አቤቱታ ለዶር ገዱ አንዳርጋቸው ከቆሰለው ማህጸኔ!

ሲከር ይበጠሳል
ሲሞላም ይፈሳል!
“አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል?
በተቀደሰው ተራራህስ ማን ይኖራል?”
መዝሙረ ዳዊት ፲፬ ቁጥር ፩
ይድረስ ለዶር ገዱ አንዳርጋቸው
የአማራ ክልላዊ መስተዳደር ፕሬዚዳንት፤
ባህርዳር


·       ብታ።
ጤና ይስጥልኝ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው እንዴት ከረሙ? በቅድሚያ በእርስዎ የተመራው ልዑክ ከስሜን አሜሪካ ወደ ባዕት በሰላም ስለገባ ህሊናዬ አርፏል። እኔ የተፈጥሮ አየሩን እራሱ አላምነውምና። መንፈሴ በሰላም ወጥታችሁ ስለመመለሳችሁ ይሰብ እናንተ ደግሞ ስለ ተልዕኳችሁ ሆነ ስኬታችሁ ትጉ፤ እንዲህ ሥራ መከፋፈል … አቨው እና እመው በጸሎት ይርዷችሁ ... 
·       መነሻ።

የከተሞች መድረክ በወረታ ከተማ ክፍል ሁለት

የከተሞች መድረክ በወረታ ከተማ ክፍል ሶስት

የከተሞች መድረክ በወረታ ከተማ ክፍል ሶስት


·       ቆሰለ ትዝብት ከማህጸን ዕንባ።
ትናንት የአማራ የብዙሃን ሚዲያ የወረታ ከተማ ነዋሪዎችን አሰባስቦ ሲያነጋግር የነበረውን ዝግጅት አዳምጥኩኝ። እንዲህ የወለጋ የወ/ሮ ታደሉ መሰል ዕጣ ፈንታ እናቶች ወረታ ላይ እንደሚኖሩ ከገመትኩት በላይ ነው የሆነብኝ።
አማራ መሬት ላይ ለ50 ዓመት የሆነውን አውቃለሁኝ። አዲስ አይደለሁም። የወያኔ ሃርነት ትግራይ የማንፌስቶ አስኳል በአማራ መቃብር ላይ ስለምትመሰረተው ታላቋ ትግራይ ህልም ተፈፃሚነት የጦስ ዶሮ አማራ ነው አሁንም አላባራም ... 
አማራ ማለቅ ነበረበት በሁለመናው፤ በመንፈስም፤ በአካልም፤ በሥነ -ልቦናም። በሃይማኖት ዘርፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በጥርስ የተያዘ ነበር። በጥርስ መያዙ የምክንያቱም ሚስጢርም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖቱ  ከኢትዮጵያዊነት ጋር ባለው መስተፋቅር ነበር። ስለሆነም በሁሉም መስክ የጥቃት ሰለባ ነበር። ማናቸውም አቅሙ በመራቆት ልጆቹም ከፖለቲካዊ ተሳትፎ መመንጠር ነበረባቸው። የዚህን ውጤት ደግሞ ዛሬ እዬዬነው ነው …  
ግፉ ተቆልሎ ሲሞላ “ሲከር ይበጠሳል ሲሞላም ይፈሳል” ሆኖ ከአማራ የህልውና የማንነት ተጋድሎ ጋር የደረሰውን እስር፤ ጭፈጨፋ፤ እንግልት እና መከራ አሁን ገመናው ሁሉ አደባባይ ስለዋለ ሉላዊ ዓለም ሳይቀር ያውቀዋል። ሊከደንም ሊሸፈንም ከቶውንም አይችልም።  
እንዲህ አስፓልት ላይ በዬደራጃው ያሉ ኢ - ሞራላዊ ሰብዕናዎች  የልጅ ለቀማ በቀልሃ እንደ ቆቅ ሲያድኑ እንደ ነበረ ግን አላውቅም ነበር። የወሉን ጥቃት ነበር እኔ እማውቀው። ከቶ ይህ ደግሞ በወያኔ ሃርነት ትግራይ  ሊመኽኝ ይሆን? 



እንዲህ እናት በዬደጁ እንደ ዶሮ ደሙ የሚፈስ ልጇን እያዬች እንዴት መሽቶ ይነጋላት ይሆን? በቃ መንገድ ላይ የተገኘው ወጣት ሁሉ እንዲህ ነበርን በዬከተሞች አደባባይ ላይ ሲረሸን የነበረውን? አዬ ብአዴን? ? ? እንደምን ያለ ድርብ አንጀት ቢሆን ይሆን በሰላም በጉዞ ላይ ያሉ ወጣቶችን እዬተለቀሙ አስፓልት ላይ ገድሎ ሲፎከር የነበረው? ስለሆነው ሁሉ “ማፈር” ቃሉ አቅም የለውም። ይህን ያደረጉትን ነው ደግሞ ሥም አትጥሩ ተብሎ ሾላ በድፍን የሆነው?
ይጎፈንናል ሥም አትጥሩ መባሉ ራሱ። ማን ተፈርቶ ነው ይህ የሚሆነው? መረቡ ከላይ ከደረሰም ይድረስ? ሁሉም በወንጀሉ ከነከረ መጠዬቅ ካለበት ይጠዬቅ? ስለምን ይሆን ወንጀል የፈጸሙት ተደላድለው ፊት ለፊት ተቀምጠው ተበዳዮች ሥም አትጥሩ ተብሎ የሚታፈኑት? ነፃነት ስለምን ይቀማል? ሁሉ እንደልቡ እዬተናገረ አማራ መሬት ስለምን አሁን አፋነው ቀጠለ? ምን የሚሉት ጭቆና ይሆን ይሄኛው ደግሞ የአዲሱ ኤደፓ አዲስ ፓሊስ እንበለው ይሆን?!
ስለም የአማራ ወጣቶች ነፃነታቸው 
ተገፎ ተከድናችሁ ብሰሉ የሚባሉት? ስለምን? 

ኢትዮጵያን ነፃ ያወጣው ብአዴንን ጨምሮ እኮ የአማራ ህዝብ ልጆቹን በገፍ ገብሮ ነው፤ ማህጸን ከስሎ፤ ዘሩን አምክኖ፤ 20 ሺህ የአማራ ወጣት ካቴና በልቶት በድብደባ ብዛት በብር ሸለቆ በታሠሩ ቀንበጦቻችን ላይ ስንት ግፍ ተፈጽሟል። 
ሌት ሌት ስንት ወጣት ነው ሲቀበር የነበረው? 50 የባህርዳር ነዋሪዎች አደባባይ ላይ ተረሽነው፤ 26 የአንባጊዮርጊስ ወንድ ልጆች ከሱዳን በመጡ ወታደሮች ፋሽስታዊ ግፍ ተፈጽሞባቸው ተጨፍጭፈው፤ በደብረታቦር፤ በጎንደር ከተማ ስንት ወጣቶች ደመ ከልብ ሆነው፤ በግፍ እስረኞች ጥፍራቸው ተነቅሎ፤ የዘር ማፍሪያቸውን ገብረው የመጣ ለውጥ ነው።
ስለምን ይሆን አማራ ደሙን ከፍሎ ባመጣው ለውጥ የአማራ ወጣቶች ነፃነታቸው ተገፎ ተከድናችሁ ብሰሉ የሚባሉት? ስለምን? ስለምን አሁንም የበደሏቸውን ተጎንብሰው ደጅ እንዲጠኑ ይደረጋል? ዶር ለማ መገርሳ ምን እንደሚሠሩ በሚዲያ ወጣቶቹ ስለሚከታተሉ በይፋ ነው የተናገሩት። ይህ ፉክክር አይደለም፤ ግን የህዝብ ድምጽ ማድመጥ ተግባራዊነት ልኬታ ነው። ከራስ መጀመር ያስፈልጋል።


ቤትን ሳያጸዱ የሌላው የጀርባ አጥንት እሆናለሁ ቢባል “ራስ ገሊቦ ቂጥ ገሊቦ ይሆናል? ለነገሩ ብአዴን የት አዳርሶት፤ 7 ወራት ሙሉ እንግዳ ሲቀበል ሲሸልም እና ሲሸኝ ነው የባጀው። ልባሙ ኦዴፓ ደግሞ በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ፤ በተገኘው ድል ህዝቡን በለውጡ ተጠቃሚ ሲያደርግ ለዛውም ኦዴፓ ያለበትን መከራ ሁላችንም እናውቀዋለን።
ሁለት ነፍሶችን ኢትዮጰውያን ተቀበሏቸው፤ ወደዷቸው ብለው ጨርቃቸውን ጥለው ያባዱ የኦነጋውያን፤ የጃዋርውያን መከራዎችን ተሸከመው ነው እንደዛ እዬተጉ የሚገኙት። ስለምን ይሆን የአማራ ወጣት የ27 አልበቃ ብሎ ተጨማሪ ቀንበር ተሸካሚ እንዲሆን የተፈረደበት? ለምን? ለምን ነው እነዚህ ዲሪቶ ዝክንትል አመራሮች ከሥልጣናቸው የማይወርዱት?
የተከበሩ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው … ሆይ!
እኔ ጎንደር ከተማ ተወልጄ ነው ያደግኩት? ወላጆቼም እንዲሁም ጎንደር ከተማ ተወልደው ነው ያደጉት። እና እኔ ዛሬ በሙሉ ዕድሜዬ ፆታ ነክ ፊልሞችን ዓይኔ ደፍሮ ማዬት አልችልም።  ሥነ ባህሬው የጎንደር በባህል ዙሪያ ጥብቅ ነው።
ቀዮዋን በርም አውቃታለሁኝ ባታን፤ ታስሬ ነበር። የሆነ ሆኖ የወጣቶች ድፈረት የደረሰባቸውን ለመግለጽ የገፉበት ሁኔታ ምን ያህል ተስፋ ማጣታቸው፤ እንደምን ጥግ ማጣታቸው እንደሆን አስገንዝቦኛል። 
የግፉ መብዛት የወረታ ወጣት ሴቶች ያገቡም ያለገቡም የሚደርስባቸውን በደል ሲገልጹ ሰውነቴ ደረቀ። ከባድ ነው ለጎንደር ልጅ የፊልም ተዋናይ መሆን ሁሉ። ምክንያቱም አስተዳደጋችን የማይፈቅዳቸው፤ ማዕቀብ የጣለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉና። ተብዕትን ሞልቶ ለማዬት እራሱ ከባድ ነው። ፆታ ነክ ጉዳዮች የማንደፍረው ጉዳይ ነው። የአሁኑን ትውልድ ባለውቀውም ግን ወግ አጥባቂነቱን አሁንም ይተዋል አልልም።  
እስከዚህ ድረስ ለጎንደር ባህል እና ትውፊት ፈርሃ እግዚያብሄር ተደፍሮ እና ተጥሶ አንዲትን ባለትዳር፤ አንዲት ሥራ ፈላጊ ወጣት በአደባባይ በኩራት አካሏን ለግብር እንድታቀርብ ተገዳ የሆነውን ሁሉ መናገር ደፍራ መቸሏ እስከምን ይህ በደሉ ቢከራፋ፤ እስከምንስ ባህላችን ቢጣስ እና ቢደበደብ ይሆን? 
ለመሆኑ እንዴትስ ነው አዲስ ትውልድ የሚባለው በምን ሞራል ይሆን ሊገናባ፤ ሊቀረጽ ሊደራጅ የታሰበው? እንሰሳነት? አራዊትነት? ጭካኔ? ድፍረት? ይሉኝታ ማጣት? ከቶ የባህርዳር የፖለቲካ ሊቃናት ይህን ሰምታችሁ ተኝታችሁ አድራችሁ ይሆን? ሴት ልጅ የላችሁንም? እህትስ?

በፈቃዳቸው የወረታ ባለሥልጣን ተብዬዎች እስከ ጉታቸው በሙሉ ልቅምቅም ብለው መውረድ ይኖርባቸዋል። 27 ዓመት ሙሉ እንዲህ በእንዲህ ለማድምጥ በሚዘገንን መከራ ግዞት ላይ መኖር የምድር ገሃነም ሲኦል ነው። ወንዱ ታድኖ ይገደላል፤ ሴቷ ደግሞ ራሷን እንድትገበር ይፈረድባታል? አሁንም ይህ ይቀጥል ነው። 
 መቼ ነው እንዲህ በጭካኔ እና በፀያፍ ሰብዕና የበከተውን አመራራችሁ ለውጣችሁ ህዝቡን እፎይ እምታሰኙት? መቼ ነው እንዲህ በሥጋ ፈቃድ የተላውን የበታች አካላችሁን አሰናብታችሁ የጠራ መስመር ተከታይ ሁናችሁ ከብአዴንነት ወደ አዴፓ የምተቀዬሩት?
እኔ ይህን አድምጦ ቁሞ ለመሄድም አሳፋሪ ነው? የጎንደር ሴት ልጅ ይህን ቃሉን ራሱን አውጥታ ስትናገረው ምን በደሉ ቢጎፈንን፤ ቢሻግት ይሆን? አሁንስ ምን ዋስትና አላቸው እነዚህ ቀንበጥ ሴት ልጆች መከፋታቸውን አውጥተው ከተናገሩ በሆዋለስ? ብሶታቸውን የገለጹት በምን ሁኔታ ላይ ይገኙ ይሆን? ደህንነታቸውም እጅግ አሳስቦኛል። ሁሉንም ብሶታቸውን ሲናገሩ ነገ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ሁሉ አያውቁቱም፤ ምክንያቱም ከላይ እስከታች በጥቅም እና በጸያፍ ተግባር ብኩል ነውና። 
የበላይ አካሉ አቤቶ ብአዴን ንጽህናው ካለው፤ ድንግልናው ከኖረው ስለምን ይሆን ያልተደፈረው ይህን ከንቱ አማራር ከሥልጣን ለማውረድ እና እርምጃ ለመውሰድ ምን አገደው? በዚህ በ7 ወር ውስጥ አማራር አካሉን ለውጦ ህዝቡ የሚፈለገውን፤ የሚወደው፤ የሚፈቀደው መሪውን የማይመርጠው ስለምን ይሆን? የጥቅም መተሳሰር? የዝምድና ጉዳይ? ስለምን ነው ህዝብ እንዲህ በግፍ የሚርመጠመጠው? ግን አላችሁን ብአዴኖች?  
ከቶ የብአዴን ጽ/ቤት እንዲህ መሸታ ቤተኝነትን በዬቢሮው ይፈቅዳልን? ህጋችሁ ይህን ከንቱነት ይፈቅዳልን? የብአዴን ጽ/ቤት አፈ ጉባኤዋ ሴት ናቸው። አሁን ይህን የሚያንገሸግሽ ነገር እያዳመጡ ልቀጥል ይሉ ይሆን? 
አንዲት ሴት አንድ የሃላፊነት ቦታ ሲሰጣት የመጀመሪያው ኢላማዋ በሴቶችን ላይ በማናቸውም ሁኔታ የሚደርሰውን ጥቃት መከላከል ነበር፤ በተለያዩ ጌጣ ጌጦች አሸብርቆ አደባባይ ሰልፍ አሳምሮ ከመዋል በፊት። ያሳፍራል እራሱ መሃያውን መውሰድ። ያልሠሩበትን ማህያ መውሰድ ወንጀልም ሃጢያትም ነው።
ክብርት ወ/ሮ ሙፍርያት ካሚል በሦስቱም ጉባኤዎች በኦህዴድ/ በብአዴን / በህውሃት የወከሉት ሴት ሊሂቃንን ነበር። ሴቶች ዕድሉን ሲያገኙ የሴቶች ነገር ግድ ሊላቸው ይገባል። ፆታቸውም አብሮ ስለሚወከል።
ወረታ ተወልደው ያደጉ ሴት ወጣቶች ምን ያህሉ ሴት ወጣቶች ጥያቄውን አሟልተው ለእንጀራ እንደበቁ መዳህኒዓለም ነው የሚያውቀው 27 ዓመት ሙሉ። እጅግ ይሰቀጥጣል። አሻም አይሆንም ያሉት ደግሞ ምን ያህሉ መንገድ ላይ ወድቀው ባክነው ቀርተው ይሆን? 
27 ዓመት የትውልዱ ብክነት በመንፈስም፤ በአካልም፤ በሥነ - ልቦናም፤ በትውፊትም ነው። በሃይማኖታዊ ዶግማም አመንዝራነት ውግዘ አርዮስ ነውና። ጸያፍ ነገር ነው አመንዝራነት። በጣም መንፈሴ የሚጸዬፈው ይህን ዘርፍ ነው። ሰው እንደ እንሰሳ እራሱን ካልተቆጣጠረ መኖሪያው ዙ ነው መሆን ያለበት። ሲታሰብም ምነው  ከእናቴ ሆድ ውሃ ሆኜ ቀርቼ በነበር ያሰኛል። ለዚህ ይሆን ሊቁ “አልወለድምን” የጻፈው። ለዛውም ባዛን በደጉ ጊዜ።
·       ጥቂት ስለወረታ።
እጅግ የማከብራችሁ የአገሬ ልጆች … ወረታ ከአማራ ርዕሰ መዲና ከባህርዳር በቅርበት የሚገኝ ከተማ ነው። ደቡብ ጎንደርን እና ስሜን ጎንደርን የሚያገናኝ ነው። ከአዲስ አባባም፤ ከወሎም የሚነሱ አውቶቡሶች መናህሪያም መተላለፊያም መስቀልኛ ነው።  ህዝቡ ጤፍ እንጀራ በእርጎ ነው። ህዝቡ ለስለሳ እና ገር የሆነ ሲሆን ከደንቢያ ያለነሰ በከበት ርባታ የለማ አካባቢ ነው። የወተት አገር ነው። ለጥ ያለም ውሃ ገብ ሜዳማ ነው። አስተዳደሩ በደቡብ ጎንደር ሥር ነው። ለሊቦ ከምከምም ቀረብ ስለሚል መንፈሱ ሰፊ ነው። የወገራ እና የሊቦ መንፈስ እንደ ሐረር ልጆች ዓይነት ነው በባህሪም በአግባብም …  
ወደ ቀደመው ጉዳዬ ምልሰት ሳደረግ ወረታ የመጀመሪያው የሩዝ ተክል በደርግ ዘመን የተጀመረበት ናሙናዊ ቦታ ነበር። ኮ/መንግሥቱ ሃይለማርያም በቅርብ የሚከታተሉት በአካልም ተገኝተው የሚጎበኙት ቦታ ነበር።
ከዛ እጅግ ጠንካራ ልክ እንደ የትኑራን የመሰለ የገበሬዎች የአማራቾች ህብረት ሥራ ማህበር ነበር። ሊቀመንበሩ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሜቴ ይሁን ተለዋጭ አባል ነበር የመላ ገበሬዎች ማህበርም እንዲሁ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበር። የደልጊ እና የወረታ አካባቢ የገበሬዎች የአማራቾች የህብረት ሥራ ማህበራት ወደ ሥልጡን የእርሻ ተግባር ለማሳደግ ናሙናዎች ነበሩ ዘመን ያሉም ነበሩ በአስተሳሰብም። 
አንድ ጊዜ ከኮርያ ይሁን ከቻይና የመጡ የሩዝ ተክል አሰልጣኞች ነበሩ እና ኮ/ መንግስቱ ሃይለማርያም ገበሬዎችን ቋንቋው እንዴት ሆናችሁ ብለው ሲጠይቁ አሁንማ ሚስጢር ማውጋት ጀምረናል አሏቸው እና ከልባቸው አስፈነደቋቸው። የጣና ገብ ገበሬዎች በተለዬ ሁኔታም አንደበተ ርቱዑ ናቸው። ቅኔው መቼም ይገባችሁዋል ብዬ አስባለሁኝ የአገላለጹ ... 
በሌላ በኩል ሁለቱም የደልጊ አካባቢ የገበሬዎች አምራቾች ህብረት ስራማህበር እና የወረታው በተለያዬ አቅጣጫ ቢሆንም አኗኗራቸው የጣና ውሃ ተጋሪዎች ስለሆኑ ወረታ እና ደልጊ ጣናን ተከትለው ያሉ አርሶ አደሮች ስለሆኑ የጭንቅላታቸው ልቅና የተለዬ ነው። ብልህ ናቸው፤ ታታሪዎች ናቸው፤ ትጉሃን ናቸው። ምናባዊም ናቸው። ሚስጢሩ አሳ መደበኛ ምግባቸው ስለሆነ ነው።
አሁን ባህርዳር፤ ደልጊ፤ ጎርጎራ፤ ወረታ ተወልዶ የሚያድጉ የከተማ ልጆች እና ከሌላ ቦታ ተወልደው የሚያድጉት ጋር ብናነጻጻረው የተለዬ የምናብ ጥንካሬ ነው ያላቸው። ተፈጥሮን የማንበብ አቅም አላቸው ጣንን ተከትለው የሚኖሩ ገበሬዎች ይሁኑ የከተማ ልጆች።
ይህ እንዳይቀጥልም ነው የእንቦጭ ወረራም የተካሄደው። የአስተዳደሩም በደል እንዲሁ። ከበደልም ወጣት ሴቶች፤ ያገቡ ሴቶች ሰውነታቸውን ለንግድ ሥራ እንዲያቀርቡ መገደድ እንዲህ በአደባባይ እና በይፋ ማድመጥ ማህጸንን ይሰነጥቃል።
ስለሆነም ዶር ገዱ አንዳርጋቸው እና ካቢኒያቸው ይህንስ እንደሌላው ጉዳይ ነገ ይደርሳል ብለው ሸፋፍነውት ይቀመጡ ይሆን? መቼም እሳቸው ሁሉንም ነገር ለዘብ አድርገው ነው የሚያዩት። 
የበታች አመራራቸው ሃፍረትን፤ ውርዴትን፤ ገመናን ታቅፎ እስከምን ድረስ ሊያስኬደው ይችል ይሆን ብአዴን? ይሉኝታ ለአምንዝራ የበታች መሪዎቻቸው ከፈቀዱ መቺም ህገ እግዚአብሄርንም መጣስም ይሆናል።  
የጀግኒት ስብሰባም በብሄራዊ ደረጃ አዳምጫላለሁኝ። እነ ጀግኒት ይህን መከራ እንዲት ሊያስተናግዱት እንደሚችሉም እጠብቃለሁኝ? ፍልሚያው መጀመር አለበት ከዬትኛውም አካል ጋር። ይህ ሥሙ ብቻ የተመሰለው የሴቶች የህፃናት የወጣቶች ሚ/ር እሱ ያንጎላች እንደ ለመደበት፤ ሌሎች ሴት የፖለቲካ ሊሂቃን ግን ለዚህ ጉዳይ ብሄራዊ ንቅናቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል ከፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ጀምሮ። 
ዛሬ የኢትዮጵያ ሴት የአገር ፕሬዚዳንት በብሄራዊ ደራጃ አላት፤ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንትም ሴት ናቸው። ስለዚህ እንዚህ የጾታ ነክ ጥቃቶች ለመመከት አሁን  የኢትዮጵያ ሴቶች ሁነኛ አላቸው ብዬ አስባለሁኝ። ክልሎች ጋርም መጋፈጥ ይኖርባቸዋል። ጠ/ሚር አብይ አህመድም ለሴቶች ጉዳይ ቅርባችን ናቸው።   
ሌላው ተመስገን የሚያሰኘው ወግ ደርሶት አማራ አንዲት አንስት ሊሂቅ በስንት መከራ አግኝቷል ክብርት ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስን። ዶር ሂሩትን ወልደማርያምን ዘንግቼ ግን አይደለም፤ በአንድም በሌላም አውቃቸዋለሁኝ ክብርቷን። አብሶ ግብጽ ላይ በሴቶች ችግር ላይ አጽህኖት ሰጥተው ባደረጉት ንግግር ተመስጦዬ የላቀ ነበር። 
ለዚህ መበቃቱ መልካምነቱ እንዚህን መሰል የተተኪ ወጣቶችን ሥነ - ልቦና ጥቃት መመከት ሲቻል ብቻ ይሆናል። ለመከፋታቸው ቅርብ የመሆን። ተጎድተዋል ወጣቶች? ውስጣቸው በጥቃት ረመጥ መቃጠሉን መከስሉን ማዬት ያስፈልጋል።
ሴት ሆነው መፈጠራቸውን ሁሉ ይጠሉታል። ይህ ደግሞ ወደዬት ሊያመራ እንደሚችል በማስተዋል ሊመረመር ይገባል። ከልብ ሆኖ። ዛሬ ሉላዊው ዓለም ብዙ ፈተና ነው ያለበት። ዘመኑም ሉላዊ መሆኑን ማገናዘብ ይገባል። ተነጥሎ የሚኖር አንድም ሉላዊ ዜጋ እና አመክንዮ የለም እና …

የትናቱ ላይባቃ እነዛ የአሳር አምራች ጉቶዎችን፤ እነዛ ህዝብን በተለያዬ መንገድ ሲያስመርሩ የኖሩ ገመነኞችን፤ እነዛ የነውረኛ አመንዝራዎችን ሥም አትዘርዝሩ ታፍናችሁ ተቀመጡ መባሉ ብቻ ሳይሆን ቀንበሩ እንዳጎበጣችሁም ቀጥሉ መባሉ ህሊና አድራሻው የት ነው ያሰኛል? ይህ ለእኔ ፈርዖናዊነት ነው
… ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ከነገመናቸው ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል እነዚህ የትውፊት ቀባሪ ሲሰኞች። ትግሉ ከተፈጥሮ ጋር ነው። ሴት ሆናችሁ ለምን ተፈጣራችሁ ነው? ተፈጥሮን ለምግታት የሚታገልን ደግሞ ህግ ሊዳኘው ይገባል። ፍርዱን  በአደባባይ ከእነ ሃፍረቱ ማግኘት ይኖርበታል፤ ፍ/ቤቱ ከኖረ?!
ከላይ የተንጠለጠለው ተስፋ መሬት ካልያዘ ተስፋን ለማዝለቅ አይቻልም። ዕውነት ለመናገር መሬት የያዘ ተግባር ብአዴን አሁን በአፋጣኝ ካልጀመረ እንዲህ አዬር ላይ ባሉ ቅርጥምጣሚ ተስፋዎች መጪውን ምርጫ ማሸነፍ አይችልም።
መጪውን ምርጫ ብአዴን ካላሸነፈ ደግሞ የለማ መንፈስ ብቻውን ይሆናል፤  በኦሮምያ ያለውን ተስፋ እያዬን ነው። እራሳቸው አክብሩልን፤ አጨብጭቡላቸው ኢትዮጵያን በጥርስ ለያዙ የፖለቲካ ድርጅቶች አነጋውያኑን፤ አክቲቢስቶች፤ ሚዲያዎች ባህርዳር ሳይቀር ከፍ ዝቅ ይበልላቸው ብለው ላይ መንበር ላይ አውጥተው ዙፋን አቀዳጇቸው። ካለ አቅም እና ወርዳቸው ከፍታ ላይ አዋሏቸው፤ በእያንዳንዷ መድረክ ፈንጅ ተቀበረ አሁን ፈንጁ እዬፈነዳ ከቁጥጥር በላይ ሆነ። ያን እነሱ አንድ አድርገው የሰበሰቡት መንፈስን ፈቀደው ኦዴፓዎች ለኦነጋውያን አወረሷቸው። ጥንቃቄ አልነበረም። 
አሁን የውሻም ሞት ሆኖ ነው እንጂ የለማ መንፈስ ብዙው ነው የተበተነው ኦሮምያ ላይ፤ የአያያዝ ግድፈት ነበር … ለሁሉም በልኩ፤ በአቅሙ ልክ መሆን ነበረበት። መኖሩ የማይተዋቀው የተረሳው ሥም ሁሉ ዘውድ ተጫነለት፤ በተጫነለት ዘውድ ልክ አሁን መንግሥት ነኝ አለ … ስለሆነም በዚህ አቅም መጪው ምርጫ ለማሸነፍ ለራሱ ለኢህአዴግ ጋዳ ነው ኦሮምያ ላይ። ለኢትዮጵያም የሰፋ አደጋ አለበት። 
ቢያንስ አማራ መሬት ላይ ብአዴን አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ቧልቱን አቁሞ ነፍስ ያለው ተግባር መሬት ላይ መጀመር ይኖርበታል። ብአዴን ለኦነጋውያን የኢትዮጵያን መንፈስ አሳልፎ ከሰጠም መርግ ነው። 
የተግባር ትጥቅ እና ስንቅ አልባ በዚህ አያያዝ ብአዴን እራቃኑን ነው የሚቀረው …  ቀድሞ ነገር ሴት ልጆችን ለሲሰኛ ግብር እያቀረበስ አለሁ ማለት ያስችለዋልን የባህርዳሩ የአማራ መንግሥት?! ይህ ለይደር የሚቀጠርም አይደለም፤ አፋጣኝ መልስ ያስፈልገዋል። ልዝ የሆነ ውሳኔና አቋም ብአዴንን የትም አያደርሰውም ሲከር ይበጠሳል ሲሞላም ይፈሳል።
·       ግልባጭ
ለአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ለዶር ደስአለኝ ጫኔ፤
ባህርዳር
የሴቶች የፆታ ጥቃት በአስቸኳይ ይቁም!
የኔዎቹ ክብረቶቼ ውስጤ እንደ ጎመራ እዬነደደ ነው የጻፍኩት፤ 
እባካችሁ ፌስ ቡክ ያላችሁ ሸር አድርጉልኝ። አደራ!
 ስለመልካሙ የማይጠገበው ትሁት ትብብራችሁ ዝቅ ብዬ
 አመሰገንኩኝ። ኑሩልኝ!



ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
27.12.2018
ከገዳማዊቷ ሲዊዘርላንድ።
መሸቢያ ጊዜ።



አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።