የጠራ የትግል መስመር የድል መባቻ ነው!

የአማራን ተጋድሎ መደገፍ ሰውን
ማዕከል ማድረግን ብቻ ይጠይቃል።

የአማራን ተጋድሎ ማጣጣል 
ሰብዕዊነትን መርገጥ ይሆናል  - ለእኔ ።

„ራህብን የሚያውቀው የተራበው ብቻ ነው„ - አሁንም - ለእኔ።

„በምድር ላይ የሰው ህይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን?“
መጽሐፈ እዮብ ፯ ቁጥር ፩



v   ይድረስ ለተከበሩ ፕሮፌስር ዓለምአንተ ገ/ሥላሴ እና
v  እንዲሁም ለዶር. ደመቀ ገሰሰ።

ከሥርጉተ© ሥላሴ  
09.11.2016
(ሲዊዘርላንድ -  ዙሪክ)

·       ቅድም።

ውዶቼ ይህም ጹሁፍ በዘመነ አማራ ተጋድሎ 09.11.2016 ላይ የተጸፋ ነው። ሦስት እርዕሰ ጉዳይን በአንድ ጥምረት የሠራሁት ነበር።
አማራ መከራህን ዋጥ አድርገህ በሰጠንህ ልክ ታገል በተባለበት ዘመን፤ ተጋድሎው ፊት በተነሳበት ወቅት የተጣፈ ነው። የጎንደር ህብረት እና የጎጃም ህብረት ግንባር ቀደምቶቹ ነበሩ። እነሱን ሞግቼ የጻፍኩት ነው። እንዲያውም የወሎ፤ የሽዋ፤ የባሌ፤ የአርሲ እያለ እንደሚቀጥል በልበ ሙሉነት ይናገሩ ነበር፤ ለዛም ተግተዋል፤ ብቻ  የውርንጫ ድካም ሆኖ ቀረላቸው እንጂ።

ጹሑፉ የተጋድሎው ሁነኛ ደጋፊዎቹ ጥቂት በነበሩበት ወቅት የተሠራ ነው። ቀንበጥ ታሪኩን በታሪኩ ከርስ ውስጥ ባለርስት ማድረግ ስላለባት እንሆ ሳተናው/ ኢትዮ ሪጅሰተር በዛን ጊዜ ፖስት ያደረገውን ለውጥ ስለሚባለው መሰረታዊ ትንፋሽ አማራ ስለፈከፈለው መስዋዕትነት እና ስለነበረበት ወጀብ ታሪኩ ስለሆነ በድጋሚ ቀርቧል።

ያላነበባችሁት እንድታነቡት፤ ያነባባችሁት ደግሞ ያን ጊዜ እኔ የጻፍኩት የጭብጥ መሰረት እና ዛሬን ማገናዘብ መዳኘት ስለሚያስቸላችሁ ደግማችሁ ብታነቡት ቢጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይኖረውም። የፊደል ግድፈትን ብቻ አርሜያለሁኝ። ያን ጊዜ እንደህ መሰል እንቅፍታቸው የ አንጀት ቁስል ስለነበሩ በዛ ስሜት ውስጥ ሆኜ የጻፍኩት ነው። ዛሬ ቢሆን እንዲህ ላይ ሆን ይችላል። ትንሽ ለዛብ ሊል ... ራስን ራስ ካቴና ሊያጠልቅት ሲፈታተነው የማይምች ነበር እና ሞገትኩት።  
  
·       እንደ - በር።  

ያልተራበው እራህብ ምንድነው ቢሉት መልሶ „ራህብ ገጹ ምን ይመስላል ክብ ነው ወይንስ ሞላላ? ቁመናውስ - አጭር ነው እረጅም ወይንስ መካከለኛ? ጠይም ነው ወይንስ ዳም፤ አይዋ እርሃብ የሚሉት ለመሆኑ ተምሯል ወይንስ አልተማረም? ከተማረስ ከዬትኛው ዩንቨርስቲ ነው የተመረቀው? የጋብቻ ሁኔታውስ አግብቷል ወይንስ አላገባም ወይንስ ፈት ነውን?“ የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ስለምን?! „የደላው ገንፎ ያላምጣል“ እንዲሉ ነውና። 

ዝም ማለት ህሊናችን ተሰዷል የለንም ማለት አይደለም። ዝም ማለታችንም የሚሆነውን ሁሉ እዬደገፍን ነው ማለት አይደለም። ዝም ማለት ስንረገጥ፤ ስነሰረዝ፤ ስንዳጥ፣ ስንገለል፣ እስራኤላውያን በዓለም ይደርስባቸው እንደ ነበረው የክፉ ዘመን ግዑፋንነት በእኛም አልደረሰብንም ማለትም አይደለም።

የታወጀብነን አሳምረን እናውቀዋለን። ውሃ አንሺዎች ሆነን እንጂ። እንደ ገናም የሚቀድመውን፣ አውራውን ጉዳይ አቅም እንስጠው በማለት እንጂ። ደማቁ ማንነት ለእኔ ኢትዮጵያዊነት መሆኑን በአጽህኖት ስለማምነበትም ጭምር ነው እንጂ ችግሩን አላዬሁህም አልሰማሁምም ብለው ደንበር አቋርጦ እኔንም እዬከተከተኝ በመሆን ቁስለቱን አዳምጠዋለሁ።

መቻል እኮ መሸነፍ አልነበረም ት/ቤት ቢሆን በማለት እንጂ። በሌላ በኩል ግን ዝም ማለት የተዳፈነ እሳተ ጎመራ ማለት እንደ ሆነም ሊታወቅ ይገባል። ሞገድ ነው አሳተ ጎመራ ቀኑን ጠብቆ የሚፈናዳ። ዝም ማለት ቅኔ ነው የጥበቦች ሁሉ ዝከረ ጉባኤ። ከቅኔ ባለቤቶችና ባላባቶች  የሞገድ ዝማሬ የሚመነጭ፣ ለዛውም በንዝረት - ከአባት አደሩ ውቅያኑስ የሚቀዳ እንደማለት ….

ከሰሞናቱ ብዙ ውጣ ውረዶችን በሃሳብ መሰላል ሳዳምጥ፤ ሳነብም ሰነባብቻለሁ። ዛሬ እንዲህ ዕይታዬንና አቋሜን በግልጽ መጻፍ ግድ አለኝና ተነሳሁ። ስለበዛና - ስለ ከረፋ። ዘሃበሻም ሆነ ሳተናው ከተማቻችሁ አውጡት። ካልተመቻችሁ ደግሞ መተው ትችላላችሁ። መብታችሁ ነው። አልጋፋም። ፈጽሞም አልከፋባችሁም።
እርእሶቼ ሦስት ቢመስሉም ውህደታቸው በአንድምታ አኃታዊነት አላቸው። የዕንባ ምጥ ዕድምታዎች ናቸው። 

የጠራቸው ዕንባ ነው። ያገናኛቸውም ዕንባ ነው። የተከበሩትን ዬፕ/ አለምአንተ ገ/ሥላሴን ከህብር ራዲዮ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንዲሁም  የተከበሩ ዬዶር. ደመቀ ገሰሰን ከአባይ ዩቱብ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አዳመጥኩት። መነሻዬም ይሄው ነው። የሁለቱም በአንድ ድምጽ ማጉያ የሁለትዮሽ ሳይሆን የአንዳዊነት ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ጠላፊ መሳሪያ ሆኖ ነው ያገኘሁት።

የመነሻቸው ድርና ማግ ሆነ ዬመዳረሻቸው ርካብ አንድ ነው መልዕክቱ። ለሌላው ብርክ የሚያስዘው ዕድምታ ለእነሱም የራስ መርዘን ሆኖባቸዋል። ስለሆነም ፋታ አጥተው በክፍለሃር የማደራጀት ዘመቻውን ተያይዘውታል። ለነገሩ ጥሩ አዝማቾችም ናችሁ - ስትገርሙ። ነገር ግን በቀዳዳ አቁማዳ እህል ቢሰፍሩት …. ዓይነት … ነው ነገርዬው። ስለምን?

ዕንባው ወጣ ገብ፣ ተዛነፍ አመራር ስለማያሻው። ስለሆነም እምትባትሉበትን - ተልዕኮ ፍሬአልቦሽም ስለሚያደርገውም። ለመሆኑ እናንተ ስትደራጁ በማን ፈቃድ ይሆን? ድንበር ዘላችሁ መደራጀት አይገባም የምትሉት። ዬመደራጀት መብት እኮ እራስን ዝቅ አድርጎ ቁና ስፈሩልኝ ብሎ የሚወድቅና የሚነሳ የማመልከቻ ማሳ አይደለም። 

መደራጀት አምላካችን አዳምን ፈጥሮ አጋሩን ከአካሉ የፈጠረለት ማዕልት የተሰጠ ሰማያዊ በረከት ነው። ስለሆነም ፈቃጂም ነሺም የለውም። የፈቀደው በፈቀደው መልክ መደራጀት ሰብዕዊ ጸጋው ነው።

የተከበሩ ዶር. ደመቀ ገሰሰ ከእኔ ጋር ሙግት ቢገጥሙ ከመጀመሪያው የፍልሚያ ንግግር በኋላ የክርክራቸው አንኳር እንደ ተወጠነ የመቀጠል ዕድላቸው በሃቅ ጭብጦች አከርካሪው ስለሚመታ፤ ለጥጋና ጋራጅ ደርሰው እስኪመለሱ ጦርነቱ በድል - ይጠናቀቅ በነበረ።

ስለምን? ክቡርነታቸው ዬዕውነትን ውቅያኖስ መሻገር ስለሚሳናቸው። ኃሳባቸውን የነዱበት ጀልባቸውም ሰንካላና አንካሳ ስለሆነ። የከሳም - ጎድጓዳም። እኔ በግሌ እስቅ ነበር፤ ክርክራቸውን እያዳመጥኩኝ ---- ውሃ ቅዳ ውሃ መልሱ ክርክራቸው እንደ ተልባ ስፍር ውልብልቢቱን መያዝ አቅቶት እንዲያ ርቱህ እውነትን ፍለጋ ሲባዝን ስመለከት፤ የታዘለውን የጀርባ ተልዕኮ አዎንታዊ ይሁን አሉታዊ ምን አለ ከአንቀልባው አውርደው እሳቸውን ሆነው ቢቀርቡ ያሰኝ ነበር። 

ለነገሩ ጠያቂውም ሳተና ወጣትም ተሟጋቹም ብዕረኛ የዋዛ አልበሩምና ሃሳባቸው መጠጊያ አጥቶ እንደ ዋለለ ተደመደመ። ሎቱ ስብኃት።
የተከበሩ ፕ/ አለምአንተ ገ/ ሥላሴ በሚመለከት እራሱ የመነሻ ሃሳባቸው መንገድ ሲጀመር ነው ትቢያ የለበሰው። ሊያሸክሙን ያሰቡትን ባይረስ ሳያቀኑት ሸማቹም - ሳይሸምተው እንደ ተፈጠረ፤ ወፍ ሳያወጣው አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ ብሎ ብን አለ። ከዚህ በላይ መሄድ የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም።

 ካሻችሁ ኢ-ሜሌን ውሰዱና እኔን በሙግት ለመርታት ሞክሩ። በዜሮ አባዝቼ ውጤታችሁን ዜሮ እንደማደርገው አውቀዋለሁ። ብትመጡ ግን ደስታውን አልችለውም። ግን የምታዘጋጁት አቁማዳ ገለባና ጭድ ተሞልቶ እንደሚመለስ አስልታችሁ ይሁን። ዬተጠዬቅ የቀደምቱ የሙግት ህጋዊ ጥበባዊ፣ ለዛዊ ሥርዓት ከአቨው አንባ አለልኝና። ክንዴም - መከታዬ።

ትእግስት የሚያስተምር  ከሆነ - አደብም የሚያስገዛ ከሆነ ተብሎ ነው ዝም የምትባሉት፤ እንጂ የሃሳብ መክለፍለፎች እንዲህ አና ብለው ሲፏልሉ እዬንን ዝም ማለታችን አቅም የለንም ማለት እንዳይመስላችሁ። 

ያው ተፈጥሯችን  እንጥሩብ የማያዘልለን፤ ሁሉንም በልክ የመያዝ ክህሎቱ ስላለን ብቻ ሲሆን ብ ማለትም ደማችንም ስለሆነ ብቻ እንጂ። አደብ የአቅማችንም ብልህነት ነው። ዝግታም አጽመ ርስታችን ነው። አይቶ እንዳላዩ ማለፍም ትውፊታችን በመሆኑ ብለን ሰነባበትን። አትነካኩን። መከራችን ተሸክምን እንቀመጥ። እባካችሁ ተውን?! ስለፈጣሪም ተለመኑም። በቁስላችን ላይ እንጨት አትስደዱበት፤ ብጣቂ ርህራሄም ይኑራችሁ። እባካችሁ~?~!

·       ለመሆኑ?

የእኔ ወላጆች አያቶቻቸው ከሽዋ፣ ከጎንደር፤ ከጎጃምና ከወሎ ይወለዳሉ፤ እኔን እና እኔን መሰል የአማራ ልጆችን እንዴት ልታደራጁን ታስባላችሁ? መልስ አላችሁን? ነው ልትሰርዙኝ ይዳዳችኋል? ስለ ቀደምቱ ተጋድሎ ታነሱና እኛ መማር ያለብን ከአባቶቻችን ነው ትሉናላችሁ። ቀበቶ መፍታት ነው ከነ አንበሳው የተማራችሁትን?! ለመሆኑ በአባቶቻችን ዘመን በዘር የተደራጀ ሀገር በቀል ደራጎን ነበርን - የገጠማቸው?

እንደ ሀገር ለመጣው ለቱርኪው፣ እንደ ሀገር ለመጣው ለፖርቺጊዙ፣ እንደ ሀገር ለመጣው ለጣሊያን፤ እንደ ሀገር ለመጣው ለእንግሊዝ፤ እንደ ሀገር ተደራጅተው ጥቃትን ግተው አፈር አስግጠው፤ ትቢያ አልብሰው፤ የጠላትን መርኃ ግብር ቅስም ሰብረው፤ የጥቁርን ገድል ለዓለም ህብረተስብ አብሥረዋል። ዘመኑ በፈቀዳላቸው ተጨባጭ ሁኔታ፣ ዘመኑ በፈቀደው ስልትና ስትራቴጂ የመጀመሪያውን የጥቁሮች ሽምቅ ተዋጊ፣ የጥቁር አንበሳ አደራጅተውና መርተው ገድላቸውን በወርቅ መዝገብ አጽፈዋል።

አሁንም የውጪ ጠላት ቢመጣ ይህ አይቀሬ ነው። ለነገሩ ስለ ኢትዮጵያዊነት ለአማራው መስብክ ድፍረት አይመስላችሁምን?! ለአማረው እኮ ቅዱስ መንፈሱ ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ለአማራው ውብ ማዕረጉ እምዬ ናት። ለአማራው የደም ጋኑ ልቡ እናትዬ ናት። አማራው መንፈሱን ስቶ፤ ልቡን አውልቆ፣ ማዕረጉን ሰርዞ፤ ዘውዱን ተላልፎ መኖርን እንደ መኖር ያዬዋል ብላችሁ ታስባላችሁን? በእውነቱ ደፋሮች ናችሁ?!


ሺ ሚሊዮን ጊዜ አባቶቻችን እንዲህና እንዲያ ስትሉን። አይቀፋችሁምን። ወጣቱ ጠፋን አላችሁን?! ….  የትኛው ሰላማዊ ሰልፍ ነው ደፍሮ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በአደባባይ ከ25 ዓመት እስር በኋዋላ ትንሳኤ የሰጠው …. ? መልስ አላችሁን? ቁልጭ ላለው ለዚህ ከእውነት በላይ እውነት ለሆነው አመክንዮ ለመሆኑ እምትገልጹበት አንደበት አላችሁን?! ማይካችሁ ይሰራል ወይንስ ባትሪው አልቋል?!

ለአማራዎች ስለ ኢትዮጵያዊነት ግርድፍና ሽርክት ዘይቤአዊ ቀስቃሽ ሂደት አያሰፈልገውም። እሺ! እሱን ስላልንም ነው በግርዶሽ እንድንቀመጥ የተገመደለብን። እዬተገፋን፣ እዬተገለልን፣ በባይተዋርነት እስኪ ይሁን በማለት ለዘመነኞች ትተን ዝም ብለን መቀመጣችን ወጀቡ ሆነ ወጨፎው አልደረሰብን ሆኖ አይመሰላችሁ። ዬችሎታችን ዲካው ለበጎ ነው ብለንም ስለምናምንመ ነው። ሁሉንም እናይ፣ እንታዘብ ዘንድ ነበር። የሆነ ሆኖ ዛሬ ግን አዲስ ቀን ነው። ነገም እንዲሁ አዲስ ቀለማም ነው።
·       „ልብ ያለው ሸብ „ ይላል ጎንደሬ …..

የሆነ ሆኖ ጎንደር በመወለድ ብቻ አማራነት፤ ወለጋ በመወለድ ብቻ ኦሮሞነት የለም። በሁለቱ ቦታ መወለድ ኢትዮጵዊነት አብሥሮ የዘር ግንዱ ደግሞ ቤተሰባዊ መልክ የግድ ይይዛል። ማንነት ጥልቅ ነው። 

ፍቺውም ሆነ ትርጉሙ ስክነትን አበክሮ ይጠይቃል። የዜግነት ማንነት አውራው ጉልላት ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ ነው። ልጆቹም አሉት። ውበቱ የሚቀዳውም ከዚህው ህብረ ቀለማት ነው።
ለእኔ የብሄር ወይንም የብሄረሰብ፤ የፆታ፤ የዕድሜ፤ የትምህርት ደረጃ፤ የሙያ ክህሎት፤ የጤና፤ የዝንባሌ - የፈጠራ፤ የፖለቲካ አቋም፤ ዬሥነ-ምግባር፤ የጋብቻ፣ የሃይማኖት፤ የሃብት ደረጃ፤ እያለ ይሄዳል። 

ማንነት የብዙ ቅምር ጥምረት ብቻም ሳይሆን የሰብዕና የደም ሥር ውህድ አካልነትም ነው። እነዚህ ማንነቶች ለአንድ ሰው ተቀላቅሎ ሳይሆን እሱን እንደ  ሰው የሚያቆሙት ተርጓሚውም  መገለጫውም ነው። 

እርስ  በእርሳቸው በሚደጋገፉ፤ እርስ በርሳቸው በተያያዙ መረቦች የሰብዕ ማንነት ይገነባል። ያድጋል። ይጎለምሳል። ለምሳሌ በሙያ ብንወስደው የህክምና ባለሙያ  የመጀመሪያው የእድገት ደረጃ ነው፣ ከዛ ቀጥሎ የልብ፣ የአንጀት፤ የኩላሊት፣ የጠቅላላ ህክምና፣ የጥርሰ፣ የዓይን፣  የስፖርት፤ እያለ በመጠነ ሰፊ ድንበር አልባ ዬተፈጥሮ ቅርንጫፎቹን እያሰፋ ይሄዳል።

ማንነት ደንበር ወይንም ክልል ወይንም ክትር ሊሰራለት ከቶውንም አይችልም። ስለምን? የመጠነ ሰፊ ተፈጥሯዊ ህልውናው፣ ልማዳዊ፣ ባህላዊ፣ ወጋዊ፣ ደማዊ፤ ታሪካዊ ሥርዓታዊ መግለጫ ነውና። ሴት ሆኜ ሴት አይደለሽም ልባል አይገባኝም። ሴትነቴ አንዱ ዬማንነቴ መግለጫ ነው። ሴት ሆኜ ነውና የተፈጠርኩት። ስለዚህ በሴቶች ተፈጥሮ ያሉት ሥነ -አምክንዮች ሁሉ በእኔ ውስጥም አሉ። በጾታዬ ማንነት ውስጥ ደግሞ የእኔ እምለው እኔን ከሌላው የሚለዬኝ ወይንም ከጥቂት ሴቶች ጋር ብቻ የሚያመሳስለኝ የብዙሃኑ ሴቶች ላይሆን የሚችል ማንነት ደግሞ የብቻዬ አለኝ።

ሌላ ምሳሌም ማዬት ይቻላል። ለምሳሌ ዕምነቴ ክርስትና ሲሆን፤ ኦርቶዶክስ ብቻውን ወይንም ፕሮቴስታንት ወይንም ካቶሊክ ግን አይደለሁም። ክርስትያን ሆኜ ዬኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ ነኝ። በዚህ ዕምነት ውስጥም አጥባቂ ወይንም ዘና ያለ ከሚለውም እኔ ዘና ያለው ውስጥ ነኝ። የተዋህዶ ልጆች ሆነው ካማይፆሙትም ወገኖቼ እለያለሁ እኔ። እፆማለሁ። ህጋዊ የፆም ዓዋጆችን ብቻ ሳይሆን ያልተደነገጉትንም አክላለሁ - የፈቃድ ፆምንም። ይህ  በዕምነቴ አቋም ሥርጉተን ይገልጻታል።

በፖለቲካ አቋሜ ፍቅራዊነት መርሁ ያደረገ፣ ደግነት የሚጎበኘው፣ ሰውን ማዕከሉ ያደረገ ሩህሩህና ቅን ዬዴሞክራሲ ሥርአት ህልሜ ነው።  ነገር ግን የፖለቲካ ድርጅት አባል የመሆን ፍላጎት በውስጤ የለም። ወይንም የማናቸውም ማህበር አባል ሆኜ ተመዝግቤ በአንድ ህግ ሥር እንድተዳደር አልፈቅድም። ምክንያቱም ጭነት የሚሸከም ትክሻ ስለለኝ። ለፈቀዱት ግን ክብር አለኝ። ሌላውን እስካልተራገጡ ድረስ።

በዘር ሐረጌ በቀደምቱ አንጡራና አውራ ኢትዮጵያዊ ማንነቴ የምኮራ፣ በቤተሰብ ዝርያ ካሉት ብሄርና ብሄረሰቦች ውስጥም ከአንዱ ወገን ብቻ ነኝ። አባቴ መምህር ስለነበር በሥራ ምክንያት እኔን ጎንደር ቢወለድም፣ ሐረር ብወለድም፤ አርሲ ሴሩ ወይንም አምኛ ወይንም ሮቤ ላይ ብወለድም እትብቴ የተቀበረበት ቦታ የቤተሰቦቼን አማራነት ሊከልስው፣ ሊበረዘው ወይንም ሊሰርዘው ከቶ አይችልም። በፍጹም።

ይህ ሂደት ኢትዮጵያዊነቴን ያደምቀዋል፤ አማራነቴንም በእኩል ሁኔታ ያደምቀዋል። ሴትነቴንም እንዲሁ። እኔ ሥርጉተ ሥላሴ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል እንደማላፍርበት ሁሉ፤ እንዲሁም ጎንደሬ ነኝ ስል እንደማላፍርበት ሁሉ፤ ሴት ነን ስልም እንደማላፍርበት ሁሉ  አማራ ነኝ ስልም አላፍርበትም። አልሸማቀቅም፤ አንገቴን አልደፋም።

እያለሁ የለሽም ስባል እዬሰማሁ ዝም ያልኩት ባለመኖር ላይ ያለ ግዑዝ ፍልስፍና በመሆኑ ከመጤፍ ስለማልቆጥረው ብቻ ነው። ከአማራ ወገን የሚወክል የለም ተብሎ መሳቂያና መሳለቂያ ስንሆንም እንዲሁ ዘመኑን ታዝቤ ዝም ነው ያልኩት። ስለምን?! ምን አንዳለን? ምን እንደምንችል እነሱም ያወቁናል እኛም አናውቃቸዋለን እና። ያለን አለን። የነጠረው ሃብታችን በውስጣችን አለ። ማንም ባሻው ሰዓት የሚዘርፈው ማንነት አይደለምና ያለን። እኛነታችን ሳናውቅ መኖርንም ጀምረነው አናውቅምና።

አማራ ሲፈጠር ተደራጅቶ ነው የሚወለደው። ድርጁ ነው። ለዚህም ነው በአርምሞና በተደሞ ከውስጡ ጋር ሆኖ በተግባሩ ገድል ብቻ እራሱን የሚሳዬው። ተግባር ብቻ እንዲተረጉመው ነው የአማራ ፈቃድና ፍላጎት፤ የነጠረ ንድፉ ለግብ ሲበቃ መንፈሱ የረበበት መሆኑን በራሱ ጊዜ ያውጃል። ድርጊቱ ብቻ ማሳውን አርሶ፣ አለስልሶ፣ አዝርቶ፣ አብቅሎ፤ ሲያፈራ ብቻ ነው የሚታዬው። ለመብል ሲደርስ እንደ ማለት።

አዝመራ ነው አማራነት። አማረነት ጥበብነት ነው። የጎንደሩን ሰላማዊ ሰልፍ ላዬ እኮ ምላሹንና የሥልጣኔውን ደረጃ መተርጎም ያስችላል። ሁሉ እያላቸው በመንግስት መዋቀር የተደራጁት፤ ሆነ በሰለጠነው ዓለም ያለነውም ብንሆ በዛ የብጡልነት ደረጃ በመንፈስም ሆነ በሥነ - ጥበቡ ሲያደርጉት አለዬንም። ከሁሉም አቅም በላይ ነበር። እጅግ የላቀ ዘመን ጠገብ ዕንቁ፤  ፍሬ ዝቀሽ ገድል ነበር።  ተለምዶው  በፍጹም ሁኔታ የለማበት ዓጼ ነበር ማለትም ይቻላል - የአስተሳሰብ ድህንት ዝር ያላለበት ብልጹግ ትዕይነትም ነበር። የብሄራዊ አንድምታ ህይወቱም እጬጌ ነበር።

ለዛ ብሄራዊ ሰላማዊ የተቃውመ ሰልፍ ፕሮፖጋንዲስትና ቀስቃሽ አያስፈልገውም ነበር። ስለምን? ገላጩ ልቅናው ነበርና። እና እነ ፕ/  አለምአንተ ገ/ ሥላሴና እነ ዶር ደመቀ ገሰሰ ብትማሩበት ወይንም ለመማር ብትዘጋጁ ታተርፉበት በነበረ። እንዲህ የሚገፋ ገድል አልነበረምና። የስልፉ ውሳጣዊ ሥነ - ተፈጥሮ የአዲስ ቀን ብርሃን ቋንቋ ነበር። የአዲሰቲ ኢትዮጵያ የትንሳኤ ዋዜማ፣ የፍሰኃም ስዋሰው ነበር።

ከድንቅ በላዩ ደግሞ የቀድሞው ሻብያና የዛሬው ህውሃት ጥርሳቸውን የነቀሉበትን፤ እንዲሁም የማርክሲስቶችን ዶክተሪን አፈር ድሜም ነበር ያስጋጠው። ደሙን ሥረ - ግንዱን አንተማ የእኔ ነህ ሲል በተግባር አተመበት። ቅኔው ይሄው ነው። ዝማሬውም። ድጓ ሆነ ፆመ ድጓውም። አማራ ማለት ይሄው ነው። አናባቢየሉም ስንባል የምንኖር፤ ጠፉ ስንባል የምናፈራ፤ መከኑ ሲባል እምንለመልም።
የሆነ ሆኖ በሁለቱም ቃለ ምልልስ ሰጪዎች እኔ በግሌ አለዘንኩባችሁም። በፕ/ አለምአንተ ገ/ሥላሴ ሆነ በዶር. ደመቀ ገሰሰ። ማዘን ያለባችው እነሱው ናቸውና። ይህ ታሪካዊ ወቅት ታሪክን እንዳንድጥ፤ ታሪክን ጥቅርሻ እንዳናለብስ አበክሮ ቆሞ እያሰተማረን ይገኛል። ታሪክ በዬዘማናቱ በሚሠሩ በጎም ሆኑ በጎም ባልሆኑ የሰዎች የመኖር ዘይቤ፤ የድርጊት ሂደት ዘመን ጠገብ ሲሆን ነው ታሪክ የሚሆነው።

ታሪካችሁን ጥላሸት የቀባችሁት እራሳችሁ ናችሁ። ጊዜ ታሪክ ሰሪ ነውና። ዘለላችሁት ልበል እንደ ታጣፊ አልጋ አጠፋችሁት? የተመቻችሁን ትወስዱ ዘንድ በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ። እኔ የሥላሴ ባሪያ ከፈጣሪዬ በስተቀር እማምንበትን ለመግለጽ ደጅ ጥናትና ቅልውጥ አልሄድም። 

አማራ ነን ብላችሁ የአማራን መከራ ለመጋራት ግን በእጅጉ ፈራችሁት። ሻታ ትዞራላችሁ። … የቆዬ ሰው ይያችሁ። ከወቅታዊ የወጣቶች ጥያቄና ተመክሮ ጋር እንዲህ ባዕድነትን ማንገሥ ህሊናን ይፈትናል ወይንም ይፈትላል።

እንጠብቃችኋለን። ህበረት ያላችሁትን ነገ ደግሞ በአውራጃ፤ በወረዳ፤ በቀበሌ ሸንሽናችሁ የሚፈሰውን የአማራ ደም ቀረመት ለበለኃስብ፤ ሥጋውን ለህውሃት ሊኳንዳ ስታቀርቡ። ማህከነ! 

የጎንደር/ ይሁን የጎጃም ህበረቱ በፖለቲካ ድርጅት የታቀፈውንም ያልታቀፈውንም፤ ጎንደር ወይንም ጎጃም የተወለደውን ሁሉንም የሚያካትት እንጂ ሞት የታወጀበትን፤ ዘሩ እንዲጣፋ የተፈረደበትን የአማራን መሰረታዊ ጥያቄ  እንደ ዓላማ የያዘ አይደለም። እንዲያውም ገድሉን ለመጋረድ የተቃጣ ሴራ ነው።

ጥያቄው እኮ አማረ ነን ትግሬ አይደለንም ነው። የትግሬ ባህል ተጭኖናልና፤ ግዛቱም በቃን ነው። ጥቃቱ ጎንደሬ ወይንም ጎጃሜ በመሆን አይደለም የሚፈጸመው። አማራ በመሆን ብቻ ነው። ጥቃቱን ለመቋቋም ደግሞ ጥቃቱ በታለመበት አቅጣጫ ተደራጅቶ መፋለም ግድ ይላል።

እንዲያውም ለእኔ ለሥርጉተ የእናንተ መንገድ አደንዛዥ ዕጽ ነው።  ዬእናንተ ደርጅት ለመንገድ ሥራ ሊሆን ይችላል። ወይንም ት/ቤት ለመሥራት፤ ለቆሰለው የአማራ ህሊና፤ ለሚደበደበው የአማራ መንፈስ፤ ሞት ለታወጀበት ለአማራ ትውልድ፤ ቀኑ ክው ብሎ ለደረቀበት አማራ ግን በቁስሉ ላይ የፈላ ዘይት ጨምሮ የሚያቃጥል፤ የሚቀቅል እንጂ የሚፈውስ አይደለም። ለነገሩ ምን ታደርጉ ከራህብ ጋር የምትተዋወቁም አይመሰለኝም። ራህብ ርቧችሁ አያውቅም። ውሃም ጠምቷችሁ አያውቅም።  ዕድለኞች ናችሁ …

አማራ ጠላቴ ነው። በአማራ መቃብር ላይ ታላቋን ትግራይ እምሰርታለሁ ብሎ ለተነሳ የሄሮድስ ማንፌስቶ፤  አጋፋሪነት ከመሆን በቁም አፈር ለብሶ መሄድ በስንት ጣዕሙ። አማራውን አትደራጅ ማለት የዘር ጥፋቱን ተከድኖ ይበስል፤ መስፋፋቱም ይቀጥል እንደማለት ነው።

ለእኔ አብሶ በፖለቲካ ዓለም መቆዬት ልምዱ ቤተ - መዘክር ወይንም ቤተመጻህፍትነት ነው። መንገዱ ጎርባጣ፣ ወጣ ገብ፤ በግጭት የተሞላ፤ በሃዘን የሰከነ፤ ፈተናው የገዘፈ ስለሚሆን እራሱ ተቋም ነው የህይወት። እናም አንድ ዕድሜውን ሙሉ በፖለቲካ ህይወት ለኖረ ለትግል የሚደራጅበት የመነሻው አስኳሉ የህዝቡ መሠረታዊ ተጨባጭ ጥያቄና በተነሳው ጥያቄ ላይ አጥቂው የሚወስደው እርምጃ የሚመክት ስልትን ማደራጀት ይጠይቅ ነበር።

እንደ ተጫባጭ ሁኔታውም አንድ በሳል ፖለቲከኛ ዕድሜ ጠገብ ተመክሮ ያለው ከሆነ፣ ተስማሚና መጣኝ ታክቲክና ስትራቴጂውን ከወቅቱ ጋር አስማምቶ የህዝቡን ቀልብ ስቦ፣ አቅምን መገንባት በቻለ ነበር። እማዬው ግን ፉርሽካና - ፉርሽነት ነው። አድማጭን መማረክ የሚቻለው እኮ የንግግር ሥነ - ህግ የሆነውን የአድማጭን ስሜት እንኩላሊት በማወቅ ነው። እሱም አውነትነት ብቻ ነው። እናንተ ግን ከተጨባጩ  እውነት ጋራ አራባና ቆቦ በመሆናችሁ ተላልፋችኋል። 

ስለሆነም የተነሳችሁበት ፍላጎት ከመዳጥ በስተቀር ወጣቶቹ ባነሱት ገድላዊ ጥያቄ ላይ የሚያሳድረው ብጣቂ ተጽዕኖ የለውም። ይሠራልናል ብላችሁ የተበተባችሁት ትብትብ የራሳችሁን ተልዕኮ ጠልፎ ከመጣል፤ ሃሳባችሁን ከባህር የወጣ አሳ ከማደረጉ በስተቀር ትርፍ አልቦ ድካም ነው። ለጊዜው ቅኖች ቢሰለፉላችሁም፤ እንደገናም ጎሽ! ተብላችሁ እንክብካቤው ቢያረግድላችሁም ነገ ግን ምች የሚመታው ተልዕኮን መሆኑ አይቀሬ ነው።

ስለምን? መሬት ዬያዘ አይደለምና። የተንሳፈፈ ሸለሸል ነውና። የፊት ለፊቱ የህዝብ ጥያቄና እናንተ ሆድና ጀርባ ናችሁና። የህዝቡ መንፈስና የህልውና ጥያቄ እና እናንተ ባዕድ ናችሁና። በዬዕለቱ በግፍ ከሚፈሰውም - ደምም ሆነ በእሥር ላይ እያሉ መንፈሳቸው እንዲዝል ከሚደረጉት የአማረ  ቀንበጦች ፍዳ ጋር ገና አልተዋወቃችሁም።

ከሱዳን በመጣ ሠራዊት ….. ወንድ የተባለ ሁሉ አንባጊዮርጊስ ላይ የአማራ የነገ ተስፋ እንደዛ ሲታጨድ። እናት ታዳጊ ልጇን ይዛ ጫካ ስትገባ፤ ልክ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዘመነ ሄርዶስ ልጇን ይዛ ወደ ግብጽ የተሰደደችበትን ዘመን ያጣቅሳል። መንፈሱን ላላጠ ሰብዕዊ ፍጡር ይህ ሰብዕዊነትን ብቻ ይጠይቃል። ለነገሩ አሁን የጽጌ ጾም ነውና ወደ ማስተዋላችሁ ትመለስችሁ ድንግልዬ። የ2009 በዕለ መስቀልስ ተዘግቶ ሲውል?! …. ከዛ በፊትም አድረሺኝ የከበረ ባህላዊ ትውፊታችን ነበር እንደዛ በደም ሲታጠብስ?!

ለኢትዮጵያውያን ካፒታል ማለት ልጅ ነው። አንድ ልጅ በአንድ ቀን ተወልዶ፣ አድጎ ለፍሬ አይበቃም። ልጅ ለወላጁና ለሀገሩ ተስፋ ነው። አንድ ልጅ በልጅነቱ ሲወለድ ምን ታደርጋለህ ሲባል ኢትዮጵያዊው ልጅ „ወላጆቼን እረዳለሁ„ ነው የሚለው። አንድ ልጅ የዘመኑ ሁሉ ዋንኛ ፕሮጀክት ወላጆቹን ማስደስት ነው። ነገ እንዲህ በህግ አልባነት በአዋጅ  እዬተገደለ፤ ነገ ከምጣቱ በፊት እንዲህ በዘመቻ እዬተቀበረ፤ እናንተ ቧልት ያዋጣናል ብላችሁ አደባባይ ወጥታችኋል … ይህ ሽበት የሚባለው ነገር በውስጥ ቢበቅል ከቶ የሰው ልጅ እንደ ዕድሜው ያስብ ይሆን?!

አንዲት ወጣት ሴት መሃን ከሆነች፤ ወዲያው ነው የወንድዬው ቤተሰብ በቅሎ አቅፈህ እሰከመቼ በማለት ጉልቻውን የሚበትኑት።ትዳራ መፍታቱ ብቻ የሥነ - ልቦናው ጫና ሚዛን የለውም። የስሜት እሰረኛ የሥነ - ልቦና በሽታም ቀጥተኛ ተጠቂ ነው የምትሆነው። ልታብድም ትችላለች። መሃን የሆነች ዕለት ያቺ ቀንበጥ - ሞታለች። እግዚብሄር ዘር አፍርታ እንድትኖር የፈቀደላትን ሰማያዊ ጸጋዋን ተነጥቃለች። 

ይህቺ ወጣት ትዳር አልባ መሆኗ ብቻ ሳይሆን ቆሞ ቀር መሆኗ በአማራ ማህበረሰብ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የሚያውቅ - ያውቀዋል።
አርግዛ መታዬት ክብሯ ነበር፣ ማርዳዋ፣ ድኮቷም ነበር፤ አምጣ አለመወለድ - መራራ ነው፤ አቅፋ አለማጥባት ኮሶ ነው።  አዝላ ሙቀቱን አለማድመጥ የኑሮ ቁም እስረኝነት ነው፣ የልጇን ጠረን አቅርባ ለማጣጣም አለመታደሏ ሞቷን እምትማጸንበት ዕለታዊ የኑሮ ሸክሟ ነው፤ ከትዳር አጋር ጋር አንተ ትብስ አንቺ ትብሺ መባባሉ ቀድሞ መቀጨቱ ዘመኗን ሁሉ ኮሶ ቆርጥማ እንድትኖር ያደርጋታል።

ፈት መቧላ፤ ቁመህ-እደር፤ ጋለሞታ መባሏ የህይወት ዘመኗን ማቅ ያለብሰዋል። ሌላዋስ ሳትፈቅድ የምትደፈረዋና ያልፈቀደችው ዘር ተሻካሚ ሆና፤ ልጇ በአባት መጠራቱ ቀርቶ በእናቱ ብቻ መሆኑስ? ለመሆኑ ሁለታችሁም ሴት ልጅ አላችሁን?! ሴት እህትስ?! የእናንተዎቹ እንዲህ በጸራራ ጸሐይ የማንነት አንዱ መለያ የሆነው ከፍቅር ጸጋ ጋር እንድትገናኝ ለሴት የተሰራላት ድልድይ ቢሰበር፤ ወይንም በግፍ ብትደፈር ምን ትላላችሁ?! የሴትነት ተፈጥሯዋ እያለ ግን የሴትነት ተፈጥሯዋ በፈርዖኖች ስተቀማ ከዚህ በላይ ምን የሃሞት ዘመን ይኖራል - ለዛች ሸበላ።

ለዚህም ነው ከእስር ቤት ለሚወጡ ሴቶች የተገባውን አክብሮት ይሰጥ ዘንድ ስማጸን የኖርኩት። መኖር ማለት መኖርን ማኖር ሲቻል ብቻ ነው። መኖር በሌለበት መኖር የለም። በቁማቸው ሙተው እንዲኖሩ ለተፈረደባቸው ጉብሎች ባለ ጋሜና ታሪዎች ማን ይሆን ጠበቃቸው?! ይህንን የሀቅ ዘለበት ነው የረገጣችሁት። ለእኔ ስፍስፍ የምንለትን ሰንደቅዓላማ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን እንደመተላለፍ ነው የምቆጥረው። …. ሴትም ስለሆንኩ መራራ ነው - ከርቤ።
ተብዕትም ሆኖ መሰሉ ከተፈጸመበት እጅግ ፈታኝ የኑሮ ግማድ ነው። ሰው ስሜቱን ከተቀማ ባዶ ቀፎ ነው የሚሆነው። እያዬ፣ እዬሰማ፣ እዬኖረ ግን አፍ ባለው መቃብር እንዲኖር የተገመደለበት። 

ከዚህ ሃቅ ጋር ለመገናኘት ሰብዕዊነት ብቻ እንጂ አማራነትን አይጠይቅም። ይህን ጉድ ተሸክመው ነው ዶር. ቴወድሮስ አድሃኖም ለዐለሙ የጤና ድርጅት የተወዳደሩት። በመወዳደራቸው በራሱ ገመናቸውን የመንገድ ቄጤማ እንዲሆን አደረጉት። የተከደኑ ዝገቶች መስመር አግኝተው ተነፈሱ። ስለሆነም ይህ ደባ ወሸኔ ነበር በማለት ነው አሁን የአማራን ተጋድሎ ለማክሳት መንገድ የጀመራችሁት። ዘመንና ትውልድ ይፋረዳችሁ፤ ሌላማ ምን ይባላል።

ዛሬ ብቻውን ከፈርዖኖች ጋር በመፋለም ላይ ያለው ወገናችሁ የባሩድ ቀለብ የሆነው አማራ በመሆኑ ብቻ ነው። አማራ በመሆኑ ብቻ ለደረሰበት ጥቃት ደግሞ አማራ ሆኖ ተደራጅቶ ከነሄሮድስ ማንፌስቶ ጋር መፋለም ነው ያለበት። 25 ዓመት እኮ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምበት ሁነኛ ባለቤት ሳይኖረው ነው የቆዬው። አሁን ደግሞ መከራቸውን ያወቁት ወጣቶች ለመከራቸው መፍትሄ ቁልፍ መንገድ ነው ብለው በተነሰቡት የመከራ ጉዞ ላይ መርዝ ትነሰንሳለችሁ። ልብ ይስጣችሁ። የሰው ልጅ ቤት ሳይጸዳ በረንዳ አያጸዳም። ግን አማራው ሲያደርግ የቆዬው ይሄንኑ ነበር። 

ለዚህም ነው የለምም የሚባለው። አይመጥንም የሚባለው። ለዛውም አይደለም እልፍኙ ታዛው እንኳን  በዬትም ሁኔታ ለማይፈቀድለት። በረንዳ እንኳን አይፈቀድለትም።

ይህን እናንተ በውስጡ ስለሌላችሁበት አታውቁትም። እራህብን የሚያውቀው የተራበው ብቻ ነውና። …. ሲራባችሁ ወይንም የጠማችሁ ዕለት ከዕንቅልፋቸሁ ትነቃላችሁ። ሚዛን - ይኖራችሁ። ለነገሩ ሚዛናችሁን ለጨረታ ዬዳረጋችሁት ይመስለኛል። በተለይም የተከበሩ ፕ/ ዓለምአንተ ገ/ሥላሴ። ትንሽ ወደ ዘር ሐረገዎትም ምልስት ቢጤ አድርገው ነበር በቃለ ምልልሱ። እና ምን አልባት ካለ ኃላፊነተዎት ይሆኑን? ግራ ነገር ነው ዝንቆላው።

አማራው በመደራጀቱ የኢትዮጵያዊነት ማገር ቢጠብቅ እንጂ አይላላውም። በአግባቡና በስልት ተይዞ ዕውቅና ካልተነፈገው። ከቶ አላያችሁትንም? ስለተዳራጁ እኮ ነው አንቱ ከተባለው አውራ ፓርቲ ጋር አነሳዎች እንኳን ለቅድሚያ ድርድር ያታጩትና በግርማ የቀረቡት። አማራው ለድርደር አይደለም ከታች ሆኖ በተከበረው ቦታ ላይ ድምጹን ለማሰማት እንኳን ወካይ አካል አልተገኘም ተብሎ ነው እኔ ያዳመጥኩት። ይህ አይጎረብጣችሁም?! ይህ አያቃጥላችሁም? ይህ አያንገረግባችሁም? ለመሆኑ እናንተ ከዬትኛው ፕላኔት ይሆን ያላችሁት?!

አውሮፓ ኮሚሽን ሰሞኑን ጥሪ እንዳደረገ ያነበብኩ ይመስለኛል። ካልተሳሳትኩኝ። መድረክ ስለተደራጀ ነው በውስጡ የያዛችውን የብሄረሰብ ስብሰቦች መንፈስ ይዞ የሚቀርበው። አማራው ግን የለም። በቃ Absent! ይህ አያርመጠምጣችሁም? ይህ መንፈሳችሁን - አይገርፈውም። ይህ ወጀብ ሄዶ ሄዶ ባላቤት የለሹን ህዝብ ዬመከራ ዕንባ ወኪል አልባ አድርጎታል። ነገም እንዲቀጥል እነ አቤቱ ፈርዳችሁበታል። በመንገዱ ላይ መሰናክል፣ መረብ ዘርግታችኋል ትፈትኑታላችሁ።እግዚአብሄር ይይላችሁ።

ሰዎች ለምን እከሌ የለም ትላላችሁ ሲሉ ወቀሳ ሰንዝረዋል። እንዴት ነው ነገሩ። ፓለቲካ ማለት እኮ በመንግስት አስተዳደር መሳተፍ ማለት ነው። በዚህ የተሳትፎ ሂደት አንድ ትልቅ ህዝብ እንደ ህዝብ ወካይ አልባ ሲሆን እራሱ አማራው ሳይጎረብጠው ሞዝቦልድ ሲሆን ከማዬት ወዲያ የሚያሳፍር ነገር የለም። በተለይ ለአማረው ሊሂቃን።

እንዲያውም ለእኔ ለሥርጉተ ህውሃት ከፈጀው በላይ ከወሰደው የበቀል እርምጃ በላይ የእናንተ መንገድ ነው መንፈሴን እዬቀጠቀጠው ያለው። ቀድሞ ነገር እንዴት „አማራ ጠላትህ ነው። በአማራ መቃብር ላይ የታላቋን ትግራይን እመስርታለሁ„ ብሎ ለተነሳ ማንፌስቶ አማራው  መደራጀት አይገባውም በማለት ትሟገታላችሁ።

እሲኪበቃው መንጥረልኝኝ ማለት መሆኑን 25 ዓመት ሙሉ አለመረዳት አዚሙ ምን ይሆን? አሁን እንኳን ያን ደማቅ ተጋድሎ ማድረጉ ሊያስመሰግነው ሲገባ፤ መስዋዕትነቱ ዕውቅና ሊሰጠው ሲገባ፤ ወጣ ገብ አዙሪቶችን ተብሎ ጥድፊያ ላይ የተሆነው።  ለነገሩ አቅም ከተገነባ ፈላጊው ከያለበት ተጠራርቶ ይመጣል። ያ አቅም እንደማይመጣ ነው እሾህን በእሾህ እንዲሉ የአማራ ሙሁራን ከወጣቶች ጋር ፍልሚያውን ሥራዬ ብላችሁ የተያያዛችሁት።

የአማራው መደራጀትን ሁሉም አይወደውም። በብሄርና በብሄረስብ ከተደራጁት ጋር አብሮ ለመሥራት እዬተፈቃቀደ። ትናንት እንኳን አንድ አይቻለሁ በኢትዮጵያ ሱማሌዎች ዙሪያ አዲስ ድርጀት መመስረቱን። እነሱን ነኪ ጎሳሚም የላቸውም።  የሆነ ሆኖ ተቀናቃኝ መንፈሱን እርባና ያለው በማደረግ እረገድ ቆራጦቹ የነገዎች ይዘውታል። የራስን ዘምን ጨርሶ ሌላውን መጋፋት አልጠገብ ባይ  …. እንዲሉ  እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባል።

ሌላው አማራው ለምን ተደራጀ? ወይንም ለምን ሊደራጅ አሰበ ተብሎ የሚወቅስ ሰው የእሱ የራሱ ብሄረሰብ ከአንድ አልፎ ሦስት አራት ሲሆን ትንፍሽ ሲል አይደመጥም። ሌላው የክትና የዘወትር ቤት አለው። ብህብረ ብሄሩም ሆነ በጎሳም። አማራው ግን ህብረ ብሄር በሚባለው እንኳን ከአሳላፊነት የተሻለ ቦታ አላዬንም። አለሰማነም።

… ነገም መንገዱ ይሄው ነው። አማራ ልብ ገዝቶ አቅሙን በአቅሙ መገንባት እስካልቻለ ድረስ ነገ ከመምጣቱ በፊት እራሱ ያደረቀው ስለመሆኑ በአንክሮና በአጽህኖት ክልቡ ሆኖ ሊመረምረው ይገባል። ያለውን አንጡራ መንፈሳዊ ሃብቱን ለውስጡ ለማዋል ንፉግ መሆንም አይኖርበትም፤ መሪ ሃሳቦችን ወጥነት ሰጥቶ ለህልውናው እስካልተጋ ድረስ ፈተናው ቀጣይ ከመሆኑም በላይ አማራው ለወደፊት የኩርዲ ዕጣ ፈንታ ይኖረዋል። …አማራው  ባሊህ ባይ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ሰብሰብ ሲልም በታኙም የራሱ ልጆች ናቸውና ….
·       ጥሞና።

ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ወሳኝ ጉዳይ …  አቅም በገነቡት ላይ እጣት ሰንዝሮ፣ የጥላቻ ግፊያ ከመጀመር ይልቅ ሙያ በልብ ነውና የራስን አቅም ከፈጣሪ በተሰጠው ክህሎት ቀምሮ ጥርት ባለ አቋም እና ሂደት መንቀሳቀስ ይኖርበታል የአማራው ተጋድሎ። የ የአማራው ተጋድሎ እራሱን አርሞ ግድፈቶችን ከውስጡ በመሆን ገስፆ መንገዱን ኮለል ባለ በጠራ መንፈስ መጀመር ይኖርበታል። ስርክራኪ አልባ። አማራው ኢትዮጵያዊነት ዘውዴ ነው ካለ ከማናቸውውም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ስልታዊ አካሄዶች ጋር መጣረዝ አያስፈልገውም። በፍጹም።

ያ ከሆነ ማዕከላዊ አቋም የያዘው፤ በገለልተኝነት ሁሉንም የሚመለከተው አብዛህኛው ህዝብ፤ የትኛውም ድርጅት አባል ሳይሆን ሁሉንም በአርምሞ ለማዬት እንደ እኔ ከወሰኑት ወገኖቹም ፍቅርን ያጣል።  አክብሮት፣ ትህትና፣ ማድመጥ፤ ፍቅራዊነት፤ የፍትህ ፈላጊው ማህበረሰብ መለያ የደም ማህተም ነውና ተዛነፍና ወጣ ገብ ዕይታዎችን ገርቶ በብልህነትና በስልት ጥላቻን ማስወገድ የተገባ ነው።

የአማራ የተጋድሎ ማዕከል ዘለፋን በማቆም ፍቅርንና ይቅርባይነትን ማተቡ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህ ሲሆን የተጎዳው የአማራ ማንነት ሥነ - ልቦናዊ ቁስለት መልሶ ማገገም ይችላል። ጥግ ያላገኙ ወገኖችም ቢያንስ በመንፈስ መጠጊያ ይኖራቸዋል። ይህ በራሱ አቅም ነውና። 

ከእስራላውያኑኑ መማር በእጅጉ ያስፈልጋል። እንደ ደረሰባቸው ቢሆን ከማንም ጋር ባልተገናኙ ነበር። …. በአንድ ወቅት ጸሐፊ ዮፍታሄ በዚህ ዙሪያ 8 ተከታታይ ጹሑፎችን አቅርበው ነበር። እኔም ውስጤን ስላገኘሁበት ሰፊ ጊዜ ሰጥቼ በጸጋዬ ራዲዮ ፕሮግራሜ በተከታታይ አቅርቤው ነበር። ልብ ብላችሁ ደግማችሁ አነብቡት። አቅምን ዬሚበሉ አሳማ ሥነ - ምግባሮች፤ አቲካራዎች፣ ያልተገቡ ቃሎች፣ ከትችቶች መታቀብ የአማራን ተጋድሎ መንፈስ ከግብ ያደርሳል።

ስለመብት እዬታገሉ በተደራጁት ላይ መዝመት ኢፍትሃዊነት ነው። እነዛ ድርጀቶችም መከራ፣ መገፋት የፈጠራቸው ናቸው። የድሎት ወይንም የሽርሽር አስኳሎች አይደሉም። በእውነቱ ውርሳችንም አይደለም ዘለፋ፣ ንቀት፤ ቂምና በቀል። ሁሉንም የፈተና ዓይነት የኛ ወጣቶች በቅን ልቦና ታስተናግዱት ዘንድ እኔ ታላቃችሁ ዝቅ ብዬ እማጸናችኋለሁ።

የእኔ ሆናችሁ የእኔ በሆኑ አቋሞች ላይ ብትዘምቱ በእጅጉ ይከፋኛል። እስራኤላውያን እኮ መጀመሪያ ላይ እንደዛ ከቤተክርስትያን የገባ ውሻ ሲሆኑ ማንም ከጎናቸው አልነበረም። ጊዜ ቀንን ይሰጣል። ጊዜ ጥሩ ቀንን አምጦ ይወልዳል። ጊዜ የተሻለውን ቀን ይሸልማል። ስለሆነም ለዬትኛውንም አሉታዊ ዘመቻ ምላሻችሁ ሆነ ስንቃችሁ ቅንነት ይሁን። ምላሻችሁ ፍቅር ይሁን። ምላሻችሁ ምህረት ይሁን።

የሰው ልጅ ሁሉንም ችግር የመፍታት አቅም የለውም፤ ፍቅር ግን ይችላል። ፍቅር ከሰው ልጆች በላይ ሰብዕዊነት ባህሪ ያለው ነው። ፍቅር ከሰው ልጆች በላይ የመቻቻል ተቋም ነው። መርኃችሁ ፍቅር ግባችሁን ነፃነት … ከባርነት ወደ ነፃነት። ከመረሳት ወደ ህላዊነት ….. ከመጥፋት ወደ መነሳት፤ ሽልማቶቻችን ናችሁና““   ድንግልዬ ትከተላችሁ። ጥላ ከለላም ትሁናችሁ። አሜን!
·       የሂደት ዕውነት  እንደ መከወኛ።

የወያኔ ሃርነት ትግራይን ጸረ ሰብዕነት የተገነዘቡ ሰዎች ትግሉን የጀመሩት ከፋሽስቱ ወያኔ የድል መባቻ ጀምሮ ነበር።

በዛ ዘመን በትጥቅ ትግል ብለው የተነሱ ነበሩ፤ ዛሬም ያሉ። ያን ጊዜ ለአቶ ሂደት ውግዘት ደርሶበታል። በትጥቅ ትግል ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ያሉ ነበሩና። ህዝብን ያንቀሳቀሰው ተጋድሏቸውም ገድል ነበር። ግን ድሉ አልሰነበተም። ደራጎንም - ደራጎን፤ ፋሽስትም - ፋሽስት፤ ሄሮድስም - ሄሮድስ ናቸውና። አይለወጡም። እነሱ ጉድጓዶች ናቸው። ሲያባጭሉ ነበር …. ዕድሉን የሰጡት። ከዛ በኋላ ሰላማዊ ትግሉ ብቻውን ለድል እንደማያበቃ የተገነዘቡት ኃይሎች ከተጫበጩ ተነስተው በትጥቅ ትግል መፋለምን መረጡ። ሰላማዊ ትግሉም እንደ ተጠበቀ ሆኖ። ለአቶ ሂደትም ተነገረው።

ይሄኛው መንገድ ትክክል ነው ተብሎ ተጨበጨበለት። ግን  አቶ ሂደት በዛ አቋም ለሰላማዊ ታጋዮች ፊት አይሰጥም ነበር። በሌላ በኩል ሰላማዊ ትግልን የመረጡ በብሄረሰብ ከተደራጁት ጋር መደረክን ሲፈጥሩ አቶ ሂደት ከፋውና ውግዝ ከአርዮስ አላቸው። እንዴት ህብረ ብሄር ፓርቲዎች ከብሄረሰብ ድርጅቶች ጋር ብሎ አቶ ሂደት አኮረፈ። ከዛ ቀድሞም በውጪ ያሉትም ህብረትን ፈጥረው ነበር። ዛሬ ዓይነህ ላፈር ሊሉት።
 
የሆነ ሆኖ  አሁን ደግሞ ወቅቱ ከተጨባጩ ጋር ተጋብቶ በይፋ ህብረ ብሄር ፓርቲዎች ከጎሳ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት ተስማሙ ብሎ አቶ ሂደት ዓወጀ። ማለፊያ ብለናል። አቶ ሂደት ይሄኛው ትክክለኛ መንገዴ እያለን ነው። ጎሽ! ተብሎ እዬተጨበጨበለት ነው። አሁንም የአማራ መደራጀትን አቶ ሂደት ጊዜ ጠብቆ ቢዛ አንደሚሰጠው የቆዬ ሰው ይዬው ….. 


ስለምን? እውነት የሚፈልቀው በሂደት ነውና። …. የእውነት ጌጡ ጊዜ ነው። የእውነት ጠበቃውም ጊዜ ነው። እውነትን የሚያነጥረው ጊዜ ነውና። ሰከን እንበል ብሏል ከያኒው መርኃችን እናድርገው …. እንደ ዕድሜያችንም አንሁን። እውነትን ተጣድፎ የቀደመ የለምና ….


ምንጭ።
Muluken Tesfaw & Dr Demeke Gessesse about Amhara Resistance on AbayTube
Ethiopia: Professor Alemante Gebreselase on Gonder Hibret | Must Listen

የጠራ የትግል መስመር የድል መባቻ ነው!
የአባቶቻችን ትውፊት በቅኝነት እንድንገዛ አይደለም! ይልቁንም ለነፃነታችን ቀናዒ እንድንሆን እንጂ!
ቂም ሌላውን ከማጥፋቱ በፊት እራስን መጀመሪያ ይደምስሳል። ከቂም የጸዳ መንገድ አትራፊ ነው።

ለነበርን ጊዜ እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ደህና ሁኑ።




አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።