድ ብሷት ወደ ግጭት እንድታመራ ግጭቱ ደግሞ ሌላ ሃይማኖት ላይ እንዲሆን ነበር ምህንድስናው። 

የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መገለል መገፋት እንደ ደረሰበት ዛሬ ማዬት ይቻላል። አስተርጓሚ አያስፈልግም። ልጆቿ አንድ ትውልድ ማለት ይቻላል በማዕቅብ ህሊናቸው ታስሮ ፤ በረቀቀ ሁኔታ ከሁሉም ቦታ ተገለው በጭቆና ላይ እንደ ነበሩ የእያንዳንዱን ቀን ዜና እና ግብዕቱን ማዬት መመርምር ይቻላል - ልብ ላለው።

ሊቀ ሊሂቃኖቿ፤ ፈላስፋዎቿ፤ ጠብተቶቿ በመሰዋት፤ በመታሰር፤ ክብራቸውን በመደፈር፤ በማሰደድ የቀደሙትን የአቦውን የሐዋርያትን መከራ ተቀበለዋል። አገር ለአገር ተሰደዋል ተንከራተዋል። አንደ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ዘመንም የቅድስት ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባቶች፤ ሊቀ ሊቃውንታት አልተሰደዱም። ፈጽሞ።

ደግነቱ ብልሆች የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ብጹዕን ፈጣሪ ከእነሱ ጋር ስለነበር ዓለም ያጣቸውን የቅድስ ቤተክርስያኗን እረድኤት እና ቅብዕ በተሰደዱበት ቦታ ሁሉ በሚያስገርም ፍጥነት አደረጀተው እና መርተው አንቱ ተግባራትን በመፈጸም በመከራ ጥናት ከአገር ለሚሰደዱ ልጆቻቸው ጋሻ እና መከታ ሆነው በተደራጀ፤ እጅግም በተቀናጀ፤ ጥበባዊ አመራር እና ክህሎት አገልግሎታቻውን ልጆቻቸውን እንዳያጡ፤ እንዳይጎድልባቸው በማድረግ የሰማዕትነት ተጋድሎን በሚያስመካ ሁኔታ ፈጥመዋል። ተመስገን። ልዑል እግዚአብሄርም ይጠብቅልን። 

                                                  ህሊናዊነት!

ያ የስደት የግርፋት ዘመን አልበቃ ብሎ ገዳማት ተዘርፈዋል፤ ቅርሶች ተራቁታዋል፤ ቤተ እግዚብሄራት ተቃጥለዋል፤ የጣና መከራ ራሱ ታቅዶ የተከወነ ተግባር ነው እግዚአብሄር በሚያውቀው። የጣና ገዳማት ሃብትነት የመላ አፍሪካ የታሪክ ቅርስ እና ውርስ ነበር።  በአገሩ ክብር ለሚኮራ ትውልድ። ብቻ ፍርድና ዳኝነቱ የ እሱ የ አንድዬ ነው፣ 

ከሁሉ በላይ አልተሳከለትም እንጂ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ በሁለቱ አንጋፋ ግዙፍ ዕምነቶች በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት እና በኢትዮጵያ እስልምና ሃይማኖት ውስጥ የሰፋ ልዩነት እንዲኖር ሰፊ የፖለቲካ ተግባርን ተሰርቶበታል። ሰፊ ድርጀታዊ ተግባራትም ተከናውኖበታል።

                                                   አሜናዊነት!

ይህ ተግባር ኢትዮጵያን በተቋም በማራቆት እረገድ በተበጣጠቀ መንፈስ፤ በግንጥል ጌጥ ሁሉም የጓዳውን ብቻ በማሰብ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የመንፈስ ማማ፤ ለአህጉሯ ሁለገብ እንብርት የጥቁሮች መመኪያ እና መላያ ዓርማ እንዳትሆን ጣሊያኖች፤ ቱርኮች፤ ፓርችጊዞች፤ እንግሊዞች ያሰሉትን የዘመናት ውጥን የፈጸመ እኩይ ተግባር ነበር የተፈጸመው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ።

የወያኔ ሃርነትትግራይ ማንፌስቶ በቀጥታ የኢትዮጵያን የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ የመሪነት፤ የጥቁር አንበሳ የሽምቅ ውጊያ ለዓለም ያሰተማረችበትን መንገድ፤ የአፍረካ አንድነት እና የተባባሩት መንግሥታትን በመመሥረት ሂደት ያለትን ባለ እርስትነት የጠኔ ሲሳይ እንዲሆን ተግቶ ሠርቶበታል።

የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ኢትዮጵያ እንደ ጣውንት እንጂ እንደ አገር ልጆቿ የሚመኩባት፤ ተስፋ የሚያደርጉባት አገር አንዳትሆን መርዙን ያበቀለው በሁለቱ አንጋፋ ሃይማኖቶች በሰራው የመሰሪነት ተግባር ነበር።

እውነት ለመናገር „ከድምጻችን ይሰማ“ ሉላዊ እንቅስቃሴ ማግሥት የተቋቋመው ሚዲያ ቢቢኤን የሰራው ተግባር ጉልበታም ነበር። የቢቢኤን መፈጠረ „የድምጽችን ይሰማ“ አንደበት ብቻ ሳይሆን አገርን እንደ አገር ለማቆዬት ሰፊ ድርሻውን ተወጥቷል ብዬ አስባለሁኝ። ድርሻው እጅግ ጉልህ ሰለነበር። መረጃ የመንፈስ መስኖ ነውና።

የኢትዮጵያ የእስልምና ዕምነት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መንትዮሽ ናቸው። ተፈጥሯቸው እትብታዊ ነው። በክፉም በደጉም አብረው የኖሩ ህሊናዊ መተሳሰራቸው ማንም እንደ ፈለገ ሊበጥሰው የማይችለው ነው። በጸሎት ሲደጋገፉም አንዱ ሲደክመው ሌላው እየጠነከረ በመተጋገዝ ነው አገር ያወረሱን። ኢትዮጵያዊነት የዚህ በኽረ ጉዳይ አውታር ነው።

ለዚህም ነው አካል የሌለው አገልጋይ ቃለ ወንጌል ነበር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱንም ሊለወጥው፤ ሊከልሰው፤ ሊያካፍለው፤ ሊያዋሰው፤ ሊለጥፈው እንደ ቁሮ እንጨት እንደማይችል አበክሮ የሚያሰተምረው።

ኢትዮጵያዊነት ፊደል መቁጠር ያልጀመረው የወያኔ ሃረነት ትግራይ ማንፌስቶ ሲነሳ  ለኢትዮጵያዊነት መሠረት ነው ብሎ ባመነበት በአማራ ማህበረሰብ እና በቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ላይ ጦሩን መምዘዙ ሌሎቹ ወዳጆቼ ናቸው ማለቱ አይደለም፤ አልነበረም። ሁለቱን በመተርትር በመንፈስ መሰንጠቅ ብቻ ነው ህልውናውን ማቆዬት የሚችለው።
                                              የነፃነት ልብ!  

ስለዚህ በመሰንጠቅ አድብቶ ጊዜ እዬጠበቀ ጥቃቱን ለሁሉም ያደርሳል። ይህንም እኔ በ2013 ጽፌው ነበር። አንዱን እስኪያጠቃ ሌላው ወደጁ ነው ለእኩይ መንፈስ ቤተኝነት፤ አንዱ መሞቱን ከረጋገጠ በኋዋላ ቀን ላወጣውም፤ ደግፎት ላቆዬውም አይራራም። ስለምን እፉኝት ስለሆነ። እፉኝት ሲረገዝ አባቱን ሲወለድ እናቱን ነው የሚያጠፋው። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ፈላስፎችም እፉኝት ነው መንፈሳቸው።

 ማጥፋት እና በማጣፈት እራስን እያራቡ መኖር ነው ህልማቸው የነበረው። የኔዎቹ ጅሎች ጎንደሬዎቹ ቅምናቶች ያልገባቸው ይኸው ብሂል ነው። ዘመን ያላስተማራቸው፤ ባሉበት የቆሙት የቅምናት ሊሂቆቻቸው የአስተሳሰብ ደረጃ የሚለካውም ከዚህ አንጻር ነው። አሁን ሽፍትንት ባሰኘው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌሰቶ ማህበርተኝነት እነሱ የልብ ናቸው። ልባቸው ውልቅ ያለው ያለው ይህን የለውጥ ዘመን ተጻሮ ከቆመው እኩይ ጋር አብሮ መሰለፍ ነው - ለዛውም በብቸኝት።

መላ ኢትዮጵያ አይደለም መላ ዓለም የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ጸረ ሰብዕና ፀረ ተፈጥሮነት አንቅሮ በተፋበት ወቅት እነሱ ጋሻ ጃግሬ ሆነው ለውጡን ላመመስ እና ለማታረማስ ጸላዬ ሰናይ ሆነው ተሰለፍዋል። ይቅር ይባላቸው። አሜን! 

ከዲያቢሎስ መንፈስ ጋር ህብረት ሳጥናኤላዊነት ነውና። ቢያንስ በግፍ የተፈናቀሉት 2 ሚሊዮን ወገኖቻቸው በሰው ሰራሽ ስለመሆኑ ሊረዱት አልፈቀዱም። ዕዝነ ልቦናቸው ተሸፍኗልና። ጊዜው ደርሶ እነሱን ቀጥቅጦ እንደ ብረት አቅልጦ አሮጌ አካፋ እና መዶሻ እስኪያደርጋቸው ድረስ ቁምጥ ብለዋል። ከአሰር ጋር ማህበርተኛ ሆነዋል። የሽሁራር ቤተኛነት ሽው ብሏቸዋል። ዲሪቶ አሰኛቸው ... ማህከነ! 

በዚህ በ27 የግዞት ዘመን ብዙ ተቋማዊ መንፈሶች ባክነዋል፤ ተንደዋል፤ ፈርሳዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ያልተለመዱ ባዕድ የሆኑ የዲቃላ እሰተሳቦች ሙጃዎች ደግሞ ፈልተዋል። ሁሉም ቦታ ብክል ነው። ይህ ይሻላል? ይህ ደህና ነው? ይህኛው ቢቆይ አይጎዳም የሚባል አንድም ቦታ የለም። ሁሉም ብክል ነው። ለዚህ ነው ይህን ለውጥ ፈተናውን ያበዛው።
ለዚህም ነው ይህ ለውጥ በሁሉም ቦታ እርምጃ ልወሰድ ቢል መለመላውን እንደሚቀር አውቆ፤ በጣም የተጎዳውን ብቻ በመለዬት ያን ለማከም ጥረት እያደረገ የሚገኘው።

በረቂቅ ሁኔታ የልቤ ብሎ ላሰበው ይህ ለውጥ ልቡ የእግዚአብሄር ነው። ስለምን ቢባል ከበቀል የጸዳ መስመር ነው የተከተለው። የተነሳው ከምህረት እና ከእርቅ መንፈስ ነው። ስለዚህ በቋሳ በበከተ የደቦ መንፈስ ውስጥ ይህን የአርቅ እና የምህረት መንፈስ መሰረት ለመፍጠር እጅግ አድካሚ ብቻ ሳይሆን የሚታሰብም አልነበረም። አንድ ትውልድ በ በአንዱ ቢያመልጥ በሌላ ተበክሏል። አንዱን ቢያስፈነጥር አልሻህም ቢለው በሌላ ስንቅር ተጠቅቷል። ሁሉም ቪክተም ነው።

ሌላ ሃይል እድሉን ቢያገኝ ኖሮ ግን ሁሉንም ጥርግርግ አድርጎ አፈራርርሶ በቀሉን እስኪበቃው ተወጥቶ፤  ከዜሮ ነበር የሚጀምረው። ያው እንደ ለመደብን። በዚህ ውስጥ የሚባከነው ስልጣኔ ብቻ ሳይሆን የሁሉም የስከነት መንፈስ አብሮ ይቃጠል ነበር። ይህ ትንሽ ከበድ ስለሚል በሌላ ጹሑፍ እመለሰበታለሁኝ።

የሆነ ሆኖ ይህ የትህትና አብዮት ሊያስገኝ ያሰበው ሃሳብ ኢትዮጵያዊነትን ገላጭ በሆኑ ትሩፋት ውስጥ ሆኖ፤  ኢትዮጵያን በሞራል ማበጀት ነው። ስለዚህ ፈተናው ግዙፍ ነው ማለት ነው። ተግባሩም እዮባዊነትን የሰነቁ አደቦች ያስፈልጉታል። 

ለዚህም ፈጣሪ አልነሳነም። ቁንጥንጡን መንፈስ ሁሉ በመግራት ስክነትን እዬገነቡ። ይገኛሉ አብዝቶ የተሰጣቸው ናቸው። የድምጻቸው ምት እራሱ በዚህ መከራ እና ማዕት ውስጥ ያሉ አይመስሉም። እኔ እጅግ ነው የሚገረመኝ። በተመስጦ እና በጥሞና እማዬው ፈጣሪ የሚሰጠው ምርቃት እንዲህ ርቁቅ ሁለገብ እና ሁለንትና መሆኑን ተምሬበታለሁኝ። በዕድሜ ከሁሉም ታናሾች ሆነው በሥርዓት ደግሞ እጬጌዎች ናቸው። የታደሉ! እኛም ታድለናል! ተመስገን! 

እራሱ ይህን ያልተረዱ መንፈሶች ወከባን ይሻሉ፤ በቀልን ይሻሉ፤ ጥርግርግ ያለ እርምጃን ይሻሉ፤ ሙሴዎቹ ከተነሱበት ዓላማ ጋር ሊገናኙ ባለመቻላቸው። እነሱ ቢሆኑ ያደርጉታል። ግን ዕድሉ ያለው በአዲሶቹ ሙሴዎች በእነ አብይ ለማ ገዱ ደመቀ አንቤ መንፈስ መዳፍ ህሊና መንፈስ ውስጥ ነው።

የሚገርመው በጥሞና ለሆነ ሰው ሁለቱንም ነው እየታዘቡ ያሉት እንዚህ ሙሴዎች ችኩሎችንም በቀል ያሰኛቸውንም፤ ሴረኞች አፍራሽ እፉኝቶችንም። እግዚአብሄር የሚመሰገነው ሃላፊነት የሚሰማው ሚዛናዊ አመራር ኢትዮጵያ ስለሰጣት ነው። አነኝህ ምርዩቃን ችሎት ናቸው ለዘመኑ። ትወልዱም ሎተሪ ወጥቶለታል። እዬተገነባ ያለው የማይታይ ግን ረቂቅ መሰረት ያለው ሁለገብ ተግባር እጹብ ድንቅ ነው። ሚስጢር ነው። ስጦታው የፈጣሪ ስለሆነ።

·       ለቤተ አማንያን እንዲህ ልላቸው ፈለግሁኝ

ክርስትናም ሆነ እስልምና ጽናት ነው መሰረቱ። ጽናት ደግሞ ደጅ አዳሪ ሳይሆን ልብ አደሪ ነው። ስለዚህ የሁለቱም አማንያን ጽናትን እዳሪ አዳሪ ሳያደርጉ ልብ አዳሪነቱን እውቅና ሰጥተው መሆን ካቻሉበት በርግጥም ለዓይናቸው ጥበቃ ወታደር ሆኑ ማለት ያስችላል።
እንደዛ እንደ መርግ የከበደውን ያቀለለ አምላክ ቀሪው ጊዜ የሚያስደስት እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይሆንም። ይህ የሚሆነው ግን እያንዳንዱ በግል ሁሉም በጋራ ሲጥር ብቻ ነው። የሰላም ልዑካን በዬአካባቢው መላክ አይደለም ቁም ነገሩ።

                                                 ማህደራዊነት!

ክፉዎችን አለመተባበር፤ ለክፉዎች ጋሻ ጀግሬ አለመሆኑ፤ የሃይማኖቶች አበው ክፉዎችን ደፍሮ መገሰጽ፤ ከአውነት ጎን ሳያወላዱ መቆም፤ ክፉዎችን ከስህተታቸው እንዲታረሙ መድፈር ማለት ከራስ መጀመር ማለት ነው። ከሊቅ እስከ ደቂቅ አበው ሊቃናት የእስልምናም ይሁኑ የክርስትና ሐዋርያት መጀመሪያ ከራሳቸው ይነሱ። ይህ ነው የሚቀደመው። 

እነሱ የጣሱትን የቁራዕን ህግጋት፤ እነሱ የጣሱትን የወንጌል ህግጋት ማን እንዲያከብራላቸው ይሻሉና? በዚህ ጥሰት ፈጽመው በዚህ ደግሞ ግንባታ አይሆንም፤ በፍጹም። ሁሉም ሥርዓተ ቀኖና፤ ሥርዓተ - ዶግማ አላቸው ይህን እዬተጋፉ፤ ይህን እዬዳጡ ምዕመናን ስለ መልካም ተግባር መስበክ የዱብሽት ቤት ወይንም የውርንጫ ድካም ነው የሚሆነው።

·       የምርቃቱ ዘመን ሊገባን ይገባል።

የመጀመሪያው ቁም ነገር ሃይማኖት ብሄር እና ብሄረሰብ የለውም። ሃይማኖት የቆዳ ቀለም አምልኮው አይደለም። ሃይማኖት የቦታ መስመር ተልዕኮው አይደለም። ምድሪቱ እና ተፈጥሮዋ የፈጣሪ ናቸው እና ልትጠብቃቸው ተፈጥረሃል ነው የሃይማኖት ተልዕኮ።

ስለዚህ ሁለቱም ሃይማኖቶች ክርስትናም እስልምናም ለዚህ የምርቃት ዘመን ወታዳሩ ሊሆኑ ይገባቸዋል። እንደ ሥርጉተ - ሥላሴ መንግሥት አድርጉ እስኪላቸው መጠበቅ የለባቸውም፤ አልነበረባቸውም። መንግስት እርዱኝ እስኪላቸው ድረስም ማንቀላፋት አይኖርባቸውም። 

ለምሳሌ ለሚፈናቀሉ ወገኖች መጠለያ መስራት ይኖረባቸዋል። በጀት በቋሚነት መመደብ ይኖርባቸዋል። ስንቅ ማቀበል ይኖርባቸዋል፤ የህክምና አግልግሎትን ማሟላት ይኖርባቸዋል። የዕምነት ልጆቻቸው ተፈናቅለው ረመዳን፤ ትንሳኤ፤ መውሊድ፤ ገናን እንዴት እንደሚያከበሩ ማሰብ ይገባል - ከውስጥ ሆኖ። ለዛውም ለ እለት ከፈን ያልበቃ ማህበረሰብ ነው ያለን። ድሆች እኮ ነን። ለምንን አዳሪዎች ነን እንደ አገር። 

አንዲት የ4ኛ ክፍል ተማሪ ጎንደር ከተማ ላይ ልደቷን ረዳት ካጡ ልጆች ጋር ነው ያከበረችው። የታናሽ ወንድሟን ልደት ደግሞ ሚዚያ ላይ ይመስለኛል እነዛን ምንዱባን ልጆችን በክብር ጠርታ አብረው እንዲያሳልፉ እንደምታደርግ ሰምቻለሁኝ። ለእሷ ጉዳይ እኛ የምነታመሰበት ጉዳይ አይደለም። በዛ ድህነት ውስጥ አቻዎቿ ማን ይሁኑ ምም ደስታ በማጣተቸው እሷን ደስ ሲላት ደስታዋን ለማጋራት እነሱን መርጣ እራሷ ሄዳ አብራቸው አከበረች ልደቷን። ስሰማ እኔ ሰውነቴ መቆጠጠር አልቻልኩም፤ እንባዬንም እስከ ማግስቱ መግታት አልቻልኩም። እኔ አማስው ትውልድ እንዲህ ዓይነት ነውና። 

ይህች የልቤ ሙዳይ ቀንበጥ ለጋ ገና ከዛሬዋ የልጆች መብት ተሟጋች ሆናለች - ለዛውም ጎንደር ላይ። ወላጆቿ በቅዱስ ቁርባን ጋብቻ እንደፈጸሙ አውቃለሁኝ። ዜግነቷን  ለመጀመሪያ ጊዜ ደውዬ ስጠይቃት ግርማ ባለው እርግጠኛ ድምጽ „ኢትዮጵያዊ ነኛ!“ ነው ያለችኝ። ሃይማኖቷን ስጠይቃት „ክርስቲያን ነኛ!“ ነው ያለችኝ። እሰቡት የኦርቶዶክስ አማንያን ልጅ ናት ግን እሷ ወንጌልን መሰረት አድርጋ „ክርስቲያን ነኛ!“ ነው ያለችኝ። ምን መሆን ትመኛለሽ ስላት „ተመራማሪ“ መሆን ነው የምፈለገው ነው ያለችኝ። 

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወላጆች ለውጡ እንግዛለን ካሉ እንዲህ ነው ልጆቻቸውን ማሳደግ ያለባቸው። ልጆቻቸው ሰውን ማዕከል እንዲያደርጉ እንዲሁም ሩህሩህ እንዲሆኑ። የሰብዕዊ መብት ተሟጋች እንዲሆኑ። ህዝባችን በሥነ - ልቦና ተጎድቷል። መኖሩ ተሰብሯልና። እንዲህ ዓይነት የሚተዛዘን ትውልድ መፍጠር ቀዳሚወን ድርሻ የሃይማኖት ተቋማት መውሰድ ይገባቸዋል። 

ይህቺ አብነት፤ ይህቺ ልዩ የሆነች ቀንበጥ ታዳጊ ወጣት ይህን ያህል ስታስብ ለእኩያዎቿ፤ ባለቤት ለሌላቸው የእኔ ቢጤ ልጆች የሚገርም ነው። እንዲህ ያለ የሰብዕዊነት ጉዞ በዚህ ዕድሜ ከዚህ አገር አድምጬው የማላውቀውን ትንግርት ስትፈጽም ለዛውም ጎንደር ላይ፤ የቅኔ ባላባቶች አባ ወራዎች እጬጌዎች፤ ሊቀ ጳጳሳት/ ፓትርያርክት፤ ሐጂዎች፤ ሸኸሆች፤ ኡስታዞች፤ ፓስተሮች፤ ካህናት፤ ቆሞሶች፤ ዲያቆናት እንደ ተቋምም መስኪዶች እና ቤተ እግዚአብሄሮች እንዴት በወገናቸው ጉዳይ ላይ ቋሚ ሁኔታ አያደራጁም? በዚህ ዙሪያም አንድ ጹሑፍ መጻፌን አስተውሳለሁኝ። 

ስብከተ ቁርዕና ሆነ ስብከት ወንጌል ከልብ የሚገባው መሬት ላይ የሚሠራ ነገር ሲኖር ነው። አብሶ ልጆች ከሚሰሙት ነገር ይልቅ በሚዩት ነገር ይመሰጣሉ። ብዙ ጎድሎብናል። እንደ ሰው በተሰጠን መክሊታችን ውስጥ አይደለንም።

·       አብነትነት። 

አብነቱ ጎንደር የሥነ - መንግሥት ተፈጥሮ ባለቤት ስለሆነ የእስልምና ሃይማኖት ባዕላቸውን ሲያከብሩ የጅጅጋው የቤተ እግዚአብሄር እና የሐዋርያት ስምዕትነት ሰሞናት ስለነበር ያን ለማስታረቅ የጎንደር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃማኖት አማንያን ዓውደ ምህረቱን የመጸለያ ቦታውን ፋሲል ግንብ ውስጥ ነበር ካልተሳሳትኩ፤ ከተሳሳትኩ እታረማለሁኝ በወል በባለቤትንት ስሜት አጸዱ።

መከረኛው ቡራዩ፤ አዲስ አበባ እና አርሲ ላይ  ቅዱስ ዮሖንስ እና መስቀል ባዕል መከራ ሲመጣ ደግሞ የጎንደር የእስልምና ሃይማኖት አማንያን ፒያሳን የመስቀል ደመራ ቦታ አጸዱ። አያችሁ ልቅና። አያችሁ ብልህነት። ይህ ነው ለውጡን ማገዝ መደገፍ ማለት። ያ እርምጃ የኢትዮጵያን ዕንባን አደረቀ፤ የተጠነሰሰውን መርዝ ቂም በቀለን ቀበረ፤ ያ ትሁት እርምጃ። ትሩፋትም ነው። ትውፊትም ነው። ለዚህ ነው አዲስ አጀንዳ የወያኔ ሃርነት ማንፌስቶ ባላንባራሶች የቅማንትን ጥያቄ ይዘው ከች ያሉት። 

ለውጡን አገዘን ለማለት አጀብ አያስፈልግም። የክርስትና እምነት አማንያን፤ ፤ መካነ እዬሱስ፤ የወንጌላዊ፤ የፕሮቴስታንት፤ የሚሲዮን፤ የካቶሊክ፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ፤ የይሁዲ፤ የእስልምና አምናያን፤ የዋቄ ፈታም በዬተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ክፉ ነገርን አለማስጠጋት፤ ቂምን መጸዬፍ፤ ክፉ ነገርን አለመተባበረ፤ በሥራ ቦታቸው ቀድመው በመግባት ዘግይተው በመውጣት፤ ሰንበትን ጨምሮ በመሥራት፤ የደከመን በማገዝ፤ አካባቢያቸውን በማጽዳት፤ ፋፍሪካዎቻቸውን በቅርብ ያሉትን በትርፍ ሰዓት ተገኝተው በመርዳት፤ ሆስፒታል ያሉ ህምምተኞችን በመጠዬቅ፤ ለውጡን ማገዝ ይችላሉ። 

ታሪሚዎችን በቦታው ተግኝተው በማዬት፤ የደከሙትን በማጽናናት፤ ጎዳና ላይ ያሉ እህት ወንድሞቻቸውን አካፍሎ በማደር፤ ያለውን ትርፍ ነገር በመስጠት፤ መጋዝን የሚያሞቁ ልብሶችን አውጥቶ በማደል፤ ያልተማሩትን ት/ቤት ከፍቶ ፊደል በማስቆጠር ብዙ ተግባራትን ተቃናጅቶ ክለብ በመፍጠር መትጋት ለውጡን ማገዝ ነው።

ለሃሜትም፤ ለበቀለም፤ ለክፉ ነገረም ጊዜ አይኖርም በዚህ መሰል ተግባር ማህበረ ምዕመናን እንዲሰማሩ የሃይማኖት ተቋማት ቢሰሩበት። የአካባቢያቸውን ውበት ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮ ጤናማ ለማደረግ ራስ ታጥቆ በማጽዳት ተፈጥሮን በመንከባከብ ነው ጤናማ ማህበረሰብ መፍጠር የሚቻለው። አሁን የከተሞች ማዘጋጃ ቤቶች ብዙ ሊረዱ ይገባቸዋል። ለአገር መስራት እኮ በነፃነት ትውልድን መገንባት ነው። አገር መውደድ ውጊያ ላይ መገኘት ብቻ ሳይሆን በሚችሉት እኔም ሃላፊነት አለብኝ ብሎ የበኩልን ለመወጣት በመጣር ነው።


·       ተገፊዎች ግንባር ቀድምትነት ይጠበቀብቸዋል።

አበሶ የእሳቱ ወላፈን ሳይሆን ነብልባሉ የቀቀላቸው እያገላበጥ ያቃጣላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እና እስልማና ሃይማኖት ይህን ዘመን እንደ አባት አደሩ እንደ ቅኔያማዎች ዘመን ይህን የምርቃት ዘመን በቁሙ ሊያነቡት፤ ሊተረጉሙት፤ ሊያመሳጥሩት ይገባል። ወደ ተግባር ለመግባት ቀን ሊሰጠው አይገባም። ዲያቢሎስን የሚያሳፍር ተግባር ለመፈጸም ቀጠሮ አያስፈልገውም። ጎስጓሽ አይስፈልገውም።

ምንድን ነው ሥራቸ የሃይማኖቶት ተቋማት? የዲያቢሎሳዊ የደቦ ጉዞን ካልታገሉ እና ካላሸነፉ? የደከመን ካልረዱ? ተስፋ ያጡትን ካላጽናኑ? የሚገርመው አንድም የሃይማኖት ተቋም 2 ሚሊዮን ወገኖች ሲፈናቀሉ እንኳንስ እርዳታ ለማሰባሰብ ሄዶ ለማዬት እንኳን አልደፈረም። ይህም ማለት የሴራው ተባባሪ ናቸውን ያሰኛል?በሌላ በኩል ተቋማቱ በዬሉም ያሉ ደመነፍስ መሆናቸውን ያመሳጥራል።

ሃይማኖታዊ ተቋማት ተልዕኳቸው የእናት ነው። ቀድመው እቦታው መደረስ የሚገባቸው እነሱው ነበሩ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ። በሰከነው በተረጋጋው ቦታ የንግሥና ባዕልም ያደላቸው ነው የሚገኙት። 

እኔ እውነት ተናገሪ ብባል 5ኛው ፓትርያከ ዘኢትዮጵያ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከህዳር ጽዮን ይልቅ እሳቸው ጅጅጋ ቢሄዱ፤ ሙያሌ ቢሄዱ፤ ውልቂጤ ቢሄዱ፤ ባህርዳር ቢሄዱ ነበር የሚያምርባቸው። ታሪክ መቼም ሾልኳልኝ። የቤተ ክርስትያኗም ክብር የተላመጠ አገዳ ሆኗል። ይህን የፈተና ዘመን ለማለፍ ሃላፊነቱን ለመውሰድ ድፍረት ርቋታልና።

በዚህ ዘመን ቅድስተ አገር እስራኤል፤ አክሱም ጽዮን፤ ላሊበላ፤ ግሼ አይደለም መሄድ የሚገባው ማህበረ ምዕመን በሙሉ መሄድ የሚጋባው ያ ብርቱ የደግነት ሐዋርያት የጂቲቪ ዋና አዘጋጅ የደግነት አንበል ዮሴፍ ገብሬ እንዳደረገው ማድረግ ነበር። እሱ ትንሳኤን  ከእነሱ ጋር ነበር ያከበረው። ሃይማኖት የገብያ ውሎ ሳይሆን የነፍስ ውሎን ስለሚጠይቅ። 

በሰው ሠራሽ መፈናቀል ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች አሉን፤ በሰው ሰራሽ መፈናቀል የተደፈሩ ልጆች አሉን፤ ቢያንስ እንዚህን ማደሪያ ቤት ማዘጋጀት፤ ወደ ትምህርት የሚሄዱበትን ሁኔታ ማመቻችት ያስፈልግ ነበር።

መከራ ውስጥ ላለ ህዝብ ቀርቶ ምቾት ውስጥ ላለም ቢሆን የደከመን፤ የተቸገርን፤ የታመመን፤ የተበደለን፤ ተስፋን ያጣን ማጽናናት መርዳት ሃይማኖትም፤ ዞግም፤ ቀለምም አይጠይቅም። ከዚህ ያሉ የፕሮቴስታንት ይሁኑ የካቶሊክ ዕምነት ተቋማት የደግነት መንፈሳቸው በእኩልነት ለሁሉም ነው። የሃይማኖት ተቋማት የተፈጠሩበትን የሚሠሩ ማለት ያስቸልኛል። 

የትኛውም ችግር ሃይማኖትም ብሄርም የለውም። ችግር ያለው ሰው መሆን ላይ ብቻ ነው። ችግር ነው የሰው ማህበርተኛ። የወንጌልም የቁራንም አማንያን በዚህ ዙሪያ ተበትነው ሳይሆን ተቋም ፈጣረው ድንገተኛ አደጋን የሚቋቋሙበትን ቋሚ ተግባር መጀመር አለባቸው - ኢትዮጵያ ውስጥ። ይህ ክፈተት አለ። ይህን ክፍተት የሃይማኖት ተቋማት የመሙላት ግዴታ አለባቸው። 

አሁን ኢትዮጵያ መንግሥትን ስላላት የኢትዮጵያን መንግሥት ሊረዱት የሚችሉት ቁንጢ ቢጢ ነገር በማድረግ ሳይሆን እንዲህ ነፍስ ባለው ነገር በቋሚነት ራሳቸውን አደራጅተው እና አጠናክረው በባለቤትነት ለድርሻቸው ሲተጉ ብቻ ይሆናል። ያን ጊዜ ጽድቅን በሥጋ ከተለዩ በሆዋላ ሳይሆን በምድርም ሆነው ያገኙታል። አሁን ደግሞ ውጭ የቆዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት አባቶች ብዙዎቹ በቀለም ዕውቀት የገፉ ናቸው። ይህን መሰል ተግባር እና ሃላፊነት ለመወጣት ብቁ ናቸው። 

ስለሆንም እርዳታ የሚያደራጁበት፤ የሚመሩበት፤ የሚያቀናጁበት ተቋማዊ ብሄራዊ ነገር መፍጠር ይኖርባቸዋል። ለዬትኛውም ድንገተኛ አደጋዎች የሃይማኖት ተቋማት ቀድመው የተሟላ መሰናዶ የሚደርጉበትን ሁኔታ መፍጠር አለባቸው። ሁሉን ነገር መንግሥት አይሠራም። የሃይማኖት ተቋማት በዚህ ዙሪያ ልብ ያለው ተግባር መፈጸም ግድ ያላቸዋል።

ልምዱን ከሆነ ሊቀ ሊቃውንቱ ዶር ካሳ ከበደ አሉ፤ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፤ ኡስታዝ አህመዲን ጀቢል ቀሲስ ዶር ገመችስ ደስታ፤ ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝም ውስጡ ሰውኛ ስለሆነ ለተጎዱት ልዩ ዝንባሌ ስላለው እሱም አለ። ኢትዮጵያ ብዙ ነገር አላት ፈቃዱ፤ ቅንነቱ ከኖረ ... 

ለእነዛ ለ2 ሚሊዮን ለተፈናቀሉት፤ አሁንም እዬተፈናቀሉ ላሉት መንዱባን የሃይማኖት ተቋማት ሃላፊነቱን ሊወስዱ ይገባል። ሃብታሞችም ናቸው። ሚዲያቸው እራሱ በዚህ ዙሪያ መስራት አለበት። 

·       ይቋጠር።

ተቋም በቋሚነት ማደራጀት፤ የእርዳት አስተባባሪ ግብረ ሃይል በሙሉ ድርጁ መንፈስ መመሥርት ይገባል። ማህበረ ምዕመኑ የለውጡ ወታደሮች እንዲሆን በመንፈስ ማዘጋጀት፤ ልጆችም በሞራል አንፆ ለማሳደግ መጣር፤ ሁሉም በዬተሰማራበት የሥራ መስክ ከሚከፈለው በላይ ይሰራ ዘንድ ማስተባበር የሃይማኖት ተቋማት ቋሚ ተግባር ሊሆን ይገባል። 

ይህ ለወጥ ለግብ ባይደርስ ተጠቂዎች ሃይማኖቶች እና ማህበረ ምዕመናን ብቻ ናቸው። ዛሬ ያ የትናንቱ ይጉዕዝ የዕብን ጉዞ ላይ አይደለነም። ዛሬ አዲስ ቀን፤ ዛሬ አዲስ ቀለም ያለው ነው። ይህን አዲስ ቀን እና አዲስ ቀለማም ቀን ማሳመር ማስዋብ ደግሞ ከቁራዕን እና ከወንጌል አርበኞች የግንባር ቀድም ድርሻ መነሳት ግድ ይላል። 

መንግሥት ባላቻላቸው ቦታዎች ሁሉ ተቋማቱ ክፈተቱን የመሙላት ሃላፊነት አለባቸው ሰማያዊ ተክሊል ካሰኛቸው። በስተቀር ገሃዳዊው ዓለም ወታደሮች በመሆን መክሊታቸውን ይተላለፉታል፤ ምርቃቱም ይነሳል። ዘመኑ የምርቃት ነው ለልበ ብርሃኖች። ምርቃቱ እንዳይነሳ እግዚአብሄር/ አላህ በሚያስደስተው መልካምነት፤ ቸርነት፤ ደግነት፤ ሰዋዊነት፤ ተፈጥሯዊነት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ...   

Ungerecht (injustice) neue
Published on Jun 28, 2015

ይህን አለፍነው በፈጣሪ እርዳታ እና ጥበብ፤ ያለፍነውን እንዳይድግም ልብ ይኑረን፤ በማስተዋል እንራመድ! የድርሻችን እንወጣ፤ ፈጣሪ ይህን ስላደረገልን ምስጋናው በተገባር መገኘት ይሁን። ለዛሬ ይሕው ይብቃኝ …

ትውፊት!


ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር ነው!


የኔዎቹ ቅኖቹ ፌስ ቡክ ያለችሁ ሸር አድርጉልኝ።
ኑሩልኝ ክብረቶቼ።


                         ማለፊያ ጊዜ - ኑረልኝ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።