ሰላሞች የተጎዳውን መንፈሳችን አከሙለን። ይባረኩ!

እንኳን ደህና መጡልኝ።

ላሞ!
„ከቸር ሰው ጋር ሆነህ ቸር ሆነህ ትገኛለህ“
መዝሙር ፲፯ ቁጥር ፳፭
ከሥርጉተ©ሥላሴ
Sergute©Selassie
06.03.2019
ከእመ ዝምታ - ሲዊዘርላንድ።
·         መነሻዬ።



መጣሁላችሁ ውዶቼ? እንዴት አላችሁልኝ። ስለ ሰላም ትርጉም ያለው ተግባር እንዲህ በኢትዮጵያ ህብራዊት ከተማ በነበረችው አዋሳ የሰላም ሐዋርያት ፈጠሙ። እሰቡ „በነበረችው“ ነው ያልኩት። አሁን ኦነጋውያኑ አዲስ የሰላ ቢላዋ ይዘው ደግሞ በአቶ ሌንጮ ለታ ፊታውራሪነት እዬሸነሸኗት ነው። መንፈሷን እያወኩት ነው አዋሳን፤ በሲዳማኛ ዜማ።

የሆነ ሆኖ ዝርዝሩን ከጉዳዩ እንብርት ከፋና ቴሌቪዥን ዝግጅት እንድታዳምጡ በትህትና ጋብዤ እኔ ስለተሰማኝ ትንሽ ወግ ቢጤ ላዋጣ።

ሰላም የፋሺን ፌስቲቫል በሀዋሳ

 „ሰላም“ ደስ ይላል። ይማርካል። ቢጠጣም፤ ቢበላም፤ በአፍ በአፍ በጉርሻ ቢያጣደፍም ተፈቅዶለት ነገረ ሰላም ሲፈጠር ታጥቦ ስለሆነ የተፈጠረው አይሰለችም - ለአደለው።

እኮ ሰላም ድንቅ ነገር። የሰላም ሚኒስተር በማቋቋምም ከዓለም የመጀመሪያ ሆነናል። ይህን ስል መዋቅራዊ ይዘቱን ሳይሆን „የሰላም ሚኒስተር“ የሚለውን ስንኙ መደፈሩን ማለቴ ነው። አዕመደ ማዋለ ምኸዋር ቃሉ ራሱ እንዲሆን መታሰቡ፤ መታጨቱ ድንቅ ነው። መዋቅራዊ ይዘቱማ የታጨቀ ነው። በርካታ ጉዳዮች ተነባብረው ካልልክ ተወጥሮ በአንድ ሚ/ር ሥር ነው የወደቀው። 

ነገር ግን „ሰላም“ የሚለውን ሃይለ ቃል እንዲህ አጉልቶ በማውጣት አረገድ ግን ዓለምን ሊያስተምር የሚችል ትልቅ ተምሳሌነት ተፈጥሟል። ቃል ሃይል አለውና።

የሰላም ሚ/ሯ ደግሞ አንስት መሆናቸው ሌላው ልባም ነገር ነው። መከራ በግራ በቀኝ በሚንጣት፤ በቁልል የፖለቲካ ሊሂቃን ኢጎ በምትታመስ አገር ውስጥ ሆኖ ያን ሃላፊነት ለመወጣት ከባድ ቢሆንም ራሱ ቃሉን በሚ/ር ደረጃ ማውጣት፤ ከፍ ለማድረግ መቻል መልካም ጅምር ነው። ቃሉ „ሰላም“ ሚኒሰተር ሲሆን። ተዚህ አንጻር ነው ሊተረጎም ሊተነበኝ ሊመሳጣር የሚገባው ውጥኑ።

ከቃሉ ጋር ያሉ ሁነቶች፤ ለቃሉ ተፈፃሚነት ግን ምቹ ሁኔታ ፈጣሪ አይመስሉኝም እንጂ እኔ እንዲያውም የፍቅር ሚ/ር ሁሉ እንዲኖር ምኞቴ ነው። መቻቻል፤ ማመን፤ መታመን፤ መታገስ፤ እውቅና፤ ፍቅር፤ ሰላም፤ ቁርጠኝነት፤ መድመጥ፤ መቀበል፤ መስጠት፤ ወዘተ የሚሉ ዩንቨርስቲዎች ኮሌጆች በዚህ ሥም ዓለም እንዲኖራት ሁሉ አሳስቢያለሁኝ  በ2015 ይህን ጥያቄ ጠይቄለሁኝም። ግራጫማዋ ዓለም ቁሳዊ ወይንም ማሽናዊ መሆኗ ዕለት ተለት ስለሚያሰጋኝ። ሃይማኖታዊ ክረቱም፤ የፖፒሊስትነት ክረቱም እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ።

ስለዚህ እራሱ „ሰላም“ ቢሮም ሚ/ር ሲኖረው ጅምሩ ወሸኔ ነው ማለፊያ ያማረበት። ውጥን ምንጊዜም ድፈረትን ይጠይቃል። ድፍረትን ብቻ ሳይሆን መልካም ነገር ለማግሥት ለማወረስ ቁርጠኝነትን በጥበብ ይጠይቃል። ዛሬ ተዳብሎም ይሁን ታጭቆ ቃሉ ቢታይም በተልዕኮው እና በሰላም ፍልስፍና ሥር ያሉ ንጥር ነገሮች ብቻ የሚስተናገዱበት ሊሆን ይችላል ወደፊት። ጥርጊያ መንገዱ ነው ፋይዳው እንደማለት።

ስለሆነም በዚህ ሥም ያለው ፖለቲካዊ ትርፍና ኪሳራው፤ ብልጥነት እና ብልህነት፤ ጥበብ እና ተስፋ ሲታሰብ በመጀመሩ ሚዛን የደፋ አክብሮት አለኝ እኔ በግሌ። ግን ሰላም በዓዋጅ አይገኝም። ሰላም በህሊና እጥቦሽ የሚገኝ ቁምነገር ነው።

·       የሰላም ጮራ … ህብራዊ ቀለማቱ።  

ሰላም ውብ ነገር የሁሉም ነፍስ እንሳሰትን ዕጽዋትን ጨምሮ ጤና ያለው ህሊና ምኞታዊ የተቃና ቃናዊ ተስፋ ነው። ሰላም መኖር ነው። ሰላም ነፍስም ነው ነባቢተ - ቅኔ ነው። ሰላም ሥነ - ህይወት ነው፤ ትንፋሽ። ሰላም ብሩኽ ነው ዝልቅ በር። ሰላም ፍቅር ነው አብሮነት። ሰላም ትልም ነው መዳረሻ የትርታ ቀጣይነት አብሳሪ እርግብዬ። ሰላም ማሳ ነው ምርታማ ሰብል ፍሬዘር። ግን በማን? እንዴት?

44 ዓመት ሙሉ በጦርነት ነጋሪት ፍልስፍና የኖረው አንጋፋው የዞግ ድርጅት ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እያሰናዳ ነው። የጉለሌው ኦነግም እንዲሁ። የኢትዮጵያም መንግስት ለአሱ አልመሰለውም መሰል በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ ደፋ ቀና ይላል። እስቲ ይቅናው።

በሌላ በኩል የብአዴን የሰሞናቱ ዝግና ይፋዊ ስብሰባን አስምልከቶም ስለሰላም ዘመረ ግርባው ብአዴን ብሎ ፌድራል መንግሥቱ ያለ የሌለውን ሚደያ ሁሉ አሰለፎ ያን ማህሌት ቆሞ አድረለት አሁን ቅዳሴ ገብቷል ኦዴፓ። 

የኢንደስትሪ ሚ/ር ብሎ ክብር በሰጣቸው ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ እግዚአብሄር ያን ያህል ፉከራ ግን ሽልማት ያዘጋጀ ይመስላል ኦዴፓ። ለግርባው ብአዴን ደግሞ በይፋ በታወጀ ጦርነትን ትካሽህን አስማምተህ የህዝብህ ሥነ - ልቦና አዝለህ፤ እዬተቀጠቀጠ ዝቅ ብለህ እንደለመደበህ የሚሰጠህን ከጌቶች አሜን! ብለህ ተገዛ ነው የሚለው የአብይ የለማ ዘመን። ሎሌ ሲገኝ በሁለም ዘርፍ … ሲያገጥም...  ቢሆንማ ማን እንደ ሰላም።

ሰላምን የመሰለ ጣዕሙም፤ ማዕዛውም፤ ጠረኑም ሁለመናው ያማረ እና የሰመረ ምን ነበር። ብቻ ህወሃት እንዳይከፋ የኦዴፓው ፌድራል መንግሥት እራሱ ሰረጋላ ያሰለፈለት ስለሆኑ በትናነቱ የዜና ዕወጃ ተረጋግጧል። ቆፍጠን ማለት ተስኖታል። ወይ መጠን አልባው የ እኛው ምስጋናውና ውደሴው አድክሞታል።

በማስታመም የሚሆን ከሆነ ይታያል። ሰላም ቅን ልቦናን እንጂ መታበይ ሃራሙ ነው። ሰላም የተጠረገ ህሊናን እንጂ ያጎረፈ መነፍስ ክፍሉ አይደለም። ዳሩ ሲደፈር ማህሉ ዳር መሆኑን ጠፍቶት እንዳንል ሙያውም ሳይንሱም መኮነንቱም ለጠ/ሚር አብይ አህመድ ፋቲክ ይጠፋዋል ሊባል አይችልም። 

የደህንነቱንም ተግባር ቢሆን ግራቀኙ ሙያው ስላላቸው ይጠፋቸዋል አይባልም። ብቻ የሃይል አሰላለፉ ዘብጦ ያው የለመደበት ግርባው ብአዴን ተጫን ካልተባለ በስተቀር። በድርብ ያን ክልል ሰቅዞ የኦነጋውያን ፍላጎት በይበልጥ ለማደላደል የትንፋሽ መሰብሰቢያ ጊዜ ካልተሰላ በስተቀረ የህወሃት ጦርነት በውስጥም የውስጥ አርበኞችን ሌት እና ቀን እዬተጋ እንደሆነ ማንም በፖለቲካ ዓለም ለኖረ ብልህ ሰው የሚጣፋ አይደለም።

 ውሉ ያልተገኘው ስውሩ መንግሥት እና ህወሃት የውል ሰነድ አንቀፃት ነው ያልተለዩት። እርግጥ ነው አንዱ አንቀጽ ‚ቅማንት‘ ሌላው አንቀጽ ‚ሲዳማ‘ ስለመሆኑ በአንድም በሌላም መገመት ይቻላል … በዚህም አለም በሌላም አማራ ላይ መከራ እንደታቀደ፤ ያን መከራ ደግሞ ለጥ ብለህ ተቀበል እንደተባለ ያዬነው እና የሰማናው የሚዲያው ሽፋን ጥልቀት ጀባ ያለ ብልህነት አለ። ሌላው 90ሺህ ህዝብ ተፈቅዶ ነው የተፈናቀለው። ጫና ለብአዴን መፍጠር ስለሚፈለግ።

ከአዲስ አባባ ጭፍጨፋ እስከ 90ሺህ መፈናቀል ያለው ጠቀራማ ጉዞም ይህን ይገልጣል። እንደማስበው አዲሱ የለውጥ ሃይል ገና ከውጥኑ ነበር አማራን ለማደከም ሰፊ ቅኝት ይዞ የተንቀሳቀሰው። ጫናው እኮ ሌላ ቦታ የለም። ለዚህ ተጠያቂዎች ደግሞ ዶር አንባቸው መኮነን፤ ዶር ገዱ አንዳርጋቸው እና አቶ ደመቀ መኮነን ናቸው የእሺታ ማህበርተኞች።
ህዝቡን ለዳግም ጥቃት እያለዘዙ በአፍዝ አደንዝዝ ቅስቀሳ ያዛሉት። በሌላ በኩል ትልቁ ጋሬጣ ኣባ ገዳ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው። ይህ እስከ አሁን በዬትኛውም ሚዲያ ያልተደፈረ፤ በዬትኛውም የአማራ ሊሂቅ ያልተሰተዋለ ገዳይ ሃዲድ ነው።   

ያው የፈረደበት ህዝብ 90ሺህ ህዝቡን ወለል ላይ ተደፍቶ ሌላ ሚሊዮኖች ደግሞ አፈር ብሎ ተብሎ የተፈረደባቸው መሆኑን ያሳያል፤ የሰሞናቱ የህውሃት ጋሻ ጃግሬ የነበረው የብአዴን ጣምራ አንደበቶች አሉ ስለሚባለው ጉዳይ። አፈ ጉባኤዋም ሆኖ አንደበተ ብአዴን ሁለቱም ፕሮ ፋይላቸው ነፍሳቸው ከህወሃት ቧንቧነት ከረጢት ሥረ መሰረት ጋር የተዋዋለ ነውና።

ሰላም እኮ የአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሁለቱም ወገን ፍላጎት ሲሆን ነው ስኬታማ የሚሆነው። ብቻ ኦዴፓ ህወሃትን ስለሚፈራው ቁንጫኑን የሚያሳርፈው በፈሪው በሎሌው በብአዴን ላይ ነው። በሌላ በኩል አግልሎም አንገዋሎም በጣለው ብአዴን ላይ ቀጣይነት እንደማይኖር ስለሚያውቅ ፈጣሪውን ህወሃትን ማስከፈትም እንደ መርግ ከብዶታል ኦደፓ።

ጉዳዩ አገራዊ ሆኖ  በጎሪጥ እዬታዬ ያለው ፍጥጫ ባሊህ ባይ አጥቷል፤ ትንሽ  የአማራ መሬት ደግሞ ይቀጥቀጥ፤ ይንደድ፤ ይማገድ እስኪ እኔ ፋታ እንዳገኝም ይመስላል አውራው ፓርቲ ኦዴፓ ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው። ወይን ደግሞ አዲስ የቀለበት ውልም ከኖረስ? አይታወቅም። ፖለቲካ ርጉምም በሽተኛም ነውና።

ተፎካካሪ/ ተቃዋሚ/ ተቀናቃኝ የሚባሉት በዚህ ማህል ኩዴታ እግዜሩ ያውርድ ብለው ሱባኤ ገብተዋል። በሌላ በኩል አንደበታቸውን በጥቁር ፕላስተር ለጉመው ለሰባዕዊ መብት እንኳኝ መቆም ተስኗቸው እራሳቸውን በራሳቸው አስረው የካቴና ጎጆ ቀልብሰው ኩርኩም ብለው በዬሾጎሪያቸው ተቀምጠዋል። አቤት ወዴት ለ ኦዴፓ እያሉ ቢሮ ለቢሮ ደጅ ጥናት እያደረጉ ... ትንንሽ ብጥቅጣቂ ሹመቶችን በመለቃቀም ... 

ይልቅ ባለጊዜው አባ ገዳ ጃዋር መሃመድ 100ሚሊዮኑን ህዝብ አስርድንል፤ አስፈራራልን እዬተባለ በጠበቂ ተኮፍሶ በሚዲያ ታጅቦ የልቡን ሽቃባት ይለዋል - ይለዋል - ይለዋል … ያቀረሻል … እንዲህ ነው ሰላም ማለት የህዝብን ሥነ - ልቦና በህግ አስደግፎ በማሳወክ … በማሳመስ፤ በማስተራመስ። 

ፖለቲከኞቻችን እንዲህ ለሰላም ጉዳይ ባይሰጣቸውም የእኔ ባይሉትም ግን  ዲዛይነር ሊዲያ አንተነህ ግን አዋሳ ላይ ቅልጥ ያለ የሰላም አውደ የፋሽን ትርኢት ላይ ነበረች ሰው እንሁንም ትላለች። 

እጅግ ድንቅ የሆኑ ወጣት ዲዛይነሮች ሙሉ አቅማቸውና ሙሉ መንፈሳቸውን ያፈሰሱበት የሞድ ትዕይንትን በሰላም ውስጥ ሆነው ነው። እራሳቸው ሰላሞች ናቸው ለእኔ። እኔ በአድናቆትም በአክብሮትም ነው የተከታተልኩት። 

በብዙ ሁኔታ የመሰከርንለት፤ በብዙ ሁኔታ ተስፋ ያደርነገው የትናንቱ ደም መላሽ የዛሬው ደግሞ ሌላ የዶር ለማ መገርሳ እምነትን፤ መታመንን፤ ቃልን ደረማምሶ ሲያፈስበን ከሰነባበተው ማዕት፤ የበረዶ ኩርኩምም፤ የመበረቅ እርግጫ፤ የነጎድጓድ ፍጥጫ ትንሽ ፋታ ተገኜ … እናም ተመስገን አለች ነፍሴ … 

·       ቢጤ …

እኔ ሞድ ማዬት አንዱ ሆቢዬ ነው። በልጅነት እናቴ ወደዛ እንዳዘነብል ፍላጎት ነበራት። አረማመድ በመደበኛ ታስተምረኝ ነበር። ያን ጊዜ ቀለሜም ቅርጼም የጉድ ነበር። ከዛ ሳድግ ልብስ ሳሰፋ የካታሎግ ደንበኛ ሆንኩኝ።

ኢሠፓ እያለሁ ልብሱ ካኪ ነበር፤ እናላችሁ በሞድ ነበር የሚሰፋው። ከዛ በፊትም ተማሪ በነበርኩበት ጊዜም በሻለቃ መላኩ ተፈራ ትእዛዝ ካኪ ነበር ልብሳችን እና በውስጥ የሆነች ነገር ትታከል ነበር፤ ፊት ለፊት ቅዷ ሰፋ በማድረግ ትንሽ ዩኒፎርሟን ደመቅ የምታደርግ ቲ ሸርት ነገረ ትታከል ነበር።

እዚህ ውጭ ስወጣም የፋሽን ትርኢቶች በመደበኛ ነው እመከታተለው። በሁለት ምክንያት። አንደኛው ትውልድ ግንባታ ተኮር መንፈስ ስላለኝ፤ሲሆን ሁለተኛው ዲዛን ላይ ዝንባሌም ከልጅነት ጀምሮ ስላለኝ ነው። ሞድ እጅግ ነው እምወደው። እጅግም ነው እምዝናናበት። እግረ መንገዱንም ብዙም ነገር ነው እምማርበት። ዓይናፋር ባልሆን ውጭ እንደወጣሁ በቀጥታ ነበር ልቀላቀል እምችለው ኢንደስትሪውን የነበረው። የዛሬን አያድርገው እንጂ ቅርጹም ደሙም ነበረኝ።

ሞድ እኮ ጥበብ ነው። ላቅ ያለ የመኖር ጥበብ። ኑሮን የሚያበለጽግ፤ ኑሮን ፈታ የሚያደርግ። በቀለማት ውስጥ ሰናይ አለ። ቀለም ሐሴት ነው። በአለባበስ ውስጥ ውበት አለ፤ በአረማመድ ውስጥ ጌጥማ ሜሎዲ አለ። በሞድ ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌለው ደስታ እና ሰናይ አለ። እናም እኔ ለዚህ ኢንደስትሪ ፍቅር ምርኮኛ ነኝ። ለዚህም ነው ሥነ - ግጥሞቼ በሞድ የተሰሩት። የኑረዬ ጣዕምም በዚህ አቅጣጫ የተቀኜ ነው ... 

ባለፈው ሳምንት በአዋሳ ያዬሁት ይህ የሞድ ጅማሮ ብዙ ነገሮችን አቅፏል። የወደፊቷን ኢትዮጵያ የንድፍ አቅጣጫ አመላካችም ነው። አንዱ ቀለም የነበረው ጥቁር ሌዘር በነጭ ሸማ ነበር። የዚህ ባሌቧቷ ዲዘይነር ሊዲያ ተስፋዬ ነበረች። ጥቁር እና ነጭ የእኔ ቀለም ነው። እዚህ ጓደኞቼ ይህን ቀለም ሲዩ የሥርጉተ ቀለም ይሉታል። ነፍሴ ጥፍት እስኪል ድረስ ነው የምወደው።


በጥቁር እና በነጭ ቅንብር የሚፈጠረው ህብርነት ሚስጢር ነው። ዓለምን በዚህ ውስጥ ታነቡበታላችሁ፤ ዕውቀትን በዚህ ውስጥ ትተረጉሙበታላችሁ፤ ደረጃን በዚህ ውስጥ ታመሳጥሩበታላችሁ፤ ሥነ - ፍጥረትን መኖርና ማለፍን በአንክሮ በቅኝት ታሸበሽቡበታላችሁ። 

ውዶቼ ... በዚህ በሁለቱ ቀለማት ሥናዊ ህብረት ውስጥ ሀዘን እና ፍሰሃን ታስተውሉበታላችሁ፤ በመኖር ውስጥ ማለፍን በምን ባህላዊ ወግ እንደምናስተናገደውም እያላችሁ ግን የነገን የሥጋን ማብቂያ ትቃኙበታላችሁ። 

የመኖርን እና የሞትን ጥምር ደማዊ ዝምድናም ትበስሉበታላችሁ። የሁለቱ ቅንብር ልብንም መንፈሰንም ያስተዳድራል። መኖርን አሳምሮ ይተረጉማል። መኖር እንዳለም ማለፍ መኖሩን ያውጃል። ሁለቱን ቀለም ስትኖሩበትም ሞትን አትፈሩም።

ሰውነታችሁ፤ ህሊናችሁ ሥነ ልቦናችሁ ይለማመደዋል የመጨረሻዋን የህቅታ ስንብት። በሌላ በኩል በመኖር ውስጥ ያሉ ሃዘኖችን የእኔ ትሉታላችሁ። በፍጥረት የሚደረሰው መናቸውም ግፍ በውስጣችሁ ቤተኛ ይሆናል። 

ፍጥረት ስል ሰብዕ ብቻ አይደለም፤ ህይወት ያለውም የሌለውም ሁሉ ያገበኛል ትሉለታላችሁ። የተፈጥሮ ተቆርቋሪ ትሆናለችሁ።

የወንዞች ገላ ሲቆሽሽ እራሱ ውስጣችሁ ይሰቃያል፤ የተራሮች መደረመስ፤ የመሬት መሰነጣጠቅ ሁሉንም በባለቤትነት ስሜት ትታደሙበታላችሁ። ተፈጥሮኛ ትሆናላችሁ። ይህ የጥቁር እና የነጭ ቅንብር ለእኔ የሰጠኝ ትርጉም በጥልቀት ሳስበው ልዑል እግዚአብሄር ዓለምን የፈጠረበት ሚስጢርን ላቅ ባለ ሁኔታ ስለመሆኑ ይነግረኛል። 

በዚህ ላይ ጹሑፌ ከደረሳት ለዲዛዬነር ሊዲያ ሌዘሩን ከምትጠቀም የፈትል ጥቁር ብትጠቀም ከቅይጣዊ ተገዢነት ባህላዊ ጽድቅነትን ማጎለበት ስለሚቻል በጥቁር ሀር እና ክር በተሰሩ አገር በቀል ሸማዎች ለመጠቀም ብትሞክር መልካም ይሆናል ብዬ አስባለሁኝ። ወጥ የሆነ እኛነትንም ያጰጵሳል። 

ሌላው ጥልፍ ነው። ጥልፍ እና ጥለት ከቦታው ውጪ እንዴት ዓይነት ዕድምታ እንዳገናኛቸው በርቀት ያስጉዛችሁና ጥበብ እና እንጨት ጋር አዋዶ ውበት ሆኖ ነፍስ ዘርቶ ነፍስ ሰጥቶ ነፍስን አረካት።

በዚህም አንድ ጥበብ ቀርቦ ነበር። ለነገሩ ከዚህ መለመላውን የቆመ እንጨት ጌጥ ነው። መለመላውን ያለ ግንድ የቤት ውስጥ ልዩ ውበት ነው። ግንድ ቤት ውስጥ ተጋድሞ እሳት ሲንቀለቀል በዛ ውስጥ ደስታ ሲፈጠር፤ መኖር ሲያብብ ዲታዎች እርካታን ይጠበቡበታል። የሲወዝ አንድ ቴሌቪዥን እኩለ ሌሊት ላይ የዚህ ቋሚ ፕሮግራም አለው። 

እኛ ያላስተዋልነው የድህነት መኖር ተደርጎ የሚወሰደው ማገዶ እዚህ ደግሞ  በላንቃው የዲታዎች የመዝናኛ ማዕከል ነው … አሁን የ ኢትዮጵያ ዲዛይነሮች ጠረኑን ወደ ውበታዊነት ለመቀዬር አህዱ ብለዋል። መስቀል በ እንጨትም እንደሚሰራ ብቻ ሳይሆን በ እንጨት ወስጥ ያለ መዳንም እንደተጠበቀ ሆኖ ሚስጢሩ በሞድ ስልጣኔ ውስጥ እንጨት ያለውን ፋይዳ በዚህ ሞዳዊ ትዕይንት ቤተኛ ነበር ... 

ሌላ ምን አዬሁኝ? ሌላማ ያዬሁት በቃ ግንጥል የሆነ ግንጥል ጌጥ ነገር። በዚህ ውስጥ የ27 ዓመቷን አላዛሯን ኢትዮጵያ ታዮዋታላችሁ። 

እጅጌው አንዱ ያለው ሌላው የሌለው፤ ወገቡ የተጎረደ በአንድ አቅጣጫ፤ ወይንም ጭን ላይ የተገነጣጠለ ዝንጥል ነገር … አቤት እንዴት ይከፋል መለያዬት  …

ለዚህ ጎንደሬዎች ቅማንት እና አማራ እያሉ የሚከታከቱት ቢማሩበት መልካም ነው፤ ሌላው አማራ እና ትግራይ ክልል የጦርነት ጉሰማም ከዚህ ቢማር ብያለሁኝ … ምክንያቱም ተለያይተው አይለያዩምና።

በተረፈ በራሱ በህወሃት የደቡብ ብሄረሰብ ተብሎ የተሰዬመው ወደ 56 ብሄረሰቦችን ጨፈላልቆ ወደ ደቡብነት ብሄረሰብነት የለሰነው መከራ አሁን ደግሞ ኦዴፓ ከቀኙ የተማረውን ሦስቱን አጉልቶ ሲዳማ፤ ጉራጌ፤ ወላይታ በማለት ሌሎችን 53ቱን ደግሞ እንደ አዋዜ ለመደቋቆስ እንደ ፍጥርጥራቸው በተባለበት ቦታ ነው ትዕይንቱ የሚካሄደው።

አደራ ውዶቼ እንዴት እንደሚከፋ ልብ ብላችሁ አስተውሉት … አዋሳ ትንሿ ኢትዮጵያ ስትበተን ሌላ አዲስ አቅም ኦነጋውያን ያገኛሉ በኢትዮጵያዊነት ላይ ለማሳደም፤ በመንፈሰም ለማሳመጽ … አሁን እሩጫው ኢትዮጵያዊነትን በመጫን ያለ ሥነ ጉዞ ነው ያለው። ረቂቅ ነው ግን አጋዳሚው ወንበር ይኸው ነው።

… ይህን ለመታገል ነው እነዚህ ዕንቡጥ ዲዛይነሮች ይህን መሰል ውብ እጅግ ረቂቅ የሆነ በትርጉም የተባ መልዕክት እና ተልዕኮ ያነገበ ተግባር እዛው አድማ በተመታበት በአዋሳ በትንሿ ኢትዮጵያ የፈጸሙት … ዕዳ ነውና መከራው። ዕዳው ደግሞ ለእነሱ ነው። አሁን ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በአገሩ ተፈናቅሏል በዚህ አያያዝ የዛሬ ዓመት 6 ሚሊዮን ህዝብ በአገሩ በቀዩ ይፈናቀላል … መፈናቀሉ አላቆመመ ቀጥሏልና … ለጦርነት ዕወጃውም መፈናቀል ስለሚናፈቅ አጀንዳ አልሆነም በኦደፓ መንግሥት። 

ሌላው ያዬሁት መስታውትን በጥበብ ቤተኛ ለማድረግ በኢትዮጵያ የተጀመረው ጉዳይ ነው። የዛሬ ዓመት ተወናይት እና የፊልም ዳሪከተር ወ/ሮ መቅደስ ጸጋዬ የተመሸረችበት አገራዊ   ወዙን በጠበቀ አኳኋን በዚህ ጥበብ ክህሎት የሰከነ እንደነበረ አሰተውያለሁኝ። በዚህ የሞድ ትርኢትም ይህን ጅምር የተከተለች ወጣት እንዳለች አስተውያለሁኝ። በዚህ ላይም ከውሃማ መስታውት ጋር የሌሎችን ቀለማት ህብረት በመስታውት ወስጥ ቢታከል የበለጠ ጥበቡ ጎልቶ የመውጣት አቅሙ አንቱ ይሆናል ባይ ነኝ። አብሶ ዝንቅ ቀለሞች ... በወጥ ዲዛይን ... 

መስታወት በጥልቅ ትርጉም ራስን ማዬት፤ ራሰንም ማስተዋል፤ ራስን መገምገም፤ ራስን መመርምር፤ የራስን ጉድፍ በጥልቀት መግራት ነውም። በዚህ እረገድ መንገዱን እዬሳተ የሚገኘው ቲም ለማ ሥራዬ ብሎ ራሱን ለማዬት መስታውት ቢገዛ መልካም ነው።

በማስተባበል፤ በመሸንገል ጊዜውንም፤ ጉልበቱንም ለማቃጠል ካድሬዎችን አሰልፎ አታካች ማስተባበያውን ጋር ከሚዳክር። በውነቱ መስታውት የሚያስፈልገው ድርጅት ቢኖር ኦዴፓ ነው። ወይ ለይቶለት ኦነጋዊ ይሁን ወይ ለይቶለት ኢትዮጵያዊ ይሁን። በማህል ሰፋሪነት ኢትዮጵያን አያምሳት ስለሆነ። እራሱን ማዬት ተስኖት በስልጣን ሽውታ ነፍሱን አጥቶ ጥድፊያ ላይ ስለሚገኝ መስታወትም መግቻ ገመድም ቢገዛ መልካም ይሆናል። ለመማር ከፈቀደ።

እፍረት የሚባልም አለ ቃልን ሲበሉ፤ በቃል ውስጥ ሳይገኙ፤ የክህደት ቤተኛ ሲሆኑ ድርብ ገመድ ገዝቶም ቢፈታተሽ መልካም ነው። ገታ የሚያደርግ በራስ ላይ ማዕቀብ ለመጣል። ህወሃት ያን ያህል ስንወቃው የባጀነው እኛን እኛ አልሸት ስላለ ነበር። ኦዴፓም እኛን እኛን አልሸተተም። ስለሆነም ምህረት የለም። ኮቢውም፤ ብራናውም አይምርህ ላልምርህ ማለት የተገባ ነው፤ አዳልጦታልና …  እጅግም ተስገበገበ … ታስሮ የባጀ ምንትሶ ነው የሆነው። በማህል ኩዴታው ካልነጠቀው በስተቀር፤ ያው ወንበሩ ባዶ ሆኖ ስላዬሁት በህልሜ አለመረጋቱን፤ ማረግረጉን አስበዋለሁኝ አዘውትሬ ... 

በመጨረሻ የማነሳው ነጭ ነው። በነጭ ብቻ የተሰራም የሞድ ትርኢት ነበር። ነጭ ዝምተኛ ነው። ግን ጥቁርም፤ ቀይም፤ ዳማም፤ ጠይምም፤ ቢጫም፤ ሰማያዊም፤ እኔን ይርሳኝ ቡኒም አረንጓዴም፤ ብርቱካንማም፤ ወይናማም፤ ጎመኒም ብቻ ተዘርዝረው የማያልቁ ቀለማት በብዛታቸው ልክ ሁሉ እንዳሻቸው ቢዳንሱበት የማይሰለቸው ተቀባዩ ነጭ ሰለዴ … እም! ይማጥለት ይሆን ተፖለቲካ ዕሳቤ አንጣር ... 

ግን ቢስማሙ እንደሚያምርባቸው ሰላም ሁኑ እባካችሁ እያለ የሚመከረው እጬጌው ነጭ ጎላ ብሎ ቀርቧል … ለዚህ የክብርት የሰላም ሚ/ሯ የወ/ሮ ሙፍርያት ካሜል ድርጅት ቱክ፤ ሹክ፤ ተክተክ የማይል ማህል ላይ ያለ አባ ዝምታ ድርጅት ነው። ባኑሩት ጉልት ብሎ የሚገኝ። 

ሁሉንም ነገር በገለልተኝነት ይሁን በባይታወርነት ነው የሚመለከተው። የውጭ አገር ድርጅት ነው የሚመስለው ደህዴን። ሚዲያው እራሱ ግርም ነው የሚለው። በነጩ ላይ ነጭ ቢጻፍ ሰውሰውሰው፤ እንዲህ ንባብ የለሽ ልሙጦሽ ይሆናል።

በቀዩ ላይ ቀይ ቢጻፍም እንዲህ ሰወሰውሰው እንዲህ። በጥቁሩ ላይ ጥቁር ቢጻፍም እንዲህ ሰውሰውስወስ እንዲህ። በድባ፤ በግራጫ ቢቸከቸክበት ጉዳዩ አይደለም ደህዴን

ይህ በፖለቲካ ዕይታ አደገኛም ነው አዘናጊም ነውና ይታሰብበት እንላለን …  ለአላዛሯ ኢትዮጵያ ሲባል … ልሙጥነት በፖለቲካ ዕሳቤ የሚበጅ አይደለም። መጎርበጥ በተወሰነ ደረጃ፤ መለስለስም በተወሰነ ደረጃ ያስፈልጋል። አልጫነት ዘወትር ግን ገዳይ ብቻ ሳይሆን ተደምሳሽነትም ነው ልክ እንደ ብአዴን። ሎሌነትም የአባት አይደለም። ቆፍጠን ያስፈልጋል።

·       ግራሞት።  

ቅኖቹ የጹሑፌ ታዳሚዎች የገረመኝ ሞድ አቅራቢ አሰልጣኝ ያላቸው መሆኑ ደግሞ ገርሞኛል አስደስቶኛልም። ፍንጭ አለ ማለት ነው ለነገ ለዚህ ኢንደስትሪ በባዕት …
ግን አንድ ነገር እረሳሁኝ እኔ አገር በነበርኩበት ጊዜ ልብስ ሰፊዎች በቃላቸው አይገኙም ነበር ዛሬስ ማለት አይቀሬ ነው? ዛሬስ እንዴት ነው ከ ሰ ዓት ጋር ብያለሁኝ?

በጥቅሉ ግን የሰላም ሞድ ትዕይንት ተልዕኮዊ መነሻም ይሁን መድረሻ እኔ ደስ ብሎኛል። አገሬ ብገባ እንደዚህ ባሉ ኢቤኔቶች ነው መሳተፍም መገኘት እምፈልገው፤ ወይ በግጥም ምሽት ወይንም በስዕል ኤግዚብሽን ወይንም ደግሞ በሞድ … ወይ ደግሞ በቲያትር … ፊልምም ከሆነ በኢትዮጵውያን ፊልም … ሌላው ግን ልጆችን ሰብዕና በመቀረጽ ባሉ ጅምሮች በስፋት መሳተፍ … አገር ብገባ ፖለቲካ እና እኔ እንፋታለን ብዬ አስባለሁኝ … በልጆች ጉዳይ ብቻ እምተጋ ይመስለኛል የቤተሰቦቼም ምርጫም ይኼው ስለሆነ …

የሆነ ሆኖ የ41ኛው የካራማራ በዕል ዝግጅት መሰናዶ እና የሰላም የሞድ ትርኢት ቀልቤን የሳቡ፤ ነፍሴን የገዙ ጉዳዮች ነበሩ። ከሰሞኑ ወጀብም አጽናኑኝ።  እዚህ እኔ ብዙ ድርጅቶችን በነፃ አግልግሎት እሰጥ ነበር። እና በምሠራበት ቦታ ሁሉ የየሙያዎች ሥነ - ምግባር ወይንም ዲስፕሊን ቋሚ ት/ቤት ስለመሆኑ አረጋግጫለሁኝ። እራሱ ሰው ሆኖ በመፈጠር ውስጥ ያለውን ነገር ማዬት በጥልቀት ማዬት አስችሎኛል።

እንዲህ መሰል በሆኑ የዕውቀት ቀለማም ገብያዎች ደግሞ መቼም ፖለቲከኞች ርህራሄ የሚባል ነገር አልፈጠረላቸውም እና እንዳሻቸው በማረሻ መንፈሳችን ሲሰቀስቁት ሰቀሰቅ ብለን አልቀስን ይህን መሰል ዝግጅት ስናይ ደግሞ ነፍሳችን ትረጋጋለች። እናም ተመስገን እንላልን። ዶር ለማ መገርሳ በ እጅጉ ጎድተውናል። ለሳቸው ጤና ሊሆን ይችላል ለቅኖች ለልበ ክፍቶ ለየዋሆች፤ ለ እኔ መሰል ጅሎች ግን ሥም የለሽ በሽታ ነው የሸለሙን። 

ስለሆነም በዚህ የሞድ ትርኢት ነፍሳችን መጽናኛ ስለገኘች አዘጋጆችን፤ ተሳታፊዎችን፤ ሃሳብ አፍላቂዎችን እጅግ አድርጌ አመሰግናቸዋለሁኝ። ይበረኩ! ከሰነባበተበኝ የተስፋ መቆራረስ ገጠመኝ ፈወስ አድርገውኛልና። 

ጥበብ ፍ ናት እል ታደርጋለች።
የኔዎቹ ኑሩልኝ።

መሸቢያ ጊዜ። 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።