የአገር ፎለቄ ፈርጥ እንደ አልባሌ?
የአገር ፎለቄ ፈርጥ
እንደ አልባሌ?
„ወገኔ ሆይ አድምጠኝ፤ ሕዝቤ ሆይ፣ ስማኝ
ህግ ከእኔ ይወጣልና ፍርዴም ለአህዛብ
ብርሃን ይሆናልና።“
ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ ፶፩ ቁጥር ፪
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
07.01.2018
ከእመ ዝምታ
· እፍታ ለአንድ አፍታ!
ውዶቼ እንዴት ናችሁ ደህና ናችሁ ወይ? ዛሬ ቀጠሮዬ ሳልባክን የጠ/ሚር አብይ አህመድን ከመምህራን ጋር ያደረጉትን ውይይት በጥሞና ላደምጥው ስለፈለግኩኝ ሦስቱንም ክፍል በበዛ ጥሞና ታደምኩበት።
ያው ለእኔ እንደ ትምህርት ክ/ ጊዜ ስለማዬው ማስተዋሻ እያያዝኩኝ ነበር ያደማጥኩት። የሚገርመው የፕሬስ ሰክሬታርያት ጽፈ/ቤት ሃላፊዎችም፤ የጠ/ ሚር/ ቢሮ የጽህፈት ቤት ሃላፊ ማስተዋሻ እንኳን አልያዙም ነበር። ታዳሚዎች ግን ሲይዙ አይቻለሁኝ። ይህም አንድ የሾለክንበት ጉዳይ ነው። ትውልዱ ከእኛ ምን ይማር? በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ትውልዱን እያሰቡ ቢሆን መልካም ነው። ልጆች ከሚሰሙት ይልቅ በሚያዩት ይመሰጣሉና።
የሆነ ሆኖ በዚህ ጠ/ሚር አብይ ባደረጉት ንግግር ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት መልስ በጥልቅነት ውስጥ የመታደላችን ልኩንም በልበ - ህሊና ለመለካት ሞከርኩኝ። አስተውሉ የኔዎቹ ሞከርኩ ነው ያልኩት። ስለምን? ይህን አልኩኝ መሰላችሀ ... የሳቸውን የተመስጦ ይዘት ለመተርጎም የዕድምታ ሊቃውንትን ስለሚጣራ። ከዕድምታ ሊቃውንትነት ጋር ይተካከላሉ ብዬ እማስባቸው ፕ/ ዶር ፍቅሬ ቶሎሳ ስለሆኑ የቤት ሥራውን ለሳቸው ልተዎው። ግን ስንቱን ይዘልቁታል?
ንግግሩን እያዳመጥኩኝ በቀደም ዕለት ሙሉ ቀን ያሸኝን የሻ/ ዳዊት የእናፍርስ ብሄራዊ ጥሪን ስለምን ደከምኩበት አልኩኝ። ምክንያቱም ሦስተኛው ክፍል ላይ ጠ/ሚር አብይ አህመድ አሳምረው መልስ ስለሰጡበት።
ስለዚህም መድከሜ አስፈላጊ አልነበረም። ይህን ሦስት ክፍል ቀድሜ አዳምጬው ብሆን እንደ ማውጫ ልጠቀምበት ብችልም እንጂ፤ ራሱን በቻለ ሁኔታ ግን አልጽፈውም ነበር። በማያዳግም ሁኔታ በማያስልስ ሁኔታ በቂ መልስ በብጡል ብቃት ተስጦበታል።
ያ ማለት ቪዥን ኢትዮጵያ ድረስ ተጓጉዞ ያሰናዳው የጉባኤ ዕድምታ ሚስጢር የሽግግር መንግሥት ጥማቱንና የለውጡን መንፈስ የአፍርሱልን ወታደራዊ ማንፌሰቶ አትኩሮት የት ላይ ስለመሆኑ ልቡን ስላገኘሁት። የዚህን የሽግግር መንግሥት እና ተጨማሪ የዕወጃ ዕድምታ አትኩሮት የነሳውም የታዳሚው ግብረ ምላሽ ነበር። ራሱ ጭብጭባው ድንቅ ነበር። ከጫፍ እስከጫፍ ነው ጭብጨባው በሙሉ ድምጽ ድምቅ ያለው። ምክንያቱም መልሱ የልብ አድርስ ሰለሆነ።
ይህን የሽግግር ጊዜ መታገስ ላቃተው ቁንጥንጥ የሥልጣን ሽሚያ ግብግብ የዕውቀት ማህደሮች በጠቅላይ ሚነስተር አብይ አገላላጽ „የአገር ዋርካ“ መምህራኖች በሙሉ ድምጽ ነበር ካለጥሪት እርቃኑን ያሰቀሩት የግርግር ፖለቲካን ህልም። ያን አሁኑኑ ፈርሶ እንይ መንፈስን የጉባኤው ተሳታፊዎች አለማስጠጋታቸውን ያበሠሩበት ልዩ አጋጣሚ ነበር። ተመስገን።
በሌላ በኩል እንዲህ አገራዊ ጉዳዮችን ፋና ቴሌቪዠን እንደተመኘሁት ስለቀረጸው ትውፈትነቱም በጥራት የተሰራ መሆኑ አርክቶኛል። ይህን የመሰለ የህሊና ሰብል እንዲህ በመሰለ ሁኔታ ተቀናብሮ ሲቀርብ ሌላ ተጨማሪ የሙያ ብቃት ታሪክ ነው። ሙያተኞች ከህሊናቸው ጋር ስለመሆናቸው ያሳዬናል። የሚከፈላቸውም ማህያንም ካለሰቀቀን፤ ከለ በደለኝነት ስሜት በምርቃት በጤና በህሊና በሰላም ደስ ብሏቸው ይጠቀሙበታል።
ከዚህው ርዕሰ ጉዳይ ስንነሳ ማፈርስ አሁን ህልም ስለመሆኑ እያሳዘነኝ አንድ ነገር ለዛሬ ላነሳ ወደደኩኝ። በማፈረስ ሄደት ውስጥ ምን ያህል ጌጣች በርብርብ በንፈስ በቀለ ስሜታዊነት ማቅ ስናለብሰው፤ ምን ያህል ፈርጣችን ስናወይበው፤ ምን ያህል የገነባነው ስናወረዛው እንደኖር ቁጭ አድርጎ የሚያስተመረን አንድ ዕውነት ጋር አገናኝቼ ታዳሜዎቼን ተሞጋቱ ልል ነው ዛሬ … እንዲህ ...
· ዕንቋዋ ቅኔ!
ከሙዚቃው ዓለም የጠፋችው ውቧ፤ ፍልቅልቋ አርቲስት ወይኒቱ ተገኘች
የአገር ፈርጥ፤ የአገር ጌጥ፤ የአገር ዕንቁ የሆነችው አንዲት ታላቅ ትውልዳዊት ህሊና የትም ወድቃ፤ ተረስታ፤ ተጎሳቁላ አዬሁኝ ሰሞኑን በአማራ መገናኛ ብዙሃን። የአማራ ቴሌቪዥን ዛሬም አስተውሶ ሄዶ ቃለ ምልልስ ማድረጉን እጅግ አድርጌ አመስግነዋለሁኝ።
አርቲስት ወ/ሮ ወይኒቱ አንዱር የሳቅ እምቤት፤ የፈገግታ ልዕልት፤ የደስታ መንፈስ፤ የውስጥንት መግለጫ፤ የኢትዮጵያዊነት ቤተ - መዘከር፤ የአብሮነት ቤተ መጻህፍት፤ የጥበብ መንበር ናት።
በኢትዮጵያ ስንት አመት ሞላው የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ታወጀ ከተባለ¡ በዬዓመቱም ይከበራል። ፋይዳውና ውጤቱ ግን ይሄ ነው። አሁን ራሱ ያለው በዬትም ቦታ ቀውስ ምንጩ ፍሬ ነገር እሱው ነው።
አንድ የቤተክርስትያን ለሂቅ ም/ ጄ አሳምነው ጽጌ በሰሰቡት ጉባኤ ላይ ሲናገሩ ጎንደር ከተማ „በህወሃት የትግል ወቅት ጫካ ነበር የድርጀቱ ህልውና የተመሰረተው የኖረውም፤ ህወሃት በድል አገርን ሲቆጣጠር ግን ጫካው ብሄር ላይ ሆነ ብለዋል።" ትክክልም ነው። የሥልጣኑን መሰረት ዓላማ እና ግብ ያመሳጠረ ታላቅ ዕድምታ ነው።
ነገር ግን ጫካው ብሄር ላይ ሆኖም በዚህ ዶክተሪን ውስጥ ያለው ዕውነት ግን የራስን ብሄረሰብ አጉልቶ በማውጣት ተጫኝ፤ አርጊ ፈጣሪ በማድረግ ሌሎችን መርገጥ፤ መደፍጠጥ፤ እንዳይወጡ ሰቅዞ መያዝ ስለመሆኑ ከእመቤት ወይኒ አንዱር በላይ ለዚህ ትውልድ ምስክር ሊሆን የሚችል አንዳችም ነገር የለም።
ይህቺ የአገር ልዩ ዜማ በፍጹም ሁኔታ ተጎሳቁላለች። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ምድር በጥበብ ቤተኞች ልብ ያለው የጥበብ ሰው ሞራል አለ ወይ? ብሎ ለመናገር እሷን አይቼ ሳሰበው እራሱ ደከመኝ - በመዛል። ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄር ብሄረሰቦች መብት ተከበረ ለማለት ከዬት መነሳት አለብን? ለሚለውም መልስ አጣሁለት - በግጠት።
ለዚህ ነበር ህወሃት ሰማዕትነቱን ድሉም ሁሉም ነገር የእኔ መሆን ይገባዋል እያለ የሚፎካክርበትን ለወና ቀረርቶ ስለመሆንም ጉስቁልናዋ አጫወተኝ? ለመሆኑ ግንቦት 20 እንዲህ የኢትዮጵያ ፍርጦችን እዬቀበረ ነውን ይዘከር የሚባለውን? ስንት የቧልት ነገር አለ? ድንቄም ...?
ለመሆኑ በዚህ አያያዝ ኢትዮጵያ "አማራውን" ትተን ህወሃት ቆሜለታለሁ ለሚላቸው እንደ ጠላትም ተፈርጀው ማንፌሰቶ ያለተቀረጸላባቸው፤ ለመመንጠር ፖሊሲ ያልተበጀላቸው እንደ ፍቅርት ወይኒ አይነት ጥበቦችን እንዴት ሲያስተናገድ ኖረ አውራው ፓርቲ ህወሃት? ዕውን የብሄር ብሄረሰቦች መብት አስከበሯል የሚባልለት ህገ መንግሥት ነፍስ ነበረውን? „ፍርድ ለራስ ነው“ ይላል የጎንደር ሰው። ፍርድና እውነትን ለእናንተው መተው ይሻለኛል።
· ኢትዮጵያ ማለት ወይንዬንም ማለት ነው - ለእኔ።
·
ጎስቋላዋን የጥበብ ታላቅ ሰው እያዬሁኝ ኢትዮጵያን አዬኋዋት። መረመርኳት። አወጋኋት። አወያየኋት። ኢትዮጵያ ማለት ጥቢት ወይንዬ ማለት ነውና። የወይንዬን መከራ ሳስበው የኢትዮጵያ መከራ በምን ያህል አረንቋ ውስጥ እንደ ሆነ አሰብኩት። እኛ ደግሞ በተንሳፈፈ የፖለቲካ ጉግስ ላይ። ዛሬን መተርጎም ተስኖን አሁንም ግርግር በገርዳሜው ተንጋዶ ህልማችን ሆኗል።
በወይንዬ መከላተም ውስጥ ኢትዮጵያን ሳስተውላት ምን ያህል ፈተና ፊት ለፊታችን እንዳለ መዘንኩት። በወይንዬ መንፈስ ውስጥ ኢትዮጵያን በዕንቧዋ ዙሪያ ስደመምባት ምን ያህል አደራ በሊታ እንደሆን አሰብኩት።
በወይንዬ የመከፋት ድባብ ውስጥ ኢትዬጵያን ሳያት ምን ያህል የትሩፋት ድርቀት ላይ እንዳለብን መዘንኩት። በወይንዬ የህሊና ትዝብ ውስጥ አዲሱን ትውልድ ሳስበው በትክክል አደራ ተረካቢ ለማድረግ የቀረን ሩቅ ጥልፍልፍ ጥምንምን መንገድ ሳሰላው ምን ያህል በፍላጎታችን ውስጥ ባዶ እንደሆን ታደምኩበት።
በወይንዬ በማትናገረው ግን መስጥራ በያዘችው እርግማን ውስጥ ምን ያህል እናት አገር ኢትዮጵያ እንደተከፋችብንም፤ እንዳዘነችብን፤ አንዳረረችብን እና የእርግማኑን ሚስጢር ወደ ምርቃት ቀዬርን ሰው ሆነን የምንቆምበት ሁኔታን ሳስበው እጅግ ከበደኝ። ብርዱም ከ አንጀቴ ገብቶ አንዘፈዘፈኝ።
ምክንያቱ እያንዳንዱ ለራሱ ምህረት ለማድረግ ገና ዝግጁ አለመሆኑን እያዬሁ ስለሆነ። ዛሬ ባልታሰበ ሁኔታ፤ ባልጠበቀነው ሁኔታ ነፃ ላወጣን ዘመን እንኳን ምን ያህል ፊት እንደ ሰጠነው ስመዝነው ለብ ለብ ይሆንብኛል። በውስጡ የለንም። አድፍጠን የምንጠብቀው የግጭት ዜናውን ብቻ ነው።
ምርቃት አለማዋቅ መርገምትን እንደሚያስከትልም አልገባንም። ምርቃቱም ሊነሳ እንደሚችል ተደፍኖብናል። ዘመናይነታችን ልክም ደንበርም የለውም። ቅልጣናችንም ወቄት አልተሠራለትም።
በዚህ ዘመን ውስጥ ሆነን እኛ ያለደረግነው እድሉን ብናገኝ ከጫፉ ልንደርስ በማንችለው የአዎንታዊ ሰዋዊ ዘመን ሆነን አንጋጠን ኩዴታን እንናፍቃለን በዬሰከንዱ። ገመናችን ይኸው ነው። … ወደ ራሳችን ተመልሰን የሰባባርነው መንፈስ ጠጋጋን፤ አቅም አጎልበትን፤ ያንጠባጠብነውን ሰብስበን የማህበረ ደራጎንን መንፈስ በፍጹም ሞራላዊ አቅም ድል ነስተን የተቀደስ ትውልድ ለመፍጠር ከነመሻው ላይ መቆማችን እራሱ ተረገጥ አልቦሽ ነው። ወለሌ!
· ትርጉም።
ጥበቢት ወይንዬ በሕይወት መኖሯን ስንተረጉመው በአጸደ ነፍስ ያሉም፤ በሥጋ የተለዩን የአገር ሃብቶች በምን ያህል ርዝመት አደራ በሊታነታችን እና ያለብን የእርግማን ናዳ ሁሉ አሰበኩት - ከምር።
ይህ የሆነበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው? ስትሉ ኢትዮጵያ በሊሂቃን የሥልጣን ግብግብ አፍርሶ ከዜሮ መጀመር ዋንኛ ዶክትሬን ስለሆነ ነው። እማዝነው አሁንም የዚህ ናፋቂዎች መበራከት፤ የትውልድ ብክንት አጀንዳችን አለመሆኑን ያመሳከርልኝ ነው። ተቆርቋሪነት በልዞ ነው እኔ እማዬው። ጠፋ ተሰበረ እንጂ እኔ የጠፋውን ልካሰው፤ የተሰበረውን ወጌሻ ልሁንለት የለም። አደንደበት እና ውስጥ አልተገናኙም። ሁሉም ናፍቆት አለበት በቆረጣ ድፍርስርስ ጉሸትን ባለዋንጫ ለማድረግ። ውዴቼ ይህን ስጽፍ እርር እያልኩኝ ነው።
ህውሃት ከጫካ ሲመጣ ሁሉንም ነገር ሲያጣጥል ግን መሰረት አድርጎ የተነሳው የኢሠፓን መዋቅር ነው። ደርግ "ዲሞክራሲያዊ አብዮትን " ነበር የሚከተለው። ብዙ በጥልቀት አልገባበትም። በቀላል አገላለጽ ግን በዛን ጊዜው ዴሞክራሲያወ አብዮት የፍልስፍናው ፍሬ ነገር ኢትዮጵያ የገበሬ አገር ስለሆነች በቀጥታ ወደ ሶሻሊዝም ለመሸጋገር እርሻውን ማሰልጠን ኢንደስትራያላዝድ መሆን ስላለባት የሽግግር ጊዜ ስለሚያስፍልጋት ተብሎ 17 ዓመት ተቆዬ። መሸጋገሪያ ጊዜ ነበር። /ሙሉው 17 ዓመትም ጦርነት ነው የነበረው።/
ኢትዮጵያ ካፒታሊዝም ላይ የነበረች አገር ሆና ቢሆን ኖሮ ግን "ዴሞክራሲያዊ አብዮት ሳያስፍለግ" በቀጥታ ወደ ሶሻሊዝም መሄድ ስለሚቻል ዴሞክራሲያዊ አብዮት አያስፍልጋትም ነበር። ስለዚህ በዛ ዘመን ፍልስፍና አጭር ጊዜ እና ረጅም ጊዜን ፕላን የሚያገናኛው ሊንኩ የመካከለኛ ጊዜው እንደሆነው ሁሉ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ሊንክ ነበር ወደ ሙሉ የሶሻሊዝም ሥርዓት ለማቅናት። ድልድይ።
ለዛም ነው የገበሬው በመንደር ምስረታ ተደራጅቶ ወደ ሰለጠን ወደ ዘመነ ማህበረሰብ የመለወጥ ውጥን የነበረው። በራሱ በዛ በአደረጃጃቱ ማልባ - ወልባ - ወላንድ የሚባሉ ፍልስፍናዎች ነበሩ። ቃሎቹ የትውስት ናቸው።
ይህ ህልም ገና በጅምር እያለ ነው ደርግ የወደቀው። የጎጃም ዬትኑራ የገበሬዎች አምራቾች የህብርት ሥራ ማህበርን ለናሙና ማንሳት እችላለሁኝ። ለልምድ ልውውጥ ካዬኋቸው ውስጥ አንዱ ነበር።
ህውሃት ሲመጣ ሪስፕሮካል አደረገው እና በቃላት ጨዋታ ዴሞክራሲን ቀዳማይ፤ አብዮትን ካልዕያ አድርጎ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብሎ አዲስ ፍልስፍና አመጣሁ አለ። እሱም ህብረተሳባዊነት ደርግም ይህንኑ ርዕዮት ዓለም ነበር የሚከተሉት። የህወሃት የሚለዬው + ዞጋዊ አደርገው።
የህወሃቱ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ትንተናውን እና ስኬቱን ታድመውበት ለቆዬቱ በአንድም በሌላም ከህውሃት ጋር አብረው ለሠሩ ጓዶቹ ባለሟለቹ እተወዋለሁኝ። ለነገሩ ተፎካካሪ/ ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ የሚበሉትም የጠራ የራዕይ ፍልስፋና ያለው እስከ አሁን አላደመጥኩኝም። ኢህአፓ ሊኖረው ይችላል መሰሉ ርዕዮት። ግልጹ ነገር የግራ ፖለቲካ ፍልስፍና የሁሉም የመንፈስ መነሻ ነው። ይህን ይዘው ነው ህወሃትን እነሱም የሚታገሉት። የዞጎቹም እንዲሁ።
በዚህ ማህል መታሰብ ያለበት ለተመሰሳይ ንድፈ ሃሳባዊ ራይይ በዬዘመኑ የሚደቀው የመንፈስ ሃብት እና የሚያባከነው የትውልድ መዋለ ጊዜ፤ ማዋለ ሃብት፤ መዋለ ትሩፋት ነው። ከኢህአፓ ውጭ ሌሎችም ቢሆኑ ከዚህ ማዕቀፍ ለመውጣት ጣር ይሆንባቸው እና በቃላት ቢያሽሞነሙኑትም በራሳቸው ህሊና የለውጥ አብዮት አለመድረጋቸውን የኖርንበት ስለሆነ ሌላ ማስረጃ አልጠብቅም - እኔ።
ሥልጣን በርግጫም በፍጥጫም ለዘላለም ተቸክሎ አንድ ሰው ተመልኮ መኖር ነው። የማያፈራ፤ ተተኪ የማይፈጥር ቁሞ ቀር ኩሬ ፖለቲካ። ህወሃትን በዴሞክራሲ ማዕከላዊነት የታሰረ ሲሉ እነሱ ደግሞ ከዛ አለመውጣቸውን በዚህ ባለንበት አገር አርፈው ተርፈው የግልሰብ ነፃነትን ተዳፍረው ሲያሳድዱ ስለኖሩ በዛ ውስጥ የከተሙ ስለመሆናቸው አለን መስካሪዎች። ሊብራል ወዘተ የሚባለው ለእኔ ለሥርጉተ ሥላሴ ተረብ ማባጨልም ነው።
ርዕዮቱን ስለተማርኩት። መንገዱን አሰራሩን፤ አደረጃጃቱን አፈጻጸሙን መሬት ላይ ሠርቼበታለሁና። ሰባዕዊነት እና ግራ እርቀሰላም የላቸውም። አጋጣሚው ከተገኜ መርሁ ያልተቀበለን በጭካኔ ማስመጥ ወይንም ለፍጻሜ መክለት። የ21ኛው ምዕተ አመት እና ሉላዊ የዲጂታል ዘመን ደግሞ ይህን በራሱ ውስጥ ያልጠና ያልሰረጸም መንፍስ ለማቆም ጋዳ ነው። ብቻ በዚህ በባዘን መከራ ውስጥ የሚደቀው ትውልድ ነው። በማያድግ፤ በማያቆጠቁጥ፤ በማያሽት፤ በማያፈራ፤ በማያሰበል … መና …
ለዚህም ነው ፓርቲዬ ኢሠፓ ግባቱ ሲፈጽም አንድም ድርጅት ጋር መንፈሴ ማህበርተኛ ሆኖ የማያውቀው። እንዲያውም ከእኔ የቀጠለው ትውልድ ያሳዝነኛል፤ ሚስጢሩን ሳያውቅ አቅሙን ሲያባክን … በዬድርጅቱ አባልነት ሲባትል፤ ሲማገድ፤ ህይወቱን ሲያሳልፍ። ዛሬ ተመስገን ነው ሰውኛ ተፈጥሮኛ መንፈስ አለ ኢትዮጵያ ውስጥ።
የመንገዳችን ፍኖተ ካርታ አይታወቀም ሲባል ይደመጣል 30/ 40 ገጽ ሐተታ ካልተደረስ አይሆንም ተብሎ። መሬት ላይ ያለው ቅዱስ አዬር ሰውኛ ነው ጠነኛ ተፈጥሮኛ ነው። ቅንኛ ነው ርህርኛ ነው። እኛዊነት እና አዎንታዊ ነው፤ የራስነገር ተኮር ነው።
ወርቀቱ ምን ይሰራልናል፤ ተኖረበት እኮ ተንቆጥቁጦ በሪባን አሸብረቆ ሲሰራ፤ ተግባር ላይ መስከሪው የድል ቅምሻ አጥቶ በመባዘን መንከላወሱ ነው። የአፍሪካ ነበርነቱም አንድ ወር ማህያ ሊከፍል የተሳነው እንደነበር ሰሞኑን ከጠ/ ሚር አብይ አህመድ አዳምጠናል።
ድንቋ አርቲስት ወይንዬ አንዱርን ያለከበረ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፤ የማያደምቅ ህገ መንግሥት በቁሙ ከነፍሬሙ የደረቀ ምስል ነው። ከሷ መንሳት አለበት ሁሉም ነገር። እሷም ዜጋ፤ እሷም አገር ናት እና። ህወሃቶች እነሱ እራሳቸው ያጸደቁት ህገ መንግሥቱ መጣሱም ይህ አንድ ናሙናዊ ማስረጃ ነው።
· የማፍረስ ጥማት።
በግራ ፍልስፍና ማፍረስ አንዱ የግብ መዳራሻ ነው። ምክንያቱም ሞግቶ በሃሳብ ልቅና እና መሬት ላይ በሚሠራ ብቁ የማደራጀት ተግባር የማሸነፍ አቅም ስለሚያንሰው ሃይል እና እርምጃ ነው ዋስትናው።
በሌላ በኩል አዎንታዊ በሆኑ በእርሾ ላይ መነሳት አይሻም። ስለምን? ለሚለው አቅም እንዴት እንደሚፈጠር የግንዛቤ እጥረት ስላለበት። የአቅም ምንጭ የፍልስፍና ድህነት ስላለበት። አቅም እራሱ ምን ስለመሆኑ አክብሮትም፤ ዕውቅናም፣ ህሊናም፤ ጊዜም ተሰጥቶት አያውቅም። ግርግር ብቻ ነው ግጥሙ።
የዬዘመኑ አቅም በቅጡ ያልሰተዳደሩ አገሮች የራሳቸው የሆነ ታሪክ፤ ትሩፋት፤ ትውፊት፤ ወግ፤ ባህል፤ ቋንቋ፤ ፊደል የላቸውም። ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በፊት ያከማቻቸው ጥሪቶች ናቸው ቢያንስ በመንፈስ ደረጃ አገር አለን፤ ትውፊት አለን፤ ብሄራዊ ሰንደቅዓላማ አለን፤ ባህል አለን፤ ቋንቋ አለን፤ ፊደል አለን፤ ሃይማኖት አለን፤ ታሪክ አለን የምንለው።
አሁን የብሄራዊ ሰንደቅዓላማ እሰጣ ገባ ዜጋ የሚለው እንዲኖር ስለማይፈልግ ነው። ዜጋ ነው አገር። አገር ነው ዜጋ ማለት። አንዲት አገር የፖለቲካ ድርጀቶች ሊኗሯት እና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል። ግን ያቺ አገር ዜጎቿ የሞቱለት ችግር ቢገጥም ሊሟቱላት የሚሰናዱበት ቋሚ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ፤ የዜጎች የወል መለያ የመንፈስ ማደሪያ ሊኖራት ግድ ይላል።
አሁን ያለው በኢህዴግ ፍልስፍና ሥር የወደቀ ነው። ይህ ማለት ይህ ዓርማ የ7 ሚሊዮን የኢህአዴግ አባሎች ዓርማ እንጂ የሰማያዊ ፓርቲ ወይንም የአብን ሊሆን ከቶ አይችልም። አብን እና ሰማያዊ አባላቶች ኢህአዴግን እና ሌሎችንም ጨምሮ 79 ግን የጋራ የዜግንት ሰንደቅዓላማ ሊኖራቸው ግድ ይላል። 27 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ህጋዊ ብሄራዊ ሰንደቅዓላማ አልነበረውም። ይህም ማለት የመንፈስ ማደሪያ አልነበረም። ሜዳ በቀል እንዲሆን ተፈርዶበታል የዜጋው መንፈስ ማለት ነው።
የድርጅት አባል ያልሆኑ ዜጎችም 27 ዓመት ሙሉ የእኔ የሚሉት የዜግነት ሰንደቅዓላማም የማንፌሰቶ መለያም አልነበራቸው። ይህ ማለት ኢትዮጵያ አንድ ነገር ብትሆን ዜጋውን የሚያሰባሰብ ብሄራዊ ሰንድቅዓላማ ስለሌለ በእግዚአብሄር ቸርነት ነው የኖረችው ማለት ነው አላዛሯ ኢትዮጵያ።
እርግጥ የባድመ ጊዜ „ከጨርቅነት“ አልፎ ለድል መታጨቱን እናውቃለን። የጭንቅ ጊዜ ሲመጣ። አሁንም የሰይጣን ጆሮ ይደፍን እንጂ ክተት ቢባል በዬትኛው የዜግነት መለያ? ይህ እኮ እርሾነቱ ትውልድን ከትውልድ ያቆዬ የኢትዮጵያ ዜግነት መለያ ነው። የወል ሃይማኖት።
እርሾ አልባ አገር አልነበረም፤ ጥሪት አልባ አገርም አይበጅም። የነበረው እርሾው ደግሞ የአቅምን ብክነት የታደገ ከዛ የተገኘ ነው። ግራ ለቀደመ ነገር ዕሴት አትኩሮት የለውም። ልብም የለውም። ታማኝነትም የለውም።
በቀደመው የኢትዮጵያ መንግሥት ግራ ርዕዮትን ይከተል እንጂ ዜግነትን ማዕከል ያደረገ ስለነበር ጭራሹኑ ኢትዮጵያዊ መንፈስ ተሟጦ አልጠፋም ነበር። ህወሃት ስልጣን ሲይዝ ኢትዮጵያዊነትን ማፈረስ ትልቁ ጀብዱ ሆነ ዜግነት መናድ ግቡ።
እንደ ተቋም ኢትዮጵያዊነት ለማፈረስ ጉሩቦ ለጉሮቦ ትንንቅ ላይ ነበር። ኢትዮጵያዊነት አገር ያቆመ ኢትዮጵያ የምትባል አገር የፈጠረ ጥልቅ ፍልስፍና ነው። ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ተቋምነቱ ፍልስፍናው የነፃነት መለያ ምልክት ነው። ይህ ማለት ለጭቁን ህዝቦች ሁሉ የመንፈስ ሪቂቅ ሃብት ነው። ይህንንም ለዓለም ህዝብ በተግባሩ አስመስክሯል። ይህ ነው ያስቀናው ህወህት እና መሰሎቹ … ስለሆነም የመጀመሪያ የጥቃት ረድፈኛ ሆነ ኢትዮጵያዊነት …
እሱ የቆመበት ምሰሶ ሁሉ ነው በዘመነ ህወሃት ተነቃቅለው የትሜና የተጣሉት። አገርን ከሚያቆሙ ምሶሶዎች ዋንኛው ኪነ - ጥበብ ነው። ኪነ -ጥበብ ፍጥረተ ነገሩ በአንድ ማዕልት አይገነባም። ኪነ- ጥበብ መክሊት ነው። ሂደትም ነው ኪነ - ጥበብ። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ቢወለድም ኪነ- ጥበባዊ ስብዕን ይዞ መወለድ ግን ከስንት አንድ የሚገጥም ልዩ ዕድል ነው።
በዚህ ዕድል ውስጥ የሚፈጠሩ ነፍሶች የአገር ቅርስ ውርስ ተቋም ናቸው። ተቋምነታቸውን ማስቀጥል የአንድ መንግሥት የመጀመሪያ ተግባሩ ነበር። ደርግ ሲመጣ የአጤዎችን መንፈሳዊ ሃብቶች በአንጻራዊ አፈርሶ ነበር። የሃብት ሃብት የሆኑ ዘመንም ታሪክም ሊታካቸው የማይችሉ የአገር ጥበቦች ላይ በቁጣ ወሰነ። እርግጥ ነው ተቋማቱ እንዳሉ እንዲቀጥሉ አድርጓል። መከላከያን ማንሳት ይቻላል። አዬር ሃይልን፤ ባህር ሃይልን፤ ምድር ጦርን። ግን ያን የፈጠሩ ያን ያደራጁ መንፈሶች ግን?
የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያዊነት እራሱ በመንፈስ ዲታነት ነበር በዛ ዘመን፤ ህወሃት ሲመጣ ግን ባላንጣ አድርጎ ሁሉንም ነቃቀለ። ኢትዮጵያዊነትን የሚገለጹ ማናቸውም ነገሮች በጠላትን ተፈረጁ። በዚህ የመፍረስ ሂደት ነው የግሼ አባይ የኪነት ባልደረባ የነበረችው የልዕልት ወይንዬ ህይወትም አብሮ የተቀጠቀጣው። ያ ሁሉ ድካሟ እንዲህ አይሆኑ ሆኖ የተቃጠለው።
እኔ ዶር አብይ አህመድ ጠ/ሚር ከመሆናቸው በፊት „ርግበ በርን“ ስጽፍ መግቢያው በዚህ ተኮር ነበር። የሥርዓት መለዋወጥ የተቋማት ንደት መሆን እንሌለበት እና ሊፈርሱ፤ ሊሻሻሉ፤ ሊወገዱ የሚገባቸው በጥናት በተመሰረተ እንዲሆን ተማፅኜ ነበር።
… አሁን ይህን ነው የሚከተሉት ጠ/ሚር አበይ አህመድ። መጸሐፌን አላገኙም ግን እኔ የቆስለኩበት ጉዳይ እሳቸውን አቁስሏቸው ስለነበር ዕድሉን ሲያገኙ በዛ ላይ ወሳኝ እርምጃ እዬወሰዱ ነው። ጥናት ሙያ ተኮር የሆኑ መጠነ ሰፊ ተግባራት እዬተከወኑ ነው። ለውጡን የሚመሩት ሃይሎች መንፈሳቸው በዚህ ላይ ጽኑ ነው። ማፈራረስን ተፀይፈውታል።
በጨለማው ዕድል ውስጥ ጎህ እንዲቀድ እያደረጉ ነው።
ይህ አልተመቸንም ነው የሚለው ቪዥን ኢትዮጵያ። እነሱን ነፃ ባወጣው መንፈስ ላይ ቆመው ፈርሳችሁ እንያችሁ እያሏቸው ነው። የሻ/ዳዊት ወታደራዊ ማንፌስቶ ነጥዬ የጻፍኩበት ይሄው ነው መንገዱ። ዕድሉን ቢያገኙ ሊያደርጉት ያሰቡትን ነው አሁን የሚነግሩን።
እንደማይችሉ ቢታወቃቸውም እያደቡ በነቀል ተከል መንፈስን ማወክ እና ማደናገር ግን መሰረታዊ ስልት ነው። ቢያውቁት በመፍረስ ውስጥ መዳን የለም። ሲፈርስ አብሮ ነው ሁሉመና የሚፈርሰው። ከሁሉ በላይ የሚበተነው የቤተስብ ብዛት መገመት አይቻልም። በመዳን ውስጥ ተጎጂው ጥቂት ትርፉ ግን ሚዛን የማይወጣለት ይሆናል።
አሁን በተያዘው ጥበብ እራሱ ጽኑ መንፈስ አይናድም! አድካሚውን መንገድ ነው የጀመሩት የለውጡ አራማጆች እና መሪዎች። ይህ ብሩክ መንገድ እንደ ሊማሊሞ ገደል ጠምዝማዛ ቢሆንም ከታሰበው ግብ አድራሽ ስለመሆኑ አልጠራጠረም። በራሳቸው ላይ የቆረጡ እና የወሰኑ የተግባር ጀግኖች ስለሆነ ለውጡን የሚመሩት። እንደሌላው አዝረክክርከው ተወጡት እንደማይሉ አስባለሁኝ። ራሳቸው ታሪኮች ናቸው። አብሶ ኢትዮጵያን በሙሉ ክብር እና ሞገስ ከውስጣቸው የተቀበሉ የተመረቁ ነፍሶች ናቸው ዛሬ በብጡል ራዕይ አገር እዬመሩ የሚገኙት።
በጣም በእርግጠኝነት ብነገራችሁ እንደ ሥርዓት የዘመኑ ሥርዓት ፈቅዶ ርዕዮቱ፤ ንድፈ ሃሳቡ ዲሞክራሲያዊያ አብዮት ደርግ ይከተል እንጂ በዛ ውስጥ የነበሩ እጅግ የሚመስጡ፤ በተወሰነ ደቂቃ ብዙ የምትማሩባቸው፤ ተደመጥው የማይጠገቡ፤ በራሳቸው ውስጥ የሰከኑ የኢትዮጵያ ጌጦች በዬትኛውም የሙያ መስክ ነበሩ። ዛሬም ይኖራሉ ብዬ አስባለሁኝ። ስለዚህ ቢያንስ እንሱ እንዲተርፉ ይህ የለውጥ ጎዳና ለድርድር የማይቀርብ ፍቱን መንገድ ነው።
በዘመን ደርግ ምርጥ ዘሮች እጅግ በርካታ ነበሩ። ሲፈርስ ግን የትም ባክነው ቀሩ። እመቤት ወይንዬ እንዷ ናት። ድንቅ የተግባር ወገኖች ነበሩ። ይህን የምላው ለላንቲካ ሳይሆን በእኔ ውስጥ ህልም የነበራቸው አለቆቼ እኔን በርዕዮት ዓለም ትምህርት - በኮርስ እንድሳተፍ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ በነበረው ዕድል ብዙ ብጡል ሰዎችን አግኝቻለሁኝም። ያን ጊዜ የሰባሰብኩትን አንጡራ ጥሪት ነው እንደ ሁኔታው መዘዝ እያደረኩኝ አክሰሱ ያላቸው ወጣቶች እንዲማሩበት እያጣቀስኩ የምጽፈው። 7 የልጆች እና የአዋቂዎች መጸሓፍትን የጻፍኩትም በዛ ጥሪት ነው።
በዛን ጊዜ እማላፍርበት በእርግጠኝነት እምናገረው በሁሉም ዘንድ ደግሞ ተወዳጅ እንደ ነበርኩኝ ነው በኮርስ ላይም ሆነ ለተወሰን ተልዕኮ ስላክ። ንቁ ቀልጣፋ ነበርኩኝ። ወጣትነቴም ሳቢና ማራኪ፤ ቀለሜም የተለዬ ጸዳል ነበረው ዓይነ ገብ ነበርኩ እንደ ዛሬው ለፊልም ተዋናይነት እንደሚመረጠው ማለት ነው።
ስለዚህ በሁለገብነት ንብ አበባው ለይታ ለማር እንደምትቀስመው ሁሉ እኔም ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ህሊናዬ ለመማር ለማወቅ ክፍት እና የሚፈቅድ ስለነበር ሊሂቃኑን በዝብዣቸዋለሁኝ እስኪበቃቸው ድረስ። የተበዘበዙት ደግሞ የሚመስጥ ሙሉ ብቃት ስለነበራቸው ነው። ከ እኩያዎቼ እንኳን ከሚበልጡኝ ነገሮች ሁሉ እማር ነበር።
እናም ያ በተለያዬ ሁኔታ በማገኘው ዕድል እምሰጥበት የነበረው ጥሪት ሁሉ ነው ደርግ ሲወድቅ ፍርስርስ ያለው። ባክኖ ቀረ። መተርጎም ያቅተኛል እንደ ዕድል የገጠሙኝን ሊሂቃን አቅም ስብዕና ሞራል ለመግለጽ።
የመንፈሳቸው ብርታቱ እና ህብረንቱ፤ በሙያቸው ያላቸው ጥልቅነት እና የፍስፍናቸው ጥራት፤ በህሊና አቋም ያላቸው በራስ የመተማመን መቅኖ የሚያስቀኑ፤ በዲፕሎማሲ አቅማቸው የሚያሰመኩ ልጆች ኢትዮጵያ ነበራት። እንደ እድል ሆኖ ለትምህርት ስላክም የኢትዮጵያን መስሪያ ቤቶችን፤ ድርጅቶች፤ የህፃናት አንባም፤ የጀግኖች አንባ፤ አዬር መንገድ፤ የጎማ ፋፍሪካን፤ የመንግሥት እርሻ ስንቱ ይዘርዝር የመጎብኘት፤ ቲያትር በመደበኛ የማዬት አጋጣሚም ስለነበረኝ በዛ ሁሉ የማያቸው ወገኖቼ ልዩ ነበሩ።
ትምህርት ቤትም ረዘም ላለ ወራት አብሮ በመቆዬት የገጠሙኝ ሊቀ ሊቃውንታት ሁሉ እንደዛ ባክነው ነው የቀሩት። የጋራ የትምህርት ክ/ ጊዜ ላይ እነ ዶር ላጲሶ ዓይነቶቹ ሁሉ እዬመጡ ያሰተምሩን ነበር። ያን ጊዜ ለእኛ ያስተማሩን እና አሁን የሚያስተምሩት ታሪክ ጫፍ እና ጫፉን ለማገናኘት እንኳን አይችልም እንኳንስ ሆድዕቃውን ለማዋህድ። እንደ ሳቸው ያሉ ሰዎችም ነበሩበት ለማለት። እሳቸውን እጅግ አድርጌ ነው የምታዘባቸው።
ብቻ በዛ የመሰናዶ የትምህርት ክ/ ጊዜ እጅግ ብዙ ጽናት የነበራቸው ሊሂቆችን አይቻለሁኝ። ተዋውቄያለሁኝ። እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ሃላፊ እዬመጣ ልምዱን እቅዱን ግቡን ያሰተምረን ነበር።
እውነት ብናገር ሃብታሞች ግን ሃብታችን በራሳችን እያቃጠልን በሁለመናው ኋላቀርነት ለራሳችን የመረቅን የተበደልን ፍጡራን ነን። እማዝነው ፈጣሪ በቃችሁ ብሎን እንኳን በጽናት፤ በታማኝነት ለውጡን ለማስቀጠል ወናነት ሲዋኝብን አስተውላለሁኝ - ማህጸኔን የእልህ ረመጥ እዬለበለበው።
የሚያሳዝነው ያ ሳያቃጥለን፤ ያ ሳይጸጽተን፤ ያ ሳያንገበግበን አሁን ደግሞ እራሳችን ማቆም የማንችል፤ የተደራጀውን አፍርስን በፈረሰ መንፈስ፤ በሬሳ ሃሳብ ኢትዮጵያን እንቅበራት ነው የሚለን ቪዥን ኢትዮጵያ።
በዛን ጊዜ የደቦ የህወሃት የፍርሻ ፖለሲ አንደ በርቋ ድንቋ አርቲስት ወይንዬን ብቻ አይደለም ያጣነው። ብዙ ወይንዬዎችን አጥተናል። አሁን እኔ ጓድ ገዛህን ወርቄን እንደ አንድ አገር መሪ ብቻ አይደለም የማያቸው። እንደ ተምሳሌት ግንድ እንጂ። ስላሳቸውም ትውልድ ያውቃቸው ዘንድ መግለጽን እሻለሁኝ ...
በኢሠፓ ማዕለካዊ ኮሜት ስብሰባ ላይ „ሁላችን ልጆቻችን ውጭ አገር እዬሰደድን የደሃ ልጅ ጦርነት እንማግዳለን“ ብለው ነበር የሞገቱት ማዕከላዊ ኮሜቴውን። እንደ ዶር ለማ መገርሳ፤ እንደ ዶር አብይ አህመድ እንደ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው፤ እንደ አቶ ደመቀ መኮነን፤ እንደ ዶር አንባቸው መኮነን ካለውቅቱ የተነሱ መሪ ነበሩ።
በኋላም ልጃቸው 18 ዓመት ሲሞላው ጠብቀው የሳቸውን ልጅ ብሄራዊ ውትድርና ልከውታል። በመጨረሻም ግዳጁን ጨርሶ ሲመለስ ከእኛ ጋር ሲከላትም ከአባቱ ጋር አርማጭሆ ላይ ያ ሸበላ አልፏል።
በግል ኑሯቸው ዘይት የሚገዙበት እና ቡና የሚገዙበት ከእነ ጋሽ ታርቄ ሱቅ ነበር። ግማሽ ሊትር ዘይት ግማሽ ኪሎ ቡና ነበር የሚገዙት። ያው ሰፈራችን አንድ ሰልሆነ እኛም ስንገዛ እህታቸውም ስትገዛ እንገናኝ ነበር።
ቢሮ ልክ እንደ እኛ ማትራሰ ነፍተው መሬት ላይ ነበር የሚያድሩት። ቤታቸው ማደር የሚባል፤ ሰንበት ማረፍ የሚባል አያውቁም። ለሁለት ሰዓት በዬቀኑ ኮሪደር ላይ አመልካችን ያስተናግዱ ነበር። እዛው ዘብ ላይ ስልክ እዬደወሉ ሁሉ ትእዛዝ እዬሰጡ ባለጉዳይን አስደስተው ይሸኙ ነበር።
በማንኛውም ሁኔታ በር ላይ ከተገናኘን ማንኛችንም ከሊቅ አስከ ደቂቅ ቁመው ቤተሰብ ጠይቀው ደህንነት ጠይቀው ነው። በማንኛውም ሁኔታ ስልክ ሲያነግሩን ሲጨርሱ አምሰግናለሁ አይቅርም። ባይገርማችሁ እኔ የቡድን ጥናት ሰብሳቢያቸው ነበርኩኝ። እርእስ ስሰጣቸው ተዘጋጅተው መጥተው ያስተምራሉ። ሌሎች መምህራኖች ሲሆኑ ደግሞ ቁጭ ብለው ይማራሉ እንደ አንድ ተራ አባል።
ተሰናድተው ስለሚመጡ በሌሎች አዘጋጆች ላይም ማጠናከሪያ ይሰጣሉ፤ አስቸኳይ ስብሰባ ሲኖርባቸው ደግሞ ደውለው ፈቃድ ይጠይቁኛል። እኔ የመመሪያ ሃላፊ አይደለሁም የክፍል ሃላፊ ነኝ።
እሳቸው ደግሞ የደርግ አባል፤ የማዕከላዊ ኮሜቴ አባል፤ እና የጎንደር ክ/ አገር የኢሰፓ ተጠሪ ናቸው። ግን እኔ በጥናት ክበብ ሰብሳቢያቸው ስለሆንኩኝ ይታዘዛሉ። ፈቃድ ይጠይቁኛል። እንዲህ ዓይነት ውስጡ መሆንን የተቀበለ መሪ ነበሩ። ትምክህት፤ ትዕቢተ ፊት መኮስኮስ አይቼ አላውቅም። የሰው አክብሮታቸው ትህትናቸው ይከብዳል። እዚህ ውጭ አገር ሳይ ደግሞ ገና በመሪነት ውስጥ ያልተፈጠሩ ገጥሞኛል። ትሁት መሆን ለመሪነት ያቀርባል። መሪነት ህዝብን በመንፈሱ ካለቀረበ አጋም እሾህ ወይንም ትሬኮላታ ነው።
ሌላው ጎንደርን እንዲለቁ ኤሊኮፍተር መጥቶላቸው ሞቴን ከጎንደር ህዝብ ጋር ብለው ነው ከልጃቸው ጋር የተሰዉት። ለዛውም እሳቸው ጎንደር እንዳይቃጠል፤ ጎንደር ህዝብ እናዳይሞት አስበው ኮማንድ ፖስቱን ላይ አርማጭሆ ትክል ድንጋይ ላይ ባያደርጉት አንድ ሰው አይተርፍም ነበር። ፋሲል ግንብን ጨምሮ የጦርነት አውድማ ይሆን ነበር። ጓድ ገዛህኝ ወርቄ ለጎንደር የመንፈሱ ፅኑ ጠባቂ ባለውለታው ናቸው።
ኢሠፓ ቀድሞ አቅሙን አውቆ ሁኔታውን የማስተዳደር አቅም ቢኖረው ይህ ሁሉ የሰው ሃብት አልግባብ ባልባከነ ነበር። ቢያንስ የመኮንኖች የኩዴታ ሙከራን የሃይል እርምጃ ታቅቦ የደርግ መንግሥት ራሱን ለማረም ቢጥር ስንት ነገር ይተርፍ ነበር። ብዙ ነፍስ ነው የባከነው። ብዙ ሃብት ነው የባከነው፤ ብዙ ዕውቀት ነው የትሜና አቧራ ለብሶ የቀረው። ዛሬ የለውጡ መሪዎች በጥበብ ይህን ታድገውታል። ጀግንነታቸው ህብር ነው። ስንት ነፍስ ነው የተረፈው አሁን? ያልደረሰበት አያውቀውም። ዕድሜ ኑሮ ህይወት አብሮ ነው የሚነደው።
በዚህ የማፍረስ አባዜ ታላቅ አገራዊ ተግባር ከውነው በባለውለታንት መንበር ላይ ሊቀመጡ ከሚገባቸው ግን ባክነው ከቀሩት ነፍሶች አንዷ ውዷ ተናፋቂዋ ፍልቅልቋ አርቲስት ወይንዬ አንዷ ናት። አሁን ከዚህ ነው የታደጉት ኢህአዴግን ሆነ በዘመኑ የተፈጠሩትን ማህበረተኞችን ሁሉ እነዚህ የለውጥ የአገር ፈርጦች። ግን ዋጋ የሚሰጠው እንብዛም ነው። ይህ ዕድል ባይኖር የሞተው ሞቶ፤ የተሰደደው ተሰዶ የቀረው ደግሞ የካቴና የበቀል ማወራራጃ ይሆን ነበር። ስንት መከላተም ነው የደረሰብን። ተዘርዝሮ ያልቃልን?
7 ሚሊዮን አባል አለው ይባላል ኢህአዴግ ይህ ለውጥ እንሱንም ማዳኑን አውቀው የተከናነቡበትን ሙልጭልጭ የሚል የገለማ ታሪክን አውልቀው፤ ራሳቸውን ለውጠው በአዲስ መንፈስ ከቂም - ከቁርሾ - ከሴራ ወጥተው አዲስ ሰው ሆነው መፈጠር ይኖርባቸዋል።
ባለሃብቶች፤ የጥበብ ሰዎች፤ የሃይማኖት ሰዎች፤ ተቋማት፤ ድርጅቶች በሙሉም የሳቦታጅ መረባቸውን አሸንፈው ራሳቸውን ከማፈረስ መታቀብ ይኖርባቸዋል። ይህ ለውጥ ቢቀለበስ የመጀመሪያ ረድፍ ተጠቂዎች እነሱ ናቸው።
ርህርራሄ የሚባል ኢትዮጵያ የግራ ፖለቲካ ፍልስፍና ሊሂቃን ተፈጥሮ አይፈቅድም። ዕድለኝነታቸው አብዩን አሜኑን የመሰለ እራሱን ማግዶ አዳኝ ሙሴ አላቸው - ዛሬ፤ ለዚህ ሙሴ አይደለም በቀን ሌሊት ቢሠራም ዋጋው፤ ውለታውን መመለስ አይቻልም። እነሱንም ነጻ አውጥቷቸዋልና። እኛ እንዲህ ዓይነት መሪ ቢኖረን የዚህ ሁሉ መከራ መረማመጃ ባልሆን ነበር።
መቻቻልን ችሎ ያዬነው ለውጥ በእኛ ዕድሜ አሁን ነው። መቻቻል ራሱ ትልቅ ፍልስፍና ነው። በአንድ ዘመን በተፈጠረ የፖለቲካ ትርምስ የተሰዉት ሳያሳስባቸው አሁንም ቁርቁሱን የሚታይ ነው። የዴሞክራሲ፤ የምህረት፤ የይቅርታ ሥልጣኔያችን በአንድም በሌላም በርዶት በደመመን ነው እኔ የማየው።
ይህ ለውጥ ካልቀጠለ የጥበቢት የወይንዬ የመከራ ህይወት ተረካቢ ሁሉም ይሆናሉ … የህወሃት ባለሟሎችን አቶ ሂደት እዬመዘዘ የጥቃት ሰለባ ያደርጋቸዋል። ግራ የቆመበት ፍስፍና ቂም በቂም መጥለፍ ነው። ጥላቻን በጥላቻ ማከም ነው።
መከለከያው ደህንነቱ ሁሉ የዚህ ሰለባ ይሆናል። እነ ተጋሩ ፈጣሪን አምስገነው ለፈጣሪ ትንግርት ራስ እሰከ መስጠት ድረስ መቁረጥ መወስን ይገባቸዋል። እንጂ አደባባይ ወጥቶ „ገዱ ሌባ፤ አብይ ሌባ“ ማለቱ የትም አያደርስም። ሺዎች በዬክልሉ አሉና። የሺዎች የዛሬ ህይወት ሳይሆን የነገ የትወልዱ ዕጣም አሳርን ያጫ ነው። በደል የሚያሸክማው ዕዳ አለባቸው ገና ሳይጠነሰሱ ... ያን ለማከብ ነው እንዚህ ቅኖች ሌት ተቀን እዬተጉ ያሉት።
ስለሆነም ዘመናይ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ቅምጥሎች እነሱም ይህ ለውጥ ከተቀለበስ እዬታደኑ በቀል ያርዳቸዋል። ሰው አላልኩም በቀል ያርዳቸዋል ነው። ስለሆነም እንደማገኘው መረጃ አሁንም የህውሃት መንግሥትን ለመመለስ የመረጃ አቀባይነት እና አተራማሽነት የምትጉ የተጋሩ ሰዎች ልብ ግዙ።
መቼም ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል ከእንግዲህ የህወሃት መንፈስ አውራ መሪ ሆኖ አገር ይመራል ተብሎ አይታሰብም። ዜጋው ከሚችለው በላይ ነው መቻቻልን ተቀብሎ እዬኖረ ያለው። እንኳንስ ተመልሶ ለሥልጣን መብቃት ቀርቶ ለማድመጥ እንኳን አቅም የለም። ህልሙም ፈጽሞ የማይቻል ነው።
አቅል ኖሮ በህወሃት የሴራ መረብ ላይ የሚታደሙትን ለማደመጥ እንኳን አለመቻሉን ነው አንዳንድ ሰዎችን ሳገኝ የሚነግሩኝ። የታመቀ፤ ያልፈነዳ ጉዳይ ሁሉ አለ። አብሶ በአንድም በሌላም የህውሃት ቤተኞች ሆነው ለቆዩ የጥፋት ተባባሪዎች። በለውጡ አራማጆች ማፍረስን የድል እርካብ መርህ አድርገው አለማዬትን እነሱን ከስጋት አትርፎ የመኖር ዋስትናቸውን ሰጥቷቸዋል ግን አላውቁበትም።
ሌላው ቀርቶ በዩንቨርስቲዎች፤ በት/ ቤቶች ማን ይበጠብጣል? ሲባል ማን እንደሆነ ህዝቡ ያውቃል። ስለዚህ መብትን ለማግኘት ግዴታንም ማወቅ ይገባል። በመፍረስ ወስጥ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለም። የዶር አብይ አህመድ ዘመን ከሌላው ይልቅ ለታገሩ የነፍስ አባት ነው። ራሱን ማግዶ ነው ሁሉንም ታግሶ በግራ በቀኝ እዬተንገበገበ ያለው …
ይህ የፍቅር አመቤቷ ወይንዬ ህይወት ለሁላችሁም ትምህርት ሊሆን ይገባል። አሁንም እንፍርስ የሚሉ ነፍሶችን ጥድፊያም ይኸው ነው። ጥርግርግ አድርጎ አስወግዶ በተለመደው መንገድ በመጫን፤ በመርገጥ መቀጠል ነው።
የሚገረመው አቅም አለመኖሩን 10/ 15/ 20/ 25/ 40/ 45 ዓመት ዕድሜ ቆጠራ እንጂ መፍትሄ ቆጠራ አለመሆናቸውን ሁሉም ያውቃዋል። ከታዳሚዎችም ጡጦ የሚጠባ የለም። አንድ የጸና መንፈስ እንኳን በሌለበት ነው ያለው ነገር ፈርሶ እኛ በምንሰጠህ ማንዴት ጠ/ሚር አብይ አህመድ ተንቀሳቀስ የተባለ ዓዋጅ የታወጀው።
የሳቅ እምቤቷ አርቲስት ወይኒ ለሁላችንም የማስተዋል ተቋማችን ናት። ወደፊትም የደግነት አንበሉ የእኛ ዮሴፍ ገበሬ፤ ትንቢተኛዋ ወ/ሮ መቅደስ ጸጋዬ፤ የብሄራዊ ሰንድቅዓላማችን ዓርማ ወ/ሮ መሰረት መብራቴ የቅንነት ጠበቃ የፈጠራ የኔታ አቶ ፍጹም አሳፋው ከብዙ በጥቂቱ የዚህችን የትውፊት መሰረት የወይንዬን ህይወት ከአቧራ አንስታችሁ ሰው አድርጋችሁ ቅርስ እና ውርስ የሆነ ቋሚ የመኖር ዋስትና ታገኝ ዘንድ የግል ጥረታችሁን ብታደርጉ ትውልደ ማነጸን የመጀመሪያ የፊደል ገባታ ት/ ቤት ከፈታችሁ ማለት ያስቸልኛል። በጠማሪም የቅኔው እንቡጥ አርቲስት ቴወድሮስ ካሳሁን እና ባለቤቱ አርቲስት ወ/ሮ አምለሰት ሙጨም በዚህ በረከት ብትሳተፉ ፈቃዴ ነው። ድረሱላት እባካችሁ!
· ኮፒ ራይትን ስለማስጠበቅ።
ሌላው ተከራካሪ ተሟጋች ዋቢ ጠበቃ ባለማግኘቷ ሃብቷ ተዘርፎ ሌላ የኪነት ባለሙያ እዬከበረበት፤ ክብርና ሞገስ እያገኘበት ስላለ ያንንም በህግ የኮፒ ራይት መብቷን አስጠብቆ፤ ካሳ ተከፍሏት ያ ድንቅ የጥበብ መንፈሳዊ ድርሳኗ ወደ ባለሃብቷ እንዲ መለስ የሚመከተው አካል ሁሉ ተረባርቦ ዋጋዋን ታገኝ ዘንድ መጣር ይገባል።
እኔ በምኖርበት አገር ሲዊዘርላንድ ሁሉን ነገር መንግሥት አይሠራም። ተቋማት ሆኑ አቅም ያላቸው ቅን ሩህሩህ ወገኖች ይህን መሰል ብሄራዊ ህዝባዊ ሃላፊነት በራሳቸው ተነሳሽነት ወስደው ከመንግሥት በበለጠ አትኩሮት ይሰሩበታል። ስለዚህም ይህችን የጥበብ ፈርጥ ወደ ቀደመው ክብሯ፤ ማዕረጓ የመመለስ ትውልዳዊ ድርሻ ይመስለኛል - ለሁሉም። በመንፈሰም፤ በሥነ - ልቦናም፤ በአኗኗርም፤ በሞራልም ቃላት ከሚገልጸው በላይ ተጎድታለች።
· ይከወን ዘንድ፤
ሃላፊነቱን በዝብሪት ሳይሆን በመከፋፈል ውብ የሆነ የምሥራች ታሰሙኝ ዘንድ ሥማችሁን ያልጠቀስኩት የአገር ሃብታት ሁሉ የምትችሉትን በማድረግ ዋቢ ጠበቃ ሆአነችሁ ጥቃቷን ታወጡላት ዘንድ በትህትና ብልመና አሳስባችሁአለሁኝ።
የቅኔው ንጉሥ ብላቴ ሎሬት ጸጋዬ ገ/ መድህንን አናገኘውም ግን መንፈሱ አለ በሁላችንም ውስጥ ባለውለታችን ወይንዬን ግን እያለች በህይወት ተረስታለች።
እኔስ እላለሁ …
የጥበብ ወጋገን አርቲስት ወይኒ አንዱር ትውልድ ናት! ሳቋ ፈገግታዋ፤ ፎለቄነቷ ውበቷ ለኢትዮጵያ ጸሐይ ነበረች …. እጅግ ድንቅ የሆነች ፍጡር ናት …. እና እባካችሁ የማከብራችሁ የኪነ ጥበብ ቤተኞች ሁሉ የምትችሉትን፤ በምትችሉት መንገድ ፈጽማችሁ ጥቃትን አውጡ፤ ለመፍትሄ በመትጋት ይህን የጉስቁልና ምዕራፏን መዳኘት ለቅኖች አይቸግርም ብዬ አስባለሁኝ። ለምትሰጡ አትኩሮት ሁሉ የላቀ የከበረ ዘንካታ የውስጥ ፍቅር እንሆ ...
ሴቶች ጥበቦች ናቸው!
የኔዎቹ የምትችሉ ፌስ ቡካችሁ ላይ ለጥፉልን። ኑሩልኝ።
መሸቢያ ጊዜ።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ