ሀውልት ለኑክሩማ ወይስ ለሥላሴ? ከጸሐፊ አቶ መስፍን ማሞ።
እንኳን ደህና መጡልኝ።
ሀውልት ለኑክሩማ ወይስ ለሥላሴ?
“ለሁሉ ዘመን አለው፤ ከሰማይ በታችም
ለሆነው ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።”
መጽሐፈ መክብብ ምዕራፍ ፫ ከቁጥር ፩ እስከ ፪
መስፍን ማሞ ተሰማ
ሠላም ለናንተ ይሁን!
{ማስታወሻ፤ ውድ አንባቢ! ቀጣዩ ፅሁፍ የተነቀሰው <ሞትና የኢትዮጵያ መሪዎች> በሚል ርዕስ በ381 ገጾች ህዳር 2006 ዓ/ም - 2013 - በአነስተኛ ቁጥር በሲድኒ ካሳተምኩት መፅሀፍ ነው። በዚህ መፅሀፍ የግርማዊነታቸውን ዘመን በሚተነትነው ምዕራፍ ዛሬ በሰፊው መነጋገሪያ የሆነው <የኢትዮጵያ ፓን አፍሪካውያን> በሚል የተደራጀው ማፍያ የህወሃት መንግሥታዊ ቡድን የግርማዊነታቸው ሀውልት በአፍሪካ ህብረት ግቢ እንዳይቆም በታሪክና በትውልድ ላይ የሰራው ሸፍጥ በዝርዝር ቀርቧል። ከአምስት ዓመት በፊት በታተመው መፅሀፍ የሚከተለው ትንተና ቀርቦ ነበር፤ መልካም ንባብ ይሁንልዎ!}
አቶ መለስና መንግሥታቸው ቀዳማዊ ሃይሥላሴ ለአፍሪካ ያበረከቱት አስተዋፅዖ እንዳይዘከርም ሆነ ቋሚ ሀውልት እንዳይተከልላቸው በፅኑ የጣሩና ጥረታቸውም ፍሬያማ እንዲሆን ያደረጉ ናቸው። “የኢትዮጵያ እንቆቅልሽ፤ ሀውልት ለኑክሩማ ወይስ ለስላሴ?” Ethiopia’s conundrum: A statue for Nkrumah or Selassie? በሚል ርዕስ የአፍሪካ ሪፖርተር ጃኔት ሾኮ /Janet Shoko/ ፌብሩዋሪ 8፤ 2012 ካቀረበችው ዘገባ የሚከተለውን ልብ ይሏል፤
የቀድሞውን የጋና መሪ ኳሚ ኑክሩማን ለመዘከር ሐውልታቸው በአፍሪካ አዳራሽ መተከሉ አግባብ ነው ሲሉ አቶ መለስ ጥብቅና ቆመውላቸዋል። የሃይለ ሥላሴ ሐውልት እንዳይተከልም ዐይነተኛ መከራከሪያቸው ያደረጉት፤ ኑክሩማ ፓን አፍሪካኒስት ናቸው - የሚል ነው።
የኑክሩማን ሚና አለመቀበል አሳፋሪ ነው። ስለ ፓን አፍሪካኒዝም ስንነጋገር የሚታወሱት አንድና አንድ ሰው ብቻ ናቸው፤ ኑክሩማ፤ በማለት አምርረው ተከራክረውላቸዋል።
የመለስ መንግሥት ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴን ዘወትር እንደወቀሰ ነው። ይሁን እንጂ ንጉሠ ነገሥቱ ለአፍሪካ ነፃነትና አንድነት ያደረጉትን ጉልህ አስተዋፅዖ የሚያደንቁ በርካቶች ናቸው።
ሃይለ ሥላሴ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ጋር ባደረገቸው ትግል ድጋፋቸውን የሰጡ መሪ ናቸው። ታጋዩን ኒልሰን ማንዴላን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማመቻቸት ማንዴላ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ትምህርት እንዲቀስሙ አድርገዋል።
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ኒልሰን ማንዴላ በመፅሀፋቸው - በዘመነ አፓርታይድ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባኤን ለመሳተፍ የቻልኩት ሃይለ ሥላሴ ባመቻቹልኝ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ምክንያት ነው - ብለዋል፤ በማለት አቶ መለስ ዜናዊ የቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ሐውልት በአፍሪካ አዳራሽ እንዳይቆም ቀንደኛው ተቃዋሚ መሆናቸውን ጋዜጠኛዋ በዘገባዋ አቅርባለች።
ታዋቂው ፓን አፍሪካኒስት የቀድሞው የጋና ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኳሚ ኑክሩማ ለአፍሪካ ህብረት መመስረት ያደረጉት ግዙፍ አስተዋፅዖ መዘከር የለበትም ወይም ሀውልታቸው መቆም አልነበረበትም የሚል አስተሳሰብ ያለው ኢትዮጵያዊ ከቶም የለም።
ኑክሩማ ሀውልታቸው በአዲሱ የአፍሪካ ዩኒየን ፅ/ቤት ግቢ የቆመው ለአፍሪካ ህብረት ባበረከቱት አስተዋፅዖ እንጂ በጋና ፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው በጋና ውስጥ ላከናወኑት ተግባር ወይም በፓን አፍሪካኒስትነታቸው ካልሆነ አቶ መለስ ዜናዊና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው የቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ሀውልት እንዳይቆም የተቃወሙት አሳቸው አውቶክራትና ፊውዳል ናቸው እንጂ ፓን አፍሪካኒስት አልነበሩም በሚል መሟገቻ ምክንያት መሆኑ አሳዛኝና አሳፋሪ ብቻም ሳይሆን አቶ መለስ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ክብርና ፍቅር እስከምን ድረስ እንደሆን ተጨማሪ ማስረጃ ስለመሆኑ ትውልድና ታሪክ እንዲያጤነው ተገቢ ነው።
አቶ መለስ ለኢትዮጵያ ታሪክና ሀገሪቷ ለነበረቻቸው ነገሥታትና ላበረከቱዋቸውም ታሪካዊ ተግባራት የውጪ ጠላት ያህል ወሰን ያለፈ ጥላቻና ቂም ያላቸው በመሆኑ እንጂ እሳቸውና መንግሥታቸው ድምፃቸውን ማሰማት ቢፈልጉ ኖሮ የኑክሩማም ሆነ የቀደማዊ ሃይለ ሥላሴ ሀውልቶች መቆም ይችሉ ነበር።
“የኢትዮጵያ ፓን አፍሪካን ማህበር” በሚል መጠሪያ የድርጅቱ ሊቀ መንበር ነኝ የሚሉ አሥራት ደፈርሳ የተባሉ ግለሰብ ፌብሩዋሪ 23 2012 /እአአ/ ለአፍሪካ ዩኒየን ኮሚሽን ተጠባባቂ ሊቀ መንበር ለተከበሩ ኢራስቱስ “የሃይለ ሥላሴ ሀውልት በአፍሪካ ዩኒየን እንዳይቆም አፍሪካ ድምጿን ታሰማለች” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ከአዲስ አበባ በፃፉት ረዥም ደብዳቤ ቀደም ሲል አቶ መለስ ያቀረቡዋቸውን መሟገቻ ሀሳቦች በሙሉ በስፋት ቃል በቃል በመተንተንና ሌሎችንም በማከል አቅርበዋል። የደብዳቤው ሙሉ ቃል አንዲህ ይላል፤
የሃይለ ሥላሴ ሀውልት በአፍሪካን ዩኒየን እንዳይቆም አፍሪካ ድምጿን ታሰማለች
በአስራት ደፈርሳ 23 ፌብሩዋሪ 2012
ለተከበሩ ሚ/ር ኢራስቱስ ምዌንቻ
የአፍሪካ ዩኒየን ኮሚሽን ተጠባባቂ ሊቀመንበር
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ክቡር ሆይ!
የሃይለ ሥላሴ ሃውልት ከዶ/ር ኳሚ ንኩሩማ ጋር በአፍሪካ ዩኒየን ፅ/ቤት ግቢ እንዲተከል ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች ባቀረቡት ጥያቄ ላይ የኢትዮጵያ ፓን አፍሪካን ማህበር የበኩሉን አስተያየት ለማቅረብ ይወዳል። በበኩላችን ክቡርነትዎን አጥብቀን የምንጠይቀው የእነዚህን ግለሰቦች ጥያቄ ቦታ እንዳይሰጡት ሲሆን ምክንያቱም የቀድሞው ንጉሠ ነገሥት ፓን አፍሪካኒስት ያልነበሩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን እንደ መራሄ መንግሥት በምሳሌነት ሊቀርቡ የማይችሉ በመሆናቸውም ጭምር ነው።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ለፓን አፍሪካኒዝም ያበረከቱት አስተዋፅዖ ሊገመገም የሚችለው፤
* የወቅቱን የኢትዮጵያን መንግሥት በሚቃወሙት ወይም በማይጨበጥ /አብስትራክት/ በሆነ ስሜት ስለ ንጉሡ በሚናገሩት፤
* ወይም በቦብ ማርሊ ዘፈኖች ወይም በሌሎች የራስታ ሬጌ ዘፋኞችና ወይም ኢትዮጵያዊው ዘፋኝ ቴዎድሮስ ካሳሁን ስለዘፈነላቸው፤
* ወይም በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በተመስረተበት ወቅት በኮንፍረንሱ ላይ ተናግረዋል የተባለውን በስሜት ላይ የተመሰረተ /ሴንቲሜንታል/ አገላለፅ አንድ ‘ስሜተኛ’ በቅርቡ እንዳቀረበው ዓይነት፤ - ሳይሆን
1. አፍሪካ በሙስና በተዘፈቀና አምባገነን በሆነ አገዛዝ ሥር በመማቀቋ ጥልቅ በሆነ ቀውስ ውስጥ ቆይታለች። ይህም በመሆኑ የምልዐተ አፍሪካውያንን ብሶት ሊያብስ የሚችል በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አስተዳደር ይኖራት ዘንድ ግፊት አመጣ። አዲሱን የአፍሪካ ትውልድም የህዝብ ብሶት በኮተኮተው በፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ ታንፆና ዴሞክራሲንና ነፃነትን ቀዳሚ ተልዕኮው አድርጎ መልካም አስተዳደርን በአፍሪካ ለማምጣት አነሳሳው።
አፍሪካ የራሷን ታሪክ ለመገንባቷም ምክንያቱ እንዲህ ያለውን አዲስ ትውልድ መኮትኮት በመቻሉ ነው። ለቀደምት የአፍሪካ መሪዎች በታሪክ የምንሰጣቸው ቦታ አይነተኛ ወሳኝነት አላቸው። ከዚህ በመነሳት ነው ለኢትዮጵያ የቀድሞ ንጉሠ ነገሥት የሚደረገውን ውዳሴ በጥብቅ የምንቃወመው።
ማንኛውም ለፓን አፍሪካኒዝም አስተዋፅዖ ያደረገ ሊመዘን የሚገባው ግለሰቡ ለፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ እድገት ባበረከተው አስተዋፅዖ ወይም አፍሪካን ከኮሎኒያሊዝም ነፃ ለማውጣትና በአህጉሪቷ ውስጥ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊና ነፃ የአስተዳደር መንገድ ለማምጣትና ፓን አፍሪካኒዝምን ለማራመድ ባደረጉት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ነው።
ከዚህ አኳያ ሃይለ ሥላሴና መንግሥታቸው ሌሎች ነፃ የአፍሪካ መንግሥታት በወቅቱ ካበረከተቱ የተለየ አንዳችም ያበረከቱት አስተዋፅዖ የለም። ኬንያ ከእንግሊዝ ኮሎኒያሊስቶች ጋር በምትዋጋበት ወቅት ንጉሡ ለኬኒያታ ቤተሰቦች ያደረጉት ርዳታም ሆነ ወይም ኒልሰን ማንዴላ ከመታሰራቸው በፊት የሰጡዋቸው ወታደራዊ ሥልጠና ከሌሎች የአፍሪካ መንግሥታት አስተዋፅዖ የተለዩ አልነበሩም።
በግንባር የሚገኙት የደቡብ አፍሪካ አዋሳኝ ሀገራት ግን በአፓርታይዱ መንግሥት ከመጠቃት ጀምሮ የበለጠ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ታንዛኒያና ሞዛምቢክ ተጠቅተዋል። በተለይ ሞዛምቢክ ተደጋጋሚ የሆነ ከአየር የቦንብ ድብደባ ደርሶባታል። የሀገሪቱን /የሞዛምቢክ/ ፕሬዚዳንት የያዘው አይሮፕላን ተመትቶ ፕሬዚዳንቱም ሳሞራ ማሼል ተገድለዋል። (ስለ መታሰቢያ ሃውልት ስናነሳ፤ ለፓን አፍሪካኒዝም የቆሙትና ራሳቸውን የሰዉት፤ ዕውነተኞቹ የአፍሪካ ነፃ አውጪ ጀግኖች የሆኑት ሳሞራ ሚሽል፤ ኤድዋርዶ ሞንደሌን፤ አሚልካል ካብራል፤ ፓትሪክ ሉሙምባ ናቸው። /ከሃይለ ሥላሴ ይልቅ/ ከንኩሩማ ጎን ሀውልቶቻቸው ሊቆሙላቸው የሚገባ እነዚህ ናቸው)
2. በሁለተኛው ሚሊኒየም መግቢያ ላይ ቢቢሲ ለአፍሪካ አድማጮቹ “አፍሪካዊ የሚለኒየሙ ሰው ማን ነው?” በሚል ላቀረበው ጥያቄ የአብዛኞቹ ድምፅ ኳሚ ኑኩሩማ የሚል ሲሆን በሁለተኝነት የተጠቀሱት ኒልሰን ማንዴላ ናቸው።
ይህ የሚያመለክተው እነዚህ ሁለት መሪዎች ለአፍሪካ ነፃነትና ለፓን አፍሪካኒዝም ያበረከቱትን ጉልህ አስተዋፅዖ ብቻ ሳይሆን በአርአያነትም በተጫወቱት ሚና ነው “አፍሪካዊ የሚለኒየም ሰው” የተባሉት። እንግዲህ አፍሪካውያን ለአፍሪካ አስተዋፅዖ ያበረከቱትን መሪዎቻቸውን የሚያስቧቸው ከዚህ አኳያ ነው።
3. ሃሳብን ከማመንጨትና ለአፍሪካ ነፃነት ቀጥተኛ አስተዋፅዖ ከማድረግ በተጨማሪ ሌላው ወሳኝ ሚዛን መሪው በገዛ ሀገሩ ውስጥ በሚያካሂደው የአስተዳደር ዘይቤ/ሚና ነው።
በሀገራቸው ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ብሄረሰቦች ላይ ያላቸው ፖሊሲ ምንድን ነው? በቅኝ አገዛዝ ኢሰብዓዊ ግፍ ለደረሰባቸው ጥቁር አፍሪካውያን ፓን አፍሪካኒዝም የማንነታቸው መለያ የሆነና በውስጣቸው የሰረፀ አመለካከት ነው። ጥቁርነቱን የማይቀበል ማንም ፓን አፍሪካኒስት ሊሆን አይችልም። በዚህ ረገድ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሪኮርድ በአጭሩ የሚዘገንን ነው ማለት ይሻላል።
በድንበር አካባቢ የሚገኙ የኒሎቲክ እና የባንቱ ጎሳዎች በንጉሡ አስተዳደር ሥር በንጉሡ በራሳቸው፤ በመኳንንቱና በፊውዳል ባላባቶች በግዳጅ እየታፈኑ በባርነት እንዲያገለግሏቸው ተደርገዋል። ከባርነታቸውም እንዳያመልጡ አብዛኛዎቹን ወንዶች ቋንጃቸውን ቆርጠዋቸዋል። ኢትዮጵያ በዚሁ የባርያ አስተዳደርዋ የተነሳ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል ለመሆን ከባድ ፈተና ገጥሟት ነበር።
ከጦርነቱ በኋላ ንጉሡ እስከ ወረዱበት 1974 የባርያ ባለቤትነት ሥርዐት በኢትዮጵያ ነበር። የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሥ ባርነትን ለማስወገድ ቅንጣት ታህል ያደረጉት አስተዋፅዖ አልነበረም። እንደውም በተቃራኒው ቀንደኛ ወይንም ዋና ባርያ አሳዳሪ ነበሩ።
በሁለተኛም ደረጃ በንጉሡ ሥር የነበሩ መኳንንት ራሳቸውን እንደ አፍሪካውያን አይቆጥሩም ነበር። አፍሪካዊ መሆን ተቀባይነት ያገኘው ኦኤዩ በሚመሰረትበት ወቅት ነበር። ነገር ግን “ጥቁርነት” /ጥቁር መሆን/ ከቶም ተቀባይነት አግኝቶ አያውቅም። ከዚህ አንፃር በ1967 ንጉሡ ጃማይካን በጎበኙበት ወቅት “እኛ ኢትዮጵያውያን ጥቁር አይደለንም” ማለታቸው የሚያስገርም አልነበረም።
በአንድ በተወሰነ ወቅት የሚገኝ የአንድ የተወሰነ ማህበረሰብ አስተሳሰብ የገዢው መደብ አስተሳሰብም ጭምር ነው። ይህም ማንኛውንም በትምክህት ላይ የተመሰረተ አፍራሽ አስተሳሰብን ያካትታል። እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች በጊዜ ካልተቀጩ ለረዥም ወቅት ሊቆዩ ይችላሉ። ይህ “ጥቁር አይደለንም” የሚለው አስተሳሰብ ዛሬም ቢሆን በኢትዮጵያውያን ውስጥ በተለይ ጎልቶ ይንፀባረቃል። የኒሎቲክንና የባንቱን አፍሪካውያን ጥቁሮች እያሉ በሚጠሩት በተለይም በዲያስፖራ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን መኸል “ጥቁር ያለመሆን” ጎልቶ ይታያል። እነዚህ ሊካዱ የማይቻሉና በቀላሉ ማስረጃም ሊቀርብባቸው የሚችሉ ዕውነቶች ናቸው።
በሶስተኛም ደረጃ የቀድሞው ንጉሥ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ብሄረሰቦች ላይ ከአማራው በቀር የነበራቸውን ፖሊሲ መመልከት ይቻላል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማራ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከኢኮኖሚው የተገለሉና መድልዖ ይደረግባቸውም ነበር። መሬታቸውን በመሬት ከበርቴዎች ተዘርፈው እንደ ሁለተኛ ዜጋ ይቆጠራሉ።
ይህን አድራጎት ተቃውመው ያመፁ ሁሉ፤ ለምሳሌ ትግራይ (1943)፤ ኤርትራ (1961-1974)፤ ኦጋዴን (1960-1974)፤ ባሌ (1967)፤ ሲዳሞና በሌሎችም ቦታዎች ያለ አንዳች ርህራሄ ተጨፍጭፈዋል። የቀድሞው ንጉሥ የክብር ዘበኞች በዲሴምበር 29 ቀን ዩኒቨርሲቲ በተሰበሰበው ተማሪ ላይ ተኩስ ከፍተዋል። ይህም የሆነው ቀደም ባለው ቀን በንጉሡ የምሥጢር ፖሊስ የተገደሉትን መሪዎቻቸውን ለማሰብ እንደተሰበሰቡ ነበር።
ጨቋኙ የሃይለ ሥላሴ መንግሥት የሠራተኛ ማህበራትንና የተማሪዎችን መሪዎች ያፍን ነበር። የሠራተኛው ማህበር መሪ አበራ ገሙ እና የተማሪዎች መሪ ጥላሁን ግዛውን የመሳሰሉት በቀን ተገድለዋል። (ጥላሁን ግዛው የፓን አፍሪካኒዝም ዋና አቀንቃኝ /ቻምፒዮን/ ፓን አፍሪካኒስት ነበር። የኢያን ስሚዝን የተናጥል ነፃነት እወጃን በመቃወም በተወጣው ሰልፍ ላይ በፖሊስ ጥይት ተመቷል። በ1969 /እኣአ/ ለደቡብ አፍሪካና ለዝንባቡዌ ህዝብ ትግል የድጋፍ አንድነትን ለማሳየት የተዘጋጀውን ሠልፍ ያቀናበረው ጥላሁን ግዛው ነበር)
ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞው ንጉሥ በጨካኝነታቸውና በአረመኔነታቸው በሚገባ ይታወቃሉ። በኤርትራና በኦጋዴን ከፈፀሙት ጭፍጨፋ ሌላ መንግሥታቸው እጅግ ሰቅጣጭ የሆነ የወንጀል ሥራ በመፈፀምም ይታወቃል። የገጠር ነዋሪ ገበሬዎችንና ዘላኖችን ጨምሮ መሬታቸውን ያለ ክፍያ በመውረስ፤ የፖለቲካና የህሊና ተቃዋሚዎችን በአረመኔ ፖሊሶች እጅ እንዲሰቃዩ በማድረግ የሚታወቅ መንግሥት ነበር። ንጉሡ የጥንቆላና የቃልቻ ተግባር አራማጅም ነበሩ።
ብሾፍቱ ሀይቅ ውስጥ ቆሪጥ በመባል ለሚታወቀው ጭራቅ መንፈስ ህፃናት ልጆችን ይገብሩ እንደነበር ይነገራል። በ1961 የተጨናገፈው የመፈንቅለ መንግሥት መሪ የነበረውን ግርማሜ ነዋይ አስከሬን ንጉሡ ራሳቸው አዝዘው በአደባባይ እንዲሰቀል አድርገዋል። ይህን ሁሉ ወንጀል ሲፈፅሙ ግን ምንም እንዳልፈፀሙ ሁሉ ርጋታና ግርማ ሞገስ የተላበሱ መስለው ለመታየት ይጥራሉ። ለክቡርነትዎ የንጉሡን ወንጀሎች ዘርዝረን ለማቅረብ የማንዘልቀው ጉዳይ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እንገልፃለን።
አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንደ ሃይለ ሥላሴና እንደ ኮሎኔል መንግሥቱ ኦቶክራት ነው ብለን እናምናለን። የኢትዮጵያ ህዝብ ለነፃነትና ለፍትህ የሚያደርገውን ትግል እናጨበጭብለታለን። የኢትዮጵያ ዲያስፖራም በዚህ ትግል ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዳለው እንገምታለን። ነገር ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ለተፈፀመው ፍትህ አልባነት በሌላ ፍትህ አልባ ትግል መተካት የሚሰራ ጉዳይ አይደለም።
ክቡር ሆይ! እኛ በአዲሱ የአፍሪካ ዩኒየን ፅ/ቤት ግቢ የኳሚ ኑክሩማ ሀውልት እንዲቆም በፅኑ እንደግፋለን። ነገር ግን የቀድሞው ንጉሥ ሃይለ ሥላሴ ሀውልት ከንኩሩማ ጋር ይቁም የሚለውን ጥያቄ ያለ አንዳች ማቅማማት ውድቅ ያደርጉት ዘንድ በጥብቅ እንጠይቃለን። ሌሎች የአፍሪካ ጀግኖች ሀውልታቸው በአፍሪካ ዩኒየን መቆም ካለበትም በኛ በኩል የምናቀርባቸው፤- ኒልሰን ማንዴላ፤ ፓትሪስ ሉሙምባ፤ አሚልካል ካብራል፤ ሳሞራ ሚሼልና ኤድዋርዶ ሞንደሌን ናቸው።
ከአክብሮት ጋር
አስራት ደፈርሳ፤ ሊቀመንበር
የኢትዮጵያ ፓን አፍሪካን ሶሳይቲ
አዲስ አበባ
(ሃይ ላይት የሆነው የኔ አፅንዖት ነው)
* * *
ይህን Africa: Say No to Haile Selassie Statue at AU የሚለውን ማመልከቻ ያነበብኩት allAfrica.com ከሚለው ድረ ገፅ ላይ ነው። የዚህ መፅሀፍ አቅራቢ ይህ አቤቱታ ወይም ፅሁፍ አንድም በራሳቸው በአቶ መለስ የተፃፈ አልያም ስማቸውን የገለፁት ሰው ፅፈው ያቀረቡትን ረቂቅ አቶ መለስ ተመልክተው ተጨማሪ ሀሳብም አክለው ያፀደቁትና በተባለው (የፈጠራ?) ድርጅት ስም እንዲላክ ያደረጉት ነው ብሎ በፅኑ ይጠረጥራል። ጥርጣሬውንም ያምንበታል፤ ምንም እንኳን አቶ መለስ ለመፃፋቸው ወይም የተፃፈውን አንብበው ለማፅደቃቸው በጥቁርና ነጭ ማስረጃ ማስደገፍ ባይችልም ቅሉ።
ከሁሉም በላይ ግን ህወሃት/ኢህአዴግ ከገጠር እስከ ከተማ የተቆጣጠረው ማንኛውም ድርጅት፤ ማህበር ወዘተ በየትኛውም መልኩ ቢሆን መንግሥታዊ በሆነ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከቶም የህወሃት/ኢህአዴግን ቡራኬ ሳያገኝ ብቻውን ራሱን ችሎ እንዲህ ያለ ማመልከቻ ለአህጉር ዐቀፍ ድርጅት ያቀርባል ብሎ ማሰብም ሆነ ማመን ከቶም አይቻልም። እንግዲህ ሊሆን የሚችለው ለሃያ ዓመታት የዘለቀው ሀወሃታዊ ሠይጣናዊ ድብብቆሽ…
“የኢትዮጵያ ፓን አፍሪካን ሶሳይቲ” በሚል ስም የወጣውን ፅሁፍ ያቀረቡት ሊቀመንበር የግል ኢሜል አድራሻቸውንም ሆነ ስልክ አላስቀመጡም። ወይንም የድርጅቱን አድራሻ ፖስታ ሳጥን ቁጥር ወይም ድረገፅ መጠሪያም አላስቀመጡም። ቢሮም ካላቸው የት እንደሆን አልተገለፀም። ስለ “ኢትዮጵያ ፓን አፍሪካን ሶሳይቲ” ለማወቅ በተለያዩ መቀናጆዎች እየተየብኩ በጉግል ፈልግ ለማግኘት ጥሬያለሁ፤ ዞሮ፤ ዞሮ የሚሄደው ‘ኦል አፍሪካን’ ድረገፅ ላይ ወደተለጠፈው ፅሁፍ ብቻ ነበር።
የሀገርን ልዕልና እና የኢትዮጵያውያንን ክብር የሚጋፋ አህጉራዊና ዓለም ዐቀፋዊ አንደምታ ያለውን ውሳኔ ለማስወሰን ለአህጉራዊ ድርጅት ‘የግርማዊነታቸውንና የመንግሥታቸውን የወንጀል አይነቶች” ‘በኢትዮጵያውያን ፓን አፍሪካኒስቶች’ ሰም ዘርዝሮ የክስ አቤቱታ ያቀረበ ድርጅት፤ አህጉራዊና ዓለም ዐቀፋዊ ይዘት ካለው ፓን አፍሪካን ሶሳይቲ ጋር ራሱን አዳብሎም የሚጠራ፤ እንዴት ስለራሱ ዓላማና ግብ ሰለምግባሩም የሚገልፅ ድረ ገፅ እንኳን የለውም? እንዴት ሊቀመንበሩ ቢያንስ የኢሜል አድራሻ እንኳን የላቸውም?
...አዲስ አበባ ባህር ነው…አዲስ አበባ ውስጥ የት ቦታ ነው ይህ “የኢትዮጵያ ፓን አፍሪካን ሶሳይቲ’ የሚገኘውና ነው ሊቀመንበሩ በድፍኑ አድራሻቸውን አዲስ አበባ ያሉት?...ወይስ አዲስ አበባ ማለት አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ይሆን?...
“ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት” ይላል የአበው ዘመን አይሽሬው ብሂል። አሁን ማን ይሙት! ከቴዲ አፍሮ ዘፈኖች፤ ከቦብ ማርሊ ዜማዎች፤ ከራስታ ሬጌ ቢቶች፤ በዲያስፖራ ከሚገኙት ተቃዋሚዎች ጀምሮ ስለ ሃይለሥላሴ የሚዘፍኑትና የሚያቀነቅኑት ሁሉ መሰረት አልባ ስሜታውያን ብቻ ሳይሆኑ ገዢውን ፓርቲ በመጥላትም የተነሱ፤ ጥቁርነታቸውን የማይቀበሉ ፀረ ፓን አፍሪካኒስቶች ናቸው በማለት ስንት ገፅ የፃፉት “የኢትዮጵያ ፓን አፍሪካኒስት” ቁንጮ በሶስት መስመር “በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ኦቶክራት ነው…” ይላሉ፤ የተከበሩ ሚ/ር ኢራሰቱስ ምዌቼን ሲደልሉ። የመንግሥት አሽቃባጭ፤ ወይም የመንግሥት ወኪል ሳንሆን የራሳችን አቋምና ዕምነት ያለን ነን - ለማለትና፤ ደብዳቤው የአንድ ወገን የገዢው ፓርቲ አካል አይደለም ለማስባል።
ምናልባት የአፍሪካ ዩኒየን ተጠባባቂ ሊቀመንበርንና ሌሎችን ማጭበረበር ችለው ይሆናል አቶ አስራት (ወይስ አቶ መለስ?)፤ ግና ሃያ አንድ ዓመት ሙሉ የሚያውቃቸውን የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲህ ያለው ደብዳቤ ምንጩና ተልዕኮው አያጭበረብረውም።
ይህ ደብዳቤ አሳዛኝና የማንንም አመዛዛኝና ፍትሀዊ ህሊና ያለውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ክብር የሚነካና በብርቱም የሚያበሳጭ ነው። ደብዳቤው በተቃርኖ የተሞላ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጥላቻ፤ ቂም በቀለኝነትንና ብቀላን ዓላመው አድርጎ የተፃፈ ነው።
መቼም ሀገር ጋቢ አይደለም፤ አይጣፋም። አንዱን ጫፍ ከሌላው ጫፍ ማጋጨት/ ማሳሳም አይቻልም። ለመሆኑ የደቡብ አፍሪካው አፓርታይዳዊ መንግሥት ጎረቤት በሆኑት ሀገራት ላይ ኢያን ስሚዝ ቦንብ ስላዘነበ በኢትዮጵያም ላይ መዝነብ ነበረበት፤ ለደቡብ አፍሪካው ታጋይ ኒልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ ያደረገችውን አስተዋፅዖ ተገቢ የታሪክ ቦታ ለመስጠት? ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ እንደ ሳሞራ ሚሼል በኢያን ስሚዝ ቦንብ መሞት ነበረባቸው?
ለመሆኑ በሃይለ ሥላሴ መንግሥት ላይ የተዘረዘሩት ወንጀሎች በአቶ መለስ መንግሥት በእጥፍ ድርብ እየተካሄዱ አይደለምን? ጥያቄው የአሰተዳደርና የፍትህ ነው ወይስ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ዕውን መሆን ስለመቻሉና ኢትዮጵያም በአፍሪካ ለተካሄደው የነፃነት ትግል አስተዋፅዖ ስለማድረጓ? በሁለቱም ቢሆን ኢትዮጵያ በቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ በተመራው መንግሥት ከየትኛውም የአፍሪካ ሀገር ያልተናነሰ ወይም ላቅ ያለ ድርሻ አበርክታለች። (ከገፅ 243 - 269 ከተፃፈው ውስጥ ተነቀሰ)
እነሆ ያ ሁሉ አለፈና <ለሁሉም ጊዜ አለው> እንዲል መፅሀፉ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ሃይለ ሥላሴ ሀውልት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ውስጥ ኢትዮጵያዊ በሆነው መሪ ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ሥራቸው ክብርና ሞገስ አግኝቶ ሀውልታቸውም ለመቆም በቃ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ!!
የካቲት 2011/ ፌብሩዋሪ 2019
ሲድኒ አውስትራሊያ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ