የዴሞክራሲ ግማዱ እና ገመዱ;
እንኳን ደህና መጡልኝ። የዴሞክራሲ ግማዱ እና ገመዱ ። „ ምንም እንኳን በለስም ባታፈራ፣ በወይን ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራ ሥራ ቢጓል እርሾችም መብልን ባይሰጡ በጎችም ከበረት ቢጠፉ ላሞችም በጋጥ ውስጥ ባይገኙ እኔ ግን በእግዚአብሄር ደስ ይለኛል፤ በመዳህኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። “ ትንቢተ ዕንባቆም ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፲፯ ቁጥር ፲፰ ከሥርጉተ©ሥላሴ Sergute©Selassie 28.02.2019 ከእመ ዝምታ - ሲዊዘርላንድ። · እፍታ። ውዶቼ እንዴት ናችሁ ደህና ናችሁ ወይ? አንዳንድ የኢሜል ወዳጆቼ መልዕክት እዬላኩልኝ ነው። እምታምኛቸው መሪዎች „ ኢትዮጵያን ከዱ“ እዬተባልኩ ማለት ነው። እኔ እኮ መልካም ሲሰሩ እንደማመሰግናቸው ሁሉ ትክክል አይደለም የምለውን ደግሞ እስሲበቃቸው ድረስ ነው እማከናንባቸው። ቅን መሆን፤ ልብን ከፍቶ መቀበል፤ አወንታዊ መሆን፤ አዲስ እንግዳ ሲመጣ አንጥፎ ጎዝጉዞ መቀበል የአባት አደሩ ነው። ይሄ ሆነ ብዬ ወደፊትም መልካም ነገር ሳይ አልሸሽም። በሌላ በኩል በቀደመው ጠ/ሚር ከመሆናቸው በፊት በነበረው የጠ/ሚር አብይ አህመድ ንግግር ውስጥ ሁሉ አንደም ውስልትና በኢትዮጵያ ላይ አላገኘሁም። አሁንም ይህ ጽኑ እምነቴ ነው። የአፍ ወለምታ ግን አያለሁኝ። ይህንም በተለያዬ ጊዜ ሞግቻቸዋለሁኝ። እራሱ የሰሞኑን የለገጣፎ ጉዳይ የድርጅታቸውን ወስኜ "አላውቀውም የከተማ ከንቲባ ስላልሆንኩ" ያሉትን ጽፌባቸዋለሁኝ። አፋር ላይ „ደርግ የወረደው ህዝብ ስለጨፈጨፈ ነው“ ስላሉም ይህንንም ሞግቻቸዋለሁኝ፤...