ግንቦት 20 ለእኔ፤ ያኔም ሆነ ዘንድሮ። ከጸሐፊና ተርጓሚ አቶ መስፍን ማሞ ተሰማ።


እንኳን ወደ ቀንበጥ ብሎግ በሰላም መጡልኝ።

ግንቦት 20 ለእኔ፤
ያኔም ሆነ ዘንድሮ።
“ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን አይጠቅምም።
ሁሉ ተፈቅዶልኛል በእኔ ላይ ግን አንድ
ነገር እንኳን አይሰለጥንብኝም።
ዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት
ወደ ቆሮንቶስ ምዕራፍ ፮ ቁጥር ፲፪”
ከጸሐፊ እና ተርጓሚ ከአቶ መስፍን ማሞ ተሰማ።




ሠላም ለናንተ ይሁን! ይላሉ ጸሐፊ እና ተርጓሚ አቶ መስፍን ተሰማ ከ አውስትራልያ ሲዲኒ … እኔም ሥርጉተ ሥላሴ ከእመ ዝማታ ሲወዘርላንድ ዘንጠፍ ያለ ትሁታዊ ሰላምታዬ ለታዳሚዎቻችን ይድረስ እላለሁኝ።

ውዶቼ ... አሁን ወደ ጸሐፊው አቶ መስፍን ማሞ ጭብጥ አብረን ብያለሁ ጀርገድ ባለ ልስሉስ አክብሮት … እንሆ …

 በድምጽ ...

"ግንቦት 20 ለእኔ፤ ያኔም ሆነ ዘንድሮ።"

 ከጸሐፊና ተርጓሚ አቶ መስፍን ማሞ ተሰማ።


በአምባ ገነኑ የደርግ ዘመነ መንግሥት እስከ ግንቦት 20/1983 / ኢትዮጵያውያን (ከዘር ሐረጋቸው በፊትና በላይ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑና የማይደራደሩ፣ ታሪካቸውን በታሪክነት ተቀበለው የታሪክ ቂም በቀል ያልወረሱና ለዚህም ያልዘመቱ ሁሉሀገር ነበራቸው፤ መቀመጫ።

ሰሜን ብንወጣ ጎጆ ብንቀልስ፤ ደቡብ ብንወርድ ስራ ብንፈልግ፤ ምሥራቅ ብንቀመጥ ሱቅ ብንከፍት፤ ምዕራብ ብንኖር ብንነግድ/ብናስተም ማንም መጤ፥ ማንም ሠፋሪ እያለ አያፈናቅለንም፥ በገጀራና በቀስት አይፈጀንም ነበር።

እንደ መንግሥት ደርግ ሁሉንም ዘር ማንዘር ሳይዘረዝር በሥልጣኑ የመጣበትን ሁሉ ፈጅቷል አስሯል አሳዷል። እኔም በወጣትነት ዘመኔ ይላሉ ጸሐፊ እና ተርጓሚ አቶ መስፍን ማሞ ተሰማ …

ደርግን ለመጣል ከህይወት መትረፍ በመለስ መራር መከራ ተቀብያለሁ፤ ለዓመታት በወህኒመማቅ ወጣትነት ዘመኔን ገብሬያለሁ፤ መስዋዕትነት ከፍያለሁ። ያም ሆነ ይህ ግን በደርግ አገዛዝ ዘመን ሀገርና ታሪክ ነበረኝ/ነበረን። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊነታችንን ደርግ አልገፈፈንም። በዘር ማንዘር ክልል ሸንሽኖ ከሰውነት ተራ አላወረደንም።

ግንቦት 20 ግን በኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ የተለየ ነው፣ የጣልያን ቅኝ ገዢ እንኳን ያላደረገውን የወያኔ ኢህአዴግ ቅኝ ገዢዎች ግፍና ዘመን ወለድ ታሪካቸውን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማርከው ቅኝ ያደረጉበት ወቅት። 

በአጭሩ ወያኔ መራሹ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን የማረከበት ጊዜ ነው፥ ግንቦት 20 ኢትዮጵያ እስከ አንገቷ ለሰጠመችበት የዘርና የመጠፋፋት ቂም በቀል አረንቋ ብቸኛው ተጠያቂ በግንቦት 20/ 1983 / የኢትዮጵያን መንበር የማረከው ኢህአዴግ የተባለ የዘረኞች ስብስብ ነው።

ኢህአዴግ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ሲገባ ኢትዮጵያን ለመማረክ የዘመተበትን የዘር ማንዘር አሸን ክታብ አራግፎ በምትኩ ኢትዮጵያዊነትን ተላበሶና አትዮጵያዊነቱን እንዳለ ተቀብሎ ከዘር ቆጠራ ከአጥንት ለቀማ ተላቆ እና የዘር ችግኝ እየዘራ ከመኮትኮት፤ ጥላቻ ወለድ ታሪክ ከመፈብረክ ይልቅ ብሄራዊ ህብረትንና ኢትዮጵያዊነትን ቢኮተኩትና ቢያሳድግ ኖሮ ዛሬ ይህ ሁሉ ዘረኝነት ዋይታ ግፍ እልቂትና መፈናቀል አይኖርም ነበር!!

አዎ! በግንቦት 20 ኢትዮጵያን የተቆጣጠረው የዘር ድርጅቶች ስብስብ ኢህአዴግ በመላዋ ኢትዮጵያ የዘረጋው ዘረኛ ሥርዓት ባይኖር ኖሮ ዛሬ መጤ፤ ሰፋሪ፤ ወራሪ፤ ክልል፤ ብሄር ብሄረሰብ ህዝብ የሚለው እጅግ ከፋፋይ እና ኋዋላ ቀር መለያ መታወቂያችን አይሆንም ነበር። ይህ ሁሉ ግን ግንቦት 20 ያፈራው አሜኬላ ነው!!

እና ይህንን የግፈኞችና የወራሪ ሥርዐት ነው በበኩሌ ሀገሬን ከለቀቅሁበት የግንቦት 20 ዋዜማ ጀምሮ በስደት ዓለም አቅሜ በፈቀደው ሁሉ ስታገለው የኖርኩት።

 ….የተሰደድኩትም ሆነ የታገልኩት ኢህአዴግ ከነ - ሥርዐተ ማህበሩና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ግሳንግሱ ጋር እንዲቀየር ነው።

እርግጥ ነው ከመጋቢት 2010 ጀምሮ ወያኔ መራሹ ኢህአዴግ በፈላጭ ቆራጭነት አራት ኪሎ ባይኖርም ቅሉ እነሆ ፍፁማዊ ትዕቢትና ይነኬነት የሚያትት መግለጫ የሚያወጣው ወያኔ አሁንም የኢህአዴግ አከርካሪ ነው።

የአራቱ ድርጅቶች አንደኛው አካላቸው ህወሃት ነው። ግንቦት 20 ኢትዮጵያና ዜጎቿ ኢትዮጵያውያን በኢህአዴግ የተማረኩበት እንጂ ነፃ የወጣንበት አይደለም። በግንቦት 20 ላይ አቋሜ 1983 ዓ/ም ላይ ይኸው ነበር ዛሬም 2011 / አቋሜ ይኸው ነው!!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

አሜን ልዕልታችን፤ ንግስታችን፤ ቅድስታችን ኢትዮጵያ ለዘላለም
ትኑርልን እኔም ልበል።
ግንቦት 20/2011 (ሜይ 28/2019)እ.አ.አ
ሲድኒ አውስትራሊያ

ጸሀፊ እና ተርጓሚ አቶ መስፍን ማሞ ተሰማን እኔም የከበረ ምስጋና ላቅርባላቸው ፈቀድሁኝ፤ ይህን ሁለንትና ታሪክ ቀመስ፤ ውስጥን የሚፈትሽ፤ በምልሰት ትናንትን ቃኝቶ የነገን መዳራሻ የተጋድሎ አውራ መንገድ አመላካች ራዕይ ስላኩልን። ዛሬም ያላባራው የትውልዱ ብክነት አሁንም ይዞናል …

የኔወቹ ውዶቼ ኑሩልኝ፤ መሸቢያ ጊዜ 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ዛሬ ያለው ነገር „ፈረቃም፤ ተረኝነትም“ አይደለም።

እህት አጊቱ ጉደታ አገር ነበረች።

አብይ ኬኛ መቅድም።