የኢትዮጵያ በሽታ (ከጸሐፊ አቶ መስፍን ማሞ ተሰማ)
እንኳን ደህና መጡልኝ።
የኢትዮጵያ
በሽታ
መስፍን ማሞ ተሰማ
ሠላም ለናንተ ይሁን!
እንግዲህ ምን ይሻላል? ኢትዮጵያ ውስጥ
ሁሉም አጥሩን /ክልሉን እያጠበቀ አትድረሱብኝ ማለቱ ብቻ ሳይሆን እዛው ተወልደውና ከብደው ቤተሰብና ንብረት አፍርተው ለዘመናት
የኖሩትንም ከደርቡሽ ወይም ከጣልያን የመጡ ይመስል - ወራሪ፤ መጤ፤ ሰፋሪ - እየተባሉ ማቄን ጨርቄን ሳይሉ በአንድ ጀንበር ከነ
እንቦቃቅላ ህፃናት ጭምር <የመሬት ባለቤት ነን> ባዮች (ክልላዊ መንግሥታትና ራስ ገዝ ቡድኖች) በግፍ ሲያባርሩና ሲገድሉ
<ለተፈናቃይ ሀገር በቀል ስደተኞች> በወቅቱና በተገቢው ሁኔታ የሚደርስላቸውም ሆነ በተግባር የሚቆረቆርላቸው <መንግሥት>
አለመኖር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሄዱ እጅግ አስጨናቂ ክስተት ሆኗል።
<ባለ መሬት ነን> ባዮቹንም
ሃይ የሚል የመንግሥት ሃላፊ የለም። እንደውም በግፍና ያለ ህግ የተፈናቀሉትን <ለኛ ፖለቲካ በሚጠቅም መልኩ አስፍረናቸዋል>
ያሉ <እንደ ሃይማኖት እናምናቸው የጀመርናቸው የለውጡ <ፊታውራሪዎች ኢትዮጵያዊ መሪዎች> ሲናገሩ ከመስማትና ከማየት
በላይ ለሰማይም ለመሬትም የከበደ በደልና ሀጢያት ከቶ ከወዴት ሀገር አለ?
ይህ ሁሉ ሰቆቃ የሚፈፀመው ደግሞ የ<ህገ
መንግሥት> ሰነድ አይናችን ላይ እያወዛወዙና <ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው> እያሉን መሆኑ ነው። እንግዲህ <ህገ
መንግሥቱ> ለዘረኝነትና ለአፓርታይዳውያን መሳሪያነት የቆመ ጠበቃ ነው ብንል ሀሰት ይሆናልን?!
<ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች>
የሚለው ቅጥ አምባሩ የጠፋና ትርጉሙም ፍንትው ብሎ በማይታወቅ <አብዮታዊ ዲሞክራሲ> ንድፈ ሀሳብ አጥር ማጠር/ክልል መመስረት
ኢህአዴግ የፈቀደው መብት ነው ተብሏል።
እነሆ አጥር ማጥበቁ፤ አዳዲስ አጥሮችም
መፍጠሩ ከትላንት ዛሬ ብሷል። ብዙ ማለት ሳያስፈልግ እነ ጃዋርና ቡድኖቹ ለውጡ በተከሰተ በዚህ አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ያደረሱትንና
እያደረሱ ያሉትን ብሄራዊ ቀውስ አመዛዛኝ ህሊና ያለው ኢትዮጵያዊ
ሁሉ በገሀድ የሚመለከተው ነው፤ እነሱን የሚከላከላቸው ሀገራዊ ሃላፊነት ያለው ሃይል ግን እስካሁን አልተገኘም። ይህ
የሚጎመዝዝ ገሀድ የወጣ ሀቅ ነው!!
{አብያዊውን መንግሥት ወይም
<ቲሙን> ደግፈን እንደ ችቦ የተደመርነው ከድጡ ወደ ማጡ ተገፋፍተንና ገፍተን ሌሎችን ለማስመጥ አይደለም፤ ተደጋግፈንና
ተባብረን ወደ ብርሃን ለመውጣት እንጂ! ለመሆኑ ምን በድለን ምንስ አጥፍተን ነው <እግዜር የላከልን ሙሴ> ያልናቸው አውላላ
ሜዳ ላይ አስጥተውን <የኔ> የሚሉትን ማህበረሰብ አቅፈው <እኛን> ያገለሉን? <ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው>
የተባልነው <ዶሮን ሲያታልሏት …> እንዲሉ ነበር ማለት
ነው?}
በቅርቡ <የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና
ህዝቦች> ጠቅላይ አጥር/ክልል ፈርሶ የብዙ ብሄረሰቦች አጥር ለማጠር ችካሎቹ እየተጠረቡ ነው። ይህንን ሂደት አሻፈረኝ የሚል
ካለ ለምሳሌ <ራስ ገዝ> የሆነው <እጄቴ> የተባለው <ጊዜ ወለድ> ቡድን እጁ እስከ የት እንደሚደርስ
እያሳየ ይገኛል - የሲዳማን ክልል/አጥር በአስቸኴይ በማካለል ጉዳይ።
ህገ መንግሥቱም አረንጔዴ መብራቱን
አብርቶለታልና! የኢህአዴግ መንግሥት ህገ መንግሥት ገና ብዙ አጥሮችን ይወልዳል። ይህ ሁሉ በየክልሉ የሚታየው የባንዲራ መዓት ገና
ብዙ <ጊዜ ወለድ> ባንዲራዎችን ይፈለፍላል።
ከሀገራዊውና ብሄራዊው ሠንደቅ ዓላማ
በላይ <ጊዜ ወለዱ> የክልል ባንዲራ ክብርና ሟች አለው - ለብሄር ብሄረሰብና ህዝብ ማንነቱ የሚሞትበትና ወንድሙን የሚገድልበት
<ጊዜ ወለድ> ታሪክና ዓርማ!!
አዲስ አበባን በተመለከተ የቁም ስቅል
እያሳየ የሚገኘው ኦነግና/ኦዲፒ በጣምራ መሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያ የጠለቀችበትን
የዘረኞች አረንቌ አሳሳቢነት ያሳያል። <ፊንፊኔ> የዚህ ደዌ ማቀንቀኛ ነው።
<በረራም> እንዲሁ። በየአቅጣጫው
እንደ ሰደድ እሳት የተስፋፋው ደዌ ዝርዝር ያታክታል። የበሽተኞቹ
ማንነት ደግሞ ተስፋ ያስቆርጣል። ችግሩን ጠቅልሎ መቀሌ ለመሸገው ህወሃት ብቻ ለማሸከም የሚቻልበት ሁኔታ የለም። <የለውጥ
አራማጁ> እያደር ራሱን እየገለጠ ነውና!
{አብያዊውን መንግሥት ገና በሌሊት
ደግፈነው ከጎኑ የቆምነው ዘረኝነትንና የአንድ ማህበረሰብን የበላይነት አብረነው ለመከላከልና ብሄራዊ ማንነትን ለማስቀደም እንጂ
ሀገራዊ ሠንደቅ ዓላማ የያዘ በተደጋጋሚ እየታሰረና <በዘራፊነት> እየተወነጀለ ገጀራ የወይራ ዱላና የጋንግስተርች አካል
መጉጃ የሚስማር ጣውላ ይዞ የወጣ ጎጠኛ ቡድን/ማህበረሰብ በአደባባይ ፎክሮብንናና ዝቶብን ወደ ቤቱ የሚገባበት አስተዳደር እያደር እየገነነብን ሲመጣ ለማየት አልነበረም።
ዕውነቱን እንነጋገር ከተባለ እንኴን
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ አስራ ስምንት ባንኮች ተዘርፈው ይቅርና አንድም ባንክ እንኳን ቢሆን በደቡብ ወይ በሰሜን ወይም
በመላው ሀገሪቷ ለመንቀሳቀስ የሠላም ጥሪ ተቀብለው ከገቡት ተፎካካሪ/ተቃዋሚ ድርጅቶች መካከል በአንዱ ተዘርፎ ቢሆን ኖሮ መንግሥትና
መከላከያ በብርሃን ፍጥነት እንደሚዘምትበት ፀሀይ በምሥራቅ እንደ መውጣቷ ያለ ዕውነት ነው።
መንግሥት በራሱ ሚዲያ ሳይቀር ኦነግ
በ18 ባንኮች ላይ ዘረፋ መፈፀሙን በይፋ ተናግሮ ግን በተግባር እየሆነ ያለውን ፍጹም ዝምታ እዚህ ላይ ማንሳት ከንቱ ድካም ነው።
አብያዊውን መንግሥት ደግፈን የቆምነው እንዲህ ያለ ዘረፋና እብሪት ሲፈፀምና ምላሽ ሲያጣ እናያለን ብለን አልነበረም!!}
እንደ አሸን የፈላው ጎጠኛና ቀበሌኛ
እንዴት ሆኖ ነው ለኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማና ለኢትዮጵያዊነቱ የሚታገለውና መስዋዕትነትንም የሚከፍለው? ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በፌዴራሊዝም
መረብ የተያዘው ከኢትዮጵያዊነቱ በፊት የክልሉ/አጥሩ ቌንቌ ተናጋሪነቱን እንደ ዜግነት ወስዶ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ይረግጣል።
እንደ ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳ <ኢትዮጵያዊ
ማንነት የለም> ብለው በኢትዮጵያ ሰማይ ስር በጎጡ ሚዲያ የሚያስተምሩትን ይከተላል <አንገቱን በሜንጫ ነው> የሚለውን
እንደ ጃዋር ያሉትን ያወድሳል እንጂ እንደ ዳግማዊ ምኒልክ ወይም
ራስ ጎበና ያሉትን ብሄራዊ መሪዋች ስማቸውን እንኴን ለመጥራት እንደ ኮሶ ያንገፈግፈዋል። የየክልሉ መንግሥታትም ይህንኑ በአደባባይ
በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሲያበረታቱ ታይተዋል፤ የለውጡ <ሃዋርያ> የተባሉት ሳይቀሩ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም አባራሪ ሆኗል።
ከመሬቴ ልቀቅ ከሀገሬ ውጣ ባይ በዝቷል - ለምን? የኔን ቌንቌ ተናጋሪ አይደለህምና። እንግዲህ ለውጥ በመጣ በዚህ አንድ አመት
ብቻ ስንት ሚሊዮን ህዝብ ከቀዬውና እትብቱ ከተቀበረበት ተፈናቀለ? ስንት መቶ ሺህ ህዝብ መፈናቀሉንና ስቃዩን <የለውጡ ሃዋርያት>
ለፖለቲካ ፍጆታ ለዲሞግራፊ የበላይነት ተጠቀሙበት? እየተጠቀሙበትስ ነው?
እጅግ የሚገርመውና እጅግም ግራ የሚያጋባው <የለውጡ
ሃዋርያት> የተባሉት ቀዳሚ የሰብዐዊ መብት ጣሽ እየሆኑ መምጣታቸው ነው። የለውጡ አንዱ ግብ ግን የሰብዐዊ መብትን
ማስጠበቅ አልነበረምን?) እንግዲህ ለማን ነው አቤት የሚባለው? በየአቅጣጫው
የሚሰማውና የሚታየው ተስፋን የሚያለመልም አይደለም። ሁኔታው በሁለት አለቶች መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የመሆን ያህል ነው። ኢህአዴግ እስትንፋሱ በሆነው የቌንቌ
ፌዴራሊዝም አልደራደርም ብሏል።
የህገ መንግሥቱ ፌዴራሊዝም ደግሞ ለኢትዮጵያውያን የግፍ፤ የስቃይ፤ የመፈናቀልና የሠላም ማጣት ከሁሉም
በላይ የጎጥና ጎጠኞች ኢንኩቤተር መሆኑ በገሀድ እየታየ ስለ ምን የለውጡ ሃይላት <በፌዴራሊዝም አንደራደርም> ይላሉ?
ለውጡ የመጣው ለማን ወይም ለነማን ነው? ህገ መንግሥቱ ለኢትዮጵያ መዳኛዋ ሳይሆን መጥፊያዋ እየሆነ ነው።
በ1983 ዓ/ም በህወሃት/ኢህአዴግ
የዘር ልክፍት የተመታችው ኢትዮጵያ ዘንድሮ በኢህአዴግ/ኢህአዴግ በሽታዋ ጫፍ ላይ እየደረሰ ይገኛል።
ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ
እስከ ምዕራብ በመሃል እስከ አዲስ አበባ በለውጡ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ስንትና ስንት ቤቶች ፈርሰው ስንትና ስንት ሚሊዮናት አውላላ
ሜዳ ላይ ወድቀዋል?
የሚገርመው ደግሞ የዚህ ሰብዐዊ ሰቆቃ
ተዋናይ እንኴን ባይሆኑ ፖለቲካዊ ተጠቃሚ መሆናቸውን በአደባባይ የተናገሩት የለውጡ <ሙሴ> ከተባሉት መካከል መሆኑ የሀገራችንን
በሽታ ጥልቀት አስፈሪነት ያገዝፈዋል።
እና እንግዲህ ማንን እንመን? መንቀፍ
ለውጥ ማደናቀፍ ነው ይባላል። የምንወዳቸውን ወይም እንወዳቸው የነበሩትን ስህተታቸውን መናገርና በጊዜ እንዲታረሙ መጎትጎት ስለ
ፍቅር ተብሎ የሚደረግ እንጂ የጠሉትንማ ስለምን እንዲታረሙ መማለድ ያስፈልጋል?
አሁን ኢትዮጵያን የተጣባት የዘር ፌዴራሊዝም
ካንሰር ቀፎ አድርጎ እንዳይፈረክሳት አስጊ የሆነው ለውጡን ከተቀላቀለው ወይም ከተደመረው ፅንፈኛ ሁሉ ጎራ በገሀድና በስውር የሚካሄደው
እኩይ ተግባር ነው። ፅንፈኞቹ ደግሞ በገሀድም በስውርም ሀያል የሆነ ከለላ እንዳላቸው የነገሮች ሂደት በራሳቸው ምስክር ናቸው።
ጎበዝ አለን ስንል ወዳለመኖር እየሄድን ነው እንዴ?
አብያዊው መንግሥት ሆይ! ኢህአዴግን
ስንታገል ኖረን ቃልህን ሰምተንና ጅማሮህን ተመልክተን አንተንና <ቲምህን> አምነንና እጃችንን ሰጥተን ኢህአዴግን ደገፍን።
<የለውጡ ቲም> የተባለው <ቲም> ግን ለለውጥ ስለመኖሩ እርግጠኞች መሆን አልቻልንም።
ከ<ቲሙ> መኻል
<ቲም> ያልሆኑ አይተናልና። አሁን ላይ ግራ ተጋብተናልና ምን ይሻላል? ማንን አምነን ከነማን ጋር እንራመድ? በርግጠኝነትስ
ወዴት እየሄድን ነው?
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቃት!
መጋቢት 2011 (ማርች 2019)
ሲድኒ አውስትራሊያ
mmtessema@gmail.com
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ