የገቢዎች ቀን አዲስ ጥረት በኢትዮጵያ።

የገቢዎች ቀን አዲስ
ጥረት በኢትዮጵያ።

„ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? 
እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል።
እናንተም፦ የሰረቅንህ በምንድር ነው? ብላችኋል።
በአሥራትና በበኵራት ነው።
ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ።“

ትንቢተ ሚልክያስ ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፲፱
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ



ዛሬ አንድ ዜና አዳምጥኩኝ የገቢዎች ሚ/ር የዘጋጀው ጉባኤ ነው። በጉባኤው ላይ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ተገኝተዋል። ጉባኤውን ያዘጋጀው የገቢዎች ሚ/ር ነው። ዛሬ በነበረው የጉባኤ ባህሬ ላይ አንድ ያስተዋልኩት ቁምነገር አለ። 

ዶር አብይ አህመድ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚ/ በነበሩበት ጊዜ ከእርምጃ ወደ ሩጭ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ የነበረው ሙሉ መንፈሳቸውን አይቻለሁኝ። ዘና ያለ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን እርግጠኛ የመሆን አቅሙም ያን ያህል ጉልበታም ሆኖ ነው ያዬሁት፤ በግራ በቀኝ የሚወራጨውን የማህበረ ደራጎን የተስፋ ንጥቂያ ዘመቻ እና ትብትብ ሴራ ከመጤፍ አልቆጠሩትም። እንደ ዛን ጊዜው ሚ/ር እንደነበሩበት ወቅት ቅልል ብሏቸዋል።

https://www.youtube.com/watch?v=vu-kkIUohRw&t=76s

Ethiopia - Dr Abiy ኢትዮጵያን ማሸጋገር ይቻላል!


ከራዕያቸው ለመድርስ በሚያደርጉት ጉዞም አሸነፊ ሆኖ የመውጣት መንፈስ ልክ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በነበረው አቅም ልክ ነው እኔ ያዬሁት -ዛሬ። ሁልጊዜም እኔ እንደምለው ንግግሩን ብቻ ሳይሆን የሰብዕን ውስጣዊ መንፈስ ለማግኘት ወደ ውስጥ ሰርስሬ ማዬትን ነው ምርጫዬ። ዛሬ የሰጠኝ ግብረ ምላሽ በጠ/ሚር አብይ አህመድ በኩል የመንፈስ ሙሉዑነት እና የለውጡ በሁለቱ እግሩ የመቆሙ የምሥራች አዲሳዊነት ሲሆን፤ ይህን እንደ ብሩህ ዜና አድርጌ ነው ያዬሁት

ስለምን? የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ /ሚር በነበሩበት ጊዜ ሞቷቸውን በውጥን ሲጀምሩም ሲቀጥሉም የሄዱበት መንገድ የመቻልን ጉልበታም ተስፋን ያመሰካረ ነበር። ከጃኬታችን እናውልቅ እሰከ ከእርምጃ እስከ ሩጫ ነበር።

Ethiopia - Dr abiy ሚኒስትር ከመሆንህ በላይ ሰዉ ነህ!

ዛሬ የቀደመው ማንነታቸው ከፍ ባለ አዲስ ማንነት መተካቱ ብቻ ሳይሆን በቀደመው ማንነታቸው ከነበራቸው የአንድ የሚ/ር መ/ቤት ሃላፊነት ወይንም የካቢኔ አባልነት ወደ ካቢኔውን መሪነት የተሸጋገረ ሆኖ ሳለ ዘና ያሉበት ሁኔታ ደግሞ ቤተሰባዊ ሰብዕናቸውን አጎልቶታል። ይሄ በዬአቅጣጫው ያለው ገጭገው፤ በግልጽም በስውርም የሚታዬው የሴራ ደቦ መታመስ ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ ስለመሆኑ በዛሬው ስብሰባ ገፃቸውን ሳይ የሰጠኝ አዲስ ቃናዊ መልዕክት ነው።

ይህ ጉባኤ መብትን ለማግኘት ግዴታን መወጣት፤ ግዴታን ተወጥቶ መብትን መጠዬቅ የሚል ነው። አሁን ከሆነ የማዳምጠው መብቴን እጠቀማለሁኝ ግን ግዴታዬን ግን አልወጣም ዓይነት ነው። በግልም በወልም እማነበው፤ እማዳምጠው።

እንደ ድርጅትም ቢሆን ራሱ ህውሃት መብቱ ተጠብቆ በብሄራዊ ደረጃ ይሁን በክልል ሊያገኝ የሚገባው ተሟልቶለት፤ ውክሎቹ በፌድራል ደረጃ ቁልፉን ቦታ እና ሃላፊነት ይዘው፤ ማሃያቸው ሳይሰተጓጎል፤ ክብራቸው ተሟልቶ እዬተንፈላሰሱ፤ ግዴታን በመወጣት ግን እኔ የስለት ልጅ ነኝ ጠያቂ እንጂ ተጠያቂ መሆን አይገባኝም ባይ ነው ድርጅታቸው።

ራሱ በፌድራል ደረጃ ያሉ የድርጅቱ ሹማምንቶች፤ በውጭ የሚገኙ አንባሳደሮቹ ሁሉ መብታቸው ተከብሮ፤ ድርጅታቸው ግዴታውን ባለመወጣቱ፤ አመጽ ላይ መሆኑ አይጎረበጥቸውም አይፈልጣቸውም አይቆርጣቸውም።

ሌላው መብቱ ተጠብቆ ግዴታውን ለመወጣት ፈቃደኛ ያለሆነው እንደ ድርጅት ደግሞ ሞገደኛው የአቶ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ ነው። በዚህ ተከብሮ ይንፈላሰሳል፤ መሬት ላይ ደግሞ የሚፈልገውን ያተራምሳል። ማተራመሱም ተፈቅዶለት ነው። ተጠያቂነት የሌለበት ልቅ የመብት አሰጣጥ።

ትግራይ ላይ ባዶ 6 ያሉ ወገኖቻችን ስቃይ ላይ ናቸው፤ ምዕራብ ወለጋ አሁንም ሞት እልቂት ስደት ነው ዜናው ሁሉ ደቡብ ላይ አማሮን፤ ቤንሻጉልን ጨምሮ። የራስን ደሴት ፈጥሮ መብትን እየኮመኮሙ ግዴታን ማሽቀንጠር ነው የሚታዬው። ይህም መቸም ሰው ከሚባል ፍጡር፤ ህሊና ካለው ነው ብሎ ለማሰብ ይቸግራል።

ይህ ዛሬ የተካሄደው አዲስ የገቢዎች የማሳባሰቢያ አገራዊ ንቅናቄ በተወሰነ ደረጃ ግዴታን መወጣት ምን ያህል ትውልዳዊ ድርሻን መወጣት እንደሆነ አማላካች ነው። ህሊና ላላቸው እንደ ሰው ተፈጥረው ሰው ነኝ ለሚሉ ሁሉ።

 „ግዴታዬን እውጣለሁ፤ መብቴን እጠይቃለሁ“ መርሁ ጥሩ ነው። መርሁን ለማስፈጸም ግን ፈቃደኛ የሆነ ህሊና ያስፈልጋል። ከሁሉ በላይ ሰላም ያስፍልጋል። የሰላም ጠንቅ የሆኑት እጃቸውን መሰብሰብ ካልቻሉ ግብር መሰብሰብ አይቻልም። ግብር መሰብሰብ ካልተቻለ ህግ መተለላፍ ተፈጥሯል ማለት ነው። ህግ መተላለፍ ከመጣ አገር እንደ አገር ማቆም ይችግራል። ግብር ጉሮሮ ነው። ይህ ደግሞ በተደራጀ ሁኔታ ሲሰራ የቆዬበት ነው።

ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ ንቅናቄ፤

የገቢዎች ሚኒስትር / አዳነች አቤቤ ብሄራዊ የታክስ ንቅናቄ ማስጀመሪያ ላይ ያደረጉት ንግግር


የሆነ ሆኖ በጉባኤው ባልተለመደ ሁኔታ ሁለት /ሦስት ውክል አካላትን አይቻለሁኝ። አንደኛው የተማሪዎች ነው፤ ሁለተኛ የተፎካካሪ ተወካዮች ድምጽ ነው። የመምህራንም እንዲሁ በሦስተኛ ማዬት እንችላለን፤ መቼ ነው እኔ ስለመምህራን የጻፍኩት? ከትናንት በስቲያ „ለማ ትወልድ ነው“ በሚል ርዕሰ ጉዳይ። የተደራጀ ብሄራዊ አትኩሮት የሚሻው መሰረታዊ ጉዳይ ስለሆነ። ዛሬ ይህን ዜና ስሰማ ደስ ነው ያለኝ።

https://sergute.blogspot.com/2018/12/blog-post_98.html

እንዲህ የመምህራን ድምጻቸውን እንዲያሰሙ መወጠኑ መልካም ጅምር ነው። ግን በድርጀት ቢሆን የበለጠ ፍሬያማ ነው የመምህራን ማህበርም አገር በአዲስ በበለጸገ አዎንታዊ የትውልድ መንፍስ ለማነፅ ሰቅ ነው።

አብሶ የገጠር መምህራን ለግብር አሰባሰብ አንባሳደር የሚሆኑበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም ነው። እነሱ ሊንክ ናቸው ለሁሉም ብሄራዊ ነገር። ገበሬውን በቅርብ ማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ገበሬው የሚኖረውን ኑረው ፈቅደው አብረውት ያሉ ቤተሰቦቹ ናቸው እና። ያደምጣቸዋልም። የአብይ ካቢኔ ማድረግ ያለበት ይህን ብልህ ጉዳይ አደብ በገዛ አትኩሮት ወደ ተግባር መለወጥ ነው። ሌላው ውክልና በአንድም በሌላም በፊትም ለሥምም ለሟሟያም ቢሆን በድርጅት ውክልና ሲፈጸም የነበረ ስለሆነ ብዙ እንግዳ ነገር የለም።

እንግዳ ነገሩ የገቢዎችን አሰባሰብ አገራዊ ንቅናቄን በሚመለከት አንባሳደሮች በፈቃደኝነት ተሰይመዋል። ፈቃደኞችም የለመድናቸው ወገኖች ናቸው ያው ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት። በሁሉም መድረክ የሚታዩት ናቸው፤ አንድ የተለዬ ነገር እኔ ያዬሁት ፈላስማ ዶር ምህረት ደበብ መኖራቸው ነው። እሳቸው ህሊናን በማጽዳት እረገድ ትጉህ ሐዋርያ ናቸው። ፈቅደውም መጡ ተጠይቀው የተገባ እርምጃ ነው።
   
ሌላው ድንቁ ጉዳይ ግን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ውክል አካላት በስተቀር ዬተወከሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ሴቶችም ድምፃቸውን በዬውክል አካላቱ እንዲኖሩ መደረጉ የኢትዮጵያ ቀጣይ ጉዞ ወደዬት ስለመሆኑ አገናዛቢ ይመስለኛል። 

አብሶ የመንግሥት ሠራተኞችን ወክለው የተገኙት እህት አጭር እና ክውን ያለ መረቅ መልክት ሲያሰተላልፉ፤ የተማሪዎች ተወካይ ደግሞ ከማጭበርበር የጸዳ የገቢ አሳባሰብ ሥርዓትን በአፅህኖት በመግለጽ ብርቱ መልክት አሰተላልፋለች ታዳጊዋ። ጠ/ሚር አብይ አህመድንም ከልብ አስቃለች። እሳቸው ለሴቶች ባላቸው ቅንነት ልክ የልባቸውን ያገኙ ይመስለኛል ...



ነገ ይህን መመስሉንም አመላካች ነው፤ ጥሩ እዬሄደ ነው የአብይ መንፈስ ነገን በዚህ መሰል አውነታዊ ሃዲድ በመዘርጋት …

https://www.youtube.com/watch?v=D1ZtxHOmt_w&t=70s

Ethiopia - New Dr Abiy - አንድ ሰዉ ብቻዉን መለወጥ ይችላል!

 

ከሽማግሌዎች ውክልም እንዲሁ አንስት ነበሩ ስለ አገሬ ሳስብ ያመኛል ነበር ያሉት። ይህ መቼም በህልምም ያልታሰበ ዱብ ዕዳ ነገር ነው ለሴቶች ይህን ያህል ዕውቅና ክብር ህልም ህልም እንጂ ዕውነት የማይመስል። ስለሆነም ነው ይህን ለውጥ የመጠበቅ ሴቶች ልዩ ግዴታ እናዳለብን በአጽህኖት እኔ እማስገነዘብው። 

https://sergute.blogspot.com/2018/12/blog-post_5.html

 በንግዱ ዘርፍም ሴት ተወካይ ነበሩ፤ በገቢዎች ንቅናቄ  አንባሳደሮችም እንዲሁ የአንስት ድምጽ ጎላ ብሎ ነው የተሰማው።

ሀገረ ኢትዮጵያ ተጥቅማ የማታውቀውን ቅምጥ የመንፈስ ሃብቷን ለመጠቀም መንገድ መጀመሯ የሚያበስር ነው ጠቅላላ ይዘቱን ስመለከተው እኔ። በዛ ላይ የዝግጅቱ ባለቤት የገቢዎች ሚ/ር ነው። ሚኒስተሯ ደግሞ አንስት ናቸው ወ/ሮ አዳናች አቤቤ ናቸው።

በሳቸው የሚ/ር መ/ቤት ጎላ ያሉ ተግባራት እዬተከወኑ ስለመሆኑ በተለያዬ ዜና አዳምጣለሁኝ። ጉልበታም እንቅስቃሴ እያደረጉ እንዳሉ፤ ፋታ እንደሌላቸው የሚያመላክቱ ሁኔታዎችን አያለሁኝ። ይህ ለሴቶች የማድረግ፤ የመቻል አቅም ብርቱ የተስፋ መንበር ነውእንደሚያሙን ሳይሆን የጠ/ሚር አብይ መንፈስ ባመንን ልክ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል።

·       ድለት።  

ትልቅ ነገር ነገር ግን ይህ ዝግጅት ጎድሎበታል ብዬ አስባለሁኝ። ትልቅ ነገር አሽልኳል። „አብይ ሆይ“ አቤቱታዬ ላይ ጽፌዋለሁኝ። የኢትዮጵያ ገበሬዎች ሁሉንም ድርሻ የሚወጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ሆነው በ27 ዓመቱ የህውሃት መራሹ ኢህአዲጋዊ ዘመን የተዘነጋ ማህበረሰብ ነው ገበሬው።


ገበሬው በማዕከላዊ መንግሥት ይሁን በፓርላማው የረባ ውክልና የሌለው ከመሆኑ በላይ የኢትዮጵያ ገበሬ መብት አልባ የግዴታ ቀንበር ተሸካሚ ሆኖ የኖረው፤ ግን የመኖር እስትፍስ ነው። ባለመኖሩ ውስጥ እያኖረ ያለ ማህበረሰብ ነው ገበሬው። እኔ አደራጅ ከነበርኩበት የማህበረሰብ ክፍሎች ለገበሬው በጣም ነው የማዳላው። አንድ ጊዜ በብሄራዊ ደረጃ የማይገኝ ዕድል አገኝቼ ገበሬውን መርጬ ዕድሌን ሚስ አድርጌያለሁኝ። 

በዚህ የገቢዎች አሰባሰብ አዲስ የዘመቻ መርሃ ግብር ዋነኛ ግብር ከፋዩ ገበሬ ሆኖ ሳለ ግን ድምጹን የሆነ ወኪል አልነበረውም። እነዚህ አንባሳደሮች እንዴት ነው ገበሬውን ግብር እንዲከፍል ሊያደርጉ የሚችሉት? የገበሬው ውክል አካል በምን ሁኔታ ነው ወደ ፖለቲካው ዓለም ወደፊት ሊመጣ የሚችለው? እስከ አሁን ባዬኋዋቸው ኢቤንቶች ሁሉ ገበሬን የወከለ አንድም መሰናዶ አይቼ አላውቅም። እናም ያመኛል። 

የስሜን ሽዋ ጉብኝት፤ የእንቦጭን አረም ላይ ያዬሁትን ሳልዘነጋ እዛ ድርስ ጠ/ሚር አብይ አህመድ እና ም/ ጠ/ሚር አቶ ደመቀ መኮነን መገኛተቸውን እንደ ተጠበቀ ሆኖ። እኔ እምሻው ግን ከዚህ ዘለግ ያለ የፖለቲካ ውክልና ነው።

ኢትዮጵያ የገበሬ አገር ናት። የኢትዮጵያ ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት ሲከፍል የኖረ የመኖራችን ትርጉም ነው - ገበሬው። ተከፋሁ ለሚለው ለራሱ እቅፍ ድግፍ አድርጎ፤ ስንቅ እና ትጥቅ ሆኖ፤ እናት እና አባት ቤተሰብ ሆኖ ነው ያኖረው። ነገር ግን በፖለቲካ የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ግዴታ እንጂ መብት አልቦሽ ማህበረሰብ ነው። ደግ ያደረገላቸው ሁሉ ውለታውን የማይመልሱ ማተበ ቢሶች ናቸው።



እርግጥ ነው አንድ ጊዜ ጠ/ሚር አብይ ሲናገሩ እንዳደመጥኩት እሳቸው የገበሬ ልጅ መሆናቸው ነግረውናል። ይህም አስደስቶኛል። ነገር ግን እራሱን ገበሬውን የሚወክል የአሰራር ሥርዓት ሊኖር ግን ግድ ይላል።  የዛሬውን አላውቅም እኔ ገበሬ አደራጅ በነበርኩበት ጊዜ ባዬሁት ግን በአርሲ በጢቾ እና በጎንደር በሥራ፤ በጎጃም እና በሽዋ በሥራ ልምድ ጉብኝት ያዬሁት የገበሬው መንፍስ ለመልካምነት ድንግል ሆኖ ነው።

ስለሆነም በገበሬ ህይወት ውስጥ ያለው ንጽህና እኔ በሌላው ማህበረሰብ ውስጥ አይቼ አላውቅም። ገበሬው ቅን ነው። ገበሬው ፈርሃ እንግዚአብሄር / ፈርሃ አላህ ያለው ነው። ገበሬው ህግ አክባሪ ነው። ገበሬው የይሁንታ አርበኛ ነው። ገበሬው እኛ ያጣናቸው የሞራል አቅሞች በእሱ ዘንድ ግን ከነተፈጥሮው ሙጃ ሳይወራቸው በንጥህና ይገኛሉ። ገበሬው አዛኝ ነው።

ገበሬው ተፈጥሮን አክባሪ ነው፤ ገበሬው የተፈጥሮም አክቲቢስት ነው - በተፈጥሮው። ገበሬው ንጹህ ወረቀት ማለት ነው። ገበሬው ሩህሩህ ነው … ገበሬው ንጹህ ውሃ ማለት ነው።ኢትዮጵያ ከገበሬው ሰብዕና ልታገኝ የሚገባት ሞራላዊ ጥሪት በ27 ዓመት ተነፍጓታል። ቢያንስ ዛሬ ይህን አብይ ጉዳይ ባሊህ ልትለው ይገባል።

በሌላ በኩል ግን አገር ነክ የለውጥ ሂደቶችን ሳስተውላቸው፤ ራሱ የፓርላመዋ የሰሞናቱ የመንፈስ ጥንካሬ እና ጉልበታም ውይይት የታመቀው አቅም ስራ ላይ ለማዋል አንድ ቅን መንፈስ መሪ ከተገኘ ብዙ የጎበጡ ነገሮችን ማረቅ እንደሚቻል ነው። አንድ አዎንታዊ ሰብዕና ብዙ ነገር መለወጥ እንደሚችል ነው እዬተመከትኩ ያለሁት። ከሁሉ በላይ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ሴራን ስለሚጸዬፉ፤ ሌብነትን ስለሚጸዬፉ ትውልዱ ብቁ ሮል ሞዴል አግኝቷል ብዬ አምናለሁኝ። ይህም የሰማይ ስጦታ ነው።

 በዚህ በዛሬው የገቢዎች አዲስ የአሰባሰብ ሂደት መርህ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ  „ከእርምጃ ወደ ሩጫ መርህ“ ጋር በጽኑ የተሳሰረ ሆኖ ነው ያገኘሁት። በመንፈስም በድርጊትም። የገበሬ ድምጽ ባለመስማቴ ግን እጅግ በጣም ከፍቶኛል - የእውነት። በዚህ ጉዳይ ላይ የጠ/ሚር ጽ/ቤት ሊያስብበት ይገባል ባይም ነኝ።

ሲጠቃለል የተገባን ግብር አለመክፍል ስርቆት ነው፤ ስርቆት ደግሞ ወንጀል ነው። የተከፈለውን ግብር መዝረፍ ደግሞ የወንጀሎች ቁንጮ ነው። ስለሆነም የሰው ልጅ ራሱን ሳይሰርቅ ለመኖር መወሰን ይችል ዘንድ ነው የዚህ ዘመቻ ወይንም ንቅናቄ ዓላማ። መዋቅሩ አለ ግን መዋቅሩን እንዲሠራ የማድረግ፤ የማነሳሳት አዲስ የምህንድስና ተግባር ነው የተጀመረው። ማለፊያ!

እድልን በታማኝነት መጠቀም ያስፈልጋል!


አራት ዓይናማው መንገዳችን የአብይ ሌጋሲ ብቻ ነው!


                                                የኔዎቹ ኑሩልኝ!
                                                መሸቢያ ጊዜ።


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።