ጦርነት ህግ የለውም፤ ጦርነት ርህርሄ ያልፈጠረለት የክስረት ክስተት ነው።
ጦርነት ህግአልቦሽ ነው!
„የማላዬውን ነገር አንተ አስተምረኝ፤“
መጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ ፴፬ ቁጥር ፴፪
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
20.01.2019
ከእመ ዝምታ ሲዊዘርላንድ።
„ግመል ሰርቆ አጎንብሶ የሚል የአቶ ዳውድ ኢብሳ“ መግለጫን አዳመጥኩት - ከልቤ ሆኜ። በኦዴፓ እና በኦነግ መሃል ያለው ጋብቻም ይሁን ፍቺ በውነቱ ይኼነው፤ ያኛው ነው ለማለት ይቸግራል። ለሰሚውም ለፈራጁም ግራ ነው።
ግራ የሆነበት መሰረታዊ ምክንያት ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን መሰከረም 5 እና ጦሱን፤ ቡራዩንና እና ሰቀቀኑን ስላዳመጥን ከባድ ነው ይህን ይኼነው ለማለት። ማን ምን እንደሆነ አሁንም መወሰንም መወገንም ይከብዳል። ሰርገኛ ጤፍ የሆነ ነገር ነው።
ማን የዬትኛው ድርጅት ደጋፊ እንደሆን በቅጡ አይታወቅም። የትኛው ኦዴፓ የትኛው ኦነጋውያን እንደሆነ አንጥሮ ማውጣት መቼውንም የሚቻል አይደለም።ለውጡ እና ተጠቃሚው የኦሮሞ ማህበረስብ ገና ልብ ለልብ አልተገናኙምና።
የሆነ ሆኖ ከሆነ፤ የሆነውን በሆነው ነገር በትክክል መንግሥት መግለጽ ይጠበቅበታል። አድሮ የሚገኝ ነገር። የፈለገ ይሆን የሆነውን እንቅጩን መናገር የተገባ ነው። አብሶ ለመንግሥት ታማኝነት ወሳኝ ስለሆነ። አድርገዋል የሚባለው ነገር አለ። መንግሥት ደግሞ አላደረኩም እያለ ነው። ቆይቶ ዕውነቱ ከተገኜ አብሶ መንግሥት አላደርኩም ባለው ላይ አድርጎ ከተገኜ ጥሩ አይሁንም። መታመንን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሊሂቃኑ ት/ቤት ገብተው መማር ያለባቸው ይመስለኛል። ስለምን? የወል ችግራቸው ስለሆነ። በመንፈስ አቅም ማፍራት እኮ ከመታደል በላይ ነው። መታመን ከጎደለ ደግሞ ያ ሃብት ይሸሻል። ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳልና።
በሌላ በኩል ደግሞ ያን ዜና ስንሰማ የአውሮፕላን ድብዳባ ተፈፀመ / አልተፈጸም በመንፈስ ክፉኛ የተጎዳን ሰዎችም አለን። ምክንያቱም መቼ እንደሚያበቃ ስለሚጨንቀን። ይህን ደግሞ ኦነጋውያኑ ይፈልጉታል። "ህዝብ ጨፈጨፈ የአብይ መንግሥት" መባልን ኦነጋውያን ብቻ ሳይሆን የአራት እግር ህልመኞች በሙሉ የሚሹት ጉዳይ ነው። በብዙ መስፈርት ሰዋዊነቱ ያመዘነው መንፈስ ጥንዝል ብሎ አቅሙ የትሜና መበተኑ የሚፈልግም ነው። ስጋቱን ለመግለጽ እኮ ቃላት አልተፈጠረም የዚህን የአዎንታዊ ዱብ እዳ ዘመን።
በሌላ በኩል ደግሞ „የኦነጉ ግመል ሰርቆ አጎንብሶ“ የሚለው ደግሞ ሲፈታተሽ ራሱን ኦነጋውያን ይመለከታል። በሁለገብ ትግል ድል እናገኛለን ብሎ ጉለሌ ላይ ተቀምጦ ጦር እያዘመተ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሰላም እታገላለሁ ብሎ ምርጫ ምንትሶ ቅብጥሮስ የማለት ነገር እሱም ሌላው „ግምል ሰርቆ አጎንብሶ“ መሆኑን ያሰተዋለው አይመስልም እራሱ የጉለሌው ሞገደኛው መንግሥት። "እንሱም እኛን እኛም እንሱን" እንዲሉ ...
በመጀመሪያ ነገር ጦርነት ሲታወጅ ወይንም የትጥቅ ትግል ምርጫው ያደረገ አንድ ድርጅት ለሰርግ ሽርሽር፤ ለጫጉላ ሽርሽር፤ ለመልስ ቅብጥ እና ቅልጥ፤ ለቅልቅል የጉርሻ መሽሞንሞኛ አይደለም ይህን የትግል ስልት የሚመረጠው፤ ገድሎ፤ አውድሞ፤ አፍራርሶ ጠላቴ የሚለውን በኢኮኖሚም አድቅቆ፤ በፖለቲካ ተቀባይነቱን አራቁቶ፤ በመንፈስ እርጋታም ህውከትን በመፍጠር ለማሸነፍ ነው።
ገድሎ ለማሸነፍ ደግሞ የጾታ፤ የዕድሜ፤ የዕውቀት፤ የሃይማኖት ልዮነት የለውም። ስለምን? ጦርነት ህግ የለውም እና። በጦርነት ውስጥ ደረሽ እና ድንገቴ አደጋዎች አይሰፈሩም፤ አይለኩም፤ ወይንም ደንበር እና ክትር አይሰራላቸውም። ጦርነት ርህርሄ ያልፈጠረለት የክስረት ክስተት ነው።
በሌላ በኩል „ነፃ መሬት“ ከኖረ በነፃው መሬት የሚካሄደው ጦርነት መደበኛ ነው የሚሆነው የፊት ለፊት ጠቅላይ አዛዦችም እነ አቶ ዳውድ ኢብሳ እዛው ከቦታቸው ሆነው ጦሩን መምራት እና መከራውን መቀበል ይኖርባቸዋል። ወይንም ኬንያ ወይንም ኡጋንዳ ላይ መሆን። ይህም ቢሆን ለመደበኛ ወይንም ለኮንቤንሽናል ጦርነት ኦነጋውያን አሁን ብቁ የሚያደርጋቸው የጦር መሰናዶ ያላቸው አይመስለኝም። ያው ቀንበጥ መማገድ ጌጥ አድርጎ ስለወሰደው ነው የአቶ ዳውድ ኢብሳ ነፍስ እንጂ።
ሌላው ሁለተኛ "የነፃ መሬቱን" ለማስፋት በሚደረገው ተጋድሎ ደግሞ በመደበኛ ሳይሆን በሽምቅ ውጊያ ነው የሚሆነው። ሽምቅ ውጊያ ደግሞ አጸፋውን ለመመለስ ለመንግሥት እጅግ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ለህዝቡም የፈተና ቁልል ነው። ሽምቅ ተዋጊው አፍርሶ፤ ዘርፎ፤ ንዶ ሲሄድ ለቀሪው ህዝብ ምን ሊገጥመው እንደሚችል ግድ አይሰጠውም ሽምቅ ተዋጊው ወይንም ጎሌራ ፋይተሩ። ይህ ማለት በሽምቅ ውጊያ ሃላፊነት የሚባል ነገር ፈጽሞ አይታሰብም። ተከሳሽ ለመሆንም እራሱ አይፈቅደውም።
በዚህ ማህል ህዝቡም እጅግ ነው የሚጎዳው፤ አማፅያኑ ሲመጣ እሚያንገላታው ያንኑ ህዝብ ነው፤ አማጽያኑ ሲሸሽ መሬት ላይ የሚገኘው ህዝብ ነው፤ መንግሥትም ሲሄድ አማጽያኑን የደገፉ - የረዱትን እዬነጠለ ሊቀጣ ይችላል። መንግሥት ህዝብን በሙሉ ተጠያቂ ማድረግ ባይችልም ሃላፊነት ስለሚሰማው ተጎጂ ዜጎች ግን የሉም ማለት አይቻልም።
መንግሥት ሃላፊነቱን ለመወጣት ደግሞ መለዬት ይኖርበታል ደጋፊውን እና የማይደግፈውን ህዝብ። ይህም በራሱ ኦሮምያ ላይ ሰርገኛ ጤፍ ነው። በራሱ ኦህዴድ ላይም ይህን አጣርቶ ለማወቅ ጋዳ ነው ፍዳ። ስለዚህ መንግሥት ይህን ለይቶ እርምጃ ለመወሰድም አቅበት ይሆንበታል። አብሶ መንግሥትን ህዝብ ካልደገፈ ሰላም ለሚፈልጉ ወገኖች ይከብዳቸዋል። ስለዚህ ህዝብ የሚጠቅመውን ለይቶ ወደ የሚጠቅመው መወገን ግድ ይለዋል።
በዚህ የዞግ መንፈስ ውስጥ ንፁሃን ለመለዬት ማንዘርዘሪያ የለም። የኦነጋውያን መሰረት ዘር ነው። ደም ነው። ደም እና ዘር የሆነ ነገር በሁሉም ልብ ያለውን ለይቶ የሚሳይ መሳሪያ ዓለም አልሰራችም። የሚጠቅመውን የሚያውቀው ህዝብ ስለሆነ ህዝብ የሚጠቅመውን መለዬት ግዴታ ይኖርበታል።
ይህም ተገዶ በመሳሪያ፤ በማስር ሳይሆን በግልጽነት ውይይት በማድረግ የሚሆን ነገር ነው። ኦነጋውያን እንዲፈንጥዙ ያደረገው ራሱ የኦህዴድ መንግሥት ነው። አሁን „አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው“ እንደሚሉት ጎንደሮች ነው የሆነው። የመስከረም 5 አንጠራርቶ አቀባበል፤ የቡራዩ መከራ፤ የአዲስ አባባ መከራ እና እርምጃው ሰፊ አስተዋፆ አለው ለኦነጋውያን ካለልክ መዘርጋት። የልብ ልብ የሰጣቸው ተመስጥሮ የተያዘው ወገናችን ናቸው፤ እንዳሻቸው ይሁኑ መባሉም ሌላው ፈታኙ እና ፈታዩ አመክንዮ ነው።
ይህን ማንም እንዲነሳበት ላይፈልግ ይችል ይሆናል። ግን እርሾው የመታበዩ ያ ነበር። የኦነግ መንግሥት እኮ በይፋ በአደባባይ ታውጇል። ይህ በህውሃት ዘመን በህልምም የማይታሰብ ነገር ነበር። ይህ እውነት ነው። አሁን ግን ቤተ መንግሥት ህውሃት ስሌለ ይፈልገዋል ህወሃት አዲሱን የለውጥ ሂደት ኦነግ እንዲንጥለት።
በቀደመው ጊዜ ግን ቢሆን ፈጽሞ አይታሰብም ነበር … በዚህ በአዲሱ የለውጥ ዘመን እርግጥ ነው የመገዳደል ፖለቲካ ይቁም ያሰማማል የለውጡ ፈለግ፤ አሁንም ግን እንደ ተለመደው አክተሮች አልተገዳደሉም፤ አክተሮች አልተቀጡም፤ አክተሮች አልተወቀሱም፤ ግን ለአክተሮች ግርማ ሞገስ ሲባል ትናትም ዛሬም የሚሞተው ንጹሃኑ ጠግቦ ያለደረው፤ ለቤት እና ለረባ ከፍን ያልበቃው ነው።
እኔ የሽሬን የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የመሰረት ድንጋይ ደልዳዋ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ሲያስቀምጡ ሳይ የሽሬ ህፃናትን፤ ታዳጊዎችን ስመለከት በጣም ነው ያዘንኩት። እኔ ብቻ አይደለሁም እህቴም እንደ እኔ ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቷት ኖሮ እጅግ የሚያሳዝን ነው ነበር ያለችኝ። ይህ ትውልድ ባልበላው ነገር ነው ዕዳ ክፍል እዬተባለ ነው ያለው … ትወልዱ የኢሊቱ ቀንበር ተሸካሚ ሆነ። ይህ ያርመጠምጣል።
ዕውን ኦነጋውያን በድንጋጤ የሁለት ወር እርጥብ ህፃን ሞት ካሳሰባቸው፤ ስለ ኦሮሞ ልጆች እናቶች ወጣቶች ታዳጊዎች ጽንሶች የሚታሰብ ከሆነ ስለምን የትጥቅ መፍታት እና አለመፍታት እንደ አንድ የፖለቲካ ስትራቴጅ እና ጫና መፍጠሪያ ሆኖ ይቀርባል? ለምን? ጀርመኖች መቼም የቃል ትርጉማቸው ድንቅ ነው። ትርፍ አንጀትን እውር አንጀት ይሉታል ብሊንድዳርም የአሁኑ የኦነጋውያን ጉዞ ዕውር አንጀት ነው የሆነው።
እውነት ለመናገር ኦነጋውያን በጣም ጨካኞች ናቸው። ደም ካላዩ፤ ህዝቡ ካልተሰቃዬ ነፃነት አይታያቸውምን? አንድ ሰው ለራሱ ወገን ቢያንስ እንዴት አያስብም? እንዴት 27 ዓመት ሙሉ በኦነጋዊነት ስንት መከራ አልፎ አሁን በማረፊያ ጊዜ እንዲህ ሌላ አራጅ ሲመጣበት ምን ግፍ ፈጽሞ ይሆን ይህ ህዝብ ያሰኛል? በለውጡ በይፋ በኦሮሞ ክልል በሚባለው እንኳን 40 ሺህ እስረኛች እንደተፈቱ ነው በዶር ለማ መገርሳ የአንድ ወቅት ገለጻ ያዳመጥኩት።
በዚህ ስሌት እያንዳንዱ ሰው በአማካኝ 5 የቅርብ ሰው ቢኖሮው 200 ሺህ ቤተሰብ ስንቅ በማቀበል፤ ምን ይሆንብኛል ብሎ በመስጋት፤ በናፍቆት ተንገላቶ፤ ከዛ መባዘን ተገላግሏል በለወጡ ትፍስህት ሲያገኝ፤ እንደገና ደግሞ ስልጠና፤ ውጊያ፤ ጉድብ ቁፋሮ መሰረታዊ አገልግሎት መቋረጥ ይህን እንደ ገና አመጣለሁ ብሎ መታገል በራሱ ጭካኔ ነው፤ አረመኔነት ነው። ለዛውም ምን ከመሰለ ሞዝቦልድ አልጋ እዬተቀማጠሉ፤ ትኩስ ከቀዝቃዛ እዬተመጉቡ፤ ምን በመሰለ በረንዳ ላይ እዬተንፈላሰሱ ከረባት እና ገበርዲን በዓይነት እያመረጡ? ?
መቼ ሃዘኑ፤ ስጋቱ፤ ሰቀቀኑ አልፎለት ነው እንደገና ጦርነት ለዛ መከረኛ ህዝብ የታወጀው? ለመሆኑ ህሊና አላቸው ኦነጋውያን? ለመሆኑ ህዝቡ በምን የሰላ የጋለ ፍም ሲንገረግብ እንደነበር ያውቁታልን? ለመሆኑ እንደ ሰው ያስባሉ ኦነጋውያን? ለመሆኑ ልጅ፤ እናት፤ ሚስት፤ እህት ወንድም አላቸውን ኦነጋውያን?
ከማሃል እስከ ደንበር 27 ዓመት ሙሉ ያ ህዝብ ሲንገላታ አንዲት ቀለሃ ያልተኮሰ፤ አንዲት የቀበሌ መንደር ያልነበረው፤ መድፍ እዬረገጡ ወጣቶች በራሳቸው ተጋድሎ ባመጡት ለውጥ ለወንበር፤ ለሥልጣን፤ ለዝና፤ ለሥም እና ለግል ኢጎ ተብሎ አሁንም እንደ ገና ሞት ማወጅ ከሰዋዊነት ውጭ ነው።
እኔ እንደምታዘበው የፖለቲካ አቅሙም የለም። ጭላጭ ነገር ነው እማዬው። ለማድመጥ ራሱ አቅም የለም። መሪ ሊያሰኝ የሚችል ክህሎቱ ድርቅ የመታው ነው እኔ እማስተውለው። መሪነት እኮ የተወለደውም ያልተወለደውም የእኔ ብሎ ማድመጥ ሲቻለው ነው።
ኦሁን የቀድሞው ፕሬዚዳን ባራክ ኦባማ ሉላዊው ዜጋ በሙሉ ነበር የተመሰጠባቸው። ያ ማለት የሉላዊ ዜጋ የመንፈስ ገዢ መሆናቸው የአካል ገዢ ሊሆን አያስችላቸውም። ማለት እያንዳንዱ አገር መሪ አለውና። እያንዳንዱ የዓለም ዜጋም አገር አለውና። እሳቸው ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆናው መመረጥ ዓለምን በማስደመም እረገድ መሪ ማለት ምን ማለት እንደሆን እንዲያ አሳይቷል። ሁሉም ደስታ እና ፍሰሃ ነበረው። ስለምን? አቅሙ ነው ቤተኛ ሁላችንም ያደረገው። አቶ ዳውድ ኢብሳን ሳስባቸው ትምክህታቸው እምኑ ላይ እንደሆነ ራሱ ይጨንቀኛል። ወጣትነቱ እንኳን የለም አይደለም እንዲህ ተፎካካሪ ሆኖ ለመውጣት …
የሆነ ሆኖ በእኛም አሁን የሚታዬው ባልተደለመደ ሁኔታ ነው የዓለም ሚዲያ፤ ጸሐፍት ተወደደ ተጠላም አይደለም ኢትዮጵያ አፍሪካ መሪ አገኘች እያሉን ነው። መሪነት እንዲህ ነው ነጥሮ የሚደምቀው እንጂ እኔ መሪ ነኝ ስላለ አንድ ምኞተኛ መሪ መሆን አይቻለውም። መሪነት የአቅም፤ የክህሎት፤ የብቃት፤ የተምክሮ፤ የሰብ ተፈጥሮ ልቅና፤ የሰብዕና አገናባብ፤ የተደማጭነት፤ የተቀባይነት ልዕልና፤ የጥበብ፤ የስልት እና የቅቡልነት፤ ወቅትን የማንበብ ጥሞና ጉዳይ ነው።
አገርን መመራትም ከሱቅ ተሂዶ የሚገዛ ሸቀጥ አይደለም። ወይንም በፕሮፖጋንዳ የሚታፈስ። ብዙ ድካም ይጠይቃል። የዛሬው የዲጀታል ዓለም ደግሞ የሚጠይቀው ተጨማሪም ብቃት አለ። ዓለምን የመረዳት ሚስጢር። በሁሉም መስክ ኢንተግሬት ለማድረግ ያለው የሁለንትናዊነት ሆነ የሁለመናነት ካንፓሲቲ ወዘተ …
እና ምኑን እና ምኑን አገናኝቶ አይደለም ለሉላዊው ዓለም ለእኛ ለኢትዮጵውያን "ኦነጋውያንን እንደ ምኞታቸው እንደ ጎረቤት አገር መሪዎች" እንያቸው ብንል እንኳን የጠብታ አቅም የለም። ፍዱስ ነው። ህዝቡም ያሳዝነኛል እኔ … እንዲህ በዬዘመኑ መታመሱ፤ ልጁን መገበሩ፤ ልማቱንም ማቃጠሉ፤ እድገቱ መጎተቱ … እንዲጠረጠር መሆኑስ? ራሱ ይህ ከባድ ነገር ነው ...
ይህን ለውጥ ከአማራ ወገኖቻቸው ጋር ሆነው አምጥተው የኦሮሞ ወጣቶች ድላቸውን ዘብ ሆነው መጠበቅ ሲገባቸው በቀቢሰ ተስፋ፤ በማይገኝ በማይታይ በማይጨበጥ የኩሬ ተስፋ እንደ ገና ወልደው ያላሳደጉትን ቀንበጥ ለጦርነት መመልመል ብቻም ሳይሆን ዘመናዊ ጦር ካለው መንግሥት ጋር አጋግሎ መመጋድ ዲያቢሎስንት ነው ለእኔ። ወቅቱም ሁኔታውንም ያላደመጠ፤ ዘመኑን ለመተርጎም የተሳናው ዝልብ ምህንድስና ነው … ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ።
ቀድሞ ነገር ጦርነት ሲታሰብ በድንጋጤ አይደለም በማናቸውም ሁኔታ ጦርነት መርጦ ህፃናትን ይለያል ተብሎ ታስቦ ነበርን? ምን ዓይነት አስተሳሰብ ነው? የታሰበው ልክ እንደ ሃውዜ አንዱ አቃጅ ሌላው ቪዲዮ አንሽ ሆኖ ይህን ሰብዕዊነትን ማዕከል አድርጎ የተነሳውን የለውጥ እንቅስቃሴ አስተጓጉሎ ኦሮምያን ደቡብ ሱዳን ማድርግ ነው።
በሽሬ በዛላ አንበሳም ታቅዶ የነበረውም ይኸው ነው። እንዴት ነፍስ ያለው ሰው ከዛሬ 30 ዓመት በፊት የነበረ የትግል መስመር ዛሬ ይሰራል፤ ዛሬ ያተርፋል ብሎ ያስባል? እንኳንስ ለእነሱ በዘመናዊ መልክ የተደራጀው የኢህአፓ የትግል ስትራቴጅ አይሆኑ ሆኖ በኖ ህዝብ አሳጭዶ ቀርቷል - መክኖ። ደርግ የወደቀበት እና ህወሃት ለ27 አመት የገዛበት ሁኔታ ሌላ መሰመር እና ሎጅክ አለበት።
ይህን የጢባ ጢቦሽ ጨዋታ በማስታመመ፤ በማቆላመጥ በጥዋቱ የጨከነ እርምጃ ለመውስድ ባለመድፈር ኦዴፓ እንደ ድርጅት ብቻ ሳይሆን እንደ አገር መሪ እንደ አውራ ፓርቲነትም ተጠያቂ ይሆንበታል።
በፈለገው መሥፈርት ከእንግዲህ ቀልሃ ሰው ገድሎ መፎከር አልነበረበትም። ቀልሃ ሰው ገድሎ እንዳያቅራራ ደግሞ በተለያዬ ሁኔታ ስንናገር መደመጥ ነበርብን። ከውጥኑ ብዙ ጽፌያለሁኝ እኔ እራሴ። ቁልጭ ያለውን የመጀመሪያ ንግግር ለማስታመም የፈለጉ ጸሐፍት ተንታኞች ቢኖሩም እኔ ግን እዬከበደ ሊሂድ እንደሚችል አስገንዝቢያለሁኝ።
እራሱ ጠ/ሚር አብይ ደንቢደሎ በተገኙ ጊዜ የነበረው አዬር አላማረኝም ብዬ ጽፌ ነበር። በአግባቡ ሊያዝ ይገባዋል ሁሉ ብዬ ጽፌ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ የሁለተኛ ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰው ኦፌኮኖች ነቀምት ሲገኙ እግራቸውን ተከትሎ ሊሰራ የሚገባው ድርጅታዊ ተግባር ነበር፤ አቶ ደዋድ ኢብሳን በመቀብል እና በማስተናገድ እረገድ ደጋግሜ እንደገለጽኩት ያን የመሰለ የፉክክር እና የምንግዴለሽነት ተግባር ከመከወን በቅጡ እና በአግባቡ መያዝ ይገባው ነበር። ስሜታዊነት እና ራዕይን ማስታረቅ ከባድ ነውና።
አሁን ላይ መንበር ላይ፤ ጉልላት ላይ ያወጣቱን ማወረድ ተቸገሩ። „ወትሮ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ወጭት ጥዶ ማልቀስ“ ሆነ። በተገባ ልክ ክብር ሲሆን ይገባል። አንድ ሚዲያ የማያውቀውን ሰው ላይ አውጥተህ እጬጌ ስታደርገው ህዝቡ የእኔ መሪ ይሄ ነው ማለቱ የተገባ ነበር። ለክብረ ባዕሉ ለመስከረም 5 ችሎ የተገኘው ሁሉ ይህን ቋጥሮ ነበር የሄደው። ያን ሰሞን የፌስ ቡክ ደንበኞች በርከትከት ብለው ነበር ጸሐፍትም እንዲሁ የልባቸውውን ዘረጋግፈው ውስጣቸውን አስቃኝተውናል።
ስለዚህ ኦህዴድ የዘራውን ነው በፈቀደው ልክ እዬሰበሰበ ያለው። በነገራችን ላይ ኦህዴድ /ኦዴፓ ባወጣው መግለጫም „ጠላቴ“ የሚለው ማን እንደሆነ ልብ ያለው ያውቀዋል። የፈለገ ጥፋት ቢፈጸም የኦነጋውያን ድርጅቶችን ጠላቴ ብሎ አይፈርጅም ከልብ መግለጫው ከተመረመረ። የግድ ጠላቴ ባይልም „ተቃዋሚዬ“ ማለት ነበረበት ግን አይልም።
አስቸጋሪው ገጠመኝ ህዝብ ተጎዳ። አይማርም፤ አይሰራም፤ አገልግሎት አያገኝም፤ ተስፋው በቤንዚን ተርከፍክፎ ተቃጥሎ በግራ ቀኝ በኩል እሳቱ ነዶ ከጭንቅላቱ ላይ አመድ ሆኗል። በመወቀስ ደረጃ ኦነጋውያንም አዴፓውያንም ተወቃሾች ናቸው። እዛው አዴፓውያን በቅንነትም በመቻልም የሆነው ነገር ሁሉ ቢኖርም፤ በሌላም በኩል በዛው በአዴፓውያን በአብይ ካቢኔ ደስተኛ ያልሆኑት ያለየላቸው፤ ይልነጠሩ፤ ያልተበጠሩ፤ ጉር ያላሉ ለስታ ስርክርክ ጉዳዮች ሁሉ አሉ።
አገር ለመመራት ከራስ መጀመር እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም አብነት መጀመር ያለበት በራስ ቤት መሆን ስላለበት። ጫናውን ካለልኩ የ8ቱን ክልል የተሸከመው እኮ ብአዴን ነው እንደ ለመደበት ልክ እንደ 27 ዓመቱ ዘመን።
በዚህ ሁኔታ ሆኖ ኦዴፓ ሰላም በሆነው ቀጠና ልማት አገልግሎት በተሟላ መልኩ ሲከውን ብአዴን ግን የፌድራሉን መንግሥት ጫና ከመቀበል ውጪ አንዲት ነፍስ ያለው ፕሮጀክት ተመረቀ፤ ተገኜ ሲባል አይደመጥም።
ሰላሙም እኩል ለእኩል ነው የራሱን ጉዳይ ቸል እያለ የሌላውን ጎፈሬ ሲያበጥር እጅግ የሚሰቀጥጡ ጉዳዮች ነው በምዕራብ ጎንደር እዬተሰማ ያለው። ከዩንቨርስቲ ለተገለሉ ወጣቶች፤ ተፈናቅለው በዬመንገዱ ላሉ ወገኖቹ እንኳ አንድ ፍሬ ያለው ነገር ማድረግም ማስደረግም አልተቻለም።
ሁሉንም መቀሌ ላይ ሆኖ በሪሞት ኮንትሮል የሚቆጣጠረው ህውሃት ደግሞ ቢያንስ ቀውስ በሚያበጅባቸው ቦታዎች ዜጎቹ አደጋ እንዳይደርሰባቸው ፈንጁን ሲልክ ቅደመ ሁኔታ በማደራጀት ነው። ይህ የተሻለ ብልህነት ነው። ቢያንስ ትግራይ ላይም ሆነ ከትግራይ ውጭ ህወሃት በሚሠራው ቀውስ የትግራይ ልጆች ዝንባቸውን እሽ አይባሉም።
ኦነጋውያን ደግሞ ራሳቸውን እያቀጠሉ ባቃጠሉት ነዲድ ያን እዬሞቁ የ4ኪሎ ወንበርን አጥብቀው በመመኘት የዓለምን ጆሮ ያስገኝልናል ባሉት ልክ እዬተንቀሳቀሱ ነው። በታሪክጥቅሙን የረገጠ ህዝብ ቢኖር የኦነጋውያን ተከታዮች ብቻ ናቸው።
የትም ቦታ በዬትም ሁኔታ የማዬው ይህን ማህበረሰብ የመካስ፤ የማስታመም፤ የመንከበካብ፤ ቦታ የመስጠት፤ ልዩ የሆነ አትኩሮት ለሊሂቃኑ የመስጠት ነገር እመለከታለሁ፤ ምን አልባት ኦነጋውያን ልብ ለማራራት ተብሎ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፤ ይህም ሆኖ አሁን እዛው ክልል ህዝብ ያልቃል፤ በስጋትም - በሞትም - በተስፋ ማጣትም። የዚህ ባለንበራሶች ደግሞ የኦነግ አምላኪዎች ናቸው።
እና ምን ይደንቃል የሁለት ወር ህፃን በድንጋጤ ቢሞት/ ብትሞት። የታቀደው ለዚህ አይደለም ወይ? ሰው ሳይሞት የሚገኝ የጦርነት ድል አለን? ኑሮ ያውቃልን? ሌላው መሳቂያው ነገር ከእኛ ለተሻሉት አቀባባል ድልቂ አድርጉ መባሉ አልበቃ ብሎ አዲስ አባባ ከተማ ላይ ጦርነት እዬተዋጀ "ነፃ መሬት አለኝ" እዬተባለ አሁንም የኢትዮጵያ መንግሥት አብሮ ስብሰባ ይቀመጣል።
ሆኖ አያውቅም፤ ተደርጎ አያውቅም። ግንቦት 7 አቅም ኖሮት የራሱ ነፃ መሬት ቢኖረው ይፈቀድለታል ወይ ቢባል ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። የዘበጠ ጉዞ ነው። ከኢትዮጵያ እገነጠላለሁ፤ የራሴን መንግሥት እመሰርታለሁ ላለ ቡድን ይህን ያህል የጫጉላ ሽርሽር ዝም ብሎ ለሚያው ሰው የትኛው ፕላኔት ላይ ተሁኖ ይሆን ይህ ኪኖ እንደሚፈጸም ለመለዬት ይቸግረዋል። ኢትዮጵያ ርዕሰ መዲና ላይ ሆነህ ኢትዮጵያን ዘንጥል? ማህከነ!
ኢትዮጵያዊያን በግዴታም በመብትም እኩል መሆን አለበት። ማንም ምንም ሃይል ከህግ በላይ ሊሆን አይገባውም። ከህግ በላይ የሆነ ማንም ምንም ሃይል በህግ ሥር ማድረግ የአንድ አገር ሉዑላዊነት ጉዳይ ነው።
አሁን እኮ ኢትዮጵያ ሉዕላዊነቷ ተጥሷል … "ነፃ መሬት እንዳትደርሱ፤ ከነፃ መሬት የመንግሥት ሃይል ከመጣ ተከላከሉ" እዬተባላ ነው እኮ። ያ ነፃ መሬት ደግሞ "የኦሮምያ ሀገረ መንግሥት ጽንሰት" ነው። "የኦሮምያ ሀገረ መንግሥት" የተሟላ ትጥቅ እና ስንቅ እስኪኖረው ድረስ የኢትዮጵያ መንግስት የአፍ ወለምታ ነው እያለ ህዝቡንም መንግሥቱንም ያለዝባል። ለሉዐላዊነት እኮ የቀልድም የተረብም ጊዜ ሊኖር አይገባም። ኢትዮጵያ የመሞከሪያ ጣቢያ አይደለችምና።
መንግሥት በፈለገው መልክ ተጠቅሞ ህዝቡን ነፃ በማውጣት፤ የተሟላ አገልግሎት ለህዝብ የመስጠት ግዴታ አለበት። ጋንቤላ ላይ ከህዝቡ ቁጥር በላይ ደቡብ ሱዳን አለ። ነገም ይኸው ይደገማል። ይህን ለዛዛ አቋም ያዬ ሌላውም መሰሉን መንገድ ይከተላል። „እናቴ በእንቁላሌ በቀጣሽኝ“ የሚያሰኘው እኮ ይህን መሰል ጉዳይ ሲገጥም ነው።
ሰላም ለፈለገ ሰላምን መስጠት ሰለምን ላልፈለገ ደግሞ ህግ ሰላምን እንዲያሰከብር መድረግ ግድ ይላል። ቀንን ቀን እዬወለደው ጮርቃው ነገር እዬበሰለ ሲሄድ ሉዑላዊነትን እንደሚገማምስ ልብ አልተባለም። "ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቁሞ ማውረድ ይቸግራል" ይሉታል ጎንደሮች ይህንን። እናም ቀልዱም ቧልቱም ይቁም! መጠዬቅ ካለበትም የኢትዮጵያ መንግሥት ህዝቡን ያድንና ይጠዬቅ። አቅም ከሌለው ደግሞ እርዳታ ይጠይቅ … ገና ኦነጋውያን ይከፋቸዋል ተብለው ህፃናት በስጋት፤ እናቶች በሰሰቀቅን መኖር አይኖርባቸውም።
ሌላው የሚገርመው ነገር "ነፃ መሬት" በተባለው ቦታ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈጸመ ስለሚባለው ጥቃት በገለልተኛ ወገን ይጣራ የሚባል ሌላም ተረብ አለ። ጦርነት አውጆ "ነፃ መሬቴ ነው" ላለ አንድ አምጽያን ስለፈጸመው ግድፈት ገለልተኛ ወገን እንዲያጠናው እንዲመረምረው በዬትኛው አገር ህግ እና ደንብ ይሆን ይህ ነገር የታዬው?
ባንኮች ተዘረፉ፤ ሰዎች ታገቱ፤ ታዳጊዎች ለስልጠና ተመለመሉ፤ ሥራ ቆመ፤ ት/ቤቶች ተዘጉ፤ እዬተደመጠ በዚህ ቀውስ ውስጥ ለሆነ ህዝብ መድረስ፤ ሰላሙ ለታወከ ህዝብ ጋሻ መከታ መሆን የተገባ መሆኑ እዬታወቀ በገለልተኛ ወገን እንዲጠና ማለት ምን እንደሆነ የሚገርም የጉድ ቁንጮ ነው። ተሳህሊነ!
በቅይጥ ጉዞ የአገር ሉዕላዊነት አይገነባም፤ ሉዑላዊነት ቆፍጠን ያል አመራርም አወሳሰንም ይጠይቃል። የአገር ሉዑላዊነት የሙሽርነት የማጫ ጉዳይ አይደለም። ህዝብ ከሚገባው በላይ ታማኝነትን በግፍ ሲቀልብ፤ ለዛ ታማኝነት ደግሞ የሚመጥነው የሃላፊነት ጉዳይ መፈጽም ግድ ይላል።
ሉዕላዊነት እኮ ከራስም በላይ ነው። ከነፍስም በላይ ነው። ሉዑላዊነት ከመኖርም በላይ ነው። ሉዕላዊነት ከታሪክም በላይ ነው። ሉዑላዊነት ከሃሳብም በላይ ነው። ለመሆኑ የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሚኒስተር ስለምን ይሆን የተደራጀው ለገበጣ ጨዋታ ነውን? ደህንነቱስ ቢሆን ቅልሞሽ ለመጫወት ነውን የተደራጀው? ለጎልፍ ጨዋታ ነበርን መላው የፌድራሉ የጸጥታው ሃይል አስከባሪ የተደራጀውን?
ያለው ነገር በአንድ አገር ልጅነት መንፈስ አይደለም? ሚስጢሩ ይህ ነው። በዚህ ሚስጢር ዙሪያ ፍርጥ ያለ እውነት አፋጧል። አገር ከሁሉም ነገር ይበልጣል ይልቃልም። ስለዚህ ትርትሩ አቋም በወጥነት ውሳኔ መልክ ሊይዝ ይገባዋል።
ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ በፊት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።
የኔዎቹ ክብረቶቼ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ