የግፍ መፈተኛ ሊቀ ትጉሃን አቶ መኮነን ገበዬሁን በምልሰት ሳስባቸው።

ግፍ።
„እግዚአብሄርን ደጅ ጥና መንገዱንም ጠበቅ፤
ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤
ሃጢያተኞችም ሲጠፉ ታያለህ።“
መዝሙረ ዳዊት ፴፮ ቁጥር ፴፬
ከሥርጉተ©ሥላሴ Sergute©Selassie
07.12.2018 ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።


                                   ሊቀ ትጉሃን አቶ መኮነን ገበዬሁ አልሞቱም 
                                                ታሪክ አለላቸው። 
 መነሻ!

አቶ ገዱ እንዳርጋቸውን ያስለቀሰው የአባቱ የአቶ መኮንን ገበየሁ
 በሼክ አላሙዲን ተንኮል እንዴት እንደሞቱ ሲገልፅና ሀብታቸው እንደተቀማ

  •  በምልሰት ልሰባቸው ሊቀ ትጉሃንን አቶ መኮነን ገበየሁን።


መቼም ይህን መረጃ ሸር ሳደርጋችሁ አዬ የሥርጉተ ነገር ደግሞ ከዚህ ምን እግር ጣላት ትሉ ይሆናል። ልዑሌ አምላኬ ከብዙ የሕይወት ዘርፎች እሳተፍ ዘንድ ሹልክ እያደረገ ያሰዬኝን ታሪካዊ ሂደት ክፈለ አካል ነው ዛሬ እማጫውታችሁ።

ይህን ቅንብር አሁን አዬሁት። እናም ደነገጥኩኝ። እኔ እኒያ ዓራት ዓይናማ ትንታግ ባለ ራዕይ በህይወት ይኖራሉ ብዬ ብቻ ሳይሆን የሚሊዬነር ሚኒዬለር ሆነዋል ብዬ አስብ ነበር። አገር ብገባም ለማዬት ከምጓጓላቸው አንዱ ነበሩ። እኔ እማውቃቸው ባላ ልቅና አዕምሮ ሊ ትጉሃን አቶ መኮነን ገበዬሁ ከሆኑ የሚገርም ምናብ የነበራቸው ሰው ነበሩ። ነፍሳቸውን ጌታዬ አምላኬ በጽርኽ አርያም ያኑርልኝ።

እኔ ያወቅኩቸው ግሎባል የሆነ ቢዝነስ ኢንሸቲብ ዳይሬክሽን የሚባል ፓሪስ የሚኖር አንድ ድርጅት በዓለም ያሉ በቢዝነስ ተግባር የተሠማሩ፤ ፈጠራቸው በልዩ ሁኔታ የተቀመረ፤ ታታሪ፤ ስኬታቸው ደግሞ ዕውቅናው ሉላዊ የሆነ ድርጅቱ በራሱ መስፈርት ዬዬአገሩንም መንግሥታዊ አስተዳደር ሳያስፈቅድ በሚያደርገው የግል ጥናት አሰሳ መሰረት በዬዓመቱ ምርጦችን ይሸልማል - በጉባኤውም ያሳትፋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ90ዎቹ መደምደሚያ በ2000 መግቢያ ላይ ይመሰለኛል። በትክክል ጊዜውን አላስተውሰውም። ብቻ ሦስት የኢትዮጵያ ታታሪ የንግድ ሰዎችን ድርጅቱ ይመርጣል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ አቶ መኮነን ገበየሁ ነበሩ። ሌላው ድርጅት አዋሽ ባንክ ሲሆን አንዱ ደግሞ የቡና ለኪና አስመጪ ድርጅት ይመሰለኛል። እኔ ችግሬ ዝንጉ ነኝ። ዝንጉነቴ እዚህ ሲዊዝ ውስጥ በ2001 ሆስፒታል ገብቼ ኮማ ውስጥ ለሁለት ቀናት ያህል ነበርኩኝ። እናም ከኮማ መልስ ትርፉ መዘንጋት እና በህይወት መትረፍ ነበር።

ወደ ቀደመው ግሎባል የቢዝነስ ጉባኤ ስመጣ በዓለም የተመረጡት የንግድ ፈጠራ እና የስኬት ባለቤቶች በተገኙበት ድርጅቱ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ሦስቱም ኢትዮጵውያን ተገኝተው ነበር። ጉባኤው እኩለ ሌሊት ነበር የተጀመረው።

መግቢያ 100.00 ዶላር ነበር በነፍስ ወከፍ። ቀለል ያሉ የምግብ እና የመጠጥ መስተንግዶም ነበር። በጉባኤው ላይ የቢዝነስ ኢኒሸቲብ ዳይሬክሽን ዳይሬክተር ተገኝተው ነበር። የድርጅቱ ዋና ጽ/ቤት ማድሬድ ስፔን ነው። ዳይሬክተሩ ነገረ ሥራቸው ጃንሆይን ይመስላሉ። አጠር ቀለል ያሉ እና ቀልጣፋም ናቸው። ከጠዬቃቸው ጋር ሁሉ ፎቶ አብረው ይነሱም ነበር። የማይከብዱ ተግባቢም ነበሩ።

በዛን ጊዜ እነዛ ሦስት ኢትዮጵውያን በዬተሰማሩበት መስክ ስኬታቸው ጥረታቸው እና ፈጠራቸው ዓለም አቀፍ ዕውቅና በማግኘቱ ከንፍሮ ጥሬ የሚያወጣው አምላክ ያወጣቸው ነበሩ ማለት እችላለሁኝ። ያልተመረጡ፤ ወኪል ያልነበራቸው አገሮች ሁሉ ነበሩ። አሁን ለምሳሌ የዩንሲኮ አንዲትም የተመዘገብ አንጡራ ሉላዊ ውርስ ቅርስ የሌላቸው አገሮች እንደሉት ሁሉ ማለት ነው።

አቶ ገበየሁ መኮነን ነፍሳቸውን ይማረው እና በቱሪዝም ዘርፍ ከትንሽ ቦታ ተነስተው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ብቻ ሳይሆን ህልማቸው የሚታሰብ አይነት አልነበረም። ጊዜ ወስጄ ሁሎችንም በወልም በተናጠልም አወያይቻቸው ነበር። የሄድኩት ዘገባ ልሰራ ስለነበር። ሪፖርቱን አጭር በሦስት ደቂቃ ሰርቼ ሁኔታው ስለመሰጠኝ ልዩ ሪፖርት 10 ደቂቃ በድምጽ ሰርቸበታለሁኝ።

አቶ ገበዬሁ መኮነን የጣና ያህል መጠነ ስፋት ያለው ምናብ ነበራቸው። ሆቴሉንም ያሰቡት ከዚህ አንፃር ነበር። ከጣና ጋር በጣም የሚስጢር ያህል ቁርኝነት ስለነበራቸው የሐይቁን መንፈስ የተጋሩ ብቻ ሳይሆን ሐይቁን ወደ ብልጽግና ለማምራት አዲስ ራዕይ የነበራቸው ታላቅ ሰው ነበሩ። ጣና ለሳቸው የህልማቸው መሰረት ነው። የውጥናቸው መንገድ "ሀ" የተባለውም በጣና መሆኑን አጫውተውኛል። ልጆቻቸውን ውጪ አገር አስተምረው በቱሪዝም ዘርፍ ለመተካት የነበራቸው ራዕይ እና ለማስተማርም እንግሊዝ ወይንም ፈረንሳይ ምርጫቸው እንደሆነ አጫውተውኝ ነበር።

የሚገርመው ከጉባኤተኞች ጋር በነበረው ቆይታቸው የልባቸው ያደረሰ ሰው ሲያገኙ ከዬትም ይምጣ ከዬትም የኢትዮጵያን ሥጦታ ያበረክቱ ነበር። 

ለእኔ ለራሱ መደቡ በጥቁር የተሰራ የኢትዮጵያ ሙሉ ካርታ ያለበት ሰጥተውኛል። ለብዙ ሰው መሰል ስጦታ አዘጋጅተው ይዘው ሁሉ ነበር። በዬአገሩ ወዳጆች ቤሰቦች እንዳላቸው አጫውተውኛል። ለሳቸው ነጭም ቢሆን ኢትዮጵያን ከወደደ ወገናቸው ነው። ሉላዊ ናቸው። ኑ ወደ ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያን እናልማት ባይ ናቸው። ራዕያቸው ሩቅ ነበር። ቅንም ለጋስም ሆነው ነበር ያገኘኋቸው። እኔን እራሱ ጋብዘውኝ ነበር ጣና እና ነባቢቱን፤ መንፈሱን ከነጥልቀቱ ሊያሰጎበኙኝ።

ምን ማለት ነው ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ራሳቸው ተቋም ነበሩ። በፍጽምና ባለውለታ  የአገር ናቸው። ገና ሰው አገኛለሁ ኢትዮጵያ ላይ ኢንቤስት ማድረግ የሚችል፤ ወይንም ለጉብኝት የሚመጣ ብለው ስጦታ በገፍ ይዘው ነበር የመጡት። የሚገርም መሰናዶ ነበር። ግቡ አገራችሁ ነበር የሚሉት። ስደቱን በፍጹም አይወዱትም። ስደት ለትምህርት ብቻ፤ ዕውቀት ቴክኖሌጂ ስልጣኔ ለመቅሰም ብቻ ነው የሚሉት።

ሥራን በሚመለከት ፍልስፍናቸው በሳቸው ዕድሜ ሲንገሩኝ ያን ጊዜ ሙሉ ዕድሜ ላይ ነው የነበሩት ደልደል ያሉ ሙሉሰው ነበሩ፤ „ሥራ ከሌለኝ እታመማለሁኝ“ ነበር ያሉኝ። ያን ጊዜ እኔ ወጣት ሳተናዊት እሳቸው ደግሞ ጎልማሳ ሙሉ ዕድሜ ላይ ነበሩ። የመንፈስ መዛል፤ የድካም ስሜት ዝር የማይልባቸው ቆቅ ነበሩ። 

የምናባቸውን ንድፉን ሁሉ አስርተው፤ በባለሙያ አስጠንተው ዲዛይኑን ይዘውት ስለነበር ባህርዳር በሳቸው ዕይታ እና ሚዛን የዓለም መሰህብ መዲና የማድረግ ህልማቸው ጸሐፊ ምስባህከ ወርቁ ዴርቶጋዳ የጻፋው ዓይነት ነበር፤ እና እኒህ ዓለም አቀፍ ተሸላሚ እና አገር ወዳድ ፍጹም ሰው ነው እንደዛ በንዴት እንዲሞቱ የተደረገውን? አንጀቴን በላው። ለነገሩ ጊዜ ደግ አሁን ሁሉን እያዬነው ነው። ማን ቋሚስ አለና? ማንስ ባፈራው ንብረቱ እሰከ ፍጻሜ ሊቀጥል፤ ዳስ ናት ምድር፤ ገብያ ናት ምድር። ሞቅ ብላ የምትፈርስ።

ብቻ የተፈጸመባቸው በደል እጅግ ያሳዝናል ብቻ ሳይሆን ያርመጠምጣል? ማለት የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ በጣም ዘግይቷል? ያን ጊዜ እኔ እንደማስበው አቶ አዲሱ ለገሰ ነበሩ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት። አቶ ታምራት ላይኔም ጠ/ሚር። የፖለቲካው ሶፍት እና ሀርድ ዌር ባለሙያው ደግሞ ሳጅን በረከት ስምዖን። በእነኝህ ጣምራ ቅርምት ነው ጣናም የታመመው፤ አቶ መኮነን ገበየሁም ለህልፈት የተጋለጡት። የጣና ህመም ታቅዶ የተጀመረው ጎንደር መሬት ላይ ነበር።

ልጃቸው ሲገልጽ ለቤተሰብ ጊዜ አልነበረውም ያለው ዕውነት ሲሆን፤ ደጋፊ ያስፈልጋቸው መካሪ ያስፈልጋቸው፤ ጽኑ እረዳት ያስፈልጋቸው እንደ ነበር ግን አጫውተውኛል። ምን ነበር ያሉኝ „ባላ ያለማገር … „ በልጆቻቸው ተስፋቸው ዝልቅም ነበር። አሁን እንዲህ ልጃቸውን ሳዬው ተስፋቸውን አሳክቶላቸዋል ብዬ አስባለሁኝ። እኔ በህይወት አሉ ብየ አስብ ስለነበር ይህን መረጃ ባልሰማ ኖሮ የማውቀውን አልገልጽም ነበር። 

ሊቀ ትጉሃን ቆሞስ መኮነን ገበዬሁ ያመጡትን መጠነ ሰፊ የትውልድ ፕሮጀክት ንድፍ ያመጡትን ቢጋር አሳይተውኝ ነበር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተዘጋጀ አይመስልም ነበር። አፍጥጬ ነበር ያዬሁት። እጅግ ሩቅ የሆነ ጉዳይ ነበር። እሳቸው እንደ ቀደምቶቹ እንደ አጤ ፋሲል፤ እንደ አጤ ሚኒሊክ፤ እንደ አጤ እያሱ፤ እንደ አጤ ኃይለ ሥላሴ የተፈጥሮ ጸጋ ሰጥቷቸው ነው እንጂ ያን ሁሉ አቅም በሙያም በመደበኛ ትምህርትም ተምረውት አልነበረም። 

ለዚህም ነው በልጆቼ የአካዳሚ ዕውቀት ላይ አልደራደርበትም ያሉኝ የሚመሰለኝ። ልጆቻቸውን የራዕያቸው ወራሽ ለማድረግ ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው። ብአዴን ይህን ድርሻውን ከመሸ ጀንበር ካዘቀዘቀም ቢሆን እሱም እራሱ ነፃ መውጣቱን ገልጦታል እና ያን ባሊህ አልባ የሆነ የብቃት አቅም ከግፈኞች የሴራ መንጋጋ አላቆ ልጆቻቸው ትካቸው ይሆኑ ዘንድ በተግባር አደራውን ማስበል አለበት ብዬም አስባለሁኝ። የ አማራ ትውልድ ብክነቱ በስልት እንዲህ ረቂቅ ነውና። ውርስ ቅርስ እንዳይኖር ታቅዶ ስሩን ማፍለስ። 

አንድ እረዳት አጥተው ታሪካቸውን፤ ራዕያቸውን መዘረፋቸው ላይበቃ እንዲህ አሰታዋሽ ማጣታቸው እጅግ ያሳዝናል። እውነት ለመናገር እሳቸው ድንግልናቸው ሥራ ወዳድ መሆናቸው ነው። ለትውልዱ ሮል ሞዴል ነበሩ። የሚታምን አልነበርም በዛ ዘመን እኒህ ብቁ ኢትዮጵያዊ የነበራቸው ሁለገብ ራዕይ እና ብቃት። አነሳሳቸውም እንዲሁ የሚገርም ታሪክ ነበር ያጨዋቱኝ። ከቤተሰብ ፈቃድ ውጪ መጻፍ የተጋባ ስላልሆነ በተደሞ ልለፈው። 

ምን ይሆናል የተፈጠሩበት መሬት እና ማህበረሰብ ነው እንዲህ ጉድ የሠራቸው። የሌላ ብሄረሰብ አባል ቢሆኑ ኖሮ ጥቃቱም አይኖርም ነበር፤ ቢኖርም አስተዋሽ ያገኙ ነበር። መካሻም ብልሃት ይኖረው ነበር። ልክ እንደ ድብ ባህሩ ባካና የማሌሊት መስራች እንዲህ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ገድል በሚሉት ላይ ተርስቶ ብን፤ ትን፤ ክስም ብሎ እንደ ቀረው ማለት ነው።

ላዩም ታቹም ጣሪያውም ግድግዳውም ጀርባውም ማገሩም አማራ ጠል በሆነበት በዛ ድቅድቅ ውስጥ የበራ ጧፍ መጥፋት ነበረበት፤ እናም ሆነ። ማን ነበራቸውና? ብቻቸውን ነው የታገሉት፤ ብቻቸውን የተጋፈጡት፤ ብቻቸውን አሳራቸውን ነው ያዩት። እኔ ሳገኛቸው የቅርብ የቤተሰብ ረዳት የማግኘት ጥማት ቢኖርባቸውም፤ ተስፋቸው ጥንዙል አልነበረም። እጅግ የፋፋ እና የማደረግ አቅሙ ቀልጣፋ ሆነ ነበር ህሊናቸውን ያገኘሁት፤ እራሱ የተስፋ ምህንድስና እርምጃቸው እርግጠኛ ነበር።

ሰውነታቸው ሙሉ፤ ወፈር ያሉ ግን ቅልጥፍናቸው ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ የሚገርም የኮበሌ ዓይነት መንፈስ እና ንቃት ነበራቸው። የነበርንበት አዳራሽ ለኮክቴል ሆነ ለራት ግብዣ የሚመች ክብ ሆኖ የተሰራ ስለነበር ለተለያዩ ጉዳዮች የመንቀሳቀስ አጋጣሚው ነበር። አዬሩ ራሱ ዘና ያለ የተፍታታ ነበር።

እንደ ገና ኮሬደሩ ፈረስ ያስጋልብ ነበር። ስለዚህ ቀሏቸው ነበር ሲንቀሳቀሱ ያዬሁዋቸው። እኔ ሁልጊዜም እንደማጫውታችሁ ውስጥን ፍለጋ ስለሆነ ትጋቴ በብዙ ሁኔታ ጥራት ያለው ንጥረ ነገር እንደ ነበራቸው አይቻለሁኝ። በጣና ዙሪያ የሚኖር ሰው ንቃቱ አሳ መደበኛ ምግቡ ሆኖ ስለሚያድግ የተለዬ ታለንት ነው ያለው። እኔ ይህን ደልጊ ጎርጎራ ወደ ደራም ወረዳ ያሉ ገበሬዎችን ሳነጋግር እና ከጣና ራቅ ያሉትን አካባቢዎች ያሉትን ሳይ በብዙ ሁኔታ ይለዩብኛል። በቀለም ትምህርትም እንዲሁ።

ከዚህም በላይ የፈጣሪ ስጦታም ታክሎበት የተለዩ ብርቅዬ ኢትዮጵያዊ፤ የሚያኮሩ ዕንቁ ነበሩ አቶ ገበዬሁ መኮነን። ለሥንት ሰው ጥላ እና ከለላ ጋሻ እና መከታ የሚሆኑ የአገር ባለውለታ ነው በጥዋቱ በደቦ ግፍ በጥዋቱ ያጣናቸው። 

እንደ ዕውነቱ ከሆነ የአማራ ክልል ቢያስብበት ባህርዳር ዩንቨርስቲ ላይ ሐውልት ሊሠራላቸው የሚገቡ የሥራ ጀግናው ናቸው። ቢያንስ ከደረት በላይ ያለ ሐውልት የማሰራት ትልም ቢኖር መልካም ነው። እኔ ለብላቴ ሎሬቱ እምመኛው እንደዛ ነው አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቋንቋ ፋክልቲ ላይ። ያው መጸሐፍቶቼ ለዚህ ተግባር ነበር ታልመው የታጠሙት የነበረ፤ ግዞት ተበይኖባቸው መጋዝን ያሞቃሉ እንጂ።

አቶ መኮነን ገበዬሁም ትወልድን በሥራ በማድረግ በመጣር አቅም የገነቡ የሥራ ሐዋርያ ናቸውና ማስታወሻ ለትውልዱ ያስፈልጋቸዋል ብዬ አስባለሁኝ። ጣና ላይ ስላለው ሆቴል የረጅም ጊዜ ዕቅድ ሲነግሩኝ ህልም ይመስለኝ ነበር። ከተማ የመገንባት ነበር ሃሳባቸው። አሁን ይህን መሰል ሃሳብ ለጋህር ላይ ከስንት ዓመት በኋዋላ ያውም በውጭ ኢንበስተሮች መታቀዱን ጠ/ሚር አብይ አህመድ ከሥፍራው ተገኝተው ሲናገሩ አዳምጫለሁኝ። ይህን ሃሳብ አቶ ገበየሁ መኮነን ሲያስቡት ዶር አብይ አህመድ ገና 20 ዓመት ዕድሜ እንኳን በቅጡ አልደፈናቸውም ብዬ አስባለሁኝ።

ዕውነት ለመናገር አቶ ገበየሁ መኮነን ሲያሰረዱኝ አንዳንዱ ይከብደኝም ነበር። እኔ
የቢዝነስ ሰው አይደለሁም። በዚህ ዙሪያም ጊዜ አጥፍቼ አላውቅም፤ ላድርገው ብልም የማልችልበት ሰው ነኝ። ተፈጥሮየም አይደለምና። አሁን ብዙ የኤኮኖሚ ውይይቶች ጹሑፎችን ደግሜ ማንበብ ግድ ይለኛል፤ ጭብጡን ለማግኘት፤ ውይይትም ከሆነ እንዲሁ። ይከብደኛል። ብቻ የተለዩ ፍጡር ነበሩ የውስጣቸው አቅም የሚመስጥ ነበር።

እንዲህ ዓይነት ብቁዎች በዘመን አንድ ጊዜ ነው የሚፈጠሩት። ደብረታቦር ከእኛ በእጥፍ በቀደመው ዘመን አቶ ስመኝ ባዬህ የተባሉ ድንቅ የፈጠራ ሰው ነበሩ። ልጃቸው አቶ አለማዬሁ ስመኝ አባታቸውን ተክተው የታወቁ የፈጠራ፤ የተግባር፤ የመሆን ታላቅ ሐዋርያ ናቸው። ካለዘመናቸው የሚፈጠሩ ዓይነት እንዲህ ዘመን ያበረክታል። እነኝህ የትውልድ በረከቶች ናቸው።

እኔ እማያቸው አቶ መኮነን ገበዬሁን ልክ እንደ አቶ ስመኝ ባዬህ ነው። እኔ ወጣት በነበርኩበት ዘመን አቶ አለማዬሁ ስመኝ ኑሯቸው ራሱ የአውሮፓ ነበር። የልጆቻቸው አያያዝ እና የቤተሰብ አደረጃጃታቸው ዕጹብ ድንቅ ነበር። አቶ አለማዬሁ ስመኝ ዕድለኛ ናቸው። ባለቤታቸው ቅድስት ናቸው በሁለመናቸው። መልካቸው ብቻ ሳይሆን የትህትና ተቋም ነበሩ። ስለዚህ ብዙም የቤት ውስጥ ችግር አልነበረባቸውም፤ አብረውም ነው የሚሠሩት። በሃላፊነት ባለቤታቸው ከእህታቸው ጋር የሚሠሩት ፕሮጀክትም ነበራቸው አዲስ አባባ ላይ። እጅግ የሚደንቅ የሰመረ የትዳር አቅም ነበር አይ የነበረው።

አቶ መኮነን ግን በዚህ ዘርፍ ምን ያህል ዕድለኛ እንደነበሩ አላውቅም። ምክንያቱም ለቤተሰብ የሚያውሉት ጊዜ እያነሰ ሲሄድ ይህን የምትረዳ የትዳር አጋር ከሌለች፤ እሳቸው እጅግ የመጠቀ ሃሳብ ሲያፈልቁ መንገዱን የምትቀይስ አጋር ከሌለች በዛ መጠራቅቅ እና ፈተና አልፎ ለመዝለቅ ጋዳ ነው። የአቶ አለማዬሁ ስመኝ የስኬት ቁልፍ እኒያ የሁሉ ነገር እመቤት ደልዳላው ወ/ሮ ለምለም ናቸው።

የሁለቱም ብሩኽነት ማለቴ የአቶ አለማዬሁ ስመኝ እና የአቶ መኮነን ገበዬሁ ልጆቻቸውን በሙያው ለመተካት፤ አካዳሚያዊ ጥረትን ተግባራዊ ለማድረግ የነበራቸው ህልም ተመሳሳይ ነበር። በሌላ በኩል የሰቲት ሁመራ አራሾችም በዘርፉ ልጆችን የማውረስ ብቻ ሳይሆን እርሻውን የበለጠ መካናይዝድ ለመድረግ ልጆችን ወደ ት/ቤት መላክ ብቻ ሳይሆን ጉልማ የሚባል  እርሻ ማሳ ሁሉ ነበራቸው። የልጆች የማበረታቻ እና የት/ቤት በጀታቸውን የሚሸፍን። ይህም አንዱ ትውፊታችን ቅርሳችን የማሰብ ልቅና ነው።

እንደ ልዩ ቦነስ በጉጉት የሚጠበቅ ነው ጉልማ እርሻ። ይህ የማነሳሻ የማበረታቻ ስልት ነበር። ብቻ ብዙ ዘመኑን የቀደሙ ዓራት ዓይናማዎችን ነበሩን። አሉንም። ችግሩ ግን መሰናክሉን ለማለፍ ባለቤት አልቦሽ መሆኑ ነው። አብሶ በአማራ ሥም የተደራጀው የቀድሞው ብአዴን  የአማራን ሁለመና አቅም በማምከን፤ በማጥፋት ላይ ነው የተመሰረተው። የተደራጀበት መሠረታዊ ዓላማ ለዚህ ነው።

የወያኔ ሃርነት ትግራይ አማራን የመመንጠር ሴራ የፍፃሜው ጦርነት ለድል አድራጊነት ነው ብአዴን የተደራጀው - የቀድሞው። አይደለም አማራ ክልል ተብሎ ተቆርምጦ በተሰጠው ክልል ከዛም ውጪ ያሉት እዬታዳኑ ተሰደዋል፤ ተሰውረዋል፤ ተገድለዋል፤ ተስፋ ቆርጠው ከሁሉም ዘርፍ ተሰናብተዋል። ቋንቋውን የተናገረ ሳይቀር ተመንጥሯል። ባለቤት የሌለው ማህበረስብ ዕጣ ፈንታው እንዲህ መክኖ መቅረት ነው። 

የሆነ ሆኖ አቶ መኮነን ገበዬሁ እዛው አማራ መሬት ላይ ስለነበሩ የበለጠ መከራውን እንዲሸከሙ ተገደዋል። አማራ ተኝቶ ለሽ ብሎ በተኛበት ዘመን አንድ ለአንድ ተገኝተው በሽታሽቶች ከምድር ገጽ እንዲወገዱ መደረጉ ግድ ነበር።

አሁንም እነ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው እንደሚሉን "ስለ ሥልጣን እከሌ በብዛት ወሰደ የሚባለውን አታንሱብን አታውሱብን ይህን ማንሳት ስንፍና ነው የፈለገው ሹመቱን ይጠቅልለው ወይንም ይቀራምተው ይህን ጥያቄ ማንሳት እንዲያውም ያሳፍራል" የሚሉት ቧልት ገታ አድርገው ለጥቃት አማራው የተጋለጠበት መሰረታዊ አምክንዮ ላይ ቢተጉ፤ የምርምር ተግባር ቢያደርጉ ይሻላቸዋል።

ፍልስፍናው አልገባቸውም። የፖለቲካ ድርጅት መደራጀት ማለት። ቁጭ ብሎ ሰቅሎ ቆሞ መውረድ ቸግሮት ነው አማራ መንገድ እዬመራ፤ እያበላ፤ እያጠጣ፤ አብሮም አንግቶ አገር አስረክቦ መከራውን አፍንጫውን ተሰንጎ ሲከሰክስ የኖራት። ያ ላይበቃ አሁን ደግሞ ተረኛው በለኝ ተመቻችልሃለሁኝ ለጽድቅ ይሆን ወይንስ ለምን? ፍቱት ውዴቼ …  

የአማራ ድርጅት ተብዬውን የወከለ የኢትዮጵያ አንባሳደር በአሜሪካ ትግሬ፤ ብአዴን በተሰጠው ዕድል እና ኮታ አንድ የአማራ የህክምና ባለሙያ ለሂቅ ጠፍቶ የፌድራል የጤና ጥበቃ ሚ/ር ተጋሩ ቀልዱ መቆም አለበት። ብአዴን አማራ ለአማራ ተደራጀሁ እሠራለሁ ካለ ከምሩ መሆን አለበት። ትናንትም ይህን መከራ አማራ ተሸክመህ ኑር ተብሎ የ27 ዓመት ቀንበር እንዲሸከም ተደርጓል ዛሬም በዛው በተቀዬሰለህ ተቀጣ ግን አያዋጣም ፈቃጅም የለም።

አንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚደራጀው ለፖለቲካ ስልጣን እንጂ ለዘበኝነት ወይንም ለበር ጠባቂነት አይደለም። በዬትም ቦታ ሰው ከሌላ መረጃውን የሚያዳምጡት ልክ እንደ እኛ በስማ በለው በሚዲያ ነው። አሁን በውጭ ጉዳይ ዘርፍ ያሉት ማናቸውንም መራጃ ከእነሱ ይልቅ እነ አቶ ዳውድ ኢብሳ የቀደመውን ትኩስ መረጃ ያገኛሉ። አሁን ባለው አያያዝ ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅም፤ ኦህዴድ እኮ በእኔ ዕይታ አራት ሰው ብቻ ነው ያለው ኢትዮጵያን ከእውነቱ ከውስጡ ያደረገ፤ ዶር ለማ መገርሳ፤ ዶር አብይ አህመድ፤ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና አቶ ካሳሁን ጎፌ።

ይህ የምን ግዴ ልቅ ጉዞ ኦዴፓንም አያድነውም ኢትዮጵያንም አያድናትም። ስለምን ቢባል ሚዛኑ ካልተጠበቀ የለማ መንፈስም ጫናው ጥሶ መውጣት ይሳነዋል። ይሸነፋል። ይዋጣል። የኦዴፓ ሃይሉ ያለው ደግሞ ብአዴን ላይ ነው።

ትናንት ኢትዮጵያ ረቂቅ ሚስጢር ናት የተከበሩ የታሪክ ሊቀ ሊቃውንቱ ፕ/ ሃይሌ ላሬቦ አሉ ብለው ሲጦፉ የነበሩት ናቸው ዛሬ ኦሮምያ ላይ ጥናት አቅራቢዎች፤ የወያኔ ሃርነት ትግራይ 600 ወገንን አቧራ አልብሶ ቀብሮ አማራ ጨቆነ ገዛ ገፋን ነበር ለምዕራባውያን ይሰጥ የነበረው መረጃ። ዛሬ ደግሞ ፕ/ ህዝቃኤል ገቢሳ ተንታኝ ናቸው ለኦዴፓ። ጹሑፍ አቅራቢ ናቸው። ወደ ዬት እዬተሄደ እንደሆን እያዬነው ነው።

በዚህ በምን ግዴየለሽ አያያዝ ነገ ጉማም ነው የሚሆነው ለሁሉም ዜጋ። ምክንያቱም ቅዱሳኑን የለማን መንፈስ ሆነ የአብይን መንፈስ ትናንትም አላቀረቡትም ወደፊትም አያቀርቡትም። ስለምን? ኢትዮጵያ በጥርስ ስለተያዘች። ሁለቱ ደግሞ ከውስጣቸው ነው እዬተጉ ያሉት ስለ ኢትዮጵያዊነት።

ኦነግውያን … ሲጀመርም አልደገፏቸው፤ አሁንም እያነኮሩት ያሉት የራሳቸው ወገኖች ናቸው። ቢናድ ቢፈርስ ምኞታቸው ነው። ስለምን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ሆና መወጣት ጣውንታቸው ስለሆነ።

ቀድሞ ነገር ብአዴን ስልጣን የማያጓጓው፤ የማያገባው፤ ግድ የማይሰጠው ከሆነ ስለምን ህንጻውን አያፈረሰውም? እራሱ የተደራጀበትን ዓላማ የተፃረረ መልስ ነው የተሰጠው። ህግ ማርቀቅ፤ ህግ ማውጣት፤ ህግ ለመወሰን፤ ህግ ለማጽደቅ ድምጽ ያስፈልጋል፤ የመወስን መብትያስፈልጋል። ዓውዱ ከሌሉ ፖለቲካ አሸንፎ የመውጣት ጥበብ እንጂ የዘገዬን የሚጠብቅ የታቱ ፍልስፋና ወይንም የቡና ተርቲም አይደለም።

አንድ ምሳሌ ላንሳ የአፍሪካ መሪዎች አንድ ልዩ ስብሰባ እደርገው ነበር፤ በነበረው አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤን አጋጣሚ ተጠቅመው ከጠ/ሚር አብይ አህመድ ጋር የተወሰኑት ልዩ ውይይት አድርገውም ነበር። እሳቸው ኢትዮጵያን ወክለው ስለሆነ በዛ ጥበብ ግርታ የለም። ውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ መዋቅሩ ስለሚጋብዛቸው ነበሩ ከኦዴፓ፤ የጠ/ሚር ጽ/ቤት ሃላፊ ነበሩ ከኦዴፓ በቃ። መረጃው ምን ያህል ለኦዴፓ እና ለአዴፓ እንደሚራራቅ ማሰብ ነው በማስተዋል ሆኖ። 

ለዛውም ኦዴፓ ሙሉ ለሙሉ የለማን መንፈስ ተከታይ ቢሆን ግድ አይሰጠነም ነበር። ለዚህ ነው እኔ ኦህዴድ ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን ህሊና አለው ስል የነበርኩት እና ብሄራዊ አገራዊ ተልዕኮን የመወጣት አቅም አለው ስል የነበረው ለዛውም በድፈርት ነበር፤ ነገር ግን ከመስከረም 5 ቀን ወዲህ ኦዴፓ ምን ያህሉ የለማ መንፈስ ፍቅረኛ እንደሆነ  ማመሳከሪያ ሰነድ አልሻም። አስተርጓሚም አልፈልግም። 

በሌላ በኩል የዛው የኦህዴድ ሊሂቃን በኢትዮጵያ አንድነት በሰባዕዊ መብት ረገጣ ላይ ያላቸው አቋም በተራችን እኛም ባዮች ስለመሆናቸው ዕድሜ ለፌስ ቡክ ሆድ ዕቃቸውን ዘረጋግፎ አሳይቶናል። ሰው አንድ ጊዜ ነው የሚታለለው ነፍስ ካለው፤ ሁለት ሦስት ጊዜ ግን ጅልነትም ብቻ ሳይሆን ግርድፍነትም ነው። ጣና ኬኛን እኮ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ደግመውት ነበር፤ አጀንዳችን አልነበረም። ልብ የሚሰጠው በግብታዊነት አይደለም።  

ጠ/ሚር አብይ አህመድ እና ዶር ለማ መገርሳን እንደ ልዩ ስጦታ አያያቸውም ራሱ ድርጅቱ ኦዴፓ። ቀድሞውንም እኛው ነን ትናንትም ስለነሱ የተጋነው ዛሬም እኛው ነን። የሚገርመው የተቃረኗቸው ናቸው ዛሬ ባለሟሎች እና የሚዲያ አባዋራዎች። በሌላ በኩል ደግሞ እዬቆሰቆሱ የሚያተራምሱላቸው ክልላቸውን ደግሞ እነሱው ናቸው። 

ለዶር ገዱ አንዳርጋቸው እምገልጽላቸው ነገን ማሰብ ዛሬ እንጂ ነገ አይደለም። ጸረ አማራ የሆኑ ፍልስፍናዎች ገነው በኖሩባት ኢትዮጵያ ከሥልጣን ብንገለልም ግድ አይሰጠንም፤ አጀንዳችን ይህ አይደለም፤ በፍጹም ሁኔታ ጅልነት ነው። ይህን ጥያቄ ማንሳትም እንደስንፍና ማዬትም ጅልነት ነው። በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ የወሉ የፖለቲካ ሊሂቃኑ ዕድምታ አማራ ጠል ነው። ከራሱ ጋር የተራቀ ለማግኘት ህልም ነው። 

አማራ የራሱን ዕድል በቸልታ አሳልፎ በመስጠት ጸረ አማራ ተልዕኮዎችን እንዲንሰራፉ አቅም እንዲያገኙ መፍቀድ ራስን ማጥፋት ነው። ጸረ አማራ የሽምቅ ውጌያውን መንፈሱን ራሱ ለመግራት በተፈለገው ቦታ ላይ ተገኝቶ የመወስንን አቅም ማጠናከር ሲቻል መሆኑ ለነገ የሚቀጠር ሊሆን አይገባም። በስተቀር ብአዴን የጉልት ገብያተኛ ሆኖ ያርፈዋል። ወይንም ወራጅ ወንዝ ... 

ብአዴን ብቻውን ተነጥሎ በአህዳዊ ነው የማምነው ካለ ራሱን ይቻል እና ከግንባሩ ይወጣ፤ የቋንቋውን እከተላለሁ ካለ ግን ይህን ዕድሉን የሰጠው የአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ነውና በተጋድሎው መስዋዕትነት ልክ መወሰን ከሚችልባቸው የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚየማህበራዊ አቅሞች ሁሉ የእኔ ብሎ ይትጋባቸው። ተጠማኝነቱን ቀልዱን ያቁም ብአዴን። ተረበኛ ድርጅት!

እነ አቶ መኮነን ገበዬሁ ታሪክ ጥረት ፈጠራ ብርታት ናሙናነት እንዲህ የውሃ ሽታ ሆነው የቀሩት፤ ያ ሁሉ ራዕያቸው ለሌላ ባለታሪክ የተሸለመው፤ አቅም ያለው ሊወስን የሚችል የአማራ ልጅ ጠፍቶ ነው። አማራ የትናንቱ ላይበቃ ዛሬም በባለቤት አልባነት ይቀጠል ነው ከፖለቲካ ሥልጣን ባሻገር ነገሮችን የማዬት ዕድምታው። መቼም እኔም እኩል ሥልጣን አለኝ አሁን ባለው የሥልጣን ድልድል ብሎ ብአዴን ተረት እና ምሳሌ እንደማያጽፍን እርግጠኛ ነኝ። ዛሬ ሥራዬ ብለን ሁሉንም ስለምንከታተለ። 

እንደ ብአዴን እድምታ አልበቃነም ሞት እና እንግልቱን፤ የዘር ምክነቱን፤ የሥነ - ልቦና ድቀቱን እና ሁሉን በቅንነት ማሰተናገዱን አሳታፊነቱን ለእኛ ይሁን የፖለቲካ ሥልጣኑ ግን እንዳሻው ይረባረብበት ማለት ቧልተኝነት ነው። ብአዴን ከቀደመው በጥበባት ህብረ ቀለማት አማራር ከተግባር ጋር ከተገናኘው የውጩ ሲኖዶስ የአማራር ቅልጥፍና እና አርቆ የማዬት ብልህነት በእጅጉ ሊማር እና ፊድል ሊቆጥር ይገባዋል።

ብጹዕና አባቶቻችን ስደት ላይ የሰሩት፤ የወሰኑት ዕጹብ ድንቅ የማስተዋል ብር አንባር ወርቅነት ነው ዛሬን ያሳመረው። ባዶ እጃቸውን አጨብጭበው ተቀምጠው ቢሆን ኖሮ ይህን ያህል ክብር እና ማዕረግ አይገኝም ነበር። ማዬት እርካታ ሳይሆን ማዬትን ለመጋራት መትጋት ነው ብልህነት። 
  
ለእኔያ ሠርተው ለማይደክሙት፤ ፈጥረው ለማይሰለቹት፤ በላባቸው፤ በጥረታቸው ልክ ዋጋቸውን ያላገኙት፤ ድካማቸው የሌላ ሲሳሳይ ለሆነው ምርጥ ጀግና የተግባር ጌታ ለአቶ ገበዬሁ መኮነን ነፍስ ይማርልኝ እያልኩኝ ቤተሰባቸውንም ያጽናናልኝ አማኑኤል እላለሁኝ። 

ጥቃቱ የሁላችንም ነው። ሀዘኑም የሁላችንም ነው። እሳቸው ልክ እንደ ቆሞስ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ፤ ልክ እንደቆሞስ ተስፋዬ ጌታቸው፤ ቆሞስም ናቸው። ውስጣቸው እንደ አረረ ከስሎ ነው የቀረው። እኔን!

ለጥቃቱ መስተካከል ካሳው ደግሞ ባህርዳር ዩንቨርስቲ ላይ ከወገብ በላይ የሆነ በሥማቸው ሐውልት ይቁምላቸው ባይ ነኝ እኔ። ሥጋቸው ያረፈበትም ቦታ እንደ ቅርስ እና ውርስ ይታይ ዘንድ በአግባቡም ይደራጅ ዘንድ የባህርዳር ከተማ አሰተዳደርን ባጋጣሚውም በትህትና ላሳስብ እሻለሁኝ። ባህርዳርን እኮ ደግመው ያበጇት የመጀመሪያው ቀንዲል ናቸው።

ልጆቻቸው ደግሞ ጀግናው በላይ ዘለቅ እንዳልሞተው ሁሉ የተግባር ዓራት ዓይናማው አቶ መኮነን ገበዬሁም ህይዋ ሆኖ ስለመቀጠሉ ማሰብ ይገባቸዋል። ይህን ቋሚ ቅርስ በማድረግ የአማራ ወጣቶች የቤት ሥራውን ሊወስዱት እንደሚጋባም በትህትና አሳስባለሁኝ። እሰከ አሁን የፈሰሰው የታሪክ ዝማሜ ይባቃል። የራስን ጌጥ የእኔ የማለት፤ የራስን ፈርጥ የእኔ የማለት ግድ ነው። በዚህ ዘርፍ አብሶ አብን እንደ አጀንዳ ይዞ ሊተጋበት የሚገባ አንድ ጉዳይ መሆን ይኖርበታል ብዬ አስባለሁኝ። የቤት ሥራው የሁሉም ነው።
 
እኔ ከሰው ጋር ስወያይ በቁም ነገር አጀንዳ ላይ ከሆነ ፍሬ ከሌለበት ገለባ ከሆነ ጊዜ አላጠፋም ልጅ እያለሁም፤ በገሃዱ ኑሩዬም እንዲሁ ነው። ሳላገባ የኖርኩበትም ፍሬ ነገር ይኸው ነው። ከአቶ መኮነን ገበዬሁ ሆኖ ከአቶ ስመኝ አለማዬሁ ጋር ያሳለፍኳቸው ወርቃም ጊዜያቶች ግን ት/ቤቶቼ ነበሩ። ቁም ነገሮች ናቸው።

እኔም በተለያዬ የታሪክ አጋጣሚ ይህን መሰል ዕድል ቸሩ መዳህኒተ ዓለም ስለሰጠኝ እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁኝ። በፖለቲካው እነ ጓድ ገብረመድህን በርጋን፤ ጓድ ዘርጋው አስፈራውን፤ ጓድ አበበ በዳዳን፤ አንባሳደር ወንደወሰን ሃይሉን፤ ኮ/አሰፋ ሞሲሳን ጓድ ስለሺ መንገሻን፤ እንዲሁም ነፍስ ይምርልኝ ጓድ ገዛህኝ ወርቄን፤ በሃይማኖቴ ቤተሰቦቼ ሊቀ ሊቃውንታንት እነ ጋሻዬ እነ አንባዬ፤ በኪነ ጥበብ ወላጅ አባቴ አበይ የጋዜጠኛ ሙያ አባቶቼ፤ በቢዝነሱም የአገር አንጡራ ሃብታትን ብልሆችን አጋጣሚ ሰጥቶኝ አቅጣጫዬ ባይሆንም ግን ጥልቀታቸውን ለማግኘት ችያለሁኝ። የሃገር ሃብታት ስለሆኑ። ተመስገን።  

እሺ የሲዊዝ አርበኞች እኔን በማሳደድ አርበኝነታችሁ የተረጋገጠላችሁ „ጀግኖች¡“ የተባላችሁ የአቅም አሳዳጆች የሥርጉተ የህይወት ቅመሞቿ ሁሉ የነጠሩበት ከነዚህ መሰል የህይወት ዓውዶችም ስለመሆኑ አሰገነዝባችሁአለሁኝ።

እያንዳንዱ ቀን ለእኔ የትምህርት፤ የዕውቀት፤ የልምድ፤ የተመክሮ ቤቴ ነበር። እንደ አልባሌ የታለፈ የፈሰሰ ነገር በእኔ ህይወት የለም። ጊዜው ሲፈቅድ ደግሞ እንዲህ እያዋዛሁ ምስክርነቱን በተደሞ ካስቀመጥኩበት ባንኬ መዘዝ አድርጌ አጋራለሁኝ ለቅኖች ብቻ። ወይንም ቅንነትን ለሚሹ፤ ወይንም ወደዛም መሄድ አትራፊ መሆኑን ላመኑት ብቻ። 
  
„እግዚአብሄርን ደጅ ጥና መንገዱንም ጠበቅ፤
ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤
ሃጢያተኞችም ሲጠፉ ታያለህ።“

የግፈኞች ፍርድ ሰጪው እዮር ነው።
የተገፊዎች የህይወት ጉዞ ግን የጽድቅ መንገድ ነው!
አይዞን ያ እንደላፈው ሁሉ ሁሉም ቀን አለው!

የኔዎቹ ኑሩልኝ።

ማለፊያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።