ይህን ማንዴላነት ኮ/ ጎሹ ወልዴ ብቻ ነው ሊወጡት የሚችሉት።

ብሄራዊ የእርቀ ሰላም ማቋቋሚያ ኮሚሽን አዋጅ የተግባራዊነት የአቅም ልቅና ፅላተ ማንዴላነት ለስኬቱ...

„ትእዛዝ በትእዛዝ፣ ሥርዓት በሥርዓት፣
 ሥርዓት በሥርዓት፤ ጥቂት በዚህ፣
ጥቂት በዚያ“
ትንቢተ ኢሳያስ ፳፰ ቁጥር ፰

ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
25.12.2018
ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ

የአላዛሯ ኢትዮጵያ ማንዴላ!

·       መነሻ።
የምክር ቤቱ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን ማፅደቀ

v   ምኞት የሚቀዳ የሃሳብ ፍሰት!

„ቸር ተመኝ ቸር እንድታገኝ።“ እንዲህ ቸር ተመኘሁኝ ተዚያ በፊት ግን እንዴት ናችሁ የኔዎቹ ቅኖቹ? ደህና ናችሁ ወይ? አሁን ከፋናም ከዋልታም ቴሌቪዥን እንደሰማሁት ዜና የኢትጵያ የተዋካዮች ምክር ቤት ዛሬ የብሄራዊ የእርቅ ማቋሟሚያ ረቂቅ ዓዋጅ በአንድ ድምጽ ተዕቅቦ፤ በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን አዳመጥኩኝ። ትልቅ እርምጃ ነው። ትልቅ እርምጃነቱ በዳይም ተበዳይም፤ የተጣላም የሚታረቅም የለም የሚል ጠሐይን የገለበጠ ሙግት ስለነበር።

እርግጥ ነው ሥራው እጅግ ውስብሰብ ነው። ሃላፊነቱም ግዙፍ ነው። ማስተዋልን፤ ትዕግስትን፤ መቻልን፤ አብዝቶ ማድመጥን፤ አረግቶ መቀመጥን፤ የሰፋ እና የዘለቀ የህይወት ተመክሮን፤ ነገሮችን በተያዬ አቅጣጫ ማዬትን፤ ተግባቢነትን፤ አቃፊነትን፤ ህሊናን መፍራትን፤ ትውፊት - ባህል - ወግ - ታሪክ - ህዝብ - ህግ አክባሪነትን፤ ፈርኃ እግዚአብሄር መኖርን መቀበልን፤ ሙሉሰው የሆነ ሰብዕናን ይጠይቃል። ጭንቅ ሃላፊነት ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ባለ የቂም ፖለቲካ ባህል፤ የበቀል ሥልጣኔ፤ የቁርሾ ቱማታ፤ የስሜት አውሎ ባለበት አገር ይህ ሃላፊትን እንደ ሌሎቹ ተቋማት የሚታይ አይደለም። የታጨቀ ችግር ነው ያለው። ያተከመረ ፈተና ነው ያለው። የቆሰለ ውስጥ ነው ያለው። የመገለ አዬር ነው ያለው። ግጭት የኒናፍቀው ሽው የሚለው ንፋስ ነው ያለው።

በጣም ወደ ላ ወደ 50 እንሂድ ከተባለ ሲንዘላዘል ትወልድ ሊቋረጥ ይችላል። እንደ እኔ የ27 ዓመቱን ብቻ ለማዬት ቢሞከር የተሻለ ነው። ራሱ የ27 ዓመቱ ቀርቶ አንዱ ነጠላው የቅርቡ የቡራዩን ወይንም የቤንሻንጉሉን ወይንም የወልቃይት ጠገዴን ወይንም የኮንሶን፤ የበደኖን፤ የወተርን፤ የአርባጉጉን በነጠላ እንይ ቢባል እንኳን አንዱ ችግር እራሱ እጅግ ከባድ ነው እንኳንስ የ50 ዓመቱን ቀርቶ …

ባለመታደል ታሪካችን እኛው እራሳችን አደማነው፤ እኛው እራሳችን አጠቆርነው፤ እኛው እራሰቻን አሰቃዬነው። እኛው እራሳችን አበለዝነው። የትናንት ክምሩ ችግር እለበቃ ብሎ ዛሬ ትናትን የሆነው የጋዜጠኛ ደምስ በለጠ አሟሟት እራሱ በምን ያህል ፈውስ ልንድን እንደምንችል ፈጣሪ ነው የሚያውቀው። 

ምናችን ወጥቶ እንደገና ብነሰራ ወይንም ብንበጅ ከቁርሾ ልንላቀቅ፤ ከሴራ ልንፋታ እንደምንችል አላውቅም። ሰው እንመራለን፤ ሰው እንስተዳድራለን ብለን ሰውን ጠልተን እንዴት እና እንዴት ሊሆን እንደሚችል ከባድ ነው።

የሆነ ሆኖ ለዚህ ላፊነት ለእኔ መንፈስ የማከብራቸው ኮ/ ጎሹ ወልዴ ኮሚሸነር ከሆኑ ነፍስ ታርፋለች። ለዚህ ቦታ ከእሳቸው ውጪ አደብ በተፈጥሮው አብዝቶ የሰጠው ነፍስ ለማግኝት ይቸግራል። ኮነሬሉ እንኳንስ ለዚህ ሃላፊነት አባትም - እናትም - እህትም - ወንድምም መሆን ሊያቅታቸው ቀርቶ አገር ለመመራት የሰጣቸው ናቸው። እዮራዊ ቅባ አላቸው። ትውልዱም ሆነ እናት አገር ኢትዮጵያ ባለመታደል አልተጠቀመባቸውም እንጂ። ሃብት ናቸው የነባቢቲም የነፍስም።

መቼም ይህ ዘመን ምሩቅ ሆኖ ኮ/ጎሹ ወልዴ አገር ስለገቡ ቢፈቅዱ ይህን ሃላፊነት አሳቸው ቢይዙት አዲስ ምዕራፍ ወይንም አዲስ ዘመን በኢትዮጵያ ያብታል ብዬ አስባለሁኝ። እራሱ ኮሚሽኑ አድዮ ነው ለእኔ። አዲስ የተስፋ ዓመት።

ያርግልን! አሜን! ይሁንልን! አሜን!

የሚጠበቀው።

ሌላው ዜጋ ደግሞ ልቡንም ህሊናውም ሰፋ አድርጎ ራሱን አጥቦ መሳተፍ ይገባዋል። ለይደር ቂምም በቀልም መቀጠር የለበትም። እርግጥ ያቀተ ነገር መሆኑን ባውቅም አገር አገር አገር ማለት ራስን ሳያሸነፉ በሽንገላ በማለት ዲሪቶ አገር አትኖርምና። አብሶ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊሂቃን ራሳቸውን ውስጣቸውን ማጠብ አለባቸው።

የኢትዮጵያ የፖቲካ ሊሂቃን መላዕክነታቸውን ገፋ አድርገው ሰው መሆናቸውን አምነው በዬዘመኑ ለሚያጠፉት፤ ለሚያብክኑት ትውልድ፤ ለሚፈጽሙት በአንድም በሌላም የመንፈስ ድቀት አታንሱብን ከማለት ይልቅ ውስጥን ገልጦ፤ ተንበርክኮ ይቅርታ መጠዬቅ ያስፈልጋል። ንስኃ መግባት። ይቅርታም፤ ምህረትም፤ ሰላምም የአንድ ቀንጣ ነፍስ፤ ወይንም የአንድ ወገን ብቻ ፍላጎት እና ጥረት ተስፋን አያሳካም ስለ አገር ማሰቡ ቧልት ካልሆነ። 
  
እኔ በግሌ ልዑል እግዚአብሄርን እማመሰግነው ትውልድ የማይተካቸው ኮ/ ጎሹ ወልዴን በህይወት ስለቆዬልን ነው። እሳቸውን የመሰለ ሙለሰው፤ ባለሙሉ መክሊት፤ ደርባባ፤ በሳል፤ ምራቁን የዋጠ፤ ጨዋ፤ አንደበት ርቱ፤ የመሆን ማህንዲስ ንጹህ ልጅ አላዛሯ ኢትዮጵያም ስላላትም ዕድለኛ ናት።

ጨርሰን እንዳንጠፋ እንዲህ ለመዳህኒት የዓይን ማረፊያ የሥለት ልጅ ማግኘት ስጦታው ረቂቅ ነው። እንደተዋህዶ አማኝነቴ እሳቸውን እንደ አጋይዝት አለሙ የሥላሴ ወዳጅ አበ ብዙኃን አብርኃም አድርጌ ነው እማመለከታቸው። ለሁሉም ምቹ የሆኑ፤ ለሁሉም ኃላፊነት ቅን እና ሚዛን ናቸው።

ይህን ዓዋጅ ተመረቅ፤ ተሳካ፤ መፍትሄ ሁን፤ የትውልድ አብነት ትሩፋት እና ትውፊት ይኑርህ፤ አትርፍ ካለው እዮር እሳቸው ኮሚሽነር ያደርግለት። ቅኖችም ሐሤት ያድርጉ። ዓለምም ይድነቀው ዐምዱ አድርጎ … እንደለመደበት … ይፍለቅለቅ ...

ዓራት ዓይናማው መንገዳችን የአብይ ሌጋሲ ብቻ ነው!
አብይ ኬኛ!

የኔዎቹ ለነበረን ሞንሟና ጊዜ አመሰግናለሁኝ። ኑሩልኝ!

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።