ገበሬው የህግ ባለሙያ አቶ ብዙአዬሁ ታዬና የአይዋ ዘመን ፍጥጫ።
እንኳን ደህና መጡልኝ።
ያፈዛልም
ያደነዝዛልም።
„አንተ ፈጣሪያችን ግን ቸር ነህ፣ ይቅር ባይ ነህ፤ የምትታገስ ነህ።
ካህሊነትህን እያወቅን ብንበድል ባንበድልም፤ ያንተ ወገኖች ነንና
በቸርነትህ ሁሉን ትሠራለህ። ነገር ግን የ አንተ ወገኖች እንደሆን እናውቃለን።
አንተን ማወቅ ፍጹም ክብር ናትና። አንተንም ማወቅ የነፍስ ህይወት ናትና።
መጽሐፈ ጥበብ ምዕራፍ ፲፭ ከ፩ እስከ ፫
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
ከእመዝምታ ከሲዊዘርላንድ።
ነፃነት!
https://www.satenaw.com/amharic/archives/62780
በመለስ ሞት ስቀሃል ተብሎ ከዳኝነት ስራው ተባሮ ወደ ግብርና የገባው ብዙአዩው
ምን አለ መኖሩን የተቀማ ሳይንቲስት ፈለስፋ ፕሮፌሰር ጸሐፊ ገበሬ? አውሮፕላን አብራሪ ገበሬ? ዛሬ ደግሞ ዜናው የሚነግረን የህግ ባለሙያ ገበሬ? ? ? ምን ላይ ይሆን የቆምነው? የምንቆመውስ? ህም! ስንት ጊዜ እናምጥ? አጥንት እርግዞ መኖር ግን እስከ መቼ?
ጤና ይስጥልኝ የኔዎቹ ደህና ናችሁ ወይ? እንደምን አላችሁ? ዛሬ ትናንት የተጀመረ ጹሑፍ ነበረኝ ወደዛ ላመራ አቅጄ ነበር። ነገር እንደ ተለመደው የነፃ ሚዲያ በር የሆነውን ሳተናውን ደህና ማደሩን ብቻ ለማረጋገጥ ስገባ አዲስ ዜና አገኘሁኝ። አዲስ ዜና ከኖረ እሱ ደህንአ ነው ማለት ነው። በ አጋጣሚ ያዝነኩበት ዜና ዛሬን ለዚህ ጉዳይ ማዋልን ወሰንኩኝ። „የአንዱን ሲሰሙት ያፈዛል የሌላው ያደነዝዛል“ እንደሚሉት ነው የሆነበኝ።
ከሰሞናቱ እኒያ የአገር እጬጌ የፍልስፍና ፈላስፋው፤ የአንትሮፖለሎጂስት ሳይንቲስቱ ፕ/ ምንዳርአለው ዘውዴ ጉዳይ ከልቤም፤ ከመንፈሴም ሊወጣ አልችል ብሏል። ውስጤ ቁስል ነው ያለው። 40 የዩንቨርስቲ መምህራን በአገራቸው መሬት ዜጋ አይደላችሁም ሲባሉ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ የተመረቀ ውጭ ጉዳይ ይሠራ የነበረ የልብ የሆነ ወዳጄ እንዴት አምርሮ እንዳዛነ አስተውሳለሁኝ። አሁን ሳስበው የኢትዮጵያ ፍዳ እንዴት ለመጨረሻ ጊዜ መጨረሻ እንዲኖረው ለማድረግ እንደሚቻል ራሱ ይጨንቀኛል።
አሁን መንገዱ ቢጀመርም የተጀመረውን መንገድ ራሱን በሚገባ ለተልዕኮው ለማብቃት መተቸትን ፈርተን፤ ይሉኝታን ተሸከምን እንደ አቤቱ ብአዴን በቸለልተኝነት እና በምንግዴለሽነት ሁሉን እምንመለከት ከሆነ መጪው ጊዜ በአስፈሪው ሁኔታ ይቀጥላል ማለት ነው።
ከልብ ሆነን በማስተዋል ሆነን ቀናውን እያደነቅን፤ ለቀናው በቂ ዕወቅና እዬሰጠን ጎባጣውን ደግሞ እንዲቃና ለማንም እና ለምንም ሳንሰስት እውነትን ብቻ ወግነን በመናገር መግራት፤ ማረቅ ካልተቻለ አሁንም ጥምዝምዝ፤ ጥምልምል፤ ጥምንም ያለ ዘመነ ለነገ አስረካቢዎች እንሆናለን ብዬ አስባለሁኝ።
ድንቅ ቅኔ!
ፕ/ የምንዳርአለው ዘውዴ እንዳሉትም „ሁለት እግር ያለው አሳማ“ ከመሆን አናልፍም። ነፃነትን ስለማክበርም እንዲህ ይሉናል የጥምር ዕውቅት ፈላስፋው „ሰው የባርነት ምቾትን ከመረጠ ለውሻ አሟሟት መፈረሙ የተረጋጋጠ ነገር ነው። በባርነት ደልቶት የኖረ ኑሮው የአሳማ ነው ሞቱ የውሻ ነው። በነፃነት ተንግላቶ የኖረ ህይወቱ ኑሮው የጀግና ነው። ሞቱ የሰምዕታት ነው።“
ይቅጣላሉ የሰብዕና አገናባብ ሳይንቲሰቱ … „በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ እግዚአብሄር የፈጠረለትን ግብ እንዲያስብ ነው። ማሰብህን በሆድህ ተክተክተህ ከዛ በኋላ ከአሳማ የምትለዬው በሁለት እግርህ መሄድህ ብቻ ከሆነ የምርም እንደዚህ አይነት ፍጡር እንዲህ አይነቱ ኑባሬ ሁሉን ነገሩን የሸጠ ነው። ነፃነቱን ጨምሮ።
አንድ ጊዜ ነፃነትን ለአንባገነኖች አሳልፈህ ከሰጠህ በኋላ ጊዜ ልጠቀም ብትል ከሱ ልትበደር ይገባሃል። እንዲህ ማለት ነው ነፃነትን ከአንባገነን እዬተበደሩ ከመኖር የባሰ በዚህ ምድር ላይ ትልቅ የምርም ትራጀዲ የለም። በህይወት ውስጥ ያለው የመጨረሻ ትራጄዲ የራሰን ነፃነት ከአንባገነን እዬተበደረክ መኖር ነው። ለምን ትበደራለህ? መጀመሪያውን አሳልፈህ ባትሰጥ ኖሮ። ለምን አሳልፈህ መጀመሪያ ትሰጠላህ? ነፃነትህን ለሆድህ አሳልፈህ ባትሰጥ ኖሮ። ለምን ለሆድህ ቅድሚያ ትስጣለህ? መጀመሪያውን የአሳማነትን ህይወት እና የውሻን አሟሟት ባትመርጥ ኖሮ።“
ይህ እንግዲህ ህሊና ያለው መንፈስ ሁሉ ልብ ብሎ ውስጡን ሊመረምርበት የሚጋባው ጉዳይ ነው። እንደ ድርጅት የቀድሞውም የአሁኑም ብአዴን የልቤ ብሎ እንደ ትናንቱ ነፃነት ተብድሮ ለመኖር ባይወስን አበክረን በአጽህኖት እንመክራለን። እኔስ እላለሁኝ… ፍትህም እኩል መሆኑን ማረጋገጥ የሚቻለው እውነትን ከወገን ብቻ ይሆናል።
ቀንዲል!
ያ ካልሆነ ማግስትን ማዳን የሚቻል አይመስለኝም። ሚዛን የጠበቀ ጉዞ እንዲያደርግ ለውጡ ከይሉኝታ መውጣት የግድ ይላል። አሁን ሁሉም አገር ገብቷል። ይህ አገር የመግባት ሁኔታን ዘላቂ ለማድረግ ሁልጊዜም ከእውነት ጎን መቆም ግድ ይላል፤ በስተቀር ጓዘ ቀላል ሆኖ ደግሞ ወደ ነበሩበት የስደት ጉዞ ምልሰት ማድረግም ሊኖር ይችላል አገር የገቡትን ማለቴ ነው።
በአንድ ላይ ከማትኮር ሁለገብ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማተኮር አስፈላጊ ይመስለኛል። ብዙ ነገር ተያያዥ ነው። ስለሆነም በማስተዋል ሁሉንም ነገር አቅርቦ የመመርመር፤ የማንዘርዘር፤ የማበጠር፤ የማንተርትር ተግባርን ባሊህ ልንለው ይገባል።
አሁን እኔ ፈላስፋው እና ሳይንቲስቱ የአገር ማገሩ ፕ/ ምንዳርአለው ዘውዴ የአዲስ አባባ ዩንቨርስቲ ዲን ቢሆኑ ምርጫዬ ነው። በሳቸው ውስጥ ያለው ዕውነት ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊነት የ እውነቱ ከሆነ ደግሞ እውነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት የነፃነት ፋይዳ ፈለስፋነት ማለት ነው። በአቶ በቀለ ገርባ ውስጥ ያለው ዕውነት ደግሞ ኦሮሞነት ብቻ ነው። አቶ በቀለ ገርባ ልጆቻቸውን በእኩል አይን የማዬት አቅም የላቸውም። አልተሰጣቸውምና። ይህን የህዝብ አባትነት ፈቅደው እና ወደው አሹልከውታል። በፈለገው ታምር እና በፈለገው ሁኔታ ቢመጡ በልብ ውስጥ ታማኝነትን ለማግኘት አይችሉም። ዘመነ ኦዴፓ ስለሆነ በዛ መሰላልነት የፈለገው ቦታ ላይ ይንጠልጠሉ አዬር ላይ የተንሳፈፈ መንፈስን ተሸክመው ነው የሚኖሩት።
ነገር ግን ሳይንቲስቱ እና ፈላስፋው ፕ/ ምንዳርአለው ዘውዴን ስንምለከታቸው ታማኝ ናቸው ለልጆቻቸው። የ ኢትዮጵያ ወላጆች ልጆቻቻውን ለዚህ ታማኝ ቢሰጡ የሰብዕና ጉብጠት፤ ወይንም ጫና ይመታል ብለው አይሰጉም። ፕ/ ምንዳርአለው ዘውዴ የሚያሳድጓቸውን የአደራ ልጆቻቸውን እውነትን አጥብተው ነው።
ስለዚህ እሳቸውን የመሰለ አገርን ማዕከል ያደረገ፤ በጉዳቱም ልክ ስንመዝነው ከመሠረቱ የተነሳ ስለሆነ በውስጥነት ላይ ውስጥነትን ለማበልጸግ መንገዳችን ቢሆን ብንጠቀም እንጂ እምንጎዳው አይኖርም። አሁንም እኔ ለአዲስ አባባ ዩንቨርስቲ ዲንነት ሪኮመንድ እማደርገው እሳቸውን ነው። ለተጎዶ ዛሬም በህይወት ለሉት እንደ ፕ/ እምሩ ስዩም መስል ሊሂቃን ካሳም ነው።
ዩንቨርስቲው እራሱ በሸተኛ ነው። ታሟል። ሐኪሙ ደግሞ ሳይንቲስቱ እና ፈላስፋው ፕ/ ምንዳርአለው ዘውዴ ናቸው። በእውነት ውስጥ የበቀለ ተቋምነት በእኒህ የጽናት ጽላት ውስጥ አለና። እርግጥ ነው ኦዴፓዎች ይህን ሰብዕና ይቀበሉታል አይቀበሉትም አላውቅም። ኦዴፓ እራሱ የራሱ ፈተና ስላለበት። የሆነ ሆኖ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እናትም አናትም ስለሆነ ይህን መሰል እርምጃ ቢወሰድን መዳንን ማዬት ይቻላል። ግራጫማ ተስፋውም ፈካ ይላል።
ወደዛሬ ተያያዥ ጉዳዬ ስመጣ ሳተናው ላይ ያገኘኋዋቸው የህግ ባለሙያም አቶ ብዙየሁ ታዬ ከክብርት ዳኛ ብርቱካን ሜዲቅሳ ከከፈለችው መስዋዕትንት ቢመጥን እንጂ የሚያንሰው አንዳችም ነገር የለውም።
በዚህ መልክ ስንት የአማራ ልጆች ወደ ግብርናው ተመለስው ይሆን ብዬ ሳስብ ቁጥሩን ለማውጣት አይቻለንም። የብአዴን የ27 ዓመት ዓመቱ ቁሞ ሞት ህይወት ይህን ይመስል ነበር። ችግሩ ዛሬስ ነው?
ዛሬም የፖለቲካ እውቅና የመውሰን አቅም ቦታውን እዬለቀቀ ስለመሆኑ በፋክት መሞገት ይቻላል። እውነቱ አለሁ ይላል ብአዴን በተመለከት። ፌድራል ላይ የምናዬው እና የምንታዘበው የሚነግረን ግን ብአዴን አይደለም በአካል በመንፈስም አለመኖሩ ነው። አማራ ነኝ ካለ ብአዴን ማለት ነው።
በቀደመው የቅልሞሽ ጨዋታ ወይንም ግርባነት ከሆነ ግን አሁንም አዲስ ስልጠና አያስፈልገውም። ዛሬ እማስተውላቸው ቁምነገሮች ትናንት ከመስተውላቸው ጋር እዬመረመርኳቸው ነው። ሥነ - ልቦናው አማራ የሆን ግን የዘር ሐረጉ ወጥ አማራ ያልሆነ ይህ ፍልስፍና የሄሮድስ መለስ ዜናዊ ፍልስፍና ነው። መቼ የዚህ ሰው መርዛም ዶክተሪን እንደሚቀብር ይናፍቀኛል።
እኔ እማስበው የትናንቱ የ27 ዓመት መከራ አሁንስ ስል መልስ አጣለታለሁኝ። እኔ እንደ ሥርጉተ ሥላሴ በምን ሁኔታ ተክድኖ ወይንም በስሎ እንደቀረ አለውቅም የጠ/ሚር አብይ ሲዊዝ መገኘት ሊቢያ ሄጄ አይሲስ የገደላቸውን ወገኖቼን አጽም አፍልሼ አመጣለሁ ያለ አንደበት ቸኩዬ መፍረድም መዳኘትም አልችልም „የቸኮለ አፍሶ ለቀመን“ መርሄ ስለማድርግ እንጂ …።
የዛ ብርቱ የሰብዕዊ መብት ተሟጋች የጀግና ረ/አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ ጉዳይ እንደ እናት ያሳስበኛል። ይጨንቀኛል። ይጠበኛል። ዕድሜው እዬተቃጠለ ነው። እንደ ገና 27 ዓመት ጠብቆ ልክ አሁን እንደምናያቸው እንደ ፕ/ ምንድርአለው ዘውዴ ስለ ጋብቻ፤ ስለልጅ ከመሼ ሊጠዬቅ ነው ወይ እላለሁኝ።
አትኩሮቱ ሳስቶ ነው የሚታዬኝና። እኔ በጥዋቱ ነበር ያመለከትኩት። ዛሬ የኦዴፓ ጽ/ቤት እስኪመስል ድረስ አዬር መንገድ የተርሚናል ምርቃት ላይ አውሮፓ የሰነበተው ልዑክ እንዳለ ተገኝቷል። ጠ/ሚር አብይ አህመድን ጨምሮ። ንግራቸው ጣልቃ ስላለመግባት አበክረው ገልጸዋል። ግን ጠረኑን ምን ምን ይል ነበር?
የሆነ ሆኖ እነዛ ከሙያቸው ተነጥለው የተሰደዱ፤ ወደ ግብርና የገቡ፤ የታሰሩ በሰው አገር እስር ቤት የሚገኙ የዚህ ድርጅት አባሎችን ጠ/ሚር አብይ አህመድ በዚህ ሥርዓት ሲገኙ አሰበዋቸው ይሆን ሁሉ ብያለሁኝ። የዛሬ ድል የእነሱም የታገድሎ ውጤት ነውና።
ሌላም ያዬሁት ሊሆን የማይጋባው ነገር አይቻለሁኝ።
ለውጡን በመታገል እረገድ ይሁን በሌላውም አቶ አባ ዱላ ገመዳ የራሳቸውን ተጋድሎ አድርገዋል። ኦህዴድን ማህል ቤት ጥለው የህውሃት አጅንዳ አስፈጻሚ ሆነው ነበር ብአዴን ባይደርስለት ኖሮ ኦህዴድ ጉድ ሆኖ ተበልቶም ተቃጥለው ነበር ሁለቱም ዶር ለማ መገርሳ ሆኑ ዶር አብይ አህመድ። ነገር ግን ተርሚናል ምረቃት ላይ ተገኝተው ተመልክቻለሁኝ። የሴራው ሶፍት ዌር እና ሃርድ ዌሩ ሳጅን በረከት ስምዖን ደግሞ በጭራቃዊ ሰብዕናቸው እስር ቤት ላይ ናቸው።
https://www.youtube.com/watch?v=18WKQYE-NSI
ፍትህን ማመጣጠን ያስፈልጋል። ቢያንስ ዞር የማድረግ። አሁን በዚህ ሰሞን አቶ አባ ዱላ ገመዳ ደረታቸውን ነፍተው እንደዛ መገኘት ነበረባቸውን? አንዱ ልጅ ሌላው እንጀራ ልጅ እንዲህ አይነት ተባደግነት ለአብዩ አሜኑ መንፈስ ቅርብ ከሆነ ሥርጉተ ትታመማለች። በፅኑ ነው የምታመመው። አብይን መንፈሱን የማስጠጋው ምክንያቱ የራሴ የሆነ ያጠናሁት አመክንዮ የቀደመ ስላለኝ ነው ከፖለቲካ እሳቤ ውጭ በፍቅራዊነት ፕሮጀክቴ። እና ያነ ዝበትን በፍጹም በዚህ ደረጃ ማዬት አልሻም።
ሚሊተሪ ላይም ፤ አዲስ አባባ ከንቲባ ጽ/ቤት ላይም፤ አዬር መንገድ ላይም፤ ኢንደስትሪ ፓርክም ላይም የስሜን አሜሪካ የህዝብ ለህዝብ ግንኙትን ላይም፤ የጀርመን ጉብኝት ላይም፤ ለአለሙ የኢኮኖሞ ፎረም የአንድ ድርጅትን ብቻ የወከሉ ሰዎች ብቻ ጎላ ብሎ ማዬት ለነገ ያጎብጣል። የማይታወቀው ነገር መጠላትን በራስ ጊዜ ማምረትም ስለመሆኑ ነው።
ኢትዮጵያ እኮ የህብረ ብሄር አገር መባሏ ለጫዋታ ማሟያ ለላንቲካ አይደለም። ይህን ስንስት ቀለማችን ይፋድሳል። እኛም እንወድቃለን። አይበቃም ወይ የ27 ዓመቱ ድቅድቅ የጨለማ ዘመን። ድቅድቅ ጨለማነት በሥጋ በልቶ በማደር አይደለም በመንፈስ ስደተኝነት ማለቴ ነው። መብላት መጠጣትማ ሲዊዝም መኖር እኮ በሙሉ ሁኔታ ይገኛል፤ ግን ሥርጉተ በሙሉ አቅሟ ተንቀሳቅሳለች ነፃነት ነበራት ሲባል ወና ነው።
ወደ ቀደመው ምልስት ሳደርግ የጠ/ሚሩ የ ኢኮኖሚ አማካሪ ተንሳፋፊው ሚ.ር ዶር አንባቸው መኮነን አልተገኙም ለዓለሙ የኢኮኖሞ ፎረም። የሰሜን አሜሪካው ጉዞም ብአዴን ውክል አካል አልነበረውም፤ በአውሮፓውም ህብረት ቆይታ ላይም እንዲሁ።
ዛሬም አዬር መንገድ እኔ እሰከሚገባኝ ድረስ የሰማዩ የትራንስፖርት ክፍለ አካል ነው። እና የትራንስፖርት ሚኒስተርን አይመለከትም ነበርን? ብቻ ያዬሁት የለም። አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንዳትሉኝ። እንዳሉም አልቆጥራቸውም እኔ። አቶ ንጉሡ ጥላሁን የራሳቸው ናቸው። ራሳቸውን እንደራሴ የሚሉም ያደረጉም። እንደ ሥማቸው ራሳቸውን ያጰጰሱ። ራሱ አሁን ላለው ለውጥም ዳገት እና ዳጥ ላይ እንደተቀመጠ ነው እኔ የሚገባኝ። የሸፈተ መንፈስ በፈለገው ቀመር ዘመድ አይሆንምና።
አብሮ ከአብይ መንፈስ ጋር መቆሙን እራሱን ወደውት - ፈቅደውት ደስ ብሏቸው አይደለም። የግድ ሆኖባቸው ነው። እንዲያውም በዚህ ሴሪሞኒ ላይ ከርፈፍ ወይንም ገርገብ ባለ መንፈስ ጭንቅ ላይም ነበሩ። ማንም የሥነ - ልቦና ሙሁር ማዬት ይችላል ይህን ሃቅ።
ባለፈው ጊዜ እንደጻፍኩት የራሳቸው ናቸው። ራሳቸውን አሁን ካሉበት ደረጃ ከፍ አድርገው ያስቀመጡ ስለሆነ እርካታው መቼውንም አይመጣም። በነገራችን ላይ የሳጅን በረከት ስምዖን የማንነት ቀውስም ይኸው ነበር። አንድ ቀን የቁንጮ ቦታ ቤተኝነት የአገር መሪ የመሆን ህልም ነበራቸው ‚ አሞራው በረረ ቅሉ ተሰበረ ሆነ እንጂ‘።
አሁን በዚህ ውስጥ እንደዚህ ግፍ ሲያንገረግባቸው የኖሩ የአማራ ልጆች ማን መንፈሳቸውን ያስጠጋው ነው ቁምነገሩ? ሙሁራንም እዮቸው አንዲትም ጠብታ አቅም ያላቸው የተፎካካሪ/ የተቃዋሚ/ የተቀናቃኝ ፓርቲ መሪ የሆነ የኦሮሞ ልጆች ሁለት ሦስት የቦርድ አባል ሆነዋል በፌድራል ደረጃ።
ሌሎችም ቁልፍ የመንግሥት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል - በፌድራል ደረጃ። ፈላስፋውን ዶር ዳኛቸው አሰፋን፤ የታሪክ ሳይንቲስቱን ረ/ፕ አባባው አያሌውን፤ የህግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላቱን ሚዲያ ላይ ታዮቸወላችሁ ቁልፍ የመንግሥት ሃላፊነት ግን ታምነው አልተሰጡም። የቦርድ አባል ሆኑ ሲባል አልሰማሁም።
ሚዲያ ላይም ለአለስልስ ነው። እኔ የሥላሴ ባሪያ የሚሰማኝን በግልጽ እና በቀጥታ ነው እምናገረው። አመስግኜ አወድሼ እንደምጽፈው ሁሉ ነገ ከምምጣቱ በፊት ታሞ ሳዬውም እውነቱን መናገር አይቀሬ ነው። ለዚህ ነው የተፈጠርኩት። ስንት ህይወት ነው ያለኝ። አንድ ብቻ ነው። በሌላ በኩል እምኖረው ኑሮም ትርፍ ህይወት ነው።
እንዲዚህ ገበሬ የሆነውን እንደ የህግ ባለሙያው ብዙአዬሁ ታዬ ዓይነት ጀግና ለእውነት ያደረ የህግ ባለሙያንም ስታስቡት ይጨልማችሁዋል። በዚህ የለውጥ አውደ ምህረት ዕውቅና ያገኙ ወይንም የተሰጣቸው የአማራ ጋዜጠኞች፤ አክቲቢስቶች፤ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፤ ተንታኞች ሞጋቾች አልሰማሁም። ስለምን? ዘመን ይመልሰው።
ከዚህ አንፃር የዚህን መከረኛ የህግ ባለሙያ ወጣት የአቶ የብዙአዬሁ ታዬን ጉዳይ ሳስበውም ነገ አቀበት ሆነብኝ። ባለቤት፤ ሁነኛ፤ ባሊህ ባይ የለውምና። የሳይንቲስት ፕ/ ምንዳርአለው ዘውዴ ስጋት የለብኝም። በሩ ተከፍቷል። የሌሎች የአማራ ምንዱብ ሊሂቃን ጉዳይ ግን እንደተዳፈነ ነው ያለው። ተቆርቋሪም አላገኘም። ወደ መደበኛ ሥራቸው የተመለሱትን የፈላስፋውን የዶር ዳኛው አሰፋን መልካም ዜና እንደ ተጠበቀ ሆኖ።
ይህ ሁሉ መከራ ተሸክሞ ነው አማራ ስለምን ብሄርተኛ ሆንክ ተብሎ በግራ በቀኝ እዬተዋከበ ያለው። መደራጀት ነው አሁኑ ብርቁ ጉዳይ፤ በቅጡ ካልተያዘ ከዚህ የዘለለም ነገር ሊመጣ ይችላል።
ሰው የማያውቀው አንድ ትልቅ ነገር አለ። ረቂቅ ስለሆነ። ጋዜጠኛ በፈቃዱ ሃይሉ በአንድ ወቅት ከብራና ራዲዮ ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ „የአማራ ተጋድሎ መንፈሱ ሙቷል“ ብሎ ነበር። እኔ በወቅቱ መልስ ሰጥቼው ነበር። በህሊናችን ውስጥ ያለውን ረመጥ እኔው ስለማውቀው።
አሁን የአማራ ልጅ በማንኛውም ሁኔታ ከቤተሰቡ ጋር ሲወያይ አጀንዳው አማራነት መሆኑን ማንም አያውቀውም። ትልቅ የተዳፈነ ሞገድ ነው ያለው። ከፈነዳ ደግሞ ያጥለቀልቃል። ስውርም ነው። የትኞቹ አማራዎች እዬተገለሉ እንዳሉም ጥናቱን የሚሰሩ ትንታጎች አሉ ብዬ አስባለሁኝ።
ሌላው መዳኛው መንገድ ለአማራነት ብቻ ሳይሆን ሚዛን ለማስጠበቅም አማራ በራሱ ውስጥ የመደራጀት ክህሎትም አንድም ቀን ሊዘናጋበት ወይንም ለሽንገላ ፖለቲካ እጁን መስጠት እንደሌለበት ነው እኔ አበክሬ መግለጽ የምሻው፤ የአብይ ጠ/ሚር ሆነ የኦዴፓ ለዚህ ድል መብቃት በአማራ ትክሻ ነው። አንድ ትንተና ላይ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሞ ልጅ „የሃይማኖት አባቶችም ማስታረቅ ቻለ“ ሲሉ አዳምጫለሁኝ። „በማን ላይ ቁመሽ እግዚአብሄርን ታሚያለሽ“ እንዲሉ ነው። እርሻው ማን ሆኖ?
ማነው ለዛ ያበቃው ኦህዴድን ብለው መጠዬቅ ይኖርባቸዋል ያን ቃል ከማውጣታቸው በፊት። መሠረቱ ማነው? ህወሃትን ለዛ ያበቃው እኮ አማራ ስለተሸከመው እንጂ ተቋርጦ ነበር የሚቀረው። ኦህዴድም በራሱ አቅም ብቻ አይደለም ከዚህ የደረሰው። ፕ/ መራራ ጉዲናም ከ አሌ ቲቢ ጋር ሰሞኑን በነበራቸው ቆይታ ለማንም፤ አብይንም፤ እኛንም ያስፈታን የኦሮሞ ተጋድሎ ነው ሲሉ አዳምጫለሁኝ።
ሁሉንም ነፃ ያወጣው „የኦሮሞ ደም ደሜ ነው“ ሃቁ ይሄ ነው። እሳቸውን አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ። ብአዴን ደግሞ ለሁለመናው የጀርባ አጥንት ሆኖ ነው። ክብሩም፤ ግርማውም፤ ዕውቅናውም የት ላይ እንደሚቆለል ደግሞ እያዬን ነው። የዶር አብይ አህመድን ሪኮምንዴሽን ይሁንታ እምንሰጠው እኮ ሌላ ምንም ሳይሆን ንጥረ ነገራችን አገር ስለሆነ ብቻ ነው። እንሱ አያደርጉትም። አላደረጉትም! ስለ አንድ አማራ ሊሂቅ ሲመሰክሩ ተደምጠው አያውቁም።
በሌላ በኩል ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚዲቃስን ስንደግፍ የኖርነው አገራዊነት ምስላችን ሳይሆን ደማችን ስለሆነ ነው፤ ፕ/ መራራ ጉዲናን ስንደግፍ የኖርነው ኢትዮጵያዊነት በፍሬም የሚቀመጥ ልስን ሳይሆን ደማችን የሚመራው ስለሆነ ነው፤ ኮ/ ጎሹ ወልዴን ታቦታችን ያደረግነውም ይሄው የማንደራደርበት የኢትዮጵያዊነት ብቁ መክሊታችን ነው፤ ወ/ሮ ማእዛ አሸናፊን ተስፋ ያደረግነው ማህተማችን የሆነው የአውራው የድንቅነሽ ማንነት ፍቅር ነው።
አማራ ተወደደም ተጠላም በሥነ - መንግሥት ፍልስፍና ሥነ - ልቦናው ተቃኝቶ ያደገ ስለሆነ አቅም - ክህሎት - ብቃት ታማኝነት ለአገር መዋለ መንፈሱን ማዋሉ መሆኑ ቢያስደስተው እንጂ የሚቀናቀነው አይደለም። በሥነ - መንግሥት ፍልስፍና ማደጋችን አገር እና ህዝብ የሚለውን ቁምነገር ጠጥተን ተመግበን እንድንኖር አድርጎናል።
እስቲ ማነው „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነውን“ የደገፈው ኦነጋውያን? ጀዋርውያን? ህዝቃኤላውያን? ግንቦት 7ውያን? በቀለውያን? ህወሃታውያን? ማን? ይነገረን። ማነው ለሬቻ ጭፍጫፋ ከውስጡ ሆኖ ለዐለም መንግሥት አቤት ያለው? ስንት ያልተለመዱ ነገሮችን እኔ ከውኜበታለሁኝ የአማራ ተጋድሎና በኦሮሞ ንቅናቄ አድማጭ እንዲያገኙ? ስለምን ወገንተኝነት ተለጥፎብን ሳይሆን መሆንን በመሆን በደማችን ውስጥ ያተምን ስለሆነ ነው።
እኔ ለዶር ለማ መገርሳ እና ለዶር አብይ አህመድ በትህትና ላሳስባቸው እምሻው አንገት እንዲኖራቸው ነው። እኔ ለተጎዱ የ ኦሮሞ ወገኖቼ የፈጸምኩትን ያህል የራሳቸው ሰዎች ውጭ ያሉት አልከወነወኑትም። ከልብ ማዘን ማህጸንን፤ አንጀትን መስጨነቅ ምን እንደሚያመጣ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው። በርካታ ረቂቅ ተግባራትን ከውኜለሁኝ። ስለሆነም ደፍሬም መጻፍ፤ ደፍሬም መወቅስ የተገባ ይሆናል። ከፈሰሰ ለማፈስ ከመጣር ሳይፈስ ማስገንዘብ ይገባልን። ጆሮ በትልቁ ከተገዛ …
በሌላ በኩል ሁሉም በደቦ ሲያዋክባቸው በነበረው ሰዓት ሳተናው የፈጸመውን ያህል የራሳቸው ሚዲያ አለውከወነም። ዛሬ ላይ መንበር ላይ ያንጠለጠሏቸው ተቋማት እና ግለሰቦች አልከወኑትም። ያ ተጋድሎ ግን የህወሃትን የፖለቲካ ሊሂቃን ገፋ ተደርገው የኦነጋውያን መንፈስን ለማስኮፈስ አይደለም። አልነበረም። አሁን የሚቀጥለው ሁለገብ የሥነ - ልቡና ወራራ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በዬሚዲያው ዶር ብርሃነመስቀል አበበ የሚነግሩን ይህንኑ ነውና።
ህወሃት የተጠላበትን ጉዳይ ስለምን ብሎ ራስን መግራት፤ ራስን ማረቅ ያስፍልጋል። ንጽህና ቅድስና ድንግልና ከማንም አልጠብቅም። ከሁለት ሰው ግን አብዝቼ እጠብቃለሁኝ። ከዶር ለማ መገርሳ እና ከዶር አብይ አህመድ።
ለአማራ ታማኝ የመሆን አቅምን አምጠው መውለድ ያለባቸው ይመስለኛል። እያቃታቸውም፤ እያቃተታቸውም እንዳለም ነው እኔ እማዬው፤ እምትዛበው።
እኔ ከዚህች ደቂቃ በኋዋላ ምን ልሆን እንደምችል አላውቀውም። ሰከንዶች የፈጣሪየ ነውና። ነገር ግን መግለጽ እምፈልገው ዋነኛው ነገር ታማኝነትን በሰጠናቸው ልክ ሳይሆን ከዛም በላይ እንዲያሳዩን እጠብቃለሁኝ። ቢያደርጉትም ባያደርጉትም ተጠቃሚዎች እነሱው እራሳቸው ብቻ ይሆናሉ።
ምክንያቱም „ከማያድሩበት ቤት አያመሻሹበት ነውና“ አማራን የሚፈልጉት ለድልድይነት ብቻ መሆን አይገባውም። ያ ከሆነ ዛሬ ላይፍርስ ይችላል ቀስ እያለ ግን ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል። ይህ አካሄድ ለህወሃትም ለግንቦት 7 አልጠቀመም። ለኦዴፓም አይጠቅምም … ይህን በእርግጠኝነት እና በልበሙሉነት ነው እምናገረው። „አንገት የተሰራው አዙሮ“ ለማዬት ነው … እንዲሉ
ሰንበትን ...
https://www.youtube.com/watch?v=76IFoT-5yrg&t=591s
አፈሬ ነው መስመሬ።
„አንተን ማወቅ ፍጹም ክብር ናውና“
የኔዎቹ ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ